ጥበብ የእግዜብሄር #ሥጦታ ነው። ሥጦታውን መታገል አይገባም።

 

ጥበብ የእግዜብሄር #ሥጦታ ነው። ሥጦታውን መታገል አይገባም።
 
"ጥበብ ቤቷን ሠራች ሰባት ምሰሶም አቆመች።"
 
እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል።
እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ፤ ጥሪ ይዞ ይወለዳል።
እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መልዕክት ይዞ ይወለዳል። በሥርጉትሻ አመክንዮ እያንዳንዱ ልጅ ለመኖር ፖስተኛ ነው ብላ ታምናለች። ግንኙነት ሲቋረጥ እሰቡት? ሰው እና ሰው ሊገናኝ ቀጠሮ መያዝ የናፍቆት "ርግብ በር" ነው። 
 
የሰው ልጅ አፈጣጠር እራሱ ጥልቅ ጥበብ ነው። ጥበቡ የአማኑኤል የአላህ ብቻ ነው። የሰው ልጅ ዳንቴል አይደለም። የሰው ልጅ ለምድሪቱም #ምርቃት ነው። ምርቃቱን ሰጪውም እግዚአብሄር አላህ ነው። 
 
አንደበት ያለው ሁሉ አያዜምም። ቡርሽ የገዛ ሁሉ #አይስልም። ድምጽ ያለው ሁሉ ርትዑ ተናጋሪ ሊሆን አይችልም። መናገር እና የንግግር ጥበብ የተለያዩ ናቸው። የመናገር ጥበብ እንደ ሌላው ተስጥዖ ነው። እርግጥ ነው ንግግርን በሥልጠና ማሰልጠን ይቻላል። ለፕረዘንቴሽን ብቃት ሥልጡንነት አሰልጥኖ ክህሎቱን ማሳዳግ ይቻላል። ይህን የሚሠራ በአገራችን ተቋምም ነበር - በቀደመው ጊዜ።
 
ንግግር ለህግ፤ ለመሪነት፤ ለሃይማኖት፤ ለጋዜጠኝነት ወሳኝ ዘርፍ እና እራሱም #መሪ ነው። አብሶ ለመሪነት የመጀመሪያው መስመርኛ ረድፍ ንግግር የማወቅ ብልህነት ነው። የፈለገ ትጋት ቢኖር ፦ የፈለገ ዓይነት መስዋዕትነት ይኑር፦ ንግግር ካልቻለ አንድ ሰብ መሪነቱን ባያስበው ይሻለዋል። ገፁን ወደ አማካሪነት፤ ወደ አደራጅነት ማዞር ይኖርበታል። እኔ እራሴ አይደለም ለመሪነት ለፈለገው የሚዲያ ዓይነት ድምፁ ካልሳበኝ አላዳምጠውም። በተለይ ራዲዮ ላይ። በቴሌቢዥን ላይ ከሆነ ገፁ፦ የእጁ እንቅስቃሴ የተወሰነውን ድክመት ሊሸፍን ስለሚችል እስኪ ይሁን። ሊባል ይችላል። የድምጽ ቃና መሰጠት ነው።
 
ንግግር፤ ማዜም፤ መፃፍ፤ መሳል መሰጠት ነው። ሥጦታው ደግሞ የእግዚአብሄር የአላህ ነው። ይህን አምላካዊ ስጦታ ማገድ፤ መገደብ፤ መጫን እግዚአብሄርን #መፈታተን ነው። የሰው ልጅ ከምድራዊውም ይሁን ከሰማያዊው ህግ በታች እንጂ በላይ ልሆን ማለት አይገባውም። ተሰደን የምንኖርበት አገር ህግ አለ። የአገራችን ህግ አለ። የሃይማኖት ህግ አለ። ሁሉም የሰውን ልጅ በመኖር ውስጥ ሞራላዊ ዕሴቱን ሳያዛባ ከእንሰሳት ተሽሎ የመገኜቱ ሚስጢር የሚመሳጠርበት ልዩ ሽልማት ነው። ሥርዓት ፒላር ነው።
 
