#ያላለቀ #ዕዳ። #ያልተቋጬ #የትውልድ #የቤት #ሥራ።


(መዝሙር ፶ ቁጥር ፩)
መቅድም።
የአቶ ታየ ደንዳንዳን መታየት አስመልክቶ እንደ ማንኛውም አድማጭ እንጂ እንደ አልፍኩበት የሚዲያም፣ የፖለቲካም ሕይወቴ አቋም ላይ ሆኜ አልተከታተልኩትም። መጀመሪያ አዲስ ኮንፓስ ከሌላ ሚዲያ አዘጋጅ ጋር የነበረውን ቆይታ አዳመጥኩኝ። በአቶ ታየ የፖለቲካ አቋም መጨከን የተሳነው ሆኖ ነው ያገኜሁት። ሌላ ገፊ ኃይል እንዳለው ያመነ ይመስላል የውይይቱ አጠቃላይ መንፈስ።
ሁለተኛ ያዳመጥኩት አንከር ሚዲያ ነው። "በድምጽ ለማስቀረት" የሚለውን ስሰማ ደንግጫለሁኝ። በሌላ በኩል የውይይቱ አየር የሹክሹክታ ሁነት መኖሩም ሌላ ክስተት ነበር። በተጨማሪም የጋዜጠኛ መሳይ መኮነን የመሻት አቅጣጫን ለመመዘን ጊዜ ሰጥቸ ተከታትየዋለሁኝ። የመሻት ጭነቱን መጠን እንደማለት።
ከዛ ቀጥየ ክፍል ፩ እና ፪ አንከር ሚዲያ በአቶ ታየ ደንድዓ የፖለቲካ አቋም ከረ/ ፕሮፌሰር ትንግርቱ ጋር ያደረገውንም ቆይታ ታደምኩኝ። ከዚህ በኋላ ነበር ከመሠረቱ ሚዲያ ሆርን ኮንቨርሴሽን ሦስቱንም ክፍል ማስታወሻ እያያዝኩ ያዳመጥኩት።
በውነቱ አወያዩ በተረጋጋ መንፈስ ካልተበራከተ መጫን ጋር በእርጋታ ቀለል ባለ የአጠያዬቅ ዘይቤ የአቶ ታየ ደንዳን የውስጥነት የመግለጥ አቋም ጊዜ ሳይሻማ፤ እንዲሁም ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲያማትር ሳያደርግ በፍጹም ጨዋነት የተካሄደ ነበር። ያልገባኝ ግን አወያዩ የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ሳይሆን የሚለው "የጎርጎሪያውያን፣ የግዕዝ አቆጣጠር" እያለ ነበር ድርጊቶች የተከወኑበትን ቀናት፣ ወራት እና ዘመናት ይጠይቅ የነበረው። ሌላ ጠያቄ የውይይቱን መሪ ሲያገኜው ለምን እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የሚለውን ማግለል እንደፈለገ ቢጠይቅልኝ ምኞቴ ነው። የኦሮሞ ፖለቲካን እና የፈላስፊት ኢትዮጵያን ሁነት ያመሳጥራልና።
ከዚህ በኋላ አንከር ሚዲያ ተምልሼ ከአቶ ታየ ደንዳዓ ጋር አንከር ሚዲያ ያደረገውን ቆይታ በድጋሚ አዳመጥኩኝ። በተጨማሪም ሆርን ኮንቨርሴሽንም ተመልሼ ክፍል ፩ ደገምኩት።
1) #የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ተስፋው።
በአጭሩ ሁሌ መውደቅ መሆኑ ያሳስባል።
2) #አቶ ታዬ ደንዳዓ እና ካቴና።
በመስተዋድድ የተዋህዱ መሆናቸውን ተረዳሁኝ።
3) #የአቶ ታዬ ደንድዓ የፖለቲካ አቋም።
አዲስ ኮንፓስ እንደሚያስበው ሆኖ እንደሰጋበት የአቶ ታዬ ደንድዓ የፖለቲካ አቋም ሹፌር፣ ካፒቴን፣ ወይንም አቅጣጫ አመልካች እንደማይሻ ተረድቻለሁኝ። አዲስ ኮንፓስ የአቶ ታየ ደንድዓን አድናቂ ላለማጣት ይሁን አምኖበት ገበር ለመሆን የፈቀደ ይመስላል። በጥንቃቄ ነው የያዘው።
አቶ ታየ የብልጽግና ሃሳብ ደጋፊ ናቸው። ምርጫ ቦርድ ለብልጽግና ስለሰጠው ዕውቅናም በመርኽ እንደተፈጸመ ያምናሉ። ያ ቢሆን ብልጽግና ሥርዓት ገብ በሆነ ነበር። በወቅቱ የፖለቲካል ፓርቲ የአደረጃጀት መርህ ጥሰት እንዳለበት ስለፃፍኩበት አልመለስበትም። በሌላ በኩል የምርጫው በኮቢድ ምክንያት መራዘሙን አምነውበታል። የተፃፈውን የብልጽግና ሰነድ ሃሳብንም እንደሚያምኑበት በተደጋጋሚ በአጽህኖት ገልጸዋል።
