ቻትጂፒቲን 'ያስናቀው' ዲፕሲክ እንዴት በኢትዮጵያ ቋንቋዎች 'ጎበዝ' ሆነ? ዓለምን ያስደነገጠበት ምሥጢርስ ምንድን ነው? BBC
ቻትጂፒቲን 'ያስናቀው' ዲፕሲክ እንዴት በኢትዮጵያ ቋንቋዎች 'ጎበዝ' ሆነ? ዓለምን ያስደነገጠበት ምሥጢርስ ምንድን ነው?
https://www.bbc.com/amharic/articles/cn0190den9lo
የአሜሪካው የቴክኖሎጂ መንደር ሲልከን ቫሊ ከዚህ በኋላ 'ማንም አይደርስብንም' የሚል አይመስልም።
ዲፕሲክ 'ድምጹን አጥፍቶ' በድንገት ገበያውን አናውጦታል።
ከሳምንታት በፊት ነበር የቻይናው ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) ተቋም ዲፕሲክ-አር1 (DeepSeek-R1) ቻትቦትን የለቀቀው።
መተግበሪያው ለአገልግሎት ከበቃ በኋላ ማሻሻያ ተደርጎበት ባለንበት ሳምንት ያልተጠበቀ የቴክኖሎጂ 'አብዮት' ፈንድቷል።
የአሜሪካን የስቶክ ገበያ የሚቆጣጠሩት ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት ገበያቸው ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አሽቆልቁሏል።
ለምዕራባውያን የቴክኖሎጂ ተቋማት ቻትቦቱ ከቻይና ብቅ ማለቱ የበለጠ አስደንግጧቸዋል፤ አስፈርቷቸዋልም።
የቻትቦቱ ፈጣሪ ቻይናዊው ሊያንግ ዌንፌግ እምብዛም ቃለ ምልልስ ባይሰጥም፣ ባለፈው ዓመት ባደረገው አንድ ቃለ ምልልስ "ቻይና በኤአይ ሁሌም ተከታይ አትሆንም" ማለቱ ተዘግቧል።
ከሁለት ዓመት በፊት ዓለምን ጉድ ያስባለው ቻትጂፒቲ ቀንደኛ ተቀናቃኝ ገጥሞታል።
ከቻትጂፒቲ ጀርባ ያለውን ኦፕንኤአይ የሚመራው ሳም አልትማን ሳይቀር በዲፕሲክ ተገርሟል።
"በጣም አስደናቂ ሞዴል ነው። በተለይ ደግሞ ከወጣበት ገንዘብ አንጻር" ብሏል።
በሌላ በኩል ኦፕንኤአይ "ቻይና ያሉ ተፎካካሪዎቼ የእኔን መተግበሪያ ተጠቅመው የተሻሻለ መተግበሪያ ሠርተዋል" ሲል ቅሬታውን አሰምቷል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፉን የሚመሩ ተቋማት ዓለም የደረሰበትን ዘመነኛ ቻትቦቶች ከሚሠሩበት ቺፕ ባነሰ ዲፕሲክ እንደተሠራ ተገልጿል።
ተቋሙ ባለ 21 ገጽ ትንታኔ ስለመተግበሪያው አውጥቷል። አሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለን ቴክኖሎጂና ማንም ሰው በነጻ የሚያገኘውን መረጃ ተጠቅሞ ቻትቦቱን መሥራቱን ይገልጻል።
በእርግጥ ምዕራባውያን በዚህ ላይ ጥርጣሬያቸውን ሳይገልጹ አላለፉም።
ከምንም በላይ ንቅናቄ የፈጠረው ቻትቦቱ (ዲፕሲክ) የተሠራበት ዋጋ ርካሽ መሆኑ ነው። ቻትጂፒቲ ቢሊዮን ዶላሮች ፈሰውበት ሲሠራ ዲፕሲክ ግን 'ከሚሊዮኖች ያለፈ' አልወጣበትም ተብሏል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ገንዘብ የሚያፈሱ ባለሃብቶች ስጋት የገባቸውም ለዚህ ነው።
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ተቋም ኢንቪዲያ ወደ 600 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የገበያ ዋጋውን አጥቷል። ይህም በአሜሪካ ታሪክ በአንድ ቀን የደረሰ ትልቁ ኪሳራ ነው።
የጉግል አጋር አልፋቤት፣ ማይክሮሶፍት እና ኦራክል የገበያ ድርሻቸው ወርዷል። የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ተቋማት በድርሻ ገበያ በአጠቃላይ ወደ አንድ ትሪሊዮን ዶላር አጥተዋል።
በአሜሪካ በርካታ ሰዎች የጫኑት ነጻ መተገብሪያ በመሆን ዲፕሲክ ቀዳሚነቱን ይዟል።
በሌላ በኩል ዲፕሲክ 'የሳይበር ጥቃት ደርሶብኛል' ብሎ ባለፈው ሰኞ የተመዝጋቢዎችን ቁጥር ገድቦ ነበር።
