ኢትዮጵያዊነት ፈተናውን እንዲያልፍ ከተፈለገ።

 

ኢትዮጵያዊነት ፈተናውን እንዲያልፍ ከተፈለገ።
 No photo description available.
1) የአማራን ህዝብ ሰቆቃ ለመርዳት የተለያዩ ተቋማት ተከፍተዋል። ጋዜጠኛ አበበ በለው የሚያስተባብረው የገዘፈ አካል አለ፣ ጥቂቶቹ …
1.1አሁን በቅርቡ የሰማሁት የተሰው የፋኖ ልጆችን ለማሳደግ በነፍስ ወከፍ የተጀመረ ቤተሰባዊ ፕሮጀክት አለ። በማስተዋል የተያዘ። ስኬታማ የሆነ።
1.2 በመንግሥት የሚመራ ለሰራዊቱ የሚሆን ሌላ ፕሮጀክት አለ።
1.3 በእነ አርበኛ ዘመነ ካሴ የሚመራ ተስፋ ሰጪ ፕሮጀክትም አለ። ሁሉም የአቅሙን፣ የሚችለውን፣ የወደደውን መርዳት መብቱ ነው።
በመንፈስ ይሁን በመዋዕለ ንዋይ። በፀሎት ይሁን በሃሳብ። ብቻ ችግር መጋራት። የቻሉትን ማድረግ። በፁሁፍም የምርምር ተግባር የከወኑት የኔታ ፕ/ ኃብታሙ ተገኜ እና የኔታ አቻም የለህ ታምሩ ዘላቂ የአማራ እርስቶችን ህጋዊ ዕውቅና እንደ ስፔኖች ለማስመለስ ዩንቨርስቲ ከፍተዋል። መፍትሄውም እሱ ነው።
በሌላ በኩል የአማራ ጉዳይ ለራሱ ለአማራ ልጆች የተተው ነው የሚመስለው። አራት ዓመት ሙሉ እዬታከተም ነው። ሌሎችም በተለያዬ ፎርማት የበኩላቸውን የሚያደርጉ እንደ ቀደምቱ ሞረሽ ዓይነቶቹም አሉ።
2/ በአፋር በአቶ ጋህሳይ የአፋር ሚዲያ ኢንፎርሜሽን ሚዲያ ማዕከል መሥራች ወይንም ሴንተር እንዳለ በጋዜጠኛ አበበ በለው ቴሌቪዥን አዳምጫለሁ። እነሱንም ማበረታታት ያስፈልግ ይመስለኛል።
የአማራ ተጋድሎን በፈጣሪ በአላህ ፈቃድ በአፋር አናብስት ባይደገፍ የዛሬው ቀን ያበቃ ነበር። ይሰበር ነበር። ስለሆነም። አፋሮችን በሃሳብ፣ በሞራል፣ በተስፋ መርዳትም ያስፈልጋል። የሚችልም በአቅም።
3) የነገሌ ቦረና ጉዳይ ነው። የኦነግ ፖለቲካ በአማራ ህዝብ ላይ በከፈተው መጠነ ሰፊ የማጥቃት መከራ ጋር ይህን ሃሳብ ሳነሳ የሚኮሰኩሳችሁ ሊኖር ይችላል። በእኔ በራሴ በግል ህይወት ሰሞኑን የገጠመኝ እጅግ የከረፋ ፈታኝ ነገር ነበር። እጅግም የበረታ።
ግን ድንግል አለችኝ። እኔ ጎዳናዬ ዕውነት እና መርኽ ነው። ከልጅነት እስከ ዕውቀት ዕጣ ፈንታዬ ይኽው ነው።
ኢትዮጵያዊ ነኝ ስል ፈተናዋን ለመሸከም ስችል ነው። ጎርባጣውንም፣ ኮረኮንቹንም፣ ሐሞቱንም ከርቤውንም።
የሆነ ሆኖ ቦረናወች ኢትዮጵያዊ ነኝ ባዮች ናቸው። ይህ ደግሞ ለኦነግ ፖለቲካ አይመችም።
ይህን በዬኔታ ጎዳና ያዕቆብ ከጥቅምት 20/2020 እስከ የሚዲያ አቆሙበት ወቅት ድረስ ያሉቱን ጭምት ውይይቶች ገብታችሁ ማድመጥ ነው። ይህ ስላልተወደደላቸው ነው ያ ተደምጦ የማይጠገብ ተቋማዊ ብቃት የታገደው።
ዛሬ ያ ንፁህ ህዝብ በድርቅ ተመቷል። ኮንታክት ፐርሰኑ ማን ይሁን ማን አላውቅም። እኔም ለወር ያህል አልነበርኩም። ትናንት ከተራራ ሚዲያ እንዳዳመጥኩት 84 ሺህ የቀንድ ከብቶች ሙተዋል። 100 ሺህ በከፋ ሁኔታ ይገኛሉ። ድርቁን ለመቋቋም የሰው ልጅን ማትረፍ ቢቻልም ዋናውን የቦረናን የኢኮኖሚ መሠረት ግን ማትረፍ አልተቻለም።
ድርቁ ለ4 ወር ይቀጥላል ተብሏል። ቦረና እና ጉርጂ እኛ ቦረና፣ እኛ ጉርጂ ነን ስለሚሉ ዛሬ ባለው የኦነግ ፖለቲካ አይወደድላቸውም።
