"የቴዎድሮስ ራዕይ ቲያትር“ ሲዊዘርላንድ።

       ተህሊና የተከወነ ዕሴታዊ ውል።
         „የቴዎድሮስ ራዕይ ቲያትር“
በጭምቷ ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ ከተማ።

      ከሥርጉተ - ሥላሴ (ዙሪክ - ሲዊዘርላንድ 07.10.2017)
„ጥበብ ከቀይ ዕንቁ ትበልጣለችና፤ የከበረ ነገር ሁለ አይተካከላትም።“ 
(መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፰ ቁጥር ፲፩)
  • የዛሬ ነገር …

በጥዋቱ ነበር እቴጌ ጠሐይ ማን ነጋሪት እንደጎሰመላት አይታወቅም ፏ ብላ ይለፉን የሰጠችኝ። አቤት ስትስቅ ሲያምርባት - የታደለች። ምን አለ ሁል ጊዜ የተስፋን ሳቅ እንዲህ እንደ ዛሬው በአዘቦቱም ብትቀልብን። ኧረ እሷ ሞገደኛ ናት፤ እንዲያውም ከሰሞናቱ ወደ ጫጉላዋ ልትሄድ ትኬት ቆርጣላች ሲሉ የሰማሁ መስሎኛል። የራሷ ጉዳይ ነው ብቻ እንኳንም ዛሬ ተገኘች።
ብሩክ ማዕልት። እንደ አማረበት ተጀምሮ፤ እንደ አማረበት የተከወነ ውል። የውስጥነት ሐሤት በገፍ የተሸመተበት ዓውድ።
ዕለተ ቅዳሜን በልዕልት ኢትዮጵያ ሥህናዊ፤ ህዋሳዊ ዓውደምህረት አሳለፍኩኝ። ከሐገሬ ከወጣሁ ለመጀመሪያ ጊዜ የሐገሬን ሙሉ ጠረን፤ ሙሉዕ ዕሴት የመገበኝን „የቴወድሮስ ራዕይን„ ሙሉዑ ትዕይንት በዕውን አዬሁት። ተመሰገንም አልኩ። የሳምንቱ ቀናት እጅግ እረዝመውብኝ ነበር። ውስጤ አንዳች ደጎስ ያለ ፍሰኃዊ ስሜት ከትሞበት ነበር የሰነበተው። በልዩ ሁኔታ ክብርና ሞገስ ነበር የዛሬይቱ ቅዳሜ የተጠበቀቸው። ከሐገሬ ከወጣሁ እንዲህ ጓጉቼ ከተቀበልኳቸው ሁለት ቀናት ሦስተኛው ማዕልት ነበር ማለትም እችላለሁ። ፍጹም የሆነ ሐሤት በውስጥ መስምሬ ይነበብ ነበር። ስደት ጨካኝ ነው፤ ብዙ ነገርን ይቀማል። ስደት ጨለማ ነው ተፈጥሯዊውን የተስፋ ብርሃን ይነጥቃል። ስደት ክፉ ነው ቸር ሰብዕናን ይፈታተናል። ስደት የተፈቀፈቀ ገጠመኝ ነው ውስጥን ሳያስጠጣ የሚያራግፍ። ፊታውራሪ ስደት በልክ ያልተሰፋ ጥብቆ ነው። ስደት ጎርጓሪ፤ ቦርቧሪ፤ ስርሳሪም ነው። ስደት ሃጢያተኛም ነው፤ ውስጥን የሚያራቁት የናፍቆት ሸጎሬ።

ዛሬ ግን እስኪ ልርሳህ ብዬ ብዬ ጉዞዬን ረፋዱ ላይ ተያያዝኩት። የተሰጠኝ አድራሻ ከሁነኛ ሰው ስለነበር ትክክለኝነቱ ባያጠራጥረኝም፤ ግን እርግጠኛ አልነበርኩም። ባቩሬን ይዤ ወደ ዙሪክ አቀናሁ። ጉዞው ከወትሮው በተለዬ ምቹ ነበር። ውስጤ አልሚ ሙቀት ነገር ነበረው - ሳዳምጠው። የሐገሬን ጠረን፤ የሐገሬን ሽታ፤ የሐገሬን አውደምህረት በብጡሏ ጥበብ ዓይን ለዛውም በስደቱ ደጀሰላም  በአካል ልሳለም … አቤት እንዴት ደስ ይላል። ዬሐገር ናፍቆት በምን ወቄት ይለካ ይሆን? ግንስ መለኪያ አለውን?

