አብይ የጎንደር ብቸኛው ጌጥ! ክፍል ሁለት፤

              አብይ ኬኛ! ለቅኖች ብቻ! ክፍል ሁለት፤
                      አብይ የጎንደር ብቸኛው ጌጥ!
                                 
 ሥርጉተ ሥላሴ (Sergute©Sselassie)
24.12.2017 (ከጭምቷ - ሲዊዘርላንድ።)
„አቤቱ ከንፈሮቼን ክፈት፤ አፌም ምስጋናህን ያወራል።“
   (መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፶ ቁጥር ፲፭
)



ጋዜጠኛ ማስረሻ አለሙ „ማማ“ በሚለው ዝግጅቱ „ከመለሳውያን ወደ ለማውያን“ በማለት እራፊ ጨርቅ ሳያክልላቸው ካብጠለጠላቸው „ለማውያን“ ወጣት የፖለቲካ ሊሂቃን መካከል ዶር. አብይ አህመድ አንዱ ናቸው። 

ጋዜጠኛ ማስረሻ አለሙ ዶር. አብይ አህመድን የቀረጸበት መንገዱ በራሱ ሃሳብ ውስጥ መቆም የተሳነው፤ ውራጅ ፖለቲካን የሙጥኝ ያለ፤ ዘልዛላ ሰብዕና አላብሶ ነው ያቀረባቸው። አምላኬ ይቅር ይበለው። ይህ የተለመደ መንገድ መሆኑ ቢገባኝም አሽኮኮ አድርጎ መኖሩ ግን የገለማኝ ስለሆነ አሁንም በተከታታይ በዚህ ዙሪያ እሞግተዋለሁ። 

አቅም ብቅ ባለ ቁጥር እንዳይበቅል፤ እንዳይጸድቅ ከዝንተአለም መከራ ሳይሆን በሞት ውስጥ መኖርን ላልተፈቀደለት ዕንባማ ህዝብ የማይበጅ መንገድ በመሆኑ በትጋት መፋለም ይገባል። እርግጥ እሱ የቤተ - መንግሥት ሜዲያ አዘጋጅና አቅራቢ ጋዜጠኛ ስለሆነ ባለ ዓለምዐቀፍ ሚዲያ ነው። 

እኔም እንደቅሚቲ በሳተናው ብራና ሚዛኑን ማስጠበቅ ይገባል ባይ ነኝ።  ጋዜጠኛ ማስረሻ አለሙም ከቤተ- መንግሥቱ መንበር ወረድ ብሎ ታች ትቢያ ላይ ያለነው ጥቁር ለባሾችም ደግሞ ምን እንደሚሰማን ማወቅ ይኖርበታል - ተገዶ። መቼስ ሁሌ እንደተጠንጠለጠሉ አይኖርም። መውረድም መውጣትም ሂደት ነው ….
  • ·         የሃሳብ ተክል። 


የዕሳቤ ጉዞ በሦስት መንገድ ሊገለጽ ይቻላል፤ አንደኛው ሃሳብ ተዋሹ በራሱ ተነሳሽነት በሌላው ሃሳብ ውስጥ ለመኖር ሲፈቅድ ነው። የዚህ ቤተኛ አቅሙን ለክቶ መነሳት ማቀድም ይቸግረዋል። ሃሳብ አፍላቂው ተዋሹን ሃሳብተኛ ሊቀበለውም ላይቀበለውም፤ ዕውቅና ሊሰጠውም ላይሰጠውም ይችላል። 

ስለሆነም ሃሳብ ተዋሹ ወይንም ሃሳብ ተጠማኙ ተወዛዋዥ መርከብ ውስጥ እንዲቀመጥ ግድ ይለዋል። አወሎ ውስጥ የከተመ የሃሳብ ጅዋጂት ይገጥመዋል። ስለምን? ሃሳብ አፍላቂው ያመነጨውን ሃሳቡን በፈለገው ሁኔታ ሊያስኬደው፤ በአሻው ሁኔታ ጊዜና ወቅት ሊዘረጋው፤ ሊያጥፈው፤ ሊኮረኩመው፤ ሊኮረኩደው ጭራሹኑ ሰርዞ ሊተወው ይችላል። 

በዚህ ሁኔታ ጥገኛው በክፍተት እንዲናጥ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ በጎጆው የተጠለሉት ተስፋ ቆራጭነት ሊያሳዩ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ጥገኛው ተሳቢ ብስጩና ገረጭራጫ ይሆናል። ተስፋ ቆራጭነት ተቋቁመው ከእሱ ጋር ሞቱን ሞታችን ያሉት ቤተኞቹ በተጨማሪነት ገረጭራጫውን ባህሪ ሲታከልባች የውስጥ ሰላማቸውን ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ጎጆው ቀስ በቀስ እዬተናደ ሊሄድ ይችላል። ሃሳብ ተጠማኙን የተጠለሉትም አንቅረው ሊተፉትም ይችላሉ። ስለሆነም ከሞቱ አማሟቱ ይሆናል። 
„የሰው ወረቅ አያደምቅ እንዲሉ ….“

ሁለተኛው ቀድሞ በታሰብ ሃሳብ ውስጥ በጭነት በሌላው ሃሳብ ውስጥ እንዲኖር የሚገደድ ደግሞ ይኖራል። ይህ ደግሞ የውራጅ ሃባሳብ ቤተኛ ነው። እንደ ራሱ ሆኖ ለመኖር ስለማይፈቀድለት እሱ ባልፈጠረው ሃሳብ ውስጥ ለመኖር መገደዱ እራሱን ሙሉ ለሙሉ ለውጦ አዲስ የቅጅ ሰብዕና ወይንም የውራጅ ሰብዕና እንዲላበስ ይገደዳል፤ ይሄኛው ወድቆ በተነሳ ቁጥር ትቢያ እዬቃመ አወዳደቁም፤ አኗኗሩም አይሆኑ ሆኖ የሚኖር የቀውስ ቤተኛ ነው። 

መስሎ ወይንም በቅጅ ህይወት እንዲኖር በመገደዱም ውስጡ የጭንቅ ምጠኛ ነው የሚሆነው። ኮሽ ባለ ቁጥር ደንጋጣ ይሆናል። ይህ አዘወትሮ መነቃነቅ የሰፈነበት የኑሮ ዓይነት ሲሆን በዚህ ዙሪያ ጠ/ ሚር ሀይለማርያም ደሳለኝን ማዬት ይቻላል። በትዳር ህይወታቻው ያላቸው ፍጹም ስክነታዊ እና አብነታዊ ሙሉዑ አቅም ለፖለቲካ ህይወታቸው ስንቅ ሊሆን አልቻለም። 

ስለሆነም ጠ/ ሚሩ በግጭት እና በስበት የተወጠረ ስንጥቅ ወይንም ትርትር የፖለቲካ ህይወት ነው ያላቸው። „ከወረቱ ስንቁ ልቆ አይነት“ ከሹመቱ ይልቅ በግራ ቀኝ የሚደርሰው ሰብዕናን የሚቀረጣጥፍ ተራጋጭ መከራን አዝለው እንዲኖሩ ተገደዋል። ግን ይችላሉ ውራጁን ወይንም የልዋጩን ልብስ አውልቀው በሚያስከብራቸው የአቅም አምክንዮ በሙያቸው የመኖር። 

በዚህም ቤተሰቦቻቸው በተለይም የትዳር አጋራቸው ቀዳማዊት እምቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ እርጋታቸውን በመመገብ ከመከራቸው ጎን ሆነው፤ የሥነ - ልቦና ጥንካሬን እንዲያገኙ የማያዳግም የውሳኔ አቅም እንዲኖራቸው መትጋት ያለባቸው ይመስለኛል። ተጠግኖ የሚድን በፍጹም አይደለም።
    
ሦስተኛው በራሱ ሃሳብ ውስጥ ለመኖር የፈቀደ ነው። ይህ በራሱ ሃሳብ ለመኖር የሚፈቅደው የማሰብ ዲታ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የሃሳቡ ማረፊያ አስተማማኝ የለማ ህሊና እንዳለው ጠንቅቆ የሚያውቅ፤ አቅሙን መጥኖ የሚንቀሰቀስ፤ በራሱ ውስጥ ለመኖር የፈቀደ፤ ጥገኛ እና የትውስት የሃሳብ ቤተኞችን የተጸዬፈ ነው። 

ስለሆነም በተረጋጋ ሁኔታ ያስባል፤ ያሰበውን እቅድ ውስጥ ያስገባል፤ ያቀደውን ይፍጽማል። አያልቅበትም ስለአለው በቂ ጥሪት። ፏፋቴ። ጎን ለጎን የሃሳብ ዲታ በመሆኑ አዳዲስ ተነሳሽ ሃሳቦችን እዬፈለቀ በድርጊት የበቀለ ስለሚሀፐን የቤተኞቹን ቁጥር ከዕለት ወደ ዕልት የመጨመር አቅም ያለው ይሆናል። ስለዚህም እርምጃው ወይንም ኮቴው አጓጒ ይሆናል። 

ይህ የዕሳቤ ጉዞ ተስፋውን ለማዬት ትትርና በብልህነት የታጠቀ፤ ምራቁን የዋጠ ጉዞ እንዲኖረው ያደርገዋል። እርግጥ ነው እንዲህ ያለው አቅም ልታይ ልታይ ስለማይል ተግባሩ ገኖ አደባባይ እስካልዋለው ድረስ በጭምትነት ነው ተግባር ተኮር አስፓልቱን የሚዘረጋው። ጎልቶ መውጣትም ምኞቱ አይደለም። ልክ እንደ ጭምቷ ሲዊዝ ተፈጥሮው የተከደነ ሲሳይ ነው ግን ያሰበለ። ሂደቱ ረቂቅ ነው፤ ውስጡም የተደላደለ ነው።  

በዚህ ስሌት ሰንሄድ ዶር. አብይ አህመድ Thinker ናቸው። ጋዜጠኛ ማስረሻ አለሙ እንደሚለን ሃሳብ ተዋሽም፤ ውራጅ ሰብሳቢም አይደሉም፤ ሃሳብ ተበዳሪም የሃሳብ ቅራሪ ለቃሚም አይደሉም። ሃሳብ ቀጂም ሆነ ሃሳብ ተጠማኝም አይደሉም። በራሳቸው የሃሳብ ማህሌት ውስጥ ለመኖር የፈቀዱ ባልርግጥ ናቸው። 

እርግጠኛ የሚያደርግ የእኔ የሚሉት የራሳቸው ሃሳብ ያላቸው ፖለቲከኛ ናቸው። ስለሆነም ነው የውስጥ መረጋጋታቸው በዬትኛውም መድረክ ሳቢና ተናፋቂ፤ መስጭና አቅራቢ፤ አወያይ እና የቀና ነገ አደርጌ እን በግሌ የማያቸው። ቁጥር ሦስት እሳቸውን በወግ ያመሳጥርልኛል። እሳቸው ነገሮችን የሚዩባቸው መንገዶች በፍጹም ሁኔታ ከኖርንበት የፖለቲካ ፍልስፍና እጅግ የራቀ ነው። ተፈጠሯዊ ነው። ይህን እኔ ስላልኩት ሳይሆን ነገም የሚታይ ነው። ይህን የአዲስ ዕሳቤ አስፓልት አልኖርንበትም፤ ከዚህ ቀደምም አላዬነውም። 

