ሴቶች ጥሩ ነገር አላቸው...

ሴቶች ጥሩ ነገር አላቸው ጊዜ እሲኪሰጣቸው ድረስ ጠብቀው ይይዙት ዘንድ  እለምናቸዋለሁ።

"አለመታገሥ ስለምን አይገባኝም?"
 መጽሐፈ እዮብ ፳፩ ቁጥር ፬  
ሥርጉተ©ሥላሴ Sergute©Selassie
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ 23.12.2013


·       መግቢያ።

አሁን ሳስበው እኔ እና ሳምንበትም ጊዜ ሰጥቷናል እላለሁኝ። ግን እንዴት ናችሁ የኔዎቹ። ይህ ብሎግ ሥራ የጀመረው በግንቦት 1 ቀን በ2018 ነው። ከዚህ ቀደም በስፋት የተሠሩባቸው ጉዳዮች በዘሃበሻ ወይንም በኢትዮ ርጅሰተር ነው። ቀደም ባለው ጊዜ በራሴ በጸጋዬ ድህረ ገጽ እና ራዲዮም ነው። እኛ እራሳችን ሲሞላብን እንደምንቀንሰው ሁሉ ዘሃበሻም ሆነ ኢትዮ ሪጅሰተር ሆነ ዘሃበሻ እነሱ ደግሞ አርኬቡ ሲሞላባቸው መቀነስ ግድ ይላቸዋል። ግሎባል ጉዳዮችን ስለሚያስተናግዱ ጫና ይበዛባቸዋልና።  

ስለዚህም ጹሑፎቼ ሊሠወሩ ይችላሉ። ታሪክ ነው። ታሪኩ የኢትዮጵያ የነጻነት ትግል በአንዲት ዜጋ ዕይታ እንደ ዘመኑ ነው። ዛሬ በ2013 እንደምጸፈው ዛሬ አልጽፍም። ስለምን? ዘመኑ በራሱ የሚያመጣው ለውጥ ስላለው። 

ግን በዛ ዘመን የነበረው ዕይታ እና ግንዛቤ ዛሬን በሃሳብ በማገናኘት እረገድ ምን ድርሻ አበርክቷል የሚለውን ያሳያል፤ በሌላ በኩል ግን የአንባቢያን ዕይታም በዛ ዘመን በነበረው ንቃተ ህሊና ልክ የተሠራ ስለመሆኑ ልብ ሊለው ይገባል። ስለሆነም ከጻፍኳቸው ወዘተረፈ ወጎች ውስጥ በዚህ ብሎግ እንዲቀመጡልኝ የምፈቅዳቸውን በተከታታይ ፖስት ለማድረግ አስባለሁኝ። www.tsegaye.ethio.info ያለው እንደ ተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።

እንዲህ ነበር የተጀመረው በ2014

·       በሴቶች ስሜት ውስጥ መሆንና በስሜቱ ውስጥ ሴቶችን ሆኖ ማሰብ ከባድ ነው።
·        
እኔን ተብድሬው አላውቅም። እኔንም ተውሼው አላውቅም። እኔንም ሸቅጬው አላውቅም። እኔንም መስዬው ሳልሆን ሆኘው ስለምጽፈው በስሜቴ ውስጥ ያሉ ነገሮች ሁሉ በአብዛኞቹ ሴት እህቶቼ ስሜት ውስጥ እንደሚኖር አስባለሁ። የድምፄ ምት ከማህጸኔ ይነሳል። የመንፈሴ ትንፋሽ ደግሞ የልቤን ክናድ ይንተራሳል።

መንፈሴ ሰግሮ ሁነኛ ማረፊያ ወይንም ድልዳል ሲያጣ ትካዜ ሲዋኝበት የኖረ ቢሆንም አሁን ከዘሃበሻ ጋር መታደሙ የመገለው ስቃይ ተግ ብሎለት ህምሙም ታግሶ፤ በስክነትና በቅደም ተከተል ማሰብና ከረመጥ ላይ የበቀለውን ጸጋ ማቆለማመጥ ጀመርኩኝ።

ስለሆነም እኔ ራህብ ላይ ሆኜ ሌላ ራህብተኛ ለማስናገድ አቅሜን በሙሉ ቀን መርቆ የሰጠኝ አምላኬ፤ ምክንያት ፈጥሮ የመተንፈሻ ቀዳዳ ለፈቀደለኝ የዘሃበሻ ድህረ ገጽ ምስጋናዬን በሐሴት ጠልፌ ተቀበሉኝ በማለት እነሆ ጀመርኩኝ … /ሁሉ በገደበኝ ሁሉ ባቆረጠኝ ሰ ዓት ነበር ዘሃበሻ ባዕቴ የሆነው በ2013/14/15 አጋማሽ/

·       ሴቶች የመኖር ቋንቋ ናቸው። የኑሮ አይደለም። ኑሮ ቅርንጫፍ መኖር ግንድ

ሀ.   ሴቶች ችግርን ለመፍታት ቁርጠኝነት ጠረናቸው ነው።

የሴቶች ተፈጥሮ መግለጫ ከሆኑት መሰረታዊ ጉዳዮች እንብርቱ ሴቶች ችግርን የማይፈሩ ደፋሮች መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኝነትን በአጽህኖት የተካኑ ከመሆናቸው ላይ ነው። እንዲያውም ሴቶች ችግር ወደ አለበት ፈጥነው የሚገሰግሱ መሆናቸው የተፈጥሯቸውን ብቃት ያመሳክራል። ስለዚህ ሴቶች ማናቸውንም ችግር ከቤት እስከ አደባባይ ያለውን ሁሉ አሳር ተዳፍረው ከመፍቻው ቁልፍ መፍትሄ የሚያስገኙ ድንቆች ናቸው። 

