ነገረ ኢህአፓ። ዕድሜ እኮ የኔታ ነው ውስጡን ለፈቀደ።
ነገረ - ኢህአፓ። ዕድሜ እኮ የኔታ ነው ውስጡን ለፈቀደ።
እንዴት አደራችሁ ማህበረ ቅንነት?
#ጠብታ።
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ላም እረኛ ምን አለን ዕውቅና ሰጥተውት እንደማያውቁ አውቃለሁኝ። ግን ውስጤን መግለጽ አይቋረጥም። ይቀጥላልም።
ኢህአፓን በሚመለከት ሚዲያ ላይ ተቀጥሬ እሰራ በነበረበት ጊዜ በስብሰባው ተገኜቼ ያየሁትን፤ የሰማሁትን ከመዘገብ ውጪ ኢህአፓን እንደ አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅትነቱ ሞግቼው አላውቅም። ምክንያቴ እንደ ልፋቱ ዕድል ያልቀናው ባተሌ መሆኑን አውቃለሁኝ። ለአውራ የፖለቲካ መሪነት እንኳን ያልበቃ ነው ኢህአፓ። መንግሥት ሆኖም ስለአላየሁት ዕድል ለተላለፈው የፖለቲካ ድርጅት ምን ፍጠር ብየ ልሞገትው? ልተቸው። ኢህአፓ በመገበር የኖረ የፖለቲካ ድርጅት ነው።
እኔ የኢህአፓ #አባልም፤ #አካልም ሆኜ አላውቅም። መንፈሱም አልተጠጋም ከእኔ። ምክንያቱም ጠንካራ እናት ስለነበረችኝ ማንኛውም እንቅስቃሴየን ትቆጣጠረው ስለነበር ወደ ኢህአፓ ትውር አላልኩም። "ትምህርት ቤት አትሂዱ፤ አትማሩ" የወቅቱ የኢህአፓ ሞቶ ነበር። እናቴ ግን ጥጧን የሚሳሳውን ይዛ፤ ደብተሬን በዘንቢል ተሸክማ ገብያ የምንሄድ መስለን ትምህርት ቤት እራሷ ትወስደኝ ነበር።
ትምህርቱ እስኪያልቅ ድረስ ጠብቃ በሄድንበት መንገድ ሳይሆን መንገድ #ቀይራ ወደ ቤት ትመልሰኛለች። ብዙ ማስጠንቀቂያወች በደጃፋ ሥር ከኢህአፓ ይላክም ነበር። የእናት፤ የፆታ፤ የሥርዓት ጭቆና አለባት ይሉ ነበር ኢህአፓወች። የማልሸሽገው ትምህርት ቤት ውስጥ፤ ከውጭም፤ በረፍት ጊዜም #ጭንቀቱ ከባድ ነበር። ስጋቱ አይጣልባችሁ። በዛ ላይ አባባ ጫካ ነበሩ። ዱር ቤቴ ብለዋል። ተሎ ደርሼም የቤተሰብ ኃላፊነት የመረከብ የታላቅ እህት ግዴታም ነበረብኝ።
በራሪ ወረቀቱን እናቴ ስታገኜው እኔን ሳታሳይ አንብባ ትቀደዋለች። እኔ ሳገኜው ደግሞ አንብቤ አስቀምጠዋለሁኝ። የማስቀምጠው የፖለቲካ ምኞት ኑሮኝ ሳይሆን በጣም አንባቢ ስለነበርኩኝ የአረፍተ ነገሮች አሰካክ ይማርኩኝ ስለነበር ነው። እኔ የሳይንስ ቶፕ ተሸላሚም ተማሪ ነው የነበርኩት።
ምኞቴ በሰው ተፈጥሮ ወይንም በዩንቨርስ ተፈጥሮ ምርምር ላይ ማተኮር ነበር። እቴጌ ጎንደር ባለባት የትውልድ ዕዳ ከፋኝ ያለውን ሁሉ ተሸክማ ማሻገር ተሰጣት እና ህልሙም፤ ራዕዩም ሆነ ወጣትነቱም፤ የትምህርት ጉጉቱም #ተኖ በኖ ቀረ። አሁን አዝናለሁ "#አትማሩ" የሚል አዲስ ንቅናቄ ሲፈጠር። ጅልነት ነው። በመፈጠር ላይ #ያደመ #ቧልት።