ምንአልባት ይሄ ቀን እንዲመጣ ያሰብን ልንኖር እንችላለን፤ በራሱ ሃሳብ ውስጥ ለመኖር የወሰነ ሊሂቀን መናፈቅ። በውራጅ ሃሳብ ውስጥ አራሱን ያልደበቀ ሊሂቅ ምኞታችን ነበር። ሃሳብ ለማፍለቅ የማይቸግረው ሊሂቅ ራህብ ነበረብን። 

ሃሳብ ማፍለቅም የማያልቅበት የሃሳብ ጧፍ የተስፋችን የኖኽ መርከብ ነበር። እርግጥ ነው እንዴት ፖለቲካ ውስጥ እንደገቡ የሚገርሙኝ ድንቅ የሞራል ፖለቲከኛ አሉ አቦ በቀለ ገርባ፤ የሳቸውም ቀለምም ተፈጥሯዊነት ነው። ለዚህም ነው ባዕቴ ያከበረቻቸው፤ ያቀሰሳቻቸው፤ ከፍ አድርጋም - በሰማዕትነት የቀደሰቻቸው።

  • ·         ለማከብረው ለአቶ ወንድም ለመሳዩ /ጋዜጠኛ/።


እግረ መንገዴን ለምወድህና ለማከብርህ ለጋዜጠኛ መሳይም መኮነንም መልዕክት አለኝ። „የኢህአዴግ ስብሰባ“ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ስላነሳህውም ተያያዥ ስለሆነ ጥቂት እንደል ወደድኩኝ። ያልከው እንደ ተጠበቀ ሆኖ - የተስማማሁበት። ዶር. አብይን አህመድን ከውስጥህ አድርገህ ብትፈትሻቸው ስጋት አይኖርብህም ብዬ አስባለሁ። ከአንተም ከእኔም ያለነሰ ከወያኔ ሃርነት ትግራይ ጋር ይተዋወቃሉ። 

ዶር. አብይ አህመድ ያጠኑት ሰላም እና ደህነነት Peace and Security ነው። እርግጥ እንደ ተለመደው እያደራጁ፤ እያመቻቹ ና ምራኝ መጠበቅ አይቻል ይሆናል፤ ስለምን? ብድር ቀረማ የሚያስኬድ የአቅም ችግር ስሌለ። በስተቀር ግን 40 ዓመት ያልታዬ ልቅና እዬታዬ ነው። አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። 

የሚበልጥ ዜጋ ስለመኖሩም ማወቅ ግድ ይላል።  „ፋኖን“ በሚመለከት ያነሰሃት ነገር ቀልቤን ስባዋለች። ብዕሬን ያደከመች አመክንዮ ስለነበረች። መልሴ „የሌለ ነገር የወንበር ሽግሽጉ አይመለከተውም¡“ ነው። አስተውል ምልክቱ ስላቅ ነው። ከልቤም ስቄያለሁ - የምሬን ነው የምልህ። „ለፋኖ“ የህልውናው ጥያቄ ያለው ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ራዕያ እና የአማራነት የመኖር ዕውቅና እና ክብር ነው። 

በሌላ በኩል የፖለቲካ ትግል እኮ ለሥልጣን የሚደረግ ነው፤ እና በሌሉበት እንኖራለን ብለው መቼም አቅም አያባክኑም በተለይ አማራ። አማራ አጀንዳ ሁኖ አያውቅም። ሌላ ሹመኛ የሚያስጠብቃቸው ነገር የለም። ምን ሊያገኙ። ቋንቋቸው አማርኛ ነው፤ ሌላ ቋንቋ ደግሞ አይችሉም። 

ምክር ቤት ካልገቡ ተወዳዳሪ ሊሆኑ አይችሉም። አንጋችነቱ በቅቶታል አማራው። ለነፃነት/ ለዲሞክራሲ ለምንትሶ ለቅብጥርሶ የሚባለው ያለንበት ስለሆነ ቀስቃሽ አያስፈልግም። ሌሎች አመክንዮች በቀጣይ የሚታዩ ይመስለኛል። „ቄሮን“ በሚመለከት ዕወቅናውን ያደመጠ በትውልዱ ዕድሜ ልክ የሚመጥን ብቻ ሳይሆን፤ ለሌላም የሚተርፍ ተስፋም የሚሆን የሰከነ፤ የተረጋጋ፤ በራሱ ሃሳብ ውስጥ የከተመ የዕውቀት አቅም በመዳፉ አለ። 

የትውስት ፖለቲካዊ ማንፌስቶ የሚፈልግ ይሆናል ብዬ አላስብም። አሳታፊነቱን በሚመለከት ሂደትን መጠበቁ ጥሩ ነው። ከላይ ከላይ መጫኑ የተገባ እይመስለኝም ይህን „ቅደመ ሁኔታ“ መወጠሩ አደብ ቢገዛ ባይም ነኝ። በእጅ ባለው ዴሚክራሲ ትችትን፤ ነቀፋን፤ ነፃ ሃሳብን ለመቀበል ያልደፈረውም ይህን እንይ ተብሎ አልተፈጣጠም። በዚህ የእውነት ማህደር እንደ ጋዜጠኛ እኔ እና አንተን የሚያስማማን ይመስለኛል። ካላዳለህ!

አየህ መሳዩ … ለእኔ ለአማራዋ ጎንደሪት የኦሮሞ ሚዲያ የጣና ጉዞ፤ „ጣና ኬኛ! አማራ ኬኛ!“ የመንፈስ ውህድነት ጉዞ፤ ጉዝጓዙ ለዚህ ነው። የበሰለ - የሰከነ - የበቀለ - የጸደቀ መንፈስ ነው። ከልባችን ቅኖች የተቀበልነውም ለዚህ ነው። 

የጋሜና የታሪያችን ዘመን መቋደሻ የሆነውን ፖለቲካዊ ህይወት እስከ ጉልምስና የፈተሸውም ይህ አምክንዮዊ ጉልበታም ተመክሮ ነው። አዬሩ አማራን አክብሮ፤ አማራን አቅፎ፤ አማራን ዕውቅና ሰጥቶ፤ የአማራን ሊሂቃን ተንከባክቦ የተነሳ ብቻ ሳይሆን መኖራችን በልቡ ያበቀለ ጉልበታም የለወጥ መንፈስ ነው ያለው ሀገር ቤት። 

ዶር. ዳኛቸው አሰፋ ፈላስፋችን ናቸው። የሆነ ሆኖ ይህን የሰቀቀን ህይወት ባመንከው፤ ቤዛዬ ባልከው፤ ሥህኔ ባልከው፤ መንፈስ ውስጥ አለመኖርህን፤ መገለልህን ስታውቅ የነበረውን የሥነ - ልቦና ቁስለት - እና የአሁኗን ጮሪትን እምናውቀው እኛ አማሮች ብቻ ነን፤ በተለይም እኔ ሥርጉተ - ሥላሴ። እሳት ውስጥ ካለ አንዳች ጥግ ሪሚጦ የነበርኩት። አንተ እንኳን አልደረስክልኝም። ብቻዬን ነው የተጋፈጥኩት።

ሌላው የጎንደርን ሥነ - ልቦና አንደ ቀላል ምናምንቴ ነገር መመልከት የተገባ አለመሆኑን አድማጭ አልተገኘም እንጂ በተከታታይ ሠርቸበታለሁ በ2013/ 2014። መወለዴ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ሃላፊነት የፖለቲካ አደራጁ ስለነበርኩኝም። 

መሬት ላይ ሠርቻለሁኝ። ሥርጉተ አርበኛውም ናት ለጎንደር። ወንዱ ተሰልፎ አስፓልት ላይ ተነጥፎ ቁሞ ውሎ ሲያድር መሳሪያውን ሊያስረክብ ለወያኔ ሃርነት አንጋች ሲሰለፍ፤ ሥርጉተ ግን ክላሹኗንም ኮልቷንም ለአልደፈርም ያሰታጠቀች ልጁ ስለመሆኗ ጎንደር ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩት የወያኔ ሃርነት ቤተኞችም አክብሮትንም የለገሷት መሆኑን ያውቃል። እርግጥ በቀላቸው ምድር ነው።

ሌላው ---- እንትዬ አንተ በቅርብ የምታገኛቸው ጎንደሬዎች ሁሉንም ከመጤፍ ሳይቆጥሩት ተመልክተህ፤ ወይንም ታዝበህ ሊሆን ይቻላል። ያለፈው ዓመት አልበቃ ብሎ የዘንድሮ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ዕጣ ፈንታ በምን ሁኔታ እንደ ተቋጨ ተመልክተናል። ውስጡ ያልነደደ አንድም ጎንደሬ አታገኝም። ከፖለቲካ ውጪ የሆኑት ሁሉ ጭሰዋል። 
  
ጎንደርን ውስጥ ማድረግ አትራፊ ነው። የዶር. አብይ አህመድ የመንፈስ ማህጸን ደግሞ ጎንደርን ፈቅዶ የፀነሰ ነው በብልጠት አይደለም። ለታክቲክና ስትራቴጅም ማሟያም አይደለም። በልጅነት መንፈስ ነው። ጎንደርን በፍጹም ልቦና ያቀረበ ብቻ ሳይሆን ስፍስፍ ብሎ የወደደ ነው በድንግል መንፈሱ። ሌሎቹም እንዲወዱት ምን መሆን እንዳለበት የተጨነቀ፤ የተጠበበ መርሃ - ጽድቅን የነደፈ መንፈስ ያለው ነው። የጎንደሮች ማንነት ፕ/ መስፍን ወ/ማርያም እንደሚጸዬፉን „ባዶዎች“ አይደለንም። 

የዶር. አብይ አህመድ መንፈስ አንደ ሌሎች የፖለቲካ ሊሂቃን እና ጸሐፍት ጎንደርን የተጸዬፈ አይደለም፤ ጎንደርን የናቀና ያጣጣለ አይደለም፤ ምን ታመጣላችሁም ያለም አይደለም፤ ትእቢትንና ማንህሎኝነት ያላስጠጋ ነው። 

ጎንደርን የእኔ ያለ የመጀመሪያው ቅዱስ መንፈስ ነው። ጎንደርን 23/ 24 ዓመት በህግ - ልቦናው የጸነሰ የዳጎሰ መንፈስ ነው ያላቸው ዶር. አብይ አህመድ። ለዛውም ከእኛ ተወለደንበታል ከምንለው በተግባር የጸደቀ ተቆርቋሪነት ነው ያላቸው። እስቲ መዝነው አጠገብህ ጎንደሬዎች አሉ እኮ። የሆነ ሆኖ ቢያንስ የአባቶቻችን ጸሎት አብሯቸው ይቆማል። ወታደራቸው ነው። ስለ ጥላቻ የሚነሱ አሉታዊ እሳቤዎችን እንዴት ያዩታል ዶር. አብይ አህመድ?
  • ·         አንደዚህ …


