እሪ! የብልህነት ያለህ!

እሪ! የብልህነት ያለህ!
ሥርጉተ - ሥላሴ 11.10.2017 (ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ።)

„እንደ ጠቢብ የሆነ ሰው ማን ነው? ነገርንስ መተርጎም የሚያውቅ ማን ነው? 
       (መጸሐፈ መክበብ ምዕራፍ ፰ ቁጥር ፩)“

የሰሞኑ አጀንዳ ደግሞ ነገረ- አባዱላ ናቸው። ኢሳት በጣም ጉልበታም ውይይት በዚህ ዙሪያ አካሄዷል። ሁለት ተቀራራቢ ግን የልዩነት መንፈሶችን በሚገባ አስተናግዷል። እኔ ማለፊያ፤ ምራቁን የዋጠ ውይይት ነበር ብዬ አስባለሁ።
« ESAT Special discussion on Abadula resignation October 10 2017 »
  • እንደ መግቢያ በር

ነፍሴ ተንጠልጥላ ነበር። በአንድ በኩል ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና የሚያነሳቸው ሃሳቦች እና ጭብጦች ቀልቤን ይገዙታል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከሥር ተነስቶ ተጨባጩን አድርቶ፤ መጪውን አስልቶ ጋዜጠኛ ኤርምያስ ለገሰ የሚያነሳቸው ለስለስ ያሉ ግን ልብን የሚያንኳኩ ጭብጦቹ ህሊናዬን ፈተኑት፤ ስለሆነም ለረዥም ጊዜ ጋዜጠኛ ኤርምያስ ለገሰ ይሁን ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና የሁለቱም ውይይት ለውሳኔ አሰጣጥ እጅግ አጓጕ እና ነፍስ አንጠልጣይ ነበር። በዚህ የውይይት ክፍለ ጊዜ ጋዜጠኛ መሳይም መኮነንም  በአወያይነት ተሰይሞ ጥሩ አድርጎ፤ ማዕከላዊ ሆኖ መርቷል ብዬ አስባለሁ። ማለፊያ
በሁለቱም የውይይት መምኽራዊ ጉዞ ውስጥ አንድ የሆነ ትልቅ ጉዳይ ግን የተዘነጋ ይመስለኛል። ወደዛ ከመሄዴ በፊት ግን በጉልበታሙ ውይይት እኔ የጋዜጠኛ ኤርምያስ ለገሰ የአቀራረብ ጭብጥ የበለጠ መንፈሴን ገዝቶታል። አንድ ራህብ ግብብግ ያደረገው ሰው ደረቅ እንጀራ ከፊቱ ቢያገኝ ወጥ ማባያ እስካገኝ ድረስ ልጠብቅ አይልም። ለራህቡ ማስታገሻ የሆነውን ደረቅ እንጀራ በውሃው አወራርዶ ወደ ዘ-መ-ን ወዳለው ፍላጎቱ ማለትም ማባያውን ማግኛ ዘዴ በቀጣይ ይተልማል። ውጥረት ላይ ያለው 100 ሚሊዮን ህዝብ መተንፈሻ ማግኘቱም እንዳዛ መታዬት አለበት ባይ ነኝ። ለሥር-ነቀል ለወጥ ሁሉንም መንገድ እንደ አማራጭ ማዬቱ የተገባ ይመስለኛል። እንቁላል ሳይጣል ጫጩት አይኖርም። ግን የተፈጥሮ ሂደት ጣስ ብሎ … እንቁላል ሳይኖር ጫጩቱ ከመጣም ማን ይጠላል። በአቋራጩ …

