#የገለበጠም #የተገለበጠም #የለም! #በሞቴ መንግስት መገልበጥ #አይሰልችህና #ሞካክረው። እኛም እንይ ………
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
እንዴት ሰነበታችሁ ማህበረ ቅንነት? እንዴት አላችሁልኝ። ውጭ የምትኖሩ ወገኖቼ ዓውደ- ዓመቱ እንዴት ይዟችኋል? ጥሞና መልካም ነገር ነው። ከቅንነት፤ ለመልካምነት ከታሰበ። መታደልም ነው።
ዛሬ ዕለቱን በአቶ (በሃጂ) ጃዋር መሃመድ ዙሪያ የግል ዕይታዬን ላጋራ ወደድኩኝ። ፁሁፋ ሊረዝም ይችላል። ለብሎጌም ጭምር ስለምሰራም። በተጨማሪም የምዕራፍ ፲፬ መከወኛ ፁሁፌም ስለሆነ።
የአቶ (የሃጂ) ጃዋር ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ማቀዱ ከምን አንፃር ነው?
1) የማህበረ ኦነግ የቤተ - መንግሥት ቆይታ እንዳያጥር ከመስጋት።
2) የማህበረ ኦነግ በትረ ሥልጣን ከተናደ አማራጭ ሆኖ ለመቅረብ።
#ሁለቱ ሃሳቦች መነሻወች መንታ ፍላጎት አላቸው።
1) አገር እናድን ጥሪ። ይህ ለውጥ #ፈላጊነትን ያሳያል። ለውጡ ግን ወደ አመራር ሽግሽግ ዝንባሌ ያለው ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ።
2) ምንም ቢሆን በኦሮሞ ሊቃናት የበላይነት የምትመራ ኢትዮጵያ ለመሪው አካል #ጥገናዊ አጥሚት አዘጋጅተን እናድነውም ዓይነት ነው።
…… ለዛውም ፕሮፌሽናል ፖለቲከኛ የፍላጎቱን አቅጣጫ መንታ መንገድ ላይ ሊገትር አይገባም ባይ ነኝ። A. B. C. D ፈተና ላይ እራስን አስቀምጦ የፍላጎት አቅጣጫን ጥርት ባለ አቋም፤ ጥርት ባለ ውሳኔ ላይ መነሳት ያስፈልጋል። አገር እንደ ጥንቸል የመሞከሪያ ጣብያ አይደለችም እና። ኤንም፦ ቢንም፥ ሲንም፥ ዲንም፥ ልሁን በትውልድ ላይ መፍረድ ይሆናል።
#አቶ (ሃጂ) ጃዋር መሐመድ።
በቅጽበት ከተከሰቱ ጥቂት ፖለቲከኞች አንዱ አቶ (ሃጂ) ጃዋር መሃመድ ነው። አነሳሱ፤ የዕውቅናው እምርታ ፍጥነት፤ የእሱ የወጣትነት ተፈጥሯዊ ባህሪ ገርሞኝ ኢሳት በይፋ ሰብዕናውን አጉልቶ ካወጣበት ዕለት ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ አመታት አጠናሁት። በዛን ጊዜ ግብረ መልሱ ግራጫማ ሲቃ ሆኖ ነበር ያገኜሁት። ይህንኑ ምልከታዬንም በ2010 እኢአ በፁሁፍ አቅርቤያለሁ። እዬተከታተልኩም አልሞገትኩትም። ይህም ምክንያታዊ ነበር። እርግጥ ጥቂት መጣጥፎችን መፃፌን አስታውሳለሁኝ።
ግራጫማ ሲቃ ያልኩት ሳቅን ለቅጽበት መግቦ ዶፋን በገፍ ስለሚለቀው፥ የሃሳብ መረጋጋት ማቃት፤ የፍላጎት ስክነት ዕድል መኮስመን፤ የጥላቻውም፤ የፍቅሩም ካታጎሬ ዝንቅንቅነት በብሄራዊ አገራዊ ቀጣይ ተስፋወች ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽዕኖ እጅግ ያሳስበኝ ስለነበር። የእሱን ፐርሰናል ሆነ ሙያዊ አቅም በቅጡ ሊመራ የሚችል ጭምት የፖለቲካ አማካሪ ሊኖረው እንደሚገባ አምንም ነበር።
የአቶ (የሃጂ) ጃዋር መሃመድ የፖለቲካ አቅም፤ የተናጋሪነት ፀጋው፤ ወጣትነቱ፤ የፍላጎቱ ዓይነት ይዘት እና ፎርማት በቅጡ ሊጠና እንጂ ሊጣጣል ወይንም ሊቃለል፤ ወይንም ሊገፋ የሚገባው አለመሆኑን አምናለሁኝ። የአቶ (የሃጂ) ጃዋር መሃመድ የመታመን አቅም ግን ይሄ ነው ብዬ በፐርሰንት ማውጣት ባልችልም፤ የፍላጎቱ፤ የንግግሩ ተለዋዋጭነት ግን አብዝቶ የሚያሳስበኝ ጉዳይ ነው።
ውህድ ማንነቱን በሚመለከት ከሚያሳስበኝ ጉዳይ አንዱ ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ችግር ሆኖ ግን ትኩረት ያላገኘው ጉዳይ የማንነት ቀውሶች እና ተከታይ ጉዳቶች ያሳስበኛል። በቁጥር አናሳ ከሆነ ማህበረሰብ መገኘት፤ ወይንም በውህድ ማንነት መፈጠር፤ የልምድ እና የተመክሮ መስኮች በደርበቡ መሆን፤ የቀለም ትምህርት ደረጃ ሁሉም በማንነት አይነት ውስጥ የራሳቸው ተጽዕኖ ስላላቸው ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ስኬት እንቅፋት እንደሆኑ ይሰማኛል። አቶ (ሃጂ ) ጃዋር መሃመድም በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ስላለ ይህም በራሱ በቅጡ ካልተያዘ አደጋው ሰፊ ነው። የቀድሞው ጠሚር አቶ (ፓስተር ) ታምራት ላይኔም ችግር ይህ እንደ ነበር ይሰማኛል።