ለዚህም ነው ልብ አምላክ ዳዊት "ህግ ተላላፊወችን ጠላሁ የሚለው።" ህግ ተላላፊወች ቢኖሩ እንኳን በእነርሱ መስመር ለመሄድ መፍካከር የተገባ አይደለም። ህግ ጣሽነትን ተከትሎ የሚመጣው ሥርዓት አልበኝነት ነውና። ይህ ደግሞ ልቅ እና ብልዝ ጎዳና ነው።
ህግ ተጣሰ፤ የሰባዕዊ ፀጋ ተጠቀጠቀ፤ ፍርድ #አሸለበ ወይንም ተገነዘ ብለን ሁለመናችን ሰጥተን፦ እራሳችን ዘንግተን፤ ከተፈጥሮ ተራ ወጥተን፤ ዕድሚያችን ፈቅደን ይለፈን ያልን ሰብዕናወች በዬትኛውም ሁኔታ #ነፃነትን ከሚቀናቀኑ ድርጊቶች መቆጠብ፤ በዬትኛውም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም #አብነት ሁነን መገኜትም ይኖርብናል።
 
ከ6 ዓመታት በፊት እኔን የሚያውቀኝ ዛሬ ቢያዬኝ እኔን አያውቀኝም። ምክንያቱም ማመን መታመንን ከመስጠት በላይ ምን የተለዬ ስጦታ አለና። ለእኔ ከሁሉም መሥፈርት በላይ ታማኝነትን ካጣሁ ውስጤ በእጅጉ ይጎዳል። ጠሚር አብይ አህመድም መታመንን ሸቀጥ ያደረጉ ሰው ናቸው። እናም የውስጤ ጉዳት ሁለመናዬን አዛባው። ስደት ላይ ላለን ወገኖቻቸው ቅንጣት አያስቡም። እዚህም ያሳድዱናል በደህንነት ሠራተኞቻቸው። ሰላማችን ያውኩታል። መኖራችን ጣዕሙን እንዲያጣ ያደርጉታል። በእጃቸው ያለውን ህዝብማ ሁለመናውን ወስደውበታል። ይሉኝታ የሚባል አልፈጠረላቸውም። ያን ሁሉ የምዕት አቅም አፈር ድሜ ነው ያስጋጡት። የማህበረ ኦነግ ፖለቲካ እና ስኬቱ በህዝብ ዋይታ አወራረዱት። ከህወሃት ሰቆቃ በእጥፍ ድርብ የጨመረው አረማዊነት ሁለመናዬን ነው የዘረፈው።
 
የስደቱ ነገር ራሱን የቻለ ሆኖ፦ የአገርን መከፋት፤ የህዝብ ዋይታ መበራከት፤ መከራን ሰርክ ማድመጥ ግን ምን ያህል የከፋ ገጠመኝ እንደሆነ በእኔ "#እኔን" አይቸዋለሁኝ። ከፋኝ። ሁለመናው - ጥረቱ ባክኖ ተኖ ቀረ። እናም ውስጤ ተጎዳ። የውስጥ ጉዳት ደግሞ መጠገኛ የለውም። ያው መራራ ስንብት ነው የሚገላግለው።
 
እኔን አትፃፊ ማለት ኦክስጅን አልባ ሁኚ ነው። ከቤተሰቦቼ ጋር የተለያዬሁትም በዚህው ነው። ለዛውም እኔ አምስት ሳንቲም አግኝቼበት አላውቅም። #በነፃ ነው ሌት ተቀን ስለ ዕንባ እምታገለው። የጥበብ ሰውን አትሥራ ማለት #ግዞት ውስጥ ተቀመጥ ነው። 365 ቀናት በኢትዮጵያ ማቅ ነው። የጥበብ ሰወች ሙዚቀኞች፥ ሰዓሊወች፤ ጸሐፊወች፤ ጋዜጠኞች የአገራቸውን፤ ከተሰደዱም የሚኖሩበት ህግን ተከትለው የመስራት መብት እና ግዴታ አለባቸው። የጥበብ ሰው ተሰዶ መኖር እኮ ከባህር የወጣ አሳ ማለት ነው። ፀጋው በባዕቱ ነው ክብር ሞገስ ማዕረግ የሚኖረው። ባክኖ ነው የሚቀረው። 
 