ቻይና ሠራሹ ቻትቦት በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ ከሌሎች መሰል ቻትቦቶች በተሻለ አገልግሎት እንደሚሰጥ እየተነገረለት ነው።
ቢቢሲ ለዚህ ዘገባ ዲፕሲክን የተወሰኑ ጥያቄዎች በአማርኛ ጠይቋል። ለጥያቄዎች በፍጥነት ምላሽ ቢሰጥም በአንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የመረጃ ክፍተት ተስተውሏል።
የተከማቸ መረጃ ሊገኝባቸው የሚችሉ እንደ ታሪክ እና ፖለቲካ ባሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተሻለ ግንዛቤ ቢኖረውም፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እርግጠኛ እና ሙሉ መረጃ ላያቀርብ ይችላል።
አንዳንዴ የፊደላት ስህተቶች ቢገኙበትም በተሻለ መንገድ ዓረፍተ ነገር አዋቅሮ ምላሽ ይሰጣል።
የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ከሌሎች መተግበሪያዎች በተሻለ የሚገነዘበው በምን መንገድ ነው? ዓለምንስ ድንገት ያናወጠው ለምንድን ነው? በሚለው ዙርያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በሮቦቲክስ ፒኤችዲውን እየሠራ ያለውን የ'ጉዞ ቴክኖሎጂስ' መሥራች ዳንኤል ጌታቸውን ጠይቀናል።
ዲፕሲክን አስገራሚ ያደረጉ አምስት ምክንያቶች
ዲፕሲክ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ቀዳሚ መነጋገሪያ የሆነው ያለ ምክንያት አይደለም።
ቀደም ብለው ከተለቀቁ ተመሳሳይ መተግበሪያዎች ከሚለይበት ምክንያት አንዱ በርካታ የቋንቋ ሞዴሎችን በመያዝ መሠራቱ ነው።
በአንድ ሳምንት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መተግበሪያውን የጫኑትም ለዚህ ነው።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሮቦቲክስ ባለሙያው ዳንኤል፣ ዲፕሲክን አስገራሚ ያደረጉ አምስት ነጥቦችን ይዘረዝራል።
አንደኛ- አሁን ካለው ኤአይ የላቀ መሆኑ
መሥራቹ ሊያንግ ዌንፌግ፣ ዲፕሲክ "ሰው መሰል ልህቀት" እንዲኖረው ይፈለጋል ብሏል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሰው ልጆች ልክ መገንዘብ ወይም መማር የሚችልበት ነጥብ አርቴፊሻል ጀነራል ኢንተለጀንስ ይባላል። ሰው ሠራሽ ሁለንተናዊ አስተውሎት በሚል በግርድፉ ሊተረጎም ይችላል።
ዲፕሲክ በአርቴፊሻል ጀነራል ኢንተለጀንስ (ኤጂአይ) መልክ እንደተሠራ እንዲሁም "ትልቁ እና በሰው ልክ ማገናዘብ የሚችሉ ሞዴሎችን የሚያካትት" እንደሆነ ዳንኤል ይገልጻል።
ይህም ማለት፣ አሁን ያለውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ችሎታ ወይም አረዳድ እጅግ አሻሽሎ አቅርቧል።
ሁለተኛ- በጣም በርካሽ መሠራቱ
ኦፕንኤአይ 500 ቢሊዮን ዶላር ነው ያወጣው። ዲፕሲክ 5.5 ሚሊዮን እንደወጣበት ተገልጿል። ቢሊዮን ዶላሮች የሚያወጣ መተግበሪያ እንዴት በሚሊዮኖች ተገነባ? የሚለው ሲልከን ቫሊን (የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል) እንቅልፍ ነስቷል።
የወጪው እውነተኛነት ላይ ጥያቄ ያነሱ ባለሙያዎችም አሉ።
እነ ቻትጂፒቲ ከ20 እስከ 200 ዶላር ሲጠይቁ፣ ዲፕሲክ አገልግሎቱን በነጻ መስጠቱ ልዩ እንደሚያደርገው ዳንኤል ይገልጻል።
እንደ ቻትጂፒቲ ያሉ ሞዴሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ በሲልከን ቫሊ የሚሠሩ ሞዴሎችን ለማሠልጠን ቢሊዮን ዶላሮች ብቻ ሳይሆን ብዙ ቺፖችም እንደሚያስፈልጉ ባለሙያው ይናገራል።