#ሴራ።
የኢትዮጵያ ወጣት ፖለቲከኞች ከኢትዮጵያ የቆዬ የሴራ ፖለቲካ ጥምጥም እራሳቸውን ሊያቅቡ ይገባል ብዬ አስባለሁኝ። በውነቱ በዚህን ያህል ደረጃ የመንበረ ሥልጣኑን ቁልፍ ቦታ ሳይዝ "የማሜ ጩሉሌ ፓርቲ" ፍጥረተ ነገር ባለቤት አቶ (ሃጂ) ጃዋር መሃመድ መሆኑን በሉዓላዊ ሚዲያ በቤቲ ሸው ዋና አዘጋጅ ሳዳምጥ እጅግ ደነገጥኩኝ። የልጆች ጨዋታ ዓይነትም ነው ሴራው። አቶ ጃዋር መሃመድ ከዚህ መጠራቅቅ እና ተጫኝነት ጉዳይ ካልነበረበት ይህንን ግልጽ ማድረግ ሊኖርበት ይገባል።
ሴራ እና ሴረኞች ብዙ ጎድተዋል እና። በፍጥነት ወጥቶ ማብራሪያ ሊሰጥበት ይገባል ባይም ነኝ። ዕውነት ከሆነ ግን ለእሱም ተስፋ ለሚያደርጉትም ገደል አፋፍ ላይ እንደ ቆመ አንድ ክስተት ይታዬኛል። ጠባሳም ነው።
በዚህ አጋጣሚ በወጣትነታችሁ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የምትሳተፋ ሁሉ ሴረኝነትን ልትፀዬፋት ይገባል። ወንጀልም ነውና። እንደ እዬምነታችሁም ሃጢያት መሆኑን ልታምኑበት ይገባል። ማንኛውም ወጣት ፖለቲከኛ የሴራን ፖለቲካ #ሃራም ሊለው ይገባል። ለግል ህይወት፤ ለማህበራዊ ህይወትም ነቀርሳ ስለሆነ።
ወጣትነት በራሱ በተፈጥሮው ወደ ቅጽበታዊነት፤ ስሜታዊነት፤ ግንፍልተኝነት፤ ችኩልነት፤ ግብታዊነት፤ አፍለኝነት፤ ስልቹነት፦ መጠኑን ያለፈ በራስ መተማመን፤ እራስን አልቆ የማዬት ወዘት ያመራል። ሁላችንም ወጣት ሆነን አልፈናል። እናውቀዋለንም። በተጨማሪም እኔ የወጣቶች አደራጅ ስለነበርኩ በጥልቀት ስለማውቃቸው እነኝህ ባህሪያትን በዕድሜ አስገዳጅነት ስለመሆኑ ይገባኛል። ለዚህም ነበር እዬተከታተልኩ እማልሞግተው።
የሆነ ሆኖ በዚህ የአብይዝም ዘመን ቅጽበታዊነት በሙሉ ዕድሜ ላይ ባሉ የፖለቲካ ሰብዕናወችም በጉልህ ተመልክቻለሁ። የቁስ ሳይሆን ከፍ ያለ ግምት ሊወጣለት የማይችል መስዋዕትነት ህዝብ ከፍሏል - በእነሱ ያልሰከነ ርግብግብ ፍላጎት ምክንያት። በማይበረክት የሳሙና አረፋ የድርጅት ምሥረታ እና ፍርሰትም ብዙ መንፈስ ተጎሳቁሏል። ስለመሆኑም ቅጽበታዊነት የአቶ (የሃጂ) ጃዋር መሃመድ ብቻ አለመሆኑን አበክሬ ልገልጽ እወዳለሁኝ። የኢትዮጵያን ፖለቲካ እየተጠናወተው የሚገኝ ወረርሽኝ ነውና።
በውነቱ ከውጣት ፖለቲከኛ ደንጋጣነት የማይጠበቅ ሰብዕና ነው። ቤቲ ሸው ዋና አዘጋጅ እንደ ገለፀችው የቡና ደጋፊወች ሞቅታ አንድ ወጣት ፖለቲከኛ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ካራደ፦ በጦር ግንባር ቢገኝ ምን ሊሆን ይሆን ብያለሁኝ። ፖለቲካ የአቋም፤ የውሳኔ ጉዳይ ነውና መጠኑን ያላለፈ ድፍረት እና ወኔን ይጠይቃል። በዚህ ዘርፍ ያዳመጥኩትን ማመን ተስኖኝ ደግሜ አዳምጫዋለሁኝ። ድፍረቱ ከሌለ የአደባባይ ሰውነቱ በተለይ በመራራው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሳትፎ እና ተስፋው የሚታመም ይመስለኛል።
የታዘብኩት የበዛ በራስ መተማመን ከድንጉጥነት ቃር ሲቀላቀል ቀለሙን መገመት ይቻላል። ይዥጎረጎራል። በጣም ወሳኝ ቁመና እና አቋም ለሚጠይቁ የፖለቲካ ውሳኔወች ደንጋጣነት ያለልኩ የተሰፋ ሽብሽቦ ይሆንብኛል - ለእኔ። ለዛውም ኢትዮጵያን ለመምራት የፊት ረድፈኛ ከሆነ ወጣት ፖለቲከኛ።
እሷ እራሷ ቤቲ ሸው እሱን ቃለ ምልልስ ለማድረግ ፍርሃት ቢጤ እንደ ነበረባት መፀሐፏ መነባነብ ላይ ስሰማ ውሽክ ብያለሁኝ። ምኑ ይሆን አቶ (ሃጂ ) ጃዋር መሃመድ የሚያስፈራው። ዓለምን በተለያዩ ሙያወች የሚመሩ ፋናወች ዛሬም ያሏት አገር እኮ ናት ኢትዮጵያ። ዩንቨር ያከበራት ሥም የሰዬመላት። በሃይማኖት ዘርፍም እንዲሁ በደግነታቸው እና በልቅናቸው ምክንያት የአክብሮት ፍርሃት የሚያሳድሩ የእነ ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ አገር እኮ እናት ኢትዮጵዪ፤ የቅዱሱ ንጉስ ላሊበላ አገር እና እናታችን። ንግሥናውን ትቶ ምናኔን የወሰነ፦ በሌላ በኩል የንግሥት ማክዳ የቅድስት እሌኒ አገር እኮ ናት ኢትዮጵያ። የእቴጌ ጣይቱም ህይወት ናት ኢትዮጵያ።
#ጃዋሪዝምን መናፈቅ።
