እናት አድማጮቿን አክብሪ ናት፤ ትናንትን በምለሰት ዛሬን በጨረፍታ ...
አቅምን የማደራጀት ክህሎት -
ከሴቶች ተፈጥሮ ይቀዳል።
(የ20014 ዓለም አቅፍ የሴቶችን ቀን ታስቦ የተዘጋጀ።)
„እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ፤
እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሰሯቸው፤
በዓይኖቻችሁም መካከል እንደ ክታብ ይሁኑ።“
ኦሪት ዘገዳግም ምዕራፍ ፲፩ ቁጥር ፲፰
ከሥርጉተ©ሥላሴ (Sergute©Selassie)
08.03.2014
(ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ)
· መግቢያ።
እንዴት ናችሁ የኔዎቹ። ይህ ብሎግ ሥራ የጀመረው በግንቦት 1 ቀን በ2018 ነው።
ከዚህ ቀደም በስፋት የተሠሩባቸው ጉዳዮች በዘሃበሻ ወይንም በኢትዮ ርጅሰተር ነው ያሉት። ቀደም ባለው ጊዜ በራሴ በጸጋዬ ድህረ ገጽ እና
ራዲዮም ነው። እኛ እራሳችን ሲሞላብን እንደምንቀንሰው ሁሉ ዘሃበሻም ሆነ ኢትዮ ሪጅሰተር እነሱ ደግሞ አርኬቡ ሲሞላባቸው
መቀነስ ግድ ይላቸዋል። ግሎባል ጉዳዮችን ስለሚያስተናግዱ ጫና ይበዛባቸዋልና።
ስለዚህም ጹሑፎቼ ሊሠወሩ ይችላሉ። ታሪክ ነው። ታሪኩ የኢትዮጵያ የነጻነት ትግል
በአንዲት ዜጋ ዕይታ እንደ ዘመኑ ነው። ዛሬ በ2014 እንደምጸፈው አልጽፍም። ስለምን? ዘመኑ በራሱ የሚያመጣው ለውጥ ስላለው።
ግን በዛ ዘመን የነበረው ዕይታ እና ግንዛቤ ዛሬን በሃሳብ በማገናኘት እረገድ ምን ድርሻ አበርክቷል የሚለውን ያሳያል፤ በሌላ
በኩል ግን የአንባቢያን ዕይታም በዛ ዘመን በነበረው ንቃተ ህሊና ልክ የተሠራ ስለመሆኑ ልብ ሊለው ይገባል። ስለሆነም ከጻፍኳቸው
ወዘተረፈ ወጎች ውስጥ በዚህ ብሎግ እንዲቀመጡልኝ የምፈቅዳቸውን በተከታታይ ፖስት ለማድረግ አስባለሁኝ።
www.tsegaye.ethio.info ያለው እንደ ተጠበቀ ሆኖ
ማለት ነው። በዚህ ጹሑፍ መግቢያ ላይ ለኢትዮጰውያን የፖለቲካ ሊሂቃን የጠፋችሁ ነገር አለ እና ፈልጉ ብዬ ነበር የጀመርኩት።
ክብር ለእሱ ለፈጠረኝ አምላኬ ይሁን እና ጠ/ሚር አብይ አህመድ ፈለገው አግኝተውታል። አሁን እንዲያውም የአፍሪካ ሴቶች አንባሳደርነቱንም አክለውበታል። ስለዚህ ዛሬ የሥርጉተ ብዕር የምሥራች ላይ ሆኗ ልቧ በሐሴት
ፈክቶ ማግስትን በተስፋ ፏ ብላ ታማትባለች … ተመስገንን ጠጥታ።
ውዶቼ ያረምኩት የአገላለጽ ሥንኝ የለም። የፊደል ግድፈት ሳድስ ላይ
ችግር ስላለብኝ እሱን ገርቻለሁኝ። በተጨማሪም ፎቶወችን ቀንሻለሁኝ። አዲስም ጨምሬያለሁኝ። ከዚያ በስተቀር ከነተፈጥሮው በ2014 ውልደቱ እንዳለ ነው
የቀረበው።
· እንዲህ ነበር የተጀመረው …
የኮፐን - ሀገን፤ ደማራ፣
ማርች ስምንትን አበራ!
· መቅድም --- Suche:
„fünf fleißig Männer oder eine Frau“ ሲተረጎም …. ፍለጋ፡ „አምስት ታታሪ (ትጉ) ወንዶች ወይንም አንዲት ሴት“ ይህ አንጀት አርስ ሀገር በቀል ብሂል የጀርመኖች
ነው። „ፍለጋ“ ዕርእሱ ነው። ሊቃናት የምርምር
ተግባር ፈጽሙበት፤ ገና ያልደረሳችሁበት ተግባር ጠገብ ሚስጢር አለ። ከተጋችሁ በዘርፉ አዲስ ሙሽራ ሰብል ገብ የጥናትና
የምርምር ተቋም ከፊታችሁ ይጠብቃችኋል። አቅጣጫ አምልካች የቀደመ መርኽ። … እኛ „ሴትና አህያ በዱላ“ እዬተባልን በጨፈገገው፣
በፍዝ - ድፍን ባለ ድንቡልቡል ዳመናማ፤ ለነገም በቀፈፈው ምሳሌ እየተደቃን ነው ያደግነው። እጅግ ግጥሜ የሆነ የምስክርነት
ሥነ - ቃል ስለሆነ መቅድሜ አድርጌ ወስጄዋለሁ። ከጭብጤ ጋርም ቅኔ ነው ንጥር። ተፈጥሮ ካልተተኛበት በስተቀር ፍሉቅ ሃቅም ይሄው ነው። „አምስት ታታሪ (ትጉ) ወንዶች ወይንም አንዲት
ሴት“
ውሳኔና ቁርጠኝነት
