ጣና ኬኛ! የአብቹ ውርሰ - ዕሴት፤

የጀግኖች አምድ የአብቹ ውርሰ - ዕሴት፤ ዬሐምሌ አምስቱ የጎንደር አብዮት ሐሤት - ቄሮ ትፍስህት።
ከሥርጉተ - ሥላሴ 17.10.2017 /ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ /
„በመጀመሪያ ቃል ነበር፣ ቃልም በእግዚአብሄር ዘንድ ነበር። ቃልም እግዚአብሄር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሄር ዘንድ ነበር። ሁሉ በእርሱ ሆነ። ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ህይወት ነበረች፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፣ ጨለማም አላሸነፈውም።“ / ዬዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፩ ከቁጥር ፩ እስከ ፭።/
 „ቃል እግዚአብሄር ሆነ።“ „እግዚአብሄር ፍቅር ነው።“  ይላል ወንጌልም። እኔ ደግሞ እላለሁ … ስለዚህም ከሁሉም ሥነ - ሕይወታት ቀድሞ፤ ከሰው ልጆች መፈጠር በፊት ፍቅር በፈጠሪ ህገ - ልቦና በቀዳሚነት ተፈጥሯል ባይ ነኝ። „በእርሱ ህይወት ነበረች፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች።“ ለእኔ ለሥርጉተ - ሥላሴ አሁንም የህይወት ንጡህ ጠሐይ፤ ንጡህ ብርሃን የፍቅራዊነት ተፈጥሯዊነት ነው ብዬ አምናለሁ። የኑሯችን ውበቱ፤ የስትንፋሳችን ህላዊነቱ ፍቅር ነው። ለፍቅር ተፈጥሮ አክብሮትን በመሆን ውስጥ በገቢር ያረጋገጥን ዕለት የውስጥ ሰላማችን ሙሉ ጌታ እንሆናለን።
  • እንደ ማኮብኮቢያ ….

የኢትዮጵያ አምሳያ እናትዓለም ወ/ሮ ፋናዬ ደሳለኝ እንኳን ደስ አለሽ። ብዕርህን እጅግ አድርጌ የምወድልህ ጸሐፊ ታሪኩ ደሳለኝ ወንድም ዓለም አንተንም እንኳን ደስ አለህ። ሆደ ሰፊው፤ ሩቅ አሳቢው „የብዕር አንጋች“ ትንታጉ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እንኳን ለዚህ አበቃህ። ደስታ እንዲህ ቀላል ነው ለካ።
  • አቮል።

ህም! ወደ ዕርአሴ ከመግባቴ በፊት እስቲ ተጨማሪ አንድ ሁለት ነገር እግረ-መንገዴን ጣል ላድርግ። ምኑ አደናበረው የባህርዳሩ ኮሸሽሌ ወይንም በየኔታ ሙሉቀን ተስፋው አገላለጽ „የብአዴን መደንገጥ ስለምንድን ነው?ብሏል። እኔው ልመልሰው …

እነ አቶ አንቀልባን በሃፍረት ቅሌት ያዘለበ እርምጃ ስለቀደመ ነው፤ እንዲህና እንዲያ የሚደናበሩት። ዝናብ ላይ ሁሉመናውን የተሰጣ አጎዛ ያደረገው የአባ ዱላ እርምጃ ነው ጉድ የሠራቸው። ይህን ታላቅ ብሄራዊ ጉዳይ „አጀንዳ ለምን ሆነ“ የሚሉም አሉ። ይህ አጀንዳ ካልሆነ የቱ አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም። „ብልሃት የሌለው ቅላት“ ትል ነበር እሚታዬ … ጽግሽ።  በሌላ በኩልም „ወያኔ ለእኛ የሰጠው የቤት ሥራ ነው“ የሚሉም አሉ። የቤት ሥራችን እማ እንዲህ ያለውን አቅም የምንጠቀመበት የመንፈስ ወጥ ቅምጥ ሐብት አስቀድሞ መገንባት ነበር። በተጨማሪም መጪ ሂደቶችን መተንበይ - ቀድሞ። ያልተጠበቁ እርምጃዎች ጅራት ከመሆን ቀንድ መሆን።
… ሌላው ግን የሰሞናቱ ተልዕኮ እንዲያው በነጠላው ፈሰስ ሲታይ ጠ/ሚር ሐይለማርያም ደሳለኝስ ለማን ይሆን መልቀቂያቸውን የሚያቀርቡት ያስባላል። እንደ እኔ ለስውሩ ጠ/ሚር ከሚሆን፤ ልብ ቢኖራቸው የሞአ ኢብራሂምን ዶላርን ተንበርክከው ቢዝቁ ይሻላቸው በነበር። ለዛ ፋውንዴሽን የመልቀቂያ ማመልከቻቸውን ቢያቀርቡ አቤት ብልህነትን በስንት ወቄት በተመዘ። አያድርገኝ እንጂ፤ እኔ እሳቸውን ብሆን እማደርገው ይህን ነበር። ለነገሩ መካሪም ያላቸው አይመስልም። መጎርጎር የለመደ የመጎርጎር፤ የመሰርስር፤ የመቦርቦር፤ የመሰረቅ ሱሱ እግር ከወርች አስሮ ይዞት በዬትስ? ተ----ወዴትስ …
  • በር ….