ከአቶ (ሃጂ) ጃዋር መሃመድ ጋር ለመለካካት የሚመኙ፤ እሱን የመሆን መሻት በብዙ ሰወች አስተውያለሁኝ። በተለይ አገር እንደገባ እና ታስሮ ሳለም። የተሳካላቸውን ግን አላዬሁም። እራሱ አቶ (ሃጂ) ጃዋር መሃመድ የትኛውን ጃዋሪዝም እንደሚያስቀጥል ባላውቅም፤ አሁን ላይ ለራሱም ጃዋሪዝምን ማስቀጠል ከቻለ ዕድለኛ ነው።
ፈንታሌ ሚዲያ ሹክ እንዳለን፦ ለኢትዮጵያ ጠሚርነት ከታጩ ሰለስቱ መካከል፦ በአንደኛ ደረጃ ለቀጣይ ጠሚር እንደታጨ መረጃ አድርሶን ነበር። የመጸሐፋ የህትምት ፍፃሜም ከዚህ ፍላጎት ወይንም ምኞት የተጸነሰ ይመስለኛል። እርግጥ ነው መረጃው እንደ ተሰራጨ በወቅቱ ምንም ዓይነት ንቅናቄ ባናይም፦ ግብረ መልስ ጠብቄ ነበረ። የሆነ ሆኖ አሁን በዓለም ዓቀፍ ሚዲያወች ሆነ በራሱ ፔጅ ላይ በአዲስ አቅም መምጣቱ ለዚህም ይመስለኛል።
አቶ (ሃጂ) ጃዋር መሐመድ እሱም እራሱ ሌላውን ፖለቲከኛ ከግምት በታች እንደሚይ አስተውላለሁኝ። እሱንም ማህበራዊ መሰረቱን እንዳጣ እና አቅም እንዳነሰውም የሚሞግቱን እያዳመጥኩ ነው። ሁለቱም ተፃራሪ ዕሳቤወች ትክክል አይመስሉኝም።
እሱን አቅሎ ማዬት የሚገባ አይመስለኝም። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ፤ በዚህ የዲጅታል ዘመን 3000000 ሦስት ሚሊዮን ህዝብ ቁጭ ብሎ ያዳመጠው ፖለቲከኛ ነው። እንዲህ አይቼ አላውቅም። ፈንታሌ እጩነቱን ሲያበስርም የሪኮመንዴሽኑ መነሻው ይህ ሊሆን እንደሚችል አስባለሁኝ።
ተደማጭነቱ ከአርተስ ሚዲያ ጋር በነበረው ቆይታ ተረጋግጧል። መልሶቹ አጫጭር ነበሩ። ርግታም ነበረው። የቢቢሲ እና የዶቼቬሌው ግን ወደ ቀደመው ሰብዕና የመለሰው ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
በራስ የመተማመን አቅሙም ገርበብ ብሎብኛል። የንግግር ጥበብ አቅሙም ሳስቶብኛል። የአርተሱ ግን ደርባባነት እና እርጋታ ነበረው። ጥሞና ጊዜው በእጅጉ ስለረዳው ብልህ ቢሆን እሱን ለማስቀጠል ቢጥር መልካም ይመስለኛል። በሌላ በኩል ሸበቱ አስደንግጦኛል። የሆነ ሆኖ በግራ ቀኙ በአጠያየቁ ላይ የቀሩ አመክንዮዊ ጉዳዮች እንደ አሉ ይሰማኛል። ሊሞገት ስለሚገባ።
#ጥሞና።
የአቶ (ሃጂ) ጃዋር መሐመድን የጥሞና ጊዜ አቅዶት ይሁን በሌላ ገፊ ምክንያት ክንውኑን ማጣጣል የተገባ አይደለም። ጽፈንላቸው እንኳን ያልፈጸሙ ፖለቲከኞች አሉን። መጠሞንን አግልሎ ስኬቱንም መመተር ይቻላል። እራስን፤ አካባቢን፤ ሁኔታን፤ ብሄራዊ፤ አህጉራዊ፤ ሉላዊ ጉዳዮችን ጊዜ ሰጥቶ ማዳመጥ ሊለመድ የሚገባው የግዴት ውል ሊሆን ይገባል - በተለይ የፊት ረድፈኛ ለሆኑ ፖለቲከኞች።
በዚህ ዘርፍ አቶ ( ሃጂ ) ጃዋር መሃመድ የወሰደው እርምጃ ቢያስመሰግነው እንጂ የሚጣጣል፤ የሚቃለል፤ አልፎ ተርፎ የሚወቀስበት አንዳችም ነገር የለም። የሃሳብ ደሃም አይደለም። ብቁ ተናጋሪም ነው። አመክንዮም ሆነ ጭብጦችን የማቅረብ አቅም አለው። ስለሆነም ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ የጥሞና ምዕራፍ እንደ ከፈተ ይሰማኛል። ጥሩ ልምድም ነው። በወቅቱም ጽፌበታለሁኝ።
መሪ የመሆን ህልመኝነት አወንታዊ ነው። በተለይ ጠሚር አብይ አህመድ መሪ ከሆኑበት ዕለት ጀምሮ እንዲህም አለ ለካ? በማለት ለኢትዮጵያ መሪነት እራሱን ያጬ፤ ለቀዳማዊ እመቤትነት ሳይቀር የታጨ መንፈስ ተከታትያለሁኝ። ይህ በጎ ነገር ነው። ነገር ግን አቅም አለኝ ወይ? ዲስፕሊኑን መወጣት እችላለሁ ወይ? ቲም ሊደርነቱን እችላለሁ ወይ?
ተመክሮወስ አለኝ ወይ? ኢትዮጵያን ያክል የመንፈስ ዲታ አገርን ለመምራት አውቃታለሁ ወይ? መሬት ላይ ህዝብን በመምራት፤ በማደራጀት አገልግሎት ላይ ተሰማርቼ አውቃለሁ ወይ? የጀመርኩትን በማሳካት፤ በማስቀጠል የታማኝነት ደረጃዬ ምን ያህል ነው ብሎ እራስን መመዘን ይገባ ይመስለኛል።
ፕሮቶኮላዊ ሥርዓትንም ከንግግር እስከ ንቅናቄ እራስን አቅምን መለካት ይገባል። ኢትዮጵያ ለእኔ አህጉርም፦ አገርም፤ ፍልስፍና፦ ሳይንስም፤ ህግም ዩንቨርስም፤ አናባቢም ተነባቢም አገር ናት። የነፃ አውጪ ድርጅት ማህበርተኞች ይህን ፋክት የመቀበል ልኬታቸው ምን ያህል ይሆን? ከባዱ እራስን መመዘን ነው።
#ተጽዕኖ ፈጣሪነት ማለት መሪነት ማለት ነውን?