#ሃኪምን አትግደሉ! ዊዝደምን አትግደሉ! ጥበብን አትግደሉ! ብዕርን አትግደሉ! ዝማሬን አትግደሉ! #ቅኔን አትግደሉ! #ዊዝደምን አትግደሉ! እያልን እኛ እዬታገልን #ገዳቢወችን#ነውረኞችን እኛ እነሱ በሚያስቡት ነውር ውስጥ እራሳችን አስምጠን፤ #አሰምጠንም መገኜት በፍፁም የለብንም። ነፃነት እኮ በራስ ላይ እንዲሰራ ማድረግ ነው ለነፃነት መታገል ማለት። ለዴሞክራሲ መታገል ማለት ዴሞክራሲ በራሴ ላይ እንዲሰራ መፍቀድ ማለት ነው - ዴሞክራሲ።
 
ትናንት የተፈጠረ ዕንቡጥ ከያኒ አቶ ዳዊት ጽጌ። ገና እርሾ የኤኮኖሚ አቅም የለለው ፀጋህን እግር ብረት #ግዛለት ማለት አትተንፍስ ኦኮ ነው። መኖሩን በምን ይምራው? ወጩን ትሸፍኑለትአላችሁን???? "ረሃብ ቀን ይሰጣልን?" ካለው ለተቸገረ የሚረዳው እኮ ሲሰራ ነው። እሱ እራሱ ምን ይብላ? የባላገሩ ቲቪን የሦሥት ዓመት የስኬት ሰብልንም አትቀናቀኑት። በዛው ሰሞን ስለ እሱም አደምጥ ስለነበር።
በ100 ዓመታት ውስጥ ደግማ የማትገኜው ልዕልት አስቴር አወቀ ዘመን ናት። ዕውቀቷን፤ ልምዷን፦ ተመክሯዋን ታሻግር ዘንድ መሻማት ሲገባ "አቁሚ" ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? ለዛውም የአስቱ ፖለቲከኝነት ታዬኝ እኮ።
 
በመከራው ዘመን ሁሉ፤ በቋያ ዘመን ውስ ሲገረፍ፦ #ማዕቀብ ሲጣልበት፤ ሲወነጀል የኖረ የቅኔ ባላባት የክብር ዶር ቴወድሮስ ካሳሁንን ፀጋህን ይከዘን፤ እኛም ሌላውም ሊሰማህ አይሻም እና "ታቀብ" ማለት ምን የሚሉት ጉዳይ ይሆን??? የቴዲ አፍሮ ተደሞው፤ ጥሞናው፤ ስክነቱ፤ እርጋታው ብቻውን አንድ ትውልድ ይገነባል። የእሱን ልክ ያለው በእሱ ይሁን በቀደመው ዕድሜ ያለ የትኛውም ወገን ይህን ፋክት ይመርምረው። ልዩ የዘመን ሥጦታ ነው። ከዘለለው ጋር - የማይዘል፤ ከአጎፈረው ጋር - የማያጎፍር፤ ከጎረፈውም ጋር - የማይጎርፍ፤ ጥንቅቅ ያለ ጥንቁቅ፤ የተረጋጋ ቋሚ እና ተከታታይነት ያለው ፀጋ ነው ያለው። ኃላፊነቱን እና ግዴታውን በቅጡም የሚረዳ፤ ፕሮፖጋንዲስትም የማያስፈልገው። የንግግሩ ምጣኔ እራሱ እኮ ዕፁብ ነው። ቁጥብነቱ ሐዋርያ ነው። ስጦታ ነው ሁለመናው።
 
አርቲስቶቻችን መኖር ተፈቅዶላቸው እስኪ ህልው ይሁኑልን። እስኪ ይኑሩልን። በዚህ 6 ዓመት ያዬነው በተቃርኖ ነው። ተኝቶ በሰላም መነሳት፤ ሆስፒታል በእግር በሰላም ሄዶ መመለስ ቀረ እኮ እንደ ዋዛ???? 
 
