የቅኔው ዕንቡጥ ቴወድሮስ ካሳሁን፤
የቅኔው ዕንቡጥ ቴወድሮስ ካሳሁን
ስለእኛ በጣና ዘገሊላ ፍቅራዊነትን
ተሰናዳ ሊመግበን።
ከሥርጉተ - ሥላሴ 13.01.2018 (ከጭምቷ - ሲዊዘርላንድ)
„ጥበብ በጎዳና ትጮኻለች፤ በአደባባይ ድምፆዋን ከፍ ታደርጋለች፤ በአደባባይ ትጣራለች፤ በከተማይቱ መግቢያ በር ቃልን ትናገራለች። እናንተ አላዋቂዎች፣ እስከ መቼ አላዋቂነትን ትውዳላችሁ? ፌዘኞችም ፌዝን ይፍቅዳሉ? ሰነፎችም ዕወቅትን ይጥላሉ?„ (መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፩ ከቁጥር ፳ እስከ ፳፪)
· መነሻ
ግዮን ላይ የንጉሦች ንጉሥን የታሪክ ቁንጮነት፤ „የፍቅር እስከ መቃብርን“ ቃናዊ እጬጌነት፤ የኢትዮጵያን ቀንዲልነት አይደመጥ ነው ትግሉ። ስንት ጠፍጣፋ ጉድ ይሰማል።
„ቴዎድሮስ ካሳሁንን ምን ነካው? ተው ተው! ፈጥነህ ውጣ! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን)“
· ምች።
አዳሜ ከፍቅረኛው/ ከትዳር ጓደኛው ጋር እንዲሁም ከልጁ ጋር አዘውትሮ ሃኒሙኑን ይከሰክሳል፤ የቤተሰቡን ሆነ የራሱን ሠርግ ቅብጥና ቅልጥ አድርጎ ደግሶ ይፍነሸነሻል፤ የልጁን፤ የራሱን ልደት አሳምሮ ይዋብበታል። የልጄ ምረቃት፤ የጓደኛዬ ዊዲንግ ሻውር፤ የመልስና የቅልቅል ልብስ ምርጫ ወዘተ ወዘተ … ይህ መልካም ሆኖ ሳለ የራስን ደስታ በታቀደና በተደራጀ ሁኔታ እዬኮመኮሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ ግን የፍቅር መንገድ „ሀ“ ሲባል፤ የሳቅ ዕለት አህዱ ሲባል የሐዋርያቱ ቅናዊ መስመር በቅናት ሲያብጠለጥሉት ይታያሉ። ለዚህም ነው አንድ ጊዜ ለማዋያን ሌላ ጊዜ ቴወድሮሳውያን/ የቴዲ ኢትዮጵያ እዬተባለ በፈረቃ የእንቅፋት ኢንደስትሪ የተከፈተው።
· የቅንነት ጣዝማ።
የእግዚአብሄርን ፍቅር ለወደዱ፤ ለፈቀዱና ለሚናፍቁት ግን ከቶውንም ባልዛለ ቅንነት የህዝብን ደህንነት ብችሎት ለመጠበቅ የሚያስላቸውን አስተዋይነት ተስጥቷቸዋል። ጥበባቸው በማድረግ ክህሎት አስደግፈው መኽራቸውን በፍቅር ማሳ፤ በፅኑ ትእግስት ይሰበስባሉ። ደግሞም ያሸነፋሉ። ዓመት ይዞ እስከ ዓመት ከሚሠራ የሚዲያ ተግባር ይልቅ የቅኖች አንዲት ዘላላ ስንኝ የሃዘን ማስታገሻ ፤ የሰቀቀን መፈወሻ ናት፤ የተስፋ ስንቅና ትጥቅም። „ጡዋት ሁልጊዜ ታርካህ፤ በፍቅር ሁልጊዜ ጥገብ“
(ምሳሌ ምዕራፍ ፭ ቁጥር ፲፱)
· ስንጥቅ፤
ስንጥቅነት የምቀኝነት ሌላው መለያው ነው። ነዳላነትም እንዲሁ። ለፍቅር መንገድ አቃቂር ማውጣትን ሥራዬ ብሎ ለያዘ ሳጥናላዊነት የልቡ መዘወሪያ ቅናት ነው። ትህትናን ገፍትረን፤ ሳቅን አልይህ ብለን፤ ሰናይን አኩርፈን፤ ቅንነትን በልምጭ ገርፍን፤ ፍቅርን ሰግተን፤ በኢጎ ተጠምቀን እስከ መቼ? የሚገርመው ጀርመኖች „ታውሽን ኮንሰርት“ የሚሉት አንድ ጣዕም ያለው የሙዚቃ ዝግጅት በዬዓመቱ አላቸው። ዘጠኝ ወይንም አስር ሊሆኑ ይችላሉ ሙዚቀኞች። እያንዳቸው ከያንያን ቀን አላቸው። በዛ ቀናቸው አባላቱ በሙሉ የዛን የባለቀን ከያኒ ሙዚቀኛ የመረጡትን ክሊፕ ይዘው ያቀርባሉ። ይህ ማለት ለምሳሌ የቴዲን የሙዚቃ ሥራ ማቅረቢያ ቀን „የቴዲ ቀን“ ይባላል። ስለሆነም በዚህ ቀን ጥበበኛው ሻንበል፤ ጥበበኛው ይሁኔ፤ ጥበበኝት አምሳል የቡድኑ አባል ከሆኑ የመረጡትን ከቴዲ ስብስብ አንዱን ይዘው ይቀርባሉ። ይህን የሚከውኑት ደቡብ አፍሪካ ላይ ሆነው ነው። እዛው እዬኖሮ እዛው እሠሩ። በዛን ዕለት ከፕሮግራሙ በኋዋላ የባለቀኑ የህይወት ታሪክ ሂደት በተጨማሪ ይቀርባል። በዚህ መልክ ረዘም ላለ ሳምንታት ይቀጥላል። በመጨረሻ ዲቢዲ ሆኖ ይወጣል። ሥልጣኔ ማለት ይሄ ነው። ኢጎ የሌለበት። ሌላው በውስጡ አድርጎ ሲጠበብት የክሊፑ ባለቤት በዕንባ እዬተራጨ ነው የሚያዳምጠው። በሥጋ የተለዬውን የዋርካውን ዬይርጋ ዱባላ ማዕዛ ከዘመኑ ጋር አጣጠመ ተብሎ ይህ ቅኔ ተወቅሷል። ይሄ ከያኒ ትውልድ በሙሉ ስጦታችን ሊለው ሲገባ ቀደምትነትን አስታዋሽ በመሆኑ እንደ ድክመት ተቆጥሮ በአደባባይ ተሂሷል። በወል ታግለው … ታግለው እንከን ማውጣት ሲያቅታቸው፤ ይህን መሰል የነፈሰበት ሂደትን ተከትለው አንድ ሰሞን ሲወቁት ነበር። አሁን ደግሞ ሌሎች በፈረቃ ተነሱበት።
ዶር አብይ አህመድ እንዲህ ዓይነቱን ጉድ እንዲህ ይገልጹታል …
„ዛሬ ልናገር የምፈልገው ሃሳብ በቆሎ በሳይንስ ከጤፍ ገዘፍ ትላለች፤ ወፍራም ናት፤ እረዘምም ትላለች፤ እና ጤፍን ወደ ታች እያዬች አሁን ሰው በከንቱ ይደክማል እንጂ ከጤፍ ማህጸን እንዴት ዱቄት ይወጣል ብሎ ይደክማል ትላለች። ያው ኢጎ እና አብሪት ዕወቀት በሌለበት ሁሉ ስላለ ማለት ነው።“ አይከፈልበት የመልካም ወገኖችን መንፈስን መጠበቅ። በቅናት ሪሚጦ ተረምጦ ለነገሩ እንዴት የፍቅር ጉዞ ይደምጥ … ቅንነት በዚህም በዚያም በእሾህና በአሜኬላ ታጥሮ በዜት ..
