#ዝምታ ቢከበር ምንኛ በታደልን ነበር በኢትዮጵያ የፖለቲካ አቅም እና አቋም።

#ዝምታ ቢከበር ምንኛ በታደልን ነበር፦ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አቅም እና አቋም።
#ጠብታ።
ለጭካኔ ሴራ ፖለቲከኛው ለአቦይ ስብኃት ነጋ የአልማዝ ጉንጉን አሰርቶ በግል ማክበር መብት ነው። የምስጋና ሴሪሞኔውን አደራጅቶ መምራትም የማይሸሹት ሞጋች ህሊና ከፈቀደ መፈጸም ይቻላል። በሌላ በኩል የህወሃት ዶግማ በመንፈሱ የታተመ ዜጋ ለአቤቱ ህወሃት የወርቅ ሃውልት በይፋ ማሰራትም ሙሉ መብት አለው። ጭካኔን እንደምናወግዘው ሁሉ ጭካኔ ናፈቀኝ ማለትም መብት ነው። በእኔ ላይ የጭካኔን አውራ አምጥቶ ለመጫን መሞከር ግን አይፈቀድም። ይህ ዱላም፤ ዝምተኛ የሆነ ስውር ጭቆና በጫናም ነው። ግፍም ነው። ስለሆነም ………
#መቃብር አይናፍቀኝም።
እኔ አዎን እኔ #ጉድጓድ አይናፍቀኝም።
#ገደል አይናፍቀኝም።
ቤተ - መቃብር አይናፍቀኝም።
ሳጥናኤላዊ #ጭካኔ አይናፍቀኝም።
#የጥላቻ ማምረቻ ቱቦ አይናፍቀኝም።
የዞግ ፖለቲካ ፈላስፋ ሽው አይለኝም።
የገዳይ የተሃድሶ ኦፕሬሽን #ካፒቴን አይናፍቀኝም።
#የክፋ ሃሳብ አፍላቂ፥ አናጺ እና የጸረ ሰው ሹፌር ትዝ አይለኝም።
የሴራ ቸረቸራ ቧንቧ ትዝ አይለኝም።
የውድመት መሐንዲስ ትዝ አይለኝም።
#ሬሳም አይናፍቀኝም።
የጸረ ሰላም ኒዩክለስ አልፈልግም።
የጭካኔ ቅሪት አካል የኑዛዜ የምክር አገልግሎትም አይናፍቀኝም። መቼውንም።
#በድል ይረሳል ወይንስ ይለመዳል?
ልመዱ ብቻ ሳይሆን በትንሳኤውም ሳቁለት¡ ማለፊያ¡ ወሸኔ¡ በሉት እየተባልን ነው። ይህን ርዕስ በዘመነ ህወሃት ደጋግሜ ጽፌበታለሁኝ። የደጉ ዘሃበሻ እና የደጉ ሳተናው ቋሚ አምደኛ በነበርኩበት ወቅት። እኔ ህወሃትን በስማ በለው አይደለም የማውቀው። ከጋሜየ እስከ ሙሉ ዕድሜየ መኖሬን ቅርጥምጥም አድርጎ የበላው ነው። ህወሃት ሲፈጥርም፤ ሲኖርም ሲቆሳስልም፤ ሲያገግምም #እንዲገባን ሆኖ የተሠራ የዞግ ድርጅት አይደለም። ማመስ፤ ማሸበር፤ ማውደም ብቻ ሳይሆን ጽንሰቱ ሆነ ውልደቱ በማንነት ቀውስ የተቃኜ ነው። ስለሆነም በቀሉ ሆነ የጭካኔው ዶክትሪን የሚመነጨው ከዚህው ከተሠራበት አጥፊ ሴል ይነሳል። ኢትዮጵያንም ሆነ ኢትዮጵያዊነትን የሚቀናበት የሚመቀኜውም ስለሆነ ምንጣሮ የሚጀምረው ከዚህ በኽረ አመክንዮ ይሆናል።
ይህም ሆኖ ህወሃትን በብዕሩ በትጋት እንደታገለ፤ #ለሽንፈት እንዳበቃ አንድ ጸሐፊ ህወሃት መንበረ ሥልጣኑን ለማስረከብ የፈቀደበት ሁነት የመፍትሄ አካልነቱን ካከበሩለት በጣም ጥቂት ሰወች አንዷ እኔ ነበርኩኝ። እነ አክቲቢስት ሥዩም ተሾመ ህወሃት ሥልጣኑን አስረክቦ በቆየባቸው ወቅቶች ሁሉ ሌት ተቀን በጸረ ህወሃት ዘመቻ ሲተጉ እኔ እነኝህ ሰወች የጤናቸውን ነውን ስል ሁሉ ነበር።
መንበረ ሥልጣንን ቁጭ ብሎ መክሮ፥ እራሱ ድምጽም ሰጥቶ ማስረክብ የላቀ የመቻል ፖለቲካዊ አቅም ስለሆነ፦ ከዛ በመለስ ያሉ ግድፈቶችን እንዳላዩ ማየት ይገባል በሚል እጅግ ለረጅም ጊዜ አንድም ጹሁፍ በህወሃት ላይ ጽፌ አላውቅም ነበር። ጦርነቱንም ቀድሜ የተቃወምኩ እኔ ነበርኩኝ። ገኖ የወጣላቸው ሌሎች ቢሆኑም። ዛሬም ነገም ከነገ ወዲያም ጦርነት አያስፈልግም አቋሜ ጽኑ ነው። ጦርነት አተረፈ ከተባለ ቂም፤ በቀል እና አመድ ናቸው ትርፋቸው።
