#ሰዋዊነት ከምድራዊ ሥልጣን እና ክብር በላይ ነው! #ሰባዕዊነት ከምድራዊ ልዕልና ልቅና በላይ ነው ህገ መንግሥቱ እዮራዊ ነውና! 14.12.2021
ኢትዮጵያ ያላችሁ የሰባዕዊ መብት ቀዳማይ ሞጋች ካፒቴኖች ባልደረባችሁን ሄዳችሁ አይታችኋት ይሆን? አቤቱታዬንስ የት አደረሳችሁት? መልስ እሻለሁ።
#ይድረስ ለማከብረወት ለዶር ዳንኤል በቀለ የሰባዕዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር።
አዲስ አበባ፣
#ይድረስ ለማከብረወት አቶ ያሬድ ኃይለማርያም የሰባዕዊ መብት ተሟጋች
ካሉበት።
#ይድረስ ለማከብርህ አቶ ኦባንግ ሜቶ የሰባዕዊ መብት ተሟጋች
አዲስ አበባ።
ጉዳዩ ስለ ሊቀ ትጉኃን ጋዜጠኛ እና የሰባዕዊ መብት ተሟጋች ባልደረባችሁ ወሮ መዓዛ መሐመድ ይመለከታል።
ስለ ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ በአካል ስለምታውቋት ብዙ ድካም አያስፈልገኝም። የሁላችን በርደን የተሸከመች ብቁ ናት። እኔ እራሴ የእሷ መንፈስ ልቆ ከወጣ ጀምሮ ያለኝ የውስጥ መረጋጋት ፈጣሪ ነው የሚያውቀው።
የውስጤ፣ የልቤ የሆነች የተግባር ልዕልቴ ናት። የአይዟችሁ ንግሥት ናት። የሃሳብ ፍሰቷ የድፍረት ልኳ፣ የግልፅነት አቅሟ እራሴን ያገኜሁባት፣ ያዬሁባት ህይወቴ ናት። በወጣትነቴ እኔ እሷን ነበርኩኝ።
ለዚህም ነው እረፍት በሚያስፈልገኝ ወቅት እስሯን ስሰማ ደንግጬ ፌስቡክ የገባሁት። እርግጥ ነው የጋዜጠኛ ታምራት ነገራን ስሰማ ደንግጬ ነበር።
የእሷ ከሴትነቷ አንፃር፣ ወጣትነቷ ታክሎ ከምትወስደው መጠነ ሰፊ የኃላፊነት እና የተጠያቂነት አድማስ አኳያ እጅግ እጅግ አስደንጋጭ ነበር እስሯ። እረፍት አይሰጥም።
አይዟችሁን የሸሸው ኦህዲድ መራሹ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ አንድ ቀን ለዚህ ሁሉ ሺህ ህልፈት ብሔራዊ ሰንደቅ ዝቅ አድርጎ ማውለብለብ የተሳነው ከንቱ ካቢኔ እሷ እና ቲሟ ግን ብዙ በጣም ብዙ ድንቅ ደግ ተግባራትን ፈፅመዋል። ያ ከንቱ ስብስብ አንድ ቀን ብሔራዊ የሐዘን ቀን ዓውጆ አያውቅም።
የሆነ ሆኖ ደግንትን ማሰር፣ እርህርኃናን ማሰር፣ እናትነትን ማሰር ከእዮር ቅጣት ያመጣል። ያ የማይቻል ይሆናል።
የዛሬው አቤቱታዬ እስካሁን ለአቤቱታዬ የሠራችሁትን ሥራ ለመጠዬቅ ነው።
ምን ሠራችሁ? ጥያቄዬን የት አደረሳችሁት? እንደ ማበሻ ጨርቅ የትሜና ወረረወራችሁትን ወይንስ ባሊህ አላችሁት? ያው አላችሁ የምለው እናንተን ብቻ ስለሆነ ነው። ገበርዲን እማ ሞልቷል።
#የማከብረወት ዶር ዳንኤል በቀለ ሆይ!
ከእርሰወ ጋር በነበራት ቃለ ምልልስ እረጅም ፁሁፍ ፅፌ ነበር። ያን ይሰቡት። ሄደው ሊጠይቋት ይገባል ስል በትህትና አሳስበወታለሁ። የፆታ ጥቃት እንዳይደርስባት፣ እንግልት እንዳይደርስባት ጠበቃዋ ሊሆኑላት ይገባል።
ቀድሞ ነገር ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ምን ሲሉ ይህን ድፍረት እንደፈፀሙት ግርም ብሎኛል። ገፊ ኃይል እንደ አለ ብረዳም። ልትበረታታ፣ ልትታገዝ ይገባል። የሃሳብ ልዩነቱ በዲያሎግ ይፈታል።
ጦርነቱ፣ ይህ ሁሉ ቀውስ የማንን ጎፈሬ ለማበጠር ይሆን? "ሥልጣናችን ከተነካ በቀን 100 ሺህ ሰው እናርዳለን ያሉት እራሳቸው አይደሉምን።
ከእንግዲህ ከእነሱ ጋር ብሰራ ብሞት ይሻለኛል አላሉንም፣ እኛ ዝሆን ነን እንበላለን፣ እንሰብራለን እንቀረጥፋለን አላሉንም፣ ለጃራ መረጃ አቀብል ነበር አላሉምን፤ ከባልደራስ ጋር ጦርነት እንገባለን አላሉምን፣ በልፅጉ ብለን ለምነን እንቢ ስላሉ አላሉምን" እሳቸውን ማን ይከሰስ?