አስተዋይ ጎንደሮች ልጆቹ ያለፋበትን የመከራ ዶፍ፤ የዕድል መደፋት ግምት ውስጥ አስገብተው ግድፈቶችን አርመው፦ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ የመጀመሪያ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል። ብዙወቹ የተማሩ ናቸው "አትማሩ" የሚሉት። ብልህነትን አስቀድሙ። ጠቃሚው ዕድልን በዕድሜ ማስተናገድ ይገባል ባይ ነኝ።
#ዛሬ እና ኢህአፓ።
ኢህአፓ አገር ውስጥ ያለው ብቁ ሴት ጸሐፊወች በየጊዜው እንዳለው ተመልክቻለሁ። የመጀመሪያዋ ጠቅላይ ሚር የመሆን ምኞት እንደነበራቸው አድምጫለሁኝ። እርግጥ አሁን ፓርቲያቸውን ለቀዋል። አሁን የተኩትም ሴት ናቸው። ይህ የሚያሳየው ኢህአፓ #ለሴቶች አቅም ልዩ ዕውቅና የመስጠት ህሊና እንዳለው ነው። በዱር ቤቴ ዘመን ትግል ወቅትም እኩል ድርሻን የኢትዮጵያ ሴቶች አበርክተዋል። እስካሁን ኢህአፓ ሴት ሊቀመንበርን የመፍጠር ፈቃዱን ባላይም ቁልፍ ቦታ መስጠቱ ሊያስመሰግነው ይገባል ባይ ነኝ።
አሁን አገር ውስጥ ያለው የየትኛው የኢህአፓ መሪ አካል እንደሆን በግልጽ አላውቅም፤ የአቶ መርሻ? የአቶ እያሱ ወይንስ የአቶ ፋሲካ? የኢህአፓ መንፈስ ወራሽስ ማን ነው ለሚለውም እኔ መልስ የለኝም። የታሰሩ ቀደምት የኢህአፓ ታጋዮች ጉዳይ ማን ኃላፊነቱን ሊወስድ ይችላል ለሚለውም መልስ የለኝም። ቢያንስ ግን የኢህአፓ ውህድ መንፈስ ሙሉ ዕድሜያቸው እስከ ህልፈት ካቴና ላይ ለሆኑት ግን አንድ ላይ ሆነው ለመፍትሄ ሊተጉ ይገባል ብየ አስባለሁ፤ አምናለሁም።
የሆነ ሆኖ ሰሞኑን አንድአፍታ ጋር የወቅቱ ጸሐፊ የሰጡትን ቃለ ምልልስ አዳምጫለሁኝ። ሙሉ አቅም እንዳላቸው ተረድቻለሁኝ። ገዢው ብልጽግና የካቢኔ አባሎቹ ጋር ሲነፃጸር ጥቂት ጠንካራ ሴት ሊቃናትን በአብይዝም ካቢኔም ስለማስተውል፤ ከጠንካሮቹ ጎን አቻዊ የአቅም ክህሎት ከኢህአፓ ጸሐፊ አይቻለሁኝ። አደራየ የአብይዝም አስተዳደር እኒህን ጠንካራ የሴት ሊቅ #ለካቴና እንዳያጭ አበክሬ በትሁት መንፈስ ላስገነዝብ እሻለሁኝ።
ሊያስተካክሉ ይገባል የምለው በዛ ቁልፍ ቦታ የተቀመጠ የአንድ ተፎካካሪ አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅት ፀሐፊ የአገር መሪን በአክብሮት መጥራት የመጀመሪያ ረድፍ #የዲስፕሊን እርምጃ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ። "#አብይ" ይህ የተገባ አይደለም። ለዛውም ጋዜጠኛ ለሆነ ሰብዕና? ይህ ግድፈት ወጥ በሆነ ሁኔታ በዘለቄታ ሊታረም ይገባል ብየ አስባለሁኝ። ወጣ ገብም ሊሆን አይገባም። በቋሚነት በባህላችን ልክ "እርስወ "የሚል ኃይለ ትውፊት ሊከበር ይገባል። ጀርመኖች ቢያዳምጡት ይደነግጣሉ። በግስ እርባታቸው፤ በስዋሰው ህገ - ደንባቸው እርስወ የሚለው ሆፍልሽካት እራሱን ችሎ ይሠራበታል። እርስወ ሲፃፋ በትልቁ ፊደል በካፒታል የመጀመሪያው ፊደል ይፃፋል። (sie #Sie #Ihr ihr ) ወዘተ ……