ምክንያቴ ተወልጄ ያደግኩበት ጂኦግራፊካል ቀጠና #ስሜን ነው። ጎንደር ከተማ። "ስሜን" የሚለው ሥያሜ ሻብያ ሠራሽ አለመሆኑን ጠቁሜ ማለፍ እፈቅዳለሁኝ። ጎንደር ስሜን በጌምድር ይባል ነበር። ስሜን አውራጃ የሚባል ሰባተኛ አውራጃም ነበር። ዋና ከተማው ደባርቅ የሆነ። በሌላ በኩል የአንድ አገር ጆግራፊያዊ አቀማመጥ ስሜን፤ ደቡብ፤ ምዕራብ፤ ምስራቅ ይባላል።
ከዚህ መንጭቶም ስሜን ምስራቅ፤ ደቡብ ምዕራብ እያለም ይቀጥላል። አንድ የዕውቀት ዘርፍ እንጂ ትናንት የተፈጠረች አገር ፖለቲካ ሥያሜ ነው ብሎ በዛ መፈረጅ የተገባ አይመስለኝም። እኔ ብዙ ጊዜ ጽፌበታለሁኝ። በሌላ በኩል በፅታየ ሴት ነኝ ስል እትብቴ የተቀበረበት በዓት አቅጣጫው ስሜነኛ ነኝ እላለሁኝ፤ በሌላ በኩል የአባቴ አባት ከስሜን አውራጃ በየዳ፤ ጃናሞራ አዲስጌ ዋልድባ ከምል አቨይ በአባቱ ስሜነኛ ነውም እላለሁኝ። ይህ የአቅጣጫ ሥያሜን መጠቀም ሻብያ መር ሊያስብል የሚገባ አይደለም። የዕውቀትም ዘርፍ ነው ጂኦግራፊ።
#ወደ ቀደመው ምልሰት ይሁን እንደ አቨው።
ሙሉ የልጅነት የወጣትነት ጊዜዬ በደርግ እና በህወሃት፤ እንዲሁም፦ በኢዲዩውና በደርግ፤ በኢህአፓና በደርግ ማህከል ጦርነት የተቃኜ ስለነበር፦ በጭንቀት፤ በስጋት እና በመሸበር ውስጥ ነበር ያደግሁት። የህወሃት የካቲት ወር ያልሠራበትን የገበሬ አዝመራም ዝርፊያ፤ የድልድይ ሰበራ፤ የፈንጅ ቀበራ፤ የትምህርት ቤት ውድመት፤ የክሊኒክ ውድመት፤ በወልቃይት፤ በጠገዴ የሚያደርሰው የቤተሰቦቼ የሰባዕዊ መብት ጥሰት እየሰማሁ ነው ያደግኩት። ተጎጂወች ሸሽተው የሚመጡት ወደ እኛ እናቴ ቤት ነበር።
ለሥራ ስደርስም የህወሃት ወረራ የተካሄደባቸው ከተሞች ውድመት በአካል ተገኜቼ አይቻለሁኝ። ለስልጣን የበቃበት የጦርነት ወቅትም በዓይኔ ያየሁት የሃቅ ዓውድ ነው። የህወሃትን እስር ቤቱንም አውቀዋለሁኝ። ስለዚህ ለእኔ ስለህወሃት ዶክተሪን ማስተማር ከንቱ ድካም ይሆናል ባይም ነኝ። ክፋውን፤ ጭካኔውን መኖሬን፤ ተስፋየን ሲያሰቃይ የኖረ ክስተት ነውና። መኖሬን በትኖታል። ተስፋየም ጨንግፏል። መማር -- መማር ነበር ህልሜ። ቤተሰቦቼም በእኔ ምክንያት እንግልትት ብለዋል።
የሆነ ሆኖ "#በደል" ሦስት ቃል ነው። አፈፃጸሙ ግን መፈጠርን የሚነቅል ነው። በህወሃት ምክንያት ዘመናችን ሁሉ መፈጠራችን ሲነቀል ነው የኖረው። ይገርመኛል በዘመነ ሥልጣኑ ወሎ፤ ንፋስ መውጫ፤ አፋር እራሱ የሠራውን፤ ብድሩ ያልተመለሰውን ፕሮጀክት ሲያወድም። ለሥልጣን ቢበቃ ለውድመቱ ህጋዊ ዕውቅና ከማግኜቱ ውጪ አመድ ማጫወት ለሚፈልግ ዕብን የዞግ ድርጅት "ድገምልኝ፤ ሰልስልኝ ምኞቴ ነህ ተመለስልኝ" ቃናው ሰውኛም ተፈጥሮኛም አይደለም። ጸረ ሰው እና ጸረ ተፈጥሮም ነው። ለካ ጭካኔ ተሰውሮ እንጂ እንዲህም፤ እንደዛም አለ።