· በዝንቅ ፍላጎት ነፃነት አይገኝም። በድብልቅ ወጀብም ቅንነት አይሰተጓጎልም።
እነ ቤተ አማራ „ሐዘን ላይ ነን!” ማለታቸውን ሰዓሊ/ ጸሐፊ አምሳለሉ በጣፉት ጡሑፍ ተረዳሁኝ። የወያኔ ሃርነት ትግራይ እስኪሰናበት ድረስ በጎንደር፤ በጎጃም፤ በወሎ፤ በሽዋ ሠርግ የለም ብላችሁ ስለምን አታዋጁም? በሌላም አካባቢ የሚኖሩት አማራዎችም መሰሉን እንዲፈጽሙ ስለምን ዘመቻ እትጀምሩም ውጪ ሐገርን ጨምሮ። ሰሚ ካገኛችሁ። ከፈጣሪ በላይ አይደላችሁ? ምን ሲያግዳችሁ? ለመሆኑ አሁን እናንተ ለአቅመ አዳም ከደረሳችሁበት ጊዜ ጀምሮ ወያኔ እስከ ገዛበት እሰከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ 27 ዓመት ሙሉ ስለ አማራ መከራ ጥቁር ልብስ ለብሳችኋዋልን? መቼስ አንድም ቀን አማራ ሳይገደል ውሎ ያደረበት ማዕልትም ሌሊትም የለም 40 ዓመት ሙሉ። በዚህ የጊዜ ሰንጠረዥ ሙዚቃ ስምታችሁ አታውቁንም? በዚህ የጊዜ ማዕቀፍ ሁሉ ሠርግ ሄዳችሁ አታውቁንም? መልስ አላችሁ ለዚህ አመክንዮ? አሁንም በጨርቅና በጌጥ ሸቀጥ ላይ ነው እምትሯሯጡት። ቃለ ምልልሱን እኮ አይተንላችኋዋል። ዝንጥ ብላችሁ - ንገሩኝ ባይ ሁሉ።
· ፍርጃ።
መሳቅ፤ ሐሤት ለእኛ ለኢትዮጵውያን እንዳይሆን ተደርጎ ተገምድሎበታል፤ ግርዶሹም በሴራ ተገምዷል። ቢቻል ኦክስጂኑም ለእኛ ባይገባ ደስታ ነው። ጸሐይ ኢትዮጵያ ላይ ሙቀቷን ብትከለክልም የህልም መቀነት ነው። ቢቻል ኢትዮጵያ ቀን እና ሌሊት በጎርፍና በመብረቅ ተንጣ ከዓለም ካርታ ብትሰረዝ የምኞት ቀበቶ ነው። በጎ ነገር ለማድመጥ ጆሯችን ዝግ ሆኖ የተፈጠርን እርጉሞች። መልካም ነገሮችን ለማዬት የማንፈቅድ ራሳችን ሲኦል ውስጥ የምናኖር ዕደለ ቢሶች። ሳቅን በሩቁ የፈራን - ምስኪኖች።
ይገርማል። አንቅፋት ሆነው አረፉ? „ቤተ አቧራ“ ብሎ ከተመጻደቀው ጥላሸት ጋር ተርቲመኛ ሆነው አረፉት። የሚገርም ነው። አሁን የወያኔ ሃርነት ትግራይ ባህርዳር ላይም ኮንሰርቱን አታሳይም ብሎ ቢከለክል ደግሞ፤ በዛ ዘመቻ ላይ አኩል ተስልፈው ከለከሉት ብለው በምስል ጆንያ ተጥቅልለው ናዳ ይለቁ ነበር። ዥንጉርጉር - ጥምልምል። እኔ በአንድ ወቅት „በመካከለኛው አፍሪካ የአማራ ጠንካራ መንግሥት እንፈጥራለን“ የሚል ቃለ ምልልስ ከSBS ጋር የነበረ ቆይታ ሰምቼ ዝም ያልኩት መሬት ላይ 10 ሰው ማግኘት እንደማይችሉ ስለማውቅ ነበር። ከኢትዮጵያ ውጪ መኖር ቀርቶ ከስሜቱ ወጥቶ መኖር አይቻልም። በማውቀው የህሊና መሠረት ላይ ይህ „የመገንጠል“ ሃሳብ አቅም ኖሮት አንዲት ስንዝር መራመድ እንደማይችልም መቼውንም እምናገረው ሀቅ ነው። „ሃሳቡ“ እራሱ ሳሃራዊ ነው ለአማራ ማህበረሰብ። የአማራን ገበሬ ሥነ - ልቦና መሬቱ ላይ፤ ሰኔል ላይ፤ ድርቆሽ ላይ፤ ክምር ላይ ተኝቼ፤ ቆላና ደጋ፤ ተራራና ዳገት፤ ወንዝና ሸለቆ ሳይገድበኝ ኑሮውን ወጣትነት ሳያምረኝ ተጋርቸዋለሁ። ያን ጊዜ ይህን ቃለ ምልልሱን ሳዳምጥ የማወቀውን ዕውነት የሚያደፍርስ ጎርፍ መጣ ብዬ አላስጨነቀኝም ነበር። አልደነገጥኩም። ማሰብ መብት ነው፤ ማለምም እንዲሁ፤ ግን ማሳ ከሌለው ህልሙ ምንም ነው። ከዜሮ በታች።
የአማራን ሥነ - ልቦና ካለማወቅ የመጣ የዘመን ወፍራም ግድፈትም ይመስለኛል። እርግጥ ወጣቶችም ናቸው። ወጣትነት እስኪያልፍ ድረስ ትዕግስትን የሚፈትኑ ተፈጣሯዊነት አለ። ይህንንም የወጣቶች አደራጅ ሆኜ በሥራ አውቀዋለሁ። ምንም እንኳን በተለያዬ ምክንያት የአፍላነትን ተጽዕኖን ብተላለፈውም/ ባልኖርበትም። ነገር ግን የአማራን ስብዕና በዚህ መሰል ጎባጣ ከረጢት መቋጠር ልክን ካለማወቅ ወይንም ምራቅን ያልዋጠ እጭነት ነው - ለእኔ።
የሆነ ሆኖ ለአማራ ማህበረሰብ በጥርስ የተያዘበት አምክንዮ እኮ የተማረውም ይሁን ያልተማረው ኢትዮጵያ የማይደራደርባት ሃይማኖቱ ስለ አደረገ እኮ ነው ለሽ ብሎ የሚጠቃው። የሌሎችም የሴራ ሰውር ሸኾና ሊገለጥለት ያልቻለውም በዚህ ምክንያት ለኢትዮጵያዊነት በመታመኑ ነው። ይህን የሃሳብ ፍስት በትክለኛው አውድ ላይ የተገባውን ክብር ለአማራነት አጎናጽፎ፤ የትግሉ አካል በማድረግ፤ አቅሙን የማይደፍር ንጥር አድርጎ በማብሰል፤ ጥገኛ ሳይሆን፤ ከማንም የሥልጣን አቅም ተጠዋሪ ሳይሆን ራሱን አስችሎ ለማውጣት የሃሳብ አደረጃጀት፤ አፈጻጻም፤ አንድነትና ልዩነት በተጠና ሁኔታ የእኔ ያለ መድህን መንገድ ጠራጊነት ዝግመትም ከዚህ መሰል የቋቆረ የችግር አንክብል የመነጨ ነው። የአማራ ተጋድሎ በዚህ መሰል ስርክራኪ ጉዞው መሸብለሉ ለመከራዎቹ የመፍትሄ ሳንክ ሆኗዋል። ሰብዕናውን አጥርቶና ጠንቅቆ፤ በጥናት የተመሰረተ ክህሎትን መሠረት አለማድርግ እንደዚህ መሰል የታሪክ ግድፈት እንዲፈጠሩ ያደርጋል። እርግጥ ነው የ አማራ ግመዱ ድርብ ነውና አደናቃፊ ገጠመኞች በዬሁኔታው እዬተፈጠሩ ትግሉን ሊፈትኑት ግድ ይላል። ሊሂቃኑ ተጋድሎውን በማግለላቸው ምክንያት የተመክሮ አያያዝ ጥበብ ሳስቶ የሚታዬውም ለዚህ ይመስለኛል።
