አለማፈር እስቲ ይጠራ ...
ወይ አለማፈር … ከሥርጉተ © ሥላሴ 25.08.2018 (ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።) „መንገዳችን እንመርምርና እንፈትን፣ ወደ እግዚአብሄርም እንመለስ።“ (ሰቆቃው ኤርምያስ ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፵) · ኢትዮጵያ ወግ ደረሳት። ኢትዮጵያ ወጉ ደርሷት የሰማዕታት ቤተሰቦችን ደውሎ የሚያጽናና መሪ ፈጠራለት። ተመስገን! የተጎዱትን ደግሞ በአካል ሄዶ የሚያይ በማጽናኛ መንፈሱ ድብስብስ የሚያደርግ ብሩክ ቅዱስ የሆነ የአሮን በትር ተሰጣት። ተመስገን! ተጎጂዎችን ለመርዳትም በመንግሥት ደረጃ እርዳታ የሚያሰባሰብ በብሄራዊ ድርጅት እስከ መፍጠር ደረሰች አላዛሯ ኢትዮጵያ። ይገርማል። በተጨማሪም አንድ ጠ/ ሚር ደም ለወገኖቹ የሚለግሥ ኢትዮጵያ ፈጠረላት። አሁንም ተመስገን። የሊቢያ ሰማዕታት ብትን የአፈር እና ዕንባ አልተፈቀደላቸውም ነበር። ለዚህ ሰውኛ ቀን ነበር ሌት ተቀን ተግተን እኔ በብዕሬ ሳተናውም ደከመኝ ሳይል በብራናው የተጋነው። ተመስገን ቃሉ አነሰብኝ። ምን ልበለው? ...