ሌላው ቀርቶ በጦርነቱ ወቅት የሰማሁት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ትግራዋይ #የዕለት እርዳታ ጠባቂ በዘመነ ህወሃት እንደነበሩ ስሰማ ቁስል ነው ያልኩት። የትግራይ ልማት ማህበሮችን አንድ ጊዜ ስብሰባቸው ላይ ለዘገባ ተገኝቼ ያየሁት ትጋት እና በህወሃቲዝም እና በአብይዝም መንግሥት አልሞት ባይ ተጋዳይነት የሰማሁት መረጃ ሊገጣጠምልኝ አልቻለም። ኢፈርትም ነበረ። በሰቲት ሁመራ የለምነት ደረጃ ቤተሰቦቼ ዘመናዊ አራሾች ስለነበሩ የመኖር ደረጃቸው ከፍታ እጅግ ድንቅ ነበር። ይህ ሁሉ ግን የትግራይን እናት ከራህብ አላዳነም። ተጠቃሚው የህወሃቲዝም ኢሊቱ እና ቤተሰቦቻቸው ደግሞ የወርቅ ትዕይንት ነበር ስናይ የኖርነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድም በሌላም፤ አኟክ፤ የ1967 የቅንጅት መራራ ስንብት እና የህዝብ እንግልት፤ የአርባጉጉ፤ የወተር ወዘተ መከራ፤ የሬቻ እና የባህርዳር ጭፍጨፋ፤ የአማራ እና የኦሮሞ ልጆች የእስር እና የቶርች ሰቀቀን፤ በገፍ የሚገደሉ፤ የሚሰወሩ የትውልድ አባላት መኖር፤ የቆሼ መከራ እና የሊቢያ ሰማዕታት መታሰቢያ መከልከል፤ የድምፃችን ይሰማ እና የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ጋር ተያይዞ የመጣው የጅምላ እስር እና ግድያ ወዘተ ……… የህወሃት የፖለቲካ አመራር ጭንቅላት ዲያቢሎሳዊ እንደነበር ያመለክታል። አሁን የዚህ የመቃብር ሴራ ጭንቅላት ተፈላጊነት ምን ይባላል? ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነው እምለው እኔ ለዚህ ነው። ፈላስፊት ኢትዮጵያ አልገባችንም። ፈጽሞ። ጭካኔ ድገመኝ፤ ሰልሰኝ እራሱ የጭካኔ ማህበርተኝነት ነው።
የህወሃት ካፒቴን አቦይ #ስብኃት ነጋ ናቸው። የጭንቅላቱ ነርብ የህወሃት #አቦይ ስብሃት ናቸው። የአንጋፋ የዞግ ማሌሊታዊ ፖለቲከኛ ቅጽል ሥያሜን ተሸክመው የኖሩት አቦይ ስብኃት ነጋ ናቸው። ጽኑ ህመማቸው #የማንነት ቀውስም ያለባቸው መሆኑም ነው። ውህድ ማንነታቸው ኢትዮ ኤርትራዊ ናቸውና። ማንነታቸው ውህድ ነው።
ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስሪት በቂ ግንዛቤ ያላገኜ ክስተት ነው። ወጥ ማንነትም ኖሮም የማንነት ቀውስ ሊፈጠር ይችላል። እንዴት? የቀለም ዕውቀት ደረጃ ማነስ፤ በህዝብ ቁጥር ከአነሰ ማህበረሰብ መፍለቅ፤ በዕድሜ እና ዘመን ሁነትም (ወጣትነት፤ ጉልምስ እና እርጅና፤) በሃይማኖት አግባብም ( ክርስትና፤ ቤተ እስራኤላዊነት፤ እስልምና፤ አይዲያሊዝም፤ ዋቄፈታ) በሁሉም ዘርፍ ተሟልቶ ስለማይገኝ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚታየው ትርምስ የማንነት ቀውስ #የተመሰጠረበት ነው። ይህን እራሳቸውን በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚበልጣቸው ማንም ሰው እንደሌለ ለራሳቸው የነገሩት፤ አንቱ ነኝ፤ ቁንጮ ፖለቲከኛ ነኝ፤ ተንታኝም ነኝ የሚሉት ያልደፈሩት የሃቅ እንክብል ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአንድም በሌላም የማንነት ቀውስ ተጠቂ ህሙም ነው።
#ከወደቀ አስተሳሰብ ዳግሚያ አብሮ ለመወዳደቅ መታጨቱስ?
