ቻትጂፒቲን 'ያስናቀው' ዲፕሲክ እንዴት በኢትዮጵያ ቋንቋዎች 'ጎበዝ' ሆነ? ዓለምን ያስደነገጠበት ምሥጢርስ ምንድን ነው? BBC
ቻትጂፒቲን 'ያስናቀው' ዲፕሲክ እንዴት በኢትዮጵያ ቋንቋዎች 'ጎበዝ' ሆነ? ዓለምን ያስደነገጠበት ምሥጢርስ ምንድን ነው? https://www.bbc.com/amharic/articles/cn0190den9lo 31 ጥር 2025 የአሜሪካው የቴክኖሎጂ መንደር ሲልከን ቫሊ ከዚህ በኋላ 'ማንም አይደርስብንም' የሚል አይመስልም። ዲፕሲክ 'ድምጹን አጥፍቶ' በድንገት ገበያውን አናውጦታል። ከሳምንታት በፊት ነበር የቻይናው ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) ተቋም ዲፕሲክ-አር1 (DeepSeek-R1) ቻትቦትን የለቀቀው። መተግበሪያው ለአገልግሎት ከበቃ በኋላ ማሻሻያ ተደርጎበት ባለንበት ሳምንት ያልተጠበቀ የቴክኖሎጂ 'አብዮት' ፈንድቷል። የአሜሪካን የስቶክ ገበያ የሚቆጣጠሩት ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት ገበያቸው ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አሽቆልቁሏል። ለምዕራባውያን የቴክኖሎጂ ተቋማት ቻትቦቱ ከቻይና ብቅ ማለቱ የበለጠ አስደንግጧቸዋል፤ አስፈርቷቸዋልም። የቻትቦቱ ፈጣሪ ቻይናዊው ሊያንግ ዌንፌግ እምብዛም ቃለ ምልልስ ባይሰጥም፣ ባለፈው ዓመት ባደረገው አንድ ቃለ ምልልስ "ቻይና በኤአይ ሁሌም ተከታይ አትሆንም" ማለቱ ተዘግቧል። ከሁለት ዓመት በፊት ዓለምን ጉድ ያስባለው ቻትጂፒቲ ቀንደኛ ተቀናቃኝ ገጥሞታል። ከቻትጂፒቲ ጀርባ ያለውን ኦፕንኤአይ የሚመራው ሳም አልትማን ሳይቀር በዲፕሲክ ተገርሟል። "በጣም አስደናቂ ሞዴል ነው። በተለይ ደግሞ ከወጣበት ገንዘብ አንጻር" ብሏል። በሌላ በኩል ኦፕንኤአይ "ቻይና ያሉ ተፎካካሪዎቼ የእኔን መተግበሪያ ተጠቅመው የተሻሻለ መተግበሪያ ሠርተዋል" ሲል ቅሬታውን አሰምቷል። የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፉን የሚመሩ ተቋማት ዓለ...