ሁለት ሚሊዮን የኢትዮጵያ የዋጣው ሰርግ።

„ሁለት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር
  የወጣበት ሠርግ“ ዕድምታው
         በእኔ ዕይታ።
                ከሥርጉተ - ሥላሴ (ሲዊዘርላንድ ዙሪክ 04.10.2017)

„ቤት በጥበብ ይሠራል፣ በማስተዋል ይጸናል።(መጸሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ 24 ቁጥር 3)
ሰሞኑን በሥነ - ጥበብ ዙሪያ ትጉህ ወጣት በሆነችው በሙሽሪት መቅደስ ጸጋዬ ሠርግ ዙሪያ ብዙ ይባላል። በአውንታዊነትም ሆነ በአሉታዊነትም። ሠርግ ባህል ነው። ወግ ነው። ልማድ ነው። ሃይማኖትም ነው። ህግም ነው። ድርጅትም ነው። ታላቅ ተቋም፣ የህብረተሰብ መሥራችም ነው። የማህበረሰብ አውራ ባላና ወጋግራ ነው። ዬፍቅር መርኽም ነው። የአንድ ህዝብ መሠረቱ በቤተሰብ ላይ የተማከለ ነው። ከዚህ በላይ ሠርግ የአንድ ጥንድ ብቻ ጉዳይ ሳይሆን፣ ጥንዶችን በሥጋም በደምም የሚገናኙ ወገኖች ሁሉ የሐሤታቸው ቋት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በሁለቱ ጥንዶች በአቅራቢያነት የሚተዋወቁ፤ የማህበራዊ ኑሮ ተጋሪዎችም የጉዳዬቸው አብራክ ነው። አለፍ ባለ ሁኔታም ደግሞ፣ እንደ ተፈጥሯችን እንደ መጣንበት ማህበረሰብ ሥነ - ልቦናዊ አቋምና ምልክታ በአስተሳሰባችን፤ በልምዳችን፤ በተመክሯችን የተለያዬን በመሆናችን፣ ይህን ልዩነት በኪዳን በውል የሚቻቻልበት የችሎት አደባባይ ነው። ስለዚህ ጋብቻው የጥንዶቹ ብቻ ሳይሆን፤ በርካታ ርቁቅ ክስተቶች አብረው በስምምነት በጸሎት የሚታደሙበት ልዑቅ ሂደት ነው።

አንድ ሰው ይማራል፤ ይመረቃል፤ ይሠራል ከዚህ በኋዋላ ተለምዶውን፤ ዕውቀቱን፣ መዋዕለ ንዋዩን የሚያፈስበት፣ ፍሬውንም አዝምሮ የሚይበት በጋብቻ ነው። ጋብቻ አንድ ማሳ ነው። ታታሪ ገበሬ የሚያሻው። ድካሙ፤ ልፋቱ፣ አስልቺው የህይወት ጉዞው ሁሉ መስከኛው ትዳር ላይ ነው። መዳረሻ። መስከኛ። ይህቺ ሸበላ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች፤ በተለያዩ የቀለም እና ዬተግባር ት/ቤቶች ፍላጎቷን ለማሳካት ያልተቋረጠ፤ ተከታታይነት ያለው ጥረት በማድረግ ዛሬ ካለችበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። ወሸኔ

ለእኔ ይህ ሠርግ ዘመነ እቴጌዎችን የመለሰ ነው ብዬ ነው እማምነው። ለእኔ ይህ ሠርግ ኢትዮጵያዊነትን ከውስጡ የተመለከተ ሠርግ ነው ብዬ ነው የማስበው። ለእኔ ይህ ሠርግ በጥበብ ጎራ አንድ ለዬት ያለ፤ 21ኛውን ምዕተ - ዓመትን ከቀደምት ኢትዮጵያዊ ጥሪቶች ጋር በውል ያሠተሳሰረ ኪዳናዊ ማህደር ነው ብዬ አስባለሁ። በተጨማሪም የትውልዱንም የማድረግ አቅም ያሰዬ፣ ያመላከት ልዩ ክህሎት ነው ብዬ ነው የማስበው። ዝክረ ትውፊት ነው።

