የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

 

እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላም መጣችሁልኝ።

„አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኽኝ?

እኔን ከማዳን ከጩኽቴ ቃል ሩቅ ነህ።

አምላኬ በቀን ወደ አንተ እጣራለሁ አልመለስህልኝም፤

በሌሊት እንኳን እረፍት የለኝም።“

(መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 21 ከቁጥር 1 እስከ 3)

ሥርጉተ©ሥላሴ

Sergute©Selassie

03.02.2021

· እኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

 

አላዛሯ ኢትዮጵያ እና ልጆቿ እንዴት እዬሆኑ ይሆን አዋዋሉ አስተዳደሩ?? እንደምን እዬሆንሽ ነው እማ! የእኔ ልዕልተይ!

እናንተስ ማህበረ ንጹኃና ቅኖቹ የብራናዬ ታዳሜዎች እንዴት ናችሁ? ስለጤንነታችሁ፤ ስለሰላማችሁ አስባለሁኝ።

እናንተ ለእኔ የህሊናዬ ቤተ - መቅደሶች ናችሁ እና። ይህን ስላችሁ ከንቱ ውዳሴ ይመስላችሁ ይሆናል። እመኑኝ ብዬ አልሞግትም።

ጥሞና ላለው ሰብዕና እኔን እኔ አድርገው የሚመሩኝ የህይወት መርሆቼን አቤቱ ጉግል፤ ፊታውራሪ ዩቱብ ቢጠዬቅ ይመልስዋል። ዛሬ መስካሪ አለን። ትናንት ምን ዛሬ ምን እንደሆን።

በልጅነት የሚያውቁኝም በዛው ልክ ስለመሆኔ ያውቃሉ። እራሴን አታልዬ ለመኖር አልተፈጠርኩበትም።

እምጽፈው እራሴ የሆንኩትን ነው። እኔ እኔን መሆን ከተሳነው እኔ ለእኔ በተሰጠው የነፃነት ልክ መቆም ካልቻለ እኔ እኔን ማሰናበት ይኖርበታል። ይህ ደግሞ አይፈቀድለትም። ይህ መርሄ ነው።

·      ሃማ ባለቀለሙ ሃሳብ?

ሃሳብ ሰላም ይሻል። ሃሳብ ፍቅር ይሻል። ሃሳብ አትኩሮት ይሻል። ሃሳብ እንክብካቤ ይሻል። ሃሳብ ሰው ይሻል። ሙሉሰው። ምራቁን የዋጠ። ስለዚህም ጊዜ መስጠት - ማድመጥ - አክብሮ ማወያዬት - ማሰከን ያስፈልጋል። ማንን? የንጉሶች ንጉሥን አጤ ሃሳብን።

ሃሳብ አልባ መኖር የለም። ሃሳብ አልባ ዕምነት የለም። ሃሳብ አልባ ፍልስፍና የለም። ሃሳብ አልባ ዕውቀት የለም። ሃሳብ አልባ ማግስት የለም። ሃሳብ አልባ ሥልጣኔ የለም። ሃሳብ አልባ ጉልቻም ቤተሰብም የለም።

ለፕላኔታችን አሳብ አልባ መኖር ውሃ አልባ ሰው የመኖር ያህል ነው። ሃሳብ ለፕላኔታችን ደሟ ነው። ፕላዝማውም። ሃሳብ ውሃ ነው። ቀለሙም ውሃማ ነው። ሃሳብ ቀና ይሆን ዘንድ ቀና ሰብዕናን ይጠይቃል። አዲስ ቀንን አምጦ እንዲወልድ። ሃሳብ ደግ ፈር እንዲኖረው ደግ ማህንዲስ ይሻል።

ሃሳብ የኖህ መርከብ ሆኖ ያሻግር ዘንድም ምራቁን የዋጠ ካፒቴን ይጠይቃል። ለዚህ ፏ ያለ ጎዳና ፈቃዱም፤ ዝግጁነቱ አለን ወይ የጥያቄ ምልክት።