በሌላ በኩል በዚህ አቅም በነበረው ውይይት ዬጋዜጠኛ ኤርምያስ ለገሰን የአቋም ነፍስ በትክክል ያዬሁበት፤ የመዘንኩበት ትክክለኛ ጊዜ ነበር ማለት እችላለሁ። እራሱ መሰደዱ ትርጉም ሰጠኝ። ጋዜጠኛ እንደዚህ ሲሆን ደስ ይላል። ጋዜጠኛ ለሚያምንበት አቋም እራሱ፣ በራሱ ተቋም ለመሆን ሃላፊነቱን ፈቅዶ እንዲህ በድፍረት ሲወስድ አብነቱ ጉልህ ነው። ለተተኪው ትውልድም ማስተማር መቻሉ ብቻ ሳይሆን፤ ሚዲያውን እራሱ ታማኝ ያደርገዋል። የሚዲያውን በውስጡ ያለውን የነፃነት ልኬታንም እግረ መንገድ ያሳያል። ሃሳቦች እንዲህ በሚያስማማቸው ላይ ሲስማሙ አብረው ሲከትሙ፤ በማያስማማቸው ላይ እንዲህ ሲፋተጉ፤ እንዲህ ሲፋለሙ፤ እንዲህ ጉጉስ ሲገጥሙ ጣዕም ይኖረዋል። የመጨረሻው የመዳረሻ መልዕክቱም መሳጭ ይሆናል። በሌላ በኩል ዬውይይቱ ሂደቱ አሰልቺ አይሆንም፤ ይልቁንም ይማርካል። ይስባል። ትንሽ አለፍ ሲልም መልካም ጠረኑ አድማጩን እንደ ጎረቤት ወይንም እንደ ሩቅ ተመልካች ሳይሆን፤ እንደ አንድ ቤተኛ ያደርጋል። በሌላ በኩል ፍላጎታችነን ባላ አልቦሽ አያደርገውም። ሃሳብን በማማከል ወደ ነጠረ መስመር የመሸጋገሪያ ድልድይ ገንቢነትን ተስፋ ያፋፋል። ፍርሃት አለ። ይህ ሊደበቅ የማይችል ጉዳይ ነው። ነገም እንደዚህ …. በአንድ ዬሃሳብ ጅረት ብቻ ለመንጎድ እንገደድ ይሆን የማለት …
  • ነገረ ዘመነ መስፍንት …

ኢትዮጵያ ዘመነ መሳፍነት ከከተመባት እኮ ከረመች። 26 ዓመት። ሩብ ዘመን። አንድ ትውልድ። በብሄረሰብ መደራጀት ሀገራዊ ዕሴትን የሚጫን ነው። ግን በፖሊሲ ደረጃ የተከወነ ተግባር ነው። የጣሊያን የረጅም ጊዜያትን ህልም ያሳካ ቅበር ስትራቴጂ። ወደ ተጨባጩ ስንመጣ ህብረ - ብሄር የሚባሉትም በመንፈሳቸው ውስጥ የዚህ እርሾ የለም ለማለት በጥናት የተደገፈ ባይሆንም፤ ከማኒፌስቷቸው መንፈስ ሆነ፤ በተጨባጭም ከመዋቅራቸው ስምሪት በርስትነት የተቀመጡ ቅሪተ አካሎች አሉባቸው። ይህ መቼም አሊ የማይባል ሃቅ ነው። ይህም ብቻ አይደለም እንጥፍጣፊ የለብንም በማለት ሊምሉ ሊገዘቱ ቢችሉም፤ አፋቸውን ሞልተው እንዳይናገሩ እጅና እግራቸውን አስሮ የያዛቸው ሌላ አስገዳጅ ተጨባጭ ሁኔታም አለ። ስለምን? ህብረት፤ ስምምነት፤ የሚፈጥሩት በጎሰኝነት ደም በቅለው ካሰበሉ ድርጅቶች ጋር ነው። በቅለው የሚታዩት ነገሮች ስልጣን ላይ ዬመምጣት ወይንም የአለመምጣት ጉዳይ አይደለም።

