"ኢትዮጵያ በየዓመቱ በ2 ሚሊዮን የሚጨምረውን ሕዝቧን መግታት ያስፈልጋት ይሆን?" BBC
https://www.bbc.com/amharic/articles/cgeyzg382rjo
ኢትዮጵያ በየዓመቱ በ2 ሚሊዮን የሚጨምረውን ሕዝቧን መግታት ያስፈልጋት ይሆን?
15 ህዳር 2024
"የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ሕዝብ ከ40 ዓመታት በኋላ 10.4 ቢሊዮን እንደሚደርስ ትንበያውን አስቀምጧል።
በዚህ ትንበያ ሕንድን ጨምሮ ስምንት የዓለማችን አገራት የዓለማችንን ግማሽ ሕዝብ ይይዛሉ።
ከእነዚህ ስምንት አገራት ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያ ትገኝበታለች።
የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በየዓመቱም በሁለት ሚሊዮን ይጨምራል። የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሕዝብ ብዛት 129.7 ሚሊዮን ደርሷል።
ይህ ቁጥር በ28 ዓመታት ውስጥ እጥፍ ሊሆን እንደሚችልም ተተንብይዋል። በዚህ ትንበያ መሠረትም በ2044 የኢትዮጵያ ሕዝብ 259.4 ሚሊዮን እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህም በሕዝብ ብዛቷ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የሆነችው ናይጄሪያ አሁን ካላት የሕዝብ ብዛት ይልቃል።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት መጨመር ምክንያቱ ምንድን ነው? መጨመሩስ ምን አደጋ ይዞ ይመጣል? ምንስ ዕድል አለው?
በተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ የሥነ ሕዝብ እና ልማት ፕሮግራም ተንታኝ የሆኑት ወ/ሮ ገዙ ብርሃኑ፣ የሕዝብ ቁጥሩ ለመጨመሩ ምክንያቶችን ለማወቅ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን ማንሳት የግድ ነው ይላሉ።
እነዚህም ውልደት፣ ሞት እና ፍልሰት ናቸው። የአንድ አገር የሕዝብ ቁጥር የሚወሰነውም እነዚህን ከግምት በማስገባት ነው።
የውልደት እና የፍልሰት መጠን ሲጨምር እና የሞት መጠን ሲቀንስ የሕዝብ ቁጥር ላይ ጭማሪን ያስከትላል።
ተንታኟ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የውልደት እና የሞት ምጣኔ በጊዜ ሒደት እየቀነሰ እንደሆነ እና በፍልሰት ምክንያት የሚከሰተው የቁጥር መጨመርም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
በአሁኑ ወቅት ላለው የሕዝብ ቁጥር መጨመር ዋነኛ ምክንያቱም በየዓመቱ የሚታየው 2.5 በመቶ የሕዝብ ቁጥር እድገት ነው ይላሉ።
ምንም እንኳን ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጻር የውልደትም ሆነ የሞት ምጣኔው እየቀነሰ ቢሆንም፤ ምጣኔው መሳ ለመሳ ባለመሆኑ በሕዝብ ቁጥር መብዛት ላይ ለውጥ እንዳስከተለ ይገልጻሉ።
በ1990ዎቹ ከሦስት በመቶ በላይ የነበረው ዓመታዊ የሕዝብ ቁጥር እድገት አሁን ላይ 2.5 በመቶ ሆኗል። ማለትም አንዲት ሴት በአማካይ 7 ልጅ ወይም ከዚያ በላይ ትወልድ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ይህ ቁጥር ወደ 4.6 ዝቅ ብሏል።
“ዓለም አቀፍ ፍልሰት ብዙም ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ የለውም” የሚሉት ተንታኟ፣ የውልደት እና የሞት መጠን የተፈጥሮ እድገትን የሚወስኑ በመሆናቸው ለሕዝብ ብዛት መጨመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ይናገራሉ።
እዚህ ላይ የሕዝብ ብዛት መጨመር እና የሕዝብ ብዛት እድገት ምጣኔን ልዩነት ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል።
የአንድ የአገር የሕዝብ ብዛት ጠቅላላ የሕዝብ ብዛት ቁጥር ሲሆን፣ የሕዝብ ብዛት እድገት ምጣኔ ደግሞ ከዓመት ወደ ዓመት የሚጨምርበትን መጠን ያመለክታል።
በመሆኑም የውልደት እና የፍልሰት ምጣኔው ከሞት ምጣኔው ጋር ካልተመጣጠነ አሊያም የሞት ምጣኔው አነስተኛ ከሆነ የሕዝብ ቁጥር ላይ ጭማሪ የሚታይ ሲሆን፣ የሕዝብ ብዛት እድገቱ ደግሞ በውልደት ምጣኔው ላይ የሚወሰን ይሆናል ማለት ነው።
የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተውም በኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ሞት ባለፉት 50 ዓመታት እየቀነሰ መጥቷል።