መገለጫቸው ነው። አህዱነት የትንፋሻቸው ልኬታ በመሆኑ ጨለማን ሳይፈራ በድል ንባብ እንዲገሰግስ የሚያደርግ ጧፋቸው ነው። ሊጥ
ሳያቦኩ እንጀራን አያስቡምና - - ሴቶች። ውኃን ሳይቀዱ ጥማትን ድል እንደማያደርጉ አሳምረው ያውቁታል። በጓዳ ትጥቃቸው እርግጠኛ ሳይሆኑ እንግዳ አይጠሩም። ትጥቅና ስንቅ
አደራጅተው ከሥልት ጋር ሳያጋቡ የጦር መሪ ጄኒራል በመሆን የጠላትን አከርካሪ ለመስበር አይነሱም። ቀድሞ ነገር የመንፈስና
የአካል ዝግጅት ሳይኖራቸው ኃላፊነቱን አይወስዱትም - በፍጹም።
የዓለሟ ድንቅ እመቤት እቴጌ ጣይቱ አይደለም እሳቸው ለመሩት ጦር ለኢትዮጵያ ድል
መባቻነት የጠላትን ወረዳ የውኃ ምንጭ አስከብበው የጣሊያንን ሆነ /የየአውሮፓን ምዕናባዊ ህልም/ አፈር አስጋጡ። ነፃነትን በድል
አቅለሙ። የጥቁርን የተግባር ታሪክ በፈርጥ ያስጊጡት የተፈጠሩበት ብቃት ምንጩ ከሴትነት እናታዊ ጸጋ ይፈልቃል።
እርግጥ የንጉሦች ንጉሥ ኃያሉ ዐጤ ሚኒሊክ የሰጧቸው ያልተበጣጠሰ መጠነ - ሰፊ መብት
አቅማቸውን በሙሉ ተጥቅመው የድሉ አጋርና ባለቤት ከመሆን አልፈው በመሪነት ረድፍም አሰለፋቸው። አብነታቸውም ትውፊትን አነጸ! ሴቶች
--- በመንፈሳቸው ወስጥ ልዩ ደም አለ።
በመንፈሳቸው ውስጥ ያለው ደም የኑሮ ተፈጥሯዊ ኬሚስትሪያቸው ነው። በሁሉም መስክ የነፃነት ፍላጎት ስኬት የድል አንባው አቅል „አቅም“
ስለመሆኑ ሴቶች ጠንቅቀው ያውቁታል። ስለዚህም ቀልጦ እንዳይፈስ፤ ወድቆ እንዳይከሰከስ ወይንም ቀረህም መጣህም ጣፊያ ነህ ተብሎ
እንዳይናቅ አጥብቀው ይጠነቀቁለታል።
· ግን አቅም ምንድን ነው?
አቅም ማናቸውም የመንፈስ፤ የቁስ ክምችት፤ ለተግባርና ለሚጠይቀው መስዋዕትነት
ተሰናድቶ የተቀመጠ በእጅ ላይ ያለ አስተማማኝ አንጡራ ጥሪት ማለት ነው - እንደ ሥርጉተ መንፈሰ - መዝገበ ቃላት ፍቺ።
· ሴቶችና አቅምስ ምን እና ምን ናቸው?
ሴቶች በራሳቸው
አቅም ናቸው። ሴቶች
አቅም መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አቅም በመፍጠርና አቅምን አደራጅቶ ለተገባው ተግባር በማሰማራት እረገድም አይነታ ናቸው።
ይህን የተግባር መስመር ሴቶች ስለምን አተኮሩበት ቢባል „50 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለ50 ሰው ግን ጌጡ“ መሆኑን በተግባራዊ
ህይወታቸው በተፈጥሮው ለክተውታል። ጥቅም ላይም አውለውታል። መተጋገዝ፤ መረዳዳት፤ ድርሻን እንደ ተፈጥሮው መክሊት ማደላደል
ያውቁበታል። ያለማጋነን መክሊታቸውም ነው። ክህሎቱ ጥልቅ፤ - ውጤቱም ዝልቅ። ለም፣ ፍሬ ሰጥ ተስጥዖ -- የእነ-እመቤት፤
· አቅም ምን ይፈጥራል?
አቅም ኃይልን - ጉልበትን፣ ማሸነፍን፣ ፍላጎትን መሬት አስይዞ ማሳካትን፤ በእርግጠኝነት
በእውቀት ይፈጥራል። ኃይል አላግባብ
ሲባክን ብቻ ሳይሆን የተገባ አትኩሮት ሲነፈገው ያመቸዋል - ሴቶች። ስለምን? የኃይልን ጥቅም ሆነ ንፁህ ተፈጥሮውን
ያውቃሉ። እንዲሁም ኃይል እንዴት ሊፈጠር
እንደሚችል ይገነዘባሉ። ሴቶች አቅም ለመፍጠር የሚጠይቀው የሂደቶች ጉዞ ድካምን ከማንም በላይ የተረዱ ድንቅ
ፍጥረቶችም ናቸው። በኃይል አጠቃቀም እረገድም ጠንቃቆች ብቻ ሳይሆኑ ብቁ ጥበቃም የሚያደርጉ የአቅም ነርሶች ናቸው - እድሉን ካገኙ። እህ! በመስኩ ብክነት እንዲጨፍር ፈቃድ አይሰጡትም -
ሥልጡኖቹ ሴቶች።
ቀደም ብዬ እንደአነሳሁት በሴቶች መንፈስ ውስጥ ያለው ቅመመ - አቅም ዬትላይ
መነሻው እንደሆነ ጠንቅቀው እንዲያውቁ ይረዳቸዋል። ስለሆነም ከአቅም የመነሻ ፌርማታ የመነሳት አቅማቸው ለሚያቅዱት ተግባር ስኬታማነት
አስተማማኝ ዋስትናቸው ነው። መነሻውን ያላወቀ ሹፌር፤ መድረሻውን እንደማያውቅ ብቻም ሳይሆን „የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ“ ስለመሆኑ