ይህን በስፋት በአውድዮ Sergute Selassie ሥርጉተ©ሥላሴ ዩቱብ ቻናሌ ላይ ሠርቸዋለሁኝ። በዚህ በማህበራዊ ሚዲያ ዲጅታል ዘመን ወዘተረፈ ተጽዕኖ ፈጣሪ ይኖራል። በሞድ፤ በኮሞዲ፤ በተውኔት፤ በገጣሚነት ሊሆን ይችላል። ይህ ማለት ግን ለአገር መሪነት ብቁ ያደርጋል ማለት አይደለም። ለዚህ ዘመን የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ጥሩ ግሎባል ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ። ኔቶን እንዲመሩ እኮ ነው የታጩት።
ኢትዮጵያን መምራትም፤ አፍሪካ ቀንድን፤ አፍሪካን አህጉሩን፤ የግሎባሉን የቡኒ መንፈስን መምራት ማለት ነው። እርግጥ ነው የአገር መሪ ተጽዕኖ ፈጣሪ ይሆናል። ነገር ግን በተለያዬ መስክ ተሳትፈው ሚሊዮን ተከታይ ያላቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰብዕናወች መሪ የመሆን አቅም ይኖራቸዋል ብዬ አላምንም። መሪነት ቅብዓም ነው። ብዙ ረቂቅ የሆኑ የአቅም ክምችቶችን ስለሚጠይቅ። ፍፁም የሆነ አድማጭነትን እና ቅንነትን ስለሚጠይቅ። አይዟችሁ ባይነትን እና አጽናኝነትን በአርምሞ ስለሚጠይቅ።
#ኦፌኮ እና አቶ ሃጂ ጃዋር መሃመድ።
የኦፌኮ መሥራች እና የመዋዕለ ዕድሜ መሪ ፕ/ ዶር መራራ ጉዲና እና በአካልም አውቃቸዋለሁኝ። ሳውቃቸው የነበረው ድርጅታቸው ከማስፈራሪያ አልፎ አገር ጠቀም፦ ህግ አክባሪ፦ ዘመናዊ የዞግ የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ ግን አይቼው አላውቅም። ከታቱ ዥግራ ተሸጋግሮም አይቼው አላውቅም። በኦፌኮ ህብረት፤ መድረክ እያለም ከሌሎች ጋር ተቀናጅቶ ያሳካው፤ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ እፎይታ የሰጠ የልምድ አብነትነትንም አይቼ አላውቅም። ስታግናንት ነውና።
አሁን ደግሞ ከኢህአፓ፤ ከመድረክ፤ ከህብር ወዘተ ጋር አብረው ለመስራት አህዱ እንዳለ አዳምጫለሁኝ። በምን የስኬት ተመክሮ ለድል እንደሚበቃ አላውቅም። አሁን ከሆነ አግላይነት እና ጭካኔን ሲያበረታታ ነው እምመለከተው። ህግ ጣሽነቱ እንደ ተጠበቀ ሆኖ።
ሁለት ጊዜም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በዘመነ ህውሃት የጣሰ ነው። ማንም ሰው ከአገር ብሄራዊ ህግ በታች እንጂ በላይ ሊሆን አይገባም። ህግ መተላለፍ የአገር ንቀት ነው - ለእኔ። ህግ ጣሽ የዞግ የፖለቲካ ድርጅትን ማህበርተኛ አድርጎ የሚጓዝ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት ዕጣ ፈንታውን አጤ ሂደት ያሳዬናል። ጠብቁት። "ህግ ተላላፊወችን ጠላሁ" ይላል ልብ አምላክ ዳዊት።
በስብስቡ ውስጥ ህብር አለ። ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት የህብር ምክትል ሊቀመንበር ናቸው። ህብርን ወክለውም ለምርጫ ተወዳድረው በብልጽግና ተሸንፈዋል። ብልጽግና በአቅሙ አይደለም ያሸነፈው። በቀውስ ዶሴው እንጅ። በሌላ በኩል የሃሳብ ደሃ ያልሆኑት ፖለቲከኛ ምንም እንኳን "ልሸነፍ ነው" የተወዳደርኩት ቢሉም። ይህንን በወቅቱ ሞግቻቸዋለሁኝ። በሳል ወጣት ፖለቲከኛ ከመሆናቸው አንፃር ነው የተሞገቱት። ኢንጂነር በማናቸውም አጀንዳ ብቁ ተናጋሪም ናቸው። ቀድሞ የመተንበይ አቅምም አላቸው።
አሁን ኢንጂነር ይልቃል በፋኖ ንቅናቄ በኩል ወሳኝ አካል ናቸው። ህብርነታቸውስ??? በዚህ ስሌት ስንሄድ አቶ ጃዋር መሐመድም የኦፌኮ ም/ ሊቀመንበር ነው። በፋኖ አቅም አቶ ጃውር ትውር እንዲል ለማይፈልጉ የፋኖ ንቅናቄ ትጉህ ሊሂቃን ይህን አመክንዮ እንዴት ሊይዙት ተሰናድተዋል?
የገረመኝ የኢንጂነር ይልቃል ጌትነት እና የፕ/ ዶ መራራ ግንኙነት በአንድ መስመር ደግመው መገናኘት ነው። በአብይዝም ዘመን ያለው የፖለቲካ ሁነት በምን እርቀ ሰላም በአንድ ጎዳና ላይ ሊገናኙ ይችላሉ? አብሮነት ከውስጥ ከሆነ፦ ጠርቶ ከተጀመረ ቢጠቅም እንጂ ጎጂ ባይሆንም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ግልጽነት፤ ይቅርባይነት፤ የቂም እና የበቀል መንፈስ እራስን ማረም፤ ማረቅ ከተቻለ ትግልን በአብሮነት ለወረት ሳይሆን ለዘለቄታ ቢታጭ ጥሩ ነው።
በዚህ ውስጥ የአቶ ጃዋር (ሃጂ) የኦፌኮ ም/ ሊቀመንበርነት ጉዳይ ፋይዳ ያለው ዕሴታዊ እምርታ በኦፌኮ ተጠብቆ ባክኖ የቀረ ወና ተስፋ ነው ባይ ነኝ። የዞግም ቢሆን ዘመን ያለ አሰራር፤ አደረጃጀት ጠብቄ ነበር። ግን {}።
አቶ( ሃጂ) ጃዋር መሃመድ ኦፌኮን ስለተቀላቀለ ድርጅቱ በረከት አልረበበለትም። ምን አልባት የእስር ጊዜው አጨናግፎት ሊሆን ይችላል ብዬ ባስብም ከእስር ከተፈታ፤ ከጥሞና ጊዜ በኋላ አክቲብ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባ ነበር።
በዚህ ስሌት ስንጓጓዝ አቶ (ሃጂ) ጃዋር መሃመድ ምን ዓይነት ተመክሮ አገኘ የዞግ ድርጅ ከፍተኛ መሪ አካል ሲሆን? ምን ተማረ? ምን አስተማረ???? ያ ተመክሮስ በምርጫ ተወዳድረው ቢያሸንፋ ለምን ትርፍ ሊውል ይችላል ብዬ ሳስበው እሱ እንዳለው ጭንቅላት ሳይኖር ጥምጣም እንደመጠምጠም ዓይነት ነው።
ከአቶ( ሃጂ) ጃዋር መሐመድ ጋር ኦፌኮ በመቀናጀቱ ትርፍ አልባ እንደሆነ ነው እማስበው? ለመሆኑ ስንት ጊዜ ቢሮ ተገኜ? ስንት ቀን በቢሮ በመደበኛ ሰራ አቴንዳስ ፈረመ? ምን ዓይነት ስትራቴጂ ነድፎ ድርጅቱን ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋገረ? ምን ያህል ሰሚናር፤ ወርክሾፕ፦ ፓናል ዲስከሽን አዘጋጄ፦ መራ?
የትኞችን መመሪያወች አሻሻለ? ወይንስ አዲስ ፈጠረ? ለምን ያህል ጊዜ ሪፖርት አቀረበ? በአመራር አካሉ ስብሰባ ምን ያህል ጊዜ ተገኜ? ከተገኜ ያሳያዘው አጀንዳ ምን ነበር??? የኦፌኮ መሪ ፕ/ ዶር መራራ ጉዲና ለረጅም ጊዜ ከአገር ሲወጡ እሱ እሳቸውን ተክቶ ምን ሠራ? የፖለቲካ ሙሁሩ አቶ (ሃጂ ) ጃዋር መሃመድ ከሊቀመንበሩ በተሻለ በትኩስ አቅም እና ጉልበት ድርጅቱን በፈጣን አመክንዮ ባቡር ምን አሳካ?