„ሳይሳከ ቢቀርስ ብዬ ለራሴ ጠዬኩት።„ እራሱ የትይንቱን ነፍስን ሳስበው በመሰንበቴ ብቻ የሸመትኩት ሐሴት ከቀን የሚያደርስ ጥሪት አይደለምን? በማለት ሳይሳከ ብመለሰም እንደማይከፋኝ ለራሴ -እራሴው ነገርኩት። ቃል ተገባባን። እኔውና ናፍቆቴ።„

ዙሪክ ከቀረሁ ረጅም ጊዜ ሆነኝ። ሄጄ አላውቅም። ዙሪክ ላይ በርከት ያሉ የወጣጠንኳቸውን ጉዳዮችንም ካቆምኳቸው ቆዬሁኝ። ዛሬ ከስንት ጊዜ በሆዋላ ነው ዙሪክ የሄድኩት። ቁርጥ ሆኖ። ለዛሬ የናፍቆቴ መዳህኒት ዙሪክ በስፋት ስንቋል፤ ለዛውም የጥበብ ማዕዶት በጠሐይና በዝቀሽ የንዑድ መንፈስ ምርቷ ተድግሷል። የጥበብ ግብረሰላም። መታደል ነበር፤ ነውም።
አይገርምም፤ የተሰጠኝ አድራሻ ትክክል ሰለነበር ቦታው በራሱ የናፍቆት ማረሳሻ ዋንጫ ሆነ። ለዛሬ ናፍቆት ተረታ። ሰዓቱ ደረሰ። … አቤት ደስ ሲል። አቤት ሲደላ። አቤት ሲያምር። አቤት ሲመች። ዘመኑ በቅኔ ተቃኜ፤ የዛች ቅኒት እማማ ኢትዮጵያ ነበልባላዊ ፍቅር ቅኔ ተዘረፈ በቅኔ ጉባኤ - ተዚህ ዙሪክ ላይ። ይህ ብቃት ያለው የሐገር ጠረን ለስንት ዐመት በህሊናዬ መቀነት ቋጥሬ አስቀምጠው ይሆን? ድህነት ነውና። ዕምነት ነውና። ፈውስ ነውና። ጠበል።

ያቺን ድንቅ የኢትዮጵያን የሥነ - ጥበብ እናትን አዋት መራሂት አለምጻህይ ወዳጆን። ያችን ቅኔ ነፍሷን ተመለከትኳት። ውስጤም በሐሴት ቲፍ አለ። አዎን ያን ዋርካም አዬሁት። ቀንዲሉን የሐገር አውራ የተውኔቱ መርኽ ነባቢተ ተዋናይ፤ ጸሐፊ፤ ገጣሚ ጌትነት እንዬውን ለዛውም ገብርዬን ሆኖ። እና ሌሎችንም የፍሬ ማር ወለላዎችን የድንቅነሽን ድንቆችን፤ ጌጦችን፤ ፈርጦችን አዬኋቸው። በፈረንጆት በሠሩት መስኮት እንዳይመስላችሁ፤ በዕውን ነው። ይህን ተልዕኮ ለማሳካት የጣሩትን ሁሉ ከሊቅ አስከ ደቂቅ መንገዳቸውን ሁሎ ፈጣሪ አምላኬ ይባርክልኝ - ይቀድስልኝ። ከዚህ ከተባረከ ማዕልት ጋር እንደገናኝ ምክንያቴ እነሱው ናቸው እና ከመቀመጫዬ ብድግ ብዬ ይሄው ከምር፤ ከዕውነት በቅኑ ትህትና አመሰገንኳችሁ። አክብሮትም ይታከልላችሁ። እማይቻለውን የቻላችሁ ልባሞች ናችሁና እና።
ከጀርመን - ከፍራንክፈርት አማይን፤ ከሆላንድ - ከአምስተርዳም ከተማ፤ ከሲዊዘርላንድም፤ ከአሜሪካ እንዲሁም ከከኢትዮጵያ የሥነ - ጥበብ ሩሖች፤ የሥነ - ጥበብ አንጎሎች፤ የሥነ - ጥበብ ዋቢዎች ያን መድረክ በአሃታዊነት ነፍስ ዘሩበት፤ ነፍስ ፈጠሩበት፤ ነፈስ - ታደጉበት። አብረው የተፈጠሩ እስኪመስሉ ድረስ። ኑሩልን። ኩራት - በትፍስህት።