ተውኔት እና ተስፋውም እየታዬ ነው። ግራጫማ - ዘመን። ተጨማሪ ተጽዕኖ ፈጣሪ መታዬት አይፈለግም። አማርኛ ቋንቋን ልቅናውን ማዬት አይሹም። በዚህ ስድስት አመት ተወጥኖ፦ ምዕራፋን ጨርሶ የተጠናቀቀ ተውኔት የለም። ሁልጊዜ በጉማጅ ነው የሚጠናቀቀው። የመሪነት አቅል ገቢያ ተሂዶ አይሸመት ነገር። 
 
የኦነግ ፖለቲካ እርጋታ የነሳው ቁንጥንጥ ነው። አቅል የለውም። ቅጽበታዊ ነው። ነበር --- የነበረ --- የቀደመ ነገርን የሚያጎላ መንፈስ ሁሉ ማዕቀብ ይጣልበታል። በስልት። በውጥኑ ነው የሚያስቀሩት። ፍልሚያው ከቀደመ ሁለገብ ሥልጣኔ ጋር ነው። የሚስባቸው የ50 ዓመት ዕድሜ ያለው ብሊንግ ብሊንግ ነው። ይህም ሆኖ ትንሽ መተንፈሻ ስትገኝ ደግሞ፦ እኛ ተደርበን ባልቦላውን ለመከርቸም መትጋት የተገባ ጉዞ አይደለም። ወደ አበው እና እመው ዊዝደም እንመለስ። ጥንቃቄ - በተደሞ። 
 
በሌላ በኩል ሙዚቃ የራሱ ቤተሰቦች አሉት። ቤተ - ዜማ። ያ ሁሉ ሚሊዮን መከፋቱን የሚያስታግስበት፤ መጽናናቱን የሚያጎርሰው፤ ብቸኝነቱን የሚያቀልለት፤ ተስፋን የሚያሳዬው፤ ቋንቋውን የሚያጣፍጥለት ሙዚቃ የሚሊዮኖች ድምጽ ከእገታ ሲያመልጥ ነው። በተለይ ለአገር ናፍቆት ፍቱን መዳህኒት ነው። 
 
አንድ የጥበብ ሰው ብቻውን አይሠራም። ብዙ ባለሙያወች አሉት። ባለሙያወች የቤተሰቦቻቸው ጉሮሮ የሚረጥበው በሥራቸው በሚያገኙት #መሃያ ነው። እና አንዲት ደሃ አገር የተፈጠረ ባለሙያ እጅህን እና እግርህን አጣምረህ ድህነት #ቅርጥም አድርጎ ይሰልቅጥህ ምን የሚሉት ይሆን -- ፍርዱ????
 
#እኔን ስለ ኢትዮጵያ መከራ አንድም ሰው ሊያስተምረኝ አይችልም። ጫካውንም፤ ካቴናውንም፤ ስደቱንም፤ ዓለም ዓቀፍ ተሳትፎውንም የኖርኩበት ነው። በሌላ በኩል የመብት እና የግዴታዬን ጣሪያ እና ግድግዳም በበቂ ሁኔታ አውቀዋለሁኝ። በልኬ ስለልኬ ነው የምኖረው። ስለሆነም ትውልዱ በትክክለኛው የመብት እና የግዴታው መስመር ይጓዝ ዘንድ #የማስገንዘብ ግዴታ አለብኝ።
 
ከዬካቲ ፩ ጀምሮ የአዛውንታት፤ የደካሞች መጠለያ ግሎባል ጥሪ አለ። አርቲስት አምለሰት ሙጬ 1000000 (አንድ ሚሊዮን) የኢትዮጵያ ብር እንደለገሰች አዳምጫለሁኝ። ያ ከምድር #አሽዋ የተገኜ ነውን? ስለተሰራ የተገኜ ነው። በዚህ የልግሥና መዋዕትነት ውስጥም ባለቤቷም ቤተሰቦቿም አሉበት። 
 
በሌላ በኩል እኔ ባስተዋልኩት ልክ የአብይዝም ሥርዓት ማደህዬት ፖሊሲው ነው። እኛ ይህን ማበረታት አለብን በራሳችን ጊዜ? አገር ሰጪ እና ነሺው፤ የጉዞ ህግ አውጪ እና ገዳቢውስ ማነው? እኛ ባልሠራነው፦ ተሰደን በተቀመጥንበት አገር - አትምጡብን ማለት ይቻል ይሆን? እስኪ ደግግማችሁ - እሰቡት። 
 
