የጉድ ዘመን - የመርዝ ናፍቆት።

እርጋሞት አለመባልህ ስለምን?
„እዬሱስ ግን ህፃናትን ወደ እርሱ ጠርቶ፣ --- ህፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሄር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሄርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀባላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አለ።“
  ሉቃስ ምዕራፍ  ፲፰ ከቁጥር ፲፮ እስከ ፲፯



ከሥርጉተ ©ሥላሴ 15.08.2018
ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ።
ይድረስ ለአብን ባህርዳር።
  • ·      መነሻ።

ሄኖክ የሺጥላ ለጀዋር ወቅታዊ ንግግሮች የሰጠው መልስ


አልፎ አልፎ ሰዎች ምን ያስባሉ ስል አንዳንድ ነገሮችን እከታተላለሁኝ። ዛሬ ያው አቶ ይቱብ አንድ ክሊፕ አመጣልኝ እና አዳምጠኩት። ስንት ግራሞት እንዳለ፤ ስንት ትከዜ እንዳለ፤ ስንት የውስጥ ሃዘን እንዳለ፤ ስንት ሰቀቀን እንዳለ ቤቱ ይቁጠረው። ደስታችን ከቅጽበት ያለፈበትን ጊዜ አላስታውሰውም።

የሻሸመኔው ሰቀቀን እህል ውሃ ጋር አጣልቶን አይናችን እንዳፈጠጠ እያሰደረን፤ ደግሞ ቀጣዩ የት ቦታ ቃጣሎ፤ የት ቦታ መፈናቀል፤ የት ቦታ የሰው እርድ እናዳምጥ ይሆን እያልን ሌቱም ቀኑም ተደባልቆብን ጭንቅ የሚለን ስደተኞች አለን። የድምጽ አልባዎች እናቶች አጀንዳኛ።

ሁለት ነገር ብቻ ላንሳ ወጣት አቶ ሄኖክ የሽጥላ ካነሳው። ግን የጤና ነው ለማለት በፍጹም አልደፍርም። አንደኛው የጎንደር ህብረትን በሚመለከት ነው እኔም የምስማማበት ነው። የማንነት ቀውስ እንደ ሳጅን በረከት ያለባቸው አማራን ደግሞ ሌላ 43 ዓመት ለመቀብር የተነሳ መንፈስ ነው። አሁን ወጣቱ ትውልድ በጅ የሚልም አይደለም ጥሏቸውም ሄዷልም። አንሱ እዛው የዛሬ 43 ዓመት ላይ እንደ ኩሬ ውሃ ረግተው ይቀመጡ።

ሌላው የቅማንት ቀውስን በሚመለከትም ገናና የሚባሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሽባ አድርጎ ያስቀራቸውም ይሄው የጋብቻ ጉዳይ ነው። ለዚህ የወያኔ ሃርነት ትግራይ እና የሻብያ አባላት አሳምረው ሚናቸውን ትናንትም ዛሬም እዬተወጡ ነው። ጀግኖች ናቸው አብሶ ሴቶች። ከቁንጮ ላይ ቁብ ይላሉ ድርቡን ተልዕኳቸውን በትጋት እና በታታታሪነት ይከውናሉ። ስለዚህ ልጅ ሄኖክ የሽጥላ ያልከው በተወሰነ ደረጃ ትክክል ነው በአንጻራዊነት ይስማማኛል።

ሁለተኛው ያነሳው ሥርዓት አልበኝነትን የአማራ ወጣቶች ከመጀመሪያ ካልተማሩ ነገ የሚገጥማቸውን ሥርዓተኛ አልባ ድርጊቶን መቋቋም ያነሳቸዋል ነው የሚለን። ምን ዓይነት የተዘቀዘቀ ፍልስፍና ነው። ይቀጥል እና የዛሬ ሦስት ዓመት አቶ ጃዋር መሃመድ የሄደበት መንገድ አቃጥል፤ አንድድ፤ አፍርስ፤ ናደው፤ ድርምሰው ወዘተ ወዘተ ፍሬ አፍርቶለታል እና ያን እንደ ሮል ሞዴል መወስድ አለበት የአማራ ወጣት ነው የሚለው። ያው እነ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ከጃዋርውያን ተማሩ ብለው ወጣቱን እንደሰበሰቡለት ማለት ነው። 