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች ይህን የማነሳው "ኢትዮጵያን እናድን" ጥሪውን ለመቀበል ፈተናውን ያለፈበት፤ መስፈርቱን ያሟላበት ጉዳዮችን ሊያቀርብ፤ ሊያስረዳን ይገባል። አገር በአመክንዮ፤ በፋክት፤ በመሆን መመራት ስላለባት። አገር መምራት ብልጠት ሳይሆን ብልህነት፦ በግብታዊነት ሳይሆን በጨመተ፤ በሰከነ፤ የሰው ልጅን እኩል በሚያይ ቅን እና ቀና የሃሳብ ብቃት እና ልቅና ልትመራ ስለሚገባ - ድንቂት ኢትዮጵያ።
#ዝምተኛው ማህበረሰብን መዘንጋት።
በሁሉም የፖለቲካ ሊቃናት፤ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚረሳው፤ እንዳለ የማይቆጠረው ዝምተኛው ማህበረሰብ ነው (ሳይለንት ማጆሪቲው)። የጎደለውን ቀዳዳ ሁሉ ከውዳሴ ከንቱ እራሱን አርቆ የተግባር ልዑል እና ልዕልት ሳይለንት ማጆሪቲው ነው። ትናንትም በሆነው፤ ዛሬም በሚሆነው፤ ነገም በሚሆነው ቸር እና መልካም ተግባር ሁሉ ይህ ቅን ኃይል አለ። ኢትዮጵያም የፀናቸው በዚህ የጨመተ ተሳትፎ ነው። ከእነሱ ውስጥም ለአገር መሪነት ብቁ የሆኑ ተፈጥሮኛ እና ሰውኛ አጽናኝ የኛወች፦ ለኢትዮጵያ እናቶች እንባ ቅርብ የሆኑ የጨመቱ እንዳሉ ሊታሰብበት ይገባል።
#ሁለቱ ቃለ ምልልሶች እና የአልፀፀትም ትዕይንት።
የቢቢሲን እና የዶችቬሌ ቃለ ምልልሶ እና የአልፀፀትም መግለጫወችን በጀርመን አዳመጥኩኝ። ትዝብቴን ከመግለፄ በፊት አቶ (ሃጂ) ጃዋር መሃመድ በህይወት ኑረህ፤ ፀሐይንም አይተህ መፀሐፍ ለማሳተም በመብቃትህ እንኳን ደስ አለህ ልልህ እወዳለሁኝ። ለይቅርታ፤ ለመፀፀት፥ እና ለአጽናኝነት ፈጣሪ ያብቃህ። አሜን። ኢትዮጵያን ለመካስም።
#ገልባጭ እና ተገልባጭ።
"መንግሥት መገልበጥ ሰልችቶናል አቶ ጃዋር መሃመድ" መቼ ነው የገለበጣችሁት? ማንን ይሆን የገለበጣችሁት? በሞቴ ብዬ እምለምንህ አይሰለችህ እና እስኪ ገልብጠህ አሳዬን???? ሞክረው? እንደ ድሮው በበዛ ድካም ያሰበለ ድካም ለሌላው እሸት መዛቂያ የሚሆን አቅም ይኖራል ብዬ አላስብም። ጊዜ ራዲዮሎጂ ነውና።
ህወሃት መራሹ ኢህዴግ የገለበጠው አንዳችም አገራዊ ተቋም፤ ወይንም የአክቲቢዝም ማህበር፦ ወይንም ዱር ቤቴ ያለ ታጋዬ አልነበረም። ቁጭ ብለን እያዬን በኢህአዴግ ደንብ እና ህግ ስብሰባ ተቀምጠው፦ እጩወች ቀርበው ግርባው ብአዴን ሙሉ ድምፁን ለኦህዴድ (ለማህበረ ኦነግ) ሸልሞ በድምጽ ብልጫ ነው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡት። ዕውነቱም ፋክቱም ይህ ነው። ምርጫው የተጠናቀቀው በእኩለ ሌሊት ነበር። ህወሃት አልተገለበጠም። ገልባጭም አልነበረውም። በአዋሳም ጉባኤ የመጋቢቱ ውሳኔ በሙሉ ድምጽ ነበር የፀደቀው።
ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ የአገረ መንግሥትን ሥልጣን ወዶ እና ፈቅዶ ከመልቀቅ በላይ ወሳኝ የፖለቲካ ጉዳይ ስላልነበር ከመጋቢት 18/2010 ዓም ጀምሮ እኔ ህወሃትን ሞግቼው እማላውቅም ለዚህው ነው።
እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ከጃዋርዚም ከእሱ በፊት ነው ከጋሜዬ ጀምሮ ህወሃትን በሃሳብ የሞገትኩት። በዚህ ውስጥ "የፈራ ይመለስ" የጎንደሩ የቀደመው የ500 ወጣቶች ልዩ ንቅናቄ፤ የግንጫው የኦሮሞ ንቅናቄ፤ የአማራ የማንነት እና የህልውና የሃምሌ ፭ቱ የኦሮሞ ደም ደሜ ነው ተጋድሎ፦ የሬቻው ጭፍጨፋ ዕሴታቸውም፦ ተጽዕኗቸውም የላቀ ነበረ። ብርታትም ጥንካሬም ነበሩ።
በሌላ በኩል ግን የህወሃት በትረ ስልጣኑን መልቀቅ ዱር ቤቴ ላሉትም፤ በሰላማዊ ለሚታገሉት የኢትዮጵያ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም፦ ለዲያስፖራው የነፃነት ታጋዮችም ደራሽ ክስተት ነው የነበረው። በዚህ መልክ ህወሃት ይለቃል ተብሎ ያሰበውም፦፦ ያለመውም አልነበረም።
እንኳንስ ሃሳባቸውን ሼር ለሚያደርጉ ግለሰባዊ ጥረቶች ቀርቶ። አቅደን፦ ስትራቴጂ ነድፈን የተባለው ኩሸት ነው። ቋሚ የሎቢ ሰራተኛም አልነበረም። ኦነግ በሎቢ ተግባር ምን አሳክቶ???፡ የተነጣጠለ ጥረት እና ተሳትፎ ነው የነበረው። ስለዚህም ለውጡ የተፅዕኖ ፈጣሪወች ስኬት አልነበረም።
ብዙ ጊዜ ጠ/ሚር አብይም ሲያነሱት እሰማለሁ። ሞተሩ እነሱ እንደሆኑ። ማን ይተካ ለሚለው ኦሮማራ ከመገኜቱ በስተቀር ሁሉም ያልነበሩበት፦ የፈጣሪ አምላክ ፈቃድ ትንግርታዊ ውጤት ነው። በጥንቃቄ፦ በዊዝደም የተከወነ ደግሞም የማይገኝ ዕድል ነበር። ቲም ገዱ በአፍ ጢሙ ደፋው እንጂ። ወርቅ ከቀለጠ ይፈሳል እና። የሚገርመው ያን የመሰለ ዕንቁ ዕድል ግርባው ብአዴን ቀብሮ አሁንም የነፃነት ትግሎችን ልምራ ብሎ ተሰልፎ ሲንደፋደፍ አያለሁኝ። ይገርመኛል። የግርባው ብአዴን ይሉኝታ ቢስነቱ። ሊያፍር፤ ሊሸሸግ እና ሊሸማቀቅ ነው የሚገባው።
#ዕቅድ።
በሚገባ የተደራጄ፤ የታቀደ፤ ስትራቴጂ የተነደፈለት እንደ ነበር አቶ (ሃጂ) ጃዋር መሃመድ ገልፆዋል። አይደለም የተቋም ይዘት ያለው ስኩን ተግባር፤ ወጥ የሃሳብ ስምምነት አልነበረም። ንገረና ለሬቻ ጭፍጨፋ የተመድ የቀድሞው በ100 ዓመት የማይገኙት ሩህሩህ ዋና ፀሐፊ ለሬቻ ጭፍጨፋ ወጥተው ሶልዳሪቲ ያሳዩት በአንተ ጥረት ነበርን? በሌላ በኩል የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ትልቅ አጋዢ ከጎኑ የቆሞ ክስተት ነበሩ።
የተመሰጠሩ ትንግርትም። እሳቸውንስ አቅዳችሁበት ይሆን???? በድፍኑ እና በድርበቡ ነው እምገልፀው። ታሪክም፤ ስኬትም ቢሆን ማጨመቱ ትርፋማ ስለሆነ። ሚስጢር የገብያ ቀጤማ አይደለም። ዊዝደም የአጥር ላይ ወይን አይደለም። ያን የመሰለ ስኬት ጉዝጓዙ ፈቃደ እግዚአብሄር ብቻ ነበር!