አንድ ፊልም የዘመነ እቴጌዎችን ለመሥራት ቢታሰብ ይህን ያህል ወጪ ይኖረዋል። እኔ ያዬሁት እንደ አንድ እውነተኛ የሠርግ ታሪክ የፊልም ተውኔት ነው። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብር አሁን ያለው የመግዛት ወይንም የማድረግ አቅሙና የኑሮው ውድነት ጋር ሲነጻጻር ለእቴጌዎች ሠርግ የሚገባውን ኩራት፤ የሚገባውን ክብር፤ የሚገባውን ብቃት፤ የሚገባውን ልቅና ሠጥቷል ብዬ አስባለሁ። ስለዚህም ወጪው ምንአልባትም ከታቀደው በላይ ከፍ ብሎም ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም የጥበብ ሥራ የማያልቅ ነው። በዬደቂቃው አዳጊ ሃሳቦችን ማስተናገድ ግድ ስለሚለው። በተጨማሪም ይህ ሠርግ አሁንም ለእኔ ለሥርጉተ - ሥላሴ ፈተና ላይ የወደቀውን ኢትዮጵያዊነትን በረቀቀ ሁኔታ ለመታደግ ታቅዶ የተከወነ ነው ብዬ አምናለሁ። ተምሳሌነቱ ፈርጥ ነውና
ሠርጉ … ሐገር በቀል በሆኑ የውስጥነት አስኳሎች ላይ ሰፊ የሆነ አትኩሮት ነበረው። ጥረትን በጥንቃቄ አቅዶ መከወን መቻል በራሱ አውራ ነገር ነው። እንደ አንድ በዕውኑ ዓለም ወይንም በጋህዱ ዓለም ያለ የሚጨበጥና የሚዳሰስ፤ ሥዕላዊና ገላጭ የተውኔት መጸሐፍ ነው እኔ በግሌ ያዬሁት።
አንዲት ምሳሌ ለማጣቀሻ ብቻ ላንሳ …
እኔ ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ሊያተኩሩባቸው በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ባተኮረው „የተስፋ በር“ መጸሐፌ ላይ አንድ ነጥብ አንስቼ ነበር። ልጆች በህይወታቸው ውስጥ በቀለም ምርጫቸው ከብሄራዊ ሰንደቃችን ውስጥ ቢያንስ አንዱን የዘወትር ምርጫቸው እንዲያደርጉት  ወላጆች ወይንም አሳዳጊዎች ባትጫኗቸውም፤ ሁናችሁ አሳዮዋቸው የሚል ዕድምታ ነበረው። አሁን በዚህ ሠርግ ላይ ወርኃ መስከረም እና አድዮ የክብር ታዳሚዎች ነበሩ። አድዮ ቦታ ሳትለይ በሁሉም የሐገራችን መሬት ላይ እኩል የምትበቅል ብሄራዊ አባባችን ናት። ኢትዮጵያ ብሄራዊ አበባም ያላት፤ ምንአልባትም ብቸኛዋ ሐገር ወይንም ከጥቂቶቹ አንዷ ትምሰለኛለች። …  (በጥናት የተደገፈ ስላልሆነ ነው በይመስለኛል የተከወነው።) ከዚህም ሌላ አድዮ አገናኝም ናት። የብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማችን ዳኛ እሷናት። አድዮ  ዬአዲስ ዘመን ብሥራት ነጋሪ ጋዜጠኛም ናት። አድዮ የተስፋ እርግብም ናት። የሠርጉ ድባብ በዚህ መንፈስ ወጥ የሆነ ነበር። ለእኔ ይህ በራሱ ፍጹም የሆነ ሐሤት ሰጥቶኛል። አድዮ አድማጭ አግኝታለች። ዬአድዮ የትርጓሜ እድምታ ተንከባካቢ አግኝቷል ባይም ነኝ። እታለም አድዮ በቂ አሳላፊ፣ አስተናጋጅም አግኝታለች። አድዮ የልጆች የእንቁጢ ዓይን ብቻ ሳትሁን፤ የማንታችንም ሸማችን ናትና። የእኩልነት ዓውዳችን። ፈጽሞ የማታዳለ - ደግዬ።