#ሌላ አቶ ታየ ደንድዓ ሊያርሙት የሚገባ ብየ እማስበው "ሊቅ" እና "ሊሂቅ" የሚለውን ኃይለ ቃላት ይሆናል። አደባልቀውታል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ በዘመኑ ሊቃናት እንጂ ሊሂቃን እንዳሉ የማይቆጠሩ፣ ተሳትፎቸውም ልሙጥ እንዲሆን የተደረገ ነው። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ እርካታ የራቀው። ምርቃቱም የተነሳው።
በሌላ በኩል የኦሮሞ ህዝብን ቁጥር አንድ ጊዜ 40 ሚሊዮን ሲሉ ሌላ ጊዜ ደግሞ 50 ሚሊዮን ሲሉ ሰማሁኝ። ይህ የታሪካቸው አካል ስለሚሆን ግምታቸው ወጥ ቢሆን ባይ ነኝ።
#ነገረ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ጋር በጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የአቅም ስስነት ላይ ያደረጉትን ውይይትን መግለፃቸው የተገባ ነው ብየ አላምንም። ምክንያቱም ለአቶ ንጉሡ ጥላሁን ደህንነት ጥሩ አይደለም እና። አንድ ጊዜ አቶ ኦባንግ ሜቶ እና አቶ ጃዋር መሃመድ (ሃጂ) በጠሚር አብይ የትምህርት መረጃ ላይ የነበራቸው ተሳትፎ ሲገለጽ የተሰማኝን ጽፌ ነበር። ምክንያቱም አቶ ጃዋር እስር ላይ ነበር፤ አቶ ኦባንግም ኢትዮጵያ ስለሚኖር። መተዛዘን ያስፈልጋል። ጥንቃቄም።
የሆነ ሆኖ እስካሁን ከአየኋቸው፣ ከአዳመጥኳቸው የኦሮሞ ፖለቲከኞች፣ የማህበረ ኦነግ ፖለቲከኞች፣ አክቲቢስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ በየደረጃው ካሉ የፖለቲካ አመራሮች የተለየ ምልከታ እንዲኖረኝ አድርጓል በተለይ ከሆርን ጋር የነበራቸው ስክን ያለ ቆይታ። አቅማቸውን፣ የአቅላቸውን ልክም መዝኛለሁኝ። ስለዚህም ለፖለቲካዊ ህይወት ብቁ ሆነው አገኜኋቸው። ጥሩም ተናጋሪ ናቸው። ፖለቲከኝነት ርትዑ ተናጋሪነትንም ይጠይቃል፣ በዘርፋ ያሟላሉ። የሴራም ሆነ የቅንነት ድህነት በገለፃቸው ፈልጌ አላገኜሁም።
ስለሁለገብ የዕውቀት ዘርፎች፣ ተያያዥ አገራዊ ጉዳዮች፣ ጥንቃቄ የሚሹ ታሪካዊ ክስተቶችን በልኩ ለልኩ የመግለጽ አቅማቸው ወደ ክህሎት አድጓል። ኦሮማራና የአማራ ተሳትፎ ሃቅ ሳያዛንፋ፣ የታሪክ ምዝበራ ሳያጓጓቸው በልኩ ለልኩ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ለዛውም ውጪ አገር ያሉ ትንታግ የአማራ ልጆች ክፍት የነበረውን የሎቢ ተግባር በመሙላት የአገር ውስጡ የኦሮማራ ንቅናቄ ለስኬት እንዲበቃ የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ የስኬት ቁልፍ ቢያውቁ ኖሮ ሁሉ ብያለሁኝ።
ካለ ግሎባል ዕውቅና እና ይሁንታ ያ አንጋፋ የህወሃት የዞግ የፖለቲካ ድርጅት ፈቅዶ እንዲለቅ ማድረግ አይቻልም ነበር። ኢትዮጵያ አንከር ናት። የተፈለገውን ሁሉ ለመፈጸም አይቻልባትም። ሁሉ በውስጡ አይናገረው እንጂ እጅግ አስፈላጊ አገር መሆኗን ያምናልና። ወደፊትም መሻትን ለማሳካት የማስተዋል ዊዝደም ይጠይቃል።
