"ኢትዮጵያ በየዓመቱ በ2 ሚሊዮን የሚጨምረውን ሕዝቧን መግታት ያስፈልጋት ይሆን?" BBC
https://www.bbc.com/amharic/articles/cgeyzg382rjo ኢትዮጵያ በየዓመቱ በ2 ሚሊዮን የሚጨምረውን ሕዝቧን መግታት ያስፈልጋት ይሆን? 15 ህዳር 2024 "የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ሕዝብ ከ40 ዓመታት በኋላ 10.4 ቢሊዮን እንደሚደርስ ትንበያውን አስቀምጧል። በዚህ ትንበያ ሕንድን ጨምሮ ስምንት የዓለማችን አገራት የዓለማችንን ግማሽ ሕዝብ ይይዛሉ። ከእነዚህ ስምንት አገራት ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያ ትገኝበታለች። የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በየዓመቱም በሁለት ሚሊዮን ይጨምራል። የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሕዝብ ብዛት 129.7 ሚሊዮን ደርሷል። ይህ ቁጥር በ28 ዓመታት ውስጥ እጥፍ ሊሆን እንደሚችልም ተተንብይዋል። በዚህ ትንበያ መሠረትም በ2044 የኢትዮጵያ ሕዝብ 259.4 ሚሊዮን እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህም በሕዝብ ብዛቷ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የሆነችው ናይጄሪያ አሁን ካላት የሕዝብ ብዛት ይልቃል። ለመሆኑ የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት መጨመር ምክንያቱ ምንድን ነው? መጨመሩስ ምን አደጋ ይዞ ይመጣል? ምንስ ዕድል አለው? በተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ የሥነ ሕዝብ እና ልማት ፕሮግራም ተንታኝ የሆኑት ወ/ሮ ገዙ ብርሃኑ፣ የሕዝብ ቁጥሩ ለመጨመሩ ምክንያቶችን ለማወቅ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን ማንሳት የግድ ነው ይላሉ። እነዚህም ውልደት፣ ሞት እና ፍልሰት ናቸው። የአንድ አገር የሕዝብ ቁጥር የሚወሰነውም እነዚህን ከግምት በማስገባት ነው። የውልደት እና የፍልሰት መጠን ሲጨምር እና የሞት መጠን ሲቀንስ የሕዝብ ቁጥር ላይ ጭማሪን ያስከትላል። ተንታኟ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የውልደት እና ...