ሠርጉ ብዙ መሳናክሎችን፤ ፈታኝ የሆኑ የሥነ - ልቦና ጫናዎችን ድጦና ደፍጥጦ ለታላቁ ተልዕኮውና መልዕክቱ ስኬታማነት የበቃ፣ የበቀለ ተግባር ከውኗል ብዬ አምናለሁ። አንድ ሰው የሚኖረው በራሱ ህሊና ውስጥ ነው። አንድ ሰው ጉዞውን አህዱ የሚለው፣ መንፈሱ በሚፈቅድለት ዕሳቤ ማዕቀፍ ውስጥ ነው። ይህቺ ወጣት ልትኖር የምትፈልገውን መምረጥ፣ መወሰን የምትችለው እሷና እሷ ብቻ ናቸው። አቅሟን ለክታ ራዕዮዋን ዕውን ማደረግ መቻሏ የተፈጥሮ ጸጋዋ ነው። ለዛውም ከዚህ ሠርግ ከቤተሰባዊ ጠቀሜታው ይልቅ ህዝበ - ጠቀምነቱ ጎልቶ፤ ገልብቶ፤ ገኖ እና ፈንድቆ የወጣ ጉልበታም እርምጃ ነው የወሰደችው - አሁንም ለእኔ። ትርጉሙ የሆነ መስህብ አለው።

ልብ አለዋሷ፤ መንፈሷን ለማሸቀጥ አለመፍቀዷ፤ ይህቺ ሙሽራ በራሷ የመተማመን አቅሟን በጉልህ እንዲታይ አድርጎታል። በዓለም ያሉ ታዋቂ ግለሰቦችም ሠርጋቸው ብዙ ቢሊዮን ዶላር ነው የሚፈስበት፤ ልደታቸውም እንዲሁ። ለሚያሳድጓቸው ውሻች ሳይቀር የሚወጣው ወጪ የት-እዬለሌ ነው። በዬሀገራቸው መንገድን ተጠልለው የሚኖሩ እጅግ በርካታ ዜጎች ይኖራሉ። ለእነሱም የሚችሉትን በግብረ ሠናይ ድርጅቶች የሚያደርጉ ይኖራሉ፤ የማያደርጉም ይኖራሉ። በግበረ - ሠናይ ጉዳይ ላይ አትኩሮት ያላቸው ታዋቂዎችም ቢሆኑ፤ የመንግሥትን ኃላፊነት ካልተወጣችሁ ተብለው አይወቀሱም፣ አይነቀሱም፣ አይከሰሱም። ይህቺ ሸበላ የምትችለውን እያደረገች ነው። መንግሥት ደግሞ አይደለችም።

ጣና ታሟል፤ ጣናን የትኛው የመንግሥት የጋዜጠኛ ቡድን እራሱን በቻለ ፕሮግራምና ንድፍ ከርዕሰ መዲናዊ፤ የትኛው የተፈጥሮ እንክብካቤ ቡድን ከዕርዕሰ መዲናዋ፤ የትኛው የጥበብ ቤተሰብ ወይንስ ከዘመኑ ሽማምንቶች ዬጠ/ ሚ ሐይለማርያም ደሳለኝ ልዑክ፤ ወይንስ የትግራይ መሳፍንቶች ልዑክ፤ ወይስ እነ አቶ በረከት፤ እነ አቶ አዲሱ ለገሰ፤ ማን ሄዶ ጠዬቀው? መቅዲ ፕሮዳክሽን ግን ከቦታው ድረስ ሄዶ ጣናን „እግዚአብሄር ይመርህ“ ብሎታል። በቂ አትኩሮት ሰጥቶታል። የሞጋቾች ቡድን በጣና ጉዳይ ላይ ቁልጭ ያለ መልዕከት እመራለሁ ለሚለው ገዢ መሪ ድርጀት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። ቅሬታቸውንም በይፋ ገልጸዋል። በድፍረት
ይህም ብቻ አይደለም ዕንቡጥ ተዋናዮችን ባህርዳር ላይ አወዳድረው፣ ያውም በጥርስ በተያዘው „የአማራ ክልል“ ለአሸናፊ አራት ተዋናዮች የአንድ ዓመት ወጪያቸውን „መቅዲ ፕሮዳክሽን“ ችሎ፤ „ከቦጋስ የጥበባት ት/ቤት ማዕከል“ ጋራ ተነጋግረው፤ በነፃ የትውና ትምህርት ለአንድ ዓመት እንዲማሩ እንቅስቃሴ ጀምሯል - ሙሽሪት በዳሪከተርነት በምትመራው ድርጅቷ።
ይህም ብቻ አይደለም፤ በአለፈው ዓመት „በማለዳ ኮከቦች“ የትወና ብቃት ውድድር ከሴትና ከወንድ አንደኛ የወጡትን ሁለት ተዋናኞች ሞጋቾች ላይ የትውና ሥራ እንዲጀምሩ አድርጓል - ድርጅቷ። ሌላም በባህርዳሩ የትወና ውድድር አንደኛ የወጣችውን ተዋናይ በተጨማሪነት በሞጋቾች ቀጣይ የትወና ጊዜ ውስጥ በቀጥታ እንድትሳተፍ ተደርጓል። ይህ መልካም ነገር አይደለምን? ለእኔ ለሥርጉተ - ሥላሴ ኃላፊነቷን ለመወጣት ቡቃያዊ ጥረቷ በቂ ነው።

