#የደም ግብር ዘረፋ በአስቸኳይ ይቁም! 14.12.2021
#ይድረስ ለዘኃበሻ ዋና አዘጋጅ ለጋዜጠኛ ሄኖክ አለማዬሁ።
#"የኢትዮጵያ ኃይሎች" እያልክ የምትዘግበው ከኡራኖስ ተላከልህን?
#የደም ግብር ዘረፋ በአስቸኳይ ይቁም!
"የኢትዮጵያ ኃይሎች" እያልክ የምትሰራው ዜና ታሪክን ጥቅርሻ የሚያለብስ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
አንተን የማዘዝ አቅሙ ባይኖረኝም የታሪክ ሊቀ - ሊቃውንት ሊሞግቱህ እንደሚገባ ግን አምናለሁ።
ስለምን ዝም እንዳሉህ ይገርመኛል። ታሪክን ነጭ ባህርዛፍ አልብሰህ መቃብር ውስጥ አታስተኛ። እረፍ!
ሃግ ልትባል ይገባል። ዜና ፕሮፖጋንዳ አይደለምና። ወይንም #የድብቅ የፖለቲካ ቅምጥ ፍላጎት ሱቅ በደረቴ።
ያን ሁሉ ዘመን የደከምክበትን የተጋድሎ ዘመን ስለምን በወሳንሳ ለቆመ ሥርዓት ለማበርከት እንደተነሳህ አይገባኝም። ፎቅ? የአንድ አውሎ የቅፅበት ጉዳይ ነው።
ከዕድሜህ በላይ አከብርህ የነበረው የቁም ነገርህ ዝልቀት ነበር። ብዙ ሠርተህ አግዘህ ነበር። የጥንቱ ሄኒ ናፍቆኛል። የዛሬው ግን ሃራም እዬሆነ ነው።
ዛሬ ግን አንተ አይደለህም። አንተ እንድትሆን እሻለሁ። ይህን ሁሉ ግብር ለሚከፍል የአማራ ህዝብ ሥሙን ለመጥራት ስለምን ፈራህ? #ቅራቅር ላይ ብቻውን ባይመከት ይህ ሁሉ ዕድል ይኖር ነበርን? መልስ አለህን?
ቀደም ባለው ጊዜ የአማራን የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ግንቦት 7 "የነፃነት ኃይል" እያለ ሲያላግጥ የአንተ ድህረ ገፅ እኛን በማሳተፍ ግንቦት 7 ስንሞግተው እንደነበር ታስታውሳለህ። አሁን አንተ #ተነከርክበት።
የት አምጥተህ ነው "የኢትዮጵያ ኃይል" የምትለው?
የሚዋደቀው።
1) የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት፣ አዬር ኃይል ጨምሮ ለዛውም በአፋር ክልል በጠነከረ ሁኔታ። በአማራ ክልል "ሸሽ አፈግፍግ" እዬተባለ።
2) የአማራ ልዩ ኃይል፣ የአማራ ሚሊሻ፣ የአማራ ፋኖ፣ የአማራ ወጣቶች። ካለምንም ሎጅስቲክስ፣ ካለተጨማሪ በጀት፣ በራሱ ትጥቅ፣ ስንቅ እና ጠበንጃ። ካለ ተጨማሪ በጀት።
3) የአፋር ልዩ ኃይል፣ የአፋር ሚሊሻ፣ የአፋር ወጣቶች።
4) የአማራ እና የአፋር አገር ውስጥም ውጪም የሚኖረው ህዝባቸው ብቻ ነው ግማዱን ዓመት ሙሉ የተሸከሙት። አትቀልድ። ቧልቱን አቁም።
ለዚህ የተበቃውም ግርባው ብአዴን በሰጠው ሙሉ ድምፅ በሙሉ አቅሙ 4 ዓመት ሙሉ በርደኑን ሙርቅርቃችሁን አሽኮኮ ስላደረገም ነው።
እማናውቀው ያለ አይምሰልህ። ፖለቲካን ተምረን፣ ሠርተንበታል። ጫካውንም ወህኒቤቱንም እናውቀዋለን። መምራቱንም ማደራጀቱም በእኛ ያለፈ ነው። ዝምታችን ያ ጠቀራ ድርጅት ህወሃት አቅም እንዳያገኝ ብቻ ነው።
የአማራ ህዝብ ተጋድሎ ከእስከ አይባልም። በኢትዮጵያ የነፃነት ተጋድሎ አንገታችን ቀና ብሎ የሚያስኬድ የወልም፣ የተናጠልም ተጋድሎ አድርገናል። ለዛውም ግሎባል። ባናርስ እናጣምዳለን።
የአማራ ሚሊሻ፣ የአማራ ፋኖ፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ የአማራ ወጣቶች፣ መላ የአማራ ህዝብ ገድል ፈፅመዋል። አትሸሹት። አትሻሙት። አትቅበሩት።
ይህን ሃቅ ድጠህ፣ ይህን ሃቅ ጨፍልቀህ፣ ይህን ኃይል ጠቅጥቅህ #የትግራይ ህዝባዊ ሠራዊትም አብሮ እንደሚሳተፍ አድርገህ "ኢትዮጵያዊ ኃይል" እያልክ አማራ ላለማለት ስትጨነቅ፣ ስትጠበብ አይኃለሁ። ከመቸ ወዲህ ያመጣኽው ሥነ ምግባር እንደሆነ ፍፁም አላውቅልህም።
#ይህ የታሪክ ዘረፋ ነው። ንፁህ ዲስክርምኔሽን ነው። ይህ ፍፁም የሆነ የትውፊት ወረራ እና አስምሌሽንም ነው።
ብዙ ሰው አሁን ከሆነ ሲበሳጭብህ የቀደመውን ተጋድሎ እዩ እያልኩ ስማገድልህ ኑሬያለሁኝ።
አሁን ግን ግልምት ነው ያልከኝ። ትንሽ ይሉኝታ የሚባል ነገር እንዳለ፣ ትውፊታችንም እንደሆነ ስለምን አታስተውልም? ኢትዮጵያዊነትም እኮ ይህንንም መቀበል ነው።
የአማራ ልዩ ኃይል፣ የአማራ ፋኖ፣ የአማራ ሚሊሻ፣ የአማራ ወጣቶች፣ የአማራ ህዝብ ለማለት አቅም አጣህ። ይኮሰኩስኃል። ለምን?
