ተጠዬቂ እስኪ አንቺ መከረኛ!
መርዝ እዬተዘራ መርዝን ማምከን አይቻልም። „ነገር ግን ወረተኛ ለጥቂት ቀን የሚሆን ወዳጅ አለና በመከራህም ጊዜ ካንተ ጋር መከራህን ከአንተ ጋር አይታገሥም እና ፈጽመህ አትመነው“ ምዕራፍ ፮ ቁጥር ፲ ከሥርጉተ© ሥላሴ 15.08.2018 ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ። ሰው መሆን ሰው ሆኖ መፈጠር ብቻ አይደለም። ስለ ሰው መፈጠርም ዕውቀት ሊኖር ግድ ይላል። ሰው መሆን ቢያንስ ከእንሰሳ መለዬት ማለት ነው በቀላል ትርጉሙ። ሰውነት ለኢትዮጵውያን ከሁሉም በላይ የላቀ ሃይማኖታዊም ዶግማም ነበር። እግዚአብሄር ሰውን ቤተ መቅደሱ አድርጎ ፈጠረ ከሚል ሃይማኖታዊ ዶግማም ጋር የሚያያዝ „ ሰውን እንደ መልካችን በአምሳላችን አንፍጠር“ አሁን ግን እኔ ሰው አይደለሁም እያልን ነው። ሰው መሆን ስለሰው መጨነቅ መሆን ቀርቶ ስለሰው እንዴት እንደሚገደል፤ እንዴት እንደሚወገድ፤ እንዴት እንደሚገለል፤ እንዴት እንደሚታረድ፤ እንዴት አካሉ እንደሚጎድል፤ እንዴት ሥነ - ልቦናው እንደሚሸነሸን፤ እንዴት የውስጥ ሰላሙ እንደሚታወክ መራቀቅ ሆኗል ጀግንነቱ። ጀግንነት ሰብዕናን ሰው መሆንን ጥላህ ከወገብ በላይ ሰው ከወገብ በታች ጭካኔ፤ ወይንም ከወገብ በላይ እንሰሳ ከወገብ በታች ሰው ሆነህ በጥምር መንፈስ በደመ ነፍስ መነዳት ሆኗል። ሰው በራሱ ኢጎ ሠረገላ እዬገላበ ብቻ በቻቻታ እና በሁካት፤ በኳኳቴ እና በዲልቃ መንገድ ሆኗል የሰውነት ደረጃው። በአደባባይ ሰው ሰው መሆን አቅቶት፤ ስለሰው ሰብዕና ማሰብ ተስኖት ጭካኔን ት/ ቤት ከፍታችሁ ልጆቻችሁን አስተምሩ፤ አረመኔነት የልጆቻችሁ መለያ ምልክት የሰብዕናውም መፈጠሪያ አስኳል ይሁን እዬተባለ ነው፤ ለሽብርተኝነት ካሪክለም ይዘጋጅ እዬተባለ ነው፤ ማፍርስ፤ ማቃጠል...