፨፨፨፨፨፨፨፨፨ አዳኙ ዐፄ ፋሲልና ቆለኛው ፨፨፨፨፨፨፨፨፨

 

፨፨፨፨፨፨፨፨፨ አዳኙ ዐፄ ፋሲልና ቆለኛው ፨፨፨፨፨፨፨፨፨
 No photo description available.No photo description available.
ዐፄ ፋሲል እንደ ነገሥታት ልጆች ሁሉ ከአእምሮና ከመንፈሳዊ ትምህርት ጋራ ውሃ ዋና አደን ..... ሲማሩ አድገዋል።ከዚህ ሁሉ ይበልጥ ግን አጥብቀው ይወዱ የነበረው አደንን ነው።አደንም ሲባል በተለይ የሚወዱት ሊያስፎክሩ ከሚችሉት አራዊት ውስጥ አንበሳና ዝኆንን ነው። ከመውደዳቸውም የተነሣ ወደ አደን ሊሄዱ ባሰቡበት ቀን ሌሊቱን እንቅልፍ አይወስዳቸውም ነበር ይባላል።በታሪክ ነገሥታቸው እንደ ተጻፈው ከዕለታት አንድ ቀን ዠግኖችን አስከትለው ወደ ሰሜን የቈላ በረሓ ላደን ሄዱ።
 
በበረሓም ወዲያና ወዲህ ሲፈልጉ አንድ ባለትልቅ ጥርስ ዝኆን አገኙና በትልቅ ጨሬ (ረዥም ጦር) ከእልቀቱ ላይ ፈለሙት።ቀጥሎም ሩጫ ቢዠምር በፈረሳቸው ላይ እንደ ሆኑ ደግመው በወጉት ጊዜ ዝኆኑ ደም እያበረረው ወደ በረሓ ገብቶ ላይን ጠፋ።ንጉሡ ዐፄ ፋሲልም የተንጠባጠበውን የደም ምልክት እየተከታተሉ ካሽከሮቻቸው ተለይተው ብቻቸውን በግልቢያ ዝኆኑን ይፈልጉ ዠመር።ነገር ግን ዝኆኑ ድቡሽትና ረግረግ ባለበት ሥፍራ ስለ ሄደ የደሙን ምልክት ለመከታተል አልቻሉም ።ለመከታተልም ቢችሉ የረግረጉ ሥፍራ ፈረሳቸውን እስከ ለኮው ድረስ እየዋጠ መሄድ አቃታቸው።
ቢሆንም ካንዱ ማጥ ወዳንዱ ማጥ ሲደርሱና ባሳር በመከራ ሲወጡ በመጨረሻው መግቢያ መውጫው ወደማይታወቅ ጭው ወደአለ በረሀ ገቡ።የመጡበትም መንገድ በፍጹም ጠፍቶ የሚያደርጉት ግራ ገባቸው።ብዙ ሰዓትም ብቻቸውን ዝኆኑን ፍለጋ ትተው መንገድ ብቻ ለመፈለግ ወዲያና ወዲህ ከባዘኑ በኃላ በመጨረሻ ባወጣው ያውጣኝ ብለው ወዳንዱ አቅጣጫ ዝም ብለው ይጋልቡ ዠመር።በዚህ ጊዜ እንዳጋጣሚ አንድ ከበረሓው ጌሾ ቈርጦ (አቤት የበረሀ ጌሾ ለጠላው ለጠጁ .....) ተሸክሞ የሚሄድ ቈለኛ ስላዩ ፈጣሪያቸውን አመስግነው ወደርሱ ግልቢያቸውን ቀጠሉ።
በደረሱም ጊዜ "እባክህ መንገድ ምራኝ "አሉት! ቆለኛውም "አዬ ወንድሜ እግረኛ ከፈረሰኛ ጋራ መቼ ትክክል ይሄዳል " ሲል መለሰላቸው ዐፄ ፋሲልም "የጌሾኽን ዋጋ ያልኸኝን ያኽል እሰጥኻለው ጌሾውን ተውና ሳይመሽ ተፈናጠጥ (ወደ ፈረሱ ውጣ) በቶሎ እንጋልብ "አሉት።
ከዚህ በኃላ ቈለኛው ጌሾውን ጥሎ እፈረሱ ላይ ተፈናጠጠና በሚያውቀው መንገድ እያመለከተ ግልቢያቸውን ዠመሩ።በመንገድም ዐፄ ፋሲል እንዳንድ ተራ ወታደር መስለው ከቈለኛው ጋራ እያወሩ መንገዳቸውን ቀጠሉ።መኳንንቱና ወታደሩ በየፊናው ተበታትኖ በኃላም ግማሹ ተገናኝቶ ስለ ንጉሡ መጥፋት አጥብቀው ሲጨነቁ ነበርና አሁን ሲመጡ ስላዩዋቸው ሁሉም በደስታ ለመቀበል ወደ ንጉሡ ይጓዙ ዠመር።
በዚያ ጊዜ ንጉሡ "ይህ ወደኛ የሚመጣው ሠራዊት ንጉሡን የሚቀበል ነው "አሉት።
ቈለኛው " ለድኻ አዛኝ የሆኑትን ንጉሥ ባይኔ ባይ ምንኛ ደስ ባለኝ" አላቸው ።
ዐፄ ፋሲልም "ስለ ወረታኽ ያልኸኝን ሁሉ ሰጥቼ ከንጉሡም አገናኝቼ ባልደረባ አሰጥኻለኹ "አሉት።
ሕዝቡም እያደር ሲጠጋ ንጉሡ ለቈለኛው እንደዚህ አሉት "ከከብት የማይወርደው ንጉሡ ነውና ያን ጊዜ ወርደኽ እጅ እንድትነሣ "
በዚያ ጊዜ ዐፄ ፋሲልን ሲያዩ መኳንንቱ ከበቅሎም ከፈረስም እየወረዱ እጅ መንሣት ሲዠምሩ ፪ቱ ብቻቸውን በፈረስ ላይ እንደ ተፈናጠጡ ቀሩ። የቀረው ሁሉ ዐፄ ፋሲልን እጅ ሲነሣ ቈለኛው ባየ ጊዜ ደነገጠ።ዐፄ ፋሲልም ንጉሡን አየኽን ብለው ቢጠይቁት «"ከሁለታችን በቀር ከፈረስ ወርዶ እጅ ያልነሣ የለም እንግዲያው ንጉሡ ወይ እርስዎ አለዚያም እኔ መሆኔ ነዋ" » ሲል መለሰ።ከዚህ በኃላ ዐፄ ፋሲል በቈለኛው አነጋገር ሥቀው ከፈረሳቸው ወርደው ለዚሁ ቈለኛ ባላገር ፈረስና በቅሎ ከሙሉ መሣሪያው ጋራ ሸልመው አስደስተው ወዳገሩ ሰደዱት።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።