ዛሬ መጪ ማለት ያሰኜኝ በምልሰት ቆፍጣናውን ጀግና አብቹን ትንግርት ከዛሬው የትውልድ ልቅና ጋር አመርቲያዊ ማድረግ ነው።
እንዲህም
ሆነ … የጀግና አብቹን አንበሶች የፍቅር ተምሳሌት ጉዞ እኔ መጀመሪያ ዜናውን የሰማሁት ከአዋዜ ነበር። ጋደም ብዬ ሰለነበር ተነስቼ ቁጭ አልኩኝ። ሰውነቴን አንዳች ነገር ወረረኝ። ሆደ ባሻ ነኝ እና ያው የተለመደው መስኮት ተከፈተ። ግን ሲቃው የፍጹም ደስታ ነበር።
አንዳንድ ጊዜ እጅግ ሰቅጣጭ አገላለፆች ስሰማ ከእኛ ቀድመው በሥጋ ያለፉት እንኳንም ይህን ሳያዩ አለፋ እል ነበር። መሞቴን አቅርቤ እያዬሁት። ያን የአዋዜን ሞገዳማ የብሥራት ዜና በስንት ዘመኔ ስሰማ ደግሞ እንኳንም ፈጣሪ አምላኬ ዕድሜ ሰጠኽኝ አልኩኝ። ከሁሉ በላይ የቅኔውን ልዑል ብላቴ ሎሬትን ጸጋዬ ገ/መድህን ሳስብ፤ በንጽጽር ደግሞ ከዛ ቅዱስ መንፈስ ያፈነገጡ ዕሳቤዎችን ሳዳማጥ … ግራነታችን ግራ ይሆንብኝ ነበር። ዛሬ ዕድሜ ለእናንተ የአብቹን ዕሴት ፍሰሃን በሰራ አከላቴ ከላ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲህ እንደናኝ አደረጋችሁት። አዳናችሁኝ። የበቀለ ውጤት በረከታችሁ ይሁን። አሜን።
አያችሁ የእኛ ክብሮች … ሰው በህይወቱ ዋጋ ሠራሁ ማለት የሚችለው የሰውን ልጅ ዕውነተኛ ደስታ መፍጠር ሲችል ብቻ ነው። የስንት ሚሊዮን ወገናችሁ የሐሤት ወጋጋን እንደሆናችሁ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው። መጠጊያ ያጣው መንፈስ እንሆ በሃይለ እግዚአብሄር ተስፋ አገኜ። ተባረኩ። ተቀደሱ። ቃለ ምልልሱ እራሱ እንዴት ነፍስን ይመልሳል፤ እንዴት ቅቤ ያጠጣል። እንዴትስ ያስተምራል። እንዴት መኖርን ይፈውሳል። እንዴት ነገን ይቀድሳል። እንዴት ብሥራትን ያውጃል። ጥላቻ እኮ በዬደቂቃው የውስጥ ሴልን የሚገደል ነቀዝ ነው። ፍቅር ግን እንደ ገና፤ አዎን! እንደ ገና የሚወልድ ድንቅ የትንሳኤ ዕለት ነው። ምጥ ገላጋይ ነው - አይዋ ፍቅር። ከሰው ልጅ ቀድሞ የተፈጠረው ፍቅር ነው ብዬ የማምነውም ለዚህ ነው። ፍቅር የሚኖረው፤ የተፈጠረውም ለሰው ልጅ ቀና አገልጋይነት ሲል ነው የሚልም የግል ጽኑ ዕይታ አለኝ። ከቶ ካለፍቅር ምድር ምንድን ናት? ኮረኮንች፤ አመዳም … ቡላ … ፋደሳ … ብልዛም ….   
  • የሥነ - ልቦናዊ ድል ዋዜማ - በጣዝማ።