#የመሪ መረጣ።
የመሪ መረጣ ልትሰሩ ትችላላችሁ ማህበረ ኦነጎች። ግን ህወሃት መሰናበቱን እርግጠኛ የሚያደርግ ነገር ሲኖር። አቶ "ሃጂ" ጃዋር መሃመድ ይህ በእጅህ ያልነበረ ሃቅ ነው። ፋክቱ ይሄ ነው። አውራ የፖለቲካ ድርጅቶችም አንድ ዓመት ኢህአዴግ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ይበተኑ ነበር። ጥረቱ እና ስኬቱ ስለተራራቁ ተስፋ ቆራጭነት ቤት ለእንግዳ ማለቱ አይቀሬ ነበር። ለዚህም ነው ዕድሉን ተጠንቅቀው የያዙ ሊሂቃን በኢትዮጵያኒዝም ጎራ ሆነ በማህበረ ሌንጮ በኩል የምናዬው። አቶ "ሃጂ" ጃዋር መሃመድም ደንግጠህ እኮ ከወዳጅህ ጋር ጄኔባ አንድ ኢቬንት ነበራችሁ።
የምስማማው ጠሚር አብይ አህመድን መቃወመህን ነው። በአቶ ሳዲቅ ሚዲያ ቀርበህ የሰጠህው ቃለ ምልልስ ነበር። በወቅቱም ሞግቸኃለሁኝ። አቶ ለማ መገርሳ (ዶር) እንዲሆኑ ፍላጎት ነበረህ። እሱም ለሽግግር ወቅት ብቻ ነው። ከዚያ እራስህን እንደምታቀርብ የታወቀ ነው። በዛን ጊዜ ዝናህ እኮ ከእውቀትህ በላይ የተናኜ ነበር። በጣም የተንጠራራ ግምት ተሰጥቶህም ነበር። የአክቲቢዝም ተሳትፎ ለመሬቱ ትግል ቢያግዝም ስኬቱ ግን ከአንተ አቅም እና ቁጥጥር ውጪ ነበር።
ዕድሜያቸውን ሙሉ በነፃ አገራቸውን ያገለግሉ፤ በዝምታ ውስጥ ለስኬት የበቁ ኢትዮጵያውያን እግዚአብሄር ይስጥልኝ እንኳን ተብለው አያውቁም። ለአንተ የተደረገው፤ ለማህበረ ኦነግ የተደረገው ልኩን ያለፈ የተቀናጣ እና ፍፁም ቀለጤ እንክብካቤ ነበር። በአደባባይ ፭ አዲስ አበባ ነዋሪወች ተረሽነዋል። 1300 ታስረው በጦላይ ተሰቃይተዋል፤ እስከ ዛሬም ካቴና ላይ ያሉም አሉ።
ይልቅ ዕውነቱን ልንገርህ በገፍ አቅም ያበረከቱ፤ ለድምጽ አልባ ወገናቸው በትጋት የባተሉ፤ የዊዝደም ስኬት ለጋሾቻችሁን የጨመቱ የአማራ ልጆችን በንፁህ ህሊና አመስግናቸው። የፖለቲካ እስረኛ፤ የብሎገር፤ የጋዜጠኛ፤ የፀሐፍት በድንገቴም፤ በታቀደም የእስር ፍቺ የብልሆቹ የአማራ ልጆች የማስተዋል ልቅና የትጋት ውጤት ነው። ከውጥኑ እስከ ፍፃሜው የእነሱ የስኬት የብልህነት ጎዳና ነው።
ዛሬ ዋና ከተማቸው ላይ ተሳዳጅ የሆኑበት ክስተት ግን እጅግ ሰቅጣጭ ጉዳይ ነው። የእነ ወሮ ከንቲባ አዳነች አበቤ የ365 ቀን የሞድ ኪኖ የአማራ ልጆች ብልህ ስኬት ልዩ ስጦታ ነበር። አንገት ላለው፤ ኢትዮጵያዊውን ይሉኝታ ለሚያውቅ ምራቁን ለዋጠ ሰብዕና።
ሃጂነት መንፈሳዊነት ነውና ቂመኝነትህን አስወግድ። ለማህበረ ኦነግ መንበር ግርባው ብአዴን ትውልዳዊ ግዴታውን በአግባቡ ሊወጣ ይችላል ተብሎ ለታሰበው አገራዊ ግዴታ ሳይበቃ ዕድሉን አልፈስፍሶ እና አፍተልትሎ ዛሬም ሰርክ የዕንባ ዳሰኛ አስደረገን - ለዚህ ሁሉ የኪሳራ ጉዳይ ገመነኛው ግርባው ብአዴን ተጠያቂ ነው።
ዕድል በማስተዋል፤ በጥንቃቄ ሊያዝ ሲገባ "ለስልጣን አልታገልኩም" ዓዋጁ ባዶ እጁን አጨብጭቦ ዛሬ ከቅኖች ጋር በአበጃት አገሩ የአማራ ህዝብ ተሳዳጅ ሆነ። ታሳሪ፤ ታጋች፤ ተሰዋሪ፤ ተቃላይ፤ በመስቃ የሚገረፍ፤ በድብደባ የሚገደል፤ በድሮን ሰርክ የሚቀጠቀጥ ተሳዳጅ ሆነ። የሚገለማ የመገለ ግፍ ነው።
#አቶ ለማ መገርሳ ጉዳይ(ዶር)
የመጋቢቱን ምርጫው በአዲስ አበባ በአዋሳው ጉባኤ ኢህአዴግ አፀድቆታል። የሆነው ይህ ነው። የቀድሞ ጠቅላይ ሚር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፈቃዳቸው እንጂ በቄሮ፤ በአብይዝም ሆነ ሌንጮይዝም ወይንም ጃዋሪዝም ንቅናቄ አልተገለበጡም። እሳቸውም ዶቼቤሌ ጋር በነበራቸው ቆይታቸው የአማራው መንፈስ እንደ ሆነ መስክረዋል። መፈንቅለ መንግሥት ፈፅሞ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተካሄደም። ገልባጭም፤ ተገልባጭም አልነበረም። ይህ ፋክት ነው። ለፕሮፖጋናዳ፤ ለውዳሴ ከንቱ ፋክትን ማዋል የተገባ አይደለም።
እያንዳንዷን ንቅናቄ የሚከታተሉ አንቱወች ነበሩበት። የፖለቲከኛ እስረኞች የመፈታት ጉዳይ፤ በሚቀዬረው መንግስት የሴት ሊሂቃን ተሳትፎ አንከር የሆኑ አመክንዮወች ልትገምተው የማትችለው ባለቤት ነበሩበት።
በሌላ በኩል ከህወሃት ጋር ድርድር ነበረን የሚልም አዳምጫለሁ። ወይ መዳህኒዓለም አባቴ። ከነበረ ቀሪ የህወሃት አካል ስላለ ወጥተው ሊነግሩን ይችላል። አቶ ለማ መገርሳ (ዶር) ያልተመረጡት፤ እራሳቸውን ለማቅረብ ጋዳ የሆነባቸው መሰረታዊ ምክንያት የፓርላማ ተመራጭ አልነበሩም።