በማይቻልበት ሁኔታ የማይቻለውን እንዲቻል ማደረግ በጥበብ፤ በስልትና በዘዴ መፈጸም ሲታደሉት ብቻ የሚገኝ የሰማይ ጸጋ ነው። ወደፊትም ቢሆን ባህሏን፤ ወጓን፤ ልማዷን፤ ማተቧና መንፈሷ ያደረገችው ሸበላ ተስፋ ያለው፣ ህዝብ ጠቀም ተግባር ትከውናለች ብዬ አስባለሁ። አያያዟ በዕወቀት ላይ መመሥረቱ ብቻ ሳይሆን፤ ውስጥን ውስጥ ያደረገ ስለሆነ። ቅንነትን እስከታጠቀች ድረስ ብዙ መስኮች አሉ ...  ባለቤት የሌላቸው፤ አስተዋሽ ያጡ ሀገር በቀል ችግሮች። ግን እንደ መንግሥት ይህንን፣ ያነን ማደረግ አለባት ተብሎ ማሰብ ግን የተገባ አይደለም። በምትችለው ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ ነው ልኬታው መሰፈር ያለበት። ይሄንን ደግሞ ሁናበታለች
እርግጥ ቢሆን ብዬ ያሰብኩት … ጥሪው ላይ የአልባሳት ምርጫ የተጋባዥ እንግዶቿ እንዲሆን ብትተዎው፤ የግል ነፃነታቸውን ብትጠብቅላቸው መልካም ነበር። ተጠሪ ለዛውም ኢትዮጵያዊ ተጋባዥ „ጥሪው በቅድመ ሁኔታ“ ሲሆን ለእኛ ተፈጥሮ ትንሽ ይሻክራል። ኢትዮጵያውያን ያልገዛም ባይነት ደም አለን ሲባል በስውር ማንም እንዳይነካቸው ገደብደንበርክትር የተበጀላቸው ያልተጻፉ ህጎች አሉን ማለት ነው። አገር ልብስንም የማይፈቅዱት ይኖራሉ። ቀልል ያለ አልባሳትም ምርጫቸው የሆኑም ሊኖሩ ይችላሉ። በሌላ በኩል ግን ይህም ቢሆን በቀና ሲታይ፤ በዕውነተኛው ሠርግ ላይ የእቴጌዎችን የግብርና የሠርግ ሥርዓትን በምልሰት ተውኔታዊ ለማድረግ ከታሰብ ቅኑ ዕይታ የመነጨ ነው ብለው ለሚያምኑት ደግሞ፤ ጉዳዩ በልስላሴ እንዲታይ ያደርገዋል። አዎንታዊነቱ  … ውበቱን ወጥና የተዋበ ለማደረግ ከታለም በጎ ጤናማ ዕይታ አንጻር ከተሰላ …
ሌላው የኢትዮጵያ ችግር እልቀተ ቢስ ነው። አሁን በዚህ ሰዓት እንዲህ ያለ  …. „የናጠጠ ሠርግ“ የሚሉ ወገኖችም ከህዝብ ተቆርቋሪነት አንጻር ይኖራሉ። በተለይ በነፃነት ትግሉ ያሉ ወገኖች። እኔ አንድ ነገር የማስታውሰው አለ። ታላቅ እህቴ ጋብቻ አባቴ እንድታደርግ ሲጠይቃት በደረግ ጊዜ ነው፤ ኢትዮጵያ ነጻ ስትወጣ እዳራለሁ አለችው። ይሄው አቨይም አለፈ ሠርጓን ሳያይ …. ኢትዮጵያም አለች እንዳለች። ልጆች ወልዳ፣ ልጆቿ የሠርጋችሁ ፎቶ አሳዩን ሲሉ መልስ አልነበራትም። ስለዚህ በተፈቀደው ጊዜና ሁኔታ የሚችሉትን ተፈጥሯዊ ዕሴት መከወን ብልህነት ነው። አብሶ ለሴት ልጅ በዕድሜዋም ሆነ  በዕድሏ ጢባ … ጢቢ መጫዋት አይኖርባትም፤ ሌላ አስገዳጅ ነገር ካልገጠማት በቀር … በጊዜዋ እንደ ተሰጣት ማደረግ ያለበትን ማደረግ ይኖርባታል። ይህም ሌላው የብቃት መክሊቷ ነው የሙሽሪት መቅደስ ጸጋዬ። ውሰጧ ፍሬነገር ነው። አልተላለፈቸውም ከጸጋዋ ጋር … ጸጋዋ ለራሷ ኑሮም ተጠቃሚ እንዲሆን ይለፍ ሰጥታዋለች። 
  