ብቻ ደግነቱ  ለናሙና የጠቢቡ ቴወድሮስ ካሳሁን ኮንሰርት በባህርዳር እና የጠ/ ሚር አብይ አህመድ ድጋፍ ሰልፍ በባህርዳር የታዬው የአማራ ወላጅ ለጆቹን በምን መልክ በምን አገራዊ ሃላፊነት ኮትኮቶ እንደሚያሳድግ ዘመን አሻጋሪ ናሙናነቱን ታይቷል። የእኔ የታናሽ እህቴ አገሬ ቀሚስ ላይም „ ኢትዮጵያዊነት ክብሬ“ የሚል ፎቶ ልከውልኝ ነበር።

መቼም የአማራ ወላጆች ጠላታቸው ድፍት ይበል እና ሙተው ካለለቁ በስተቀር ሥርዓተ አልበኝነት በቤታቸው ኮትኩተው አያሳድጉም። እርግጥ ነው ይህን ሃላፊነት የሰጠው ለአዲሱ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ለአብን ነው። አብን በቁሙ መፍረስ ከፈለገው ይሄን ይፈጽም። ግን አብን የራሱ ዓላማ እና ግብ የለውንም? አብን የሚመራው የዲያስፖራው ፖለቲካ ነውን?

 ለዚህም ነው አብን ሲመሰረት ከውጭ ካለ ማናቸውም ድርጅት ይሁን ግለሰብ ጋር የመንፈስ እና የፋይናስ ጥገኛ እንዳይሆን አበክሬ ያስገነዘብኩት። ምከንያቱም ቅንጅት፤ ሰማያዊ ከሁለት የተገመሰው፤ አልያንሱ፤ አንድነት፤ ህብረት፤ የፈረሱት በዚህ በውጭ የድጋፍ ሰጪ ቻፕተር በሚባለው ጉድ ነው። አልፎ ተርፎ ማህበራዊ ኑሯችን ሁሉ እንዳልነበረ አድርጎ ያፈለሰው።

ልጅ ሄኖክ አብን ሲመክር በይፋ አይደለም ነው የሚለው በህቡ ነው ይህን ማድረግ ያለባችሁ፤ ወጣቶችን በሰውር ሥርአተ አልበኝነትን አስተመሩት ነው የሚለው። ሽብርተኛ አድርጋችሁ ኮትኩትኩታችሁ አሳድጉ ነው። በ አሸባሪነት መከከሰስ ሲቀር ቆጠቆጠው። አጀንዳ ሲጣፋ ይሄ ደግሞ ተገኜ።

ይሄ ሁለት መልክ አለው አብን ለጥቃት እንዲጋለጥ፤ በጥርጣሬ እንዲታይ፤ በራስ የመተማማኑ አቅሙ ሰላላ መላላ እንዲሆን፤ በስጋት ተውጦ ራዕዩን እንዳአሳካ፤ የውስጥ ሰላም እንዳይነረው፤ እና ሥርዓት አልበኝነት በተከሰተ ቁጥር አብን ያደራጃቸው ወጣቶች ናቸው እዬተባለ ገና በችግኙ አብን እንዲነቀል የሚያደርግ መርዝ ነው። ያው ስብስብ ብለው ደግሞ የአብ አመራሮች እስር ቤት ሲገቡ ያን ጊዜ ደግሞ ሌላ መልክ እና ቅርጽ ይመጣል።

ሁለተኛው ወጣቶች ትውልዳዊ ድርሻቸውን እንዳይወጡ፤ ሃላፊነት እንዳይሰማቸው፤ ማግስትን እንዳያስቡ፤ ተቆርቋሪነት እንዳይኖራቸው፤ ዕሴቶቻቸውን እያወደሙ፤ ራሳቸውን እንዲያሾልኩ፤ የባከነ ትውልድ እንዲ ፈጠረ እና በዛ በባከነ ትውልድ ውስጥ እራሰን የማስኮፈስ ከፍ ብሎ የመታዬት ምኞት እና ህልም ነው፤ የሄኖክ ማንፌሰቶ ሃውልት እንደማለት … ከዚህች ቀን ጀምሮ አማራ አካባቢ የሚነሳው ማንኛውም ዓይነት የግጭት ነገር „አብን“ ላይ ይሁን ነው የሚለው። ወላጆችም ሴቶችም ተማሪዎችም ይደራጁ በዚህ መስመር ይጓዙ ነው የሚለው። ምን ዓይነት ጭካኔ ነው።