የኢህአዴግ የማዕከላዊ ኮሚቴ፤ የሥ/አ/ ኮሚቴ አባልነትን ይጠይቃል ለኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስተርነት፤ ጠቅላይ ሚር ለመሆን - የኢህአድጉ የግንባሩ ህግ። ይህ ፋክት ነው። ይህ መርህ ነው። ፋክቱን ከመቀበል ውጪ ሌላ መደራደሪያ ነጥብ ሊቀርብበት አይገባም። ሂደቱ አሳማኝ እና መርኃዊ ነውና። ይልቅ አሁን እራሳችሁን ለኢትዮጵያ መሪነት ያጫችሁ ሁሉ ያ ድምጽ አልባው ታምር ቀማሪ የእዮሩ ንጉስ መዳህኒዓለም አባቴ እንዴት እንዳሳካው አቅሙ ካላችሁ አጥኑት።
#በጥሞናዬ ጊዜ የሎቢ ተግባር ከውኛለሁኝ አቶ (ሃጂ) ጃዋር መሃመድ።
ይህን ብዙ አላምንበትም። ትክክለኛ የሎቢ ተግባር ክሱት ነው። ይህን አላዬሁም። አጥብቄ ከነፍሴ የምከታተለው በኽረ ጉዳይ ነውና። ግብረ መልሱም ፈጣን እና ተደራሽ መሆኑን አሳምሬ አውቃለሁኝ። ስለዚህ ላምንህ አልችልም። በግል እንደ ተጽዕኖ ፈጣሪነትህ የሚጠይቁህ ሊኖሩ ይችላሉ። ለስኬት ያበቃ ግን ትናንትም አላዬሁም፤ ዛሬም አላዬሁም።
ወደፊት ከቀናህ አብረን እምናዬው ይሆናል። እስከ ዛሬይቱ ዕለት ግን አላዬሁም።
የጃል መሮ ዕውቅና ከሆነ ህወሃት መንበረ ሥልጣኑን መልሶ እንዲይዝ የዲፕሎማሲው ጫና ሳለ ለዛ እንዲረዳው እንደ አቅም ተጠቅሞ መረጃ ለሚያምኑት አካላት ድሪም ለሚያደርጉት ነግሮ ዕውቅና እንደ አሰጠ አምናለሁኝ። እንጂ ከዛ በፊት ብዙም አይቼ የማውቀው የማህበረ ኦነግ የሎቢ ስኬት አላውቅም። የኦፌኮ መሪ ፕ/ ዶር መራራ ጉዲና በዘመነ አብይዝም ለሰኔት፤ ሆነ ለኮንግረስ ግንባር የማስመታት ዕድልስ በቅተው ያውቃሉን? በዘመነ ህወሃት ቤተኛ ስለነበሩ።
ከዚህ ላይ እማነሳው ቁም ነገር ህወሃት በጦርነቱ ጊዜ በተመድ የፀጥታ አካላት፤ በምዕራብውያን፤ በአውሮፓውያን የስለት ልጅ መሆኑን አይተናል። ይህ ተቀባይነት እያለው በህወሃት ሥልጣን መልቀቅ እንደምን እነኝህ አካላት ተስማሙ የሚለውንም አጥኑት። በምን ሁኔታ ያ የማይደፈርን አቅምን ሰብሮ የገባ አመክንዮ ምን ነበር ብላችሁ መርምሩት። አንዳንዶች በዶር ቴወድሮስ አድሃኖም የጤና ድርጅት ዲያሪክተር አቅም ነው ሲሉ እሰማለሁኝ።
ህወሃት ሥልጣን እንዲለቅ ሲደረግ እኮ ዶር ቴወድሮስ ጄኔባ ነበሩ። የግርግሩን፤ የተኩረፈረፈውን ፖለቲካ አስክኖ ፋክት ተኮር ጥናት ማድረግ የስኬት መዳረሻ ነው። በሌላ በኩል በድጋሚ ወደ ሥልጣን ህወሃትን ለማምጣት መሻትም ነበር። ያ መሻት ስለምን ተሸበሸበ ብላችሁም አጥኑት።
በተጨማሪም እራሱ ጫካ ከነበረው ኦነግ ይልቅ የኡጋዴ ነፃ አውጪ ደህና ሽፋን በውጩ የዲፕሎማቱ ማህበረሰብ ዘንድ ያገኝ ነበር በዘመነ ህወሃት። በሎቢ ዘርፍ የወደፊቱን አብረን የምናዬው ሲሆን በቀደመው ግን የአቶ (ሃጂ) ጃዋር መሃመድ ሚና ጎልቶ የወጣበት አንድም ክስተት የለም።
ኢትዮጵያ ከፖለቲካ እስረኞች ነፃ እንድትሆን የተደረገበት አመክንዮም ከማህበረ ኦነግ የሎቢ ተግባር ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ አልነበረውም። ቀድሞ ነገር ከአብይዝም በፊት ለማህበረ ኦነግ ፖለቲካ ኢትዮጵያ አንጡራ ጠላት ናት።
ማህበረ ሌንጮን ከኢትዮጵውያን ጋር ገጥ ለገጥ ያገናኜውም የአቶ (ሃጂ) ጃውር ንቅናቄ አልነበረም። የግንቦት 7 አገራዊ ንቅናቄ ምስረታ እና ሂደት ነበር። ለወግም ለማእረግም ያበቃው። ለውጥ ተብይወ ሲመጣም ኦነግን የቀደመው አልነበረም ቀድሞ አገር ሲገባ።
#ክውና።
ፖለቲከኞች በመታመን ላይ በራሳችሁ ላይ የምትሠሩት ተግባር ይወስነዋል። ዕውነትን አትተላለፋት። ግልጽ እና ቀጥተኛ ፍላጎታችሁን ጠረጴዛ ላይ አውሉት። የጀርባ ሆነ የቁርጭምጭሚት ጉዞን አትድፈሩት። ተፀፀቱ። ከሴራ፤ ከቂም አፓርትመንት፤ ከበቀል ክምር፤ ከጥላቻ ትንፋሽ እራሳችሁን አግልሉ። ትዕዛዝ አይደለም የባተሌ እህት ትህትናዊ አስተያዬት ነው።
የጎዳችሁትን ማህበረሰብ ይቅርታ ጠይቁ። የኢትዮጵያ እናቶች ማህፀን ከእንግዲህ ቄራ የሚሆነው ለእናንተ ኢጎ ሊሆን አይገባም። ለህዝቡ እዘኑለት። አገራዊ ሰብዕና መኖር ከመታደል በላይ መመረቅ ነው። ለዚህ ዕውቅና ስጡ።