ደስታው ወላዊ ነበር። በነፍስ ወከፍ በእያንዳንዱ የህሊና መንፈስ ውስጥ ሙሉዑ ሐሴት ነበር። ልጆች ከአዋቂዎች እኩል መገኘታቸው ብቻ ሳይሆን፤ ሳቃቸው፤ ፍኃሰቸውን ላይ አንድ ወጥ መጸሐፍ ያጽፋል። የልጆች የሳቅ ቃናዊ ምቱ እኮ ህብር ነበረው። የነበረው የዛች ታላቅ ሐገር ማግኔታዊ ብሄራዊ ስሜት ወርቅ ነበር። ፈጽሞ በስብሰባ፤ በሰላማዊ ሰልፍ ተገኝተው የማያውቁት ሁሉ ነበር የተገኙት። ይህን የመሰለ ብሄራዊ የመተሳሰብ አህዳዊ ጉዞ ያዳመጥኩት የአረብ ሐገር እህቶቻችን ሰቆቃ ለመጋራት በርን ላይ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ነበር። ልክ እንደዛ ዛሬም የጸደቀ መንፈስ በውስጥ ለውስጥ የመገናኛ ሐዲዱን ዘርግቶ ነበር ያዬሁት። የታዘብኩትም። ታቦት የመጣ እሰኪመስለኝ ደረስ ፈጽሞ የማልጠብቃቸው ወገኖቼ ሁሉ ነበር የተገኙት። የአርሴማ ሲገርመኝ … ዙሪክ ያላችሁ ከትንሿ አንደልፊንገን እያያን ታውቋታላችሁ አይደል? እሷ ተገኘች።  ሁለተኛው ዙር ላይ ልትገባ እዬተዳፈች ስትመጣ አገኘኋት። ግርም ድንቅ የሚል ነገር። ኧረ እንደ እኔ ግርም ይበላችሁ? እያያ? መስህቡ ምን ይሆን ሚስጢሩ? ሌሎችንም ከተለያዬን ረጅም ጊዜ ነበር፤ ዛሬ ከእነዛ ወገኖቼ ጋር እንሆ በጣይቱ ማዕከል ህሊና ተገናኘን። መገናኛ። ይገርማል።

ሌላ የሚገርም ነገርም ደግሞ አለኝ እኛ የመጀመሪያው ዙር ነን። እኛ ስንወጣ ደግሞ ሁለተኛ ዙር ይገባል። ሰልፉ በጣም ይገርም ነበር። መቆሚያ ቦታ አልነበረውም። የእውነት። የእኛ ጊዜ እራሱ ቦታው አንሶ ትዕይነቱን ቆመው በደስታ የተከታተሉ ሁሉ ነበሩ። ወይ ኢትዮጵያ ስንት የተከደነ የመንፈስ ጥሪት ነው ያላት? ሲዊዘርላንድ ላይ ይህን ያክል በጥበብ ፍቅር ልቡ የነደደ ልጅም አላትን? ታዳሚዎችም ከሁሉም የሲዊዘርላንድ ክ/ሐገሮችና ከተሞች የመጡ ነበሩ። ይህ የወልዮሽ ዬባለቤትነት ስሜት ጠረን በሥነ - ጥበብ ረቂቅ ተፈጥሮ አቅም፤ ብቃት፤ ትትርና የታፈሰ ሐብት ይመስለኛል ወገንን ከዬጓዳው የጠራው …

