ነፃነት ቅኔ ነው!
ነፃነት ቅኔ ነው!
"በእውነት ጥበበኛ ሰው ራሱን ይጠቅማልን?"
መጽሐፈ እዮብ ፳፩ ቁጥር ፪
ከሥርጉተ©ሥላሴ Sergute© Selassie
16.06.2013 ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።
እንዴት ናችሁ ክብረቶቼ ይህም የ2013 ጡሑፍ ነው።፡
እሜቴ ነፃነት እንድምን ይዞሻል?
እንዴትስ ከርመሻል?
ከእመናው ሸክማ ሸክምሽ ዘንድሮስ ከብዶሻል
እልፈት የለው ኑሮሽ እንዲህ ይፈትልሻል።
ተርጓሚ ሲገኝ ነፃነት ቅኔ ነው። ነፃነት ረቂቅ ጥልቅ የተባረከ የመንፈስ ውስጥ ፍላጎት ነው። ነፃነት የሰለጠነ ህዝብ ብቸኛ የግናዘቤ መለኪያ ነው። ነፃነት ሰፊ የሰብዕዊነት ማሳ ነው። ነፃነት የሃይማኖት መሰረታዊ ቃል ነው። ነፃነት በጥሬው ብቻ ሊተረጎም የማይችል ውስጥን በራስነት የማናፅ ሥልጡን ክስተት ነው።
ነፃነት ዛሬ የዓለማችን ጉልተ - አጀንዳ ነው። ነፃነት ዛሬ የዓለምን መንፈስ በአንድ ሃዲድ ያገናኘ ቅዱስ አምክንዮ ነው። ነፃነት ህይወት ላላቸው ብቻ ሳይሆን ለግዑዛን ሳይቀር ተቆርቋሪ ጠበቃ ነው። ይህችን ትንሽ ዘርዘር ባደርጋት መልካም ነው ከተጠቀለለች እንዳትጠጥር … በመጠኑ
ስለምን ነፃነት ለግዑዛን ሳይቀር አስትንፋስ ሆነ? ምክንያቱም ግዑዛኑም ቢሆኖ በሰው ልጅ ታሪካዊ ሂደቶች ብቁ ታዳሚ ከመሆናቸው በላይ ትናንትን ለዛሬ - ዛሬን ለነገ፤ ነገን ለነገ ተወዲያ ያቀባባሉ፤ ያሰብላሉም ባለውለታዎቻችን ናቸውና፤ አሁን የዋሻ ዘመናት ታሪክ በድንጋይ ላይ ተቀርጸው ይገኛሉ። ብዙም ይናገራሉ፤ መሬት በከርሷ እፍን ሽክፍ አድርጋ ያያዘቻቸው ቅሬተ - አካላት ትናትን አበክረው ያውጃሉ፤ ከመነሻም ይገነባሉ። ለዝንተ ዓለም ዝክረ ንዑዳን ናቸው። ለዛሬ ሥልጣኔም የምርምር ማዕከል እኮ የትናት ትንግርት ክንውን ነው። ክንውኑ በምስል፤ በቅርፃ ቅርጽ፤ ወይንም በፁሑፍ ሊሆን ይችላል።
… አሁን በድንጋይ መፋጨት የእሳት መገኘት በራሱ የሰው ልጅ ብርኃንን በእጁ የመፍጠር አቅሙን ጠቋሚ አድርጎታል። ሳይንሳዊ በሆነ መልኩም ፊዚክስንና ኬሚስትርን መቅኖ ሆኖለታል። የሰው ልጅ ሥልጣኔ እንደገና መወለድን /ሪናይሰንስን/ ዓላማ አሳክቷል። የሰው ልጅ የአንኗኗር ዘይቤ፤ አምልኮዊ ሆነ ዕምነታዊ ሂደት ሁሉ በስዕል ሆነ በመጸሐፍት እንደ ተፈጥሯቸው ይገኛሉ። በጦርነት በመስፋፋት ከወደሙት የተረፉት። ብቻ እነዚህ ሁሉ በነፃነት ማዕፍ ውስጥ ሲካተቱ የነፃነትን ሊቅነትን፤ ቅኔነትን ያናገራሉ። የነፃነትን ድርሻ መጠነ ሰፊ ያደርገዋል።