የፈለገ ዓይነት፣ በፈለገ ሁኔታ፣ በፈለገ መጠን፣ በፈለገ ጊዜ፣ በፈለገ ግንኙነት፣ በፈለገ ልኬታ፣ ችግር በቅሎ ይጠብቃቸው አብዛኞቹ እንደ አመጣጡ መክተው፣ መንገዱን ጠርገው ለጥ ያለ አስፓልት በመጥረግ ወጣ ገቡን የሚታድጉ የመፍትሄ ማሃንዲሶች ናቸው። አቅርቧቸውና ፈትኗቸው ወኔው ካላችሁ …. /ውዶቼ አሁን ህሊና ያለው ሙሴ ኢትዮጵያ ስላገኘች እንፈታትን ብሎ ቁልፉን አሰርክቦናል፤ መሆን ደግሞ ሃላፊነቱን የተሰጣቸው ሴት ሊሂቃን ድርሻ ይሆናል።/

ለዚህ ማገናዘቢያ ይሆን ዘንድ …. እኔ በተመስጦ የኩርድሽ ሴቶችን የጫካ ትግል ይመስጠኛል። ወንዶች ከተማ ሆነው የሎቢ ተግባር ይሰራሉ፤ ሴቶች ጫካ ሆነው የጀግንነት ግሩም ድርጊት ይከውናሉ። ጦር አዛዧ ሴት፤ የግንኙነት ኃላፊዋ ሴት፤ የሎጅስቲክስ ስምሪት አስተዳዳሪዋ ሴት፣ የጓድ መሪዋ ሴት፣ አዝማች ሴት … ወዘተ
ከትንግርት በላይ ነው።

ጥንካሬያቸው፣ ብርታታቸው፣ ትብብራቸው፣ ጽናታቸው፣ የጫካ ህይወት ፍቅራቸው ንዑድ ነው። አምላኬን የምለምነው እንዲህ እንደ ጨው ዘር የተበተነውን ለእነሱ ቅንነት ሲል እንኳን በጉልበተኞች የተወሰደባቸውን መሬት አግኘተው ለሀገራቸው እንዲበቁ ነው። የአርበኝነት ውሏቸው ሰው መሆንን ይመረምራልና። ዓላማቸውን አሳክቶ አርበኛነታቸውን ለፍሬ አብቅቶ መሬት አልባነት ከትሞ እማዊ የተግባር ሰውነት ምን ያህል ፍሬ ስለመሆኑ በ21ኛው ምዕተ - ዓመት በዓለም ዓቀፍ ዕውቅና እንዲያስጌጥ የዘወትር ፀሎቴ ነው።

ለ.  ሴቶች ስልት ተፈጥሯቸው ነው።

የሴቶች የአያያዝ ጥበብ በስልት ነው። ስልቱ ደግሞ ሩቅ ዓላማን ሰንቆ የቅርብ ፍላጎትን ሳይዘል አስማምቶ፣ አስመችቶም የመከወን ጠንካራ አቅም አላቸው። አሁን የቅርብ ምሳሌ ባነሳ በሳውዲ ላይ የተፈጠረው ችግር ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት መረባረቡን ሴቶች ከልብ ያምኑበታል። ነገር ግን ይህ የመከራ ዘመን የሚመክንበት ጉዳይ ላይ በርትቶ መስራትን ያሰምሩበታል። 

ለዚህም ዕድሉ ቢኖራቸው ቅደም ተከተል ሰጥተው የአቅም ክፍፍሉን አሳምረው ይቀይሱታል እንጂ ሳቢያዎች በሚፈጥሩት ውጤቶች ላይ ብቻ ጊዜያቸው እንዲላ አይፈቅዱም። በፍጹም። ነገም ሌላ ችግር በባሰ እንደሚበቅል ጠንቅቀው ያውቁታል። ስለሆነም አትኩሮታቸው በሳቢያ ላይ የሚያጠነጥን ሳይሆን ይልቁንም በምክንያት ውጤቶች ላይ የተሳላ ነው። ተግባባን? የችግሩ መፈልፈያ መድረቅ አለበት። መነቀል አለበት - የሥራዓት መሰረታዊ ለውጥ ላይ አብዝቶ ከተሰራበት አብዛኞቹ የዛሬ ችግሮቻችን በሂደት ያስተካከለዋልን።
      
ሐ. የሴቶች ቀድሞ የመተንበይ አቅም ዓይነታ ነው።

አንድ ጊዜ በ90ዎቹ አጋማሽ ውጭ ሀገር አንድ የሥራ ባልደረባዬ፤ አለቃችን ሳይኖር አለቃዬም ነበር ለነገሩ  አዛውንት ጋዜጠኛ ታዋቂ በድንገት ሞቶ ቀብሩ ላይ ነበርኩኝ። አስከሬኑ ተቃጥሎ በትንሽ ነገር ተይዛላች። እኔ እምጠብቀው ሳጥን ስለነበረ ከአጠገቤ ላለው ባልደረባዬ የተግባር መምህሬም ነው፤ መቼ ነው አስከሬኑ የሚመጣው? ስል ጠዬኩት ሂደቱን አጫወተኝ። 