- · የሰማያዊ ሚስጢራት ጠባሳነት።
ኪነ - ጥበብ ከፍ ያለች የዕውቅት አፍ ናት። ኪነ - ጥበብ እኮ የራሷ ተልዕኮ፤ የረሷ ግብ፤ የራሷ መዳረሻ ያላት ልዑቅ የስሜት ጸጋዊ ጭንቅላት ናት። አንድ ሰው ሺህ ሚሊዮን ጊዜ ከሚጽፈው ጥራዝ ይልቅ በስድስት ስንኝ የተቋጠረች ቤተ ሥነ - ጥበብ በቃናዋ፤ በለዛዋ፤ በጣዕሟ፤ በጠረኗ በኪናዊነቷ እልፍን አሰልፋ የውስጥ ታደርጋለች። ኪነ- ጥበብ የህይወት መድህን መንገድም ናት። ኪነ - ጥበብ የሩህ ጠበል ናት። ኪነ-ጥበብ ጨለማን የምታነጋ ተፈጣሯዊ ህግጋት ናት። ኪነ- ጥበብ የስሜት ንጹህ ድንጋጌ ናት፤ የማድርግ፤ የመሆን ችሎትም ናት። ኪነ - ጥበብ ጥሩ አድማጭም፤ የወጣላት ተናጋሪም ናት። በገሃዳዊነትም ሆነ በረቂቅ መንፈሳዊነትም የተባረከችና የለማችም ናት።
ኪነ-ጥበብ የሰው ሥራ አይደለችም። ቀን እና ሌሊትን፤ ክርምትና በጋን፤ ሰው እና እንሰሳትን፤ ዐዝርት እና እጽዋትን፤ ህይወት ያለውና እና የሌለውን፤ መልከዕ-ምድርን እና ጠፈርን የፈጠረ አምላክ እነኝህን እንደ ተፈጥሮ ለመኖር ውበት፤ ለነፍስ ትፍስህት ዕልፍኝ አድርጎ የፈጣራት ብጽዕት ናት ኪነ - ጥበብ። ኪነ- ጥበብ ለሃዘናችን መጽናኛ፤ ለደስታችን መንበር ናት። ኪነ - ጥበብ እንደ አንድ ግዙፍ የተፈጥሮ ጸጋ በአውራነት፤ በምሰሶነት፤ በግድግዳነት፤ በማገርነትና በጣሪያነት መሠረትነት ለተፈጥሮ አገልጋይ ሆና በፈጣሪያችን የተባረከች የመኖር ልዩ ህዋስ ናት። በቀንም ውስጥ ሆኖ ጨለማ እንዳይሆን የብርሃን አውታር ሰቁ ናት። በግርማ ሌሊትም የድቅድቁ ስጋት እንዳያውከን ለደህንነታችን የተፈጠረች የወልዮሽ ዘበኛችን ናት። ጠበቃም ናት። በከፋን እለት ማገዶ ሆና ፊት ለፊት የምትጋፈጥ ብቸኛ አርበኛ ናት። ከጎናችን የማትርቅ፤ ብናጠፋ የማትጸዬፈን ቤተ ሥርዬትና - አረጋጊም ናት።
ሥነ - ጥበብ በቀንም በሌሊትም የምታበራ መቀመጫዋን መሬት ላይ ያደረገች ሁለተኛዋ ጸሐይ ናት። መሬት ሁለት ጸሐይ አላት። አንደኛዋ ሰማይ ላይ ሌላኛዋ መሬት ላይ ትንፋሸ ኪነ - ጥበብ። መሬት ሌላም የብርሃን ምንጭ አላት ሰማይ ላይ ጨረቃ መሬት ላይ ቤተ - ኪነ ጥበብ። መሬት ሌላ አጋዥ ብርሃን ፈንጣቂ ማሾ አላት ክዋክብት ሰማይ ላይ፤ መሬት ላይ ህብረ ሥነ -ጥበብ። ቤተ - ብርሃን መሬት ላይ የጸሐይንም፤ የጨረቃንም፤ የክዋክብትንም ድርሻ ጠቅልላ በክህሎት የያዘችው አናባቢና ተነባቢዋ ኪነ - ጥበብ ናት። ኪነ - ጥበብ የነባቢተ ነፍስ ዓይን ናት። ሥነ - ጥበብ ለትንፋሽ የጆሮ ዓይኑ ናት። የመኖር ወጥ ቀለሙ የሚብራራበት በሥነ - ጥበብ ሰዋዊትነትና ተፈጥሯዊነት አቅም ነው። ሥነ - ጥበብ ወሰን ደንበር - ክልል የሌለት የትሁን ሁለመና የፊደል ገበታ ናት። የምታልቅም አይደለችም። የምታረጅም አይደለችም። እሸት ናት። ምንጯ አይደርቅም - ፏፏቴ። አትደክምም የተፈጥሮ መቅኖ አላት። በነበራት ላይ እዬነበረች፤ በትልቅ ጆሮዋ ዘመንን በተመስጦ እያዳመጣች፤ ዓለምን በጥሞና የምታስደመም፤ በወጉ የምታነብ ሙሉዑ የምድር ምህዋር ናት። ኪነ-ጥበብ ተንባይም ናት የነገ አስተናባሪ። ኪነ- ጥበብ ነብይም ናት የማግስታዊነት ሊጋባ። ኪነ - ጥበብ ሐዋርያም ናት የተራራው የጽድቅ ስብከት እንደራሴ።
ኪነ - ጥበብ ሙቀት ናት ልዩ ባለድርሻ። ኪነ -ጥበብ ትናንትን ከዛሬ፤ ዛሬን ከነገ፤ ነገን ከነገ ወዲያ የምታገናኝ መገናኛ ድልድል ናት። መገናኛነቷ የዘመኑን ሥልጣኔ እንደ ዘመኑ ቀድማ በመቀበሏ በሥልጡን መንገዷ ቤተሰቦቿ እልፍ አንዲሆኑ የማድረግ አቅሟ ጉልበታም እና አሸናፊም ነው። ተከታታይና ቋሚም ነው። ሥነ ጥበብ ብቁ አስተናባሪ፤ አደራጅ፤ ወቅትን መሪና ተርጓሚም ናት።