ከሁሉም ለየት ባለ መልኩ የአማራን ህዝብ ሙሉ አቅም፣ ለለውጡ የነበረው ጉልህ ሚና ሳይድጡ፣ ሳይጨፈላልቁ፣ አጓጉቷቸው ለእኛ ለእኛ ሳይሉ ያስተዋለ የዘመን ትክክለኛ ዳኛ ሆነው ስለአገኜኋቸው ላመሰግናቸው እሻለሁኝ። "እኔ ነኝ ሞተሩ፣ እኛ ነን ጄነቴሩ፥ ካልኩሌተሩ" ከሚሉ ልጥፍ ዕሳቤወች የዳኑ ናቸው አቶ ታየ ደንድዓ። ልጽፍም ያነሳሳኝ ትልቁ አመክንዮ ዕውነት ጸሐይ ስለወጣለት ነው።
#የአለሎ አብዮታዊ ማራቶን በሁለት የማህበረ ኦነግ ሊቃናት።
ከሰሞኑም የዶር ለገሰ ቱሉ እና የአቶ ጃዋር መሃመድ (ሃጂ) የአለሎ አብዮት ማራቶን ነበር። አላዳርሰኝ ብሎ አልፃፍኩበትም እንጂ። በአጭሩ እንቅጩ በድንጋይ ውርዋሮ የወደቀ ሥርዓት የለም። ወደፊትም አይኖርም።
በጥበብ፣ በማስተዋል፣ በስክነት፣ በፈጣሪ እርዳታ ብቻ ህወሃት ፈቅዶ እና ወዶ እራሱም ድምጽ ሰጥቶ መንበረ ስልጣኑን አስረክቧል። አቶ ጃዋር መሃመድ (ሃጂ) አልነበረበትም። ቢኖርበት ይከሽፍ ነበር። ያን ኤክስትሪሚዝም የሚፈርም አንድም የሉላዊ ሊቃውንታት አይኖሩምና።
አፈፃጸሙ እንዴት? በምን ስልት? በማን አቅም? በምን የዊዝደም ልክ ለስኬት እንደበቃ በፍጹም ከጃዋሪዝም አቅም በላይ የተከወነ #ዘመን ሰጥ ክስተት ነበር። የዛን ጊዜው አጤ ግንቦት 7 ሆነ የሁሉም የአቅም ማዕከል፣ አብዛኛውን የለውጥ መሻት መሪ የነበረው የኤርትራ መንግሥት እንኳን በነጠረ ዕውነት ላይ እንዲህ ለመረማመድ አልፈቀዱም። ሰሞኑን የኤርትራው ፕሬዚዳንት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዕውነቱን ተናግረዋል።
ጃዋሪዝም ሆይ! ከተቻለ በሞቴ አፈር ስሆንልህ በድንጋይ ውርዋሮ፦ በአለሎ አብዮት አብይዝምን #አሰናብተኽ ታሳየን ዘንድ ትጠየቃለኽ። ባለፈውም በጀርመኑ ስብሰባህ መንግሥት መገልበጥ አይሰልችህና እባክህ አድርገኽ አሳየን ብየኃለሁኝ።
ወደ ቀደመው ……
#ከግንጫ ንቅናቄ በፊት ሆነ ከሐምሌ ፭ቱ "የኦሮሞ ደም ደሜ ነው፤ ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፣ ወዘተ" በፊት ቀድሞ አቶ ሞገስ አስጎደም ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ 500 የጎንደር ወጣቶች "#የፈራ ይመለስ" የተሜን አስተምኽሮ ይዘው አደባባይ ወጥተው ብዙ ፍዳ በዘመነ ህወሃት ተከፍሎበታል። ታሪክ ነጥሮ፥ ልቅም ብሎ፣ ሳይጋነን ወይንም ሳይንኳሰስ በልኩ ሊገለጽ ይገባል።
በዚህ አግባብ አቶ ታዬ ደንዳዓ የኦሮማራ ትጉህ ተሳታፊ የመሆናቸውን ያህል ሚዛናዊ ዕይታቸው አስደምሞኛል። ጠያቂው ቄሮ ኢህዴግን ለመጣል ያስቻለው ሁኔታ ብሎ ነበር ዘንጥሎ ቅርንጫፍ ጥያቄ ያቀረበው። አቶ ታየ ግን ዕውነትን አፈለቁት። ከዬትኛውም የኦሮሞ ሊቃውንት ያልተሰማ የሚያፈልቀውን ዕውነትን ገልጸዋል። የዘመኑን ክስተታዊ ድል ከክህደትም፣ ከቀማኛነትም፣ ከሽሚያ ፖለቲካ ዕውነትን አድነውታል። ባሉበት ፈጣሪ ይጠብቃቸወ። አሜን።
በጣም የገረመኝ እኛ ባተሌወች የአገርም የዓለም ዓቀፍ መሪወችን እንዳአሻን ለማግኜት ስንችል፦ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ጋዳ መሆኑ። አቶ ለማ መገርሳን (ዶር) ለማግኜት ሰማይ ቤት እንደነበር ተረዳሁ። የተከበሩ አንባሳደር ካሳ ከበደም ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት ፈጣሪ ያኑርልን እና፣ እሳቸም አቶ ለማ መገርሳን (ዶር) ለማግኜት ፈልገው እንዳልቻሉ በአንድ ቃለ ምልልስ ሲገልጡ ሰምቻለሁኝ። የእነሱን የፖለቲካ አቋም አምነው ለሄዱ እንኳን በሩ የተከረቸመ ነበር። #ያሳፍራል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድን ለማግኜትም ሙሉ አንድ ዓመት እንደፈጄም አዳመጥኩኝ። ደነገጥኩም። የማይበላ፣ የማይዳሰስ፤ የማይጨበጥ ጉድ ሆነ መሪነት ለኢትዮጵያ። ለዛውም በህዝብ ተመረጥኩ ለሚል።