„ሰው ጠልተህ መተኛት አትችልም። ሌሊቱን ሰውዬው በሌለበት ስትቃጠል ነው የምታድረው። እሱ አያይህም። ያለህበትን ሁኔታ አያውቅም። አንተ ግን ስትቃጠል ታድራለህ። ከዚህ ውጪ መወጣት አለበት። ሰውን ለመጥላት መሮጥ ነገርን ለማሰብ  አዕምሮአችን ማበላሸት የለብንም! ጊዜያችን ማጥፋት የለብንም! እኛ ምን እንደርጋለን? ሰው እንወዳለን! ሰው እናቀርባለን! እስከተቻለን ድረስ ሰውን እንረዳለን። ነገር ግን የሚጠሉን ሰዎች እንደሚኖሩ እናውቃለን። ዓለም እንዲህ ስለሆነች። ሰዎች ሲጠሉህ አንተም ቁልቁል ተመልሰህ ጥላቻ ውስጥ ከገባህ በእነሱ ሜዳ ውስጥ ገብተህ እዬተጫወትክ ነው ማለት ነው። የጦር ሜዳውን እንቀይር እምንለው ለዚህ ነው።“
  • ·         ቢሆን።


ጋዜጠኛ ማስረሻ አለሙ አሁንስ ትንሽ ወደ ራስህ ተመልሰህ እንደ አንድ የቤተ - መንግሥት እወቅ ጋዜጠኝነትህ ከዕውነት ጋር ለመታረቅ ህሊናህ ውስጥ መኖር አለና ከመኖር ጋር ብትፈታተሹ ምን ይመስልሃል? ምክንያቱም ጥላቻን እንዴት አንደሚጸዬፉት ወጣቱ ሊሂቅ ፖለቲከኛ መልዕክት የላኩልህ ይመስላል። አሁን ወደ ተነሳሁበት አብይ ኬኛ! ጭብጥ መጪ ልበል  … በዚያውም ለአቦ አባ ዱላ ገመዳም ጥብቅ መልዕክት አለኝ - ዛሬ።

·         የጣናን እናት ውሃ ጠማት። የጣና እናት 27 ዓመት ሙሉ ጨለማ ዘነጠባት፤ ድቅድቅ ተሽቀረቀረባት።

አዬህ ጋዜጠኛ ማስረሻ አለሙ --- ጎንደር አንድ ጀሪካን ውሃ 26.00 የኢትዮጵያ ብር ይሸጥባታል። ግን ጎንደር የጣና እናት ናት። እኔ እዛ በነበርኩበት ጊዜ የዛሬ 23/ 24 ዓመት አንገረብ ግድብ ነበር። አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ አላውቅም። በዘመነ ፋሽት ትግራይ በወር አንድ ቀን እንኳን የጎንደር ቧንቡ-ውሃ አይመጣለትም። ጎንደር ወፍጮ በፈረቃ ነው። ጎንደር በደሙ ዋጋ ያገኘው የመብራት ጄነሬትር ስግብግቦቹ፤ ስስታሞቹ እንደገቡ ነበር ነቅለው ትግራይ ወስደው የተከሉት። 

ጣና ላይ የተነሳ ኤሌትሪክ ጎንደርን አልፎ ትግራይ ሄዶ ያበራል። ጎንደር ግን አሁንም ጨላማ ይኳልባታል። የሚገርመው ትግራይ የመብራት አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ፤ የኢንደስትሪ ብልጽግናዋ እንዳይተጓጎል የጎንደር ገበሬ ሌትና ቀን ተገትሮ ቁሞ ይጠብቃል። ቁሞ ያበላል ማለት ነው የሥርዎዕ መንግሥቱን ቤተ - መንግሥት የሉዑላንን ቤተሰቦች። 

27 ዓመት ሙሉ ልጁን እዬገበረ፤ መሬቱን ተቀምቶ፤ የተመረተው ሁሉ እዬተጋዘ፤ አፈር ሳይቀር እዬተጫነ ደግሞ በተጨማሪነት ለትግራይ ብርሃን ቁሙ በጋ በሃሩር፤ ክረምት በቁር እና በዝናብ ሰምጦ ገሳ ለብሶ ይጠብቃል - ያ ድሃ መከረኛ፤ ፍዳው የጠና፤ ቀኑ የጠቆረበት። ዝቅ ብለህ በምታገኘው ሊንክ ደግሞ ሀገሬው መብራት ውሃ በማጣቱ ሥራውን አቋርጦ ሞትን ለማኝ ሆኗል። ይህን መከራ ከውስጡ የተቀበለ በታሪኳ ጎንደር አንድ የፖለቲካ መሪ ቢኖሩ ዶር. አብይ አህመድ ብቻ ናቸው። 

በዓጼውም ይሁን በዘመነ ደርግ አንድስም እንኳን ተቆርቋሪ የእኔ የምትለው አልነበራትም - ጎንደር። ስለሆነም ዶር. አብይ አህመድ ለጎንደር ጌጧዋ ብቻ ሳይሆኑ የተስፋዋ ጉህ ናቸው። አይዞሽን ሳይሰስቱ በቅንነት የመገቡ የመንፈሷዋ ልዩ የክብር እንግዳ ናቸው። ጨለማ ውስጥ የኖረው መንፈሴ ብርሃን ያገኘው በሳቸው ምክንያት ነው። 

ምክንያታዊ ለሆነ መነሻዬ ደግሞ አቅማቸው ፈጣሪዬ ሥጋ ወንድሜ ባደረክልኝ የሚያሰኝ እንጂ የሚያሸማቅቀኝ፤ ወይንም የማፍርበት ወይንም አንገቴን የምደፋበት በፍጹም አይደለም። እኔ ብቻም አይደለሁም፤ በእኔ መንፈስ ዙሪያ ያሉ ቅኖች የዚህ የቅንነት ጋላሪ አባልተኞች - ቤተኞች ናቸው። ሃሳቡን ለማብራራት እዬቆራረጥኩ ነበር በክፍል አንድ ያቀረብኩት ዛሬ ግን ሙሉውን ታሪካቸው ስለሆነ ማቅረብ ይኖርብኛል።
  • ·         ፍትሃት።


„የዛሬ 23 / 24 ዓመት ገደማ አጋጣሚ እዚህ ጎንደር ነበርኩኝ። ይሄ ቦታ አዳራሽ አልነበረም። በጣም የሚገርማችሁ ጎንደር ኢትዮጵያ ሆቴል፣ ፎገራ ሆቴል፣ ጎሃና ቋራ የሚባሉ ትላልቅ ሆቴሎች ነበሩት። „ገብያ ማዕከሉም በጊዜው ትንሽ ሞደርን“ የሚባል ነበር። በጊዜው ከዚህ ወደ ርዋንዳ ዘመትኩኝ። ያኔ ሩዋንዳ 1994 ግጭት ነበርና ስዘምት ኪጋሊ ገጠር ነበረች። ከጎንደር አንጻር። አይወዳደሩም። ኪጋሊና ጎንደር በፍጹም አይወዳደሩም። ግን ኪጋሊ ባለፉት 20 ዓመታት ፕሬዚዳንቷ ማህበረሰባዊ እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር። ካጋሜ በወሩ መጨረሻ ቀን አካባቢ እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር። በዬወሩ ህዝብ ጋር ወጥቶ ከተማ ያጸዳል። እሚገነባ ላይብራሪ ካለ አብሮ ይገነባል። እሚሠራ ሥራ ካለ ይሳተፋል። መሪው ይሄ ስለሆነ አሁን ኪጋሊና ጎንደር ሳይሆን ኪጋሊና „አዲስ አበባን“ ልናወዳደር አንችልም። 

ለምሳሌ ይህን ፕሮግራም ያዘጋጃችሁ ሰዎች የፕሮግራሙ መጨረሻ አንድ ቀን ሲቀረው ሁሉም ታዳሚ ዶር. አንባቸውን ጨምሮ ጥዋት 12.00 ሰዓት ተንስቶ ጎንደርን ሳያጸዳ ከሄደ መጥቶ ገንዘብ አፍስሶ ሊሆን ይቻላል፤ ድግስ ደግሶ ሊሆን ይችላል፤ ግን አንድ ነገር አስተምሮ አልሄደም ማለት ነው። የጎንደር ዩንቨርስቲ 50,000/45,000 ሺህ ማህበረሰብ አለው። በወር አንድ ቀን አንድ እሁድ ጥዋት ለአንድ ሰዓት ለሁለት ሰዓት ተከፋፍሎ ጎንደርን ማጽዳት ሃምሳ ሺው ሁለት ሁለት/ ሦስት ሦስት ዛፍ መትከል ቢለምድ ብዙ ገንዘብ የማይመለስው ሥራ ይሠራል። ሥራም ብቻም አይደለም፤ ሰው ጎንደርን ይወዳል፤ ጎንደርም ዩንቨርስቲውን ይወዳል፤ ተቋሙ ትርፍ ይሆናል ማለት ነው። በዛ መንገድ የተመረቀ (graduated) ያደረገው ሰው ደግሞ ITW ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ የማሰብ ችሎታ (Emotional Intelligence) ያለው ይሆናል። ማገልገል የገባው ይሆናል። ለምሳሌ የዚህ ከተማ ከንቲባ (Mayor) በዚህ ዓመት ሥራ ሲቀጥር አንዱ ክራይተሪያ መሆን የሚገባው ሳትቀጠር በነጻ ስንት ጊዜ ከተማን  አጽድተሃል የሚል ሰርትፊኬት ያስፈልግዋል። በነፃ ያለገለገል ሰው ብትከፍለውም አያገለግልህም። ይህ ሰው  (this guy's) ሥራ ፈት/ አጥ ዓይነት (Unemployed) ነው የሚሆነው። የተቀጠረ ግን የማይስራ ነው የሚሆነው። ሰው በነፃ ማገልገል ሲማር ነው ሲከፈለው የበለጠ የሚያገለግለው። እኛ ጋ ስትወስዱ እብዛኛው ሰው ቢሮ ይገባል። ጃኬት ያንጠለጥላል እንዳለ ይታሰባል። አቶ እከሌ ስትሉት „አሁን ወጣ“ ይባላል። 11.00 ሰዓት ላይ ጃኬት የለም። ይህ ሰው (this guy's) የአገር ኢኮኖሚ የሚገድል ነው።“
Gonder Vs Kigali, Dr Abey explains why Gonder remained poor. / አቢያ ኪጋሊንና ጎንደርን ያወዳደሩበት።“
  • ·         ቱን።


ቅንነት የነገ መንገድ ነው። መንገዱ ወጣ ገብ ቢሆንም ከቅናዊ ዕሳቤዎች ጋር በተክሊል ለመቁረብ ግን በእጅ ያለ የመወሰን የአቅም ፍቱን ክህሎት ስለሆነ ማድረግ ይቻላል። መሆን በመሆን ውስጥ ነው በፍቱንነት እሚተረጎመው። መሆን በመቀበል ውስጥ ይኖራል። መሆን በመፍቀድ ውስጥ ይጸድቃል። መሆን በቅንነት ውስጥ ይበቅላል። ኑሮን ለማኖር ቅንነትን በመኖር ውስጥ መፍቀድ ያስፈልጋል። እርግጥ ነው አፍ ባለው መቃብር ውስጥ ባለችው ጎንደር ውስጥ መተንፈስም ሲደላ ነው። 