ዓለም ወጥ ቋንቋ የላትም። የዓለም ወጥ ቋንቋ አላት የሚያሰኛት አንድ ነገር ብቻ ነው። እሱም በኪነ - ጥበብ ነው። ስለሆነም ኪነ -ጥበብ ብቸኛዋ የዓለም የወልዮሽ የመግባቢያ ቋንቋ ናት። ይህን ጸጋ ነው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ተዳፍሮ ከፈጣሪ በላይ በመሆን በዬአጋጣሚው መንገዶችን እየዘጋ፤ እያሸገ የአማኑኤልን ፍጹም የማይገሰስ ሰማያዊ ሥልጣነ ክህሎቱን ተፃራሪ ሆኖ የሚገኘው። የከያኒውን ልሳን ብቻ ሳይሆን የአድማጩንም የውስጥ ጆሮ ከርችሞ በካቴና አዋውሎታል። መንገድ የሚዘጋ ዲያቢሎስ ብቻ ነው። ለዚህ ዲያቢሎሳዊ ጎዳና በመንገድ ጠራጊነት መሰለፍ ዘመን ይቅር የማይለው ጥቁር ጥለት ነው። የሰው ልጅ እንዴት ለሰው ልጅ አገልግሎት የተፈጠረውን ሰማያዊ መክሊቱን ሥነ - ጥበብን ድንጋይ ኮልኩሎ አታልፍም ብሎ ሊያገደው ይችላል።
እስከ መቼ ድረስ ነውስ ኢትዮጵያውያን ከያንያን ሙዚቃ ማሳታማቸውን፤ ገጣምያን መጻፈቸውን እንዲያቆሙ የሚታገዱት። ቤተ - አማራዎች ይህን ከቻላችሁ፤ አቅሙ ካላችሁ ሰማይን ወደ ምድር፤ ምድርን ወደ ሰማይ ለምን በፈረቃ አታቀያይሯቸውም። ሁለቱ ተቀያይረው ማዬትን ስለምትናፍቁ፤ ከፈጣሪ በላይ መሆንም ስላሰኛችሁ። ፈርሃ እግዚአብሄርም ነጥፎባችኋዋል። የፈጣሪን ሥልጣንም፤ ክህሎትም ክፉኛ በመታበይ እዬታገላችሁት፤ እዬተጋፋችሁት ነው ልክ እንደ ወያኔ ሃርነት ትግራይ። „ህግ ተላላፊዎችን ጠላሁ“ ይላል ህገ - አምላክ ዳዊት። ከእግዚአብሄር ክብረት ጋር መታገል አትራፊ አይደለም። ቢያንስ ፈጣሪን ፍሩ …
ይህ አካሄድ በዘመነ ኢህአፓም „ትምህርት አትማሩ የምትሄዱትንም እንግድላችኋላን የሚል መልዕክት በበራችን ሥር በነፍስ ወከፍ ፖስታ ይላክልን“ ነበር። ወላጆቻችን ደግሞ መሄድ አንዳለብን ይጫኑን ነበር። እኔ እራሴ እናቴ ይዛኝ ት/ ቤት ትሄድ ነበር። የሚገርመው ጨርሼ እስከ ወጣ ድረስ ጥጥ ይዛ ስለምትሄድ እዛው ቁጭ ብላ ትፍትላለች። ወይንም ኩታ አዲስ ከኖረ ከዛው ላይ ሆና ትቋጭ ነበር። ስንመለስ ደግሞ ደብተሬን ዘንቢል ውስጥ አድርጋ፤ ገብያ የሄድን መስለን መንገድን ቀይረን ወደ ቤት እንመለስ ነበር። ዓመቱን ሙሉ። የጎንደር እናት ፈተናዋ ዘርፈ ብዙ ነው። አሁንም 27 ዓመት ሙሉ ትግራይ ወህ ብላ፤ የጎንደር እናት ግን ትቢያ ትቆጥራለች። አሳርን ታጥቃለች።
ይሄው 40 ዓመት ሙሉ ኢህአፓ ስልጣን አልያዘም። ይሄን አላጋጭነት በማስተዋል ሁናችሁ ቅኖች ተመልከቱት። አንሱ ውጪ ወጥተው እዬተማሩ ነው ኢትዮጵያ ያለነው አትማሩ እያሉ ፍዳችን ያሰከፍሉን የነበረው። የውስጥ ሰላማችንም ያውኩት ነበር። በተናጠ መንፈስ ት/ ቤት መቀመጥ እንጂ መማርም አይባልም። አሳዛኙ አሁንም ይሄው መሆኑ ነው። ቤተሰቦቻችንም ስጋታቸው ይሄ ነው አይባልም። በሌላ በኩል ደግሞ በመንግሥት በኩልም ሌሊት መተኛት አንችልም ነበር። የስፔሻል መኪና ሌሊቱን ሁሉ በዬቤቱ ስለሚመጣ። አንድ ጊዜ እናቴ ለእኔ እና ለወንድሜ ከአልጋው ሥር የመቃብር ጉድጓድ ያህል በቁመታችን ልክ ቁፋሮ ጀምራ ነበር። የሆነ ሆኖ 40 ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ት/ ሚር ዩንቨርስቲዎች፤ ኮሌጆች፤ ት/ ቤቶች እንዲዘጉ ነበር የኢህአፓ ዓዋጁ። እሰቡት 40 ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያ ከትምህርት ዐለም ታግታ መኖርን። በዛ ውስጥ የነበሩ ሠራተኞች ሁሉ 40 ዓመት ሙሉ ቦታ የላቸውም፤ አዲስም አይፈጠርም፤ ነባሩም ሥራ ፈት ይሁን ነበር ትግሉ።
የሱማሌያ ጦርነትም አትዋጉ ነበር። ወላጆቻችን ለስንቅ ዝግጅት ቀበሌ ሲሄዱ የነበረው ፍዳ ከ - እስከ አይባልም ነበር። ት/ቤት ላይም ይሄውን ለወላጆቻችን እንድንናገር እንገደድ ነበር። ያን ጊዜ ደርግ ሞጥሮ ባይዋጋ ኖሮ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በጎኑ ባይሰለፍ ኖሮ፤ ዛሬ ኢትዮጵያ በሥም እንኳን አትኖርም ነበር። ሌላው ኢትዮጰያዊ ሃይማኖታዊ ዕሴትም፤ ቋንቋም፤ ትውፊትም፤ ትሩፋትም የሱማሌ ምስለኔ ይሆን ነበር። የአልሸባብን አሸበሪነትንም አክሎ። ለዚህ ካሊም በመሆንም የወያኔ ሃርነት ትግራይ ኢትዮጵያዊ ተቋማትን ታግሎ አሁን ካለበት ደረጃ አድርሶታል። ሶሻሊዝም እንዲህ ነው። መንቀል እንጂ መትከል አያውቅም። የዛ ግልባጭ ነው የአሁኑ ዓዋጅ የቅኔው ዕንቡጥ የቴወድሮስ ካሳሁን ኮንሰርት የዛቻ ዘመቻ። ዘመን ትውልዱን ሊያሰተምር አልቻለም። ያ ዘመን እንዳለተረፈን ይታወቃል። ከዛሬ በላይ ምስክር ከቶውንም የለም። በዘመናቸው ውስጥ ሆንው ያን ዘመንን ያላደመጠ አጥፊና አክሳይን መንገድ የሚከተሉ ወጣቶች ዛሬ ላይ መኖሩ መራራ ነው። ብስለት የለም። እርጋታ የለም። ስክነት የለም። ምድረ በዳ።ሁልጊዜ በደመነፍስና በግብታዊነት መንጨባረቅ። ከገደል ወደ ገደል። ከአረንቋ ወደ አረንቋ። ከንቱነት። አንድ ጊዜ አንድ ጹሑፍ አንብቤ ነበር “የመጣነው መንገድ” ብቻ ሳይሆን “የምንሄደው መንገድም” ያሳዝናል የሚል። ያ ጹሁፍ ደወለብኝ - ዛሬ። ዕውነትም ነው። ንጡር ፍልስፍና በእርቀት ውስጣችን የተመለከተ።