ከጎናቸው መሰለፍ የኢትዮጵያዊነትን ፈተና ማለፍ ይመስለኛል። ቢያንስ አይዟችሁን መቀለብ። ከመልካምነት የሚታጣ የለም። መልካም መሆን ጠረኑ ሰላም ነው።
ደግነት ርህርህና መፅናናት፣ ማፅናናት የፈጣሪ ስጦታ የኢትዮጵያዊነት ፀጋ የሰውነት መለኪያ ነው። ያን ስንስት ሰውነታችን መለመላ ይሆናል።
ቦረና ፀዓዳ ነው። ቦረና ንፅህና ያለው ህዝብ ስለመሆኑ እኔ በቤተሰብ እዬተነገረኝ ነው ያደግሁት። ከእኛም ፎገራ፣ ወረታ፣ ደንቢያ ወገራ እንደ ቦረና ናቸው ይባላል።
የወተት ጥገት ስለሆኑ። የምንችለውን እናድርግ። በፀሎት፣ በሃሳብ፣ በአይዟችሁ እንደጋገፍ።
ኢትዮጵያዊነት ሰንደቅ መልበስ ሳይሆን ውስጥን በውስጥነት መመገብ ነው። ፈተናን ለማለፍ ለማለፍ በመሆን ውስጥ መስከን። ግን ቂምን ተጠይፎ ቅንነትን መዋጥ ይጠይቃል።
4) ጋዜጠኛ ዶር ታምራት ነገራ የተራራ ሚዲያ ኔት ወርክ መሥራች ታስሯል። እስሩ ከባድ ነው። ከሌሎችም እስረኞች የገዘፈ ይመስላል። በርቀት እንደማስተውለው።
ስለዚህ ሚዲያው በህይወት እስካለ ድረስ ሚዲያውን ሳብስክራይብ፣ ሼር፣ ላይክ፣ ፎሎው በማድረግ መተባበር የሚገባ ይመስለኛል።
በእሱ ዙሪያም የሚነሱ ጉዳዮች አሉ። የተደማሪነት ጉዳይ። ጎልቶ ሊታይ የሚገባው ሚኒሊካዊ መሆኑ ነው። በኢትዮጵያዊነቱ አይደራደርም ታሜዋ።
ስለዚህ ከጎኑ መቆም ግድ ይላል። ሚዲያውን ካልዘጉበት ሚዲያውን በሞራል፣ በሃሳብ ማገዝ ይገባል። የእሱን ሁኔታ መከታተልም ጉዳያችን ሊሆን ይገባል።
የሃሳብ ልዩነቶች አሁን በዬቤቱ ያለው ጉግስ እከሌ ከእከሌ የለበትም ድብድብ ነው። በትርታ ጭንቀት ጉዳይ፣ በካቴና ጉዳይ በዕውነተኛ የኢትዮጵያ አርበኞች ጉዳይ አብሮ መቆም ይገባል ባይ ነኝ።
እኔ ሁልጊዜ ከተጠቁት ጎን ስለምቆም ሁልጊዜ ተጠቂ ነኝ። ለዚህም ነው ቤተሰቦቼ እንኳን ሊረዱኝ የማይችሉት። እኔም ብዙ ሰወች ባይረዱኝ አይደንቀኝም።
ምክንያቱም የወለዱኝ ወላጆቼ እህት ወንድሞቼ የቅርብ ጓደኞቼ ውስጤን የሰጠኋቸው ሳይቀር ያልተረዱኝ ከሌላው ምን ልጠብቅ ልቻል። የፈጠረኝ ስለምን እንደፈጠረኝ ያውቃል። ጥሪም መልዕክትም አለብኝ።
እንደ ሥርጉተ ወይንም እንደ ሰብለ ተፈጥሬ ተውልጄ፣ ኑሬ በዚኽው ሰብዕናዬ አልፋለሁ።
ይህን ሰብዕናዬን አልጨፈልቀውም፣ አልድጠውም ወይንም አልዋሰውም።
ውራጅ ሰብዕና ኑሮኝ አያውቅም እንዲኖረኝም አልፈቅድም። እማከብረውን ሰብዕና ይሁን አምክንዮ እንዳከብርኩት ኑሬ አልፋለሁ። ይኽው ነው።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
14/12/2021
እኔ ለእኔ ያልሆንኩ ዕለት እኔ እኔን ማሰናበት ይኖርበታል።
ያ ደግሞ የመንፈስ ቀብር ነው። ይህ አይፈቀድም!





  • Sergute Selassie shared a memory.

    አስተያየቶች

    ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

    ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

    እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

    አብይ ኬኛ መቅድም።