የተቻለው ያህል መሬት በተጋሩ ተወሯል፤ ልታድግበት - ልትለማበት - እንደ ሌላው እኩል ልትሆንበት የምትችለው አንጡራ የገንዘብ ሰብሎች (Cash Crops) ለም መሬቷን ጎንደር በግፍ እና በሃይል ተቀምታለች። እንኳንስ ለእሷ ዛሬ ለሚሞትላት አማራ አብሶ ለጎጃም ህዝብ፤ ትዕይንቱን በታዛቢነት ሲመከት ለነበረው አማራ ሁሉ ከበቂ በላይ ነበር መዋዕለ ጥሪቱ። የቀረውም ኩርማንም በሶስት ተሸንሽኖ ለግዳጅ ዝግጁ ሆኗል ምጥ ላይ ነው ያለው፤ የተያዘ የተረዘዘው ሁሉ ቀን ከሌት እዬተጫነ ህዝቡ በድህነት ተወሯል፤ ኑሮ ጎንደር ላይ ከማህል ሐገር በከፋ ሁኔታ እጅግ ውድ ነው። 

አፈር ሳይቀር ሌሊት ጉዞ ወደ ታላቋ ተንዳላቃቂ ብርሃናማዋ ትግራይ ሆኗል። ይህም አንሶ እሳት በቤንዚን ለታዘዘላት ጎንደር ይህ ዝልቅ ብቁል ቅንነት የማይሠራ ነው የሚሆነው - ዛሬ። ልጅ የላትም። ተቆርቋሪ የላትም። ጥቃቷን የሚያወጣ አንድስም እንኳን የላትም ጎንደሪት። ኢትዮጵያን የጠላት ሁሉ ክንዱ የሚያርፈው ጎንደር ላይ ነውና። ኮሶ ጠጥታ መሻር አልቻለችም ጎንደር። 40 ዓመት አርግዛ መገላገል ያልቻለች ናት ጎንደር። ጽንሱ በሆዷ ውስጥ አጥንት ሆኖ ይነስታታል። ያሰቃያታል። ይጠዘጥዛታል። 

በዕንባ አውሎ የምትገረፍ … መከረኛ ናት ጎንደር። ከባለ 6ቱ የትግራይ ሪጅን ኩርማን ዕውቅና ያልደረሳት። ካሳ ሊከፈላት ሲገባ ቁማ ለትግርይ ራት የምታበላ፤ እሷ ግን ጨለማ የከተመባት። ከቤንሻጉል ጉምዝ ከተማ በእጅጉ ያነሰች- የተረገጠች - የተጠቀጠቀች - የተጨፈለቀች - የተናቀች - የደቀቀች።  
  • ·         ጎንደር እና ጥቁር ዕጣዋ።


የጎንደር ኑሮ መከራ የተከዘነበት ነው። ስለምን? ለሚለው አቀማመጧ ምሽግ ስለሆነ። ህዝቧ ደግሞ ዜግነቱ ደግንት ስለሆነ። ማንነቱ ደግሞ ፈርሃ እግዚአብሄር በመሆኑ። ይኸው ጸጋው ጠቅሟታል ወይ ቢባል ጎንደር እንደ እኛ ሰውነት ኩነኔና ጽድቅ ስላልተሠራላት የምትጠብቀው የገነት ህልም የላትም - ጎንደር። 

ኑሯዋ ምድራዊ ብቻ ስለሆነ ንጹህ ተፈጥሯዋ ጎድሏታል። እንደ ሰው ሰማያዊውን ሐገር የምትናፍቅ ቢሆን ግን ጎንደር በእዮር አደባባይ የጎንደር ጽላት ይቀረጽላት በነበረ። የተግባር እምቤት ናትና። የመሆን ልዕልት ናት - ጎንደሪት እማ ቅኒት - መቀነቲት።

የመጣው ገዢ ሁሉ በዙር የሚቀጠቅጣት፤ እዬቆራረጠ የሚያሳንስት፤ መከረኛዋ፤ የዕንባ ጓደኛዋ ጎንደር ከዛሬ 22/23/24/ አመት ጋር እንኳን ሊነጻጻር የሚችል ምንም የሌላት ምንም ሆናለች። የእኛ ዶር. አብይ አህመድ ውስጣቸው የጤሰበትን አምክንዮ ሲገልጡ ጢሱ ሲትጎለጎል የሚታዬውም ይህን ዕውነት ስላመኑት ነው። 

የእኛ ዶር. አብይ አህመድ በዕውነት ውስጥ የበለጸገው የዕእምሮ ልቅናቸው ነፍሳቸውን እናይ ዘንድ ይለፍ አስገኝቷል። እሳቸው ያዩት በዛ ዘመን ዘመናዊ የነበረው ገብያ ዛሬ አመድ ለብሷል። በግፍ በተደራጁ የትግራይ ነፍሰበላዎች በቤንዚን ጢሷል፤ የእሳት እራት ሆኗል። ነዷል። ከተማዋ በድቀት መክኗል። ተስፋዋ በተስፋ አልባነት ተገንዟል - ዝጓልም። 

ልጆቿ 40 ዓመት ሙሉ ለስጋት፤ ለጭንቅ፤ ለመረሸን፤ ለእስራት፤ ለአካል ጉዳተኝነት የታደሉ ናቸው። ሽልማታቸው ይሄው ነው። ኢትዮጵያን በማዳኑ በኩልም እንደ ሌላው ወገናቸው የደም ግብር ከፍለዋል፤ በሁሉም የጦር ግንባር የተመሰከረላቸው ጀግኖች ናቸው ጎንደሬዎች። ግን ጎንደር ዛሬም ጨለማ፤ ነገም ጨለማ፤ ተነገወዲያም። ጎንደር ላይ በህብረት አሳሮች የዕንባ ኦርኬስተር አቋቁመው በዋይታ እዬተራጩ ይዘምራሉ፤ ጨለማዎቹ በወልዮሽ ይዳንሳሉ፤ ግጥግጡንም በሰቀቀን ጠልፈው ያስነኩታል በጭጋግ ተውጠው።
  • ·         ስለምን ጎንደር የቁርሾ መጋገሪያ ሙጎጎ ሆነች …


1.      የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የመንግሥት ቅርጽ መሠረትነት በንጉሦች ንጉሥ በዓጤ ቴወድሮስ የቀደመ፤ ሥልጡን አቮል ዕሳቤ ጎንደር ስለተባረከች። ከጥበብ በላይ ልቅና ነበርው ይህ „ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ የህልም መንፈስ“ ዛሬም ኢትዮጵያን ሊያጠፉ የሚንደፋደፉ ሁሉ የበቀሉን በትር የሚያሳርፉት ጎንደር ላይ በደቦ ነው። ለዚህም ነው የጠቢቡ ቴወድሮስ ቅኔ የታደፈነው። እገዳ የተፈረደበት። 

    በድርጅታዊ ሥራ በነፍስ ወከፍ እንዳይደመጥ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ትእዛዝ ማስተላላፉን ወጣቶች ይናገራሉ። አፓርታይድ። የጥበብ ቀንዱ ሀጫሉ ሁንዴ ጥቃት የሚያወጣ ወገን ስላለው በ2,000, 000 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር የተዋዋለውን የግዮን ኮንሰርቱ 1,000000 ተቀብሎ ስለታገደበት ተመላሽ ሆነ። 

    ነገር ግን መንፈሱን በሌላ መድረክ ዕድሉን አግኝቶ ገለጸ። ፈርጣማ ክንድ ስላለው፤ ጠቢቡ የቅኔ ዕንቡጥ ቴዲስ? ጎንደርን ያነሳ ኑሮው በሞት ውስጥ ነው። ስለምን? የኢትዮጵያዊነት አስፈሪ ግርማ ሞገስ ያለው ጥልቅ ይባቤ ስለሆነ።  

2.       የመጀመሪያው ባለ ብሩህ ራዕይ ድንቁ የጥበብ ፍልቅ ሩህሩሁ ዓጼ ፋሲል በዬጊዜው ሲባክን የነበረውን፤ ማዕከል ያልነበረውን መንግሥታዊ አስተዳደር ማዕከላዊ የንጉሦች ሥርዓተ - ህግጋትን በመሥራችነት፤ በብልጹግ ቤተ -መንግሥታዊ ኪናዊ ጥበብ ጎንደር ላይ ስላዋቀሩት ነው። ይህ የጥቁሮች የመጀመሪያው ቤተ መንግሥት ቋሚ ቦታ ሳይኖረው ከታች ከላይ ይል የነበረውን ይርጋ ያለ ነበር። 

     መንፈሱ ከሰለጠነው ዓለም ጋር የተስተካከለ፤ ተወዳዳሪ የሆነ ቤተ - መንግሥት መሠረት መሆኑ ጎንደርን ለጥቃት ዓይነ - ገብ እንድትሆን አድርጓታል። ቅርሱ የዓለም ሀበት መሆኑ፤ እንዲሁም የመጀመሪያው ጥራቱን፤ ደረጃውን የጠበቀ ቀዳማይ አፍሪካዊ የጥቁሮች ቤተ - መንግሥት መሆኑ፤ አፍሪካም በዚህ ውስጥ፤ ጥቁሮችም በዚህ ውስጥ በጥበብ ተስተጋብረዋል። ጸድቀዋል። 

    ጎንደር እጅግ በላቀ ሁኔታ ለአፍሪካዊነትም Pan-africanism ራሱ ጥንግ ድርብ የሆነ የትውፊት መሰረት ነው። ከዚህ በኋዋላ እኮ ነው የአፍሪካ አንድንት ድርጅት የተመሰረተው። መሰረቱ ግን ፋሲል ግንብ ነው። የጥቁሮች የወል ሰማይ።

3.       የነገሥታቱ፤ የልዑላኑ መሠረት መሆን። ህብራዊነት በተለይም ከኦሮሞ ማህበረስብ ጋር ያለው ጥልቅ ሥነ - ጥበባዊ የእትብት ደማማዊ ሥህን ልቅና እዚህ ጎንደር ላይ በዕሴት ለምቶ፤ አፍርቶና አጎርምቶ ይገኛል። እኔም በቅኔው ልዑል በብላቴ ጌታ ጸጋዬ ገ/ መድህን ትጋቴ መሠረቱ ይሄው ነው። ከስንት ዘመን ጠገብ የፍትጊያ ጉዞ በኋላ አሁን ላይ ያለው የመተሳሰር „የኦሮሞ ደም ደሜ ነው። በቀለ ገርባ መሪዬ ነው።

“ ዳግም ልደቱ የነበረውን የዝምታ ወይንም የድምጽ ተዕቅቦውን ጥሶ መውጣቱ ልዩ ብሥራት መሆኑ ጎንደርን የቀጥታ የጥቃቱ ዓላማ አድርጓታል። ጎንደርን ለሌላ የሳላ እጥፍ ድርብ ጥቃት አጋልጧታል። የቅማንት ጉዳይ/ እንደ ገና በሦሰት እንድተሸነሸን ሊኳንዳ ቤት መከፈቱ፤ ጎጃምና ጎንደር ላይ የፈሰሰው የነጹሓን ደም እና ሃያ ሺህ ወጣቶች በአንድ ወር ውስጥ መታሰር ብቻ ሳይሆን ሌሊት ሌሊት በገፍ የነበረው ቀብር ሁሉ ምንጩ 16/ 17ኛው መቶ ክ/ ዘመን ታሪካዊ ትውፊት ደም ተገብሮለት ብርሃን ስለወጣለት ነው። 

    የቀደምቱ የዓፄዎች በፍቅራዊነት መስህብ የሁለቱ ማህበረሰቦች የአማራና የኦሮሞ ትንሳዔው በመታወጁ ነው። ከተኖረው በደል በላይ ሌላ የቁርሾ ጦስ የፈጠረው ይሄው የሚስጢር ጣዝማ በመንጠሩ ነው። ቀደምቱን ሊሂቃንም አጀንዳ አልቦ አድርጓቸዋል ያ ታምራዊ ተጋድሎ። በሃሳብ ጉጉሱ አትራፊዎችንም ውስጣቸውን ይመረምሩ ዘንድ መክሯል። ይህ የአማራ ተጋድሎ አምክንዮ ትውልዱን በደሙ በድጋሜ የገመደ አዲስ ምዕራፍ መሆኑ ኢትዮጵያን ለሚጸየፋት ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ብቻ ሳይሆን ሻብያም ገብቶ ለማንኮር ያነሳሳው መሰረታዊ አምክንዮ ነበር። ችሏል? አልቻለም። ከሽፏል!