ለምሳሌ በ1970 ከአንድ ሺህ ሕፃናት 244 ጨቅላዎች ይሞቱ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በ2019 ወደ 50 ወርዷል።
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የነበረው የሕዝብ ብዛት እድገትም ፈጣን የሚባል አልነበረም።
ባለሙያዋም “የውልደት ምጣኔ ሲጨምር እና የሞት ምጣኔ ሲቀንስ ልዩነታቸው እየሰፋ ነው ያለው” ይላሉ።
በ2016 የሥነ ሕዝብ እና ጤና ጥናት አንዲት ሴት በአማካይ 4.6 ልጅ እንደምትወልድ ያመለክታል። ይህ ቁጥር በተለይ ከሞት ምጣኔ አንጻር ሲታይ ከፍተኛ እንደሆነ ባለሙያዋ ያስረዳሉ።ይህም ለሕዝብ ቁጥር መጨመር አስተዋፅኦ አድርጓል።
የሕዝብ ብዛት ከቆዳ ስፋት ጋር ሲነጻጸር
እንደ ተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ መረጃ ኢትዮጵያ 1.12 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት አላት።
ይህ አሁን ላላት የሕዝብ ብዛት ሲካፈል የጥግግት መጠኑ 107 አካባቢ ይሆናል።
ይህ ማለት በአማካይ በአንድ ስኩዌር ኪሎሜትር 107 ሰዎች ይኖራሉ ማለት ነው።በከተሞች አካባቢ ከፍተኛ የሕዝብ ጥግግት አለ።
በቅርቡ በዓለም በሕዝብ ብዛቷ በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ሕንድ 2 ሚሊዮን 973 ሺህ 190 ኪሎ ሜትር ስኩዌር የቆዳ ስፋት ያላት ሲሆን፣ የሕዝቧ የጥግግት መጠን 488 ነው።
በኢትዮጵያ ያለው የጥግግት መጠን አከራካሪ ቢሆንም ከፍተኛ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።
በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ባጋጠሙ የሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎችም እየተፈተነች ነው። ሥራ አጥነት እና ኑሮ ውድነት ተባብሷል። የዋጋ ግሽበቱም አሻቅቧል።በምጣኔ ሃብታቸው አላደጉም ከሚባሉ አገራት መካከልም ነው የምትመደበው።
የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) እየተገባደደ ባለው የፈረንጆቹ ዓመት ድህነትን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት በድህነት ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ዜጎች ከሚኖሩባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ሪፖርቱ 6.3 ቢሊዮን ሕዝብ በሚኖርባቸው 112 አገራት ውስጥ 1.1 ቢሊዮን የሚሆነው ሕዝብ በድህነት ውስጥ እንደሚኖር አመልክቷል።
ከእነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ [48.2 በመቶው] የሚኖሩት ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ውስጥ ሲሆን አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ደግሞ በደቡብ እስያ ባሉ አገራት ይኖራሉ።
ከእነዚህ አገራት መካከል ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት ተጠቅሰዋል።
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በኢትዮጵያ 86 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ በድኅነት ውስጥ ነው የሚኖረው።
በቅርቡም የተባበሩት መንግሥታት ምጣኔ ሃብታቸው የሚንገዳገድ አገራት የሕዝብ ቁጥር እድገት አደጋ ሊሆንባቸው እንደሚችል አስጠንቅቋል።
የድርጅቱ የምጣኔ ሃብት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዋና ፀሐፊ ሊዪ ዤንሚን የሕዝብ ቁጥር መጨመሩ ድህነትን ለመግታት፤ የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ እንዲሁም ትምህርት እና ጤናን ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት ይፈትነዋል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ለንደን የሚገኙት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አብዱልመናን መሐመድም የሕዝብ እድገት እና ምጣኔ ሃብት የሚነጣጠሉ እንዳልሆኑ ነው የሚናገሩት።
የምጣኔ ሃብት እድገት የሦስት ማዕዘናት ውጤት ነው ይላሉ ባለሙያው።
“አንደኛው የሰው ጉልበት ነው፤ ሁለተኛው የካፒታል ክምችት ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ የቴክኖሎጂ መሻሻል ነው።”
አብዱልመናን፤ እነዚህ ሦስቱ ከተቀናጁ ለምጣኔ ሃብት እድገት ያላቸው ፋይዳ የትየለሌ ነው ባይ ናቸው።