ባለቤቱ የውጭ ዜጋ እንደ ነበረች እንደ እምነቷ፣ ቦታም ገንዘብም ለመቆጠብ እሬሳው እንዲቃጠል መወሰኗን አብራርልኝ። ይህን አሰቃቂ  ትዕይንት ስሰማም ሳይም የመጀመሪያ ቀኔ ስለነበር አካባቢው እራሱ ቀፈፈኝ። ከአጠገቤ ደግሞ አንዲት አባባ የመሰለች ውብ ሴት እጅግ አምርራ ታለቅሳላች። ወደ እሷ ዞር አልኩኝና ጠጋ ብዬ እንድትታገስ ነገርኳት። ከዛ ምን እንዳለችኝ ታውቃላችሁ“ለራሴ ነው የማለቅሰው“ እንዴት? ስል ጓጉቼ ጠዬኳት። ለዛውም ሰው ፈቅዶ ካልነገረኝ ስለምንም ነገር መጠዬቅ አልወድም።

… ብቻ ጠዬኳት „ እኔ ተሰደድኩ፤ የስደቱን ፈተና ስላልቻልኩት የውጭ ዜጋ አገባሁ፤ ወለድኩኝ። አዬሽ አይደል መመለሻ የለኝም፤ አስከረኔም የሀገሬ አፈር አያገኝም - በሁለት ምክንያት። ቀድሜ ብሞት ባለቤቴ የሚያደርገው ይህንኑ ነው። እንደ ባህሉ ያቃጥለዋል። ልጆቼም በዚህ ውስጥ ስለሚያድጉ ያፀድቁለታል አለችኝ“ ሁሉ እንዲህ ባያደርግም ዛሬ ላይ ሆኜ የትናት ትንበያዋን ያ ሁለቱ የተፈጥሮ መስኮቶቿ ተከፈተው ገድቡን ጥሶ ሙላቱን ይለቀው የነበረው ፍላሎት ዛሬ ላይ በምልሰት ስቃኘው ሚስጢሩ ተገለጠልኝ። 

ሴቶች ነገን የማየት አቅማቸው ብጡል* (ጥንካሬው የደመቀ ልዩ) ነውና። ይህን ዘመን በድርብ ስመዝነው ደግሞ አይደለም ውጪ ሀገር … ሀገር ውስጥም መሰሉ ሊፈጸም እንደሚችል ምልክቶች ይጠቋቁማሉ። አስፓልቶች የኢትዮጵያ መሬት አይመስሉም፤ የገጠር መንደሮችም እንዲሁ …. ተወራላች ሀገራችን … በዕንባ.

… በዛው የቀብር ሥርዓት ያቺ ፔርሙስ በምትመስል ሰፋ ባለች ጎድጓዳ ማህል እጅ ላይ ተቀምጣ የነበረችው አፈሩ ጫረጫር ተባለላትና እንደ ሀገሬው ባህል ወጉ ደራሳት። መሬቷ አንድ ስንዝር ብትሆን ነው። ያን ዕለት ከጎኔ ላለው ለማከብረው የቅርብ አለቃዬ ጠጋ አልኩና እኔ ደግሞ „በሰው እጅ የሞተ ይመስለኛል አልኩት።“ በጣም ፍጥነት የተሞላበት ነገር ነበር የተመለከቱት ነበርና። 

እሱም “እናንተ ሴቶች መቅደም ተፈጥሯችሁ ነው። አብረን በኖርንባቸው ወቅቶች የታወቀ ምንም ዓይነት በሽታ አልነበረውም። ሁልጊዜም የህክምና ቁጥጥር ያደርጋል። ባለቤቱን ስለሁኔታው ደውዬ ስጠይቃት በመረጋጋትና  በአሸናፊነት መንፈስ ነበር ያጫወተችኝ። 

አሁን አንቺ ይህን ስትይ ግን የተሰወረ ግን ልንድርስበት ያልቻልነው ነገር አለበት ብዬ አስባለሁ። ለዚህም ይሆናል ብቻዋን ወሰዳ እንዲቃጠል ካስደረገች በኋላ የቀብር ሥርዓት ላይ ብቻ እንድንገኝ የነገረችን“ አለኝ። ከዚህ ላይ እኔ ትንቢተኛ ነኝ ለማለት አይደለም። ሴቶች ደራሽ ችግሮችን በተለያዬ አቅጣጫ እንደሚያዩት ለማጠዬቅ እንጂ …

ሴቶች ንደ ወረደ የሚያስተናግዱት ምንም ነገር የለም በፍጹም። ይበልቱታል። የበለቱትን ክፍል ሰጥተው ይደለድሉታል። የደለደሉትን ንክኪና ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ ከአገናኙ በኋላ ይፈታትሹታል በዬአቅጣጫው፣ በዬዞኑ። ፍተሻው ጠንከር ያለ የበራ ፊድ ባክ ይሰጣቸዋል። ያ ፊድ ባክ ዕርገታቸውን ያሳካላቸዋል …. እህታችሁን፤ የትዳር አጋራችሁን፤ እናታችሁን ለናሙና ወስዳችሁ መመዘን ይቻል ይመስለኛል።

መ. ሴቶች በተፈጥሯቸው የተደራጁ ናቸው።

በሙያዬ አደራጅም ስለነበርኩ ብዙ ሳልጓዝ ብዕሬ በተወሰነ ጉዳይ ላይ ብቻ እንድታጠነጥን እለምናታለሁ። መደራጀት ከዬት የሚጀምር ይመስላችኋል። ከማህል? ከጠርዝ? ከማዕዘን? ከቀኝ - ከግራ - ከፊት - ከበስተኋላ? የሴቶች መደራጀት የሚጀመርው ከመንፈሳቸው አስኳል ነው። እንቅስቃሴያቸው „ሀን“ ዘሎ „ለን“ አይጀምርም - በፍጹም። እራሳቸውን አደራጅተው ነው የሚኖሩት። የሴቶችን እንቅስቃሴ የሚመራው በተደራጀ በተሰናዳና በተከወነ መንፈስ ነው። 