በቃ! አበቃ! ጦር ሳይመዘዝበት፤ ቃታ ሳይሳብበት እንዲህ ብትክ ሆነ ቀረ የወያኔ ሃርነት ትግራይ የአርባ ዓመት ትግል። ዋንኛው ጠላት „አማራ“ ብሎ የተነሳበት ናላው ተነደለ፤ ድልድዩም እንሆ ተናደ። የእንቧይ ካብ ሆነ። ነገ የነገዎቹ ማግስታዊነትን እንዲህ መሆንን በአቅም አፋፍተው ሲያቀልሙት፤ እንዲህ ህገ መንግሥት አድርገው ሲከበክቡት፤ ሚሊዮኖች ለውጡን፤ ሥልጡኑን ፈር ቀያሽ ምህንድስና ይቀላቀላሉ። አዎን! ዋንኛው ተወዳጅ አማራ ሆኖ አረፈው። „አራዊት፤ ጨካኝ፤ ሰው በሊታ“ ተደርጎ በወያኔ ሃርነት ትግራይ የተሳለው የአማረው የአማረ የአብሮነት ፍልስፍና እንዲህ ዘመን ድልን አቀዳጀው። እንዲህ ዘመን የሚስጢርነቱን ዕድምታውን አብራራው። ነገም ይህን ዕልፍ የሥነ- ልቦና ብቃት የሚጋሩ ሚሊዮኖች ይሆናሉ። አስተምኽሮቱ እኮ ከላይ ወደ ታች ሳይሆን ከታች ወደ ላይ ሆነ። ግሩም ነው። አቤት እንዴት ደስ ይላል! አቤት እንዴት ይደላል! አቅሙ ከአቅም ላይ የሰከነ ፍትሃዊ ብጡል። ትውልድን የሚክስ የጥበብ ዕንቁ። ለነገሩ ይህ የሰው ጥበብ የከወነው አይደለም። የሰማይ የአርያም ምርቃት በሁለት መቶ ባለመክሊትያን /ባለመክሊትያት/ ያስዋበው እንጂ። ፈጽሞ ፈጣሪ አምላካችን ልዕልት ኢትዮጵያን የማይረሳት መሆኑ የታዬበት ትንግርት ነው።

አንድ ጽንሰ ሃሳብ ረቂቅነቱ የሚፈተነው በውስጥ የርቁቅ ንጥረ ነገሮች ውህድነት፤ ጥልቅ ተመስጧዊ ዕሴታዊ ውበቱ ነው። እነኝህ ድንቅ ወጣቶች ይህን ልዕልና ያለውን የሚሊዮን ድምጽ፤ የሚሊዮን ተስፋ ሲያቅዱት የሃሳቡ ጌጣማ ውበቱ የማደረግ አቅሙን እራሱ የችሎት አደባባይ ሆኖ በይኖለታል። ጉዞ ወደ በበቀል ድቅቅ፤ ስብርብር ወደ አለው የግፉዕን ዬአማራ መንፈስ ሆነ። የምኽረት ስምረቶች። ከድንቅ በላይ። ታዕምር። በልቦና ተመስጥሮ ተሸጎጦ በዬኮረቻው የተያዘው የጥላቻ ታንኳ እንኩትኩት አለ። አስዬ የእኔ ቀንዲሎች።

ከዚህ ሌላ አማራን በራሱ በውስጡ ነቀረሳ ፈጥሮ እራሱን እንዲያጠፋ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አዲስ ያሰናዳው የቅምንት ጉዳይም ውሃ የበላው ቅል እንዲሆን በይኖበታል - ቅዱሱ የጣናው ስብከት ቀኖና። ተመስገን። የወያኔ ሃርነት ሊቃናት ትልም የቅማንትን ከተፈጥሮው የመዘንጠል፤ በኋዋላም የማጠቃለል ህልም ቂጡ የወለቀ እንስራ ሆኖ እንዲህ አረፈው። ብቻውን የቆመ ዘነዘናዊ ህልም መሆኑ ታዬ - በአደባባይ። ልባሞቹ ቅማነቶችም ከነክብራቸው፤ ከነተፈጥሯቸው በደማቸው ውስጥ ይኖራሉ። ደሜ ይመራኝ እንዲሉ ነጋሪቱን የቄሮ ሐሤቶች አውጀውታልና። ቄሮ በፍጹም ሁኔታ ድንጋጌ ሆነ። ይህ እንግዲህ በጥልቀት ሲቃኝ የሚሰጠው ግብረ ምላሽ ነው። ከላይ እስከ ታች ነው ያናጋው እርምጃው ሆነ ተግባራዊው የጀግኖች ውሎ።