እንደ ማስበው አሁን አማራ መሬት ላይ ይነሳል ተብሎ የታሰበው የቅማንት ጉዳይ መልክ ሲይዝ ቁጭት ይመስለኛል። ምክንያቱም አንጻራዊ ሰላም አማራ ክልል አለ ለዛውም ምንጃር ላይ ጥሩ ዜና የለም።  ብቻ በጎላ መልኩ  ልክ እንደ ሲዳሞው፤ እንደ ኢትዮ ሱማሌው፤ አሁን በሻሸመኔ እንደታየው ሰቅጣጭ ሰቀቀን አማራ መሬት ላይም ማዬት ወጣቱ ናፈቀው።

በዚህ የአብይ ሌጋሲ ደግሞ አማራ ክልል እንዲታመስ ተፈለገ። ምክንያቱም የአብይ ሌጋሲ በአማራ ላይ ያለው ትኩረት  ስስ ነው፤ ነገር ግን  አማራ ለአብይ ሌጋሲ የሰጠው ትኩረት የሥልጣኔ ከፍታ አለው። ይሄ ድርጁው የአማራ መንፈስ በትውፊቱ ውስጥ በዝልቀት የማካኑን  ስክነትን አመክንዮ ያሳያል። ህውከት ሊፈጥሩ ያሰቡትን ተባባራሪ ጫናዎች አማራ ተቋቁሞ ለውጡን የእኔ በማለት የመንፈስ ቤተኝነቱን በእዮባዊነት በተወሰነ ደረጃ  እያስኬደው ነው። ይሄ ደግሞ ለአጀንዳ አልቦሾች እረፍት አልሰጣቸውም። ስለዚህ ሌላ የአማራ ግጭት ናፈቀው፤ …  
ሰው አንዴት ሥርዓተ አልበኝነትን አስተምሩ ብሎ ይሰብካል? መበደል ብቻ ሳይሆን ሰው መሆንን መዳጣም ነው። ሥርዓተ አልበኝነት እንዴት ይናፍቃል።  ሰው እንዴት ጋጠ ወጥ ሁን ተብሎ ይመከራል? ሰው እንዴት ባለጌ ሁን ተብሎ ይወተወታል? እጅግ ይገርማል። ማቃጠል ምን ጥቅም አለው? መግደልስ ምን ጥቅም አለው? በቀልስ ምን ፋይዳ አለው? ጥላቻስ ምን ትርፍ አለው። ባዶ ነው ውጤታቸው። ስንት ሰው ነው የታማሚው ቁጥር? ስንት ሰው ነው እያበደ ያለው?

እኔ በዚህ ዙሪያ አብን መልስ ቢሰጥበት እና ግልጽ አቋሙን ማሳወቅ ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም ፍረስ ነው እውጃው። አሸባሪ ሁን ሌላ ምንም ትርጉም አይሰጠውም። በጣባጭ፤ ገርጭራጫ ሁን።
ይህ መርዛማ መንገድ አብን ነገ ደግሞ የፈለገው አይነት ብጥብጥ በተነሳ ቁጥር አንተ ነህ እዬተባለ ካሳበው ሳይደርስ ተስብሮ እንዲቀርም ነው። ሌላ አካባቢም ቃጠሎ በተነሳ ቁጥር አማራዎች ናቸው እዬተባለ ሌላ የዘር ጥፋትን መናፈቅ ነው። እንዴት አይነት አሰቃቂ ዜና ነው የሚሰማው።