በሌላ በኩል የአንድ አገር መሪ መጠሪያው የሚመራት #አገር ናት// ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ አገር ልትከበር ይገባል። የአገር መሪ ተወደደም፤ ተቀበልነውም /// አልተቀበለውም የፈላስፊት ኢትዮጵያ የመቅድም መጠሪያ አቶ እገሌ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚር መባሉ ግድ ነው። አክሰሱ ላላቸው ታዳጊ ወጣቶችም እኛን በሚያብራሩ የከበሩ ይተብኃሎቻችን ላይ በጥንቃቄ ድርጊት ላይ ማዋል ግዴታችን ነው። ማንኛውም የመንግሥት አካል ተከብሮ ሊጠራ ይገባል።
በሌላ በኩል የኢህአፓ የወቅቱ ጸሐፊ ከአንድአፍታ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ውስጥ "ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው አንድ ስብሰባ ድርጅታቸው እንዳልተገኘ" ጠቅሰዋል። መገኜትም // አለመገኜትም መብት ቢሆንም፤ አለመገኘቱ ግን ጠቃሚ ነው ብየ በፍፁም አላምንም።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ከተጠማኝ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ከተደማሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ከተዋህጅ እጩ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይም ኢህአፓ በስተመጨረሻ ላይ ስብሰባውን ረግጦ መውጣቱን፤ ጉብኝቱ ላይም መኪና ውስጥ ቁጭ ብለው የኢህአፓ ተወካዮች እንዳሳለፋ ከአንከር ሚዲያ ጋር የኢህአፓ ውክል አካል በነበራቸው ቆይታ ሲገልጡ ሰምቻለሁኝ። ይህን ማድረጋቸው መብታቸው ነው። ግን የሚጠቅም አይመስለኝም። እርግጥ ነው ኢህአፓ ጥያቄ የማቅረብ መብቱ እንደተነፈገ አድምጫለሁኝ። ይህም የተገባ አይደለም። የአገር መሪነት ኩርፊያ ምራኝነት ኮበሌያዊ መንፈስ ግዛኝ ነው።
ጋብዞም በር ለዛውም ዋናውን መዝጋት፦ የክት እና የዘወትር፤ የቤት እና #የእዳሪ ልጅነት ዝንባሌ #ጥሬከብስል የሆነ የፖለቲካ አቅም ነው። መሪነት ከሰፈር - ከግል ምኞት - ከስሜታዊነት - ከግል ዝንባሌ ጋር ሊለካለክ በፍጹም አይገባም። አብይዝም ያገኜው የ፯ ዓመታት ዕድል ሊያሰለጥነው፦ ከለጋዊ አሰተሳሰብ እና ሂደት ሊያፋታው ይገባ ነበር።