ባለፈው ጥቅምት ሰባት ቀን ያችው የሥነ - ጥበብ የንቦች ነባቢት አዘውትሬ ከምከታተለው ህብር ራዲዮ ጋር በነበራት ቆይታ ያሰተላለፈችውን ጥሪ ተቀብዬ መሄዴን፤ የተሰማኝንም ገልጨ ነበር። ታዲያ እኔ ጣጣዬን ከጨረስኩ ማቄን ጨርቄን አላውቅም። ሰብሰብ ብዬ ወደ ጎጆዬ መጪ ነው። ታዲያንላችሁ አንድ የቀድሞ ወዳጄ ከኋላ፣ ኋላዬ  እዬተከተለ „ኩራት ያዳብር አለና በማስቀጠልም ጎንደር ታሳዝናለች፤ ሰነጣጠቋት አለኝ።“ እኔም ዞር አልኩኝ እና ሥነ - ልቦናውን አይቻልም አልኩትና ወደ ቤቴ ገሰገስኩ። ፍሬ ነገሩ ያለው ለጎንደር ልጅ ከሥነ - ልቦናው ላይ ነው። የትም ይወለድ ወጥ የሆነ የሥነ - ልቦና አቅም አለው። እንዲህ በዬወጀቡ የሚናውጸው የለም። በሌላ በኩል ደግሞ የትም ቦታ፤ በዬትም ሁኔታ ጎንደር መፈጠር አሳሩ ልክ አልተበጀለትም። ተሰደንም ፍዳችን ተራራ ነው። የመረረኝ ነገር እኔ በግሌ ይሄ ነው። የሆነ ሆኖ ዘመነኛው የትግሬ የመሳፍነት ዘመን ከሰላሳ፤ አርባ መሬቱን ሊተረትሩት ይችላሉ „ቀን የሰጠው ቅል …“  እንዲሉ …

መታወቅ ያለበት ግን … ግን ሥነ -  ልቦናችን ከቶውንም የማይነካ፤ ከቶውንም የማይደፈር፤ ከቶውንም የማይሰነጣጠቅ፤  ከመሆኑ ላይ ነው። በእንቁላል ውሃ የታነጸ ግንብ ነው። ለነገሩ የእንቁላል አግናባት ጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴ ላይ አለ። እንደ ደማችን ለመኖር የፈቀድን ነን። ሙያ በልብ መርኃችን ነው። ተድቦልቡሎ ወይንም ተጠፍጥፎ ሸክላ የሚሆን ነገር አልፈጠረብንም። ስናይም እናዝናለን እንኳንስ እኛ ህይወቱን ልንኖረው። 
ያ … እንደ አግባቡ ንባቡ እንኳን ያለተደረሰው „የኦሮሞ ደም ደሜ ነው፤ በቀለ ገርባ መሪዬ ነው“  ሲል አጭር ቁንጽል የጽንሰሃሳብ ፍሰት ሳይሆን የሚሳዬን የጎንደርን አልፋና ኦሜጋ መሆኑን ነበር። ከመሠረቱ የተነሳ ብልህነት፤ ምራቁን የወጣ የልቅና እጬጌ ነበር። መርኽ ነበር። ሰነድም ነበር። ዓዋጅም ነበር። አንዳች ማደንዘዣ ካልቀቡት በስተቀር በምንም ታምር ልብ እንዲገጠምለት የሚፈቅድ፤ ልብ እንዲገጠምላት የምትፈቅድ ጎንደሬ የለም/ ጎንደሪት የለችም። አትፈጠረም/ አይፈጠርም። የወያኔ ሃርነት ፍች የጠፋው የዓዋጅ ጋጋታ፤ የክተት ጦርነት ሁሉ ልኩን ካለማወቅ የመጣ መውተፍተፍ ነው። „እንከባባር“ ነበር የዘንድሮው ዬመስቀል ዕድምታ  … ለተርጓሚው … የተሰጠው የቤት ሥራ  ሆነ የክፍል ሥራ …   
  • የእኛ የመንፈሳችን ጆሮዎች  …

