አይ No“ ልዩ አቅም ነው።
አይ No“ ልዩ አቅም ነው። ከሥርጉተ© ሥላሴ (Sergute©Sselassie) 04.03.2018 (ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ።) „ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሄር ምህረት የተናሳ ነው። ርህራሄው አያልቅምና።“ ሰቆቃው ኤርምያስ (ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፳፪) እስቲ ዛሬ ትንሽ ስለ «አይ» እናውጋ። ወግ ቢጤ። ሁልጊዜ የሰው ልጅ ሃሳቡ ተቀባይነት ሲያገኝ እጅግ ደስተኛ እና ሳቂተኛ ይሆናል። „እሺ“ ከሁሉም በላይ የመልካም ነገር ማህጸን ነው እና። እንደ እኔ ዕይታ ደግሞ „አይ“ ማለትም ተወዳጅ ሰብዕና ነው። ብልጽግናው „በማዬት“ አድማጭነት ስለሚለካ። እንደዚህ ዓይነት ሰብዕና ፊት ለፊት ሲሞግተን ደስ ሊለን ይገባል። „እሺን“ ሆነ „ይሁንን“ ስንቀበል ደስ እንደሚለን ሁሉ „አይ“ „አይቻልም“ „አልተቀበልኩትም“ ስንባልም ከውስጣችን ደስ ሊለን ይገባል። ምክንያቱም „በአይሆንም“ ውስጥም ሌላ የአቅም ቅምጥ ሃብት አለና። አንደኛ የሰው ልጅ እንደ ፈጣሪ እራሱን ከሚያይበት ወንበር ዝቅ ብሎ ተፈጣሪ መሆኑን ያውቅበታል። የሰው ልጅ የአቅሙን፤ የመብቱን ጣሪያና ግድግዳ ማወቅ በቻለ ቁጥር የሰውነቱን የማስተዋል ፍሬ ነገር ያያል። በሌላ በኩል የ„አይ“ ቤተሰቦች መንፈስ „ከእሺ“ የበለጡና የተሻሉ ሲሆኑ፤ መሬት ላይ ሙሉ የሆነ ስብዕናን የተላበሱ መንፈሶች ጥሪታቸው እንዲሆን የማድረግ ባለ ልዩ አቅም ናቸው። ሰው ከቁሳዊ ነገሮች አምልኮት ጋር ባበደበት በዚህ ዘመን „አይን“ የሚደፍሩ የህሊና ዓይን ያላቸው ብቻ ናቸው። ምከንያቱም ጥልቅ የተፈጠሮ ሚስጢራት መገለጫዎች „ከማዬት“ ማዬት የተገኙ ናቸው እና። ምንም ነገር በምድር ላይ ግኝቱ „በማዬት“ ውስጥ የተፈጠረ ነው። „ማዬት“ ትልቅ ጸጋ ነው። „ማዬት“ ትልቅ ጸጋ የሚሆነው ከውስጥ በአትኩሮት ከተቀመመ ብቻ ነው።...