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች መነሻችሁ ይገባኛል። እራሴን ከርክሜ፤ "ይበቃኛልን" ዶግማይ አድሬ ገድሜም ኑሬበታለሁኝ። ግን የሌላውን መብት በመጫን ሊሆን ፈፅሞ አይገባም። ይህ እኮ ተሞክሮ ያልሠራ ጉዳይ ነው። ትልልቆቹ ሊቃናት ሞክረወት አገር አላዳነም። ለውጥም አላመጣም። መቃቃር፤ መፈራረቅ፤ መራራቅን ባን መደራረግ ነው ያተረፍንበት።
 
"በኢትዮጵያ አዬር መንገድ አትጓዙ፤ ግዱቡ ላይ አትሳተፋ፦ የእከሌን ሙዚቃ አታዳምጡ፤ ተውኔት አትዩ" ፈጽሞ የማይጠቅም ከንቱ ድካም ነው የነበረው። መላልሰን፤ መላልሰን - እንሰበው። ትውልድ እንዲህ አይገነባም። በቅርቡ ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ የሚገርሙ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ካናዳ ላይ ቃለምልልስ ሲያደርግላቸው ከአሜሪካን አገር ተሰደው እዬኖሩ ለሙዚቃ ሥራቸው ፈቃድ ሰጪው እንደ እሱ ተሰዶ የሚኖር የፖለቲካ ድርጅት መሆኑን አዳመጥኩኝ። ማህጸኔ እንደ ዱባ ነው የተቀደደው። ተሰደህም በራስህ ወገን ደግመህ መሰደድ የመገለ ገጠመኝ ነበር። 
 
ሌላ በተለይ የአማራ ፖለቲካ ብርቱ ጥንቃቄ ሊያደርግ የሚገባው አመክንዮ፤ ብዙ አሁን በማዬው የትግል መስመር የደክምንላቸው ሁሉ #አፍቅሮተ ህወሃት እንዳለባቸው እያስተዋልኩ ነው። እኛ ጅሎች ነን። ሁልጊዜ መጃጃል። መስለው ሲቀርቡ፦ አቅማችን አፍሰን ቁንጮ እናደርጋቸዋለን። ከዛ አናውቃችሁም ነው፦ ይህን ነው እያዬሁ ያለሁት። ይህ የፈጠጠ የዘመናችን ሃቅ ነው። በተለይ የአማራ ፖለቲካ ብርቱ፤ እጅግ ብርቱ ጥንቃቄን ይሻል። ማስተዋልን ፈቅዶ #ሊጨልጥም ይገባል። ምርቃታችን እንዳይነሳ ልንጠነቀቅ ይገባል። 
 
በሙዚቃ ውስጥ የቋንቋ፤ የትዝታ፤ የባቲ፤ የአንች ሆዬ፤ የአንባሰል ቅኝትን ለማጥፋት ትግል አለ፤ እኛ ተባባሪ ስንሆን ምን ይባል? አልሰማችሁንም አማርኛ ቋንቋ ከሥርዓተ ትምህርት መታገቱን? አማርኛ ቋንቋ መጨቆኑን? ለግዞት መታጨቱን? ይህን የሚታገልን መስመር መዝጋት ለማን ይሆን ጥቅሙ??
 
ፍራቻው ይገባኛል። የኢትዮጵያዊነት ክብር ጎልቶ እንዳይወጣም ይፈለጋል። ይህም አደገኛ ዝንባሌ ነው። የአማራ ህዝብ ከሚስጢሩ ከወጣ ልቅናውም ሆነ ልዕልናው ምስጥ ይበላዋል። በሌላ በኩል እንደ ፍልስጤም ህዝብ ብትን አፈር ለማኝነትን መናፈቅ ነው??? የንጉሶች ንጉሥ አጤ ሚኒሊክን እና እቴጌ ጣይቱ ብጡልን #መካድም ነው። ለምን ዔለም ዓቀፍ ደረጃ ያለው የዓድዋ ድል ይከበራል??? ስክነት የሚጠይቁ አመክንዮወች እርምጃችን ያፋጥጡታል።
 