የራስ አካል፣ ምክትል ሚር ጠቅላይ ሚኒስተሩን ለማግኜት አለመቻል ሲሰሙት እራሱ #መርግ ነው። ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ ዕልም እልም እንደሆነም ተረዳሁኝ። በተጨማሪም ቲም ወርክ በኢትዮጵያ በባዶ ቤት ኤሉሄ ላይ መሆኑን አገናዝቤበታለሁኝ። እኔ እማስበው ቢያንስ የኦሮሞ ሊቃናትን ለማግኜት ይቀላል ብየ ነበር። ጥሩ መረጃ ነው። በመሃል ያለውን ክፍተት፣ የመጠራጠር መንፈስ ይሁን የመፈራራት ብቻ ጥሩ ያልሆነ አየር እንዳለ ይገልፃል።
ጨዋታን ጨዋታ ያነሰዋል ይላሉ ባለ ቅኔወቹ ጎንደሮች።
አቶ ታዬ ደንድዓ እኔ በአማራ ማስ ሚዲያ በወል በነበራቸው ቆይታ " ኦነግ መሆን ወንጀል አይደለም" ብለው በድፍረት ሲናገሩ ስሰማ " ታዩ ማን ነው?" የሚለውን መከታተል ጀመርኩኝ። በወቅቱ ከአክቲቢስት ስዩም ተሾመ ጋር ሲታሰሩም ይፈቱ ዘንድ በደጉ ሳተናው ድህረ ገጽ ተግቼ ነበር።
ከተፈቱ በኋላ የነበራቸው የፖለቲካ አቋም ከግምቴ ውጭ ነበር። ስለዚህ በመቆጠብ ነበር እምከታተላቸው በተለይ አዲስ አበባ ላይ 5 ንጹኃን ሲረሸኑ፣ ለኦነግ አቀባበል 1300 ነዋሪወቿ ጦላይ ሲወረወሩ የአቶ ታዬ ደንድዓ የፖለቲካ አቋማቸው ምቾት አልሰጠኝም ነበር። አሁን ድረስም ያልተፈቱ እስረኞች አሉን። ፭ቱን ሰማዕታቱንማ የሚያስታውሳቸውም የለም።
አቶ ታዬ ደንዳን ይገልፃል። ለእኔ የሚሉት ቅርጥምጣሚ የድሎት መሻት አላየሁባቸውም። ግልጽነታቸውም፦ የሚዘሏቸው ጉዳዮች ቢኖሩም የአመኑበትን ሃሳብ በመግለጽ ረገድ አጥር የላቸውም።
ሌላው የታዘብኩት ሴራ ላይ ቤተኛ የመሆን ፍላጎታቸው ልሙጥ ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ። ጥንቃቄ በአንፃራዊነት ለራሳቸው ለማድረግ አለማሰባቸው ከግራሞት በላይ ነው።
ከአንከር ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድን የሰብዕና የገለጹበት ሁኔታ የነገ ተስፋ ሱባኤ እንዲገባ የሚማጸን ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ።
በሌላ በኩል "ልምድ ማነስ፣ ክህሎት አልባነት፣ አቅመ ቢስነት፣ የበታችነት ስሜት ማየል" ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የተገለጹበት የሰብዕና ጉዳዮች ናቸው።
የኢትዮጵያ የ፯ ዓመታቱ የቀውስ መፈልፈያ ማሽን ሥርዓቱ ሳይሆን ግለሰባዊ ትልም ስለመሆኑም በማገናዘቢያ አቅርበውታል።
ጥላቻ፣ ማፍረስ፣ መናድ፣ ሦስቱም የጦርነት ዓውዶች ግንባሮች ሁሉም የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የእጅ ሥራ ውጤት እንደሆኑ አቶ ታዬ ገልጸዋል።
#የአቶ ታዬ ደንዳዓ ኃይለ ስንኛት።