ከተጨባጭ እለታዊ ማህበራዊ ኑሯቸው ተምረውበታል።
ሴቶች መሬት አስይዘው የሚጀምሩት ማናቸውም ኃላፊነት፤ ስርክራኪን አጣርቶ፤ ንጥር
ፍላጎትን ባለዙፋን የማድረግ አቅሙ ለመርኃቸው ትልም ሙሴ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቁታል። ከሁሉም በላይ ሴቶች ስለነገ አጥብቀው
የሚያስቡ ግንባር ቀደም የድርጊት አርበኞች ናቸው - ሰማዕትም።
ማናቸውንም መስዋዕትነት አይፈሩም። ለፍላጎታቸው ተፈፃሚነት ከቆረጡ ደፋሮችም ናቸው። ለነገ ፍላጎት የተፈለገውን
መስዋዕትነት ከፍለው ዛሬን ማሰናዳት እንዳለባቸው ስለሚገነዙቡ እርሾ አላቸው - ጥበበኞቹ። ፍላጎትን መረዳት ብቻ ሳይሆን ፍላጎትን ለመርዳትም
ዝግጁነታቸው ከልብ ነው።
አንዲት እናት አንጀራ ስትጋግር ሳይሆን ለእንጀራ የሚያገለግላትን እህል (ጤፍ፣
ገብስ፣ ወዳከር፤ ቡሌ፤ ዳጉሳ፣ ገብስ፤ ወዳአርባ፣ ባህርማሽላ፤ ስንዴም ሊሆን ይችላል) ስትገዛ ሆነ ከጎታዋ* (ከጭቃ የሚሰራ
የእህል መያዣ) ስታወጣ ለምን ያህል ቀን እንደሚያቆያት የምታውቀው የምታስተዳድራቸውን ቤተሰቦቿን ቁጥር መሰረት አድርጋ ነው።
ለምሳሌ፣ … በዛ ወር ውስጥ ድግስ ካለባት እሱንም ግምት ወስጥ
አስገብታ ወይንም አክላ ነው። በእጅ ፈጭታ ይሁን በሞተር ወፍጮ የምታስፈጨውን እህል መጥና ነው እምትገዛው ወይንም እምታዘጋጀው።
እራሱ ተፈጭቶ መጥቶ የሚቀመጥበት ዱቄት ማስቀመጫዋ በልክ የተሠራ ነው - በርሚል ይሁን ጉሽጉሻ።
የእንጀራ ቅድመ መሰናዶዋ ሊጥ በማቡካት ይጀምራል። ስታቦካ ለምን ያህል ቀን
እንደሚበቃት ካልታቀዱ ገጠመኞቿ ጋር አጣጥማ ነው። ሁላችንም ስናድግ እናቶቻችን ሲያድርጉ ያዬነውን ልብ ብለን በምልስት ብንቃኜው
ዕቅድና ግብ ስኬታማ መሆናቸውን መረዳት እንችላለን። በእዕምሮ ሰሌዳ ኑሮን ትልም አለው። ሌላው ቀርቶ የሙጎጎ* (የእንጀራ ምጣድ)
ማሰሻው /ጎመንዘር፣ ኑግ፣ ተልባ፣ ሰሊጥ/ ሳይቀር ታቅዶ ተወቅጦ በሚገባ ነው የሚዘጋጀው። እኔ በግሌ ለአንድ ዓምት አቅደው
የሚያዘጋጁ እናቶችን አውቃለሁ እንኳንስ ሌላው። ህይወት
እኮ መሪዋ ሴት ናት! ሴት ለኑሮ ሥነ ህይወቱ ግጥሙ ናት!
ለነገሩ በሴቶች ተፈጥሯዊ ጸጋ ያለው የውስጥ ውበት በአንድ አቅጣጫ ብቻ፤ ቢበዛ
ደግሞ በሁለት ብቻ ያለውን ለዛውም በግርድፉ ተነካክቶ ሊሆን
ይችላል እንጂ እያንዳንዷ የብቃት ልኬታቸው ድንግል
መሬት ነው ማለት ይቻላል። ብጣቂ
የምርምር ተግባር ያልተሰራበት … ። በሴቶች ተፈጥሯዊ የብቃት ልኬታ እኮ የትምህርት ተቋም ሊያስከፍት የሚችል ቅምጥ ጥበብ ነበር። እውነት ለመናገር ወደ አቅማቸው ዘለግ ተብሎ ሲጓዙ ዓለምን በሰላም፣ በተረጋጋ፣በሰከነ፣ ሥልጡን በሆነ ሁኔታ በብልህነት
ሊመራ የሚችል ፍሬ ዘር ባለሙሉ - ባለድርሻ ናቸው - ልዕልቶቼ!
እንደ እኔ እንደ ሥርጉተ ዕይታ ዓለም ሴቶች አጀንዳዋ ቢሆኑ እንዴት ባማረባት ነበር። አብዛኞቹ ብልህነትና ጥበብን፤ ትጋትንና ፍጥነትን
የታደሉ ናቸው። ይህንን ለናሙና ከቅርቡ ጊዜ ተነስተን አንድ ምሳሌ ብናይ …. ለሁለት ዓመት የዘለቀው፤ ከድንቅ በላይ የሆነው
„የድምጻችን ይሰማ“ እንቅስቃሴ ልብን አንጠልጥሎ፤ በብቁ አመራር የሰከነ ተግባር ከውኖ፤ በተቋምነት የዘለቀው ዓናታዊ ጉዳዩ
የሴቶች ተሳትፎ ሙሉዑና የተገባውም ተገቢ አክብሮት የተሰጠው ስለነበር ነው። እኛ እንደ ታዳሚነታችን እንቅስቃሴው ከፍላጎታችን
ጋር በማቀራረብ ብቻ ለነፃነት ትግሉ ያለውን አስተዋፆ ላይ አትኩሮታችን አሳረፍንበት እንጂ፤ የሰላማዊ ትግል አዲስ ምዕራፍ
ማፍታቱ፤ የሴቶች የእኩልነት ትግል ፈር ቀያሽነቱና ፋናነቱ ነበር ለዘመኑ ለምርምር ተግባር ሊውል የሚገባው ብቁ ጭብጥ - ማሾው!