እኔ የሙዚቃ አድማጭ አይደለሁም። በህይወቴ ሙሉ ኮንሰርት ገብቼም፦ ተወዛውዤም አላውቅም። ሚዲያ ላይም ራዲዮ ፕሮግራሜ በወፎች ዝማሬ ነበር እማቀርበው። ተጠይቄ ነው ከ14 ዓመት በኋላ የመሳሪያ ቅንብር ማቅረብ የጀመርኩት። እንጂ የፏፏቴ፤ የእንሰሳት፤ የዝናብ ድምጽን ነው እምወደው። ብዙ ሲዲወቼም እነዛው ናቸው።
 
ግን ኪነጥበብ ሙሉ ነፃነቱ ይጠበቅለት ዘንድ፤ ሥልጣኒያዊ ጉዞ ይቀጥል ዘንድ እተጋለሁኝ። የሰው ልጅ ህሊና በምግብ እና በመጠጥ ብቻ አይኖርም። የጥበብ መስኖ ይሻል። በጥበብ ውስጥ ታሪክ አለ። በጥበብ ውስጥ ሰው አለ። በጥበብ ውስጥ ተፈጥሮ አለ። በጥበብ ውስጥ ፈርኃ እግዚአብሄር እና ፈርኃ አላህ አለ። በጥበብ ውስጥ ባህል አለ። በጥበብ ውስጥ ህግ ደንብ ሥርዓት አለ።
 
በጥበብ ውስጥ ህዝብ አለ። በጥበብ ውስጥ መኖር አለ። በጥበብ ውስጥ ዕውነት አለ። በጥበብ ውስጥ ተስፋ አለ። በጥበብ ውስጥ ሥልጣኔ አለ። በጥበብ ውስጥ ነገ አለ። በጥበብ ውስጥ ህብራዊነት አለ። በጥበብ ውስጥ ሰብዕዊነት አለ። በጥበብ ውስጥ ደግነት አለ። በጥበብ ውስጥ ናፍቆት አለ። በጥበብ ውስጥ #እሺታ አለ። በጥበብ ውስጥ ብርኃን አለ ወዘተ ……
 
እኛ የራሳችን ብዙ ያልሰራናቸው የቤት ሥራወች አሉን። ብዙ ነዳላወች ወይንም ቀዳዳወች አሉ። ከቻልን እነዛን እንድፈን። አንድ ሰው እራሱ የራሱ መብት እና ግዴታውን ብቻ ነው ማዘዝ የሚችለው። የሌላውን ከፈለገ ባለቤቱን ፈቃዱን ቢሰጥም፦ ህሊናውን ውሳኔው ግን የመስጠት ግዴታ የለበት። ስጠኝም ማለት ስስታምነት ነው።
 
ይህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተለመደ ፈተና ነው። ያ ሁሉ ስውር ባን በእኔ ላይ የደረሰው ህሊናዬን #ለወረራ ስላልፈቀድኩ ነው። ይህ ደግሞ መቼውንም አይታሰብም። እራስን መሆን እንዳለ ሁሉ፤ መተላለፍም ይኖራል። ከሁሉ የሚከፋው ግን እራስን ማንበብ ሲሳን ነው። እኔ ለእኔ ካልሆንኩ እኔን እኔ ማሰናበት ይኖርበታል። ይህ ደግሞ የመንፈስ የቁም ቀብር ይመስለኛል። ሁለተኛው የአዋቂወች የግጥም መድብሌ መክሊት መጸሐፌ ጀርባ ላይ የተፃፈ ነው። መርሄም ነው። የህሊናዬ እንደራሴ እኔው ብቻ ነኝ። ለዚህም ነው በዚህ መስመር የሚመጡ ፈንገጥ ያሉ የትግል አይነቶችን ሁሉ ፊት ለፊት ወጥቼ - እምሞገተው።
 