ሙሉ ዕድሜውን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ሲፈትን፤ ተስፋን ቀራንዮ አድርጎ ሲቀጠቅጥ የኖረን መንፈስ አድነን¡ ¿¿¿¿ ዛሬም የአቦይ ስብኃት እርዳታም፤ ቡራኬም ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ያስፈልጋል ቹፌ መንገድ ነው። (ቹፌ ቀን የማይታይ ሌሊት ሌሊት ግን ደም እየተፋ የሚያሰቃይ የቆዳ እከክ በሽታ ነው።) በደልህ ናፈቀኝ¡ ሴራህ ይጥመኛል¡ በቀልህ ይግዛኝ¡ ጭካኔያዊ አስተሳሰብህ ይጥመቀኝ ግራ የተጋባ ቤርሙዳ ትርያንግል የሆነ ጎዳና ነው።
አቦይ ስብኃት ሲማረኩም እልል አላልኩም። አቦይ ስብኃት ከእስር ሲፈቱም ኡኡ አላልኩም። አቦይ ስብኃት ወደ አሜሪካ እንዲጓዙ ፈቃድ ሲሰጡም ለምን? እንዴት አላልኩም። ዝምታየ ሆነ ተደሞየ ከልክ በላይ ነበር። ይህ ዝምታየን ማክበር የተሳነው የንቀት፤ የፌዝ ቧልት ግን ላልፈው አላስቻለኝም። እሳቸው አሁን ሃይማኖት ቢኖራቸው የሱባኤ ጊዜያቸው፤ የጸጸት፤ ይቅርታ የሚጠይቁበት ጊዜ በሆነ ነበር። እንዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ላነኩር፤ ላጓጉል፤ ላጎፍር ብለው ሊሰለፋ ባልተገባ ነበር። የጭካኔ አሻራ ደብቁኝ እንጂ እዩኝ፤ እዩኝ የማያሰኝ ነውና።
በሌላ በኩል የሳቸው የኑዛዜ ቃለ ምህዳን ያስፈልገናል ተብሎ የተሄደበት ጉዞ የኢትዮጵያን ህዝብ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ምን ያህል እንደሚናቁ ያነበብኩበት ሲሆን፦ መተርጎሙን እና ማመሳጠሩን ደግሞ ለአቨው የእድምታ ባለሙያወች መተው ይገባል ብየ አምናለሁኝ። አቦይ ቅድስቷን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን ተዳፍረው "እንዳትነሳ አድርገን ሰባብረናታል" ያሉ ደፋር እኮ ናቸው።
እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ህወሃትን እንደተከታተለ ሰብዕና አቦይ ስብኃትን የመፍትሄ አፈላላጊ ይሁን የቀጣይ ጉዞ መንገድ መሪ አድርጎ መድረክ ማመቻቸት ድፍረቱ የተንጠራራ መሆኑን ተረድቻለሁኝ። ዝምታ አለማወቅ አይደለም። ዝምታ የማስተዋል ልቅና ነው። ዝም ስንል በኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዱ ኤክስፐርት ሌላው አልባሌ ሆኖ አይደለም። ፖለቲካን በሚመለከት ከእያንዳንዱን ዜጋ ህይወት ጋር የተያያዘ ስለሆነ በነቂስ ኢትዮጵያዊው ጥቅሙን እና ጉዳቱን ቢያንስ ለይቶ ያውቀዋል። እንኳንስ ቋሚ ሠራተኛ ለሆነ ሰብዕና። ለነገሩ አንድ የቀበሌ ሊቀመንበር በመሆን፤ በሥርዓተ መንግሥት አስተዳደሪው ሁነት የመሳተፍ ዕድሉም ፈቃዱም ከሌለ እንዲህ ዓይነት የነተበ ጉዞ ሽው ሊል ይችላል። አንድ የቀበሌ ሊቀመንበር በሥርዓተ የመንግሥት አስተዳደር ስለሚሳተፍ ከዕውነት ጋር የታረቀ የፖለቲካ አንበል የመሆን አቅሙ ብቁ ነው።