ሁለተኛው ከአንድ ቤት የሠርግ ለት አንዱ ሟች፣ አንዱ ሠርገኛ ልጅ ቢሆኑ፤ ወላጆች ሁለቱንም ባህላዊ ትውፊቶች በተፈቀደላቸው ሥርዓት እንዲከወኑ ይፈቅዳሉ። ሬሳ ተቀምጦ ሠርግ አለ። ኃዘን - ተፍሰኃ ይሉታል ቀደምቶች። ዕሴታችን ይኸው ነው። 

ስለ እሷ ካነሳሁ ነገረ ኢትዮጵያዊነት በሚገርምና በሚደንቅ ሁኔታ እዬፈነደቀ፤ እንደ አዲስ ፏፏቴ ፍንድቅድቅ ብሎ እዬተንፎለፎለ ነው። አሁን „የማለዳ ኮከቦች“ የዚህ ዓመት የውድድር ነፍስ ረቂቅ እና ጥልቅ ነው። እራሱ ሃሳቡ፣ ፈጠራው ረቂቅ ነው። የጸና ትውልድን መገንባት እኮ ነው ትልሙ። ወጣቶቹን በሞራል፤ በሥነ-ምግባር፤ በራስ መተማመን መንፈስ፤ በጋራ ሥራና ሃላፊነትን በመቀበልና በመወጣት፤ በመቻቻልና በአብሮነት ሁነት እዬቀረጸ ነው። ተተኪ በማፍራት እረገድ የፈጠራው ባለቤት፤ የአዲስ ሃሳብ አፍላቂው የገጣሚ ፍጹም አሰፋው ተልዕኮና ፍልስፍና እጅግ ያረካል። ብሩክ ራዕይ። የተስፋ ኩላሊት። ምስባክ።