ወደ ቤት ስመለስ ትራም 14 ላይ ሦስት ወገኖቼን አገኘሁ። እነሱን ከዚህ ቀደም አላውቃቸውም፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር ያገኘኋቸው፤ እና ምን ተሰማችሁ? ስል ጠዬቅኳቸው።“ ከደስታ በላይ አሉኝ“  እንዲያውም „ምነው በዬወሩ በሆነ“ ሲሉም አዳመጥኳቸው። ድካሙ፤ ጥረቱ፤ ልፋቱ ፍሬ ያፈረበት ቀን ነበር ማለት ይቻላል። ዓውደ ምህረቱ እንዲህ በታዳሚ ቲፍ ሲል ለተዋናዩም ማዕረግ ነው። „የቴውድሮስ ራዕይ“ በፈተና፤ በመከራ የተሞላ ስለሆነ ታዳሚው በሙሉ ያን ድባብ ተጋርቷታል ብዬ አስባለሁ። ተመስጦው ልቅና ነበረው። ለቅሶው እጅግ ረቂቅ ነበር። የተዋቡ „የተነስ፤ ምን ትጠብቃለህ!“ ወኔው ራሱ፤ ድሉ፤ የንግሥ -ሥራዓቱ ሲታይ ደግሞ እልልታው በመቀባበል በጋራ ይቀልጣል። በታዳሚውና በተዋናይ። ተውኔቱ በሚገባ ከአድማጩ ጋር የተዋህደ ነበር። ያ … ረቂቅ የውስጥነት ስሜቱ 100% ለታዳሚው ተደራሽ ነበር። የስሜት ውርርሱ ባልተቋረጠ መልኩ ይታይ ነበር። የስሜት ለውጡም እንዲሁ። ድባቡ፤ ግርማ ሞገሱ ልዩ ነበር።

ይህን ሳይ እንዲህም አልኩኝ …

ኢትዮጵያዊነትን በማቅለም ረገድ መንገዱ ተገኝቷል ብዬ አስባለሁ። የጥበብ መንገድ የተበተነን መንፈስ ይሰበስባል፤ ይመራል፤ ያስተዳድራልም። …. የዜግነት ድርሻ ብቻ ሳይሆን፣ የዜግነት እኩልነትም በጥበብ ዓውደ ምህረት ያርጋል እና፤ እናማ ሥነ - ጥበብ ብስል ከቀሊል ሳይል ሁሉን በእኩልነት የሚያስተናግድ የመቻቻል ተቋም ነው። በስሜት ነው ሐዲዱ የሚዘረጋው። በስሜት ነው መንፈስ ከመንፈስ የሚያስተሳስረው፤ በስሜት ነው ንጥር ኪዳን ውል የሚያስማማው።  ያ … እኔ ያዬሁት እና ውስጤ የተቀመጠው የማይገኝ የሆነ ረቂቅ የተደሞ እድምታ ነገን የማብቀል አቅሙ ሚዛን ሊወጣለት ፈጽሞ አይችልም። በተከታታይ ቢሠራበት ውጤቱ ስብላማ ይሆናል ብዬም አስባለሁ። የሥነ - ጥበብ ሰው መንፈስን ወደ ፈለገው አቅጣጫ የመግራት አቅሙ የጸሐይ ብርሃን ጉልበት ያህል ነው። ተንባይም ነው። ስበቱም ያን ያህል ጉልበታም ነው። ሁሉ በወል  ሲስቅ - ደስ ሲለው፤ እኩል ሲያስብ በጥልቀት እና በተመስጦ፤ እኩል ሲቆረቆር በባለቤትነት ስሜት፤ እንዴት ደስ ይላል። ከዚህ በላይ ከቶ ምን ሰናይ ይኖር ይሆን? ሁሉም የእናት ሐገሩን መከፋት ሲይ በሲቃ ሲያዝን - ሲያለቅስ፤ ደስ ሲላት ደግሞ ፍንክንክ ሲል ምንኛ ይደላል።