ለዚህም ነው ፕሮፌሰር ዶር ብርኃኑ ነጋ ያገኙትን የስንጥር ያህል ዕድል ተጠቅመው መገኜታቸውን፤ የሚበልጡትን ሰብዕና ዝቅ ብለው ታዛዥነትን ተቀብለው ሳይ፤ ይሁንታቸውን በአርምሞ፤ በተደሞ አወንታዊ በሆነ ሁኔታ እየተከታተልኩት የምገኜው። በዚህ ያላለፈ ሰብዕና እራሱን ለአገር #መሪነት ሲያጭ ከምገረምባቸው ክስተቶች አንዱ ነው። ህዝብ ውስጥ ሆኖ፥ የህዝብን ስሜት ለማስተዳደር ደሞዝ እየተከፈለው በሥራ ሰዓት ገብቶ ሲሰራ ልምዱ፤ ተመክሮው ዲስፕሊኑ ሌላ ፕላኔት ነውና። ብልህነትም ነው ለእኔ።
የአቦይ ስብኃት ነጋ የሰብዕና ትንሳኤን ለማምጣት ይህን ያክል መጓዝ አይስፈልግም ነበር። መረጃው ከሰው ተመርጦ፤ ከዜጋ ለምርጥ ዘር፤ ከሚዲያም ለተለዩ ሚዲያወች እንደ ተሰጠ አድምጫለሁኝ። የተለመደም ነው። እራስን ማሸነፍ ያልቻለም ጉዳይ ነው። ንቀት የኢትዮጵያዊነት ተፈጥሮ አሻራችን አይደለምና። ሥያሜ መሆንን ይጠይቃል። በመሆን ውስጥ ሳይገኙ ትርፋ ትዝብት እና የልክን ገመና እንደ ቄጤማ መነስነስ ነው።
የጭካኔ ጭንቅላትን ምራን፤ ንዳን ይህ የኢትዮጵያን የዕውነት መንገድ ኮረኮንች የሚያደርግ እንጂ ቀና የሚያደርግ ፈጽሞ አይደለም። ቅንነትም የተነነበትም ነው። ሰዋዊነትም የተጣሰበት ነው። ትችትን ፈርቶ ፖለቲከኝነት፤ ግድፈቴን አታንሱ ብሎ ከእኔ ወዲያ ፖለቲከኛ ለአሳር ነውም አረማሞ መንገድ ነው።( አረማሞ ከእህል ዘር ውስጥ የሚፈጠር የአዝርት በሽታ ሲሆን ፍሬውን በክሎ የጠቀራ ዱቄት የሚያደርግ ነው።)
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ዝምተኛውን ማህበረሰብ ይንቁታል። አቃለውም ያዩታል። አልተጠቀሙም። ድካማቸው ሲያፈራ ሳይሆን ሲፈስ ነው የኖረው። ዝምተኛው ማህበረሰብ "ሙያ በልብን" የሚከውን መካች፦ ጥቃት አውጪ አቅም ያለው ነው። ድል የሚገኘውም አክብሮ በመነሳት ብቻ ይሆናል። የአቦይ ስብኃት የጭካኔ መስመር የምክር አገልግሎት ትርፍ እና ኪሳራውን የወደፊቱን አብረን እናያለን። በአቦይ ስብኃት ካፒቴንነት የሚገነባ ትውልድ፤ የሚቀጥል አወንታዊ ታሪክ፤ ጸንቶ የሚቆም ኢትዮጵያዊ፤ ፓን አፍሪካዊ አደራ ከኖረ ይታያል።
#ከአቦይ ስብኃት ነጋ የምጠብቀው ቅርጥምጣሚ የልቅና አቅም¡ እንዲሁም ትርፍራፊ ተስፋ የለም።
ጭካኔ፤ ሴራ፤ ወልጋዳነት፤ ፍልስነት፤ መፋደስ፦ በቀል፤ የማንነት ቀውስ የሚወልዳቸው ድውይ ዕሳቢወች ናፍቆኝ ከህወሃቱ የነርብ ሞተር ከሆኑት ከአቦይ ስብኃት ነጋ የምጠብቀው የተስፋ ቅርጫ የለም። ሊኖርም ፈጽሞ አይችልም። ግፍ እና በደልን እንደምን ማስተዳደር፤ ጭካኔ እና አረማዊነትን እንደምን ኮኦርድኔት ማድረግ እንደሚቻል ላቀተው ነፍስ አቦይ ስብኃት ነጋ ትክክለኛው ሰው ስለሆኑ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው።
#የአቤል ዕንባ ይጮኃል፤ የራሄል ዕንባም ምንጊዜም ወደ እዮር ይማጸናል።