በዚህ አጋጣሚ በሙሉ አቅማቸው እኩል ድርሻቸውን ለተወጡ ሀገር ውስጥና ውጪም
ለሚገኙ ታታሪ የእስልምና እምነት ተከታይ እህቶቼ ያለኝን አክብሮትና ልባዊ አድናቆት ልገልጽ እፈልጋለሁ። „የድምጻችን ይሰማ“ አቅም ምንጩ የአጋርነት ዕውቅና በተገቢው ሁኔታ ሳይሳሳ መሰጠቱና ማደመጡ መሆኑን ጠንቅቄ
ስለማውቅ አንድ ውብ ታሪካዊ ክፍል ነው እላለሁ። በተለይም ለሴቶች እኩልነት ዕውቅናን በክብር በመስጠትና በመተግባር እረገድም
ምሳሌ ነው። ስለሆነም ከልብ ሆኜ በሚገባ ተከታትዬዋለሁ። በራዲዮ ፕሮግራሜም ብዙ ሽፋን ሰጥቼዋለሁ። የእኔ ብዬ ያቀረብኩት
የተባ ተግባር ስለነበር።
የዛሬ የጸሑፌ አላማ መሰረታዊ ጉዳይ „አቅም“
ስለሆነ ይህንን „የድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ“ ሳልዘጋ የእስልምና እምነት ተከታይ እህቶቼ የማናቸውም ዓይነት እኩላዊ መብት
ሊረጋገጥ የሚችለው፤ እኩላዊ ፍላጎት ሊያስተናግድ የሚችል ሥርዓት ሲፈጠር ብቻ መሆኑን በመረዳት ይህን „ ልዩ አቅም“ ከነፃነት
ፈላጊ ቤተሰቦች ጋር በመሆን፤ ለዘለቄታ ሥር - ነቀል ለወጥ ተግተው ይመግቡት ዘንድ ዝቅ ብዬ አሳስባለሁ።
ቀለማሙ ተሳትፏችሁ ለቋሚው ፍላጎት ጠረኑን ሆነ ትንፋሹን አጋር ታደርጉት ዘንድም
- በትሁት መንፈስ እጠቁማለሁ። የ2014 ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ማርች ስምንትን በጋራ ስናስብ ወይንም በእኛ የካቲት 29ን
2006ን ስናስብ፤ በማናቸውም ድርጅት ለነፃነት የተሰዉትን ሴት እህቶቻችን በድንበር አልቦሽ አሰበን፤ አሁንም በመሰዋት ያሉትን
አድናቆታችን በአኃቲ ድምጽ አዋውለን ዋጋ መስጠት ይኖርብናል። ወቅቱ ትግሉን ተካታታይ በማድረግ ወደ አጥቂነት ለማሸጋገር ማዕዱን ሰፋ አድርጎ
መጓዝን ይጠይቃል። ልምዱና ተመክሮው ዝቀሽ ስለነበር በአግባቡ ተይዞ „የአሻም ህዝባዊ እንቅስቃሴ“ ገበር እንዲሆን ማደረግ
መሰረታዊ ነው።
አሁን ወደ ቀደመው። የሴቶች ሙሉ አቅምን የመምራት ብቃት --- ለቤታቸው፣
ለትዳራቸው፤ ለሥራ መስካቸው፤ ለሙያ ኃላፊነታቸው፤ ለዕምነታቸው፤ ለማህበራዊነታቸው ብቻ ሳይሆን የአንድ ፍላጎትን ሆነ ራዕይን
ከውጥኑ ጀምሮ በጥንቃቄና በእናታዊ ጸጋቸው የማስተናገድ ፍሬ ዘለቅ ልምዳቸው ጉዟቸውን ስኬታማ ያደርገዋል።
እርግጥ ፈተናቸው ከ - እስከ ተብሎ ተዘርዝሮም ተጽፎም አያልቅም። በእያንዳንዷ ኢንቺ ጋሬጣ አለባቸው። በፆታቸው፣ በብቃታቸው፤ በብልህነታቸው፤ በመብለጣቸው፤
በክህሎታቸው፤ በአቅማቸው እንዲሁም በስምረታቸው ዙሪያ …. ነገር ግን ሁሉንም እዬተጋፉ በግላቸው ከሚወጥኗቸው
ማናቸውም ዕለታዊ ህይወት እስከ ትልቁ ብሄራዊ ጉዳይ ድረስ አጋጣሚውን ካገኙ አድማጫቸው በርካታ፤ ሰብላቸውም ምርታማ። ይህ ደግሞ የአቅም አያያዝና የአቅም ስምሪት
እንዲሁም አቅምን አዳምጦ በእጅ የማቆዬት ጸጋቸው ሥር ይዞ ቢጠና ለቋሚውና ለዘለቄታዊ ፍላጎት ብቸኛው መዳህኒት ነው።
ሴቶችን ማወቅ የነፃነት ትግልን ጣዕምና ፍሬ
ማወቅ ነው - ለብልሆች፤ የመንፈስ ህሊና ለማዬት ለታደሉት ለዓይናማዎች።
አቅም አቅም ነው። አቅም ግብ ነው። አቅም መርኃ ግብር ነው። አቅም ጉልበት ነው፤
አቅም ኃይል ነው። አቅም ማሸነፍ ነው። አቅም ድል ነው። አቅም ድህነት ነው። አቅም ብሥራት ነው። አቅም ዕውቀት ነው። አቅም
ለዕንባ ምህረት ነው። አቅም ነገ ነው። አቅም ተነገ ወዲያም ተዚያ ወዲያም ነው …. አቅም ፈጣን ዳኛ ነው። የእያንዳንዱ አቅም
ፍጥረተ ነገር እንደ ተፈጥሯዊው ባህሪው ወጥ ወይንም ዝንቅ ሊሆን ይችላል። በወጥነቱ ውስጥ ቅይጥነት፤ በቅይጥነት ወስጥም ወጥነት አብረውና ተቻችለው በሰምና ወርቅነት ተጋብተው
ይገኛሉ።
ችግሩ አጠቃቀሙና አተረጓጎሙን ከማወቁ ላይ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን መቼቱና
ወቅቱንም ከዬባህሪያዊ አርቱ ጋር በጥምረት በጥናትና በስልታዊ ሥምሪት ብቻ ሳይሆን ክትትልንም በጥሞና ይጠይቃል። ከዚህ ላይ
ትንሽ ፈታ አድርጌ ማቅረብ እፈልጋለሁ። ግን አንዲት ብጣቂ ነጠላ ጉዳይን ተንተርሼ … ነው። አቅም በፈጠራ - አቅም - ሥርጭት
- ድለደላ - አያያዝ - ማግሥት - ግምገማ ወዘተ ስለሆነ … እራሱን የቻለ አንድ ትልቅ መድብል ይወጣዋል።
· ወጥነት ስል ምን ለማለት ነው?