እርግጥ ነው እኔ በአብን አመሰራረት እና ሂደት የራሴ የሆነ ሪዘርበሽን ቢኖረኝም መኖሩ ግን የተገባ መሆኑን አምናለሁኝ። ስለዚህም መጨረሻውን ማዬት ስለምሻ ተደናቅፎ እንዲቀር አልሻም። አሁን እኮ አክቲቢስትም አያስፈልገም ድርጅቱ ተደራጅቷል መዋቅር ደንብ እና ፕሮግራም አለው። ስለዚህ የቀረባቸው ደግሞ ገብቶ መበጥበጥ ሲያቅት ለነገ መንበር ዛሬ መርህ ነዳፊ መሆን ፈለጉ።

ብቻ ይሄ የአቤቱ ሄኖክ የሽጥላ አዲስ መመሪያ አዲስ መርሆ በሚመለከት ሌላ አዲስ የማስጠመጃ መንገድ ነው ለአማራ ወጣቶች። አማራ በግንቦት 7 ሥም ያዬው አልበቃ ብሎ አሁን ደግሞ አዲስ ወጥመድ ተዘጋጅቶለታል። ምን ዓይነት ዕጣ ፈንታ ነው። ምን ዓይነትስ መረገም ነው? ሰሞኑን የ አማራ ወጣቶች መደራጀት ከዲያስፖራ ፖለቲካኞች መዳፍ ዕውቀት ውጪ ነው። ጭምምጭምታው ሳይሰማ ነው ሙያ በልብ የተከወነው እና ገና ከመፈጠሩ ሌላ መጥለፊያ መንገድ ተሰናዳለት።

የአብይ ሌጋሲ የመናገር፤ የመጻፍ፤ የመሰብሰብ፤ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፤ የመደራጀት፤ የመፎካከር ነፃነት ስጥቷል ስለምን ነው  የአማራ ወጣት ለአመጽ ት/ ቤት የሚከፈትለት? ስለምን? ምን ቀረብኝ ብሎ? ጥያቄዎችን ለማስመለስ፤ በዘላቂም ትውልዱን በተሟላ ብሄራዊ ሃላፊነት ቀርፆ ለማሰደግ ሜዳውም ፈረሱም ተብሏል …
ማንም ሰው የትም አገር ከህግ በታች እንጂ ከህግ በላይ አይደለም። የወጣት ሄኖክ የሺጥላ አስተምህሮ ከህግ በላይ ሁኑ ነው የሚለው። ያልሰከነ የተበጠበጠ ትውልድ መናፈቅ። ወይ አለመታደል? መረገም ነው። እስር፤ ሞት፤ እንግልት እንዲህ ይናፍቃል? አይበቃም ወይ የሰተዛሬው? 

ነገ ደግሞ ገድላችሁ አቃጥሉ አይቀሬ ነው። ለመግደል አሰልጥኑት ወጣቱን ነው የሚለው። እንዴት አይነት መርዝ ነው። አማራ እኮ መሪ አለው መሬት ላይ። ከእንግዲህ አማራ የዲያስፖራ አመራር አያስፈልገውም። አርበኞቹ ተፈታዋል፤ አታጋዮቹ ከቅርቡ አሉ ከዬትኛውም የግል ይሁን የወል አመራር፤ ቀጥተኛ ይሁን ተዘዋዋሪ አመራር የሚቀበልበት መንገድ የለም - አማራ።

የፈለገ ሄዶ አገር ቤት መታገል ነው። አማራ የበላውን በልቶ፤ የጠጣውን ጠጥቶ። የከለከለ የለም። አቅሙ ወኔው ከኖረ። ማደራጀት የሳይበር ቢሮ አይደለም። ይህን ደግሞ ወጣት ሄኖክ የሺጥላ የገጠሯን ሽፍትነት ጀምሯት አንደ ነበር ነገርሮናል ከዚህ ቀደምም።

ሌላው ያነሳው የንጉሦች ንጉሥ የአጤ ሚኒሊክ ጉዳይ ነው። ይህም ለአማራ የህልውና ተጋድሎ አታጋይ መርህ አይደለም። አጤ ሚኒሊክ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝቦች ምልክት ናቸው። እኛ ብንተዋቸውም በዓለም አደበባይ ብዙ ነፍሳት አሏቸው። ፓን አፍሪካኒሶቶችም አጀንዳቸው ናቸው። ዓመት ይዞ እስከ አመት ይህን ይዞ መጓተትም የተገባ አይደለም።