“ለምሳሌ የሕዝብ እድገቱ ፍጥነቱ የተቀዛቀዘባቸው አገራት የካፒታል ክምችታቸው እና ቴክኖሎጂ አግዟቸው ካልሆነ በቀር ምጣኔ ሃብቱን ማሳደግ አይችሉም” ይላሉ።
እርግጥ ነው አንዳንድ አገራት በቴክኖሎጂ ቢራቀቁም በሕዝብ ቁጥር መመናመን እየተፈተኑ ነው። ዜጎቻቸው እንዲወልዱ ማበረታቻ እስከ መስጠት የደረሱ አገራትም አሉ።
እንደ ጃፓን ፣ ኮሪያ እና ቻይና ያሉ አገራት ደግሞ የውልደት ምጣኔያቸው አነስተኛ በመሆኑ የሠራተኛ ኃይል እጥረት ገጥሟቸዋል። በዚህም ምክንያት በቅርቡ ቻይና የሠራተኞቿን የጡረታ መውጫ ዕድሜ ከፍ አድርጋለች። ሌሎች አገራትም ይህንን ጉድለት ለመሙላት ሮቦቶችን ጨምሮ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀሙ ነው።
በተቃራኒው የወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ በሆነበት አህጉረ- አፍሪካ ደግሞ ነዋሪዎች በሥራ እጦት እና በዋጋ ግሽበት እንዲሁም በሌሎች ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች እየተናጡ ነው።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አብዱልመናንም ሦስቱን ማዕዘናት አቀናጅቶ ጥቅም ላይ አለማዋል ፖለቲካዊ ችግር ሊያስከት እንደሚችል ያስረዳሉ።
አብዱልመናን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወጣት እንደሆነ በመጠቆም “ወጣቱ ሥራ ከሌለው ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ” እንደሚዳርግ ይናገራሉ።
ወ/ሮ ገዙ በበኩላቸው የሕዝብ ቁጥር መብዛት ስጋትም ዕድልም የሚሆነው አንድ አገር በሚከተለው ፖሊሲ ነው።
ትክክለኛ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ተነድፎ ተግባራዊ በሚደረግበት ሁኔታ የአገሪቷን እድገት ከሚወስኑ ቁልፍ ጉዳዮች ‘አምራች ሕዝብ’ እንደመሆኑ ሕዝብ እንደ ሃብት እንደሚቆጠር ባለሙያዋ ይናገራሉ።
በመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት መሠረት በኢትዮጵያ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ከ15 እስከ 64 ዓመት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሕዝቦች ከግማሽ በላይ የሆነውን (58 በመቶ) የያዘ ነው።
በመሆኑም አምራች የሚባለው እና በመካከለኛ የዕድሜ ክልል የሚገኘው የሕዝብ መብዛት ዕድል እንጂ ስጋት አይሆንም ይላሉ ባለሙያዋ።
ዕድል የሚሆነው ግን አገሪቷ በምትከተለው ፖሊሲ ይህንን ሃብት ማብቃት እና መጠቀም ስትችል ነው።
ኑሮ በናረበት፣ ሥራ አጥነት እና የትምህርት ተደራሽነት ባልተስፋፋበት፣ በትምህርት፣ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ እንዲሁም በማኅበራዊ ብቁ ያልሆነ ትውልድ ባለበት ግን ይህ ለአንድ አገር ስጋት እንደሚሆን ባለሙያዋ ያስረዳሉ።
በመሆኑም የአንድን አገር ሕዝብ ቁጥር መብዛት ዕድል ወይም ስጋት የሚያደርገው አገሪቷ የምትከተለው ፖሊሲ ነው ይላሉ።
መንግሥት የአየር ንብረት ለውጥ፣ የከተሞች መስፋፋት እና የወጣቶች ተሳትፎ ጉዳዮች ላይ እየተከተላቸው ያሉ ፖሊሲዎች አገሪቷ ትክክለኛ መንገድ ላይ እንዳለች ይጠቁማል የሚሉት ወ/ሮ ገዙ፣ የእነዚህ ፖሊሲዎች ቁልፍ ጉዳዮች በሥነ ሕዝብ ፖሊሲው ውስጥ ተካተው ወጣት ተኮር የሥነ ሕዝብ ፕሮግራም ተነድፎ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ይመክራሉ።
ኢትዮጵያ እስካሁን የምትከተለው የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ በ1985 ዓ.ም. የወጣውን ነው። በተደጋጋሚ ፖሊሲው እንዲሻሻል ባለሙያዎች ሲወተውቱ ቢቆዩም እስካሁን ማሻሻያ አልተደረገበትም።
ሆኖም ፖሊሲው አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ማለትም በሥነ ሕዝብ ስብጥሩ እና የዓለም ለውጥ ምክንያት እንዲከለስ መወሰኑን ባለሙያዋ ገልጸዋል።
ፖሊሲው ሊቀረጽ የተዘጋጀውም የአምራች ሕዝቡን የኢኮኖሚ አበርክቶ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው ብለዋል። ለዚህም ድርጅታቸው ለመንግሥት ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ወ/ሮ ገዙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የ1985ቱ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ምን ይላል?