በወጥነት ተመሳሳይ ፍላጎትና ዓላማን መሰረት ያደረገ አንድ ጉዳይ ተኮር ስብስብ
እንደ ማለት። ለናሙና ትንሽ ነገር ብናይ ----ዬአንድ አባወራ ትዳር፤ የአብነት ት/ ቤት፣ የሴቶች ድርጅት፤ የወጣቶች
ድርጅት፤ የሃይማኖት ተቋም፤ የሙያ ማህበር፤ ወዘተ …
ቅይጥነትን በሚመለከት አመሰራረቱ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን አማክሎ፤ ወይንም የተለያዩ
ማህበረሰብ ክፍሎችን አሰባብስቦ በአንድ
ፍላጎት መቋጠርን እንደማለት ---- እድር፤ ሰንበቴ፤
አክስዮን ወዘተ …
· ቅይጥና ወጥ እንዴት? ----
ይህ እንግዲህ በዝንቅ ፍላጎት ውስጥ ወጥነት መገኘቱን ለማጠዬቅ ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ስትሆን፤ የሴቶች ባለጥልፍ ሙሉ ወርድ ቀሚስ ውበትም፤ ከጥጥ ምርቱ ጀምሮ አስከ ፍጻሜው የብዙ ነገሮች አቅማዊ
ተሳትፎ አለበት። እስቲ --- ትንሽ ቀለልና በተን አድርጌ
ለማሳዬት ልሞከር … በቅይጡ ውስጥ ወጥነት፤ በወጥነት ውስጥ ቅይጥነት …. ተዋህደው ወይንም
ተመሳስለው ፍላጎትን ማደላደል ይታያል።
ምሳሌ፤ … የፆታን
ጭቆና ለመፋለም የሚቋቋመው በወጥ ፍላጎት ዓላማ ዙሪያ የሚደራጀውን የሴቶች ድርጅት በወጥነት መውሰድ ይቻላል። ይህ ማለት ግን
በሴቶች ድርጅት ውሰጥ ቅይጥ ባህሪያት የሉም ማለት አይደለም። ሴቶች በፆታቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን ማናቸውንም የትምክህት ጫናን
ለመመከት ወጥ መንፈስ ይዘው ይነሳሉ። በዚህ ድርጅት ዙሪያም ለእኩልነታቸው ሴቶች ይሰባሰባሉ። ተደራጅተውም ይታገላሉ። በፖለቲካ
ድርጅት አስተሳሰባቸው የተለያዬ ሊሆን ቢችልም በወጥ መሰረታዊ ጥያቄያቸው ዙሪያ ግን ተግተው ይታገላሉ።
በእምነት ዘርፍም እንዲሁ …. በሌላ በኩል በሴቶች ድርጀት ውስጥ ጠለቅ ብለን የአቅምን ስምሪት ስናስብ፤
የተገባውን ቦታ ለተገባው ብቃት ለማደላደል ሌሎች ቅይጥ ሁነቶችን ማዬት ግድ ይላል። ምሳሌ … በአንድ የሴቶች ድርጅት ውስጥ የዕድሜና የሙያ ስብጥር ለማዬት ስንገባ
ቅይጥ የሆኑ ገጠመኞቹ ይኖራሉ። ከዚህም ሌላ በተመሳሳይ ሙያ በተመሳሳይ ዕድሜና እምነትና የፖለቲካ አቋም ያሉትም ቢሆኑ በአኗኗር
ዘይቤያቸው ሆነ በሥነ - ምግባራቸው የበርካታ ቀለማት ሐረጋት ውህድ ሆነው እናገኛቸዋለን።
ስለሆነም የሴቶች ድርጅትን ለቅይጡም ሆነ ለወጡ ፍላጎት ማዕከላዊ ዕይታን እንደ መነሻነት
መወስድ ይቻል ይመስለኛል። ከዚህም ጭብጥ በላይ በስፋት መሄድም ይቻላል። በሴቶች ድርጅት ውስጥ መምህራን ሴቶችን ለናሙና ብንወስድ
የቋንቋ፤ የሳይንስ ትምህርት አስተማሪነት ወዘተ … የአንደኛ የሁለተኛ ደረጃ …. መምህርነት፤ ወዘተ ዕድሜው ወስጥ ስንገባ
ደግሞ ሌላ ሥዕል እናገኛለን …. ጉዳዬ ከሴቶች የአቅም ፍጥረተ ነገር ጋር የምዕናብ ሰርበዬር ለማዬት ነው እንደ ምሳሌ
የወሰድኩት …. አንድ የሴቶች ድርጅት እነዚህን ሁሉ ዘርግቶ የተግባሩን ካርታ በማስተዋል መንደፍ አለበት ለማለት ነው። ስለሆነም
የአቅም አወቃቀርና ውህዳዊ ሃዲድ በዚህ ፍሰት መታዬት አለበት።
…. ከዚህ አንፃር
አንዲት የገጠር ሴት ቤቷን፤ ትዳሯን መርታ እንዴት ኃላፊነቷን እንደምትወጣ በተጨባጩ ዓለም ተገኝታችሁ ብታዩት ምስክርነቱ የእኔ
ብቻ ሳይሆን የበርካቶችን የስምምነት ዳኝነት ያገኝ በነበረ። እኔ ሥርጉተ የታድለኩ ነኝ።
ከአርሲ ሮቤ - ሴሩ እስከ ማህል
ሸዋ፤ ከማህል ሽዋ አስከ ዬትኑራ፤ ከሰቲት ኡምናኽጀር አስከ የኋንስ ከተማ፤ ከሃይቅ ደንበር እስከ አንድአቤት፤
ከጫቆ መኪና አይታ ከማታውቀው አጋር እህቴ እስከ ማጠቢያ ጠረፍ … ከጣናዎቹ በቅመማ ቅመም ሳቢ ጠረን ዕውደት ካለው የአለፋ ጣቁሳ የገጠር
መንደሮች እስከ ተራራማው አርማጭሆ ከዛም እስከ ሊማሊሞ የእመቤቶቼን የአኗኗር ዘይቤ ስለ አዬሁ፤ አብሬም በህይወቱ ውስጠት
ሰኔል ወይንም አጎዛዋን፤ ወይንም ላመነቷን ከመደቧ ላይ ጣል ብላ፤ መደብ
- ወለል - ቆጥ ወይንም የጤፍ ክምር ላይ ለሽ ብሎ ንጹሑን ተፈጥሮ መኮምኮሙን - አግኝቸዋለሁ - አድምጨዋለሁ።
ብቻ
በዚህ ዙሪያ የጠገበ ልምዱ ስላለኝ በልበ ሙሉነት አሳምሬ ብቃታቸውን እመሰክራለሁ። ሴቶች የአቅም መሃንዲሶች ናቸው ብዬ … አንዲት ማህል ሽዋ ነፋሻማ የጉራጌ የገጠር መንደር ሴት የቤት አያየዝና
ጎንደር በጭልጋ አውራጃ የአዳኝ ሀገር ቆለኛ ሴት ተመሳሳይ፣ ወጥ አቀራረብና ስንዱነት ነው ያዬሁት። ለእኔ የሰጠኝ ፌድባክ
በተለያዬ ቦታ የምትኖር ቆለኛ ሴት ከደጋዋ ጉራጌ ሴት ጋር የብቃት መሳነትን ተመልክቻለሁ። ፍጥነታቸውና ጥራታቸውም እንዲሁ
/// ክውኖች!