የኢትዮጵያ የፖለቲካ የሰውን ህሊና በፈቀደው ልክ አቅርቦ አቅሙን ከመመገብ በመጫን ትርፍን ይጠብቃል። ያ ሁሉ ድካማችን ፈሶ እንደ ገና ከዜሮ ለዛውም ተበታትነን የጀመርነው በዛ ዘባጣ እና የወዬበ አስተምህሮ ነው። ኪሳራ። ያ አክሳሪ ጉዞ ዛሬም ልድገመው የሚገባ አይደለም። ነፃነት ከራስ የጀመረ ሊሆን ይገባል። እኔ ነፃነት ሲናፍቀኝ የሌላውን ነፃነት አክብሬ መሆን አለበት። ሙዚቃ ቢዝነስ፤ ሙያ፤ ሥራ ነው። እንደ ሃኪም፤ እንደ አይቲ፤ እንደ መምህር። ልዩነቱ ሙዚቃ በመማር ብቻ ሳይሆን ቅብዓ የሚጠዬቅ በመሆኑም ነው። ስለዚህ ሥራ ፈት ሁንልኝ ምን ማለት ይሆን? ማድመጥ የሚፈልጉም ሚሊዮኖች ይኖራሉ። ዲስክርምኔሽን እዬተጠዬፍን እኛን በዛ ውስጥ ማግኜትም የተገባ አይደለም። " ልክን ማወቅ፤ ከልክ ያደርሳል" ይላሉ ባለ ቅኔወች ጎንደሮች። 
 
ግቢ ነፍስ ውጪ ነፍስ ላይ ያለ አንድ ህመምተኛ ኦክስጅኑ ቢነቀል ያልፋል? የጥበብ ሰውም ከፀጋው ከወጣ ትንፋሽ ያጥረዋል። ሥልጣኔን ፀጋን መገደብ ተፈጥሯዊ አይደለም። ፈጽሞ። የፖለቲካ ትግል እና ስኬቱም በዚህ ጉዞ አንድ ስንዝር አይራመድም። ኮንሰርት የማያሰኜው ከቤቱ ይቀመጥ። አይሂድ። እኔ አንድ ቀን ሙዚቃ ከፍቼ አዳምጬ አላውቅም እንኳንስ ኮንሰርት። ከልጅነቴ ጀምሮ። ግን ሙዚቃ የነፍስ ትፍስህት፤ የፍቅር ተክሊል መሆኑን እቀበላለሁኝ። የላይኛው ምርቃት መሆኑን በጽኑ አምናለሁኝ። ለሰው ልጅ አኗኗሪ ሽልማት መሆኑንም አምናለሁኝ። እናም ለነፃነቱ እሳሳለሁኝ። ትውልድ ለትውልድ ትውፊቱ በዚህም መስመር ነውና።
 
አንድ ሰብ ሥርዓቱ አይመቸኝም ብሎ እንደሚታገለው ሁሉ፤ ሥርዓቱ ይመቸኛል የሚል ሰብ መኖሩ መቀበል ደግሞ ግድ ነው። ለዚህም ነው ኮፒ የለለን። አሻራችን የተለያዬ የሆነው። ያልተመቸን ነገር በፋክት፤ በአመክንዮ መመከት እንጂ እገዳ 21ኛው ምዕተ ዓመት አይፈቅድም። ግሎባሊዝም ሥልጣኔው እራሱ አይፈቅድም።
 
ሰው ነፃ ፍጥረት ነው። የነፃነት ሩቦ ሲሶ ደግሞ የለውም። ስለሆነም የነፃነት ዓርማ በሆነች አገር የተፈጠረ ሰብ ስለማንኛውም የተፈጥሮ ፀጋ ነፃነት #ቀናዕይ ሊሆን ይገባል። የነፃነት ንባቡ፤ ትርጉሙ እና የማመሳጠር አቅሙ ከተገኜ። 
 
ዕውን ግን አብዛኛው በዬቤቱ ሙዚቃ በሩን ዘግቶ አያዳምጥምን? የወል ሲሆን ለምን ይፈራል????
ውዶቼ ክብሮቼ አደብ ስክነት መግበን ጉዟችን እንመርምር። አትራፊውን ጥሞናዊ ጎዳና እንከተል። ሳይለንት ማጆሪቱ የአቅም አንከር ነው። የአማራ ፖለቲካ የሳይላንት ማጆሪቲውን ዕንቁ አቅም እንዳያጣ ብልህነትን ይመገብ። መሪነት የማይመችን አመክንዮ አስመችቶ ማኔጅ ማድረግም ነውና። 
 
ቸር አስበን፦ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፦ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
10/02/2025
 
ፍቅር ሲያልቅ፦ ትዕግሥት ይሰደዳል።
ትዕግሥት ሲያልቅም፦ ፍቅር ይሰደዳል።
ጊዜ ሐዋርያነቱ ራዲዮሎጂስት በመሆኑም ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?