1) "ብልጽግና የሚባል ሥርዓት የለም። ብልጽግናም የለም ያለው የማፍያ ሥርዓት ነው።"
2) "የተፃፈ ብልጽግና፦ ያልተፃፈ ብልግና።"
3) "አስተማሪን ማስራብ ትውልድ መግደል ነው።"
4) "ሃኪም ሲርበው ሰው በበሽታ እንዲያልቅ ነው።"
5) "ሥርዓቱ በጦር ወንጀል፤ በሰባዕዊ መብት ጥሰት፤ እና ሙስና ይገልጸዋል።"
6)"ስሜን ዕዝ እንዲመታ እኛ ነው ያደረግነው፤ ፋኖ እንዲተነፍስ ወሎን ህወሃት እንዲይዘው አድርገናል፤ ጠቅላይ ሚር አብይ መሃመድ ይህን ደፍረው ተናግረውታል" የመልካምነት ድርቀት።
7) "ፍርኃትን እንደ ፖለቲካ መዋለ ኃብት" ሥራ ላይ ስለመዋሉ።
8) "ፖለቲካ ፍቅር አይደለም። ፖለቲካ ውስጥ ያሉት ፍትህ፤ እኩልነት፤ ነፃነት የሚቆጠሩ ማሳያ ያላቸው ናቸው ፖለቲካ።"
9) "የልጅ ልጆቼ አገር እንዲኖራቸው እፈለግለሁኝ።"
10) "እግዚአብሄር ሌላ አገርን መርቆ፤ እኛን የሚረግምበት ሁኔታ የለም።"
11) "ህዝብ ጨቋኝ ሆኖ አያውቅም።"
12) "የምክክር ኮሚሽኑ አገራዊ ጨዋታ ነው።"
13) "የደሰቲቱ ነዋሪወች" (ማህበረ ብልጽግናን ይመስለኛል) ጠያቂወች እነማን ናቸው ብለው ተጨማሪ ማብራሪያ ሊጠይቁበት ይገባ ነበር።
14) "ወንጀል ግለሰባዊ ነው።"
15) በታሰሩበት ቦታ ማዕከላዊ አለመዘጋቱን ሲገልጡ "ጥፍሩ የተነቀለ፤ ሰውነቱ #የተለተለ፤ እግሩ የተሰበረ እስረኛ" ማየታቸውን ገልጸዋል። ኦሮሞ ቢሆን ይገልጹት ነበር። የሌላ ማህበረሰብ አባል መሆኑን መመዘን ይቻላል። ጠያቂው ተጨማሪ ማብራሪያ ሊጠይቅበት የሚገባ ጉዳይ ሆኖ ሳለ አልፎታል። በተጨማሪም እሳቸው ለ፬ ወራት ጨለማ ውስጥ እንደታሰሩም አክለው ገልጸዋል።
16) በዘመነ ህወሃት "ፎርማሊቲ ነበር፤ ወንጀል በግለሰብ ደረጃ ሲሆን" በአብይዝም ግን የተገለበጠ መሆኑን ጠቅሰው፦ በሳቸው ቤተሰብ የደረሰውን ወንጀል በዘር ሐረግ ይተላለፍ ይመስል ወደ 28 የቤተሰቡ አባላትን ማካተቱ፤ "የሸኔ አባላት ቤተሰብ መንገላታት" በመመሪያ ስለመሆኑም አልደበቁም።
17) "ከጠላት ጋር ለምን ትገናኛለህ?" በቀጥታ ከጠቅላይ ሚር አብይ የቀረበ ጥያቄ ሲሆን፤ ጠላት የተባሉት አቶ ቹቹ አለባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
18) "የአማራን ውስጡን መፍረስ" የጠቅላይ ሚር አብይ ግዙፋ ፕሮጀክት ስለመሆኑ፤
19) የወልቃይት ጉዳይ "መንጠልጠል" የታቀደበት ሁኔታም እንዳለ በግልጽ አስረድተዋል።
20) "በሙያዊ፤ በሞራላዊ፤ በሶሻል ተወዳዳሪነት" የብልጽግናው መሪ ፕሬዚዳንት አብይ አህመድ ወድቀዋል ባይ ናቸው አቶ ታዬ።
21) ለአቶ ሙስጦፌን ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ "ከፌስቡክ ውረድ" የሚል ግሳፄ መስጠታቸውን ነግረውናል፤
22) "መደመር መበተን፤ መበልጸግ መጎሳቆል።"
23) "ሌብነት ቀይ ምንጣፍ ሆኗል፤ ሁላችሁም ሂዱበት ተብሏል።" #ክስተታዊ አገላለጽ ነው።
24) "የታሰበበት ጭቆና።"
25) "ከሰው ተኮር ቁስ ተኮር።"
26) "ነፃነት፤ ወንድማማችነት፤ እኩልነት እነኝህን ቃላቶች የሚጠሉ አይደሉም። አስምረህ ትጽፈዋለህ። ዋናው ጉዳይ ግን ልበወለድ ነው አሁን ላይ። የተፃፈ፤ የተነገረ፤ የተገባ ቃል አልተፈጸመም። ተቃራኒው ነው የተፈጸመው። እኔ ያመንኩት የተፃፈውን ነው። "