ስሊዚህ የአማራ ተጋድሎ በተልእኮቹ ዙሪያ ብቻ ነው መሥራት የሚኖርበት። አቅም ማባከን የለበትም። ለዛሬ እና ለነገ አማራን ኢትዮጵያዊ  ዜጋ መሆኑን፤ አማራ አገርኛ መሆኑን፤ አማራ መኖሩን በሁሉም የህይወት ዘርፋት እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን አቅሙን አብቅሎ በአቅሙ ልክ ተፎካካሪ ሆኖ መውጣት እንጂ እራሱን አስሮ ተብትቦ ከሚያስቀረው አጀንዳ ውስጥ ተቀርቅሮ መዳመጫ መሆን አይገባውም።

 ብሄራዊ ፓርቲዎች ይሄን ይሥሩ፤ ካሻቸው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያም ዛሬ መንግሥት አላት። አልሰማም መሰል ወጣቱ ከተወሰነ ጊዜ በኋዋላ የሚኒሊክ ቤተ መንግሥት የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ ጥናት ላይ ስለመሆኑ …

ሌላው የአኖሌ ጉዳይ ነው። ደግሞ ደጋግሞ ነው የሚያነሰው። እንደ ቅድመ ሁኔታም መደራደሪያ ሲያቀርበው እሰማለሁኝ። ስለምን ከቻሉ በዬቤታቸው አያስገነቡትም።

ይሄ በውነቱ ወጣቱ በእጣ ፍንታው ላይ ትኩረት እንዳይኖረው መንፈሱን ማባክን ነው። እኔ ስለ ድንጋይ ሃውልት አይደለም የሚጨንቀኝ። የሚጨንቀኝ አሁን ያለው ነፍስ በድንጋይ ተውግሮ፤ ተገድሎ፤ ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ፤ እሬሳው በሚኪና መጎተቱ፤ በህይውት እያለ አይን የሚወጣበት፤ በህይወት እያለ የሚንኮላሽበት፤ አሰቃቂ ነገር ነው እኔ እንዲቆም እምተጋው።

ዛሬ ለመኖር ዋስትና የትም አካባቢ የለም። ስለዚህ ለአማራ አስፈላጊው ነገር የህግ ጥበቃ የሚያገኝበት እንጂ አኖሌ ሃውልት ለእኔ አጀንዳ ሆኖ አያውቅም። አኖሌ ሃውልቱ ያለው ይልቁንም በወጣት ሄኖክ የሺጥላ ጭንቅላት ውስጥ ነው። ተጋጭ፤ ተፋጭ፤ ተፋለጥ፤ ሰላም አትሁን፤ ሰላም አትስጥ፤ ከሰውነት ተራ ወጥተህ ጭካኔን ተማር እያለ ነው የሚያሰተምረው።

በውነቱ ይህ መንገድ አምነት ላለው አማራ ዲያቢሎሳዊ ነው። ማንነታችንም የሚያነድ። አማራነት እኮ እንዲህ አይደለም። ፈርሃ ፈጣሪ የሚባል ይህይወት መርህም ተመክሮም ያለን ማህበርሰብ ነን። በህግ አማላክ ቃሉ እንኳን ስንት ነገር አለው። 

„የበላሃ ልበልሃ“ በራሱ የዳኝነት ውሎ የነፍሳችን መደወሪያ እኮ ነው። ማነው እንግዳ ሲመጣ ቁጭ ብሎ የሚቀበለው? ማነውስ ታላቆች እያሉ ቀድሞ እጁን ሆነ እግሩን እሚታጠበው፤ ማነውስ ታታላቆች እያሉ ቀድሞ መንገድ የሚያቆርጠው? ተዘርዝሮ የማያልቅ ያልተጻፈ ድንጋጌ አለን። ያ ትውፊታችን፤ ያ ትሩፋታችን፤ ያ ቅርሳችን፤ ያ ቀለማችን ጠቅጥቁት ነው የሚለው ወጣት ሄኖክ የሺጥላ። 