በሴቶች ድርጅት ውስጥ የሴቶችን ጭቆና መክቶ ሁለገብ ተሳትፏቸውን ለማጎልበት ወጥና
ቅይጥ ሁነቶችን አስማምቶ በአግባቡ በመያዝ አቅምን ፈጥሮ፤ ጥቅም
ላይ ለመዋል የድርጅቱ ውስጠ አካል ከመምራት በፊት ከነዚህ ጥቃቅን የሆኑ ጉልህ ተዋፆዎች፤ መሰረታዊ ሁነቶች መነሳት ግድ ይላል።
ይህ ከሆነ ከመሰረቱ ሲነሳ ድርጅቱ አቅምን አውቆ ይነሳል። ሃብትን በአግባቡ መያዝም
ይቻላል። ለነገሩ ካለምንም የግል ፍላጎትና
የሌላ ኃይል ጫና የተፈጠረ የሴቶች ድርጅት ባለመኖሩ ምክንያት የሴቶች አቅም ባለቤት አልባና ዋቢ አልባ ሆኑ ሲባክን ይታያል።
እንዲያውም አጥሩን ገፍትረው የወጡም ኢሚኒት ቢኖሩ ጋዳ ነው በቀጣይነት ዘላቂ ችግራቸውን ለመመከት ያለው የመደረክ ሃዲድ ቁልፍ
ነው። ለዚህም ነው አቅማቸው በባዕድ ሀገር እንዲህ በግፍ ሲገፋና ሲቀጠቀጥ ባለፈም ሲገደል የሚታዬው ….
ሃብት እኮ መቻል ነው። ሃብት ዬአንድ ድርጅት የአቅም ማገር ነው። ሃብቱ ደግሞ የድርጅቱ አባላት ናቸው። አላማውን አወቀው ፈቅደውና ወደው
ለመታገል የቆረጡ የአንድ ፍላጎት ቤተሰቦች። እነዚህ ሃይሎች የድርጅቱ ሀብቶች ስለሆኑ የድርጅቱ ወሳኝ አንጎሎች ናቸው። ይህን
ወሳኝ አንጎል በቅጡ መርቶ እግቡ ለማድረስ ደግሞ መሪ ያስፈልገዋል።
አመሰራረቱ በጥቂት ተቆርቋሪዎች ከላይ ወይንም ከታች ሊሆን ይችላል። ግን ጊዜ
ሳያጠፋ ታች ወርዶ የማደራጀት ተግባር በመፈጸም፤ መሰረት ይዞ መሪውን ማምጣት ግድ ይለዋል። መስራችነት ስሜትን ጫሪነት ነው።
የፍላጎቱ አስኳል መነሳት ያለበት ግን አቅምና ጉልበት ካለው ከታች መሆን አለበት። የእኔ፤ የእኛ የሚለውን ብቸኛ ተቆርቋሪ ሰራዊት መፍጠር የሚችለው
የማያወለዳው ሃቅ ይህ ነው። ከብዙኃኑ አቅም የተነሳ የይሁንታ ይለፍ።
በዚህ መልክ ድጋፍ ሆነ ተቀባይነት ሲፈጠር፤ ካለ ጫና ሲመጣ ነው አቅም ብርቱ ጠበቂ
የሚሆነው። አጥር ቅጥር የሚሆነው። ይህ አመጣጥ ቅይጡንና ወጡን ፍላጎት ይዞ ይነሳል። ስለሆነም ለዚህ ኃላፊነት ላበቃው አካል
ፍጹም ታማኝ የመሆን አጋጣሚው ሰፊና መሰረት ዬያዘ የተግባር ርስት ይሆናል። ተጠያቂነትና ተቀባይነትም በተግባር ክናድ ይለካሉ።
አቅሙም የተዋበው በበርካታ ስብጥር ብቁ ውርስ ስለሆነ አበባማ - ማራኪና አጓጒ፤ እንዲሁም ተወዳጅ ያደርገዋል። ተቆርቋሪነት የሁሉም የውዴታ ግዴታ ይሆናል -
በፈቃደኝነት።
ከላይ በተጠቀሰው መልክ የሚፈጠረው አቅም ደግሞ ወጀብ የማይነቀንቀው ዘላቂና
ተወራራሽ ሆኖ እንዲቀጥል የማድረግ አቅም ይኖራዋል። ለዚህም ሴቶች እነቱ ናቸው። የእኔ ጹሑፍ ዓላማም ይኸው ነው። ለአንድ
ድርጅት አቅም ስምሪትና ተጠቃሚነት አቅሙን የሚፈጥረው ወይንም አቅምን ፈቅዶ የለገሰው ኃይል ከምንም በላይ ሊከበርና ድምጹ ሊደመጥ ይገባል።
እናት እናት ሁና እድሜዋን ሁሉ ተወዳ፤ ታምና፤ ቅርስና ውርስ ሆና፤ እንዲሁም የህይወት ፈርጥና ጌጥ ሆና፤ የተስፋ ጥግና ማገር
ሆና፤ የራህብ መዳህኒትና ዋቢ ሆና ባልጓጎለ፤ ወጣ ገብ ባልሆነ፤ ቋሚና ዘላቂ ወጥ ባላ ፍቅርን ያገኘችበት ሚስጢር ይህ ነው።
እናት አድማጮቿን አክባሪ
ናት። እናት
ለአድማጯ ሎሌነቷን ትፈቅድለታለች። እናት አያያዝ ትችላለች። ስለዚህም ነው እናት አድማጯ ነጥፎባት ወይንም ርቋት ወይንም ቤቷ ተጓድሎባት የማያውቀው።
በልኳ ልክ እንደ ልኳ የተፈጠረች።
እናት - ሳትታባይ በአግባቡ ፍቅርን ሰጥታ
ፍቅር ተቀብላ ፍቅር ሆና ትኖራላች።
የሰው ልጅ በህይወቱ ሙሉ ከእውነተኛው ደስታ ከሐሤት ጋር የሚያገናኘው ድልድይ
ብቸኛውም ማለት ይቻላል እናቱን ሲያስብ ብቻ ነው። ለምን? እናት ጥሩ አድማጭ ናት። ለአድማጮቿ እናት የኑሮ ሙሴ ናትና። እናት አቅምን በአቅም ይዛ ግብር
ላይ አውላ ድልን የማዘዝ አቅም ያላት ብቸኛ ፍጡር ናት። እናት ቂም የሌላት የምህርት ነፍስ ናት። የትኛው
ግለሰብ - ድርጅት - ማህበር፣ ፓርቲ - እምነት - ንቅናቄ - ሚዲያ - ለአድምጩና ለተከታዩ ምን ያህል ጥንቃቄ እንደሚያደርግ
ያላችሁበት ስለሆነ ለኩት። አድማጭ ሲበዛለት፣ ሲሞቅለት ዝቅ ዝቅ እያለ ለመገዛት ትክሻውን በማመቻት ፈንታ … ሂዱበት መንገዱ
የሰላ ነው …..