- · ወርቀ ዘቦ ዘመን እንደ መስታውት።
ለካንስ የቅኔው ዕንቡጥ ቴወድሮስ ካሳሁን ኮንሰርቱ ሲታገድ፤ „የጧፍ እስከ ማር“ ያ ታምራዊ ትንግርት፤ የተግባር ልዑቅ፤ ማህለቅ የምርቃት በአሉ ሲስተጓጎል፤ ተምስጥሮ ለዋንጫችን ተብሎ ኑሯል ከወያኔ ሃርነት መሳፍንቶች ጋራ። ወይ ዘመን እንዴት ሸጋ ነህ። ወርቀ ዘቦው ዘመን እንዴትስ መስተዋት ነህ። እንዴትስ ኤክስ ረዬ ነህ። ባገኝህ የወርቅ ሃብል ባሰርኩልህ በነበረ። እኔ ሌላው የነፃነት ቅኔ ሃንጫሉ ሁንዱሴ በግዮን ሲከለከል፤ የተቀበለውን የ1, 000,000 የኢትዮጵያ ብር የቀብድ ተመላሽነት ስሰማ እጅግ አዝኜ ነበር።ነገር ግን በሚሊዬም አዳራሽ ተፈቅዶለት ሞራሉ ተጠበቀለት። 21 ሺህ ታዳሚ ነበረው። ደስም አለኝ። የቅኔው ዕንቡጥማ ተቆርቋሪ ክንድ ስላለው ሃሳቡን መግለጫ አጣ ብዬም ጽፌ ነበር። ሃሳብ ለምንድነው የሚታገደው? ሰላማዊ ኪናዊ ትግል ስለምን ይሆን የሚፈራው? መንገድ ሲገኝ ስለምን ነው እንዲታገድ ድርና ማገር የሚኮነው? የነፃነት ትግል ናፍቆት በጥሬው ሳይሆን በለዛ ተቀምሞ፤ በቅኔ ተውቦ፤ በዘመን ተጥልፎ ሲቀርብ እንዴት የጥቃት ዘመቻ ይታወጅበታል?
„ሀንጫሉ ሁንዴሳ አቶ ለማ መገርሳ በተገኙበት ኮንሰርት ህዝቡን አሳበደው [ዘፈኖቹ ፖለቲካዊ ይዝትም አላቸው]“
· ጥቃት ስለማውጣት።
አሁን ይህን ጥቃት ደም የሚመለስ ለዛውም ከብአዴን ሲገኝ ደስ ሊለን፤ ልናበረታታቸው፤ ከዚህም አልፈን ልናመሰግናቸው ሲገባ ጭራሽ ሌላ ሴራ፤ ሌላ ደባ፤ ሌላ ጦርነት ማወጅ - የዘመን አሳንጋላነት ነው። ይህ ማለት ለእኔ „በሬ ካራጁ ጋር“ እንደሚሉት ነው የሆነው። ፈረንሳይ ከፍ ያለ መከራ በ2015/ 2016 አስተናገደች፤ ግን አንድም ጊዜ ኮንሰርት አልተቋረጠም። እንዲያውም የአውሮፓን የስፖርትን የዋንጫ ውድድር በዛ ጭንቅ ሆና አስተናገደች። መከራና ሰው፤ ሀዘን እና ደስታ አብረው የኖሩ ናቸው - የተፈጠሩም። ነገም ቢሆን ዘመኑ የሚፈጣራቸው ሌላ መከራዎች ይኖራሉ። ሁለቱ ተፈጥረዋል። አንደኛው ለሳቅ ሌላኛው ለእንባ። የተሻለ ሥርዓት ቢመጣ መቀነስ ቢቻል ነው እንጂ ሙሉ ለሙሉ በዓዋጅ ማጥፋት አይቻልም። ምክንያቱም ዘመን የሚወልዳቸው አዲስ ችግሮች ደግሞ ይመጣሉ። አሁን ሲዊዝ የሰላም ሀገር ናት። ግን ህዝቡን ስታዩት ውስጡ ደስተኛ አይደለም። ሁሉም እያለው ትልቅ ነገር እረቆታል - ደስታ። አብዛኛው ሰው ስታዩት የሞላለት መስሎ ይታያል። ለብሶ / ተጫምቶ ተምሮ - አምሮም። ያልተመረቀ ተማሪ ከዚህ ማግኘት ይቸግራል። ዓላማቸውም ግባቸውም እንያንዳንዱ ልጅ በሙያ መብቀል አለበት ነው። ተሰጥዖ በትርፍነት ነው ከዚህ የሚያዘው። ክፍያው ደግሞ አድነኝ ነው። ማለት የኑሮ ደረጃው ከፍ ያለ ነው። ግን አብዛኛው በእንቅልፍ ክኒን መዳህኒት ነው የሚተኛው። በርካቶች በስነ - ልቦና ሃኪም ተረጅዎች ናቸው። ዓለም ሞልታ አታውቅም ጎደሎ ናት። ዛሬ ቴሬሪዝም ነገ ደግሞ ድራጊዝም ወይንም ሞቲዝም ወይንም ፖፕሊዝም፤ ይስፍናል …. እንኳንስ መላ በሌለው ረግረግ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ቀርቶ።
… በጥር ወር ኢትዮጵያ በጣም ብዙ ሰው ይዳራል። ጥር „የጣና ዘግሊላ“ ተምሳሌት ስለሆነች የሰርግ ወር ናት። እና እሱንስ እናስቆመዋለን ብላችሁ ትዝቱ ይሆን እነ ቤተ አማራ? በአንድ ቀን ጎንደር ከተማ ብቻ ከ30 ሙሽራ በላይ ይዳራል። ገጠሩማ ምን ስፍር፤ ምን ቁጥር አለው። ወሩን ሙሉ ሠርግ ነው። ተፈጥሮን ኢትዮጵያ ላይ አቁም ነው ትግሉ። በዚህ ስሌት ስኬድ ጸጋው፤ መክሊቱ የተሰጣቸው ኢትዮጵያውያን ሚሊዮን ዓመት ድረስ የሙዚቃ ህትምት ይዘጋ ብላችሁ ይሆን ነጋሪት እምትጎስሙት? ሰው ሆኖ መፈጠርን እራሱ እዬታገላችሁት ነው። አትደስት፣ አትሳቅ፤ ትንፋሽ አይኑርህ፤ ሠርግ አታድርግ፤ አትፃፍ፤ አትግጠም፤ በጭንቀት መኖሩ ብቻ ይበቃሃል። እንደ ታፈነክ መቃብር ውረድ እኮ ነው እዬተባለ ያለው። ለእኔ መክሊትን የሚዘጋ ሁሉ የዲያቢሎስ ማህበርተኛ ነው …
ምንድነው የምትፈልጉት ታላቋን ትግራይን ወይንስ ታላቋን ኢትዮጵያን በመንፈስ ጎልብታ ማዬት? ማነው የሚበልጥባችሁ? የአማራ ወጣቶች ያሉትን ከቶ አልሰማችሁንም? ለማድመጥ ተከልክለናል፤ ትታሰራላችሁ ተብለናል ነበር ያሉት እኮ። መከራው ከእናንተ ከዘመናዮቹ ይልቅ በዬዕለቱ የሚደስቃቸው እነሱን ነው። ነገር ግን ከያንያን ያደምጣሉ፤ በኪነጥበብ ሃይል መከራቸውን እና ፍዳቸውን ያስታግሳሉ። https://www.youtube.com/watch?v=VXAer5Ovsro „Amahara warns.“