አሁን ዩኒስኮ የተቋቋመበት መሰረታዊ ዓላማ የግዑዛንን መብት ለማስጠበቅ በጥብቅና ለመቆም ነው። እግዚአብሄር ይመስገን እሰከ 2012 ድረስ የእኛ ሰባት የነበረው በ2013 መጨረሻ ላይ ወደ ስምንት አድጓል። ይቀጥላልም። ያው ጠንክረን ከሰራን አደጉ ተመነደጉ የተባሉት ሀገሮች የሌላቸው እኛ ግን እኛ ያለን ብዙ የቅርስና የውርስ ጥበቃ በአለም ዓቀፍ ደረጃ የሚያስፈልጋቸው ሃብታት አሉንና … ይህ የማንነት ምንጭ አክባሪ ሲያጣ ግን እጅግ ያማል …. ውስጥንም ይመራል። ለማንኛውም ይህ በራሱ የሚያሳዬን የነፃነት ደንበር የለሽ የአብሮነትን ስክነተ አመክንዮነትን ነው። የነፃነት ቤተኝነት ድንበር የለሽ መሆኑን ነው።
ከሁሉም ነገር በላይ ፍቅር በመተርጎም ሂደት ነፃነት ልዩ ልብ አለው። ነፃነት ሁሉንም በፍቅር አክብሮ የሚያወራርሰው የመንፈሳችን ልዑቅ ምኞት ነው። ምኞቱ እጅግ ተናፋቂ የሚያደርገው ከነፃነት መልስ የሰው ልጅ ደም መፋሰሱን እረዳው … አቃጥለው … አንድድድው የሚለውን ጠናና አመለካከትን ገርቶ ምህርትን አውጆ ሰላምን የሚፈጥር፤ ተግባራዊ ለማደረግም የሚተጋ ብቁ ሐዋርያ ስለሆነ ነው።
ነገ መምጣት ወይንም መገኘት የሚችለው …. ዛሬን ሳናጠፋው ከቀረን ዛሬን በላፒስ ካለሰረዝነው ብቻ ነው። ነፃነት ለትናት ሰፊ አክብሮት አለው፤ ለዛሬም ልዩ አክብሮት አለው። ለነገም ጥብቅና ቋሚነቱ በሥነ - ጥብብ ነው። ስለዚህ የነፃነት ተፈጥሮ ቅድመ - ማዕክላዊና - ድህረ ሆኖ እኩልነትን በገፍ ይሸልማል። መደማመጥን ይሞሽራል። መቻቻልን ያነግሳል። ይህ የነፃነት በኸረ አምክንዮ አንጎል ነው።
ነፃነት መርህም ህግግታም ጥብቅናም ሁሉንም ለመተግበር የመጀመሪያ ጥያቄ አለው። እሱ እራሱን ነፃ መውጣት በቅድሚያ ይሻል። ማለት ተተርጓሚነት፤ ተጠበቂነት፤ ለጋስነት በፈጻሚነት።
ሀ. ተተርጓሚነት ሲባል ነፃነት ያሰገኛቸው ፋይዳዎች መሪዎች እንዲሆኑ መፍቀድን፤
ለ. ተጠባቂነት ሲባልም ነፃነት ባስገኛቸው ውጤቶች ዙሪያ የማህበረሰቡ ወይንም የህብረ - ሃብት የሆኑ መስዋዕትነቶችና ውጤቶቻቸው ጣባቂ ባለቤቱ ተጠቃሚው ህዝቡ እንዲሆን መሻትን።
ሐ. ለጋስነት በፈጻሚነት፤ ነፃነት ፈላጊው አካል ነጻነቱን ቢገኝ ለጋስነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል። ከሩቆቹ ጋር ሳይሆን የጥቁር ነፃነት ታሪክ መሰረት ከሆነችው እናት ሀገረችን ላይ መነሳቱ እኛን አዙረን በማዬት ወደ ልቦናችን ቢመልሰን ሁለመናችን መነሳት አለበት ብዬ የማምነው። ለማናቸውም ቀደምት ጉዳይ ነፃነትን መስጠት። ለቅርሱ ይሁን ለታሪኩ፤ ለታሪኩ ይሁን ለትሩፋቱ።
„ በ እጅ የያዙት ወርቅ“ ሆኖ እንጂ ከቅርባችን መነሳቱ ነው አሸናፊ ሊያደርገን የሚችለው። ኢትዮጵያ ለራሷ ማገናዘቢያ ሆነ ማውጫ እራሷ መሆን የምትችል ሀገር ናትና። ትውስት አይደለም የኢትዮጵያ ሥህነ -ተፍጥሮ። ስለሆነም መነሻዬ ከዚህ እንዲሆን እፈቅዳለሁ ትንሽ ዘርዘር አድርጌ ልሂድበት …..