ሥጦታችሁ የመንፈስ ነበር። ለዛውም ለሚሊዮኖች። አርበኛ አብቹ የአርበኝነትን ማዕረግ በክብር የተቀዳጀው ገና ታዳጊ ወጣት እያለ በ16 ዓመቱ ነበር። የአባቱን ጋሻ ሲያነሳ ከሁለት ወንድሞች ጋር ሆኖ የተፈጠረባትን ማህጸን፤ አብራክ ቀዬ በጀግንነት የቀደሰው ገና በቁንጮው ነበር። የጀግኖች ተደሞ አብቹ አብረው የዘመተው ከሁለት ወንድሞቹ ጋር ሲሆን፤ ከሁለት ወንድሞቹ መሀከል የአንዱን የጀግንነት ህልፈት፤ የሁለተኛ ወንድሙን ደግሞ  መሰወር በተመስጦ ነበር ያዳመጠው። በዛን ጊዜ ያሳሰበው ከደም እና ከሥጋ መንፈሶቹ መለዬቱ ብቻ ሳይሆን፤ ይልቁንም የሠራዊቱ የመሪ ማጣት ጉዳይ ውስጡን እንደ አነደደው ነበር የውጭ ጸሐፍት ዝክረ ታሪኩን የጻፉት። የጀግና አብቹ እልሁ ዳር ድረስ የሄደ ነበር። ያን ጊዜ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ የተነሳው ጀግና አብቹ ሁለት መቶ እኩዮችን አሰልፎ ነበር ታላቁን ተጋድሎውን አህዱ ያለው። ገድለኛው አብቹ ካለዘመኑ የተፈጠረ፤ ካለዘመኑ የተወለደ ነበር። አብቹ ዳግሚያ ቴወድሮስ ቢባል ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም። የነፃነት ዓርማው አብቹ ጠላትን እያጋደመ፤ የውስጥ አርበኛ ባንዳን ሲያራውጥ ዜናው ሮም ድረስ ከትሞ ነበር። ኮነሬል አብቹ ሰማይ ጠቀስ ድፍረቱና ውጤቱ የዓጤውን ካቢኔ ሳይቀር የናጠ አብሪ ኮከብ እንደ ነበር የውጭ ጸሐፊዎች አብክረው ገልጸውታል። በእኛማ እንደ አልባሌ የታዬ፤  አንዲት ብጣቂ ማስታወሻ እንኳን እንዳይኖረው ተደርጎ ታፍኖ የቀረ፤ የተረሳ ነበር። ማፈር ብቻ ሳይሆን ልንሸማቀቅ የሚገባን ከንቱዎች ነን። እምንችላቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ። ልጅ ሁሉ ሲወለድ አብቹ ቢባል ከቶ ምን ይገደን ነበር። በሥሙ የተለያዩ ነገሮችን መጀመር ብንችል ምን ያቅት ነበር … አብቹ ፌስ ቡክ፤ አብቹ ራዲዮ …. አብቹ ቲያትር፤ አብቹ ፊልም ቀላሉ … ነቁጥ ነበር።

የጀግኖች ካፒቴን አብቹ ብሩህ አዕምሮው በፍጹም ሁኔታ የታደለ፤ የማደራጀት አቅሙ ከዕድሜው መጠን በላይ የነበረ፤ የመምራት ልኬታው ልቅና የቀደመ፤ ጥልቀትና ፋና ወጊ የነበረ የተመስጦ ዕንቁ ነበር። በፍጹም ሁኔታ ልዩ የጦር አዝማችና ፍጹም የሆነ የሰማይ መክሊት የተሰጠው ሳተና ወጣት ነበር። በዛ ልክና ደንበር ባልተሠራለት የአቅም ልቅና የወገንን የዋና ዋና ጦር አለቆችን ምሽግ ሳይቀር እራቁት ያሰቅር ነበር። በመሆኑም እሱን እያሉ የሚመጡ አርበኞች ቁጥር ከእለት ዕለት በመበራከት እዬገዘፈ፤ ዝናውም እዬሠፋ እዬተንሠራፋ የሄደ ንቁ፤ ብቁ አንበሳ ወታደር ነበር።

አቤ ለከፍተኛ ትምህርት የነበረውን ዕድሉን ሠርዞ ነበር ገና በቀንበጥነቱ አርበኞችን የተቀላቀለው። ያ …  ዘመንን ቀድሞ የተፈጠረው የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት ታዳጊ ወጣት፤ ጉልላት እና የተግባር አምድ ሲሆን፤ መንፈሱ ከሺህ ሠራዊት፤ መድፍና መትረዬስ በላይ ጥንካሬና ጉልበት ነበረው። ህሊናው የጣናን ያህል መጠነ ሰፊ ነበር። ጣና ሲነገር ባህርዳር ብቻ የሚመስላቸው ሊኖሩ ይችላሉ። ሥነ - ግጥምም አዳምጫለሁ ጥብቆ የሆነ፤ ጣና እራሱ አንድ ሐገር ነው። ከአለፋ ጣቁሳ የደካ ደንቢያን አካሎ፤ ደራን አክሎ ባህርዳር ላይ የዓውደ ምህረቱን ዕድምታ ያሰክናል። ጣና ጥልቀቱም ስፋቱም አለቅነቱም ረቂቅ ነው። እግዚአብሄር ይመስግን እንደ ጸሐፊ ምስባዕክ ወርቁ ዓይነት በሊቀ ጉባውኤው የጥበብ ማዕከል በሆነው የሥነ - ጹሑፍ ድባብ የተፈጥሮውን ድንቅነት እና ዲካ በጥልቀት እና በምጥቀት „በዴርቶ ጋዳ“ ፍልስፍናዊ ሆኖ ተተርኳል። እንዲያውም የዛ ድንጋጤ ይሆን ጣና እንዲህ ሥውር ጠላት ያፈራው እስከ ማለትም ደርሻለሁ እኔ በግሌ። በቀል አያበቅለው የለም እና። የበታችነት አይመክረው ሴራ የለም እና።

