ምጥን።
ምጥን። ከሥርጉተ - ሥላሴ ( Sergute © Sselassie ) 06.03.2018 (ከጭምቷ - ሲዊዘርላንድ) „የሰው ልብ መንገድ ያዘጋጃል፤ እግዚአብሄር ደግሞ አካሄዱን ያቃናለታል።“ (ምሳሌ ምዕራፍ ፲፮ ቁጥር ፱) · መነሻ። ጤና ይስጥልጥኝ የማክበረዎት አቶ ሰርጸ ደስታ፤ እንደምን አሉልን። „ ቢያንስ ቪኦኤና ዶቼቪሌ እንዴት ዋሹን ? ይቅርታ ይጠይቁን !! አዋጁ አልጸደቀም ! ( ሰርፀ ደስታ ) “ ህግ ገዝቶት ለማያውቀው ማህበረ ፈርዖን ቁጥር ሳይሆን ሰው ስለመፈጠሩም ያልተቀበለ፤ ሊቀበልም የማይፈቅድ ስለመሆኑ በዚህ ጉዳይ ሃሳብ ለመስጠት አይደለም የዛሬው ጉዳዬ። በሌላ በኩል ጉዳይ እኔን ስለማንሳተዎት ሳይሆን ፍላጎታችን የንፋስ ቤተኛ ስለሆነ ምጥን ማመጣጠን ያው ሴታዊ ተግባሬም ነው - የሽሮዋን ተክተክ ይሰቧት እንደ ማለት። ስለሆነም ዛሬም የምለው ይኖረኛል። በሽሮ ምጥን ያው አንታማም። ዘገዬሁ መስል ሰለ ሰላምታው? ግን እንዴት ሰነበቱ ጸሐፊ አቶ ሰርጸ ደስታ? አስተያየተዎን ደስ ብሎኝ ነው ያነበብኩት። የዛሬ አይደለም አንባቢነቴ፤ የእርስዎ ጹሑፍ ታዳሚነቴ የጻፉትን ቢጽፉ በብራናዎት ላይ ለሙግት ትውር ብዬ አላውቅም። ያ ማለት በሁሉ ነገር ተስማምቼ አይደለም። የሚስማማኝን፤ የማይስማማኝን አነባለሁኝ። የማነበው እርስዎም የሐገሬ ኢትዮጵያ ነገር ግድ ስለሚለዎት ነው የሚጽፉት እንጂ እንደሌላው ቁጭ ማለት ይችላሉ። መጻፍ ወገብ ቁርጥ ነው የሚያደርገው። በዚህ ስሌት ስንሄድ እማነበው...