ሀ. ተተርጓሚነት
በትርጉም ሊቃኑ የማይችሉ ፈላሲ ስሜቴችን ዘልዬ፤ መሬት ላይ ባሉት ባተኩር ይሻላል። ይህ በረቀቀ መልኩ ሊታይ የሚችል ነገር ነው። ነገር ግን ለንጽጽር በነፃነት ያደጉ ውጭ ሀገር ያሉ ልጆችና ሀገር ቤት እኛ ስናድግ የነበረውን ኮድኳዳ ወይንም ጎድጓዳ ዘመን ብናሰላው ፍቺውን ማግኘት በቀላሉ የሚቻል ይመስለኛል። ሩቅ አትሂዱ ይህን ዘመን በዚህ ልኬታ ፈትሹት ከጓዳችሁ ተነስታችሁ …
…. እራህብን የሚያውቀው የተራበው ብቻ ነው። ራህብን የማያውቀው ሰው ቢጠዬቅ ራህብ ምንድን ነው ብሎ ይጠይቃችኋል። አያውቀውምና፤ አሁን ሀገራቸው በባዕድ ቅኝ ተገዝቶ የነበረ አንድ የአፍሪካ ሀገር ሰውና እኛ ስለ ቅኝ ግዛት አስከፊነት ብንጠዬቅ አናውቀውም …. ስለምን አልተገዛነም።
የሚያሳዝነው ነገር በባዕድ ባለመገዛታችን ምክንያት የእኛነታችን መግለጫዎች ሁሉ ከእነ ሙሉ አካላቸው ሳይቀዬጡ አሉን። ፈታትተን ብናዬው ስሜታችንም፤ ፍላጎታችንም መነሻው ሆነ መድረሻው ከዛ ላይ ነው። እንጀራን ስታስቡት ሰፍ ብለን እንወደዋለን። ሆዳችን ሞልቶ እንጀራ አለ ከተባለ ማዕደኛ እንሆናለን። ተገዘተን ቢሆንስ? ዕውነታውን ሳንርቅ አቅርበን እናወያዬው ….ሌሎችንም ትሩፋቶች ስናስብ ከነውስጣችን በተፈጥሯችን ልክ የሆን ነን።
ቋንቋውን ብትመለከቱት ቀበልኘው ብቻ የትእዬለሌ ነው፤ አለባበሱን ብታዩት ቀለማም፤ አመጋገቡን ብታዩት የማይጠበገብ፤ የግብይት ሥርዓቱን ብትመለከቱት ወዝ አለው፤ የማህበራዊ ኑሮ ትውፊቶቻችን ዘርዘር አድርገን ብንመለከታቸው ጠረናቸው የኛ ብቻ የሆኑ በፍጹም ሁኔታ ያልተዳቀሉ። ስለፊደል ገበታችን ሌላ ጊዜ ብመለስበትም እሱ በእራሱ ውበታችን ያነጥረዋል። „የተወሶ ይሄዳል ተመልሶ“ አይደለም።
ከሁሉ በላይ የትም ቦታ በራስ የመተማመን መንፈሳችን ያልተቀማን በመሆናችን እርግጠኝነት በውስጣችን ስላለ፤ ተሰደን እንኳን የበታችነት ስሜት ፈጽሞ አይሰማነም። ስለምን? ማንነት ያለው ሙሉዑ ሰብዕና ስላለን። ነገር ግን ይህ የነፃነት ታላቁ ዕሴት ተዘሎ ነፃነቱን ለማስገኘት በተደረጉ ሂደቶች የተፈጠሩ ሳቢያዎች ላይ እናተኩራለን። የመኖራችን ምክንያታዊ ጭብጥ አናቱ ያለው ግን አራሳችን የሰጠን የአባቶቻችን የተጋድሎ ታሪክ ነፃ ህዝብ መሆናችን ነበር።