ስለዚህ ከመደራጀት የሚገኘው ዕሴት ሁሉ ተጠቃሚ ናቸው። በዓለም የመጀመሪያው የድርጅትን ጥቅም አውቆ ጥቅም ላይ የዋለ ፍጥረት ቢኖር ሴቶች ናቸው። በሴቶች ህይወት ውስጥ ምን ያልተዳረጀ ነገር አለና? ስለሆነም አቅማቸውን በሥርዓት መርተው ለአቀዱት ዓላማ ጥቅም ላይ በአግባቡ ያውሉታል /ኢንቤስት/ ያድረጉታል …. ኃይላቸው ብክነት የለበትም። የፍሬ ነገሩ ኩላሊት ያለው ተዚህ ላይ ነው። 

ኃይላቸው ጥግና መጠለያ ምንጊዜም አለው። አሁን በዚህ የነፃነት ትግል የሚባክነውን ገንዘብ? ጊዜ? የሰው ኃይል ቁጭ ብዬ ሳዬው የነፃነት ራህብተኛ ነኝና እስላለሁ … እንደ እኔ ሚሊዮኖችም …. አቅም እኮ አድመጭ ያጣ ቅምጥ ሃብት ነው። ለነፃነት ትግሉ ግን ጆሮም የለም ጊዜም በኩርማን ተቆንጥጣ … ለዛው ከተገኘ … በጠብታ …. ስለ አቅም ፍልስፍና ያልተደረሰበት ብክነት።

ሠ.       የድምጽ እንቁጢ የሴቶች መክሊት።

ካለ ዓመት የማትመጣው ብሄራዊ አባባችን እንቁጣጣሽ ትባላለች። እንቁጢ ተናፋቂ ናት። እንቁጢ ተስፋ ድውለቷ ነው። እንቁጢ አዲስነት ቅልጥሟ ነው። እንቁጢ ፍቅር ብርንዷዋ ነው። ታጥቦ የፈጠራት፣ ተናፍቃ ትመጣላች ሳትጠገብ ደግሞ ሽው …. እሷን ባደረገኝ።

ሴቶች ድምፃቸው በደመቀ - በለሰለሰ - በሰከነ  - ልዩ ቃና የጣፈጠ ነው። ደወሉ የመንፈስ ድህነት ነው። ምቱ … የተዘጋ ይከፍታል። የታመመ ይፈውሳል። ተስፋን ላጣ በገፍ ተስፋን ይቸራል። የደከመን ያበረታታል። የጎበጠን ያቃናል። መፍቻ ያጠን ያፍታታል። ምን የማይሆነው አለ? የሴቶች ድሪያማ ውብ ቅላፄ ይጠጣል።  ይጎረሳል። ይዋራረዳል። ያግራል። ያፍለቀልቃል። ያጽናናልም …. ይብቃ አይደል ወራጅ አለ በሉኝ።

ለማንኛውም ይህ ሃብት ግን ከቁጥር የማይገባ … ከፋይዳ የተዘለለ፤ ከመርኃ - ግብር የተፋቀ የተረሳ ጸጋ ነው። ዘንቦ ተባርቆ የሚዲያ የራዲዮ ሆነ የቴሌቪዥን ሰራተኛ ካልተሆነ ምክነት አብዝቶ የሚጨፍርበት አንጡራ ሃብት። በዬትኛውም ቤታ የአሸናፊነት መንገዱ ሁሉንም አካባቢ ዳስሶ በታቀደና በተደራጀ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ኢትዮጵያዊነትን መታደግ ሲቻል … ፀጋው ውሃ ሲሄድበት የከረመ አለት ሆኖ ኤሉሄ አሉሄ ይላል …. ሞገዳማ ተንቀሳቃሽ ድምጽ የአጥቂነት ትጥቅ ነበር ላወቀበት ግን እንዴት የታነቀ እውነት ….

ረ.  እናትነት።

ይህ እንግዲህ ለተዕባት የተከለከለው መንገድ የራሳችን አንጡራ ሃብት ነው። ተቀናቃኝን በራሱ ጊዜ የመከተ። በፌክም ከማስመሰል በስተቀር መሆን የማይቻልበት ለሴቶች ብቻ የሰማዩ ዳኛ መርቆ የሰጠን የጸጋዎች እጬጌ ነው። 

እናትነት የድርብርብ ፍቅር ክታብ። እናትነት በልቡ ውስጥ ልብ ነው። የእናትነት ነገር ሲነሳ ወላዊና አውንታዊ እድምታ ላይ እንደርሳለን። እናትነት ሚስትነት ነው። የጡት ባህረ መዝገብ ሲገለጥ እናትነትን ሚስጢር የሚለው ቃል ሊገልጸው የሚችለው አይመስለኝም። የተከደነ ታምር ወይንስ የገድላት ቅዱስ መጸሐፍ ልበለው። እናትነት አይደለም ለሰው ልጆች እንሰሳ ላይ እንኳን ሲታይ ታምሩን የሰው ልጅ በጥበቡ ሁሉ ያልደረሰብት መክሊት ነው። እናትንት በተን ግን ጠቅላል ያሉ ሰንደቅ ቃሎችን ወይንም ሃብታቱ …