ከ30 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብ ፖሊሲ የሕዝብ ብዛት እድገት እና የኢኮኖሚ አቅም መካከል ያለውን ክፍተት መድፈንን ያለመ ነው።
የነበረውን የውልደት ምጣኔ አንዲት እናት በአማካይ ትወልድ ከነበረው ከ7.7 ልጆች እአአ በ2015 ዓ.ም. ወደ 4. 0 ዝቅ ማድረግ፣ የእርግዝና መከላከያ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከነበረው ከአራት በመቶ በ2015 ወደ 44 በመቶ ከፍ ማድረግ፣ የእናቶች እና ሕጻናትን ሞት መቀነስ፣ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ የሚሉት ይገኙበታል።
ወ/ሮ ገዙ እንደሚሉትም የ1985ቱ ፖሊሲ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ወደ ማኅበረሰብ በማድረስ እና ተጠቃሚነቱን በማሳደግ የሥነ ሕዝብ ቁጥርን የመግታት ዓላማን የያዘ ነው።
አሁን መንግሥት ለመከለስ ያቀደው ፖሊሲ ግን የሕዝብ ቁጥርን የመግታት ዓላማ እንደሌለው ባለሙያዋ ተናግረዋል።
የሚሻሻለው ፖሊሲ እስከ 60 በመቶ የሚደርሰውን አምራች ሕዝብ እንደ ኃይል ተጠቅሞ የአገሪቷን ኢኮኖሚ የማሳደግ ዓላማ ያነገበ ነው። በመሆኑም “የሕዝብ መብዛትን እንደ ስጋት የመቁጠር ሁኔታ የለም” ይላሉ።
ድርጅታቸው ያቀረበው ምክረ ሃሳብም ይህንኑ መሆኑን ወ/ሮ ገዙ ተናግረዋል።
ነገር ግን በትምህርት፣ በጤና፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የወጣቶችን ፍላጎት ከግምት በማስገባት መሥራት እንደሚያስፈልግ መክረዋል።
የሴቶች ቁጥር ከወንዶች ይበልጥ ይሆን?
አገራት የሕዝባቸው የፆታ እና የዕድሜ ምጣኔ ፈተና ሲሆንባቸው ይታያል።
ለምሳሌ በጃፓን ከአስር ሰዎች አንዱ 80 እና ከ80 ዓመት በላይ ነው። የአገሪቷ ብሔራዊ መረጃ እንዳመለከተው አገሪቷ ካላት 125 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ከ29 በመቶ በላይ የሚሆነው ዕድሜው 65 እና ከ65 ዓመት በላይ ነው።
ይህም በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያስከተለ እንደሆነ ይነገራል።
በኢትዮጵያ የውልደት እና የሞት ምጣኔው እየቀነሰ ስለሄደ ከ15 ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት ቁጥር በአንጻራዊነት እየቀነሰ ሲሆን፣ ከ15 እስከ 55 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው አምራቹ ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ መረጃ ያመለክታል።
የፆታ ምጣኔን ስንመለከትም በዓለም ላይ የወንዶች ቁጥር ከሴቶች በመጠኑም ቢሆን ከፍ ያለ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ነገር ግን የፆታ ጥምርታው እንደየ አገራቱ ይለያያል።በአውሮፓውያኑ 2022 በወጣ አንድ መረጃ በከፍተኛ የሴቶች ቁጥር አርሜኒያ እና ዩክሬን በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።
የአውሮፓ ኅብርት ኮሚሽን በአውሮፓውያኑ በ2021 ባወጣው መረጃ በጠቅላላው በኅብረቱ ያለው የሴቶች ቁጥር ከወንዶቹ በ10 ሚሊዮን እንደሚልቅ አመልክቷል።
በተቃራኒው ደግሞ በኳታር፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና በኦማን የወንዶች ቁጥር ከሴቶቹ ከፍ ይላል።
2.5 ሚሊዮን የሕዝብ ብዛት ባላት ኳታር የሴቶቹ ቁጥር ከ700 ሺህ ያነሰ ነው።
በኢትዮጵያስ?
እንደ ተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ተንታኟ ከሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፆታ ስብጥር መሳ ለመሳ ነው። በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየውም ኢትዮጵያ ካላት ሕዝብ 49.9 በመቶ ወንዶች ሲሆኑ ሴቶች ደግሞ 50.1 በመቶውን ይይዛሉ።አብዛኞቹም በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
የፆታ ጥምርታው ወደፊትም በዚህ መልኩ ይቀጥላል የሚል ግምት እንዳለ ወ/ሮ ገዙ ጠቁመዋል።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