የቀደመው የህወሃት ግፍ ብዕርም ብራናም አይችለውም። ከጦርነቱ ማግሥት ህወሃት ሰብሰብ ብሎ ቢቀመጥ የትግራይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ መነጠል ምቾት ከማይሰጣቸው ወገኖች አንዷ ስለሆንኩኝ፤ ቂምም ስለማላውቅ የመቻቻል መንገድ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያራምድ ዘንድ እምለውን እል ነበር። አይመቸኝም እቴጌ ትግራይ በኢትዮጵያ ካቢኔ፤ እቴጌ ትግራይ በኢትዮጵያ ፓርላማ፤ እቴጌ ትግራይ በኢትዮጵያ የፌድሬሽን ምክር ቤት ውክልና አለመኖር ለእኔ ግንጥል ጌጥ ነው።
ይህን ለማረም ብዙ የአስተሳሰብ ለውጥ ከትግራይ የፖለቲካ ሊቃናት ብቻ ሳይሆን፤ ከባለ ተስጥዖ ሊሂቃንም ያስፈልጋል። ጉዞው እና መስዋዕትነቱን ሚዛን ላይ አስቀምጦ ብልህነት ቀለብ ቢሆን። አደብ፤ ስክነት ሰውን ማዕከል ቢያደርግ መዳን በተገኜ። እራሱ ከቅኒት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይሞኖት ለ፴፫ ዓመታት እጬጌ ሁና ግን አሻም የተባለበት ምክንያት የቀደምቶችን የዊዝደም መንገድ ሁሉ የሚፈትን ገጠመኝ ነው ለእኔ። ምንም ጽፌ አላውቅም። በዝምታ ነው የተከታተልኩት።
የሆነ ሆኖ ህወሃት ቁመናው ሲለካ ታጥቆ የተነሳው በቀልን ሰንቆ ጭካኔን መፈጸም ነው። ህወሃት ትናንትም ያልዳነ፤ ዛሬም የማይድን መሆኑን የተረዳሁበት አጋጣሚ ነበር የአማራ እና የአፋር ክልልን የድጋሚ የህወሃት የወረራ ፕሮጀክት። ዛሬም ህወሃት ያልጠራ፤ ጠቃሚ ያልሆነ ከማህል አልመለስ፤ ከዳር አልታረስ ብሎ ኢትዮጵያዊ መንፈስን እያወከበት ያለው መንገድ በራሱ ትሬኮላታ ነው።
#ወረራው በጥቂቱ።
1) ወረባቡ ወሮ አይሻ አዛውንት እናታቸው ተገድለው አስከሬናቸው ለጅብ ተሰጥቷል።
2) ፎቶዋን የምታዮዋት ህፃን ህፃን አዝላ ጭካኔን ሽሽት 32 ኪሎሜትር ብቻዋን በእግሯ ተጉዛ ነፍስ አትርፋለች። ለዓለም ዜና የሚበቃም ፈታኝ ክስተትም ነበር። ከዩክሬን ወደ ፖላንድ ውሻዋን ይዛ የተጓዘችው አንስት መነጋገሪያ እንደሆነችው ሁሉ።
3) ምንኩስና ተደፍሮ አሰቃቂ ኢሰባዕዊ ድርጊት ተፈጽሟል።
4) ነፍሰጥሩ እናቶች ጫካ ውስጥ ወልደዋል።
5) የጭና ጭፍጨፋ ቤት ውስጥ መቃብር እስከ መሆን አድርሷል፤
6) የማይካድራው ሰቅጣጭ የጀምላ ጭፍጨፋም ለታሪካችን ብልዘት ነው።
7) የኮንቦልቻ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ቃጠሎ የሰው ገላ ጭስ ህወሃት አካባቢውን ለቆ እንኳን ጭሱ መቀጠሉን ዘገባ ላይ አዳምጫለሁኝ።
8) ወሎ ወርቄ ላይ ታስረው የተገደሉት የአዛውንት ታሪክ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ካቀረበው ዘገባ ተረድቻለሁኝ።
9) ወደ ትግራይ የሚወስደው ጠንካራ ድልድይም ያን ጊዜ ነበር የተደረመሰው።
10) ይህ አልበቃ ብሎ ያሰበሉ አዝዕርት እሳት ተለቆባቸዋል።
11) ቤት ያፈራው ሁሉ የተቻለው ተጭኖ፤ ያልተቻለው ለነዲድ ተሰጥቷል።
12) ብዙ ህሙማን ከአልጋ ላይ እንዳሉ ሰማዕትነት ተቀብለዋል።