ያለው የቡድኑ ቤተሰባዊነት ስሜት፤ የወጣቶች ሥነ  - ልቦናዊ ብቃታቸውን ኮትኩቶ አቅጣጫ በማስያዝ ላይ ያለው ዕድምታ፣ ይገርማል። እራሱ ወጣቶቹ በጓደኞቻቸው ላይ ዳኝነት ሲሰጡ ስቅስቅ ብለው እያለቀሱ፤ „በራሴ ላይ ልወስን እያሉ፤ እሱ/ እሷ ከእኔ ትሻላለች እያሉ ነው።“ ይህ የት ይገኛል? ለ40 ዓመት ከዚህም  ለሚበልጥ ጊዜ በሴራ ፖለቲካ በተተበተበ፤ በኢጎ መርዝ ፍላጎታችን እና ራዕያችን መቃብር ውስጥ በከተሙበት ዘመን ይህን ጥሶ የወጣ የተግባር ት/ቤት ነው ድንቁ ወጣት የገነባው። አሁንም ይገርማል። ብጡል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶም ተስምቶም በማይታወቅ ሁኔታ ሴቶች እኩል መድረክ ያገኙበት „በቦጋስ“ ነው። „ቦጋስ“ ብቸኛው የእኩልነት ሥነ - ትምህርት ቤት ነው። መጨረሻ ማለፍ ላይም አስር ተዋናይ አምስት ከሴት አምስት ከወንድ። ከድንቅ በላይ። አሸናፊዎች ስድስት ሲሆኑ ሦስት ከሴት፤ ሦስት ከወንድ። ዋንጫ አንድ ለሴት አሸናፊ/ አንድ ለወንድ አሸናፊ። አይገርምም? ስንቱን ዳገትና ቁልቁለት ነው የፍጹሜ ግሬደር እዬደለደለ ያለው። ዓራት ዓይናማ መሃንዲስ።

ይህም ብቻ አይደለም፤ ለሴት እህቶቹ ያለው ፍቅር ያላበለ ፍጹም ተፍጥሯዊ ነው። ከመንፈሱ ከውስጡ ነው። እናት አንጀት ነው። የህይወቴን ህልፈት፤ የሰማዕቷን ታዳጊ ወጣት የሀንዬን የግፍ ሸለቆ፤ መውደዷን ገልጻ ከማህበረሰቡ ስለምትገለለው ባተሌ አንስት እህቱ የተቆርቋሪነቱ መንፈስ እጅግ፣ እጅግ ቅርብ ነው።  በእውነት ትመስጣለህ መታደልህ አባ ቅንዬ። ገጣሚነትህንም አትፍራዎ። ነህ።

የፍጹሜ ራዕይ በር ለተዘጋባቸው በር ማሰከፈት ነው። አማራጭ መንገዶችን ማሳዬት ነው። አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው ያቺ ወጣት ዬሃና ኔሪ ፉከራና ሽለላ አቅምና ጉልበት፤ የምዕራፍ ጎሳዬ እመቤት ጣይቱን አንድ አፍታ በምናብ እንዴት እንዳመጣቻት፤ የታሪኩን ለዛውም ከጅማ ያን ልዑቅ መንፈስ ላዬ፤ የአማንን ከሰቆጣ የፈጠራ ውብ ትዕይንት ላዬ፤  ይህ ወጣት ስንት የተከደነ ሲሳይ በቀጣይ ዓመታት የአደይ አበባ ፀሐይ ሊያደርግ እንደሚችል ሲታሰብ አንድ ሚዛናዊት፤ ሃላፊነት እና ተጠያቂነት ከሚሰማው ትክክለኛ በሕዝብ ከተመረጠ መሪ ከሆነ መንግሥት ከሚሠራው በላይ፤ በላይ፤ በላይ ድርሻውን እዬተወጣ ያለ እጅግ ሩቅ፣ በጣም ሩቅ ወጣት መሆኑ ይታያል።

የተግባር ቡድን አመሠራረት ሥያሜ …  „እቴጌዎቹ፤ የቋራው፤ መይሳው፤ ሚኒልክ፤ ጥቁር ሰው፤ እሳቶቹ፤ ተምሳሌዎቹ …. ወዘተ … ተውኔታዊ ግጥሞቹ የቴወድሮስ ስንብት፤ ሚኒሊክ፤  ወዘተ ወዘተ ወዘተ ….
ምን ስንቱ ብቃትና ጥልቀት ይነሳል … አንድ ታሪክና ምሳሌ እንዴት ያለ ድንቅ ተውኔት እንደወጣው …. ይገርማል።
  