የጥላቻው ሃውልት ያለው ከህሊና ውስጥ ነው። በውስጡ የጣለው ነገር አለ። ጥላችን ቢሆን መልካም በሆነ ነበር። እሱ ግን ጥላቻችን አብቅላችሁ አሳድጉ እያለ ነው። ይሄ የጥላቻ ሃውልት በውስጥ ባይኖር ሥርዓተ አልበኝነት ከልጅነት የአማራ ወጣቶች እዬተማሩ ይደጉ ተብሎ አይመከረም።

የትናንት ሌሎች ያበቀሉት ክፉ ነገር ውጦን በዬሰከንዱ መርዶ እያዳመጥን አሁን ደግሞ በጤናማ መንፈስ ውስጥ ያደጉ የአማራ ወጣቶች ወደ አውሬነት ተለወጡ የሚል ስብከት ጎንድ ተ/ሃይማኖት የሚያሰውስድ ነው። ለነገሩ እማዬ ከሌለች ማን ባለቤት ሲሆን። እሷ ነፍሷን አጸደ ገነት ያኑራት እንጂ ይህን ጉዷን ሳትሰማ ተሎ ወደ መላዕክታኑ ዘንድ ሄዳለች ብሎ አንድ ጊዜ አጫውቶናል።

የሆነ ሆኖ ይሄው ነው የነበረው የአማራ የግዞት ኑሮ ተቆርቋሪነት። ነጻነቱ ሲገኝ ደግሞ ያገኘኻውን ነጻነት በስርዓተ አልበኝነት ቅበረው፤ ትውልዱም መክኖ ይቅር። እግዚኦ! እርግማን።

 ምን ዓይነት ትውልድ ነው ይሄ አዲስ የሚባለው። ምን በሽታ ነው? ጭካኔ፤ አረመኔነት፤ ለህግ አለመገዛት ልጆች ተምረው ይደጉ ተብሎ ይመከራልን? ምን ተጠቀሙ ጃዋርውያን? የእለቱ ጭብጨባ እና ቻቻታ እንደ ሆነ የሳሙና አረፋት ነው። በዬአንዳንዱ ደቂቃ የግል ሰብዕናቸውን እያቃጠሉት እያነደዱት ነው። ማን ከእነሱ ጋር ይዛመዳል? የወዳጃል? ማድመጥ በራሱ ከሃጢያት ቁጥር ነው።

በፈረስ ሰብዕና ነው አሁን ያሉት ጃዋርውያን። ያን ያህል ተሸክሟቸው አሽኮኮ አድርጓቸው የሰነበተው አጀብ እኮ እንዳልኩት ቅጽበቶች ቅጽበት ለመሆን 30 ቀን አልፈጀባቸውም። ያ የሚሊዬንም አዳራሽ ክብር እና ልዕልና ባክኗል። ምክንያትም ነፍሱ ከእሱ ጋር ያለ ሰው ግራጫማ ሰብዕና ብዙም ሳይጠብቅ ዛሬ የሆነው ይሄው ነው …
ብፈልግ ኦሮሚያን ከአራት ወር በፊት መገንጠል እችል ነበር” “ዛሬም ብፈልግ ኦሮሚያን እገነጥላለሁጃዋር መሀመድ

ሠዎች ዛሬ በሻሸመኔ የዱር አራዊት ሆነዋል! (ሐይሉ አባይ ተገኝ)


በዚህ ዓመት እነ ዶር ለማ መግርሳ ሠራነው ያሉት የአንድነት ግንብ ይሄው ተደርምሶ እነሱንም ሊደረምስ እያጉረመረመ ነው። እስከ አሁን ማናቸውም መረጃ ለምዕራባውያን ይደርሳል። እዛው ውስጥ አሏቸው ኤጀንቶቻቸው። „አገር የመምራት አቅም የላችሁም“ ልብ ይሏል።
ይሄን መሰል ውርዴት  በአማራ ደግሞ ደርሶ ማየት ሽው አለው አቶ ሄኖከን የሺጥላ። ስለምን? አማራ መሬትስ የባጀበት አሰቃቂ ነገር አልበቃውም እና ይከል ወጣቶቹ በሥርዐተ አልበኝነት ይጎዙ እና ያቃጣሉ፤ ያንድዱ፤ ይደርምሱ፤ ከቻሉም የቻሉትን ሁሉ ማድርግ የሚያስችል ስልጠና ተቋም ክፈትላቸው አብን ነው የሚለው። 