አለሁነት …. መቅድምነት …ቤተሰባዊነት … ታማኝነት … ተሳታፊነት …ቅርብነት … እቅፍነት …ተከታታይነት … አራራቢነት … አቀናባሪነት …ቀጥተኝነት … ዕንባመነት …ማራኪነት … ቻይነት … መሪነት … ሃላፊነትን በፈቃድ መውሰድ … ርህርህና … ስብዕዊነት … ሚዛናዊነት … ፍቅር … ቅንነት … አዎንታዊነት … አርቆ አሳቢነት … መምህርነት … ማህበራዊነት … ታማኝነት … ግልጽነት … ቀጥተኛነት … አድናቂነት … አክባሪነት … ተንከባካቢነት …. ኪዳንነት …. ለችግር ቀድሞ ደራሽንት … አጉራሽነት … አጽናኝነት … እውነትነት … ፈጣንነት … ባለሙያነት …. መሪነት …  አስተዳዳሪነት … መስዋዕትነትን ፈቅዶና ቆርጦ ተቀባይነት … አደራጅነት … አስተባባሪነት … ተጠያቂነት … ለጋስነት … ቸርንት …. አድማጭነት … አዛኝነት … ፈቃደኝነት … ቀዳሚነት … ኑሮነት …. ሁለመናነት … የሁሉዬነት …. መሆንነት …

እያንዳንዱ ሥነ ተፈጥሯዊ ገፀ ባህሪ ደግሞ የራሱ ጭብጥና አምክንዮ አለው። እንደ እራሱ የመኖር ነፃነትና ከሌሎች ጋርም በመፈቃቀድ የሚያስተሳስረው ወርቃዊ ሃዲድም አለው። ድንበርና ወሰንም። ይህ ተፈጥሯዊ የገነት ህይወት ያለው የጸጋ ጅረት የራሱም ሥነ ምግባር፣ የራሱ አርትና ጣዕም አለው። ዬራሱ ዜማና ቃና አለው። የራሱ ማንነትና መግለጫ አለው። የራሱ አናትና ልብ አለው። የራሱ ፋይዳና ዕሴት አለው … የራሱ መተዳደሪያ ደንብና ሰነድም አለው። ይህ ሁሉ ተዝቆ የማያልቅ ጥሪትና እምቅ ቋሚ ሃብት ተዘሎ ይታቀደላል ሁል ጊዜ ግን ታቱ ዥግራ …

ሰ.  ሴቶች ብልህነት ወስጣቸው ነው።
      
የሴቶች ጸጋ ልጥፍ አይደለም። ከውስጣቸው በመሆን ያታተመ እንጂ። ሴቶች እጅግ ሲባዛ ብልሆች ናቸው።  በእያንዳንዱ የዓለም ታዋቂ ወንድ በሉት፤ ጀግና ሳይንቲስት በሉት፤ ተመራማሪ በሉት ተወዳጅ መሪ፤ በስተጀርባ አንዲት ብልህ ሴት በቅርበት አለች። 

አብዛኛውን ጊዜ የትዳር አጋራቸውን የሰሙ፤ ያዳመጡ፤ የተከበሩ መሪዎች ሆኑ ለሽልማት የሚበቁ የስኬት ቁልፋቸው በእጃቸው መኖሩን ይቀበሉና ያረጋግጡ ። እርማጃቸውን አንድ ብለው ከመጀመራቸው በፊት። የሁሉም ነገር መፍቻ ስልትና ብልሃት የመዳፋቸው እርስና እርት ሆኗልና እንኳን ደስ አላቸው።

የንጉሦች ንጉሥ የአፄ ቴውድሮስ ጠቅላላ ታሪክ በዛ መልክ የተጠናቀቀው እቴጌ ምንትዋብ በሞት ስለተለዮዋቸው ብቻ ነበር እንጅ እቴጌ በህይወት እያሉማ ድል በድል እዬተነባበረ የአሸነፊነትም የመሪነቱ እርክን አንቱ ነበር። የዐጤው መንፈሳቸው በድል ሰረገላ ላይ ያሸበሽብ ነበር። እቴጌ ለንጉሡ መዳህኒት ነበሩ ….  በብልህነት ሴቶች ተዝቆ የማያልቅ ፍጹም ልዩ ሥጣታ ነው ያላቸው። ደግሞም ስልታቸውን ተክትሎ ለሚጓዝ ህልሙ ቅርብ ነው። ድሉም ከፊት ለፊቱ ….

እስቲ ጠይቁልኝ እርቃ ሳትሄድ
እቴጌ ተዋበች ሚስትናት ገረድ
እጅግ „ሥራ አዋቂ“ ትናንትና ሞተች
መዳህኒቱን „ምሳ“ ታበላኝ ነበረች።

/ምዕራፍ 19 ከዐፄ ቴውድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ መጸሐፍ የተወሰደ።/  እጅግ „ሥራ አዋቂ ይህ ኃይለ ቃል የሴቶች ሥነ - ተፍጥሮ ተግባር ስለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ዕውቀታዊ ወስጥንም አሳምሮ ይገልጠዋል። ሴቶች ለቧልት ጊዜ የላቸውምና። ሁለተኛው „ምሳ“ ታበለኛለች የሚለው ሰምና ወርቅ ነው። ሰሙ የማዕከላዊ የምግብ ክፈለ ጊዜን ማዕደኝነት ሲገልጽ፤ ወርቁ ሁለት ጥንድ ትርጉምን ይዟል። 