ወደ ዲፕሲክ ስንመጣ ደግሞ ሞዴሉ የሠለጠነው በ 2,000 ቺፖች መሆኑን ተቋሙ ይገልጻል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሞዴሎችን ለጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡ ከማስቻል አንስቶ ውስብስብ የሒሳብ ቀመር እንዲፈቱ ለማስቻል ጥቅም ላይ የሚውለው የቺፕ ዓይነት ቻይና እንዳይገባ አሜሪካ ዕግድ ጥላ ነበር።
ዕገዳው ከመጣሉ ቀድሞ ዲፕሲክ ከ10,000 እስከ 50,000 ኢንቪዲያ ኤ100 ቺፖች ማከማቸቱን ኤምአይቲ ሪቪው አስነብቧል።
ሦስተኛ- ከሌሎች ቻትቦቶች በተሻለ የኢትዮጵያን ቋንቋዎች መረዳቱ
በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ የሚሰጠው ምላሽ እስካሁን ከታዩት መሰል መተግበሪያዎች የተሻለ እንደሆነ ዳንኤል ይናገራል።
"እንደ ሌሎች ስህተት የበዛበት አይደለም። የቃላት አጠቃቀሙ እና የሰዋሰው መዋቅሩም የተሻለ ነው" ይላል።
ቋንቋዎቹን በተሻለ ፍጥነት ተረድቶ ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች ጠለቅ ያለ ምላሽ ይሰጣል።
አራተኛ- በብዙ ዘርፍ ተጽዕኖ የሚፈጥር መሆኑ
ዲፕሲክ አሁን ካለው ሰው ሠራሽ አስተውሎት በተሻለ በጤና በትምህርት እና በሌሎችም ዘርፎች ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ዳንኤል ይናገራል።
ዲፕሲክ የተሠራው በኦፕን ሶርስ ዲፕሲክ-ቪ3 ሞዴል ነው።
የአሜሪካ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት የተሻለ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ለመዘርጋት በጋራ 500 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ ለማድረግ የተስማሙት በቅርቡ ነው።
ምናልባትም እንደ ቻይና ያሉ ተፎካካሪ አገራትን ለማሸነፍ መሰል ትብብር ያስፈልግ ይሆናል።
አምስተኛ- ፈጣን መረጃ የማብላላት ብቃቱ
ዲፕሲክ መረጃ የማብላላት (ፕሮሰሲንግ) አቅሙ በጣም ፈጣን ነው።
"የሚሰጣቸውን ምላሾች እና የሞዴሉን ባህሪ ስናይ በአነስተኛ ወጪ ቶሎ የሚሠራ ነው" ሲል ዳንኤል ይገልጸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካሪ እና የሲልከን ቫሊ ባለ ሃብት ማርክ አንደርሰን ዲፕሲክ-አር1 "በሰው ሠራሽ አስተውሎት እንደ ስፑትኒክ ያለ ክስተት ነው" ብለዋል።
ስፑትኒክ እአአ በ1957 ሶቭየት ኅብረት ያመጠቀችው ሳተላይት ነው። ወቅቱ አሜሪካ በሌሎች ተፎካካሪ አገራት በሳተላይት ቴክኖሎጂ እበለጣለሁ ብላ የምትሰጋበት ነበር።
እንዴት በኢትዮጵያ ቋንቋዎች 'ጎበዝ' ሆነ?
ዲፕሲክ በቀናት ዕድሜው ቀዳሚ ቻትቦት እንዲሆን ያስቻለው አንድም ቋንቋዎችን በጥልቀት መረዳቱ ይሆናል።
አብዛኛውን ጊዜ ቻትቦቶች ከእንግሊዝኛ ውጪ ባሉ ቋንቋዎች በጥልቀት ስለማይሠለጥኑ ስህተት ያበዛሉ። ጉግል ትራንስሌት እና ቻትጂፒቲ ምሳሌ ይሆናሉ።
በኢትዮጵያ ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጡ ቻትቦቶችን የሠሩ ባለሙያዎች ቢኖሩም ያን ያህል ጥልቅ እና ተደራሽ ናቸው ለማለት ይከብዳል።
"ቻይና ገበያውን ተረድታ እና ብዙ ተጠቃሚዎችን ታሳቢ አድርጋ የሚፈለገውን ነው የምታቀርበው። የአፍሪካን ገበያ ለመረዳትም ቻይና ቅርብ ናት" ይላል ዳንኤል፣ ዲፕሲክ እንዴት ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ቅርብ እንደሆነ ሲያስረዳ።
የቴክኖሎጂ ገበያ ፉክክር ስለሆነ በቀጣይ የሚመጡ መተግበሪያዎችም የቻይናን መንገድ ሊከተሉ ይችላሉ።
ዲፕሲክ የቴክኖሎጂ 'ጦርነት' ውጤት ነው?