እኮ ስለምን መተላላፍ መጣ ሲባል … ነፃነትን መተርጎም ስለቃተን። ነፃነት ለራሱ ከሚፈልገው ነፃነት ላይ እንኳን ለመነሳት አቅማችን ሰላላ - መላላ በመሆኑ ምክንያት። አይደለም በቅኝ ግዛት ያለውን ባርነት ዘመን ከእንሰሳ አንሶ መኖር ቀርቶ ተሰደን እንኳን መኖሪያ ፈቃድ አጥተን ስንገላታ የሚደርሰው ሰቆቀቃ ሁሉ ብንፈትሸው ዋናውን አናቱን ነገር ማግኘት ይቻላል።
በነገራችን ላይ ሀገር ያላቸው ዜጎች ስደት አይጠይቁም። የሁለተኛ ደራጃ ዝቅተኛ ኑሮ አይናፍቃቸውምና። ለዚህ ነበር በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ከተማሩ ውጭ ሀገር ዕውቀት ከቀሰሙ በኋላ ሙሑራን ወደ ሀገራቸው በደስታ የሚመለሱት። መሰደድ ውርዴት ነው በዛ ዘመን። የዚህ ዋጋው የሚላካው በመንፈስ ስሌት ነው። ነፃነት መኖር ነው፤ መኖሩ ጣዕሙ በራሱ ይዘትና ቅርጽ የተዋቀረ ነው። የዛሬን የዘመነ ዬወያኔን ሃርነት ትግራይ ተውት … አድርጉት። በዬደቂቃው አሜኬላ ችግኝ ይፈላል፤ ተንከባክቦ ያጸድቃል ተዋጊ አድርጎ ያሰልፋል …. የተፋለሰ እሾኽማ ዘመን። …. ለማንኛውም ነፃነት የተሰጠው ተርጓሚ አጥብቆ ይሻል።
ለ. ተጠባቂነት
የነፃነት ግኝቱ ከሰማይ በታች በሰዎች መስዋዕትነት የቀለመ ነው። ይህ ቀለማም ጥሪት ቅርስና ውርስ ደግሞ የእኛ እንጂ የአንድ ጎሳ ወይንም የአንድ ኢሊት አይደለም። ሃብትነቱ ውድ ህይወት ተከፍሎለት ስለሆነ የተከበረ ስጦታ ነው የቀራኒዎ ሚስጢር። ይህን ታላቅ ስጦታ ጠብቆ ለልጅ ልጅ ለማቆዬት ብቁና የሰለጠነ፤ የብሄራዊ ስሜት የሚያንገበግበው፤ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም ግዴታ ነው።
ምክንያቱም የነፃነት ሃብትነቱ የህዝብ ነውና። ይህንን ሃብትነት የመጠበቅ የማሰጠበቅ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነበር …. ዛሬ በአገራችን በኢትዮጵያ ሳንክ ቢገጥመውም የነፃነት ጥበቃ ነገ ግን ኃላፊነት ያለው ሥርዓት ሲዘረጋ መዘከሩ አይቀሬ ነው ….. እርግጥ አሁንም ከእኛ አልፎ እነ ተፈሪውያን፤ የተከበሩ ኔልሰን ማንዴላም …. የፓን አፍሪካ ቀደምቶች ይሁኑ የዛሬዎቹ አቀንቃኞች ሁሉ በክብር ያከበሩት በመንፈሰቸው አጉልተው የጻፉት ታላቅ መጽሐፋቸው፤ ትውልድ ቢለዋዋጠም ዋጋው ሳይቀንስ እንዲዘልቅ የሚተጉ ቀለሞቻችን አሉ። ተመስገን!