13) ቅዱሳን ቦታወች ተደፍረዋል። ፈንጅ ተቀብሮም አገልጋዮች እና ነዋየ ቅድሳት ወድመዋል።
14) መስጊዶችም ከፈተናው አላመለጡም።
ይህ ሁሉ መከራ በአማራ እና በአፋር ክልል በቀል ምራን ተብሎ በተካሄደው አውዳሚ ጦርነት የትግራይ ልጆችም መሰሉን መከራ ተቀብለዋል። ስንት ባለተስፋ ወጣቶች አካለ ጎደሎ ሆኑ? ልትገድል፤ ልትበቀል ስትሄድ መሰሉ መከራም ይገጥማል እና። ህወሃት ሲፈጠር ፈጣሪወቹ በጸረ ሰው፤ እና በጸረ ተፈጥሮ ዶክተሪን ስለሆነ ዘመናቸውን ሁሉ ከፈጣሪ፤ ከአላህ ቃል በመጣላት ነው ያሳለፋት። ከቅዱሱ ወንጌል ዘፍጥረትን በኢትዮጵያ ምድር የቀጠቀጠው በዞግ ድርጅት አባቱ በህወሃት ነው። ካፒቴኑ ደግሞ አቦይ ስብኃት ነጋ ናቸው። እንደምን? ስለምን የአቦይ ስብኃት ነገ የጭካኔ ህዳሴ ተፈቀደ? ተፈለገስ???
#ህም!
ማሸበር፤ ማሰቃየት፤ ማስፈራራት፤ መደርመስ፤ ማውደም የለት ተግባሩ ነው ህወሃት። ዛሬም በግልጽ የኢትዮጵያ ህዝብ ያየው ዘንድ ተዘረጋግቶ የህውከት ምግባሩ ትዕይንት እየታየ ነው። ምን እንደሚፈልግ? ለማን እንደሚጠቅም? አቅጣጫው ውል የለሽ የሆነ ታጥቦ ጭቃ የሆነ ድርጅት ነው። ሁልጊዜ ጥድፊያ ሰርክ በስብሰባ፤ ሁልጊዜ ህወከት - በሽብር፤ ሁልጊዜ ቂም - በበቀል፤ ሁልጊዜ ጥላቻ - በመርኽነት፤ ሁልጊዜ ጭካኔ - በዶግማነት የተቀበለ የማይማር ድርጅት ቢኖር ህወሃት ነው። ህዝብ ተሰቃየ። መጥኔ።
የዚህ #ማስተር ማይንድ የሆኑት አቦይ ስብኃት በድጋሚ እንዲሆኑ አዲስ የሰብዕና ግንባታ መፍጠር ሰው ሆኖ መፈጠር ፈተና ላይ መውደቁን ያመለክታል። በውነቱ የሚያሳዝን እርምጃ ነው ባልልም መታሰቡ ግን የማስተዋል መራቆትን አመልክቶኛል።
በሌላ በኩል እንደ አወንታዊ የፖለቲካ አቅም የማየው መኖራችን ያወከውን፤ የውስጥ ሰላማችን የሚንጠውን አመክንዮ ደፍሮ ሊተያዩ የማይፈቅዱ፤ ሊደማማጡ የማይታሰቡ ወገኖችን ለመንፈስ የቅርቦች ብቻ ነጥሎ አገናኝቶ ማወያየት፤ ማነጋገር፤ አቅም ማዋጣት ነውር ሊሆን አይገባም ባይ ነኝ። ይህን ደፍረው የሚወስኑ ወገኖችም ሊበረታቱ ይገባል እንጂ ሊወነጀሉ አይገባም።
ግን እርማቱ ከራስ መጀመር ይጠይቃል። እንዳያይ፤ እንዳያገኝ ከሚፈልገውም አካል፤ ተቋም ጋርም ለመገናኜት መፍቀድ መቅደም ነበረበት ባይ ነኝ። ቤተ - ቅንጅት ላይ የተሠራው የልዩነት ወሰን ቀድሞ ሊሰበር ይገባል ባይ ነኝ።
ይህ ሆኖ ውጥኑ ላይ ግድፈት መታየቱ የሰውኛ ባህሬ ስለሆነ ድክመቱን አድናቂ ነኝ። ፕላኔታችን ቤተ - ፍጹማን አይደለችም። አንድ ሃሳብ ቀርቶ አንድ ጹሁፍ ስትወጥኑት ካሰባችሁት በላይ ይዟችሁ ይሸመጥጣል። ያድጋል፤ ይሰፋል፤ ይፋፋል። ግድፈቶቹም ቢሆኑም፤ የኦን ላይን የአጠቃቀም ግድፈት የሚጠበቅ ነው። ሁሉ ሰው IT ባለሙያ አይደለም እና። ሥልጣኔው ለሁላችንም አዲስ ነውና። ስለዚህ ጭለሃ ላይ ሙሉ እንጀራ መጠበቅ፤ ጥረቱን ማቃለል፤ ወይንም ማጣጣል የተገባ አይመስለኝም።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዘመን ሰጥ የሆኑ ግን የማይቻሉ ክስተቶች አሉ። በዘመነ ቅንጅት፤ በዘመነ የቅንጅት ልጆች (ሰማያዊ፤ አንድነት፤ ግንቦት 7) በዘመነ የቅንጅት የልጅ ልጆች (ኢዜማ፥ ባልደራስ) የገጠሙ አትራፊ ሂደቶችን ዛሬ በዲያስፖራው ማህበረሰብ ልድገምህ ቢባል የሚቻል አይሆንም።