27) የአርቲስት ሃጫሉ ግድያ "ሌላ ቦታ ላይ ነው የተገደለው። ሬሳው ከተገደለበት ቦታ አይደለም የተገኜው ሌላ ቦታ ተወስዶ ነው የተገኜው። በሂደት "ሴራ" እንደሆነ መረዳታቸውን ገልጸዋል። የኢንጂነር ስመኜውም እንደዚህ ነበር የሚሉም ነበሩ። ሌላ ቦታ ተገድለው አስከሬኑ ወደ መስቀል አደባባይ እንደተወሰደ የሚያምኑ ብዙወች ናቸው።
28) ከጫካው ኦነግ ጋር የነበረው "ድርድር በብልጽግና ዘንድ በሰላም እንዲያልቅ አልተፈለገም።"
29) "መቼ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አይታወቅም።" ይከበደው መረጃ።
#የአቶ ታዬ የምክር አገልግሎት ለቀጣዩ የተስፋ ሂደት።
ሀ) "የራስን የክብር ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል።"
ለ) "ግልጽ ዓላማ ሊኖር ይገባል።"
ሐ) "ውጤት እና ዕድልን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል።" ዕድልን #አለማፍሰስ ብለው ይሻል ይመስለኛል።
መ) "ከግል ኢጎ ጋር መፋታት።"
ሰ) "በፍትህ፤ በነፃነት፤ በእኩልነት ኮንሴፕቶች ላይ በሚገባ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል።"
ረ) "መብት እና ግዴታ ግልጽ ሊሆን ይገባል።"
ሠ) "ታሪክን ልንማርበት እንጂ ልንጣላበት አይገባም።"
ሸ) "ፍላጎትን ማወቅ ያስፈልጋል።" እኔ በዘመነ ህወሃት ለመሆኑ ፍላጎታችን #እናውቀዋለን ብየ አንድ መጣጥፍ ጽፌ ነበር። ያን ነው አጽህኖት የሰጡት።
ቀ) "የተስፋ መዳረሻ ለማን? ተብሎ አስቀድሞ ሊሠራባት ይገባል"
#ጸጸት።
ሙሉበሙሉም ባይሆን አንፃራዊ መጸጸት አይቻለሁኝ።
#ፊትለፊት ወጥቶ የመታገል አቅም።
A+ 100% ታዝቤያለሁኝ። የደህንነት ባለሙያ በሚመራት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለምንም መጋረጃ ይህን ያህል ግልጽነት እና ድፍረት የሚደንቅ ሰብዕና ነው። ነገር ግን እራስን አድኖ መታገል ብልህነት መሆኑን አበክሬ አስገነዝባለሁ። ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም።
አቶ ታዬ ደንድዓ የ66ቱ/// የ1997 እኢአ // የግንጫ እና የሐምሌ ፭ቱ የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ያላነሰ ዕጣ ነፍሳቸውን በሰላማዊ ሁኔታ ታግለው ለድጋሚ ለካቴና ቤተኝነት ተዳርገዋል። ያነሷቸው ነጥቦች ብቻ ሳይሆን የአገላለፅ ግዝፈት ስለ ቀጣይ ህይወታቸው ሆነ ስለሚደርስባቸው የቀራንዮ ውሎ ቅንጣት አጀንዳቸው እንዳልሆነ ተረድቻለሁኝ።
በአብይዝም ሥርዓት ውስጥ ሆነው የሚያምኑበትን የማህበረ - ኦነግ መንፈስ በሂደት ለማሳካት የነበራቸው ትጋት እክል ገጥሞታል። ይህን ያህል የገዘፈ እና የደፈረ ሙግት ለጠሚር አብይ አህመድ ሆነ በዘመነ ህወሃትም ሳስበው የአቶ ታየ ደንድዓ ልቆብኛል። ለሚታገሉለት ህዝብ እና ለዓላማቸው አቶ ታየ ደንዳ እንደ ክስተት ሊታዩ ይችላሉ። ሳስበው የደም ዓይነታቸው O ይመስለኛል። ኦወች እጅግ ደፋሮች እና ለስኬታቸው እራሳቸውን ይሰጣሉ ይላሉ የዘርፋ ባለሙያወች። የሳቸው ያህል ግልጽ የተከበሩ አቶ ገ/ መድህን አርያን ማንሳት እችላለሁኝ። ሌላው ሲያፈነግጥ፤ አንጃ ሲፈጥር መለስ ቀለስ ነው።