ነፃነትን የተማሩበት ተቋማቸው፤ ስለሆነም የጥቁር ህዝብ ለነፃነት ታሪካችን ጥበቃ ከእኛም አልፎ የተደራጀ ተግባር ከፈጸምን አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን የነፃነት ዓላማ አራማጆች፤ ሰብዕዊ ድርጅቶች ሁሉ የሚጋሩት ይሆናል።
ይህን መፋቅ ከቶውንም አይቻልም። አብሶ የነፃነት አቀንቃኝ ሁሉ ፍሰቱ የነፃነት ፍላጎትና ተፈጥሮ ተጋፍቶ ወይንም ገፍትሮ መሆን አይገባውም። ውስጥን አስቀድሞ መርምሮ መፈወስ ያስፈልጋል …. ወደ ኋላ ተኑሮ አይታወቅም። ለዘመኑ የተመቹ ገጠመኞች ሁሉ ውስጥ ሊያበቅላቸው የሚገቡ ጭብጦች ናቸው፤ በስተቀር የነፃነትን ሥነ - ተፈጥሮ ጋር መገናኘት አይቻልም።
ሐ. ለጋስነት- በፈጻሚነት።
ነፃነት ከቤት ጀምሮ ተወዳጅ ጉዳይ ነው። ነፃነት ለዕድገት፤ ለሥልጣኔ ለፈጠራ ለሁሉም መንገድ ጠራጊ ነው። የነፃነት ፈላጊው ብዛት ህልቆ መሳፍርት ነው። ነፃነት ተግባራዊ በማድረግ እረገድ በአደጉ ሀገሮች አንፃራዊ በሆነ ወይንም ልቅ በሆነ ወይንም መጠራቅቅ ባላው ሁኔታ የተረጎሙት ሀገሮች አሉ።
ይህ ወደ እኛ ስንመጣ ለነፃነት የቆመ አካል፤ ድርጅት፤ ተቋም ግን ነፃነት መስጠትን ወይንም ማግኘትን ራህብተኛ የመሆኑን ያህል በነፃነት ዙሪያ ያሉ ነፃነት የሚለግሳቸው አምክንዮችን በመተርጎም እረገድ ገና አልጀመርነውም። ፊደልም ያልቆጠርነበት ጉዳይ ይመስለኛል።
ዛሬ ማታ ነፃነታችን በእጃችን ቢገባ በአግባቡ አስተዳድረን የሚመቸንና የማይመቸንን ፍላጎቶች አስማምተን የነፃነትን ሥነ - ምግባር ካለ መጠራቅቅ እንፈጽማለን ወይ? ዝግጁ ነን ወይ? ስንዱ ነን ወይ?
የዕውነት አይደለነም። ሃቁ ይህ ነው።
ከእኛ ፍላጎት ትንሽ ፈቀቅ ያለ ነገር ቀርቶ ተመሳሳዩን ሃሳብ የሚደግፍ ግን የተሻለ ሃሳብን፤ የዳበረ ዕይታን፤ የተደራጀን ፈጠራን፤ የበለጠን አመለካከትን፤ የቀደመን መንፈስን ለማስናገድ እንኳን የፍርፋሬ ትዕግስት የለም። አልፍ ሲልም ጦርነት ይተወጅበታል። በዛው በእኔ ፍላጎት ዙሪያ እያለ ጦር ይመዘዝበታል። ስለዚህ አንዱ ለሌላው በእጁ ያለውን ነፃነት ለመስጠት ገድጋዳ ሙልጭ ያለ ንፉግነት ነው እኔ እምታዘበው።
ይህ የሃሳብ ልዩነትን በመዋዋጥ መደማመጣ በጓዳ ይቀመጥና፤ በመስመራችን ላለው እንኳን ከእኛ መንፈስ ወይንም ብቃት በታች መሆኑ ካልተረጋገጠ ያዳልጠናል ነፃነትን ለመስጠት። …. ስለዚህ በጠራ ቋንቋ ነፃነት በእጃችን ቢገባ ለሌላው ለመስጠት የወጣልን የንፉግነት ተዋናዮች ወይን አጋፋሪዎች ነን። ይህ ሲሰላ፤ ሲመነዘር ስለ ነፃነት ብለን ከፈልን የምንለው መስዋዕትነት የውርንጫ ድካም ሆኖ ቁጭ ይላል። ተቆርቋሪነቱም ባዶ ቀረርቶ ብቻ ….ንፉጎች።