·      ግ ሃሳብ ኮንፓስም ካንፓስም ነው።

ደግ ሃሳብ እራሱ ማህንዲስም ነው። ደግ ሃሳብ ኮንፓስም ነው። ደግ ሃሳብ ካንፓስም ነው። ፍቅርም ኮንፓስ ነው። ፍቅርም ካንፓስ ነው። ፍቅር በሃሳብ ውስጥ ይገኛል። ሃሳብም በፍቅር ውስጥ ይገኛል። ሃሳብን ጠማዳ ያለደረጉ ሰዎች ጥሩ አፍቃሪዎችም ናቸው።

ግልጽም ቀጥተኛ ናቸው። ለትውልድ ይሆኑ ዘንድ ፈልጎ ማግኜት የእኛ ተግባር ይሆናል። ማግኜት ብቻ በቂ አይሆንም። በዘመቻ ማስበርገጉንም ማክሰም ይኖርበናል። አቃቂር ማውጣቱንም እንዲሁ።

ቋሚ ሃሳብ ያለው ሰው ደፋር ነው። ድንግል አዎንታዊ ሃሳብ ብጹዑ ጎዳና ነው። ግን ጎዳናው ስኬታማ - ለምለም - ሰብላማ ይሆን ዘንድ የተጠረገ ልቦና እና ጥሩ አድማጭነት ይሻል።

ያ የተጠረገ ልቦና ተፈጥሯዊነት ነው። ተፈጥሮዊነት ከጭምት ሰብዕና ጋራ ተዋህደው ሃሳብ ጸንሰው ሲወልዱ ትውልድ ይድናል። ይህን ትምህርተ ጎዳና ልንለው እንችላለን። ወይንም የኔታ ጎዳና። ሐዋርያ ነዋ! እራሱን በተፈጥሮው ልክ የቀዬሰ ….

ይህ ካልተገኜ ፍልሰት ይሆናል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ የማዬው ይህን ነው። ፍልሰት። አድሮ ጥጃነትም። ጎዳናውን የሳተ ባቡር ጎራዳ ነው።

ህሊና ለመልካምነት ይትጋ። ሁሉም ላፒስ ይግዛ። እራሱን የሚያርምበት። ጠፍተናል። ግን መጥፋታችን አልታወቀንም። የጠፋነው ሁላችን ላይሆን ይችላል። ግን ብዙዎቻችን ጠፍተናል። ስጋቴ እንዲህ እንደጠፋን እንደተጠፋፋንም እንዳንቀር ነው።

·      ዳኛው እራስን ማሸነፍ ነው።

ምራቅ ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ ከደም ጋር ማዋህድ። በብዙ ሳስተውል የለችም። ግልቢያው፣ ኳኳቴ የሰብዕና ግንባታ ግርግር ብቻ። ብትን አፍር አጥተን እንደ ኩርድሾች እንዳንሆን እሰጋለሁኝ። መሬቱ መኖሩ ብቻ ሳይሆን የነፃነት ቃናው መወዬቡ ያሳስበኛል። የሂደቱ ምት ጥምልምልነት፤ ጥምንም ማለትም ያስጨንቀኛል። ደጉ ሃሳብ ተደብቋል ወይ ተነፍጓል።    

የሰው ልጅ ቁጥር አንድ ጥያቄው ሊሆን የሚገባው የነፃነት ጉዳይ ነው። የሰው ልጅ ከሌላ ነፃነት ከሚጠብቅ ይልቅ እራሱን ቀድሞ ነፃ ያድርግ። ትችቱ፤ ወቀሳው፤ ነቀሳው ከራስ ሲደርስ አይደፈርም። ለምን ስትሉ ነፃነት ያለው ሰብዕና እንብዛም ስለሆነ። ነፃነኝ ብሎ ሲተነትን፤ ሲነገር ታዬዋለህ ግን እራሱን ማሰሩን አያዬውም ከምል አያስተውለውም። ማዬት እና ማስተዋል ልዩነት አላቸው።

 ማዬት ለገሃዳዊ አለም ለምናገኜው ክስተት ሁሉ ነገር እንደ ወረደ ሲሆን ማስተዋል ለመንፈሳዊው ዓለምም ለገሃዳዊው ዓለም የሚያገናኝ የሃሳብ መስመር ነው። ሰቅ። አዲስ ነገር ለማግኜት የሚጓጓገ የሚመኝ የሚመራመር። አትኩረተ - ሁለንትናዊነት። ማዬት ወደ ክህሎት ሲያድግ ነው ማስተዋል የሚሆነው በሥርጉትሻ ዕይታ።