ጋዜጠኛ አበበ በለው በዲሲ ያዘጋጀውን ሰላማዊ ሰልፍ፣ ልጅ ተድላ መላኩ ተግኝቶ ያደረገው ንግግር ዕፁብ ድንቅ ነበር። ያን አገለልከው። ያን ለመዘገብ አቅም አልነበረህም። ታሳዝናለህ። ቀንህ ተሰበረ። አሻገትከው።
የዘንድሮን የመስቀል በዓል አከባበር የማሟያ ዜና አድርገህ መጀመሪያ ላይ አቅርበኽው ነበር። የክብርህን አቅም አጠወለግከው።
በኋላ ይሉኝታ ይዞህ ሙሉውን አቀረብከው። ጥቂት ቀን ሳይቆይ ፔጅህ እክል ገጠመው። በአንደበትህ ሳብስክራይብ ልመና ገባህ። የላይኛውን ፍራ። የሰውን ትተህ።
እኛንም ቤተኞችህንም አድምጥ። ቢያንስ በተመክሮም በዕድሜም እንበልጥኃለን። በሽልንግ ባንገናኝ። በዘመንተኝነት ባንቀራረብ።
በዲሲው የአዲስ ድምፅ የአማራ ሰላማዊ ሰልፍ የዘገባ ግለትህ ያልታዘብኩህ ይመስልኃልን?
የድሮው ሰብዕናህ ይሻልኃል። #ኢትዮጵያዊነት የቀን ሰውነት አይደለምና። ጆኖሳይድን መተባበር ጋዜጠኝነትን ያስቀጥላል ብለህስ ታምናለህ? መልሰው?
#ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን …
የአማራ ህዝብ ሆነ የአፋር ህዝብ በርደኑን ተሸክመው ፎቶ ቢዲዮ ስትደረድር የምትውለው የማንን እንደሆነ እያዬንልህ ነው። ለስጋው አደላ ሆነኃል። እንቅጩ ይህ ነው።
ህወሃትን በምትቀጠቅጠው ልክ አንተ በዛው ልክ እንደ ተነከርክ አልታወቀህም። እንደ አንድ የዘሐበሻ ቋሚ አምደኛ የምነግርህ #ተዘፍቀህበታል። ዕውነቱ ይህ ነው። ሁሉም ጊዜ ሲሰጠው ብሶ ከች ይላል። ያዬነው ይህን ነው።
ይህ "የኢትዮጵያ ኃይል" የምትለውን የአስምሌሽን ታፔላህን ትተህ ደም እዬገበረ ያለውን የህዝብ ልጅ ዋጋ ዕውቅና ሰጥተህ በሥሙ ጥራው። "አማራ" በል። "አፋር" በል። ዘመን የሰጠው ካልሆነብህ።
አይምሰልህ ያ እንዳለፈው ሁሉ ይህም ያልፋል፣ ለዛውም የኦነግ ሙርቅርቅ፣ ዝልግልግ የፖለቲካ አቅም ……ነዳላ ………
እግዚአብሔር ይስጥልኝ
አጤ
ዘሐበሻ ፋኖን ዛሬ ላይ ሎጎው አድርጓል። መልካም ርምጃ ነው። ቤቴም ስለነበር መደመሩን በዚህ መልክ ወቃቅሼው
ነበር። ለአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ዘሃበሻ፤ ሳተናው እና ህብር በመደበኛ በትጋት የሠሩ ሚዲያወች
ናቸው። እንመሰክራለን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
14/12/2021
ኢትዮጵያዊነት የማስታወቂያ ሰሌዳ አይደለም!
የደም ግብር ዘረፋ በአስቸኳይ ይቁም!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