ነፃነት ቅኔ ነው!
ነፃነት ቅኔ ነው! "በእውነት ጥበበኛ ሰው ራሱን ይጠቅማልን?" መጽሐፈ እዮብ ፳፩ ቁጥር ፪ ከሥርጉተ©ሥላሴ Sergute© Selassie 16.06.2013 ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ። እንዴት ናችሁ ክብረቶቼ ይህም የ2013 ጡሑፍ ነው። ፡ እሜቴ ነፃነት እንድምን ይዞሻል? እንዴትስ ከርመሻል? ከእመናው ሸክማ ሸክምሽ ዘንድሮስ ከብዶሻል እልፈት የለው ኑሮሽ እንዲህ ይፈትልሻል። ተርጓሚ ሲገኝ ነፃነት ቅኔ ነው። ነፃነት ረቂቅ ጥልቅ የተባረከ የመንፈስ ውስጥ ፍላጎት ነው። ነፃነት የሰለጠነ ህዝብ ብቸኛ የግናዘቤ መለኪያ ነው። ነፃነት ሰፊ የሰብዕዊነት ማሳ ነው። ነፃነት የሃይማኖት መሰረታዊ ቃል ነው። ነፃነት በጥሬው ብቻ ሊተረጎም የማይችል ውስጥን በራስነት የማናፅ ሥልጡን ክስተት ነው። ነፃነት ዛሬ የዓለማችን ጉልተ - አጀንዳ ነው። ነፃነት ዛሬ የዓለምን መንፈስ በአንድ ሃዲድ ያገናኘ ቅዱስ አምክንዮ ነው። ነፃነት ህይወት ላላቸው ብቻ ሳይሆን ለግዑዛን ሳይቀር ተቆርቋሪ ጠበቃ ነው። ይህችን ትንሽ ዘርዘር ባደርጋት መልካም ነው ከተጠቀለለች እንዳትጠጥር … በመጠኑ ስለምን ነፃነት ለግዑዛን ሳይቀር አስትንፋስ ሆነ? ምክንያቱም ግዑዛኑም ቢሆኖ በሰው ልጅ ታሪካዊ ሂደቶች ብቁ ታዳሚ ከመሆናቸው በላይ ትናንትን ለዛሬ - ዛሬን ለነገ፤ ነገን ለነገ ተወዲያ ያቀባባሉ፤ ያሰብላሉም ባለውለታዎቻችን ናቸውና፤ አሁን የዋሻ ዘመናት ታሪክ በድንጋይ ላይ ተቀርጸው ይገኛሉ። ብዙም ይናገራሉ፤ መሬት በከርሷ እፍን ሽክፍ አድርጋ ያያዘቻቸው ቅሬተ - አካላት ትናትን አበክረው ያውጃሉ፤ ከመነሻም ይገነባሉ። ለዝንተ ዓለም ዝክረ ንዑዳን ናቸው። ለዛሬ ሥልጣኔም የምርምር ማዕከል እኮ የትናት ትንግርት ክንውን ነው...