አንዲት ነገር ልከል ወደ ማጠቃለያዬ ከመሄዴ በፊት፤ ባለፈው ዓመት በተመስጦ እከታተላቸው የነበሩት ደማሙና ቀነኒ ነበሩ። አብሶ ለቀነኒ ያን የመሰለ ጸጋ ቦታ ብታገኝ ምንኛ ውብ በሆነ። ከልቤ የቀረች ተወዳዳሪ ነበረች። እርግጥ ደማሙ ሦስተኛ ወጥቷል። ግን ሁለቱን በአንድ ላይ አድርጎ አንድ ድንቅ ተከታታይነት ያለው ወርቅ ተግባር መከወንም የሚቻል ይመስለኛል - በቋሚነት። መክሊታቸው እሸታማ ነውና …
በሌላ በኩል፤ ሳልጠቅሰው ማለፍ እማልሻው ዳኝነቱ ራሱ ተቋም ነው፤ እኔ ኢትዮጵያ ለሰባት ወር በጥቂቱ ነገረ  - ቲያትርን፤ ሰፊ ጊዜውን በሥነ - ጹሑፍ ከአዲስ አበባ ባህልና ስፖርት ኮሚሽን ተምሬያለሁ፤ ከዚህ ሐገርም ቲያትርን ተግባርና ንድፈ ሃሳቡን ለስድስት ወር ያህል ተምሬያለሁ። ሥነ -ጹሑፍም እንዲሁ በሌሎች የተግባር መስኮች ተምሬያለሁ፤ ግን „የቦጋስ ዳኞች“ የሚሰጡት ዳኝነት ይበልጥብኛል፤ ብዙ ያስተምረኛል። ደብተሬን ይዤ ቁጭ ብዬ እማራለሁ። እዬጻፍኩኝ። አይጠገብም። የዳኝነት ኃይለ ቃሎቹ ብዙም አያሳቅቁኝም፤ ምክንያቱም ከዚህም ካለሁበት ሀገር ይሁን ከጎረቤት ሐገሮች ያሉት ዳኞች የሚሰጡት ዳኝነት እጅግ አጥንት ሰብሮ የሚገባ መሆኑን ስለማውቅ። እንዲያውም ሲብስ እጽፋለሁኝ። መልስም ይልኩልኛል። የዬትኛውም ሐገር ዜጋ ይሁን የቀጣይ ትውልድ ግንባታ ጉዳይ ቀልቤ ነው፤ በቂ አትከሮትም አለኝ። የሆነ ሆኖ „የቦጋስ የዳኝነቱ ሂደት“ አስተማሪነቱ እጅግ ያመዝናል። የሚያስበረግግ ወይንም ዬወጣቶችን ቀጣይ ተስፋ የሚቀማ አይደለም። 
በፍጹም።
    
ክወና። እነኝህ ወጣቶች የትኛውንም የፖለቲካ ድርጅት ሊደግፉ ይችላሉ። ቁም ነገሩ በተሰጣቸው የጊዜ ሰንጠረዥ እና ባገኙት አጋጣሚ የተግባራቸው ማዕከል ትናንትን ከነገ በጥበብና በስልት፤ እንዲሁም በዘዴ ከማጋባቱ ላይ ነው። ማለትም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ለማፋፋት ያላቸው ትጋትና ብቃት ዛሬን ማሳደሩ ነገንም ማብቀሉ ላይ ነው። በዛሬ ማህጸን ነገ አለና።  በሌላ በኩል ሰውን ማዕከል ያደረገ ቅን ትውልድን ለመገንባት የሚችሉትን ማደረግ ነው። አብሶ አዲሱ ትውልድ ጸጋውን፤ ተስጥዖውን የሚያወጣበት ቀዳዳ ማበጀት ታላቁ፤ ባለቤት ያልነበረው አመክንዮ ነበር፤ ይህን እያደረጉት ነው። አዎን! በማይቻለው ሁኔታ የማይቻለውን ችለው እያደረጉ ያሉ ድንቅ ቅን ወጣቶች ናቸው - ሁለቱም። አሁን የጣና ነገር እንዴት ከውስጤ እንደገባ … ጣና ታዛቢ የለውም። ጣና ብድር መላሽም የለውም። ጣና ይቀዬመኛል ተብሎ የሚሰጋበት ትክሻ የለውም ….
የምናፍቃችሁ የሐገሬ ልጆች ….