ይህን እስር የፈታ፤ ይህን ደባ ያከሸፈ እርምጃ ነው አሁን ብአዴን የወሰደው። በደስታ ነው የተቀበሉት። አበጃችሁ ልንላቸው ይገባል። ለዚህም እኔ እጅግ አድርጌ አመሰግናችኋዋለሁ ማለትን ደስ ብሎኝ ነው የምገልጸው። አንዲህ እዬጀገኑ ከመጡ እኮ የተሻለ ተስፋ መጠበቅ ይቻላል ልክ እንደ ኦህዲድ። ይህ እኮ ታላቅ እርምጃ ነው ለነፃነት ትግሉ። ይህ አኮ ለኢትዮጵያዊነት ታላቅ ትነሳኤ ነው። የታሰሩበትን የባርነት ሰንሰለት በድፍረትና በሙሉ ልብነት ለመፍታት መንገድ እንደ ጀመሩ ምልክትም አዲስ ጽናጽልም ነው። መልካሙን ማመስገን ካልተቻል በምን አቅም ይሆን ደካማ ጎኑን መተቸት የምንችለው። ስለምንድን ነው ሁሉን ነገር በድምስሱ ጥላሸት ቀብተን ጥቁር ዘመን እንዲቀጥል የምንናፈቀው? ህሊና የሚባል ነገር አለ። ክፉና ደጉን፤ እንክርዳድና ስንዴውን የሚያበጥር መንሹ። ቤተ አማራዎች ለዚህ ስላልታደላችሁ ፌርማታው ሳትደርሱ ከበለል ብላችኋዋል። ተሳህለን!
- · ተጨማሪ የዘር ጥፋት ምኞት።
ኢትዮጵያ ከፍ ስትል ስለምን ነው እንዲህ ረመጥ የሚበዛው? ስለምን ይሆን እንዲህ የሚያንገበግብ? ስለምን ይሆን እንዲህ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚባለው? በዚህ ኮንሰርት ላይ አንዳች ነገር ከተፈጠረ 2.5 ሚሊዮን በዘመነ ናዚዝም የጠፋው የአማራ ዘር በእጥፍ እንዳጠፋችሁት ይቆጠራል። ለመሆኑ ማንን ነው እዬታገላችሁት ያለው? ምንድንስ ነው የምትፈልጉት? የአማራ ሥነ - ልቦናዊ አንድነት እንዲኖር ስለምን ይሆን የማትሹት? አቤቱ ማህከነ!
ከእንደዚህ ዓይነት እኩይ ማህበርተኝነትም ማረን፤ ኧረ ማረን! የእኔ ስጋት ወያኔ ሃርነት ትግራይ ያግደውን ይሆን? ሰላሙን ያደፈርሰውን ይሆን? በሚል ነበር። ምክንያቱም ዘውዱም ጠመንጃውም የዘመንተኞች ስለሆነ። ኢትዮጵያ ለወያኔ ሃርነት ትግራይ አንጡራ ተፎካካሪው አድርጎ ነው የሚያት። አንድ ቪዲዮ አይቼ ነበር „በኢትዮጵያዊነት መኖር ካልቻልን ትግራዊነቱን ለእኛም ፍቀዱልን“ የሚል። እናንተን በዚህ የመንፈስ አጋርነት የተቀበሏችሁ ይመስላል። አበስኩ ገበርኩ!
ዛሬ ፍሬ ነገሩን መናገር አልፈልግም „ሰከን በል“ ለእኔ አቅምና ጉልበት፤ እንዲሁም የሃይል ምንጭ ስለሆነኝ ድንቅ ብሄራዊ ተደማጭነትን አትርፌበታለሁ። ሌላው ቅኔ ይሁኔ በላይ የእናቴ የልብ ወዳጅ ነው። እኔ እንደሚመስለኝ ዘማናዊውን እና ባህላዊውን ዜማው በወግ ተዋህደው የሚገኙበት ስለሆነ ይመስለኛል እናቴ እሱን ለይታ የምትወደው። እጅግ ነው እምትሳሳለት። አገር ቤት እያለሁ ባገናኛት እል ሁሉ ነበር። እኔ ደግሞ ሙዚቃ የምከታተል አይደለሁም፤ ነገር ግን አሁን ከሆነ የሀገር ናፍቆትም፤ የነፃነት ጥማትም ስላለብኝ ይሆናል ሰዎች ሊንኩን ሲልኩልኝ አዳመጣለሁኝ። በህይወቴ ከ200 ጊዜ በላይ ያዳመጥኩት „ሰከን በልን“ ነበር። ሥራ -ስለሰራሁበት። ከውስጤ ነው የገባው። አንዲህ ልቤን ገዝቶ እርምጃ እንደወስድ ያነሳሳኝ ፍጹም ልዩ አጋጣሚ አልነበረም። የተሳካም ነበር። ወፍ ያወጣው። በአጋጣሚው የሰብል ውዴን አመሰግነዋለሁ።
ኢትዮጵያ በታሪኳ በዓለም የሙዚቃ ሰንጠረዥ ገብታ ዓለምን ያነጋገረችበት ወቅት ደግሞ „ኢትዮጵያ“ የሚለው የቅኔው ዕንቡጥ ሲዲ ነበር። በዓለም ዐቀፍ የሙዚቃ መድረክ እጅግ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ መውጣቱ በጎደላት መስክ ለዚህ ለ21ኛው ምዕተ ዓመት የአድዋን ድል ያህል ከፍ ወደ አለ ደረጃ ያሸጋገረ አዲስ ዘመን ነበር። ለሁላችን ብሥራታዊ ሽልማት። ይህ ዕውነት ስለጎረበጠው፤ ስለሻከረው፤ ስለሻአነፈው ነው የወያኔ ሃርነት ሥርዕዎ መንግሥት ያን ያህል በይፋና በስውር ይህን ቀንበጥ የታገለው። ሃይሉ፤ ጉልበቱ፤ አቅሙ የሚያስፈራ ማናቸውም ኢትዮጵያ የሚወለድ አዲስ መንገድ ሁሉ ተፈሪ ነው። ስለምን? ኢጎ። ኢጎ ቀዝቃዛው ጦርነት ነው። ኢጎ የቅናት ነቀዝ ነው። ኢጎ የምቀኝነት ሳጥናኤላዊ ጊንጥ ነው። ኢጎ የሸር ቅንቅን አጋፋሪ እባብ ነው።
- · „ጣና ዘገሊላ።“
ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ጥር እኮ የሠርግ ወቅት ነው። ለተዋህዶም „ጣና ዘገሊላ“ ነው። „ጣና ዘገሊላ“ በግዮን ቢያብብ ትንሽም ህዝቡ ትንፋሽ ቢያገኝ ስለምን ይሆን ተቀናቃኝ የሚኮነው? ሃዘን ተፍስሃ ይላሉ አባቶቻችን። ከአንድ ቤት በአንድ ቀን ሠርግም ሞትም ይኖራል። አንዱ ልጅ ሊሞት ሌላው ልጅ ሊዳር ይችላል። ሠርጉም እንደ ሠርጉ፤ ሞቱም እንደ ሞቱ ሥርዓተ ትውፊቱ በቅደም ተከተል ይከወናል። ለሠርጉ ነጭ ተልብሶ፤ ለሞቱ ጥቁር ተለብሶ በተደሞ፤ ባልተጻፈው ህጋችን በሥርዓት ይከወናል። ባህል ማለት አኮ ይሄ ነው። ትውፊት ማለት ይሄ ነው። ዕሴት ማለት ይሄ ነው። ወግ ማለት ይሄ ነው። ሞት የሌለበትን ቀን አናገኝም። በፍጹም።
በጥንት ዘመን ኢትዮጵያ የሰላም አንባ ሆና መኗሯ ያስጨነቃቸው ንጉሥ መሬት ደብድበው ጦርነት አምጣ ብለው ፈጣሪን ለመኑት። ግራኝ መሃመድ ተነሳለችው። ያን ያህል ቅርስ ወደመ፤ ያን ያህል ህዝብ አለቀ። አሁንም ይኸው ነው የሚታዬው።
ወደ ፍቅር የሚያመጣ ቅኑዑ መንገድ ሲመጣ መክለፍለፍ ነው። ትክክል ነው ኢትዮጵያ በተነኮረ የቂም፤ የሴራ፤ የሸር፤ የኢጎ፤ የምቀኝት፤ የተንኮል፤ የጥላቻ ሥር ተተብትባ፤ ይህን መንገድ የጠረገ እርምጃ በድንቆች መንፈስ ልቅና ሲጀመር በዬቦታው ያዙኝ ልቀቁኝ ሆነ፤ …. ለምን ይሆን? ከልብና እውነተኛ የሆነ ከሆነ የለበጣ ልጥ ከሌለበት ፍቅርን፤ መቀራረብን፤ መተሳሰብን፤ መደመማመጥን፤ መቻቻልን የምንፈራው? ይህ የተጀመረው ፖለቲካዊ ብልህ የጸዳ መንገድ መዳኛችን መሆኑ ያስፈራቸው ወገኖች ናቸው እዬተበጠበጡ የሚገኙት። መሠረት እንዲይዝ አይፈልጉም - ፍቅር። ፍቅር ተንሳፎ፤ ፍቅር ተንሻፎ፤ ፍቅር ወላለቆ የአዬር ላይ ሲሳይ ሆኖ እንዲቀጥል ነው የሚሹት። ግን ጭንቅላት ካለበት ቦታ አለ፤ እንደ ተፈለገው ዘውሮ ወይንም ወጥሮ የራስን ዓላማ ማሳኪያ ሊሆን ከቶውንም አይችልም። ኪነ - ጥበብ ደግሞ ግዴታ አለባት ይህን መሥመር የማያስያዝ። የተጣመመውን የማቃናት፤ ወልጋዳውን አርቃ የመግራት፤ የዘበጠውን ጠርባ የማስተካከል። ኪነ - ጥበብ አናጺም፣ መሃንዲስም ናት።
ብአዴንን እኮ በሳል በሆነ አምክንዮ የሞገቱት ታላቅ ሰው አሉ? ያን አዳመጠ - የአማራሚደያ። መፍትሄው እየራቀ የሄደው እኮ ማዳመጥ ስለቃተተ ነው። ከእያንዳንዳችን የሚዋጣው ሃሳብ ከቁም ነገር ስለማይቆጠርም ነው። ያቀተውን ነገር ተደፍሮ መሆን ሲገኝ ደስ ይላል። ይህ የሚያሰመሰግን እንጂ ከቶውንም እንደ ወንጀል ተቆጥሮባቸው በእቅዱ ላይ ሳንክ በዘመቻ ሊታወጅባቸው አይገባም። በፍጹም። ይሄ የጠላት ሥራ ነው። ለዛውም የኢትዮጵያ። ይህ ማለት በቀጥታ እና በጠራ ቋንቋ የሙሶሎኒ ማንፌስቶ አጋፋሪነት ነው። ፋሺዝምን አጥብቆ፤ አስልቶና አቅዶ መናፈቅ። ስንክሳር። ስርክራኪ ዕሳቤ።
- · የማድመጥ አቅም ሙሉዑነት።
Teddy Afro - Mar Eske Tuaf | በአማራ ክልል ምክር ቤት በቴዲ አፍሮ ላይ ጉዳይ ጥያቄ ተነሳ
አንድ ድንቅ ወገኔ እንዲህ ብለው ብአዴህንን ሞግተውት ነበር። „እኔ አንድ የሚገርመኝ ነገር አለ ለምሳሌ። እኛ አሁን ምድረ ጎጃም ውስጥ ነው ያለነው። ጎጃም የኢዲስ አለማዬሁ አገር ነው። ፍቅር እስከ መቃብርን ያለነበበ የለም። ወጋዬሁ ንጋቱን ሳያዳምጥ ያለፈ የዚህ ዘመን ምንአልባት የአሁኑ ትውልድ ካልሆነ በስተቀር ብዙዎቻችን አዳምጠናል። ግን ህይወት የዘራበት ወጋዬሁ ንጋቱ ነው የአዲስ አለማዬሁን መጸሐፍ። አሁን ደግሞ ቴወድሮስ ካሳሁን የበለጠ ነፍስ ዘርቶበታል። በዛብህ ሰብለ ወንጌልን እያሳደደ በእነ ጉዱ ካሳ ፈረስ እዬጋለበ ይዘፍናል። በአማራ መገናኛ ብዙሃን ይሄን ዜማ ሰምቼው አላውቅም ነበር። ለእኔ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ይሄ የሰልፍ ሴንሰር ሽፕ ውጤት ነው ከመባል በስተቀር፤ ካልሆነ በስተቀር ምን ሊሆን ይችላል ይሄ? እራስን የማቀብ ዓይነት ሰልፍ ሴንሰር ሽፕ። ይሄ ሎካል ሚዲያ ነው። ሎካል ሚደያ እንደ መሆኑ መጠን የግዴታ ይሄ ዜማ በሌላ ሚዲያ አስኪሰማ መጠበቅ አለበት ብዬ አላስብም።“ ቦንብ ነው። እድሜዎትን የማቱሳላ ያድርግልኝ። የተወሰኑ ተግባሮቹ የአማራ ቴሌቪዥን ለእኔ የተሻለና ጣዕሜ ነው። ነፋሻማ ገጠሩን አይበታለሁ። የህዝብን ብሶት አዳምጥበታለሁ መልካም ጅምር ነው …
ቤተ - አማራዎች ይህ አንጎላዊ ጥያቄ የህዝብ ጥያቄ ነው። የብአዴንም አይደለም። ብአዴን ሊያሰመሰግናቸው የሚገባውም ቁም ነገር ምንአልባት ከኖሮበት ዘመን ሁሉ አንዲት ተግባር ሰራን ቢሉ ይህን በድፈረት ማድመጥ መቻላቸው ነው። ይሄ ከተደመጠ
በኋዋላ ደግሞ አንዴት „ማር አስከ ጧፍ“ እንደተሠራ ቃለ ምልልስ ተደርጓል።
- · ዕጹብ ድንቅ የእኔ ጎጃም!
„የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ‹‹ማር እስከጧፏ›› በዛብህን ወክሎ በተወነው ወጣት አንደበት-በአማራ ቴሌቪዥን“
ዕጹብ ድንቅ የሚያሰኘው የማርቆስ ህዝብ በሙሉ የኪነ-ጥበብ ብቁ አድማጭ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለተዋናይነት አብሮ መሰለፉ ነበር። ክፍያ አንፈልግም ነው ያለው። ሥራዋን የተዋጣ ያደረገውም ይሄው ህዝባዊ ተሳትፎ ነበር። በሙሉ ህዝቡ የተለጠፈውን ማስታወቂያ አይቶ በፈቃዱ ነበር ለካስቲንግ የተዘጋጀው። ይሄ ከሰማይ ታዕምር በላይ ነው። አማራጭ ተዋዳደሪው ቁጥር ሥፍር አልነበረውም። ከልጅ እሰከ አዋቂ፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ። በዛብህን እኔ በምናቤ የማወቀው በትክል በዛብህ ነው የመጣው። የሚናፍቀኝ በዛብህ። በመንፈስ የፈቀድኩት ላዬው የሳሳሁለት በዛብህ። ጉዱ ካሳ የሳልኩት ጉዱ ካሳ እራሱ በነፍሱ ነው የመጣልኝ። ፊውታራሪ ያስብኳቸው ከነ ግርማ ሞገሳቸው ነው የመጡልኝ። ሥርዓቱ ጮማው ዛሬ እንዲህ ይኖራል ብዬ አላስብም ነበር። ጎታው ወራንታው፤ ሰፊዱ፤ አግልግሎ ለዛው ምድጃው ስንቱ … ምክንያቱም 15 ጊዜ አንብቤዋለሁ። ማድመጡን በሚመለከት የካቲት 66 ፖለቲካ ኢኒስቲቲዩት በዬሩማችን ትረካው ይደመጣል። በመደበኛ። ኮርሱን ጀምርን እስከ ጨረስንበት ድርስ 6 ወራት ሙሉ። „ፍቅር አስከ መቃብር“ በውስጤ ነው ያለው። ወንጌል እረዘመ ብዬ 8ኛ ክፍል ላይ ከሥሜ ማውጣቴ አሁን ነው የጸጸተኝ። ምንለበለው አንደ ልቤ አብሮ የተፈጠረ ነው መጸሐፉ እራሱ። ለዶክተር አዲስ አለማዬሁም አንዱ መጸሐፌ ላይ የመታሰቢያ ግጥም ጽፌላቸዋለሁ። ለማንኩሳም እንደዚኸው። ይሄን ሥራ ልናቃለው አንዲህ እንደ አልባሌ ነገር የምናከባልለው፤ አልዬሁህም የምንለው አይደለም። በፍጹም። የማስተማሪያ መሳሪያ ነው። ኢትዮጵያና ፊውዳሊዝምን በነፍሱ ከነተጥፈጥሮው ያለ አስተማሪ የሚያሳይ ነው። መጸሐፉ ሥዕላዊ፤ ታሪካዊ፤ ገላጭዊ፤ ትውኔታዊ፤ ገምጋሚያዊም ነው። የቃናዊትን የወ/ሮ አምለሰት ሙጬ „የበዛብህ“ የምርጫ ጥልቅትና ብቃት አስከ አሁን ድርስ ቃል አላገኘሁለትም።
ከፍቅሬ ልክ አለመኖር ብዛት „የወጋዬዩሁ ንጋቱ የትውና ጥበብ ክበብ“ ነበር አዲስ አባባ። እና አማስተኛ ሙት ዓመቱ በብሄራዊ ቲያትር ሲያከብር ክበቡ „እሱ ማነው?“ የሚል ሥነ - ግጥሜ ተወዳድሮ አሸንፈ። እናም ለመጀመሪያ ጊዜ በብሄራዊ ቲያትር አቅርቤው ነበር። አንዱ መጸሐፌ ላይም አለ ሙሉው ግጥም። ከተመስጥኩባቸው አንኳር ጉዳዮች ታሪኩን እንደራሴ አድርጌ ስለማዬው ነው። ከደሜ ጋር ተዋህዶ የኖረበት የራሱ የሚስጢር ህግጋት አሉት። በዛብህን እንደ ፈልገኩት ኖሬ አሁን ግን የልቧን መዳህኒተ ዓለም ይሙላልኝ ሐሤታዊትን ወ/ሮ አምለሰት ሙጬ አገኘችልኝ። አንዴት የልቤን እንዳደረሰቸው - ትርጉም ልበላት፤ ውስጤን ከገለጸልኝ። አደራ እንድታዩት እራሱ የምርጫው ሂደት እና ለቃለ ምልስ ሲገባ አገባቡ በዜማ ነበር። ነፍስ ነው። እራሱ ባለቅኔው በዛብህ በነፍሱ ነው የመጣው። በመጨረሻ የእኔ ቅኔ ሃሳብህ ተሳክቶ ጉዞኽ ተባርኮ፤ የተሰበረው ልቦናህ ተጠግኖ ለማዬት ያብቃኝ። እጅግ አድርጌ አመሰግንሃለሁ አካል - ተ - አማሳልህ ጋራ። አንዲሳካ ለምትጥሩት ወገኖቼም መንገዳችሁን ሁሉ ፈጣሪ አምላኬ ይጠብቅልኝ። ድንግልዬ ከእናንተ ጋር ትሁን። መጨረሻውን ያሳምረው። አሜን! PROUD! STOLZ!
- · እርገት ይሁን …
ዳግማዊ ጠበቃ ተክለ-ሚኬኤሎች፤ በዬቤቱ እዬሄዳችሁ የዚህን ህዝብ ፍቅር እስኪ ለመንጠቅ ሙከራ አድርጉ፤ ከተሳካላችሁ። በኢትዮጵያ እንዴት ይቀናል?
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