  • 4.     የጎንደር ቅርስ ዲታነት ከመሬት በላይ ብቻ ሳይሆን ከርሰ ምድርም አንቱነቱ ሊቅ ነው።


5.     ከዚህ መሠረታዊ የሆነ የሥልጣኔ አርክቦት ጋር የህዝቡ ህሊና ወይንም ሥነ - ልቦና በብቃትና በብልህነት የመገንባቱ ውርርስ ትውፊታዊ ዕሴት መሳጭነቱ፤ መሬት ያዬዘ የህሊና አቅም የመሆን ብልሃቱ፤ ይህን በዚህ ዘመን እንኳን የአማራ ተጋድሎ ወላዱ የጎንደር የአማራ የማንነት አብዮት ሀገራዊ ምልከታው ሆነ ልቅናውን በውል ፏ ብሎ እንዲታይ አድርጎታል - በዓለም አደባባይ። ለዚህ ነው ባልተለመደ ሁኔታ የተጋሩ ባለስልጣኖች ጎንደር ላይ ከነ አጋዚያቸው ሰሞኑን የከተሙት። ልቡን አግኝተዋል፤ እእ፤ „ገድሎ እግዚአብሄር ይምርህ“ ይለዋል የጎንደር ብሂል እንዲህ ዓይነቱን ቧልት።

6.     ለምሽግ የሆነ ቦታ ብቻ ሳይሆን ምሽጉን፤ ምሽግ ሊያደርግ የሚችል የመንፈስ ሃብታትም፤ መሃንዲስነትም፤ ሙሉዑ የጥሪት ባለቤትነት፤ ብልጹግ መሆኑ ሌላው የማይደፈር ዕውነት ነው። የግንባር - ሥጋነት ባለሟልነትን አክሎ እውነት እና ድፈርት ኪዳናዊ ትስስር በአብሮነት ውልነት መስከኑ ጎንደርን በክፉ ዓይን እንድታይ አድርጓታል - በዬዘመኑ።

7.       የማህበረሰቡ አፈጣጠር ህብራዊነት፤ የቀለሙ ጥልቀትና መስተዋድዳዊ መስተጋብሩ ጽናታዊ ህላዊነት ቅቡል መሆኑ  የዕንባ ተሸካሚ አድርጎታል - ጎንደርን። የአብሮነት መንፈሱ ትውልድ አሻጋሪነቱ ልዩ አንጸባራቂ ዘመን ጠገብ መሆኑ የጦርነት ቀጣና ድርጓታል - ጎንደርን። ጎንደር የሁሉም ቤት ናት። ነገም። 

    የተፈጠረ - ቢፈጠር፤ የተቀዬረ - ቢቀዬር ግፈኞች በፈጠሩት ምክንያት ሰላማዊዎቹን ወገኖች አቅፎ፤ ደግፎ፤ ተጋብቶ ተዋልዶ ይኖራል፤ ቂም ቋጥሮ ለነገ አያሳድርም ጎንደር ሃላፊነት የሚሰማው ሚዛናዊ የሆነ ህዝብ ነው። ግልጥነት ውስጡ ነው። ግን በማይደራደርበት - አይደራደርም፤ ደንበር ደንበር ነው። አፈርም አፍር። ማንነትም ማንነት። 

     ከኤርትራ ወገኖቹ ሲፈናቀሉ ርቆ እሰከ ኮሰዬ ድረስ በመሄድ ነበር በዬመንገዱ አንጥፎ ጎዝጉዞ በፍቅር ብሄረሰብ ሃይማኖት ሳይለይ ያስተናገደው። በዬቤቱ ከ10 ያላነሱን ወገኖቹን በፍቅር አስተናግዷል። ኤርትራውያኑ ደግሞ እንዲለቁ ሲበዬንባቸው ዕቃቸውን ሸሽጎ እዬሸጠ በውጪ ሀገር ባንክ ልኮላቸዋል። ጎንደር ትርጉም ነው። ጎንደር ሚስጢር ነው። ከዚህ ሁሉ አንድ ሰው ብቻ ነው የጎንደር ልብ ሆኖ የተገኘው ዶር. አብይ አህመድ። 

ከነዚህ መሠራታዊ፣ ማራኪና ሳቢ፤ አልፋና ኦሜጋ ዕውነታዎች ስንነሳ ጎንደር የውስጥ ሰላሟ ብቻ ሳይሆን ዳር ድንበሯም ጥሰት እንዲኖረው ተደርጋለች። ቀና ብለው የሚወጡ ልጆቿም እዬተነጠሉ፤ እዬተለቀሙ የቁርሾ ሰለባ በገፍ ሆነዋል - እዬሆኑም ነው። በዬዘመኑ ከዚህ መከራ ጎንደር አርፋ ውስጧ ሰላም አግኝቶ አያውቅም። ጎንደር ኗሪዎቿ ተዋላጆች የበርካታ በሽታዎች መደብር ሆነዋል። የውስጥ ሃዘን በባይታዋርነት ማስተናገድ የመቆም ስቅላት ነው። ይህን ነው ማስተዋል የተሳናቸው ቤተ - ተጋሩ።
  • ·         የልሳነ ሀገር አሻራ።


ጎንደር ልሳነ ሀገር መሆን መቻል የምትችለው አቅሟን የጠበቀ ዕውቅና ሲሰጣት ብቻ ነው። አዲስ አበባ እኮ ከጎንደር በኋዋላ የተፈጠረች እርሰ መዲና ናት። ለዚህም ነው ጎንደር ላይ ቋንቋ፤ ብሄረሰብ፤ የትውልድ ሥፍራ አጀንዳ ሆኖ የማያውቀው። ስለበዛ ነው „አማራ ነን“ ብለን እንድንወጣ የተገደድነው። 

ጎንደር በመንግሥት አደረጃጃት በቅርጽ ሆነ በይዘት እጅግ በሚገርም የጥበብ ብቃት፤ የምህንድስና አቅም የተሠራው የፋሲል ቤተ - መንግሥት የኢትዮጵያ የሁለመናዋ ማዕከል ነው። ስለሆነም ለጎንደር በፍጹም ሁኔታ የተለዬ የከተማ ደረጃነት ሊሰጣት ይገባል። 

አፍሪካውያን ጉባኤያቸውን ሁሉ መከተም ያለበት ጎንደር ላይ መሆን አለበት። ጥቁር ንጉሥ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ንግሥናው በብቃቱ ልክ የተገነባ ስለመሆኑ በአፈ - ታሪክ ሳይሆን በሚጨበጥ፤ በሚዳሰስ የሚታዬበት የነፍስ ማደሪያ፤ የመንፈስ ጉልላት ነው ያለው ጎንደር ላይ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የጎንደር የደብር ብርሃን ሥላሴ የአርት ልቅና ሌላው የቀደሙት የአባቶቻችን የምናብ ምጥቀትን ያሳያል፤ በዙሪያው ያሉት አግናባቱ በእንቁላል ውሃ የተገነቡ ናቸው። ይህ መቼም ከድንቅ በላይ ነው። 

ቁስቋም ማርያምንም ብንወስድ በተመሳሳይ ከአንቱ በላይ የታሪክ ማህደር ነው ፍጹም ልዩ የሆነ የትውፊት ቅኔ እናገኛለን። በዬዳ ማርያምን፤ ሊቦ - ጋፋትን፤ ደብረታቦርን፤ ደንቢያ፤ ጣና ገዳምት ቢኬድ እጹብ ድንቅ የሆኑ የትናት ኢትዮጵያዊ አሻራዎችን እናገኛለን የግራኝ መሀመድን ሳየቀር። የፈለስፋውን የዘረያቆብ፤ የጥበብ ዓይኑን የቅዱስ ያሬድን መንፈስ ሁሉ ያረፈባት ናት ጎንደር። ስለምን ጎንደር „ሰው“ ነው ማዕከሏ።

ይሄን አክብሮ የሚነሳ ትውልድ መፍጠር ያስፈልጋል። እውነት ለመናገር የቀደሙት የሠሩት ልቅና በቀጣይ 500 ዓመት እንኳን የሚታሰብ አይደለም። ዘመኑን በዕውቀት ላይ ለማያያዝ የተፈጠረው ክፍተትም የኢትዮጵያን ታላቅነት እና የማድረግ አቅም መቅኖ አጥቶ እንዲቀር ለማድረግ ነው። ለዚህ ነው ጎንደር በእጥፍ ድርብ ዒላማ የሆነችው። ከዛ ያለው የሥነ - ልቦና አቅምም በቀላል የቋንቋ ቅብብሎሽ መፍቻ አይገኝለትም።

 በዝምታው ውስጥ የላቁ ልቅናዎች በቅኔ ተጠልፈው፤ በደርባበነቱ ተመስጦ ውስጥ በድጓ ተዘምዝመው ያሉ ፍልቅ ሃቆች አሉ፤ በእርጋታው ውስጥ በጾመ ድጓ ተዋደው የሰከኑ ዲታ ትውፊቶች አሉ። ግን ቀን አጥተው አንገታቸውን ደፍተዋል። ቅስማቸው በወያኔ እና በሻብያ ተሰብሯል። ይህን ማዳን የትውልዱ ዕጣ ፋንታ ቢሆንም ማነቆ የሆኑት አቶ በርከት ስምዖን ኤርትራ ልቃ ኢትዮጵያ ደቃ ለማዬት ባላቸው ረጅም ህልም ያደረጉት ሴራ ነው። ሲያድጉ ይህን ልቅና በቂም ቋጥረው ነበር። 

የመቶ አመት ታሪክ የምትለው ኤርትራ ቢሆን በምንም መሥፈርት የቀደመ የኢትዮጵያን የዘመናት አሻራ ለመስማት የማትፈቅድ ናት። ኤርትራ በኢትዮጵያ የቀደምት የሥልጣኔ ውርሶች ላይ መቼውንም ቢሆን አታንቀላፋም። ስለ ታላቋ ኢትዮጵያ ቁሞ የሚናገር ሐዋርያዊ ተግባር ጎንደር ላይ ለምስክርነት አለ። ለዛውም በኦሮሞ እና በአማራ ማህበረሰብ የደም ህትምት የታነጸ እውነት። ይሄ አይመቻትም ለኤርትራ። „ልብ ያለው ሸብ።“

ለጎንደር የተለዬ አትኩሮት፤ ከተለዬ የከተማ ዕውቅና ጋር ቀዳሚው የትኩሮት መሠረት ሊሆን ይገባል። የዶር. አብይ አህመድ መንፈስም ሊታይ፤ ሊመረመር፤ የእኔ ሊባል የሚገባው ከዚህ ጥልቅ መንፈሳዊ የሃብት ማዕዶት ላይ ሊሆን ይገባል። ልቅናው በግልብ እና በድንገቴ ፖለቲካ ጅዋጂዊት ማድመቂያ ሊሆንም አይገባም። 

