የእዮር አደባባይ ዬታምር ደወል አድማጭ አላገኜም። 14.12.2019
የእዮር አደባባይ ዬታምር ደወል አድማጭ አላገኜም።
በመጋቢት 18 ቀን 2010 የዶር አብይ አህመድ የኦህዴድ ሊቀመንበር የሹመት ዋዜማ አንድ የእዮር ደወል ተደመጠ፣ ልብ ያለው ስላልነበር እኔ በቀንበጥ ብሎጌ ታሪክን አጣቅሼ ፃፍኩበት። በመቀሌ አቅራቢያ ጉዳት ያላደረሰ የመሬት መናጥ ስለተዘገበ።
ከዛ ቀጥሎ በጉራጌ ዞን ሦስት ታምራዊ ጉዳዮች በአንድ የጊዜ ዓውድ ተከወነ። ታይቶ የማይታወቅ ዶፍ፣ ተሰምቶ የማያውቅ የሰማይ ጩኽት፣ መሬት ከሁለት የመገመስ ትዕይንት። ይህንንም ኧረ ምን ምልክት ነው ስል ፃፍኩት። ለእህቴም ያስፈራል ስላት አታሟርቺ አለችኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሃይማኖታዊ ጉዳይ ወጥታ የአብይወለማ የገዱወአንባቸው ፍቅር ምርኮኛ ስለነበረች።
መስከረም አምስት የሆነውን አይታችኋል። የዘንድሮ መስቀልም የብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ የእስር ቀን ቢባል መልካም ነው። ደብረዘይትም በዓሉ ተዘጋ ብፁዕ አባታችንም ታግተው ነበር። ግፋ ጣሪያ ነክቷል።
ይህም ብቻ አይደለም አድባራት በጅጅጋ ሲነዱ ያዬ እዮር ቁጣውን እሳት ሰማይ ላይ አዘነበ፣ ይህንንም ፃፍኩት፣ ከዛ በመቀጠል ቤት ከሁለት በደቡብ ዞን ተተረተረ እግዚኦ ብዬ ፃፍኩት።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ነበር መጋቢት አንድ በልደታ ሌላ ዓለምን በኃዘን ኩርምት ያደረገ፣ አውሮፕላን መሬትን ሰንጥቆ የገባበት መከራ በኢትዮጵያ የተስተናገደው። ያን ጊዜ አብይወለማ አመድ ነስንሰው ሱባኤ ይግቡ ብዬ የፃፍኩት። ፍርኃቴ እዬጨመረ ስለመጣ።
አሁን በቅርብ ጊዜ ሽዋ ውስጥ ከተለመደው ውጪ የፀሐይ ብርሐን እንደታዬም አንብቤያለሁ ፌስ ቡክ። ፎቶውም አለ።
ጥቅምት እና ለቅሶው ደግሞ ሌላ እዮራዊ ታምር አስከትሏል። የኔታዋን ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶን አቅዶ ለመንቀል ባለው ዘመቻ አማንያን በሃይማኖታቸው ይፀኑ ዘንድ ማተቤን እዬር ልኮላቸዋል።
ዛሬ መስቀል ይነዳል፣ ቅዱስ መፅሐፍ ይቃጠላል። ንዋዬ ቅድሳት የዶግ አመድ ይሆናሉ። ካህናት፣ ማህበር ምዕመናን እንደ በሬ ስጋ ይታረዳሉ፣ ይከተፋሉ፣ አፈር ለመቅመሥ ይታገዳሉ፣ አራስ በድንጋይ ተቀጥቅጣ ትገደላለች፣ እናት በድንጋይ ተቀጥቅጣ ትገደላለች፣ በዘመናችን 50/100 ካቢኔ ሴት ሚኒስትራት ባሉበት፣ ሴት ፕሬዚዳንት በሆኑበት፣ ሴት የፍትኽ ቁንጮ በሆኑበት፣ ሴት የፌድሬሽን ምክር ቤት ሰብሳቢ በሆኑባት ሴት የሰላም ሚኒስተር በሆኑባት ኢትዮጵያ ? ? ? ?
ይህን ያዬ ፈጣሪ አምላክ ታምሩን እንሆ ገለፀ ለካዱትም፣ አምላካዊ ኃይሉን ለረገጡትም እና ላስረገጡትም የዘመኑ አጤዎች እና እቴጌዎች የመንፈስ ፍተሻ ያደርጉ ዘንድ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
እግዚአብሄር አምላክ ይህን አውሬያዊ መንፈስ ከቅድስት አገር ኢትዮጵያ ያትንንልን። አሜን።
ማተቤን የሰጠን አምላክ ይክበር ይመስገን። አሜን።
ማተቤን ያሳድግልን። አሜን።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