ለአብይዝም ትክክለኛ ሞረዱ አብን ሳይሆን ኢህአፓ ወይንም እናት ፓርቲ ናቸው። እነኝህን የፖለቲካ ድርጅቶች ብልጽግና ሚስ ላለማድረግ ከቶፋ ልብ ወደ ቸረቸራ ልበሰፊነት ሊሸጋገሩ ይገባል። ለሥልጡን የፖለቲካ ድርጅት የሚቅለሰለስ ጓዳ- ለጓዳ የሚትበሰበስ ሳይሆን በጠንካራ መንፈስ፤ በግልጽ ዓላማና ግብ በሙሉ ሞራል እና ኮንፊደንስ የሚሞግት የፖለቲካ ድርጅት መኖር ለአንድ አገር ገዢ የፖለቲካ ድርጅት ህልውና ስጦታ ወይንም ሽልማት ነው። ፍጽምና አይጠበቅም። ፍጽምና እንኳን ከጀማሪው ብልጽግና ከአንጋፋወችም የለምና።
#በሌላ በኩል ……
ኢህአፓ እኮ አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅት ነው። እንደ አንጋፋነቱ #የስክነት ፖለቲካ በእጅጉ ሊናፍቀው ይገባል። ይህም ስለሆነ ነው አገር ውስጥ ገብቶ በህጋዊ ዕውቅና ትግል የጀመረው። ስለሆነም የተረጋጋ የፖለቲካ እርምጃ የፊደል ገበታ የኢህአፓ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ። ለሌሎችም ኢህአፓ የሮልሞዴል ሚናን ሊጫወት በተግባር ይገባል። እኔ ቀደም ብየ እንደገለጽኩት ኢህአፓ አይደለሁም። ኢህአፓም ሆኜ አላውቅም። ግን በውጭ እንደምከታተለው የኢህአፓ ህልውና ማዕከሉ ዲስፕሊን መሆኑን አዳምጣለሁኝ። ከቀደምት የኢህአፓ ተመክሮ ጠቃሚውን ብቻ ለይቶ ማስቀጠል ከድርጅቱ የሚጠበቅ በኽረ ጉዳይም ይመስለኛል።
የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ በሰላማዊ ሁኔታ እታገላለሁ ላለ የትኛውም አካል #ካፒቴኑ ነው። መርከቧ ካለካፒቴን ውቅያኖስን መሻገር አይችልም። ስለሆነም በሰላማዊ ሁኔታ ታግየ በትረ ሥልጣኑን እረከባለሁ፤ ወይንም ተመጣጣኝ ዕድል ቢገጥመኝ በጥምረትም ይሁን በውህደት ሳይንቲስቷ ን ኢትዮጵያን እመራለሁ የሚል የህሊና ሙሉ የአቅም እና ጥሪት ያለው ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት ከስማ በለው ይልቅ በቦታው ተገኝቶ የሚባለውን አድምጦ እና መዝኖ፤ ለዓላማው ስኬት የሚበጀውን ሃሳብ አቅርቦ፤ ሃሳቡን የሚገዙ አጋሮቹንም አፍርቶ፤ ገዢው ብልጽግናንም በሃሳብ ብልጫ መምራት እየቻለ #የለሁምን ፈቅዶ አለመገኜት የተገባ አይደለም።
ኢህአፓ የትናንት፤ ወይንም የዛሬ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም። ከየቤተሰቡ ብዙ በጣም ብዙ ቤተሰብ ተገብሮብናል። ብዙወች እንደወጡ ቀርተዋል። ስንት ሳይንቲስት፡ ስንት ፈላስፋ፤ ስንት የግሎባል የዕውቀት መንበር ሊሆኑ የሚችሉ ባለ ብሩህ አዕምሮ ዕንቁወች ተገብረውበታል፤ ያን የሚክስ ሁነት መፍጠር ባይቻል እንኳን ዘመኑን የመጠነ የእርጋታ ጉዞ መጀመር ኢህአፓ ይገባዋል ባይ ነኝ - እኔ። የአቶ እያሱ አለማየሁ መጸሐፍ ወደ ተውኔት መቀየሩ የስክነት ፖለቲካ ስኬት ነው። ትውልድ በአንድም በሌላም ይማርበታልና።