የሰከነ ልብ፤ የረጋ መንፈስ ይጠይቃል ዶር. አብይ አህመድን የአቅም ሥህነ - ነባቢት ለመተርጎም። ጎንደር ሳያነሱ፤ የሁለቱን ሃይማኖቶች ልቅና ሳያነሱ ንግግር አያደርጉም። ስለምን? በውስጣቸው ያለችው ታላቅ ሐገር ኢትዮጵያ ውበቷን ውስጣቸው ስላደረጉ። ቅብ አይደለም የእሳቸው ተመስጦ፤ ቅጅ አይደለም ጥሞናቸው፤ ተፈጥሯዊ ነው። መቻቻል ተቋማቸው ስላደረጉ ነው። መነሻ መሰረታቸውን አክብረው የእኔ ብለው ስለፈረሙበትም።
  • ·         ጎንደር እና ቅንነቷ፤ ኪሳራዋ እና የጨለማ ሽልማቷዋ።


ቀደም ብዬ እንደ ገለጽኩት ምሽግነቷ፤ ብልህነቷ በዬጊዜው ሰዎች ገዢዎች አልተመቹንም ሲሉ የሚመጡት ወደ ጎንደር ነው። ሽዌው በሽዋ አይመሽግም፤ ወይንም የጋሞ ሰው ጋሞ ጫካ ላይ አይመሽግም። አርሲውም አርሲ ላይ አይመሽግም፤ የሚተመው ሁሉም ወደ ጎንደር ነው። ጎንደር የከፋቸውን ሁሉ በቅንነት ባሰጠጋችው ልክ ተቀናቃኙ ሥልጣን ላይ የሚኖረው ዬዬወቅቱ ገዢ መደብ ደግሞ ባልወለደ አንጀቱ በፋስ አናት አናቷን ይቀጠቅጣታል። 

ጎንደሬ የተባለው ሁሉ በጥርጣሬ መታዬት ብቻ ሳይሆን፤ በተለያዬ ሁኔታ እንዲሰዋ ይደረጋል። ይህን ጥሶ የወጣ፣ ነፃነት ያገኘ፤ ባለሙሉ ዜግነት የተሰጠው፤ በክፉ ዓይን በጥርጣሬ የማይታይ የህሊና አቅም ለማግኘት ይቸግራል። ከሥሩ ነው ጎንደሬ በዬደረሰበት የሚነቀለው። ውጪ ሀገርም።

አሁን ኢህአፓ፤ ኢዲዩ፤ ኦህዲድ፤ ኢህዲህን፤ ወያኔ ሃርነት ትግራይ፤ ከፋኝ፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር፤ አብሶ ሻብያ እና ኢህአፓ ከተማ ውስጥ ብዙ አባሎች ነበሯቸው፤ የከተሙት ጎንደር ላይ ነበር። 

የትውልድ እልቀቱን ያወራረደው የጎንደር ማህጸንና አብራክ ነበር። ቀይ ሽብሩ ሆነ ነጭ ሽብሩ የሞት ግጥግጣቸው ጎንደር ላይ ነበር። የጎንደር ሰው ኢዲዩን ለማጥቃት የሚመጣውን ድርጅት ተቋቁሞ ያን ሰው ደብቆ አደራ ያወጣል። 

ኢህአፓንም ለማጥቃት የሄደውን እንዲሁ ይጠበቃል። ወያኔ ሃርነት ትግራይም ቢሆን እንዲሁ ጥቃት እንዳያገኘው ክውን አድርጎ ይይዘዋል። ኦህዲድንም እንዲሁ ደርግ ሊያጠቃው ቢሄድ ሽክፍ አድርጎ ይይዘዋል። የደርግ ሠራዊትም ቢሆን ለአሰሳ ሲሄድ በአካባቢው ካሉ ታጣቂዎች ጋር ግጭት እንዳይፈጠር ጥላ ከለለ ይሆነዋል። 

ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው። ይህን ያውቃል የጎንደር ህዝብ። አደራ በማውጣት ቃል ኪዳኑን ጎንደር ይጠብቃል። ጎንደር ከእናትም እናት ናት። ሁሉንም የደርግን ሠራዊት፤ የኢህአፓን ሠራዊት፤ የኦህዲድን ሠራዊት፤ የኢህዲህን ሠራዊት፤ የኢዲዩን ሠራዊት፤ የከፋኝን ሠራዊት፤  የኢትዮጵያን አርበኞች ግንባር ሠራዊትን፤ የወያኔ ሃርነት ትግራይን ሠራዊትን ሁሉንም ያቀፈ፤ የቀለበ፤ ጥግ ከለላ የሆነ፤ ያጽናና አይዟችሁ ያለ ቅን ህዝብ ነው ጎንደሬ። 

በፍጹም ሁኔታ ጎንደር ብልህ ማተበኛ በመሆን ውስጥ የኖረ ሥነ - ግጥም ነው። አንዱ ድርጅት ሌላውን ለመበቀል በሚያደርገው ሂደት የሚጨፈጨፈው ደግሞ የጎንደር ህዝብ ነው። መሬቱ - ጥሪቱ - ትውፊቱ - የሚወረሰው ደግሞ ያው ጎንደር ነው። በጦርነትም የሚደቀው ያው እሱ ነው። 

በደርግ ዘመን ወያኔ ሃርነት ትግራይ ለሰሞናት በሚቆጣጠራቸው ቦታዎች የመጀመሪያ ተግባሩ ት/ቤቶችን ማቃጠል፤ ክሊኒኮችን ማንደድ ነበር። ድልድዮችን መስበር፤ ዙሮ የሚመሽገው ደግሞ ጎንደር ላይ ነው። ስንቁን የሚዘርፈውም የካቲት ላይ ከጎንደር ገበሬ ነው። 

የፈረሱት ት/ ቤቶች ሆኑ ክሊኒኮች ከወያኔ ወረራ በኋዋላም ቦታዎች ጠፍ ሆነው ይቀራሉ። ት/ቤት ሆነ ክሊኒክ እንደገና አይሰራባቸውም። ዛሬም የሚቃጠለው ጎንደር ነው። በግራ በቀኝ የሁሉም መከራ ቡፌ፤ እንደ ድፎ ዳቦ በላይ በታች ሲነድበት፤ ሲቀቀል የኖረ ህዝብ ኑሮ ነው በጎንደር።

በዚህ ውስጥ የዕእምሮ ሰላም ማጣት ህሊና ተረጋጋቶ ማሰብ፣ መመራመር መፍጠር አይችልም ማለት ነው። ተማሪዎች ተረጋግተው መማርም አይቻላቸውም። ስለሆነም ጎንደር ውስጥ የሚያድግ ልጅ በምን ያህል ሰቆቃ ውስጥ እንደሚያድግ ዶር. አብይ አህመድ በዕምሮ ፈጠራ ላይ የተለዬ የምርምር ተግባር እዬከወኑ ስለሆነ ሚዛኑን ማስላት ይሳነዎታል ብዬ አላስብም። 

ስንት ሳይንቲስት፤ ስንት ፈላስፋ፤ ስንት ተማራማሪ፤ ስንት ንጥር የጥበብ ሰው ሊሆኑ የሚችሉ እትብቶቿን ከ40 ዓመት በላይ በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት፤ ዛሬም ባላባራው ጦርነት ጎንደር ልጆቿን፤ ተስፋዎቿን አጥታለች። እኔ አባባ በይሸፍቱ ትምህርቴን እቀጥል ነበር። የት እደርስ ነበር። አይደለም ትናንት ዛሬም? ይህም ሆኖ አሁንም የውስጥ ሰላሟ ታውኮ የሁሉንም የመከራ ዓይነት በማስተናገድ ላይ ትገኛለች። ኑዛዜ ላይ ናት ጎንደር። ሰኔል ተዘጋጅቶ ቹቻ የረጠበላት ናት ጎንደር።
  • ·         ጎንደር ቀንበር።


ነፃነትን እናስገኛለን ብለው ወደ ጎንደር የሚተሙት ታጋዮች የተፈጠሩበት እትብት በሰላም ይኖራል። ከዛ ያለው ትውልድም በተረጋጋ ሁኔታ ይማራል። ዛሬ እንዲህ አቅም ያለው የሚታይ ሰው ማዬት ያልተቻለውም ለዚህ ነው። ከዚህ ላይ የትውልድ እርሾ አልቦሽነት የጎንደር ሊሂቃን መነሳትን አይፈቅዱም። 

ወያኔ ጎንደር የተቆጣጠረው በማትሪክ ሰሞን ነበር። ተማሪዎች መፈተን አልቻሉም ነበር። ታናሽ ወንድሜ ተፈታኛ ነበር። የደረጃ ተማሪ ነበር - ከሙሉ ሥነ ምግባር ጋር። አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ ክልሉን ጥሶ የአቶ አባይ ወልዱ ጥጋብ ጦርነት የከፈተው በህጻነት ላይ የማትሪክ ሰሞናት ነው። ይህን ማድመጥ አይፈቅዱም የጎንደር ሊሂቃን፤ ከዚህ መነሳትንም አይወዱትም። 

ሽዌው፣ ወለጌው፣ አርሲው፣ ወደ ጎንደር መጥቶ ሲመሽግ እዛ ያለው ህዝቡም ሰላሙ ይጠበቃለታል፤ በወቅቱ ካሉ ገዢዎች ጋርም ቅራኔ አይገባም። ተማሪዎችም ተረጋግተው ይማራሉ። ኑሮውን በተለመደው ሁኔታ ይመራል። ይዳራል፤ ይኳላል፤ ይወልዳል ይከብዳል። የጦርነት ጩኸት አይረብሻቸውም። 

የሥነ - ልቦና ጥቃት አይሰነዘርባቸውም። ስለሆነም በሁሉም ቦታ ለነገ እርሾ ይኖራል። አሁን የሚታዬው አቅም የዛ ዘመን የውስጥ ሰላም ሰብል ነው። ውጪ ሄዶ የሚማረው ውጪ ይሄዳል፤ ሀገር ውስጥ የሚማረውም እንዲሁ። ጎንደር ግን በጦርነት 40 ዓመት ሙሉ ታቃስታላች፤ ልጆቿን ለእርድ ታዘጋጃለች - አሁንም። ቀለብ ትሆናለች የሌሎች አካባቢ ልጆች ግን አሁንም ይማራሉ። 

ጎንደር በቅንነት ያለማቋረጥ መንፈስ ታዋጣለች። ይህም ሆኖ የ27 ዓመቱ ልግጫ እንደዛ ያን ሁሉ ገመናን ተሸክሞ የኖረ አማራ በጠላትነት ተፈርጆ ዘሩ ጠፋ፤ ተፈናቀለ፤ ተባረረ። ይህ በዬትኛው የፍትህ አደባባይ ይሆን መፍትሄ የሚያገኘው? እኔ እንደማስበው ከሁሉ በላይ አቦ አባዱላ ገመዳ የዛሬውን ዝምታ የሰበረ ንግግር አድርገዋል፤ በኢህአፓው ዝንጣፌ በብአህዴን 37ኛ ጉባኤ ላይ። 