መሠረታዊ ጉዳዩ፤ በሥነ - ልቦና ላይ ያለው ቅምጥ ንጥረ ነገር፤ ያመጣው ለውጥ ነው። አስኪ የኦነግን መለያ አርማ ያልያዘ፤  ዬኢትዮጵያን ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ የያዘ የተቃውሞ ሂደት የት ላይ ታዬ „ኦሮምያ“ ብሎ ወያኔ በቀዬሰው ቦታ።  ይህን የሥነ - ልቦና አብዮት ከፈጠሩ በኋላ እንሱም እራሳቸው ይህን እንዳዘሉ አንድ ሁለት ሰው ህብረ - ብሄርን ዕሳቤ ተቀብለዋል፤ ከእነሱ ድርሽ ማለት አያስፈልገም የሚባለው ነገር ለእኔ በራሱ እንደ ድል ሊታይ አይገባም ባይ ነኝ። ምክንያቱም ያዘሩት ዘረኝነት አብቅሎ አስብሎ እዬታዬ ነው። ሌላውም ለጥቃት መከላከል፤ እኩል ደረጃውን የጠበቀ አቅም ለመገንባት እዬታገለ ያለው በዚህ መስምር የመጣ አስተምኽሮ ነው። ስለሆነም የሁለት ወይንም የሶስት ሰው ህሊና የአቀደውን ከከወነ በኋላ ባዶ እጁን ህብረ ብሄርነትን ተቀበልኩ ብሎ መምጣቱ ሌላም ታክቲክ ሌላም ስትራቴጅ ይኖረዋል ባይ ነኝ። ይህ በራሱ ሰፊ የጥናትና የምርምር ጊዜ የሚፈልግ ይመስለኛል። ስለሆነም ለእኔ አቶ ሌንጮ ለታ ወደ ኢትዮጵያዊነት መምጣት ብርቄ አይደለም። ድልም አይደለም - ለእኔ።  አማራጭ ካገኙ ወደነበሩበት የማይመለሱበት ምንም ጋራንቲ የለም። እንደ ሽንብራ ቂጣ ሲገላባበጥ የኖረው ስብዕና ይህን ፍንትው አድርጎ ያሳያል። በሌላ በኩል ቀደም ባለው ጊዜ ብዙ አውሮፓ የተካሄዱ ህብረቶች ጥመረቶች ስበሰባቸውን ሲያካሂዱ የአንድም ፓርቲ ዓርማ አይቼ አላውቅም። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ብቻ ነበር የነበረው። አናጋፋው ኢህአፓ እንኳን አድርጎት አያውቅም ነበር። ባለፈው ዓመት ያዬሁት ደግሞ ያን መንፈስ ሙሉ ለሙሉ የለወጠ፤ የሻረ አዲስ አስተምኽሮ ነበር። በውህደቱ ወይንም በጥምረቱ ዕለት የተገባ ነው። ከዛ ባለፈ ግን አዝላችሁት ዙሩ ዕዳ እስከ አራጣ ክፈሉ ነው። ተደጋግሞ ነገረ ሌንጮ ለታ እንደ አትራፊነት ስለሚገለጽ እግረ መንገዴን ንጹሑን ዕውነት መናገር እሻለሁ። ይህስ ዘመነ መሳፍነትነት ነገ ሳይሆን በነፃ ተሰደን ከምንኖርበት ሀገር እንኳን ሰላማችን እዬቀማ መሆኑ ለእኔ እና ለመሰሎቼ ምን ሊባል ይሆን?

በሌላ በኩል ወደ ነገረ አባዱላ ስመጣ በጫናም፤ በግፊትም፤ በራስ አነሳሽነትም ይምጣ፤ እንደ ሥርጉተ ዕይታ እንደ አንድ ተጨማሪ ሃይል፤ ጉልበትና አቅም ሊታይ ይገባዋል ባይ ነኝ። ከፋይዳ ውጪ ተደርጎ ሊታይ አይገባም። ከፋይዳ ውጪ ተደርጎ የተጻፉ ጹሑፎችንም ስላነበብኩኝ። አንድ ሰው አንድ ብቻ አይደለም የሥራ መልቀቂያ ያቀረበው። የእሳቸው ደጋፊዎች ሁሉ ፍቺ እንደ ፈጸሙ ይሰማኛል። ጋዜጠኛ ኤርመያስ እንዳሰረዳን ከሆነ በተለይ የማደራጀት አቅም ላለው ሰብዕና የእሳቸውን ከሥልጣን መውረድ እንደ ወረደ መተርጎም የሚገባም አይመስለኝም። ማደራጀት ሳይንስ ነው። ሳይንሱ ደግሞ አጥር ቅጥር መስራትን መሠረቱ አድርጎ ስለሚነሳ አቅም ያለው የመንፈስ ሃብት ነው። ግብረ ምላሹ ምንም ይሁን ምንም ሙቀት ፈጣሪነቱን በአግባቡ ተጠቃሚ ለማድረግ፤ እርምጃውን አቅሎ ሳይሆን አክብሮ መነሳት ያስፈልጋል። አንድ ሰው ብዙ ነው። የእኔ የተግባር ንግሥት ተዋናይት መቅደስ ፀጋዬ አንድ ነፍሷን ምን አቅዳ ምን እንደ ከወነች ያቺ ቀንበጥ አይተናል።