ሥርዓተ አልበኝነት ነው ዓራት ዓይናማው መንገድ በዚህ ነው መከበር ዕውቅና እምታገኘው ነው የሚባለው አብን። ልክ ባለፈው ሰሞን ሰላማዊው የደቡብ ክልል በሳይበር ቅስቀሳ እንደሆነው ዓይነት … 800 ሺህ ህዝብ ተፈናቅሎ ማዬት ደግሞ ሽው ትዝ አለው። ማህከነ!
ከእንዴት ዓይነት ቤተስብ ሰው እንደሚያድግ አይገባኝም። እኔ ሳድግ እርግብ ስትሞት ከጣሪያ ወደ ታች ስትወድቅ በሥነ - ሥርዓት  አልቀሰን በልጅነት እንቀብራት ነበር። ዛሬ ሰው ስለሚባለው ታላቅ ክቡር ነገር ምናችን አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን እኛም ሟች መሆናችን ልናገናዝብ አልቻልነም።

የሚያስደስትን ትውልድ ሰላሙን አጥቶ በስጋት እና በሽብር፤ በህውከት እና ሰላም በማጣት ባክኖ ሲቀር ማዬት ነው። የራሳችን ኑሮ አደላድለን፤ ልጆቻችን እያስተማርን ነው ሌላው ተማግዶ ሌላው ነዶ ማዬት የሚናፍቀን። ለዛውም ዛሬ? ውጭ ያለው የፖለቲካ ድርጅት፤ የሃይማኖት አባቶች አገር ቤት በሚገቡበት ሰዓት። ምን ይሁን አጀንዳ ጠፋ ተንጠፈጠፈ …

በዬሁኔታው ጭካኔ፤ አረመኔነት፤ አወሬነት፤ ጭራቅነት … እርግማን>>፡
ማስተዋል ያለበት ጉዳይ ዛሬ የሚዛራው መርዝ ነገን አሳርሮ እንደሚያስቀር መታወቅ አለበት። „ሰው የዘራውን ነው የሚያጭደው“ እንዴት ያለ መርዛማ ጉድ ነው።  አብን ተግቶ መስራት ያለበት ጉዳይ ለሳይበር መርዝ ወጣቶችን እንዳይበክል መትጋት አላባቸው። የአማራ ወላጆችም እንዲሁ። ልጆች ነገን ለመግደል የሚያስችላቸውን ህግ አልባነት ተምረው ይደጉ ነው የሚለው። እንዴት ነው ሰው ሰውነቱን እያፈረሰው እኮ ነው ያለው። ነፃነት የሚባለው ለዚህ ከሆነ ባፍንጫዬ ይውጣ … መደራጀት ለዚህ ከሆነም በ አፍንጫዬ ይውጣ። የ27 ዓመቱ መርዝ መንቀያ ጠፍቶ መከራ እዬታዬ ሌላ መርዝ ደግሞ በገፍ በዬቤቱ ይመረት ነው የሚባለው። አንድ መርዝ ነው ይህን ሁሉ ማዕት ያመጠባን።

በዚህ አያያዝ እንዴት ሞት ሊቆም ይችላል? ሞት ረብሻ ብጥብጥ ግድያ ደም መጋባት የሚናፈቀው ትውልድ? ስንት ንጉሥ ነው ኢትዮጵያ ያለት? ተበጠበጥን!

ጌታ ሆይ በምህረት ዓይንህ እዬን!

የኔዎቹ መተኛት አልቻልኩም። ታዩት አላችሁ አሁን በእኛ እኮ ከሌሊቱ አስር  ሰ ዓት ተኩል ነው። እንዴት ይተኛል ይሄው ጉድ ተደምጦ።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።