#ትውልዱ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ።
" አንድ ነገር ከመፈጠሩ በፊት ድምፃቸውን ማስቀረት።" ከባድ ዋርኒግ ነው። ከዚህ አንፃር ለተወሰነ ጊዜ መታሰራቸው ከየትኛውም ስሜታዊ አጥቂ የሚታደጋቸው ይመስለኛል። ስጋቴ ይህ አቅም ይለፍ መቼ ያገኛል? መልስ አላገኜሁለትም። በሌላ በኩል አዕምሯቸውንስ አሁን ባለው አቅሙ ልክ እንዲቀጥል ይፈቀድለታል ወይ? የሚያሰጉ ሁኔታወች አሉበት።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የራሳቸው የውስጥ አዋቂ፥ አካላቸው በዚህ ልክ አደባባይ ወጥቶ ሲሞግታቸው ታግሰው ለትውልዱ አብነት የሚሆን አወንታዊ ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ ወይ? ለዚህም መልስ የለኝም። የብልጽግናው ፕሬዚዳንት ስሜታቸው ስስ እንደሆነ በተለያዬ ጊዜ አስተውያለሁኝ። መሪነትን የሚያልቅ የመቻል ልዩ አማካሪ ከቅርባቸው ይኖራልን? እሳቸውስ ምክር ይቀበላሉን? ይህም ሌላ ያስጨነቀኝ ጉዳይ ነው።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አቶ ታየ ደንዳዓ የሚያቀርቡትን ትችት ፊት ለፊት እያገኙ በማወያዬት እርምት ለማድረግ አለመፍቀዳቸው፥ ሲከር ይበጠሳል፤ ሲሞላም ይፈሳል ሆነ። ይህ ለትውልዱ ያለው ጠቀሜታ ኪሳራ ይመስለኛል።
ሌላው የአማራ ልጆችን፤ የአማራን ህዝብ፤ የአማራን መንፈስ በዚህ ልክ በዬፌርማታው ከጠሉት ጠቅላይሚር አብይ አህመድ አሊ ጋብቻ ከአማራ ልጅ ጋር ለምን ፈቀዱ? ሰሞኑን ከራሴ ጋር የተሟገትኩበት አንኳር ነጥብ ነበር። ወደፊት ከፈቀዱላቸው የአማራ ሊቃናት ጋርስ በምን ስምረታዊ ጉዞ የስልጣን ዘመናቸው ይቀጥል ይሆን? ይህም ከህሊናየ አቅም በላይ የሆነ ያልተመለሰልኝ ጉዳይ ነው።
በሌላ በኩል የከረዩ አባገዳወች ጉዳይ፤ የአርቲስት ሃጫሉ ጉዳይ፤ በጠቅላላ ነገረ ኦሮሞ ጉዳይንስ አቅረበውታልን? በሰማሁት ቃለ ምልልስ እና ባገኙት አጋጣሚ ደቡቦችን ወደፊት የማምጣት ጥረታቸው የተሻለ ዝንባሌ ለደቡብ ህዝብ እንዳላቸው ልሰብ አልኩና፤ ነገረ ጋሞ፤ ነገረ ወላይታ፤ ነገረ ጌዲኦ፤ ነገረ ጉራጌን አሰብኩ እና ጠቅላይ ሚር አብይ የማን - ለማን ናቸው? የሚለውን መፍቻ ፍለጋ ማሰንኩኝ።
በዚህ ቃለ ምልልስ ብዙ ሰው ሊያስተውለው የሚገባ ጉዳይ በኢትዮጵያ የስሜት ፖለቲካ ወደ ስክነት ፖለቲካ የማሸጋጋር አቅም ያለው ቲም ሊደር እና ተቋም እንደሚያስፈልጋት ያስረዳል። ይህ ብቻ ሳይሆን የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የመፍትሄ አካልነትን ሰርዞ መነሳት የማያዋጣ ጎዳና መሆኑ ያመሳጥራል። ለዚህም ነው እኔ አብይዝምን አሳቻ፤ ዘመኑንም አሳቻ የምለው። ጥንቃቄ የሚሹ ብዙ ጉዳዮች አሉ።
አቶ ታየ ካነሱት እኔ እማልስማማበት አቅም፤ ክህሎት፤ ልምድ ለተባለው ነገር። የኢንሳ መሥራች፤ የሳይንስእና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር፤ የኦሮምያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት እና ጸሐፊም፤ የቢሮ ኃላፊ፤ የፓርላማ አባልነት ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድን ከክህሎት፤ ከልምድ ነፃ ሊያደርጋቸው አይችልም የሚል ሙሉ ዕምነት አለኝ። ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚር የትውልድ አድርገው መሠረቱን አጥብቀው እንዳበጁት ስከታተላቸው ስለነበር ሃሳቡን ልገዛው አልቻልኩም።