· /ውዶቼ ይህን የጻፍኩት በ2013 የሚገርመው በ2018 ዕድሉን አግኝተን እንኳን ለመጠቀም እሳት መቆስቆሻ ነው ያደረግነው/
ዛሬ ነፃነት ከራበኝ ብገናኘው እኔ እራሴ ሐዋርያ ሆኜ እራሴን ውስጤን መንፈሴ ለድምጽ ብልጫው ካላስገዛሁ ከንቱ ነው። ትግሉ በሉት፣ ልፋቱ በሉት፣ መስዋዕትነቱ በሉት፤ እኔ እጅግ ቁርጥምጥም የሚያደርገኝ ምን እንደሆን ታውቃላችሁ? የነፃነት ታጋይ ከመባላችን በፊት ስለ ነፃነት ተፈጥሮ ሆነ ሥነ - ምግባር የምናውቀው ምንም ነገር የሌላ መሆኑን ነው።
ከዚህ ባለፈ በመንፈሴ ሰሌዳ የማገድናቸው … ለበለኃሰብ አሳልፈን የሰጠናቸው ነፃነት፤ እኩልነት፤ የመጻፍ የመሰብሰብ የመደራጀት የመናገር ነፃነት እዩሉ በዬዘመኑ በባሩድ የነደዱት፤ ዛሬም የሚሰውት፤ እስር ላይ የሚማቅቁት ወገኖቼን አብዛኞቹ ደግሞ መኖርን ያልጀመሩት ወጣቶች ናቸው እዬተጣፉ ያለቁት፤ ወይንም በፋሽስት በቀል የሚሰለቁት። ይህን ሳስብ ውስጤ ይርመጠመጣል።
ፈፃሚነታችን በእጃችን ሲገባ ስለምነዘለው።
ካለ ዘመኑ ካለ ብቃታችን የተፈጠሩ የበለጡ ጀግኖች የሚከፍሉትን መስዋዕትንት ማድመጥ አለመቻለችን …. ሰቀቀን ነው። እሳት ነው ረመጥ። በተመሳሳይ ፍለጎትና ዓላማ ዙሪያ በተለያየ ሥም ስሜታችነን ከዘነን የእኔ ካልሆነ የሱስ ፍትጊያ ብቻ። የምሽጉ ፍልሚያ ይህ ነው …. በቃ … ስለምን? ….
አንድ ለነፃነት የሚታገል ድርጅት፤ ግለሰብ፤ ቡድን ለሌላው ነፃነት ተቆርቋሪ መሆን አለበት። ለምሳሌ ሥነ - ጥበብን ልውሰድ። ሥነ ጥበብ ስለፈለግነው ብቻ ተስጥዖው ሊገኝ አይችልም። የሰማይ ሥጦታ ነው። ለዚህ የሰማይ ሥጦታ እንኳን የምንፈጥረው ማጣበቂያ፤ የሚጣለው ተዕቅቦ በጣም ድልዝ የሆነ፤ የነፃነት ፈላጊነታችን በእጅጉ የሚያሳርረው የተጋጠ ገጠመኝ ነው እኔ እማስተውለው።
ትናንት ልንሳሳት እንችላለን። ዛሬ ግን ያለፍንበትን ገምግመን ሁሉንም በአውንታዊና በቅንነት መተርጎም ይጋባል። ውስጥ ፈቅዶ ማረም ይገባል። ዕድሜም ቁጥር፤ መማርም ቁጥር መሆኑ እራሳችን አብሶም ህሊናችን እረፍት የማይሰጠን የትውልድ ዕዳ ተሸከምንን ሳናካፍል ማለፍ አለመፈጠር ይሻላል። የቀደምቱ ነብይ ጸሐፊ „የአልወለድም“ ሚስጢር ተዚህ ላይ ተገኘ። የነፃነት ታጋይ ነፃነትን ለመስጠት ስስታም ሳይሆን ሲቀር ውስጡ በፈፃሚነት መዳሰስ አለበት … በስተቀር ውሃ ወቀጣ ነው …..