በሌላ በኩል ኢህአፓ ቢቀናው በትረ ስልጣኑን የማዕከላዊ መንግሥት ቢረከብ የኢትዮጵያ መዋለ ንዋይ የፈሰሰበትን፤ የኢትዮጵያ መዋዕለ መንፈስ የረበበትን፤ ከህዝብም አንፃር በውጤቱ የተወሰነው የህዝባችን ክፍል የረካበትን የአብይዝም የተለያዬ ፕሮጀክቶች ጉብኝት አለመሳተፍ አትራፊ ነው ብየ አላምንም።
ምክንያቱም ነገ ማዕከላዊ ሥልጣን ኢህአፓ ቢረከብ፥ የአብይዝም ጠረን ያለበት የግንባት ሂደት ሁሉ አልይህ አልስማህ የሚል ከሆነ ባለፍንባቸው የትግል መስመሮች ሁሉ የገደፍንባቸውን ስንኩል ጎዳናወችን መድገም ይሆናል። ቀደም ባለው ጊዜ ከህወሃት ጋር ይሰራሉ የሚባሉ የጥበብ ሰብዕናወች ሙዚቃን በሚዲያ ማግለል፤ አንድ መጠሪያችን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስኬት መጠየፍ፤ የአባይ ግድብን ታላቅ ፕሮጀክት አልይህ አልስማህ ማለት የጠቀመው - ያተረፈው - ያሳካው አንዳችም ፋይዳ አልነበረም። ያ የግድፈት መስመር ሊታረም ሲገባ ይድገም የተገባ አይደለም። ጀማሪ ፖለቲከኞች ቢያደርጉት አይደንቀኝም። ለኢህአፓ ትውልዳዊ ጉዞ ግን ፈጽሞ የማይጠቅም እርምጃ ነው ብየ አምናለሁኝ።
በተጨማሪም ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ጋር በነበረው ስብሰባም ኢህአፓ ጥሪውን አክብሮ መገኜቱ የተገባ ነበር። ዕድልን አለማፍሰስ ነው። ከተገኙ በኋላም አንጋፋ የትውልድ የፖለቲካ ድርጅት ቁጭላ ልብ፦ ሳይሆን ግሎባል ልቡን ተጠቅሞ፤ ጠብቆም አስደማሚ የሆነ ትዕግስቱን፤ የመቻል አቅሙን በራሱ እጅ ሊጽፍ ሲገባ ስብሰባውን ረግጦ መውጣቱ የተገባ ነው ብየ በፍጹም አላምንም። ኮበሌ - ጎረምሳ - ኮረዳ መንፈስ የሚመራቸው አቅሞች እንዲህ ሊፈጽሙ ይችላሉ። ለኢህአፓ አፈጣጠር ይሁን የዘመን የተጋድሎ ተከታታይ ጉዞው ግን የሚመጥን እርምጃ ነው ብየ በፍጹም አላምንም።
ጠቅላይ ሚር አብይ እና በሚያስከትሏቸው የካቢኔ አባሎቻቸውን ገጽ ለገጽ ማግኜት፤ የመልስ አሰጣጡ ሂደት የአካል እንቅስቃሴ እና መንፈሱን በአካል ከማየት፤ ከመገምገም ይልቅ ባይተዋርነትን ፈቅዶ፤ በስማ በለው መረጃን ማሽተት፤ የራስን የዕድል ማዕድ በር በራስ እጅ ዘግቶ ኤሉሄ የሚያዋጣ ጉዞ አይደለም። ምን ተባለ? እንደምን ተጠናቀቀ? ብሎ ሌላ ሦስተኛ አካል መጠየቅ ወይንስ የነበረው እንዲህ ነበር ብሎ ያዩትን ለአባላቱ፤ ለአካላቱ መግለጽ የቱ ይቀላል? የቱስ ነው የብልህነት ጉዞ? #ዕድሜ እኮ #የኔታ ነው።