እጅግ የምወዳችሁ፤ የማፈቅራችሁ የመንፈሴ ልቦች፤ የሀገሬ ሴቶች፤ አዎን! ነፃነታችን
እንፈልጋለን። እኩልነታችን በማንኛውም መስክ እንሻለን። በተገኘው አጋጣሚ፤ በተገኘው ቦታ ሁሉ ….. ነቀል ተከል የሚለውን
ፍላጎት አርቆና አስተካክሎ በማያዝ ዘላቂ ለውጥ በሃገራችን እንዲመጣ አቅምን በሚበትኑ ድርጊቶች ካለመሳተፍ ጀምሮ „ ማናቸውንም
የነፃነት ትግላችን ነቀርሳዊ ጉዳዮችን ሁሉ „እንብኝ“ የማለት አቅም የመገንባት በዘመኑን ልናተኩርበት የሚገባ ታላቅ የተጋድሎ
መስካችን ሊሆን ይገባል። እደግመዋለሁ፣ በተገኘው ቦታ ሁሉ ….. ነቀል ተከል የሚለውን ፍላጎት አርቆና አስተካክሎ በማያዝ
ዘላቂ ለውጥ በሃገራችን እንዲመጣ አቅምን
በሚበትኑ ድርጊቶች ካለመሳተፍ ጀምሮ ማናቸውንም
የነፃነት ትግላችን ነቀርሳዊ ጉዳዮችን ሁሉ „እንብኝ“
የማለት አቅም የመገንባት በዘመኑን ልናተኩርበት የሚገባ ታላቅ የተጋድሎ መስካችን ሊሆን ይገባል።
አብሶ ለተሰደድንበት ምክንያት ምክነት መጀመር ያለብን የራሳችን ነፃነት ከማወጅ መሆን አለበት። ከዚህም ጋር
እንቢተኞች የሚወስዱትን እርምጃ አድናቆታችንና አጋራችነን ማድረግም ይኖርብናል።
ከሁሉ በፊት „ ከአንድ ብርቱ ሁለት መዳህኒቱ“ ለነፃነት ትግሉ
አቅም ወሳኝ ነው፤ ይህንን አቅም በእጅ ያለውን እንኳን አዝድቆ አዝልቆ ለማቆት ያለው የአያያዝ ጥበብ ስስ ነው በጣም። ቀድሞ
ነገር እያንዳንዱ ድርጅት፣ ሚዲያ፣ ፍላጎት፤ ራዕይና ተስፋ ሁሉ ከአድማጩ በታች እንጂ በላይ ከቶውንም ሊሆን አይገባም። የሚታዬው
ግን የተገለበጠ ነው። ይህን እንድታስተካክሉ፤ ቅመም ሁናችሁ መልክ ታስይዙት ዘንድ ዘመኑ ፊቱን አፍጥጦ እዬጠበቃችሁ ነው። መድረካችሁን እባካችሁ ተጠቀሙበት። ሥነ ጥበብ ማለት ውስጥን ማድመጥ ነው። የነፃነትን ውስጥ አድምጡት ሥነ ጥበቡም
ሁኑ!