ስለሆነም ዘመኑ በሚመጥነው አዲስ ስልት ተከትሎ የተጀመረው ቅየሳ የሚጣጣል አይደለም። "አጀንዳ የለውም፤ ዓላማ የለውም" ሊባልም አይገባም። በአንድ መድረክ የተለያዩ የፖለቲካ መሻቶችን ለአንድ ሰዓት በአንድ መድረክ ማገናኜት የዓላማ ጨረረ አድርጌ ነው ያየሁት። ቸር ዜና ነው። ይቅጥላል አይቀጥልም የካፒቴኑ የአቦይ ስብኃት የኑዛዜ ዘለላ የሚወስነው ይመስለኛል። ጊዜ እራሱን የሚገልጽበት ሂደት ስለሚኖርም መጠበቅን ማጥበቅ ይገባል ባይ ነኝ። ያው ጥሞና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ባይደፈርም።
የሆነ ሆኖ የአቦይ ስብኃት የምክር ዘለላ የማዳን መንገድ ፈጽሞ አይደለም። ከአቦይ ስብኃት የሚጠበቅ ምንም ዓይነት የፈውስ ጥምቀት ወይንም ቃለ ምህዳን የለም። መሃን ነው። አዲስ ፈተና ቀርፆ የማን ደም ፈሰሰ ሊያስብል የናፈቀ ሂደትም ነው። ከዚህ ቀደም ሙከራወችን አይቻለሁኝ። አልፃፍኩም። ዛሬ ግን ዝምታ የለም። ወደፊትም እንዲሁ። የህወሃት ትንሳኤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ቁንጮነት ባጉምባጉም አይመቸኝም። ይሞገታል። እረፍት ነሱን።
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል። ፍቅርም ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል። የሆነው ይሄው ነው። አንድ ሰው ከቅን እና ቀና መንፈሱ ጋር ሙሉ አቅም አለው። ለዜግነታችን ሰጪም ነሺም ማንም የለም። በወሰን እና በደንበር የሚሸነሽን ዕሳቤም ሊገራ ይገባል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዱ ልጅ ሌላው የእዳሪ ልጅ አይደለም እና አክብሮ መሞገት ብቻ ሳይሆን ሂደቱን ተከታትሎ በተገባው ልክ መመከትም ይገባል። አልተኛሁም! አላንቀላፋሁምም!
«የወልቃይት አማራ የተሰቃየባቸው የትህነግ 15 ድብቅ እስር ቤቶች!» (ፀሐፊ አቶ ቢኒያም መስፍን)
#ክወና።
በሰው ልጅ ስቃይ እንዲህም፤ እንደዛም መሆን ቀበጥ ያለ ዘመናይነት ነው። "በሰው ቁስል ……" ቢረሳ ቢረሳ ማይካድራ ይረሳል???? እራህብን የሚያውቀው የተራበ እንጂ የጠገበ አይደለም።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እንዴት አድራችሁ፤ አርፍዳችሁ ዋላችሁ ቤተ ቅንነት።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
09/06/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
ፍቅርም ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