እርግጥ ከአንድ የሚር ደረጃ፤ ከአንድ የክልል አካልነት ወደ አገር መሪነት ለዛውም የሁሉ የመንፈስ ማረፊያን ኢትዮጵያን መምራት ጋር ሳይጣጣም የቀረ ክፍተት እንዳለ አያለሁኝ። የአትኩሮት አቅጣጫ ውስንነትም አስተውላለሁኝ። ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብሎ ቢሮክራሲያዊ የሆኑ ተግባራትን በመከወንም እረገድ ስስነት እመለከታለሁኝ።
ብቻ ……… የሆነ ሮንግ የሆነ የውስጥ መሻት ከተጨባጩ ኢትዮጵያዊ ተፈጥሮ ጋር አለመናኜት መተላለፍ፤ በተፈጥሮኛ፤ በሰውኛ አግባብም ቂም፤ ጥላቻ፤ በቀልን ለመንቀል ተጨባጭ እርምጃ አላየሁም። የማዘን፤ አጽናኝነት፤ አይዟችሁ ባይነት ቦታ እንዳላገኙም እመለከታለሁኝ።
ይህም ሆኖ ተስፈኛው ምን አለው? ማንስ አለው? ከተለመደው የድረስ ድረስ ፖለቲካ ስክነትን የሰነቀ፤ በሃሳብ የቀደም ክንውን አላይም። ቃለ ምልልሶችን ሳዳምጥ ጥላቻ የገዛቸው ናቸው። ጥላቻን ጥላቻ ሊፈውሰው ፈጽሞ አይችልም። የተሻለው ኢትዮጵያዊ ውስጥነት ቢሰነቅ፤ ከሚስጢር ጋር ለመተዋወቅ ቢፈቀድ ነገን ለማግኜት ይቻል ይመስለኝ። በፈግጪው ፖለቲካ አንከሯ ኢትዮጵያን ማዳን የሚቻል አይመስለኝም።
ሌላው ሦስቱንም የጦርነት ሁኔታ በመድቀቅ፤ በመፍረስ፤ በመበታተን ታቅዶ የሚከወን ከሆነ ኢትዮጵያ በጠላት አገር ወይንስ በልጆቿ ይሆን የምትመራው ያሰኛል።
አዲስ ኮንፓስ የአቶ ታዬ ደንድዓ የሳምንት ጉዳይ ነው ሲል አድምጫለሁኝ። ሂደቱ፤ ጭብጡ፤ የተገኙ መረጃወች፤ ቀጣዩ አቅጣጫ ሁሉም ከብልጽግና ጋር የተያያዘ ስለሆነ አመክንዮው ተኖ የሚቀር አይመስለኝም። ይሄው እኔ እንኳን ፃፍኩበት። ብዙውን ጉዳይ ጨምቼ ነው እምከታተለው። ምክንያቴ ዕውነት እና መርኽ ጠበቃ አጥተው ክልትምትም ሲሉ ስለምመለከት ነገ እራሱ ከመምጣቱ በፊት ያስፈራኛልና።
የእኔ ክብሮች የፊደል ግድፈቶች ቀስ እያልኩ አርማቸዋለሁ። ጭብጡ ሳይጠነዝል በሚል ነው ሃሳቡ የቀረበው። የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ መዳፋችን ላይ አለ። እሱም ቅንነት።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ሆርን ኮንቨርሴሽን ስለ አዲስ አበባው የመስከረሙ 2011 ዓም 5 ንጹኃን ርሸና፣ ስለ ሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ሊቃናት ትራጀዲ ቢያነሳ ልቤ ፈልጎ ነበር።
ልዩ ቆይታ ከአቶ ታዬ ደንደአ አረዶ ጋር (ክፍል 1)
ልዩ ቆይታ ከአቶ ታዬ ደንደአ አረዶ ጋር (ክፍል 2)
ልዩ ቆይታ ከአቶ ታዬ ደንደአ አረዶ ጋር (ክፍል 3)
Anchor Special ከአቶ ታዬ ደንደአ ጋር የተደረገ ቆይታ (ከመታሰሩ በፊት)
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
22/06/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