በዬጊዜው የሚነሱ አንቀሳቃሽ ሃይሎችን ከረጅም ፍላጎታችን ጋር የግድ እንደ ስሚንቶ ካልተጣበቁ ብለን እውቅና መስጠትን ከነፈግነው የነገ አዳር ኪሳራ ይሆናል። ድልድይነቱም ያነክሳል። ተስፋነቱም ይሻክራል። አብነቱም ይንሳፈፋል። ስለዚህ እነኝህ ሂደቶችን እንደ ተፈቀደላቸው ወቅትና ጊዜ እንደ ሃይል አቀንቃኝ አድርጎ፤ አቅማቸውን ለመጠቀም መሰናዳቱ ይበጃል። ያው የእኛ ነገር ይመጣል ብሎ የሚተነብይ፤ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ አስቀድሞ የማዬት አቅም ስሌለን፤ በደራሽ ገፊ ሃይሎች ብቻ ስለምንባትል ነው እንጂ ይህ አቅም ማሰቀመጫ ባንክ ቢኖረን፤ የአቅም ጥሪቱ ትክክለኛ ቦታ ላይ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን፤ በአግባቡ እና በቅጡ መምራትም በተቻለ ነበር። ለዚህም ነው ሰክን ያሉ ኢትዮጵውያን ሙሁራን ፖለቲካ ሳይንስ ነው። ፖለቲካ ፍልስፍና ነው እያሉ የሚያስተምሩን። ብናዳምጣቸው ለዚህ ጊዜ የሚሆን መጠለያ አስቀድሞ ይኖረው ነበር ይህ ያልተጠበቀ፤ ያልታቀደ አቅምን  በአግባቡ ቢያንስ በመንፈስ ለማስቀመጥ እንኳን። የኢትዮጵውያን የ26 ዓመታት የመስዋዕትነት አቅም እኮ አንደ አባይ ወንዝ ባለቤት አልባ ነው ሲፈስ የሚታዬው ….. ልብ ይስጠን። አሜን!

ይህ ሲባል ዘመነ መሰፍንት ህልም ያላቸው ሊኖሩ አይችሉም ማለት ባይቻልም፤ ከዚህ መንፈስ እና ዕሳቤ ጠንክር ያሉ ምልክቶች ግን ታይተዋል። ከዘመነ መሳፍንት መንፈስ ያፈነገጡ። ለምሳሌ የአማራ ህልውና ተጋድሎ አብዮት የነረን፤ ያስተማረን ብልህነት ነበር። „በቀለ ገርባ መሪዬ“ ብሎ ነበር የወጣው። „በዬትኛውም የሐገሬ መሬት የሚፈሰው ደም ደሜ ነው“ ብሎ ነበር የተነሳው። አቅም የለም ይህን ድንቅ አቅም ከልብ አድምጦ በጥበብ፤ በሥርዓት ማስተዳደር የሚችል። ፉክክር ነበር የታዬው። ምራቁን የዋጠ የበሰለ የአመራር ክህሎት አልተገኘም። ያን ያህል ደም የተገበረበት አብዮት ባክኖ እንዲቀር ተበዬነበት። ህዝብ አቅም ያለው ከልቡ ሊገባ የሚችል አዲስ ፈር ቀያሽ እረኛ ወይንም ሙሴ ይሻል። ህዝብማ ከዛ በላይ ምን እንዲያደረግ ይሆን የሚፈለገው። ትዳሩን፤ ቤቱን፤ ልጁን ገበረ እኮ ካለ አንድ አይዞህ ባይ። ካለ አንድ ደጋፊ። ዘጋርድያን እኮ ሰሞናቱን ሲዘግብ ጎንደርን ሚዲያ የሌላት ከተማ ነበር ያለው። ከፍላጎታችን ጋር መተላለፍ ልማድ የሆነብን እኛው እንደዛ ያን የመሰለ የታሪክ ማህደር መስዋዕትነት ዕወቅና ነስቶ አቅሙ ተበተነ፤ መስዋዕትነቱ ባክኖ አንዲቀር ተደረገ። በወቅቱ ለጊዜያዊ ፖለቲካ ትርፍ ሳይሆን፤ ለዘላቂ ፍላጎት በታማኝነት ቀበቶ  አቅሙን በአቅም መምራትና ማስተዳደር ያስፈልግ ነበር። የህዝብ ፍቅር እኮ ገብያ ላይ አይገዛም፤ ወይም አይቀናም።