  • የሐገሬ ልጆች …

„የቴውድሮስ ራዕይን“ የአውሮፓ ጉዞ ተልዕኮና ግብረ ምላሹን ከጭብጥ አቅሙ ጋር በማገናዘብ ከእኔ ከፍ ባለ ዕውቀትና ተመክሮ ያላቸው ሁለት ወንድሞቼ የተከበሩ  ዶር. ፈቃደ በቀለ ከበርሊን እና ከአምስተርዳም ደግሞ ጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ የራዕዩን ነፍስ በተባ ብዕራቸው፤ እንዲሁም በዕውቀት ላይ በተመሰረተ ትርጓሜያቸው አመሳጠረውታል።
ስለሆነም እኔ በግሌ በዛች ቅጽበት የተሰማኝን ስሜቴን፣ ውስጤ ያለኝን ደግሞ ከሐተታዊ ወደ ግጥማዊ ቀይሬዋለሁ እና እንሆ … የቻላችሁ ከደስታዬ ብዛት ለመጀመሪያ ጊዜ ፈጥኜ ግጥሙን በምለጥፍላችሁ ሊንክ ማግኘት ትችላላችሁ። ምን አልባት ለሳተናው የላኩት አውዲዮ አይዋ ጉግል ካላደረሰው። የሥነ - ጥበብ ፍቅር ከተፈጥራዊ ፍቅር በላይ ነው። የልብ አድርስ - አረስርስ።  የሐገር ሽታ ጠረኑ፤ ፍቅሩም ከተፈጥራዊ ፍቅር በላይ ነው …. የሐገርን ፍቅር የሚተረጉም ወይንም የሚያመሳጥር ቃል ምድር አልሠራችለትም። ሐገር ነፍስና ሥጋን ያዋሐደ ርቁቅ መንፈስ ነው።  ደስታዬ ይሄው  …. ኮምኮሙ … መሸቢያ ጊዜ ….

ሱባኤዋ ትዕይንት ….