አንደኛው ቀደም ባለው ጊዜም ሆነ አሁን በገጠሩ ሀገረሰብዕዊ መዳህኒቶች ከተክል ሥር ወይንም ከዕፅ ተቆፍሮ የሚገኝ ስለመሆኑ፤ ዶሱ ወይንም መጠኑ በጣት ተለክቶ እንደ ዕድሜው መሰጠቱን ይገልፃል። ስለዚህ ዐፄ ቴወድሮስ ህምም ሲሰማቸው ፈርማሲያቸው፣ ሃኪማቸው ከቤታቸው ነበሩ። እመቤት እቴጌ ምንትዋብ። 

ሌላው የወርቁ መጠነ ሰፊ ክፍለ አካል በዘመናችን ቁብ ያልተሰጠው ፍሬ ዘር ወይንም ነገረ ሚስጢር ግን ዐፄ ቴውድሮስ በንግሥና ዘመናቸውም ሆነ ሃሳባቸውን ሲወጥኑት በልጅ ካሳነት ዘመናቸው ጀምሮ አስተዳደራዊ ብቃታቸው  ከእቴጌ ይቀዳ እንደነበር ለማጠዬቅ ነው።

በሌላ በኩል የአልጋቸው ጽኑ ጠባቂ የፕሮቶኮል ሹማቸው እቴጌ መሆናቸውን ያመሳጥርልናል። ከዚህ ላይ የጉዳዩን ኩላሊት ከልብ ስንፈታትሽው ደግሞ ቀደምት ንጉሦቻችን የሴቶችን ተፈጥራዊ ልክ የማይወጣለት ብቃት ለመዳህኒትነት፣ ለችግር መፍቻነት ለጭንቅ መበተኛነት፣ በአግባቡ ጥቅም ላይ ያዋሉና በዚህም ፈውስና ድህነት ማግኘታቸውን ቁልጭ አድርጉ ያስተምረናል ….

ከዚህ ጋር በተያያዘ የደህንነት እና የልጅነት ሚስጢርን በእናትነት ፀጋ ጎልምሶ የምናዬው ክፍል ደግሞ እቴጌ ሲሞቱ የነበረው አመክንዮን እና ያስከተለው ቀውስን ነበር። የዛሬዎችስ? …. ከታች ከሥር ጀምሮ ሹሞች ብዙም ሳያውቁት ቀርተዋል ማለት አልችልም። ወያኔ ሃርነት ትግራይ ብዕርን እንደ ጦር  እንደሚፈራው ሁሉ የተደረጃውን የሴቶችን የመክሊት ብቃትና ተሳትፎ 95% የሚሆኑ ተብእቶች አብዝተው ይፈሩታል። የእውነት አንመጣጠንም …  ምክንያቱም ጸጋው ሰው ሰራሽ አርቲፊሻል ወይንም ቅብና ልብጥ አይደለምና …

ከዚህ ጋር እቴጌ ለባለቤታቸው አድልተው ወደ ትዳራቸው ፍላጎታቸው ቢመዝንም እንደ ቤተሰባዊ ጸጋቸው በሴት ልጅነታቸውም አባታቸው በነበሩበት የግዞት ዘመን ሁሉ ከጎናቸው ነበሩ፤ ባላቸውን ሳያስከፉ በጥንቃቄ የልጅነት ድርሻቸውን በስውር ተወጥተዋል። ሊደረግላቸው የሚገባውን ተግባር ሁሉ አድርገዋል። እጥፍ ጸጋ። ሴት ልጅና ወንድ ልጅ ለወላጆቹ እኩል ተግባር ላይ አይገኙም። በቤተሰብ አያያዝና ክህሎትም ቢሆን  እኩል የመሆን አቅም ፈጽሞ የላቸውም - ፈጽሞ ። ለዚህ ነበር ራስ ዐሊ ልጃቸውን ሞት ሲነጥቅባቸው …. እንዲህ ብለው ቅኔውን የዘረፉት …. የጎደለ ሞይነት - ሁለመናናት … ሁሉዬ ሴት!

ጠጅ አማረኝ ስላት ማሩን ትሰዳለች
(ለተጠማ ሆነ ለአምሮት ደራሽነት)
ራበኝም ስላት እኽሉን ታስጭናለች
(ለራህብ ፈጥኖ ደራሽነት)
በረደኝም ስላት ሸማ ትሰዳለች     
(ለታረዘ አልባሽነት)
ሌባዬ ተይዛ ባልጋ ትሄዳለች       
(የድህንነት ጥበቅ ተግባር በስውርና በጥበብ)
የት አባቷን ዐውቃ ታሳዝነኛለች   
(ችግርን ተጋሪ ሲርቅ ረመጥ ስለመሆኑ)
የጣቴን ቀለበት አንተ አድርገው ካሳ
(ኪዳንህን ጠብቅ፤ ጥብቅ አደራ፤ ጽና!)
በኔማ ጣት ገብቶ አስጨነቀኝሳ
(የሃዘኑ ቋያ ረመጥ ልኬታ አለመኖሩን)
ያመላክተናል … ( ከዐፄ ቴወድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከተክለ ጻድቅ መኩሪያ መጽሐፍ ገጽ 20) የተወሰደ

ሴት ልጅ - እናት፤ እህት - ጓደኛ - አክስት -  ስትሆን ጣና ዘገሊላ ነው ….. ዛሬስ አቶ ወንዶች ይህን የማመሳጥር አቅም አላችሁን?

