ነገረ ኢህአፓ። ዕድሜ እኮ የኔታ ነው ውስጡን ለፈቀደ።

ነገረ - ኢህአፓ። ዕድሜ እኮ የኔታ ነው ውስጡን ለፈቀደ። "እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም።" እንዴት አደራችሁ ማህበረ ቅንነት? #ጠብታ ። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ላም እረኛ ምን አለን ዕውቅና ሰጥተውት እንደማያውቁ አውቃለሁኝ። ግን ውስጤን መግለጽ አይቋረጥም። ይቀጥላልም። ኢህአፓን በሚመለከት ሚዲያ ላይ ተቀጥሬ እሰራ በነበረበት ጊዜ በስብሰባው ተገኜቼ ያየሁትን፤ የሰማሁትን ከመዘገብ ውጪ ኢህአፓን እንደ አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅትነቱ ሞግቼው አላውቅም። ምክንያቴ እንደ ልፋቱ ዕድል ያልቀናው ባተሌ መሆኑን አውቃለሁኝ። ለአውራ የፖለቲካ መሪነት እንኳን ያልበቃ ነው ኢህአፓ። መንግሥት ሆኖም ስለአላየሁት ዕድል ለተላለፈው የፖለቲካ ድርጅት ምን ፍጠር ብየ ልሞገትው? ልተቸው። ኢህአፓ በመገበር የኖረ የፖለቲካ ድርጅት ነው። እኔ የኢህአፓ #አባልም ፤ #አካልም ሆኜ አላውቅም። መንፈሱም አልተጠጋም ከእኔ። ምክንያቱም ጠንካራ እናት ስለነበረችኝ ማንኛውም እንቅስቃሴየን ትቆጣጠረው ስለነበር ወደ ኢህአፓ ትውር አላልኩም። "ትምህርት ቤት አትሂዱ፤ አትማሩ" የወቅቱ የኢህአፓ ሞቶ ነበር። እናቴ ግን ጥጧን የሚሳሳውን ይዛ፤ ደብተሬን በዘንቢል ተሸክማ ገብያ የምንሄድ መስለን ትምህርት ቤት እራሷ ትወስደኝ ነበር። ትምህርቱ እስኪያልቅ ድረስ ጠብቃ በሄድንበት መንገድ ሳይሆን መንገድ #ቀይራ ወደ ቤት ትመልሰኛለች። ብዙ ማስጠንቀቂያወች በደጃፋ ሥር ከኢህአፓ ይላክም ነበር። የእናት፤ የፆታ፤ የሥርዓት ጭቆና አለባት ይሉ ነበር ኢህአፓወች። የማልሸሽገው ትምህርት ቤት ውስጥ፤ ከውጭም፤ በረፍት ጊዜም #ጭንቀቱ ከባድ ነበር። ስጋቱ አይጣልባችሁ። በዛ ላይ አባባ ጫካ ነበሩ። ...