የሆነ ሆኖ በዚኸው በጣና ሥም እጅግ በጣም የጎንደር ሴት ልጆች „ጣናነሽ፤ ዬጣና ወርቅ፤ የጣና“ እዬተባሉ ይጠራሉ። ከሁሉ በላይ የጣና ጠረን የሚያውደው ወደ ደልጊ ሲያቀኑ ነው። በስንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቀድሞ „እንኳን ደህና መጡ“ የሚለው፤ የአለፋ ጣቁሳ ብሩኽ የስለት ልጅ የደልጊ የነጭ አዝሙዱ፤ የዝቃቅቤው፤ የጥቁር አዝሙዱ ሽታ ጋር ውህዱ ሰጊድ ለከ ያሰኛል - መንፈስን። ጣናን ተክትሎ የሚወለዱ ልጆች ደግሞ የተለዬ ጸጋ አላቸው። አሳ እዬበሉ ስለሚያድጉ የብሩኽ ህሊና ባለቤቶች ናቸው። አንድ ፊደል ያልቆጠረ አባወራ፤ አንዲት ፊደል ያልቆጠረች እማወራ የህሊና አቅማቸው ከ- እስከ የለውም። ወገኖቼ - ያለውን ዕውነት ነው እዬነገርኳችሁ ያለሁት።

ሌላው የአባይና የጣና ተፈጠሯዊ አፈጣጠር፤ የአብሮነት ዝማሬ ሌላው የሰማይ ድንቅ ጥበብ የሚታይበት ፍጹም ልዩ የሆነ የተደሞ ዕድምታ ነው። በጣና ላይ አባይ፤ በአባይ ላይ ጣና ሥራዓተ ተክሊል ፈጽመው በጣና ዘገሊላ ይቆርባሉ። … ኢትዮጵያዊነትም ይሄው ነው ድርሳኑ። ያ ዋርካው፤ ሚስጢርን የመተርጎም ብቃቱ፤ ክህሎቱ ፍጹም ልዩ የሆነው የዛሬው ትውልድ የጎንደርን እና የጎጃምን ውል በደሙ ጠልፎታል። ለዚህ ነው ደጋግሜ አንስቼ የማልጠግበው የትውልዱ የብቃት ልኬታ ዘለግ ያለ መሆኑን አብክሬም አምገልጸው። ስንት እንኩሮ ነገር ነው በዚህ ትውልድ የሰከነው። ተመስገን።

አዎን! ድንቁ የአማራ ተጋድሎ ወላዱ የሐምሌ 5ቱ የጎንደር አብዮት የዕድምታ ጉባኤ ተርጓሚ፤ አመሳጣሪ አላገኘም እያልኩ ስቸከችክ ነበር። ይህን ስል ዋርካውን ጎጃምን አይመለከትም። ዛሬ ዕድሜ ለአብቹ ሐሤቶች የሐምሌ አምስቱን የጎንደር አብዮት ገድል አነበቡት፤ ተረጎሙት፤ አሳምረው በወግ አመሳጠሩት። ያን ጊዜ ብሩኹ አብቹ የራሱን አቅም ለማማከል ከወቅቱ የጦር መሪ አለቆቹ የጠዬቀው፤ ተፈቅዶለትም አብረው የከተሙት 200 በእኩያ ዕድሜው የነበሩ ወጣቶች ነበሩ። ዛሬም ታሪክ ራሱን ደገመ። ሁለት መቶ የቄሮ አንበሶች የአያቶቻቸውን ገድል ደገሙት፤ ሰለሱት። ብሄራዊ ጀግንታቸውን በተግባር አቅለሙት። „እማርፍበት ቢኖረኝ ተመልሼ መምጣት እፈልጋለሁ አለችን ድንቂት አመርቲ፤ አብሮነታችን ተቀደሰ፤ ተዘመረለት፤ „ ስንቱን ላንሳሳው። ጥሩ አድርጎ አሁንም አዋዜ ምዕራፍ ሁለትን የታዳሚዎችን፤ የተሳታፊዎችን ዕይታ በድጋሚ ሠርቶታል። ሥራችን ሊሆን የሚገባው ይህ ነው። ልብ ቢኖረው የባህርዳሩ እንኮሸሽሌ በሁለት መቶ የተግባር አንበሶች ሥም ክሊኒክ ት/ቤት … ይሰይም ነበር። ከዚህ በላይ ምን ገድለ - ቅዱሳን፤ ምንስ ገድለ - ድርሳናት፤ ምንስ ታምራዊ መጸሐፍት ሊኖር … ይችላል። ወጣትነት መቅድምነት ነው። መቅድመነቱ በዕሴት ተዋውሎ ሐሴት ላይ እንዲህ ሲያርግ ደግሞ ህሊናን ያበለጽጋል። ነገን ቀድሞ ይታደጋል። ክብረ ተመስገን የእኛ ጌታ …                                               
በቃ! ይህ ረቂቅነት፤ ይህ ሚስጢራዊነትን በሽታሽቶ በሶሻሊስት ባዕድ ፍልስፍና፤ እንዲሁም በጎሳ ዶክተሪን በር ተዘግቶበት ደጅ አዳሪ ሆኖ ውርጩም፤ ዝናቡም፤ ሐሩሩም ግርማ ሌሊቱም ሲገርፈው የኖረው የድንቅነሽ ድንቅ ይሄው ዛሬ ቀን ወጣለት። የፖለቲካ ሊቃናትም የሥማቸው መቅረጫ አድርገውት የነበረው ጣዖት እንሆ አይሆኑ ሆነ። ትውልዱ እንዲህ ነው። የልዩነቱን ሰንሰለት እዬበጣጠሰ እንሆ ለዛ ትርጉም ላልተሠራለት፤ ቃል ላልተፈጠረለት፤ ስዋሰው ላልተሠራለት አነባቢው ተፈጥሯዊ ማንነት፤ ተነባቢው ማንነት ውስጥ ከተመ። እልልልልልልልልል …..