„ኦህዲድን ከዬት መጣህ? ምንድነው ሃይማኖትህ፤ የቱ ነው ብሄረሰብህ ብሎ የአርማጭሆ፤ የበለሳ፤ የላሊበላ የአማራ ህዝብ አልጠዬቀውም፤ እንዲያውም ከእኛ የሚጠበቀውን ንገሩን እንርዳችሁ ብሎ ከጎናችን ተሰለፈ“ ብለዋል ነግረውናል። ተከድኖ የኖረ ዕውነቱን አፍርጠው ተናግረዋል።
  • ·         ዓይነ ጥላው የተገፈፈ የሃቅ መሰረት።


https://www.youtube.com/watch?v=OjNinT_zF-0 የኢህዴን/ብአዴን 37 ዓመትን ማክበር ማለት ለኦህዴድ የራሱን በዓል እንደማክበር ነው ሲሉ የኦህዴድ መስራች ታጋይ አባ ዱላ ገመዳ ተናገሩ“ ይህን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በኦሮምኛ አጀንዳ አድርገው የቁቤን ትውልድ የሚያሰተመሩበት ተቋም ሊኖራቸው ይገባል።

 ዛሬ ተፎካካሪ ብቻ ሳይሆን አቅም ሆኖ የወጣው ድርጅታቸው ኦህዲድ ነፍሱ መሠረቱ ማን እንደሆነ፤ የትኛው የመንፈስ አቅሙ፤ ስንቁ ትጥቁ እንደሆነ ይህን ዕውነት ደፍረው ለልጆቻቸው፤ ለልጅ ልጆቸው ማስተማር ይገባቸዋል። በህይወት መቆዬታቸው ትርጉሙ ይህ ነው። 

ስለ ጎንደር ቁመው ሊሟገቱለት ይገባል። ስለወሎም ቁመው ሊፋለሙለት ይገባል። ስለ አማራ ህዝብ ቅንነት እና ኢትዮጵያዊነት፤ ቤተሰባዊነት ቀበቷቸውን በድርብ ታጥቀው ጥቃቱን ሁሉ ሊመክቱለት ይገባል። ኪዳን ማለት ይህ ነው። ውል ማለት ይሄ ነው። ከራስ በላይ ራሱን ለሰጠ ህዝብ ተቆርቋሪነቱ በተግባር በልጽጎ እኔ በግሌ ማዬትን ከመቼውም ጊዜ በላይ ይናፍቀኛል። በተሳሳተ ዶክትሬን ከ2.5 ሚሊዮን ህዝብ በላይ አማራ ያለቀበት የአምክንዮ እንብርት ፍርጥርጥ ብሎ መልክ መያዝ አለበት። 

ዛሬ በቱማታ ላይሆን ይችላል። ግን በህሊና ሰሌዳ መታቀድ ይኖርበታል። ከውለታም በላይ ነው ትውልድን ማትረፍ እሱ እዬሞተ ሌለው የእውቀት፤ የኑሮ መሰረቱን  አደራጅቶና ጠብቆ እንዲኖር መፍቀድ። 

ይህን የሰማይ መለእክት እንኳን የማይፈጽሙት ገድል ነው። መላእክታን ሳይመቻቸው ሲቀር እነሱ ቁጡዎች ናቸው። የዚህ ጥልቅ ህዝብ ጥልቅ ፍቅር ከዚህ ሁሉ የጀምላ ጥቃት በዋላ እንኳን አሁንም ጎንደር „የኦሮሞ ደም ደሜ ነው በቀለ ገርባ መሪዬ ነው የጋንቤላው ደም ደሜ ነው“ ማለቱ ብቻ ሳይሆን በአማራነት ደም ውስጥ ከጎጃም ጋር እራሱን ገብሮበታል። 

ከዚህ ዕውነት ጋር አቦ አባ ዱላ ገመዳ ሊገናኙ ይገባል። እውነት እውነት የሚሆነው ተግባር ሲታጠቅ ብቻ ነው። ከውሳጣቸው ሊገባ ይገባል። ሰው መሆን ማለት በሆነው ውስጥ ሆኖ መገኘት ማለት ነው። ይህ ለአቦ አባ ዱላ ገመዳ የምሰጣቸው የትውልዳዊ ድርሻዬ ቁራሽ ሳይሆን የህሊናዬ ጭማቂ የቤት ሥራ ነው። አማራን በሚመለከት እሳቸውን በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ነው እያንዳንዷን ድርጊታቸውን እምሰፍረው። ግዙፍነትን በማድረግ ግዙፍነት። ግዙፍነትን በመሆን ግዙፍነት። አሁን ወደ አብያዊ ጉዳዬ …
  • ·         ድ ለሆድ።


የማከብረዎት ዶር አብይ አህመድ አንድ ተጨባጭ በምሳሌ ልንገረዎት፤ ከልበዎት አንደሚያዳምጡኝ ተስፋ በማድረግ፤

አንዲት የጎንደር እናት ባለቤቷ ኢድዩ፤ ልጇ አንዱ ኢህአፓ፤ አንዱ የደርግ ወታደር፤ የመጨረሻዋ ደግሞ የደረግ ሰራተኛ ሊሆኑ ይቻላሉ። በዚህ ሁሉ ዘመኗ ዕንባ ነው ስንቁ። በእናቴ ውስጥ የጎንደርን ማህጸን መቃኘት ይችላሉ ብዬ አስባለሁ።
ወላጅ እናቴ ባለቤቷ የሁመራ አራሽ ስለነበሩ አበባ ሲሸፍቱ የኢዲዩ ቤተሰብ ተብላ በርሃ እዬበላት ያፈራቸው ሃብቷ የገዛችው ቦታ ሁሉ ተወረሰባት። 

ባይገርመዎት በዛ ዘመን የባህርዛፍ ተክል ፍል ተፈልቶ የሚለማበት በገንዘባቸው የገዙት ቦታ ሁሉ ነበራቸው እዛው ጎንደር ውስጥ። ሃሳባቸው ጎንደር እንደ ሁመራ በራሃማናት ሊያጠቃት ይችላል የሚል ትንበያ ነበራቸው።በዛውም ውበቷንም ለመጠበቅ ጎላ ብሎ ከወጣ ኮረብታ ቆብ አስጥል ከሚባል ቦታ ለአንገርብ ትይዩ በሆነ ቦታ ነበር የሚያለሙት። 

ልጅ እያለሁ በሥሜ ሁሉ የተተከለ ባህርዛፍ ነበር። አባባ ብልህ ነበሩ ሰሊጥ ያመርታሉ፤ ዘይት ማውጫም ቤት ውስጥ ነበራቸው። ነገር ግን አባባ ኢዲዩ ሲሆኑ ሁሉም ተወረሰ። በዚህ ሂደት አናቴ ልጆቿን ለማሳደግ ከፍ ያለ ችግር ገጠማት። ሁላችንም ትናንሾች ነበርን። ከእህቶቼና ከወንድሞቼ ታላቅ እኔ ነበርኩኝ። 

ስለሆነም ገና በውል ወደ ታዳጊ ወጣት ሳልሸጋገር ነው ጎብጬ በሃላፊነት ብዛት ያደኩት። አሁን እኔ የታዳጊ ወጣትነት፤ የወጣትነት ታሪክ ልምድም ሆነ ተመክሮ የለኝም። ምንም እማውቀው ነገር የለኝም። እራሴን ቀጥቼ ከሁሉም ነገር በጣም ርቄ የምኖረውም በዚህ ምክንያት ነው። 

ሁሉ ነገር ያስፈራኛል - አልደፍረውም። እኔ እና ታዳጊ ወጣትነት ሆነ ወጣትነት ተላልፈናል። አላወቀውም ታዳጊ ወጣትነቴን ሆነ ወጣትነቴን ምን ስሜት እንደ ነበረው እራሱ አላውቀውም። ደግመን ላንገናኝም ተማምለናል። ሳያውቀኝ ሳላውቀው ተላለፍን - ተረሳሳን። የሚያሳዝነው እህቶቼም ይህን የእኔን መንገድ ነው የተከተሉት። ተጽዕኖ አሳደርኩባቸው።

ለሥራ ስደርስ ትምህርት መቀጠሉን ትቼ ለእህቶቼ በአፋጣኝ መድረስ ነበረብኝ። ጎበዝ የደረጃ ተማሪ ነበርኩኝ። የባይወሎጂና የኬሚስትሪ 100 ነበር ማርኬ። ባዛን ጊዜ ኢንሳይኮሎፖዲያን በአማርኛ መተርጎም ጀምሬው ነበር። በትምህርት የመቀጠሉን ዕድሉን ትቼ ሥራ ስይዝ ከነበረኝ ንቃት፤ ቅልጥፍና፤ ሥልጡንነት፤ ሥራ - መውደድ ጋር ተያይዞ እድገቴ ባልተጠበቀ ሁኔታ እጅግ ፈጣን ነበር። የኢሰፓ ቋሚ ሠራተኛ ሆንኩኝ። ኢሠፓ ሲወድቅ አሁንም እናቴ ተጠቂ ሆነች። 

ቤት አልነበራትም ሜዳ ላይ ነበር የተወረወረችው። እህቶቼ ታሰሩ። 10 ዓመት ሙሉ እህቶቼ ትምህርታቸውን ትተው ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት ይባክኑ ነበር። ዜሮ አምስት ሳንቲም አልነበራቸውም። ኑሯቸውን ለማሸነፍ እንኳን ጊዜ አጡ። ከጫካ ስመለስ ምህረት እናቴ ጠይቃ ስገባ ደግሞ ሌላ ዲል ያለ ፈተና ደግሞ ጠበቃቸው። ምህረት ተጠይቆ ከገባሁ በኋዋላ ነበር እኔ የታሰርኩት። 

እስር ቤት ውስጥ ውስጥ የነበረውን ማንሳቱ ተገቢ አይመሰለኝም። ምን አልባት ከኖርኩ አንድ ቀን አምገልጠው ነገር ይኖረኛል። ብቻ ይህ በዓለም የሌለ ጥቁር ታሪክ ነው። ምህረት ምህረት ነው። የሆነ ሆኖ ተጨማሪ ዕዳ ሆንኩባቸው። 

የእህቶቼ ጮርቃ ጭንቅላት በሰቀቀን ተወልዶ - አደገ። መጀመሪያ በወላጅ አባታቸው፤ በኋላም እንደ እናት አባትም ሆና ባሳደገቻቸው በእህታቸው። እናቴ ልግስና ስለምታበዛ፤ ሆድም ይበሳት ስለነበር ሃላፊነቱ በእኔ ላይ የተጫነ ነበር። አሁን ደግሞ እናቴ ትኑር አትኑር አላውቅም። እሷም እኔ ልኑር አልኑር አታወቅም። 

ሃሳብ መግለጽ በኢትዮጵያ የወንጀሎች ቁንጮ በመሆኑ ምክንያት። በስጋት እንድትኖር አልፈልግም። ቢያንስ ሰቀቀን ትርፍ እንዲሆናት አልሻም። ሟች ወታደርም ልጅም አላት እምዬዋ። ያ ሀዘን ማህጸኗን ያሳረረው ይበቃታል። ይህም ሆኖ በጎንደር ዳመና ውስጥ እሷም የስጋት ቤተኛ ናት። ሁልጊዜ በባሩድ ጤስ መኖሯ ጎንደር የእሷንም ነፍስ ይነስታትል። ዘመኗ ሁሉ በሃዘን፤ በዋይታ፤ በመከፋት ድባብ የተለሰነ ሆነ። በጭንቅ ያማጠ። ችግሯ ቢገባኝም ግን እኔ ሃሳቤን ከመግለጽ መታቀብን አልፈቀድኩላትም። ፈቃዷን ልፈጽም አልቻልኩም። ይህም ለእኔ ከፈቃድ ውጪ መሆን ከባድ ነው።