·       ዛሬስ ስል በ2013 ማለቴ ነው። 2018 እማ አናባቢያችን አግኝተን ከዜግነት ጋር ተገኘን።

ሸ. የተረጋጋ መንፈስ።

ይህ የሴቶች ተፈጥሮ ተግባር ላይ የሚውለው በትዳራቸው፤ በእናትና ልጅ ዙሪያ ወይንም በስብዕዊነት ዙሪያ አይደለም። ስለምን? በዚህ ዙሪያ ለሚመጡ ሰቀቀኖች ሴቶች ስሜታቸው ስስ ነውና። ነገር ግን ኃላፊነትን በሚጠይቁ የመወሰን የመቁረጥ ሂደቶች፤ ሂደቶችን ተከትለው በሚመጡ አጣብቂኝ ፈተናዎች ዙሪያ ሴቶች የሰከነና መሬት ያዬዘ የተረጋጋ መንፈስ አላቸው።

በመጀመሪያ ነገር ጉዞውን ሲጀምሩትም ይመጣል ብለው ካላሙት ችግር ውስጥ ያፈነገጠ አይሆንም። ይህም ማለት የህሊና መሰናዶው ቀድሞ ድርጁ ነው ማለት ነው። ስለሆነም በታቀደ እንቅስቃሴ ውስጥ የተጠበቀን ፈተና ለማስተናገድ ሴቶች ተረጋጋግተው የማስተናገድ ሆነ የመራመድ አቅማቸው ማገር - ፒላር ነው። በተፈጥሮ ሊቅነት … ሥጦታ ከኤልሻዳይ ትምህርት ተመክሮ ሲታክልበት እንዲሁም የተከበረ ተደማጭነት ሲያገኙ … መስፈርቱ ዕሴቱን ለመለካት አይችለውም … ዝልቅ ነዋ!

በ.  ማስተዋል ሴቶችን ይገልጣቸዋል።

ሴቶች አጋጣሚዎች የሚመራቸው ፍጥረቶች አይደሉም። ወይንም ሴቶች አጋጣሚን ተጠልለው አያቅዱም። መርኃ ግብራቸው እራሱን የቻለ እና ግብታዊነት የማይመራው በመሆኑ አትኩሮታቸው በጭብጡ ማዕክላዊ ዙሪያ ስለሚሆን ለግቦች ቅርብት ሆነ ለውጤቶች አስተማማኝ ግብዕት ናቸው። የሴቶች የፍላጎት ትልም ለወጀብ ሆነ ለአውሎ የተጋለጠ አይደለም  … እሳተ ጎመራን የመቋቋም ብቃቱ መካች ነው።

ተ. ነፃነት ናፈቂነት

ይህ የሴቶች በኽረ ህልም ነው። ምክንያቱም ውስጣቸውን ጠንቅቀው ስለሚያውቁት ድርሻቸውን ለመወጣት ተድቦልቡሎ ግን ተስውሮ የሚፈታታናቸውን የትምክህት ቲወሪ የሚመክት ነፃነት ይሻሉ። ለዚህ ነፃነትም ትርጉም ያለው፣ ፍሬያዊ ትርጉምነትን በማስቀድም በግንባር ቀደምትነት ይጋፈጣሉ። እርግጥ ዘመንና ጊዜ የሚጠበቁ ነገሮች እንዳሉ ቢገነዘቡም፤ አጋጣሚዎችን ሳይዘሉ የምልክት ደወል መደወላቸውን ግን አያቋርጡም። 

ከናፍቆታቸው ጋርም ለመገናኘት ተግባር እንደሚያሸንፍ ስለሚያምኑ ድምጻቸውን አጠፍተው ከድርጊት ጋር ይባትላሉ - ይመስናሉ … በታሪክ ጊዜ የሌላቸው ቢዚ ፍጥረቶች ቢኖሩ ሴቶች ናቸው። በሁሉም ቦታ በተጫነ ጉልበታም ትምክህት ሥር ወድቀው ግን ተሳትፏቸውን በትጋት ይወጣሉ። እንግሊዘኛው ስለሚገልጽልኝ ሙሉ ፓኬታቸው ትንታግ ነው። ለዚህም ነው ዕርሴ መጠበቅን ጽላቱ በማድርግ ሴቶች ጥሩ ነገር አላቸው ጊዜ እሲኪሰጣቸው ድረስ ጠብቀው ይይዙት ዘንድ  እለምናቸዋለሁ ያልኩት። 

 ጠቅለል ይበል …

የተፈጥሮ ውብ ጥሎሽ የሴቶች ብቃት ነው። ዝም ብዬ ቁጭ እልና ሴቶችን ፊት ለፊቴ አስቀምጬ ሁለመናቸውን እፈትሸዋለሁ። እንደ ሰርጀሪ ነገር …  ሁለመናቸውን አስተውለዋለሁ። እያንዳንዱን ቅመማዊ ተፈጥሮ እዬነጠልኩም አናግረዋለሁ። ሁለመናቸውን እዬተነተንኩም እመካበታለሁ። ሁለመናቸውን እያፍታታሁ እጽናናባቸዋለሁ

ሁለማናቸውን እያስተዋልኩ አደንቃቸዋለሁ። ሁለመናቸው እዬዳሰስኩ እበረታባቸዋለሁ - እውዳቸዋለሁም። ሁለማናቸውን በዓይኔ ውስጥ አስቀምጬ መንፈሴ እንዲደለው ፈቅጄ ነገን አልመበታለሁ። ቀደም ባለው ጊዜ „ እረኛ ምን አለ“ ይባል ነበር።