ባለ ጥምር ሰይፉ፤ ባለ ጥቁር ፈረሱ የሰላሌ ሜዳ የአደራ ኪዳን ውርስ ቅርስ፤ የጀግኖች ጠሐይ አብቹ የት እንደደረሰ፤ ምን እንደተደረገ የሚያውቅ የለም። እንደ ሙጌራ ዳቦ ነበር በግራ በቀኝ የቀቀሉት። ዛሬም ይኼው በወያኔ ሠፈር የጥቃት ሰለባነት አልበቃ ተብሎ በወገን ደግሞ የማሰናከያ ባሩድ ይዘንባል። ከትናንት ዛሬ አማንማር እኛ … ወገኑ የወገኑን፤ ሃይሉን፤ አቅሙን፤ ጉልበቱን ሌሊት ሲንድ፤ ሲጠርብ ይውላል። „ እንዲህ ናት አንዲያ ነው እያለ ሲያብጠለጥል“ በሴራ ፖለቲካ በሃሞት ሲለውስ፤ በማዕልት ደግሞ የተራረፈውን በአደባባይ ወያኔ „አሸባሪ፤ ትምክህተኛ፤ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ እያለ“ ይለቅማል። ውጪም በገባ ግቢቱ እዬተከታተለ መከረኛውን፤ ናፍቆት ያበለዘውን ስደተኛ ያሳድዳል። ከእኛ የሙጥኝ ያለው ህልሙ፤ ራዕዩ መጠጊያ አጥቶ ያው እንደ እኛው ይባዝናል። የመከራው ቀንም እዬተራዘመ፤ እኛም እንደ ደማሚት ያለፍንበትን አቲካራ ልልበስህ፤ ልቀድስህ፤ ላወድስህ፤ ምን ልሁንልህ እያልን የመከረኞችን ፍዳ እና አሳራ በቀጥል ይለፍ … እንሰጠዋለን። ከቅነነት ጋር፤ ከመልካምነት ጋር፤ ከቸርነት ጋር፤ ከመተሳሰብ ጋር፤ ከመረዳዳት ጋር፤ ከመደማመጥ ጋር፤ ከመተጋገዝ ጋር፤ ሀዘንን ከመጋራት ጋር በእርቀት ቁመን ስንተክዝ እንሆ አዲስ የብሥራት ቀን በቄሮ አንበሶች፤ በቄሮ አናብስት ታወጀ። ወህም! አልን። ብሞትም ከእንግዲህ ቅጭጭ አይለኝም ከዚህ በኋዋላ።
የቄሮ እርምጃ ሐሤቱን በሥነ - ጥበባዊ ክህሎት ቀመሙት። ለመሆኑ በመከራ ጊዜ ከመገኘት በላይ ምን የሰውነት መለኪያ ይኖራል? አሁን በእኔ ደም ውስጥ ምን ቃል ተጥፎ ይገኛል ቢባል። ጎጃም የሚል ቃል ተጥፎ ይገኛል። „ጣና የእኛ ጣና ኬኛ።“ አዎ! ቄሮም የእኛ። አዎን! ቄሮ የእኛ ብሄራዊ ጀግና። አዎን! ቄሮ የእኛ የብርሃናማ ፈርጥ ዓርማችን። አዎ! ቄሮ የእኛ የቅኔ መንበራችን። አዎን! ቄሮ የእኛ የትርጉም ላሊበላችን፤ አዎ! ቄሮ የእኛ የፋሲል ዜማችን። አዎ! ቄሮ የእኛ የበካፋ ድጓችን፤ አዎን! ቄሮ የገላውድዮስ መዝሙራችን። አዎን! ቄሮ የእኛ የደብርብርሃን ገድላችን፤ አዎን! ቄሮ የእኛ የቴውድሮስ አዲስ ኪዳናችን። አዎን! ቄሮ የጣና ወንጌል ዘወርቃችን። አዎን! ቄሮ የእኛ የመሆን አዝመራችን። አዎን! ቄሮ ዬእኛ የግዮን ፏፏቴ ሰናያችን። አዎን! ቄሮ የዘለቀ ሲሳያችን። አዎን! ቄሮ የእኛ የእያሱ ማተባችን። አዎን! ቄሮ የእኛ የአንዲት እናት ትንፋሽ ህገ - መንግሥታችን። አዎ! ቄሮ የእኛ የእናት ጓዳ ፍስሃ - ክናዳችን። አዎን! ቄሮ የእኛ የሐገር ፍቅር ናፍቆት፤ ማር የሚያዘነበው የሐገራችን ትዝታ ደቂቀ - አዳማችን።
  • የሐገሬ ልጆች ..