አንድ ሰው ሲጽፍ፤ ሲተውን፤ ሲዘፍን፤ ሲስል ሌላ ዓለም ውስጥ ሆኖ ነው። ለነገሩ በዚህ ልዩ ዓለም ለመኖር ላልታደሉት ምንም ሊመስል ይችላል ይሆናል። በሥነ - ጥበብ ዓለም ሲኖር ጨለማ ውስጥ ሆናችሁ ብርኃን ይታያችኋል፡ ደማናማ ቀኖች የጸደይ አባባዎች ሆነው ፈክተው ይታያችኋል። በስምጥ ሸለቆ ጉድጓድ ሆናችሁ ተስፋ ይታያችሁዋል። ይህም ይታገዳል። ይህም ማዕቀብ ይጣልበታል።
ረግረግ ላይ ሆናችሁ መሰላሉን ያቀበላችኋል፤ እጅግ ጨቀጨቅ ውስጥ ሆናችሁ ካለ መሰናክል የምትወጡበት ደረጃ ይሰራላችሁ። ወንዝ ሞልቶባችሁ መሻገሪያ ድልድይ ወይ ታንኳ ያቀርብላችኋል። ማን ሥነ ጥበብ። በጣም ውስብስብ ያለ ፈተና እያለ ወይ እንደ ጠፍር* መዬመፍትሄ ጭላንጭል እንደሌለው እአያችሁት ግን ብቃትን - ጥንካሬን - ጽናትን - ተስፋን ያቀብላችኋል። ሥነ - ጥብብ አዲስ ፕላኔት ነው። 13ኛው ፕላኔት።
በተለይ ቤተኛው በውስጡ ሆኖ ሲሆንበት። ታዳሚው ሲታከልበት ደግሞ ዳግሚያ ትንሳኤ ነው። መከራው፤ ፈተናው፤ ሳንኩ ሁሉ የጥቡ ዕድገት ወተቶች ናቸው። ስተወጡት ማደጋችሁን ታዩበታለችሁ። ይህንን የሰማይ መክሊት እንኳን እንገድባለን በማለት የነፃነትን ጅረት ለመገደብ ማሰብ ቀንና ሌሊትን መፈራቀቅ የማቆም ያህል ስለመሆኑ ማስተዋል የከሰለበት እርምጃ ይመስለኛል።
ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ „ህግ ተላላፊዎችን ጠላሁ ይላል“ በዬትኛውም ዕምነት ወይንም ሃይማኖት ህግ ላይ ድርድር የለም፤ ታዲያ የሰማይ ሥጦታን መዳፈር መተላለፍ አይሆንም …. የነፃነት ፈላጊነታችን ትርጉምስ የት ላይ ይረፍ? ይህን ቅጥ አንባሩ የጠፋ ወጣ ገብ ዘመን ፈጣሪ ይክላልን። አሜን!
· መከወኛ?
አሁን ትግሉ ነፃነት ወይንስ ባርነት? ነፃነት ከሆነ አንተላለፈው። ነፃነት ተወዳጅ ሥነ - ተፈጥሮ አለው። ግብታዊ ስሜቶቻችን ሁሉ መለስ ብለን ፈታትሸን …. ፍላጎታችን ነፃነት ስለመሆኑ ተግባር ላይ እንገኝ።
ቅልሞሹ ገበጣ ጨዋታው እንድርቺ እንድርቺው ለልጆቻችን የልጅነት ህይወትእንዳይሾልክባቸው በዘመናቸው ይዝናኑበት በዚህ ውስጥም ይለፉ። እኛ ግን እንደ ዕድሜያችን፤ እንደ ትምህርት ደረጃችን፤ እንደ ተመክሮችን ለመሆን ውስጣችን እናሸንፈው፤ ግብታዊ ስሜቶቻችን እንግራቸው፤ ቅኑ እንሁን …..
አባቶቻችን ያለፉበትን ቅኝ ተገዢነት ናፋቂ አንሁን። ነፃነትን መቀማት በራሱ ቅኝ ተገዢነት ናፋቂነት ነው። ስለዚህ ባለ አደራ ነንና ፍቅርን በፍቅር አባዝተን ከብረን እናስከብረው። ሁሉ ያላት ታላቅ ሀገር አለችናና! እሷን ከፍ አድርገን ለማቆዬት ተግተን ለነፃነታችን እንሥራ።
እጅግ የማከብራችሁ የጹሑፌ ታዳሚዎች ስለፈቀዳችሁልኝ መልካም ጊዜ አትዮጵያዊ አክበሮት በያላችሁበት አንሆ ላኩኝ።
አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሄር የሰጠንን መስተዋል እንተረጎምው ዘንድ ወደ ልቦናችን ይመልሰን። አሜን!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ማለፊያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