አስደማሚ ታሪክ /ከጸሐፊ መስፍን ማሞ/
አስደማሚ ታሪክ “እግዚአብሔርን፤ --- አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ። መዝሙር” ምዕራፍ ፲፭ ቁጥር ፪ መስፍን ማሞ ተሰማ ሠላም ለናንተ ይሁን! ኢትዮጵያ የአውሮፓን አይሁዶች ከሂትለር እልቂት ታድጋለች! (ትርጉም) የኢየሩሳሌም ፖስት (The Jerusalem Post) በ27/1/19 ባስነበበው ዕትሙ ይዞት የወጣው ታሪክ ‘ርዕስ’ ነው - ከላይ የቀረበው። ይዘቱ እንዲህ ይከተላል። በአውሮፓ በናዚዎች የሚካሄደው ዕልቂት ጡዘት ላይ በደረሰበት ኦገስት 1943 (እኣአ) ኢትዮጵያውያን አይሁዶች (ፈላሻዎች) በመሪዎቻቸው አማካይነት ንጉሠ ነገሥት ሃይለ ሥላሴን በመቅረብ አስደማሚ የሆነ ጉዳይ አቀረቡላቸው። የአውሮፓ አይሁዳውያንን ኢትዮጵያ በስደተኝነት እንድትቀበልና እነሱም በፈላሻዎች መኖሪያ መጠለያ እንዲያገኙ ንጉሡ እንዲረዱ የሚል ነበር ጥያቄያቸው። በዋርሶ (Warsow) የጌቶ (Ghetto) አመፅ ከተካሄደ ሶስት ወር በሁዋላና የናዚዎች ማሰቃያዎች አራቱ የኦሽዊትዝ ማቃጠያዎች (Auschwitz crematoria) በሥራ ላይ ከዋሉ ሁለት ወር በሁዋላ የዛሬው ጄሩሳሌም ፖስት በቀድሞው መጠሪያው ፓልስታይን ፖስት (Palestine Post) ኢትዮጵያ አይሁዳውያን ስደተኞችን መቀበሏን የሚያትት ዘገባ ይዞ ወጣ። ኦገስት 8/1943 የታተመው ይህ ጋዜጣ ሲያብራራ “የአይሁዳውያንን ወደ ኢትዮጵያ የመሰደድ (Jewish Immigration to Abyssinia) አማራጭ በሎንዶን የሚገኙት የኢትዮጵያ ሚኒስትር ከአቶ ሃሪ ጉድማን (Harry Goodman) እና ከእስራኤል የአጉዳቱ ዶ/ር ስፕሪንገር (Dr. Springer of Agudath) ጋር ተወያይተዋል” ብሏል። “የአውሮፓ አይሁዳውያንን በፈላሻዎች መንደር እንዲጠለ...