አድማጭ ጊዜውን - ጉልበቱን - ገንዘቡን ሲያጠፋ ሊከበር ይገባል። ሊመሰገን
ይገባል። አይከፈልበት። አልፎ ተርፎ ትርፍ ነገሩ የትም አያደርስም። የንጉሦች ንጉሥ ዐጤ ቴወድሮስ „ዕዳ ማስቀመጥ“ ይሉታል። ዕንባን
እንሰበው፤ የእህል ጠረን የራቃቸው እልፍ ስጋዎቻችን እናስባቸው፤ ሀገራችን ሞትና የማይበርድ እሳት ተደግሶላታል በወያኔ ሃርነት
ትግራይ፤ ነገ እንደ ኩርድሽ መሬት አልባ፣ ጥርኝ አልባ፤ መቀበሪያ ብትን አፈር አልባ፤ እንድንሆን ነው ተተግቶ እዬተሰራ ያለው፤
ስለዚህ ሁሉም ነገር ከዚህ በታች እንጂ በላይ ሊሆን ስለማይገባ፤ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ እራሳችን እዬቀጣን ይልቁንም ሴቶች አርያ በመሆን
ትግሉን ወደ ፊት ታራምዱት ዘንድ እለምናለሁ እኔ ባሪያችሁ ሥርጉተ ሥላሴ።
ችግሩ እዬሰፋ ሲመጣ የበለጠ መደራጀት መሰባሰብ ቢያንስ የሃሳብ ኃይል መፍጠር
ሲገባ የሚታዬው ግን …. መራር ገጠመኝ ነው። በዚህ ክፈተት፤ በዚህ ቀዳዳ ዕድሉ ካላቸው ሴት እህቶቼ ብዙ በጣም ብዙ
እጠብቃለሁ። አዲስ ኃይል በመፍጠር ረገድ ያለው መከራ ተዘርዝሮ አያልቅም። በዚህም ዙሪያ ለአዳዲሶችም የትግሉ ቤተሰቦች የተለዬ እንክብካቤና እይታ አብዮት ማካሄድ
ያስፈልጋል። ትብትቡን ሰብሮ ገብቶ ቤትን ማሰናዳት የሴቶች ድርሻ ሊሆን ይገባል። ከሁሉ በላይ ጠንከረው በሚወጡ ሴቶች ላይ
ያለው የተመሳሳይ ፆታ መገፋፋትም
ሌላው ሊታረምና ሊታረቅ የሚገባው አብይ ጉዳይ ነው።
ሳንክ እዬፈጠሩ ተቀባይነትን ማጉደፍ በሚመለከት ሳውዲ አረብያ ላይ በቢላዋ
ተዘልዝለው ደማቸው ባፈሰሱት ወገኖቻችንና ክብሩ በደም ለተጥለቀቀለቀው ሰንደቅአላማችን ስንል እንኳን ለባከነው ጊዜ በህሊናችን
ይቅርታ ጠይቅን አጋራችነን የማጠናከር ተግባር መከወን ግድ ይላል
ነፃነት ፈላጊ የእውነት ከሆን …. ንጹህ ልብ ይኑረን።
በተረፈ እንደ አመታዊ የአሜሪካን ሀገር ስቴት ዲፓርትመንት የ2013 ሪፖርት
ትንትና ሺህ እህቶቻችን ግፍና በድል እዬደረሰባቸው ነው። የሳውዲው መከራ አላለቀም፤ በዬሀገሩ ተሰደው ኢ-ሰባዊ ድርጊት
የሚፈጠርባቸው እህቶቻችን ሰቀቀን ቀጥሏል። ሁሉንም መካራ አስብን የምንችለውን ለማድረግ እንትጋ።
ከሴቶች ጋር የሚይያያዝ ምንም አይነት ችግር ከቶውንም የለም …. ከላይም ሆነ
ከታች፤ በግራ ቀኝ እንደ አረስቶ ሥጋ እዬተቀቀሉ ያሉት ሴቶች ናቸው። ይህን ለመመከት አቅም በመሆን - አቅም በመፍጠር -
አቅምን በሆደ ሰፊነት በማስተናገድ - አቅምን በጽናት በማናጽ፤ አቅምን በማድመጥ አደራጅቶ በመምራት እረገድ ጎደሎውን ሁሉ ትሞሉ
ዘንድ ዝቅ ብዬ አሳስባለሁ። አብሶ ለወረተኛና ለሰሞንተኛ ትግል እጃችሁን ሳትሰጡ ለዘላቂ ሥር ነቀል የድል መጨበጫ ዋናው ጉልላታዊ
ፍላጎት በማይናወጽ ሁኔታ በቋሚነት በውስጥ ማነጽ ያስፈልጋል።
· መቋጫ፤
ወርቅ በአግባቡ ካልያዙት ቀልጦ ይፈሳል። በሳቢያዎች ሳይሆን በምክንያቶች ዙሪያ
አቅምን ማፍሰስ የራዕያችን ብቸኛው መንገድ መሆን አለበት። በዬንዳንዱ የምኞታችን የእንቅስቃሴ ጉዞ ሁሉ ከግብ መዳረሻ
መንገዳችን በተለያዬ ሁኔታ በስንጥር ስንጥቅ የሚጠፋውን ጊዜ ቆጠብ አድርጎ፤ በርቀት በማዬት - በመተንበይ፤ የሚመጡትን ሳንኮች
ታጥቆ መጠበቅ የፊት ለፊት የተግባር መርኃዊ ሰሌዳችን ሊሆን ይገባል። ነፃነት ሁልጊዜም የበቃ ትጥቅና ስንቅ ንጹህ አዬሩ።
የእኔ ክብረቶች አቅምን በመፍጠር፤ ያለን አቅም በማወቅ፤ በማስተዳደርና አክብሮቶ
ሰጥቶ በጥንቃቄ ይዞ ለማቆዬት የትግል ዘመናችን ሁለመና ተመክሮዎችን ተግባር ላይ ማዋል ለነገ ሊቀጠር የሚገባው ጉዳይ
አይደለም። የኃይል አሰላለፉ በተቀያዬረ
ቁጥር ትጥቅ ሳንፈታ፤ አትኮሮታችን በፍላጎታችን ልዕለ ዘላቂ ማሳ ሊሆን ይገባል።
የማከብራችሁ የዕይታዬ ታዳሚዎች ስለሰጣችሁኝ የከበረ ጊዜ ፍቅርና አክብሮት በገፍ
አቀረብኩ።
በመጨረሻ እንዲህ በተሳትፎ ደምቄ ባዕሌን እንዳከብር ያደረገኝን የእኩልነት አንባ የዘሀበሻን
ማህበራዊ ድህረ ገጽን ቦርድ ከልባችሁ አመስግኑልኝ አደራ - የተሰበረውን ድልድይ ገንብተው ያገናኙን እነሱ ናቸው። ፈቃዳችሁ
ከሆነ በመጪው መጋቢት 13.03.2014 በዕለተ ሃሙስ ማርች 8ትን አዬር ላይ ከ15. 00 ሰዓት እስከ 16.00 ሰዓት www.lora.ch.tsegaye አብረን እናክብር - መልካም በዓል!
የመቻል ጥልፍ በሴቶች ብቃት ተለክቷል!
ሴቶች የመሆን ውስጥ አዋቂዎችና ጥበቦች ናቸው!
ኢትዮጵያዊነት ነገም ይኖራል!
· የጀርመንኛ Suche እና fleißig ቃላት ቀጥተኛ ትርጉም የወሰድኩት ከተርጓሚ አቶ ዳዊት ብርሃኑ „ጀርመንኛ አማርኛና
እንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት“ መጸሐፍ ነው።
እኔ ይህን መጣጠፍ ስጽፍ በ2014 ነበር ዛሬ በከአራት ዓመት በሆዋላ በ2018 ደግሞ እንዲህ ...ከምንም እዚህ ደረጃ ላይ እንሆ ደረሰ። ተመስገን!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
መሸቢያ ጊዜ ኑሩልኝ!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