ንግግራችሁ በሆናችሁት ልክ ይሁን። የህሊና ሚዛን ያለው ከህዝብ ስለመሆኑ አትተላለፋ። ከሰማዩም ከምድሩም ህግ በላይ ጉልላት ነኝ አትበሉ። ይህም ትህትናዊ ዕይታዬ ነው። በመታበይ ውስጥ፤ ሁሉን አድርጌዋለሁ ከማለት ይልቅ ዝቅታን ብትመርጡ መልካም ነው። ድርጊተኞች ይታዘቧችኋል።
እናንተ የምትመኙትን ነፃነት ለሌላው ለመስጠት ንፋግ አትሁኑ። ኢትዮጵያ ደክሟታልና። እኔ እማምንበት በተፈጥሯዊነት፤ በሰዋዊነት ላይ ትኩረት ያላቸው ቅን፤ ታዛዥ እና እሩህሩኃን፤ አጽናኝ በሆነ በቲም ኢትዮጵያን ቢመሯት ምኞቴ ነው። በቃት መከራ ኢትዮጵያ። ለፖለቲካ ሊቃናት ተብሎ የሰው ግብር እና ማገዶነት ይቁም!……
በሽታሽቶ የአማራ ህዝብ ተጎድቷል። ካሳም ሊሰጠው፦ ይቅርታም ከንፁህ ልብ ፈልቆ ሊጠዬቅ ይገባል። ብዙውን የኢትዮጵያን ቀዳዳ የሚደፍኑት የሰከኑ የአማራ ልጆች ናቸው። ከፍ ያለው ግማድ ተሸካሚወችም መሬት ላይ የአማራ ልጆች ናቸው። ለአማራ ልጆች ትጋት የሚሰጠው ዕውቅና በኢትዮጵያ ፖለቲካ {}፦
በተለይ የአናት መጠሪያ ከሌለ ከቁጥርም አይገቡም ኢሊት ካልሆኑ። ኢትዮጵያ የተሰራችው በኢሊት ሳይሆን በሊሂቃን ነው። ሊሂቃኑ ፈርኃ እግዚአብሄር፤ ፈርኃ አላህ ያደረባቸው የተሰጣቸው ስለነበሩ ሚስጢር ተገለጠላቸው።
ከሁሉ እሚያሳዝነኝ የኢትዮጵያ ፖለቲካ #ካጂ መሆኑ እና የአማራ ህዝብ ተሳትፎ #አመድ አፋሽ መሆኑ ነው። በመጨረሻም የቢቢሲው እና የዶቼቬሌ ቃለምልልስ አድራጊ ሁለት የጨመቱ ጋዜጠኞች ምስጋናዬ ይድረሳቸው።
አቶ (ሃጂ) ጃዋር መሃመድ ስለ አዲስ አበባ፤ ስለ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ፤ ስለ ነገረ መከበብ እና ጦሱ ቢጠዬቅ መሻቴ ነበር። ኢትዮጵያዊነት ከአዲስ አበባ ውጪ፦ ፓን አፍሪካኒዝም ከመዲናዋ ውጭ፤ አዲስ አበባዬ የዓለም መንፈስ ማረፊያነቷ ወደ አንድ ጥብቆ ምልከታ ስትዘዋወር ምን እንደሚሰማው ወጣቱ ፖለቲከኛ ሊጠዬቅ ይገባ ነበር? ከዚህም ሌላ በሃይማኖት እኩልነት ላይ ያለውን የአቋም ሁኔታማ መስማት እሻለሁኝ።
ሌላው እጅግ የገረመኝ ከኦሮሞ ይቅደምነት ኢትዮጵያ ትቅደም የአቶ ሃጂ ጃዋር እርምጃ መሆኑ ነው። እራሱን ችሎ ጥናት እና ምርምር ሊካሄድበት የሚገባ አመክንዮ ይመስለኛል። ሰፊ ክትትልም የሚጠይቅ በኽረ ጉዳይ ነው።
አቶ ለማ መገርሳ (ዶር) "እፈራለሁ፤ ፍርሃት አለብኝ፦ ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው" ያሉትን ሞደርናይዝ አድርጎ አቀረበው። ሌላ አዲስ ነገር የለውም። ለኢትዮጵያ ተጎጂወች ያደረገው ምግባረ ሰናይ ድጎማም እስከ አሁን አላዬሁም። የተጎዱትን ሄዶ ለመጎብኜት እንኳን አልሞከረውም። ኢትዮጵያን ማዳን ህልሙ ከዚህ አንፃር ዝርግ እና ልሙጥ ሆኖ ነው ያገኜሁት።ያው እንደ ተለመደው ኮንፊውዝድና ኮንቢንስ የማይሰለቸው ደግሞ ጣዕሜ ሲል አዳምጫለሁኝ።
ቅንነት ቢለመልም፤ ጥላቻ ድል ቢነሳ ኢትዮጵያ ለሁላችሁም ትበቃለች።
ኢትዮጵያ ከዚህ የባሰ አናርኪዝም ውስጥ እንዳትገባ ከጠቅላይ ሚር አብይ አቅም እና ፍላጎት በላይ የነጠረ፤ የበቃ የሃሳብ ልዕልና የተቋም ብቃት ያስፈልጋል።
ከሁሉ በላይ ሩህሩህ እና አዛኝ መንፈስ በእጅጉ ያስፈልጋል። ለዚህ ምን ያህል ክህሎት እንዳላችሁ እራሳችሁን ለኢትዮጵያ መሪነት ያጫችሁ ሁሉ ማረጋገጥ ይኖርባችኋል። በሌላ በኩል የጠሚር አብይ አህመድ አሊን አሳቻ ሰብዕና ሳትንቁ፤ ሳታቃሉ፦ ሳታጣጥሉ አጥኑት። ለመሆኑ የሎሬት የሰላም ተሸላሚውን ጠሚር አዋቅችኋቸዋልን?????
ተጽዕኖ ፈጣሪነት ማለት መሪነት ማለት አይደለም፤ መሪነት ግን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሊሆን ይችላል። Einfluss ist keine Führung; Aber ...
ቸር አስበን፥ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፥ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ፁሁፍ ፲፬ ኛው ምዕራፌ በዚህው ይጠናቀቃል። ነገ አንድ አውዲዮ ብቻ ይኖረኛል።
መሸቢያ ምሽት። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
30/12/2024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