·      ሉሰው።

ሙሉ ሰው ለመሆን ቂመኝነትን መጠዬፍ መቻል ይጠይቃል። ለዛ ደግሞ ነፃ ሆኖ ማሰብን ብቻ ሳይሆን ባገኙት ፊድባክ መሆን መቻልን ይጠይቃል። በቀልን እጠዬፋለሁ ሲልህ ታደምጣለህ። በቀል ሲነግሥ ግን ሲያቆላምጥ ታገኜዋለህ። ውስጥን ማጣት ያሳስባል። ውስጥን ማጣት እናዳይኖር በሌላው ዓይን ብቻ ሳይሆን በራስ ዓይን ውስጥ እራስን ማዬት ይገባል። ሽንገላ ከሸመገለ አገር ይጠፋል።

አንድ ሰው ከሌላ ሰው ጋር ሲወያይ ወይንም ሲያወያይ፤ ወይንም የጻፈውን ሲያነብ በዛ ሰው ያገኜው መልካም ነገር ምንድን ነው ብሎ እራሱን መጠዬቅ ይገባዋል። እኔስ የሌለኝ ምን ይሆን ብሎ ሚዛን ላይ መቀመት ይኖርበታል።

መልካሙን ነገር ማግኜት ብቻም ፋይዳ የለውም። እኔስ አለኝ ወይ ያ የመልካምነት ብቃት ብሎ መጠዬቅ ይገባል? ከሌለው ላፒስ ለመግዛት ሱቅ መሄድ ይኖርበታል።

ዛስ?

ቆሻሻውን አጽድቶ ያን መልካም አስተሳብ ለራስ መስኖ መጠቀም ይገባል። የሰው ልጅ በእህል እና በውሃ አይኖርም። የሰው ልጅ ህሊና በመስኖ መልማት አለበት። በመልካም ሃሳብ፤ በእውነት ላይ በጨመቱ የጥበብ ጭማቂዎች መስከን። መታደል!

ኢትዮጵያ ይልኃል። ግን የጠላውን ሰው አንተ እና አንቺ እያለ ሲያብጠለጥል ታገኜዋለህ። ኢትዮጵያ የአክብሮት መንበር ናት። እንደ ቀረቤታው የመጠሪያ የወል ሥም አለ። አቶ/ወሮ/ወት/ እታለም/ወንድምጋሼ/ወለላ/ እቴቴ/ ጋሼ ወዘተ … ይህን ጥሰህ ስለ ኢትዮጵያም ስለትውልድም አስባለሁ ብታለኝ አይሆንም። አላምንህም።

አክብረህ ጠርተህ አጉድሏል የምትለውን ውቀስ፤ አክብረህ ጠርተህ አጉድላለች የምትለውን ንቀስ። ይህን እንኳን መግራት ሳንችል ትውልድ፤ አደራ፤ ብሄራዊነት፤ ሰንደቅ ዓላማ፤ ህገ መንግሥት፤ አዲስ ሥርዓት ወዘተ ላይ መንጠልጠል ሳይፀነሱ የመወለድ ያህል የተፈጥሮ ዝበት ነው። አብሶ የሚዲያ ሰዎች እባካችሁ ከትውፊት ከትሩፋታችን አትውጡ። የስድብ ሆነ አቃሉ የማዬት ተርቲም ለትውልዱ ብክነት ዲዲቲ ነው።

መታበይን ተጠይፈህ አንተ በመታበይ ውስጥ መኖርህ ግን አይታይህም። እራስን ማረም - መረቅ - መቆንጠጥ - መገሰጽ ይቅደም። የጥሞና ጊዜም ይኑረን። ትዕዛዝ አይደለም። እህታዊ ዕይታ እንጂ።

 

እግዚአብሔር ይስጥልኝ።

መሸቢያ ማዕልት!

ኑሩልኝ ለእኔም ለዳንኤሏ ኢትዮጵያም። አሜን!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።