ደፍሬ ወጥቼ ለመናገር ግልጽና ቀጥተኛ የሆነው ተፈጥሮዬ ያስገድደኛል። የተፈጥርኩትም ለዚህ ነው። ሳላውቀው ነበር ፖለቲካ ውስጥ ተጠልፌ የገባሁት። ሰምጬ ቀረሁ። እኔ በሰው ተፈጥሯዊ ባህሪ ላይ መመራመር ነበር የምፈልገው። አሁን ይህቺ ምስኪን እናት መቼ ነው ሰላሟ የሚመጣላት? በህይወት ካለች። 

ከእኔ ጋር የምትሰቀውስ መቼ ነው ቢያንስ በስልክ? እህቶቼስ የውስጣቸው ሰላም የሚሰፍንላቸው መቼ ነው? ወደ ኑሯቸውስ የሚመለሱት እንዴት ይሁን? በአባታቸው፤ በእህታቸው፤ በወታደር ወንድማቸው ሞት የቅድሚያ ተጠቂዎች ናቸው። የትውልዱም አካል ናቸው። እንዲህ ናት የጎንደር እናት። አንዲህም ነው የጎንደር ቤተሰብ። በማያባራ የዕንባ ዶፍ እድሜ ልክ መማቀቅ። የጭንቅ ረግረግ ነጠላ የለበሰች ናት ጎንደር። የስጋት ሙሉወርድ በድርብ ቹቻ የታጠቀች ናት ጎንደር።

የሚገርመዎት ስደተኛ ካንፕ ውስጥ ስኖር 20 መጽሐፍትን ጉልበቴ ላይ አስደግፌ በእጄ ጻፍኩኝ። ችዬ 7ቱን አሳተምኩኝ። የትውልዱ ነገር ስለሚጨንቀኝ በዛ ዙሪያ ለምክር አገልግሎት የተሠሩ እጅግ ጠቃሚ መጸሐፍት ናቸው። የልጆችም የአዋቂዎችም። እነሱን እንኳን የመሸጥ ነፃነት እዚህ በነፃ ሐገር የለኝም። ጎንደሬነቴ/ አማራነቴ በፈጠረው ቀውስ ምክንያት እንዲሁም የፖለቲካ ማንፌስቶ ቤተኛ ባለመሆኔ። የጾታውም ይታከልበት። የመንፈስ ሃብቶቼ ተዘግቶባቸዋል። ይህ ለእኔ ዐውደ-ጽሑፋዊ መድልዎ ነው (contextual Discrimination) ነው። 

እኔ ለእማማ ጎንደር ብርቋ ልጇዋ መሆኔን አሳምሬ አውቃለሁ። በቅንጣት የሥነ - ምግባር ብክለት እትብቴን አሳፍሬያት አላውቅም። የትም ቦታ በዬትኛውም ሁኔታ የጎንደር ልጅ በዛ ሰቀቀን ውስጥ አልፎም፤ ያን ሁሉ መከራ ተሸክሞ አድጎም፤ እስራቱንም በአይነት ተቀብሎ፤ ስደት እዬገረፈውም አቅሙ እስረኛ ነው ለዛውም አንስት ጽኑ ሴት። ዕወቀቱ እስረኛ ነው። የማድረግ ችሎታው በእሾኽ የታጠረ ነው። ስለምን? ጎንደሬነት ግማድ ነው፤ ጎንደሬነት ቀራንዮ ነው፤ ጎንደሬነት ጎለጎታ ነው በዚህ ላይ ወጥ አማራነት ደግሞ የድርብ ጥቃት ሰለባ ነው።
   
ጎንደሬዋ እናት የወለደችው ልጅ በስደት ይህን መሰል ተደራቢ ግለትና አድሎ ስትሰማ ምን ትላለች? ውስጧ አንዴት በሃዘን ይርመጠመጣል? እንዴትስ ከእሳት እንደገባ ብላስቲክ ማህጸኗ ኩምትር ይል? ጎንደር እራሷ የመጀመሪያዋ ሴት ጸሐፊ ልጇዋ ስታዝን እንዴትስ ከምር ይከፋት? እንዴትስ ሰቅሰቅ ብላ ታለቅስ? በፍጹም ሁኔታ ግብረ ምላሹ ረቂቅ ነው። ምን ዓይነት ነጻነት ትጠብቅ የጎንደር እናት? እንዴትስ ያለ መሪ ትጠብቅ? ጎንደርም እሰከ እትብቶቿ እስረኛ ናት በዬትም ቦታ በዬትም ሁኔታ። 

በዬትኛው ዘመን ፍቺ ሊያገኝ እንደሚችል መገመት ይቸግራል። ስለዚህ ይህን መሰል ከመሰረቱ መጠጊያ ያጣ የወገን ሰቆቃ፤ የሚመስጥ የትውልድ ፍዳ፤ አብሶ የጎንደርን ከሦስት ትውልድ በላይ ያሸማቀቀ የእንባ ዋናተኛ እናትን የሀዘን ስሜት የእኔ ብሎ፤ ከውስጡ ሆኖ ባለቤት ሊሆን የሚችል አይደለም ሰው ህልም እንኳን በሌለኝ ሰዓት ነው የእርስዎን ንግግር ያገኘሁት። ደስታ ቀላል ነው። 

ሙሉ ዕድሜዬን በውስጤ አምቄ የኖርኩት የፈውስ ቀን ነበር ብለዎት ይሻለኛል። ተቆርቋሪነት ቃሉ ቀላል ይመስላል። ትውልድን ግን ከሥነ - ልቦና ጥቃት ታድጎ ተስፋ አምራች የመንፈስ መስኖ ነው። ገነት። ኤዶም። ንግግርዎት ጤናአዳም ነበር። ተስፋ ነበር። ነገ ነበር። ውስጥወት የውስጥን ቁስለት እንዲሽር በፈቀዳኝነትና በፍጹም የመቆርቆር ህሊና ሸለሙን። ውስጠዎትን በስውር የተሰበረውን መንፈስ ወጌሻ እንዲሆን በልግስና ሰጡን። ወጌሻነቱ ለዛውም የነባቢት - የሥነ ልቦና። 

ነፍሴ እነሆ ተመለሰች - ሐሤትም አዋዋለች። እውነት ለመናገር ከጎጃም የአማራ ወጣቶች ያገኘሁትን ብርታት እና ጥንካሬ ያህል ንግግርዎት በልግስና ተስፋን በገፍ መግቦኛል። ዶር. አብይ አህመድ እርስዎም እንደሚያውቁት የሰው ልጅ በመጠጥና በውሃ አይኖርም። ለመንፈሱ ልማት የቅንነት መስኖ ያስፈልገዋል። አይዟህ/ አይዞሽ መዳህኒት - መድህንም ነው ለዛውም ለስደተኛ አንስት እህት። ረቂቅ ነው ትርፉ። ይባረኩ። ይኑሩልን።
·         ፍዳ ዙረህ እቀፈኝ ያለው የዐለም ባንክ ብድር የወያኔ ሃርነት የልግጫ መሰልቀጫ። ምርኩዝ። 

§  በውሃ ጥም፣ በመብራት አቅርቦት እጦት፣ በበቀል እዬተፈጨ ያለ ምስኪን ህዝብ … በዕዳ ተሠራ ስለተባለው የልግጫ ፍጥጫ … 
„ከወራት ወዲህ የውሃ አቅርቦት ችግራችን ተቀርፏል፡-የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች“
ነገረ ጎንደር በዕዳ ተውጣ ስትማቅቅ ትግራይ የውጭ እርዳታ በሙሉ ማለት እስኪቻል ድረስ በእርዳታ ትጥለቀለቃለች፤ ያልተሰራበት በጀት ተብሎም ፈሰሱ በዓይነት ይጎርፍላታል። ተጎድታለች ብሎም ክልሎች እጃቸውን በልግስና ይዘረጉላታል። በጌታው በረከት ስምኦን፤ በታጋሩ አንብርት በአቶ አለምነህ መኮንን። ግን እስከ መቼ?
§  ቁሞ ቀሩ የአዘዞ መናህሪያ ፤


„በ86 ሚሊዮን ብር የተገነባው የአዘዞ መናኽሪያ ወደ ስራ መግባት እንዳልቻለ ከወራት በፊት በጣቢያችን መዘገቡ ይታወሳል፡፡አሁን የሚገኝበትን ሁኔታ ቃኝቷል፡፡“
§  መብራት ውሃ የሌለበት፤ ተስፋ የመከነበት፤ አታለዩ የወያኔ ሃርነት ትግራይ የበቀል ቁርሾ ማወራረጃ ፕሮጀክት።

„በጎንደር ከተማ 138 ፕሮጀክቶች በኢንዳስትሪው ዘርፍ መሬት ተረክበው በተለያዩ የግንባታ ሂደት ላይ ናቸው፡፡“

 ድንቄም የኢንደስትሪ ዘርፍ ያውም ጎንደር ላይ¡ አዬ ቀለድ እና ማላገጥ ትግራይ ላይ ዝንጥ ብለው ፋብሪካዎች በጣና ኤሌትሪክ መልስና ግጥጥግጥ ሲያደርጉ የጎንደር ባለሃብቶች ደግሞ በደረቅ መሬት የታደላቸውን የአሞሌ መላሾ ይመልሳሉ። ውሃና ኤሌትሪክ አልቦሽ ለቁጥር፤ ለዳታ …. የዕብለት ፍጥጫ -  በርግጫ የወያኔ ሃርነት ትግራይ የቧልት ጨዋታ።

·         እንደ መከወኛ … ተመሰገን ስለው፤

የመምራት አቅማዊ ጥበብ ለጠራቸው - ባተሌ፤ ዕውነት ለሳበችው - ሳተና፤ ቅንነት ለአጨችው - ፍጡር፤ ውሳኔ ለተመኘችው -ሰብዕና፤ ነገ ጥግ ለተገኘለት - ተፈጥሮ፤ ትውፊቱን ላከበረ - ተመስጦ፤ የአጽናኝነትን ደቀመዝሙርነትን ለተቀበለ - ነፍስ፤ አደራ አንጎሉ ለሆነችው - ትንታግ፤ የውስጥ ቀለሙ „ሰውን“ ማዕከሉ ላደረገ - የእኔ፤ ጥላቻን ለተጸዬፈ - ደግ፤ ምስጋናም ያንሰዋል። ሌላ አቅም ስሌለኝ አመስግናለሁ፤ እግዚአብሄር ይስጥልኝን በትሁት ቃና ልኬአለሁ ለዶር. አብይ አህመድ። ይቀጥላል ….

 

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።

ትዕግስታችሁ፤ ተደሟችሁ ቁሞ አስተምሮኛልና ዝቅ ብዬ አንባቢዎቼን አመስግናችሁዋለሁ። ኑሩልኝ የኔዎቹ።



እግዚአብሄር ይስጥልኝ። መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።