ሆይ! ቆሞሱ በደም ውስጥ ተቀልሞ፤ ውስጥነት ተሳልሞ …
ዘመን ሲረጎም ከማማ ላይ ሰፍኖ፤ መንሹ ተንሰራፋ ማግሥትን ተልሞ።
የበርኖስ ሙቀቱ ክኽሎቱ ላይ ሰክኖ፤ ሥነ - ነባቢቱ፣ ክብካብን አልሞ፣
ብራናው አጌጠ መሆንን ከውኖ፤ አሜንን ከትቦ።
አቋቋም በተስፋ በምልሰት ሸምኖ፤ በልባም ህሊና ሩ----------------ቅን ከንድቶ፤
ሽማግሌው ዕውነት በጉልቱ አንቡጦ፣ ያለለት በርክቶ።
እህ! „የእብድነት¡“ ስብከት እንጥሉ ጠውልጎ፤ በህምታ አማጠ እንደደነገጠ፣
የታሪክ ትልልፍ ከወገብ ተቀጨ፤ ቀረ እንደ ተጠ፣
አጎንበሶ ሄደ እንደጎባ-በጠ - እንደሆመጠጠ - እዬተሟ-ጠ-ጠ።
እልልልልልልልል …..
የገደመው መክሊት ዘውዱ ላይ ዘምሮ፣
ማህሌት - ተዜማ በቅኔ ጎምሮ፤ በዝልቀት አምሮ
እውነት ቀን ወጣለት በሠቁ ዘ-----ምኖ።
ሃቅ እሸት ሆነ፣ አዬነው ደምሮ፤ -ማምሮ፤ ጨምሮ - -ማምሮ …. ጨማምሮ … ጨማምሮ።
የንጉሦች ንጉሥ ልቅናው ሲደጉስ፤ ድርሳን በመወድስ ጽናጽሉ በቅርስ
እሱባለው ለታ … „የቴውድሮስ ራዕይ“ የአኃቲነት ህዋስ፤
ማዕዶተ - ህብስት፤ የምት ደምመላሽ፣ ሆነ ʼልብ አድርስ።  
ትናንትን ከዛሬ፤ ዛሬንም ከነገ ቅዬሳው ፍሩንድስ
የትሩፋት - ተክሊል፤ የትውፊት ተቋም ልብስ።
ሱባኤትዕይንት ….  እንደዛ ተውባ፤ ደመቃ ተሞሽራ፤
ቁርባኗ-ን ነቁጣ፤ ከሥ አዳምጣ፤ እንደራሴ ሆነች የነገዋ ብ
የጥበብ ጎመራ - ባላና ወጋግራ።
ጥብብ ዓውዷን ሠራች - በመክሊቷ ድራ፤ ለማተበ - ለቃሉ - ለአራ አራ።
 ግድፈትን አክፍላ፤ ተዘዴ ተጣብታ - ዕልፍን አበራክታ፣
መጪ አለች …..  እቴጌ ዕዮብን …. አቅንታ።
ጥበብ ዓይን አፍርታ፣ ኩሏነን ተኩላ፤ ማስተዋል ተቃኝታ፤ ብቃትን መስክራ፣
ግልጽነት ጸልያ፤ ሚዛን አደላድላ፤ ቀደምት ʼርስት አʼርጋ፤ ጥልቀትን ፈርማ - ክህሎትን አስብካ፤
ዬጽናት  - ማዕከል የተፈጥሮ  ዋርካ።
መኸርን ፤ ጸደይን፤ ክረምትና በጋን በመርኽ ወርባ … አስብላ ዘክራ …
ሰርዴታ ተሰርታ፤ አለባሶ አክላ፤ ቀልቤዋንም በቀልብ እንሆነን ጠልፋ፤ አደሱን ጨምራ፣
መቼቱ ሁልʼቀፍ የሁሉዬ አʼርጋ፤ ʼር--------------ጋን አዜመችው በተደሞ አስኽና /  በዕድምታ ሠርታ።
ክብር አሰከበረች - ድርብ ተደርባ፤ ማርከሻ አነባብራ … ደ-ራ-ር-ባ፤ ደራርባ … ደራርባ … ደራርባ ….
የኛዋ ወ/ሮ፣ ማኛዋ ደርባባ፤ ጭብጥን የተረዳች የቅምር ዘንባባ።
እንሆ እንዲህም ሆነ ….. በውማዊት ቅባት ….
ልቅና ቀደሰ፤ ግብር ቀንዲል ሆነ፤ 
አፈር ተወደሰ፤ ትናንትም ቀ-------------ሰሰ፤
ተመስገን ተናኝቶ //  ኪዳን አደረሰ።
ሰንደቅ ቀን ወጣለት፤ ኖ---------------ነት ተቃኜ … ልጆቹን አሰሰ ….
ራዕይ ተክሊል ሆነ፤ መንፈስ ተመለሰ፤ እዬገሰገሰ ወደራስ  ሞገሰ።

እኔ ተመስገን ብያለሁ።
ሥጦታ „ለቴወድሮስ ራዕይ“ መላ አካላትና ነፍስ ይሁንልኝ።
ሲዊዘርላንድ - ቪንተርቱር። ጥቅምት 7..2017 እ.አ.አ።

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
እግዚአብሄር አምላክ ልዕልት ኢትዮጵያንና ዓለምን ይጠብቅልን።
አሜን።
„ፍቅር ያሸንፋል።“

ሥርጉተ - ሥላሴ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።