14,12,2019 ራስን የማዬት ጉዳይ የተዘለለ ይመስለኛል። ጥሞና የመኖር ኦክስጅን ነው።
ራስን የማዬት ጉዳይ የተዘለለ ይመስለኛል።
ጥሞና የመኖር ኦክስጅን ነው።
ራስን የማዬት ጊዜ የቀደምት አገርን የማበጀት፣ የመምራት፣ የማሳደግ፣ የማሰልጠን ዓላማ የነበራቸው የፖለቲካ፣ የጥበብ፣ የሃይማኖት መሪዎች መለያ የመኖራቸውም ታላቅ ሚስጢር ነበር።
ጥሞና የራስን ህይወት ለመምራት እራሱ አስፈላጊ ጉዳይ ነው እንኳንስ ከ100 ሚሊዮን በላይ የሆነን ፍላጎትን አቻችሎ ለመምራት። ልክ እንደ ምግብ፣ መጠለያ፣ ከፈን ሁሉ። ጥሞና የመኖር ኦክስጅን ነው። ይህን ካጣ መኖር ድርቅ ይመታዋል። ዘመናችን በዚህ ምክንያት ድርቅ የመታው፣ መለመላውን የቀረ ግንድ ሆኗል። እግዚኦ።
እጅግ የሚገርሙ ብቻ ሳይሆን የሚከረፋ ነገሮችን አስተውላለሁኝ። በፖለቲካ ሊሂቃኑ፣ በማህበራዊ አንቂው፣ በልሳናት በሚዲያዎች አዘጋጅ እና አቀናባሪዎች፣ በኪነጥበብ ሰዎች፣ በሃይማኖት አባቶች ሳይቀር፣ ጊዜ ሰጥቷቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆኑትም ሁሉ የሚታዬው የኃላፊነት ቁርጠኝነት፣ ከራስ ጋር ለመታረቅ የዳገቱ ዳጥ መሰረታዊ ችግር እራስን ለማድመጥ፣ ለማረቅ የጥሞና ጊዜ ከመኖር ሰሌዳ መሰረዙ ይመስለኛል። በዚህም ምክንያት እንደ ፈረሰኛ ውኃ ሙላት ግልቢያ ብቻ ሆነ ነገር ዓለሙ። ውጤቱም የሳሙና አረፋ። ማህከነ።
አንዳንዱ ሰብዕናው ንግሥና ላይ፣ ሌላው አጥቢያ ደብሩ ላይ፣ ጥቂት የማይባለው ዞጉ ላይ፣ ብዙው አውራጃ ወረዳው ላይ፣ ያላነሰ ቁጥር ያለው በሙያው ውስጥ ተጠልሎ ወጀቡን ሲያዝ ውሎ ያድራል። በዚህ ማህል ትውልድ እና ተስፋ ዕብድ የዘራው አዝመራ ሆነ ዕጣ ፈንታው። ማረን።
ከ20/30 ዓመት በኋላ የአደራ ተረካቢው መዳረሻ የት ላይ ይሆን አድራሻው የሚል የተመጣጠነ ቀመር ቀማሪ ብልህነት እንዲህ ክው ብሎ የደረቀበት ምክንያት ሳስበው የጥሞና ጊዜ የሚባል ጉዳይ አሳቢ የለሽ ከመሆኑ የመነጨ ይመስለኛል።
የቅድመ አያቶቻችን ዛሬን ያስገኙበት ጥበብ ልቅናው ሆነ ልዕልናው ያለው እንደ እዬ እምነታቸው የጥሞና፣ የተደሞ፣ እራስን የመፈተሽ ጊዜ ስለነበራቸው ነበር።
ዛሬ የጥሞና ጊዜ የካሜራ ሞድ ህግ አስከባሪነት ነው። ዛሬ ለህዝብ ትሩፋት የሠሩ ብርቆች ሲወደሱ ቅጥያው አውራጃ ወረዳ ላይ ሲወርድ ይገለማል። ከማን ጋር በምን ሁኔታ ተግባብተን፣ ተጋብተን ወይንም አበልጅነት ተናስተን እንደኖርን ሳስበው ሳንተዋወቅ የምንኖር የአገር ልጆች መሆናችን ቁልጭ ብሎ ይከሰትልኛል።
አሁን ቲፎዞው ጅረቱ ቡፌ ሆኗል ከዚህ ውጥንቅጥ ዝንቅንቅ ዝብርቅ ዕሳቤ ጋር። ነገ ወይንም ማግሥት በዚህ ውስጥ ሲታሰብ ልቅና ወድቆ አምቻ ጋብቻ አምልኮተ መለኮት ወይንም አላህ ይሆናል። በውነት ያስፈራል። ይጨንቃልም።
ያለቀባቸው ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የኪነጥበብ ሰዎች፣ ዬማህበራዊ አንቂዎች፣ የኃይማኖት መሪዎች የሻገተ ዕሳቤን እንዲህ ከሚያስታምሙ ዞር ቢሉ የሚሻል ይመስለኛል። ለቀጣዩ ትውልድ የስክነት ግንባታ ሲባል።
የ60 ዓመቱ መከራ ላይበቃ አሁንም ይህ መከረኛ ትውልድ አደራውን ለመረከብ፣ ተረክቦም ለማስረከብ እንዳአረጋ ወተት ቅቀላ መንፈሱን እዬበጣጠሱ ፍዳውን የሚያስከፍሉት አብነት ነን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነን፣ መሪ ነን የሚሉት ሁሉ ወደ እራሳቸው ተመልሰው እራሳቸውን የሚያዩበት የጥሞና፣ የራስ ጊዜ ሊኖራቸው ይገባ ይመስለኛል። ጎሽቷል ነገር ዓለሙ ሁሉ።
ተዚህ ላይ እከሌ ተከሌ ብዬ ሥም ማንሳት አልሻም። ሁሉም ልቡ ያውቀዋል። የት ላይ ስሜቱ ስስ እንደሆነ። ሁሉም ያውቀዋል ብዕሩን ሲያነሳ መንፈሱ ብልጫ የሚሰጥበትን። ሁሉም ያውቀዋል ማይክ ላይ ሲጣድ ለዬት እንደሚወግን። እግዚኦ ነው የዚህ ዘመን ነገር።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
ፈጣሪ ወደ ልቦናችን ይመልሰን። አሜን።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