ኢህአፓ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አናባቢም፤ ተነባቢም ሊሆን የሚችለው በፍጹም ሁኔታ ከወጣትነት- ከኮበሌነት - ከኮረዳነት - ከጎረምሳነት - ከእልህ፤ ከገረጭራጫነት ጸበለ ፃዲቅ አቅዶ መለየት ሲችል ብቻ ይሆናል። እኔ በጋሜየ ነበር ፖለቲካ ውስጥ የነበርኩት። ፖለቲካ ውስጥ የገባሁት አውቄው አልነበረም። በሥራየ ትጉህ ነበርኩኝ። እጅግ ትጉህ። በዛ ትጋቴ ተመርጬ ለፖለቲካ ኮርስ ስላክ ከጎበዝ ተማሪነቴ ጋር በባዕቴ የጦርነት ቀጠናነት ምክንያት ስለተለያየሁ ዕድሉን የሰማይ ስጦታ ነበር። የሆነ ሆኖ ከውስብስቡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አጋጣሚ ሲዶለኝ የመጀመሪያ እርምጃየ #ወጣትነቴ ጋር መተላለፍ ነበረብኝ። ወጣትነቴን መርሳት። ወጣትነቴ ሳያውቀኝ እኔም ሳላውቀው ፈቅጄ፤ ተፈቃቅደን ተላለፍን። ለምን? በዛ ዕድሜ የተሰጠኝ ኃላፊነት ግዙፍ ስለነበር። ዓላማም ስለነበረኝ። የቤተሰብ ኃላፊነትን የምትረክብልኝን ታናሼን ባርችን ተክቼ እኔ ትምህርቴን የመቀጠል ግዙፍ ፕሮጀክት ስለነበረኝ።
የኢህአፓን የየወቅቱን ጸሐፊወች ሳዳምጥ ውስጤን አይበታለሁ። ግን እኔ በፍጹም ሁኔታ ወጣትነቴ ሰርዤ ነው እሰራ የነበርኩት። ቦይፍሬንድ፣ ፍቅር በልጅነት ጎጆ ታስበው የማያውቁ ነበሩ በእኔ ህይወት። ሙዚቃ እንኳን ሰምቼ አላውቅም። ሁልጊዜ በሥራ መጠመድ ብቻ። ከዕድሜየ በእጅጉ የበለጡ የበሰሉም የፖለቲካ ሊቃናት ነበር ኮትኩተው ያበቀሉኝ፤ ያሰበሉኝ። ወጣትነቴን ባልተላለፈው ለዛ ፈጣን የሆነ የደረጃ ዕድገትም ሆነ ተቀባይነትም አልበቃም ነበር። በዘመኔ በዕድሜየ አቻ የሆነ አለቃ ገጥሞኝ አያውቅም። በወጣትነቴ ላይ ተጽዕኖ እንዳደረገብኝ ባውቅም ግን ዲስፕሊኑ በእጅጉ ጠቅሞኛል።
ወጣት ፖለቲከኞች በፖለቲካ ድርጅት መሪነታቸው ባገኙት የመሪነት ዕድል የድርጅታቸው ዓላማ እና ግብ ለማሳካት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። እያንዳንዱ የቃል #ዘለላ ወለምታ ይሁን ውልቃት ጉዟቸውን እንዳያሰናክል ጥንቃቄ ሊያደርጉበት ይገባል ባይ ነኝ። "ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅምም" ይላል የእግዚአብሄር ቃል። የሚጠቅም ቢሆን እንኳን ጊዜ፤ ሁኔታ እና ቦታ ጋር መጣጣሙ ሊታይ ይገባል። የሚጠቅም ዕውነት ሁልጊዜ ሊጠቅም አይችልም። ጊዜ መስጠት፤ የቦታ ለውጥ ማድረግ የሚጠይቁ ሁነቶችን በማስተዋል መመርመር ይገባል። ቢያንስ ኢህአፓ እንኳን የትውልድ የፖለቲካ ድርጅት የመሆን ዕድሉ እንዳይጎሳቆል ለህልውናው ጥንቃቄ መሪወቹ ቢደረጉለት ፍላጎቴ ነው።
የአብይዝም የህሊና ውል የሆኑ የፕሮጀክት ትልሞች ዓላማቸው እና ግባቸውን ለማስፈጸም የሚፈሰው መዋዕለ ንዋይ፤ መንፈስ እና ሥልጡን አቅም ለህዝብ ከሚሰጠው ጥቅም፤ ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል የስንት ሰው ህይወት እንደተዛባ፤ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ብሄራዊ ጉዳዮች እንዳሉ እኔም አምናለሁኝ።