ስንት የሚቻል ነገር ተዳፍኖ፤ ከስሎ፤ ፋድሶ ተቀብሮ ቀርቷል እኮ። አይደለም ኢትዮጵያ እዚህ ውጪ ሀገር። ስንት እየተቻለ፤ ስንት ለውጤት የሚያበቃ ክህሎት፣ ብቃት አንገቱን ተሰብሮ፣ ጀርባው በሽታሽቶ ደቆ፤ ከማህበረሰቡ ተገልሎ ቀርቷል በሴራ ፖለቲካ፤ በሴራ ፍልስፍና።
ሐገር ቤት ስንት ቪሊዮን ዶላር የኢትዮጵያ ህዝብ አንጡራ ሃብት፤ ልዕልት ኢትዮጵያ ተጠውራ ይሁን ተብደራ ያገኘችው የግል መንፈራሰሻ ሆኖ የለ። ዕዳው የነገ የትውልዱ ነው። ባልበላው ዕዳ ከፋይ ነው መከረኛው ቀጣይ ትውልድ። እኛማ እናልፋለን ….

በሌላ በኩል ውጪ ሐገርም ያላቸው ሰዎች ዲል ባለ ሠርግ ይዳራሉ፤ ልደቶችም እንዲሁ ዲል ባለ ሁኔታ ይከወናሉ። ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ሐገርም ይሁን ውጪ ጠረኑ እኩል ነው ስሜቱ። በሌላ በኩል ሠርግ መብትም፤ ነፃነትም፤ ትውልዳዊ ድርሻም ነው። የወላጆች ህልም ዕውንነት ሠርግ ላይ ያርጋል፤ ተሰርቆ፤ ተዘርፎ እሰካልሆነ ድረስ ….

ይልቅ ለሙሽሪት የእኔ መልዕክት ….
ጋብቻ አብነት ነውና ቀጣዩ ጊዜ ይህ አብነታዊ ጉዞ በድርጊት በልጽጎ፤ በመሆን ፋፍቶ፤ ህይወቱ መምህር ሆኖ እንዲቀጥል በማደረጉ ላይ ጎላ ያለ ሃላፊነት ሙሽሪትን ይጠብቅሻል። እኔም ይህን  በአጽህኖት እጠብቃለሁ።
ምኞት … ተፋቀሩ፤ ተጋቡ፤ ወለዱ፤ አብረው ዘለቁ፤ ያፈሯቸው ልጆችም ተምሳሌት ሆኑ … እንዲሆን ነው። የአደባባይ ሰው ሳሎን ቤት ያለ ጉድፍ ማለት ነው። ለሁሉ ተጋላጭ ነው። መጋረጃ የለውም። መጋረጃው ሆኖ በመገኘት ጋብቻውን እንደ ተልዕኮው ከግቡ ማድረስ ብቻ ነው።

ለነገ ኢትዮጵያ አስመስጋኝ ቤተሰብ መፍጠር በማህረሰብ ግንባታ ላይ ትልቅ አስተዋፆ አለውና፤ እንደ አንድ ትልቅ ፕሮጀክት አቅዶ መሆንን ማዝመር፤ መሆንን ማስበል ትልቁ ትውልዳዊ ድርሻ ነው።…. እስካሁን ባለው ሁኔታ  ገጣሚ ፍጹሜ ይሁን፤ ተዋናይት ሙሽሪት መቅዲም ጥረታችሁ ድንቅ ነው። ቀጥሉበት። ብልህነታችሁ በራሱ ት/ቤት ነው።  ትውልዱን በመገንባት ላይ፤ ፍቅርን በማጎልመስ ላይ፤ መቻቻልን በመኮትኮት ላይ ጠንክሩ። በርቱ። ተባረኩ። ሰላማዊ ትግላችሁን፤ ጥረታችሁን እንደ ጥበብ ሰውነታችሁ ሁሉንም በስልት ለመያዝ የምታደርጉት ብርቱ ጥረት እና ብቃትን በተመለከትም እጅግ አከብረዋለሁ። 100 ሚሊዮን ህዝብ ሊሰደድ አይችልም። ልሰደድም ቢልም አይችልም። በአለበት፣ በዛች በተፈቀደችለት ሁነት ለበጎነት፤ ለመልካምነት፤ ለቅንነት መታጋቱ ንብነት ነው። መምህርነትም ነው። በድጋሚ ተባረኩ።

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሽንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
„ፍቅር ያሸንፋል“

መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።