እስከዛሬ ገድሎች፤ ታምራቶች የሚጻፉት የመሪዎች ብቻ ነበር። ወይንም ዕውቅና ያላቸው ግለሰቦች አሁን ግን ዘመኑን ለወጡት ቀዳማይ ወጣቶቻችን። ታሪካቸውን እራሳቸው በፈርጣማ ብራና በወርቅ ጻፉት። መጸሐፍ። ምዕራፍ። ዘመን። ህይወቶች። መድህኖች። የአብሮነት ፍስፍናዎች። የፍቅራዊነት ማዕረጎች።
ክተት ሐገሬ!
የአብቹ አንበሶች ሁለት መቶቹ
የቄሮ ንቦች ሁለት መቶቹ
ርገት ወረደ በብልሆቹ።
ቀኑን አደሰ ዘመን ፈወሰ
ጥቁር ፈረሱ ድጓ አወረሰ
በሞቴ እያለ አለሰለሰ።
የግዮን ካስማ
የቄሮ ዳማ
በመከራው ቀን ታዬ በአውድማ።
በቀንበጥ ዕድሜው ድልን ሲያገሳ
በክንዱ ብረት ጣሊያን ያከሳ
ቆፍጣነው አቤ ያ አይበገሬ
ዛሬም ተክቷል ክተት ሐገሬ።
ቄሮ ሐሤት ነው ቋንቋ ʼማይችለው …
…. ቄሮ ዕሴት ነው ግሥ ʼማይችለው
ቄሮ መቅድም ነው ቅኔ ʼማይችለው ….
የአቩዬን ችሎት እንዲህ ʼያስቻለው።
አንቀጽ ነበረው ዬአብቹ መንፈስ
በጣሊያን ምሽግ ሰላም አደፍርስ
ለባንዳዎችም ʼማይመለስ
ብልሁ ወጣት የልብ የሚያደርስ።
ዛሬም ህያው ነው ርገት ትንሳኤ
ቄሮ ተነስቷል ሊያድስ ጉባኤ።
ዛሬም ህያው ነው ዳግሚያ ትንሳኤ
ቄሮ ተነስቷል ሊያድስ ጉባኤ!
  • ·        ጦታ ….  ለጀግና አብቹ እና ለቄሮ ትንታጎች ይሁንልኝ። ጥቅምት 17. ቀን 2017 እ.ኣ.አ. /ሲወዘርላንድ/
  • መኽሩ ይከወን …

እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ዘመኑን ትውልዱ አሳምሮ እዬመራው ነው። ትፍስህት - በስልት፤ ብልህነት -በቅነነት፤ ውስጥነት - በጉልላትነት፤ ትሩፋት - በትውፊትነት፤ ማግስታዊነት በሰከነ የማስተዋል ክንድነት። ተመስገን!
ማሳሰቢያ።

·        „የብዕር አንጋች“  ይህቺ ንጥረ ቃል የሊቁ የአቶ የሱፍ ያሲን ስለሆነች ነው በትምህርተ ጥቅስ የተቀመጠችው። የእኔ ሃብት አይደለችም። 

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
„ፍቅር ያሸንፋል።“ ይህቺም የጥበበኛው ቴዲ አፍሮ ናት።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ። መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።