ግን አይቶ መሞገት ወይንስ ሳያዩ መሞገት የቱ ይቀላል? እያዩም እኮ ገለፃው ላይ ገላጮችን መሞገት ይቻላል። መልካም አገር ጠቀም፤ ህዝብ ጠቀም የሆኑ ከሆነም ዕውቅና መስጠቱ ሥልጣኔ ነው። ቀደም ብየ እንዳነሳሁትም ዕድል ቢቀናው ኢህአፓ እነኝህን ፕሮጀክቶች ማስቀጠል እንጂ እንደ ህወሃት ደርግ የሠራውን አልይህ አልስማህ ማለቱ፤ በሌላ በኩል ጦርነቱን ተከትሎ ህወሃት አማራ እና አፋር ክልልን እራሱ የሰራቸውን የህዝብ መገልገያወች በበቀል ማውደም፤ ለዛውም የብድር ዕዳው ተከፍሎ ሳያልቅ የፖለቲካ #ቆባነት ነው ለእኔ። ይህን የማይጠቅም ውርስ ማስቀጠል መቼውንም ቢሆን ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ህይወት ጎጂ የሆነ አክሳሪ ጎዳና ነው።
በሌላ በኩል የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት በሚሳተፋቸው ህዝባዊ መድረኮች ሁሉ ትውልድ ሊማርበት የሚችለውን ታሪክ መሥራት ያስፈልጋል። ወጣትነትን የፖለቲካ ተሳትፎ ጋር ሲገናኙ በቅጡ ማስተዳደር እና መምራት ይገባል ባይ ነኝ። ሳንከባበር መደማመጥ አይገኝም እና። ሳንከባበር የትውልድ ተስፋ መሆን አይቻልም እና። ዕውቅና ሳንሰጥ ዕውቅና ማግኜት አይቻልም እና። በዳታ ማውጣት ባይቻልም አብይዝም ይምራን ያሉ የፈቀዱ፦ የወደዱ የማህበረሰቡ አባላት የተፎካካሪውም፤ የተጠማኙም፤ የተዋህጂውም፤ የተደማሪውም አካል ናቸው።
ዴሞክራሲ // ለመረጠም ላልመረጠም፤ ለተቀበለም // ለሚሞግትም እኩል የማስተናገድ ክህሎት ነው። ስለሆነም እራስን አርሞ መነሳት፤ ለራስ ንጹህ ፍላጎት ብቻ መትጋት፤ የጠራ መስመር መከተል፤ በማንኛውም ሁኔታ መስዋዕትነት የሚቀንስበት ተግባር ላይ አትኩሮት መስጠት፤ በምንጊዜም ከገዢው የብልጽግና መንግስት ጋር ያልተገባ ቅራኔ ውስጥ ገብቶ #ማገዶነትን መቀነስ ያስፈልጋል ባይ ነኝ።
አበክሬ ደግሜ እማስገነዝበው የኢህአፓ የወቅቱ ጸሐፊ ሲገልጡ የሰማሁት "ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ኢህአፓ እንዳልተገኜ" አዳምጫለሁኝ። በሰላማዊ ትግል ሞግቼ አገር እረከባለሁ የሚል አንድ የፖለቲካ ድርጅት ከፈቃድ ሰጪም፤ ነሺ አካሉ ጋር ገጥ ለገጥ መገናኜቱ ብቻ ነው ጠቃሚው መንገድ። ወጀብ ሲኖር ዝቅ ብሎ ማሳለፍ ብልህነት ነው።
ከሁሉ ቀድሞ ኢህአፓ የኢትዮጵያ ቅንነትን መርሁ ሊያደርግ ይገባል።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
23/06/2025
ጊዜ የኔታ ነው።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