ማን በህግ ፊት ይገትር? ጋዜጠኛ ማዕዛ መሐመድ እሳቸው አቅደው ለፈፀሙት ነገር ተጠያቂ የምትሆንበት ምክንያት ምንድን ነው።
መቀሌ በመረጠ በሳምንቱ ፌድራል ምርጫ አወጄ፣ ምርጫ ባጠናቀቀ በሳምንቱ በስንት መስዋዕትነት የተያዘው መቀሌ ተለቀቀ። ይህ ለአንድ የሰባዕዊ መብት ተሟጋች ለህግ ባለሙያ ይጠፋዋልን? ዕውነት ይደፈር። ዕውነት ቀኑ አይሰበር።
#የማከብርህ አቶ ኦባንግ ሜቶ ሆይ!
አሁን ልትፈተን ነው ብቸኛዋ የተጎጂወች እናት፣ የዕንባ ዋናተኞች ተቆርቋሪ ታሰረች፣ ሂደህ ታያታለህ ወይንስ እንደ የቀድሞ አክባሪህ አሜሪካ ድረስ እንደ ጋብዝከው እስክንድር ዛሬ ካቴና ላይ ሲሆን ኢግኖር ታደርጋታለህ? እሷ የዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል አይደለችም።
እንደ አንተው ለዕንባ የቆመች ባተሌ ናት። ኢትዮጵያዊነት ይህን ፈተና ማለፍ መቻል አለበት ብዬ አስባለሁ።
#የማከብረወት አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ሆይ!
የእርስወ እና የእኔ ነገር የቅርብ ሩቆች ነን።
ኢትዮጵያ ካሉ ተቀራርባችሁ ትሰሩ ስለነበር ጠበቃዋ ቢሆኑ ምርጫዬ ነው።
ኢትዮጵያ ካልሆኑ ቤተሰቧን አግኝተው ዕለት በለት ቢያገኙ። የኦህዴድ መራሹን መንግስትም ቢሞግቱ እና ለመፍትሄው መላ ቢሉ ጥሩ ነው። እነኝህ ነገሮች ብዙ ነገሮች ያበላሻሉ።
ለህውኃት አቅም ይጨምራሉ። በሙሉ አቅም መሥራታችን ስለማይቀር። እዬሠራሁም ስለሆነ። አንድ ሰው አላሰሩም።
ዕውነት ብነግረወት ዶር አብይ አህመድ ዓይነ ጠባብ ናቸው። የአዮ ልጅ አይደሉም። ኢትዮጵያ እኮ ሰፊ አገር ናት።
አንዲት ትጉህ፣ ታታሪ ከአማራ ማህፀን እና አብራክ የተገኜች ተፅዕኖ ፈጣሪ ሞጋች ጋዜጠኛን ማዬት አቅም አጡ። እኔ ለሳቸው የተገበርኩትን ሳስብ ባይፀፅተኝም አፍርበታለሁ።
የታጠቁ እደግድገው ያሉ እናቶችን አስተውሉ ማንኛችንም እናንተን ጨምሮ በቀያቸው ተገኞቶ አላፅናንም። የታጋች ልጆቻችን ወላጆች ናቸው። እሷ ግን አድርጋዋለች።
ታዲያ እና እናንተ አዲስ አበባ እሷን ሄዳችሁ በአካል መጠዬቅ ይሳናችሁ ይሆን?
ልመናዬ ሄዳችሁ ጠይቁልኝ ነኝ። ሰባዕዊነትን ጨፍላቂው ኦህዲዳዊውን አስተዳደር በምትግባቡት ዘይቤ ጠይቁልኝ ነው። ለይደር አትቅጠሩት። ብዙ ነፍሶች የእሷ ድምፅ ያስፈልጋቸዋል እና።
እሷ የሚሊዮን ድምፅ ናት። ለሚሊዮን ድምፅ ቁሙ። ሞልቶ ከሚፈሰው ዕንባ ጎን ለቆመች ብርቱ ወጣት ቅድሚያ ይሰጥ። እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
14/12/2021
ሰዋዊነት ከምድራዊ ክብርና ሥልጣን በላይ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