ዲፕሲክን የመሰሉ መተግበሪያዎች ጦርነት በጦር መሣሪያ ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂም ጭምር እንደሆነ ጠቋሚ መሆናቸውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሮቦቲክስ ባለሙያው ይገልጻል።
ቀድሞ አንድን ቴክኖሎጂ ለመያዝ ወይም ለማሳደግ፣ የተለየ እና አዲስ ቴክኖሎጂ ለመፍጠር፣ ገበያውን ለመቆጣጠር እንዲሁም የሌሎችን ገበያ ለመንጠቅ ሙከራ ባደጉት አገራት መካከል ግልጽ ፉክክር አለ። በተለይ ደግሞ በቻይና እና በአሜሪካ መካከል።
ቻይና "አንድን ነገር አይቶ በመቅዳት እንዲሁም ባነሰ ዋጋ ጥሩ አገልግሎት በመስጠት" ቀዳሚ እየሆነች ይመስላል።
በመኪና ምርት ቻይና የፈጠረችውን ጫና ለመቋቋም ምዕራባውያን ተቋማት ለመጣመር መወሰናቸው አንድ ማሳያ ነው።
ዳንኤል የቴክኖሎጂ ገበያ ሽሚያውን "ሰው የማይሞትበት ጦርነት" ይለዋል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ባለሙያዎች ዋነኛ ስጋት ቴክኖሎጂ ከቁጥጥር የሚወጣበት እና የሰው ልጆችን ሥልጣኔ የሚገዳደርበት አልፎም የሚቀለብስበት ነጥብ ላይ መድረስ ነው።
ይሄንን ለመከላከልም የሰው ሠራሽ አስተውሎት የሥነ ምግባር መርሆች ተቀምጠዋል። ኤአይ ኢቲክስ ይባላል።
"እነዚህ ሞዴሎች በኃላፊነት ካልተሠሩ ወዴት እንደሚሄዱ እና ዓላማቸው ምን እንደሆነ ማንም አያውቅም" ይላል ዳንኤል።
ኒውክሌር የሚያስከትለው ጉዳት ስለሚታወቅ አገራት በጥንቃቄ ይጠባበቃሉ። ቴክኖሎጂ ግን ወዴት እያመራ እንደሆነ ማወቅም ከባድ ነው።
አብሮ መሥራት ካልተቻለ እና የሰዎች ጥቅም ቅድሚያ ካልተሰጠው እስከ ግጭት እንደሚያደርስ ባለሙያው ያስጠነቅቃል።
"ኤአአይ በሥነ ምግባር መሠራት አለበት። የተዛባ መሆን የለበትም። ስለ አንድ አገር የተዛባ ምልከታ ኖሮት የተዛባ መረጃ ከሰጠ የፖለቲካ መጠቀሚያ ይሆናል። አስፈሪ ነው።"
አገራት ድምጻቸውን አጥፍተው በቴክኖሎጂ ሲዋጉ የሰው ልጆችን የበለጠ ለአደጋ ያጋልጣሉ።
ቻይና ከሰሞኑ የተቆጣጠረችውን የቴክኖሎጂ መድረክ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ የአውሮፓ አገራትም ለመገዳደር ቀን ከሌት ይሠራሉ።
ቻትቦት ጥያቄ ሲጠየቅ መመለሱ፣ ኢሜይል ወይም ንግግር መጻፉ አልያም ምሥል መፍጠሩም አሁን ላይ ያን ያህል አስፈሪ አይመስልም።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት መስማት የምንሻውን ሙዚቃ መገመቱ ወይም መግዛት የምንፈልገውን ዕቃ ቀድሞ ማወቁም ለብዙዎች በጎ ጎን ነው።
ሆኖም ግን ከእነዚህ ሁሉ ጀርባ "ሰው ያልሆኑ ግን እንደ ሰው የሚያስቡ ሲስተሞች እየፈጠርን ነው" ይላል ዳንኤል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት የላቀ ደረጃ ሲደርስ ሰው-መሰል ባህሪ ይይዛል።
ይሄን ልህቀት ወደ ሮቦቶች ስንወስደው "ሌላ ደረጃ ነው" ይላል የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሮቦቲክስ ባለሙያው።
ለምሳሌ፣ አንድ ሮቦት ዕቃ እየጣለ እያነሳ በመለማመድ ራሱን እንዲያሻሽል ሲሠለጥን በተለያዩ ዘርፎች የሚገባበት መንገድ እየተከፈተ ይሄዳል።
ሮቦቶች- ወታደር፣ ሐኪም፣ አስተናጋጅ፣ ጋዜጠኛ. . . የሚሆኑበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
"ምን ማድረግ እንደሚችል ቻይና አሳይታናለች። ትራምፕ አንቂ ደውል ያሉት ለሁላችንም ይሆናል" ይላል ዳንኤል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