አሁን ሰሞኑን የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ፍላጎትን ሳጠና ከአንድ ጥቅል ፍላጎት ላይ ደረስኩ“ጣይቱ“ የሚለው አዲሱ  የአንስት ወላዊ፣ ትንቢታዊ፣ ፍላጎታዊ፣ ፈቃዳዊ፣ ጠያቂያዊ … ዜማ … እርገቱ በታዳጊ ወጣት የተስፋ ጠቅላይ ሚ/ር ቃለ ምልስልስ ሲጠናቀቅ ጨዋው ህዝባችን፤ ፈረኃ እግዚአብሄር ያለው ህዝባችን፤ ለእምነቱ ዶግማና ቅኖና ሞቱን የሚመርጠው ህዝባቸን አንድ ነገር መንፈስ ቅዱስ እንደ አቀበለው ልብ አልኩኝ …. እንኩይ ….. የናፈቀው የሰከነ ፖለቲካዊ አመራር ከአንስት ነውና … /ይህም በ2018 ትንቢቱ መሰረቱን አግኝቷል። የጣይቱ ሙዚቃ/

ከዚህ ጋር በተያያዘ ደግሞ መራኂት አርቲስት አለምጸኃይ ወዳጆ „የጣይቱን የሥነ - ጥበብ ማዕከል“ አሜሪካን ላይ አደራጅታ ጥበብን ተጠዬቅ ስትል፤ ቀድሞ የታያት ወርቅ እንደነባራትም ተገለጠልኝ።

 …. እሷም እኮ አለች … የጀመሪያው የተውኔት ባላሙያዎች ማህበር ብሄራዊ ሊቀመንበር … ኢሳት ይመስገን ተዚህ ላይ። … በሶስተኛ ጉባዔው ላይ ገላጭ አድርጓት አይቻለሁ፤ ግን ይህ በቂ አይደለም … ማስታወሱ መልካም ሆኖ ግን ሩቅ መጓዝ፤ ትብትቡን ፈቶ ቅኔዊ ውስጧን በቋሚነት ጥቅም ላይ መዋል ይገባል … ስብሰባ እኔ የምተረጉመው ገብያ በማለት ነው።


እናቴ ስትነግረኝ በልጅነቷ ጓደኛ ታበዛ ነበርና መሞታቸውን አውቀው፣ ሰኔልና ቹቻ አዘጋጅተው፣ ልጆቻቸውን መርቀውና ተሰነባተው ጸሎት ቤታቸው በሰላም ያረፉት ሊቀ - ሊቃውንቱ አያቷ መላክ ብርኃን ልሳንወርቅ ኃይለ ሥላሴ ቤተሰብ „ገብያነሽ“ ያላትን አስቀሩት። ስለምን? ገብያ ተሎ ይፈታል ብለው። ልጄ ዕድሜዋ ተግባሯም አጭር ይሆናል፤ በማለት ሌላ ድንቅ ስም አወጡላት። 

አሁንም ሰው ወዳጅ ስለሆነች ተከባ ተከብራም አለች በባዕቷ። ምን ለማለት ነው እጅግ የፍቅሯን ንጥር ቅቤ ጠጥቶ ባደገው የልቤ ሙዳይ ውስጥ ብቸኛ ቦታ የሰጣት መራኂት ዓለምጸኃይ ወዳጆ … ቶሎ ለሚፈታ ጉባዔ ብቻ አትታጭ ዘለግ ዘለቅ፤ ትርጉም ላለው ተሳትፎ፤  አቅሙ ጉልበታም ለሆነ ቦታም ትታሰብ እንላለን … እንጮኃለን …. ተፈጥሮ እንዲያምርበት ማጣፈጫ አምላክ ፈጠረለት ሴትን

ሉሲ የ21ኛው ምዕተ ዓመት የሰው ልጅ ምንጭ ሆነች … ሳይንስም የኢትዮጵያዊነትን ሚስጢር ሳይነቅፍ ከሃቅ ጋር እርቀ ሰላም አወረደ። አመሳጠረ። ታዲያ ድንቅነሽ ማለት እኮ ሴት ናት … ተዚህ ማዕከል ይኮንና በኩነኔ ተፈርጆ ጋህንም የተወረወረው የሴቶች ብቃት ባሊህ ይባል እንላለን። የተከረቸመው በርም ይነቅነቅ እንላለን ///  እኔና የተከበረችው ብዕሬ - መንፈሴም ይታከል ….  ከዓውደ ምህረቱ ሆኖ  እንቢልታውን እያስነካ ውስጡን ላከ … ለጆሮ ….  

ውዶቼ፤ ለነበረን የመደማመጥ ሸጋ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ዘንካታ ምስጋና አቅርቤ ለዛሬ ልሰናበት። ቸር ያሰንብተን፤ ቸር ያሰማን አምላካችን አሜን።


ይቅርታ በትህትና አክብሮትም ታክሎበት አንዳንድ ቦታ ላይ እንግሊዘኛውን ቃል ወስጃለሁ፤ ብችል ጀርመንኛው የበለጠ ውስጤን ይገልፀው ነበር። ውስጤ በአማርኛ ቋንቋ አቅም አንሶት አይደለም ፍላጎቴን የበለጠ አስረግጦ የሚገልጸው እንግሊዘኛው ሲሆንብኝ ነበር … ትንሽ ዲቃላ ነገር የሆኑት ገለፃዎቼ …

ሴቶች የድርጊት ጀግኖች ናቸው!!!!!
የሴቶች ተሳትፎ በማለት የሰከረ ሳይሆን መሆንን የሰነቀ ነው!!!!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።