ቢያንስ አሁን ደግሞ ባለው ዕውነት ላይ የተመሠረተ አቅማዊ የሆነ ግልጽ ፖሊሲ ያስፈልጋል። መቼም ዓይን መጋረጃ ተስርቶለት መንገድህን ዕወቀው ማለት አይቻልም። ጠንቋይ የሚቀልብ የለም እና። የማይታወቁት፤ የሚታወቁት በጥበብ ልቅናቸው፤ በተግባር ብቃታቸው ነው። የስንት ጊዜ ታናናሾቻችን በአቅማቸው፣ በሥራቸው፤ በሚከውኑት መልካም ቅናዊ ቀና ነገር እኮ ነው ንጹሑን ልብ እዬሸለምናቸው ያለው። የኔታ የምንላቸው። ጉልበት ያለው ተግባር ህሊናን ይገዛል፤ ይመራል፤ ይነዳል። ከቁስል የተነሳ ዕውነተኛ አጽናኝ መሪ ህዝብ ይሻል። ወቅትን መተርጎም የሚችልም አዲስ መዝገበ ቃላት የሚያስፈልገን ይመስለኛል። በአውሎ ደራሽ ወጨፎ ፍላጎቶችን ይማራን ከማለት ቢታደገን … 
  • በውይይቱ ያልተነሳው ጉልበታም አቅም።

በሌላ በኩል መሪን ጋዜጠኛ ኤርምያስ ለገሰ እንዳለው ሂደት ይፈጥረዋል። ይህ እንደ ተጠበቀ ሆኖ መሪ የለም ብለን ማሰብ ደግሞ ያለብን አይመስለኝም። መሪዎች አሉ። ካቴና የተፈረደባቸው። የታሠሩት መሪዎች አይደሉምን? ዶር መራራ ጉዲና በዕውቀት ላይ በተመሠረተ፤ ልማዳቸውና አቅማቸው፤ በሞራል ላይ ሰፊ ተመስጦ ያላቸው አቶ በቀለ ገርባ መሪ አይደሉንም? በብሄራዊ አንድነትና ልዑላዊነት ጽኑ አቋም ያለው ትንታጉ አንዱአለም አራጌ መሪ አይደለምን? በማደራጀት ህይወት ውስጥ የሰከነ አቅምና ብቃት ያላቸው አቶ አንደርጋቸው ጽጌ መሪ ለማሆን ምን ያንሳቸዋል? በሚዲያ እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ እነ ጋዜጠኛ ውብሸት፤ እነ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አቅም መሆን ያነሳቸዋልን፤ በመከላከያ አነ ኮ/ ደመቀ ዘውዴ በመፈንቀለ መንግሥቱ የታሰሩት መኮነኖች …. በሴቶች ዘርፍ እነ ወ/ሮ እማዋይሽ እነኝህ ሁሉ አኮ መከራውን የተጋሩ፤ እንደ ጥንቸል ሁሉንም የጭካኔ ዓይነት ሙከራ የተደረጋባቸው ዓራት ዓይናማ የትውልድ ፈርጥ እኮ ናቸው።

የተወሰነ ክፍተት ቢፈጠር እስረኞች ካለምንም ቅደመ ሁኔታ ከእስር ይለቀቃሉ፤ በመከራና በአሳር ተቀቅሎ የበሰለው ዬተመክሮ አቅማቸው የነፃነት ነፍስ የጀርባ አጥንት ይሆናል። ኢትዮጵያ ውስጥ በአስተሰሳቡ ምክንያት የስቃይ ደበሎ ተሸካሚ መሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይሞታል። ስለምን? ኑሮው አይተውታል እና። ይህን የሰቆቃ የበቀል ኮሶ ለወገናቸው መልሰው እንደማያቅዱት እኔ በግሌ አስባለሁ። እነኝህ ወገኖች  በአንደም በሌላም ከህዝብ ጋር ኑረው ስቃዩንና መከራውን በቅርብ የታገሩ፤ ስደትን አጥብቀው የተጸየፉም አሉበት እኮ፤ ነፍሳቸውን ለበለሃሰብ ፈቅደው ወደ ሞት የገሰገሱ፤ እራሳቸውን የሰጡ የጥምር ብቃት ብሄራዊ ጀግኖች ናቸው።

በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሄኛው ፓርቲ ወይንም ያኛው አይደለም። ሁሉንም አሳታፊ ሥርዓት እንዲዘረጋ መደረጉ ብቻ ነው የሚያስፈልጋት። ከቻለ ወያኔስ ስለምን ተፎካካሪ ሆኖ አያዬውም። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባምን ሥልጣን ላይ አስቀምጧቸው የነበረው ሥርዓቱ ስለተዘረጋ ብቻ ነው። ሥርዓቱ ከተዘረጋ፤ ህዝቡ ዕድሉ ከተሰጠው የሚመርጠውን ያውቃል። አንድ ብቻ  አውራ ፓርቲ ለኢትዮጵያ የመፍትሄ መንገድ አይደለም። ይሄ የሶሻሊዝም ጉድጓድ፤ ጎድጓዳም ቅኝት ነው። የመፍትሄ መንገድ ፓርቲዎች እኩል፤ ካለ ተጽዕኖ ተፎካክረው በሚያገኙት ነፃ መንገድ ተልዕኮቸውን ማሳካት ነው። ሲያጠፉ፤ ህግ ሲተላለፉ ደግሞ ህዝብ ማውረድ የሚችልበት ሥርዓት መዘርጋት ነው ያለበት። ሚዲያዎችም ማበረታት ያለባቸው በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ነው መሆን ያለበት። በጭነት የሚሆን ነገር የለም። የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ ሩቅ፤ ብልህ፤ ቻይ፤ ጨዋ ህዝብ ነው። ዕድሉን ካገኘ የሚመርጠውን እራሱ ያውቀዋል። ተምክሮው ዝቀሽ ነው። ምርጫን እንደ ዕመነቱ ነው የሚያው። ስለሆነም ሙሉዑ ተሳትፎ ነው የሚያደርገው። ጀማሪ አይደለም የኢትዮጵያ ህዝብ። መተንፈሻ ቧንቧ ከተገኘ መከላከያው ሆነ ደህንነቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም አስከባሪ ሊሆን የሚችልበትን መስመር ለመዘርጋት ይቻላል። የመዋቅር ለውጥ ከሥነ - ልቦና ለወጥ ጋር ማዋደድ - በቃ። ግን የተገኙትን ዕድሎች በአግባቡ ማሰተዳደር፤ መምራት ከተቻለ። „ሀ“ ሳይባል „ለ“ አይባልም ….
  • የሐገር ቤቱ የትውልዱ የአቅም ልክ።     

 …. ከዚህ በላይ ሐገር ቤት ያለው በተለያዬ ሙያና ክህሎት ያለው መንፈሱን በአቅምነት የማሰለፉ ነገር ትውልዱ እጅግ የላቀ እና ብልህ ነው። ከምናስበው በላይ የተለዬ ትውልድ ነው። አምሰማቸው ፍልስፍናዎች እጅግ የሚገርሙ ናቸው። ብዙሃኑ የወሰነበት ወጣት ብቃቱን በማዬት፤ የብዙሃኑ ውሳኔ ሊጫናው አይገባም ሲል „የማለዳ ኮከቦች የዳኞች ጉባኤ“ ሰኞ ዕለት ወስኖ በሰጨኝ ሃይለእዬሱስ ለቀጣዩ ውድድር አለፈ።  ይህ ፍልስፍና … ብዙሃኑ ቢያሸንፍ እንኳን ተሸናፊው ሃቅ አስካለው ድረስ እንደ ገና ዬሃቁ ጭብጥ ሊመረመርለት ይገባል ነው የእነ ፍጹሜ ፍልስፍና። ሌላው ደግሞ በቡድን ደረጃ ማለፍ ቢኖርም፤ ጠንካሮችን ተጠልለው ደካሞች ማለፍ የለባቸውም፤ ከተሸናፊው ወገንም ለተሸናፊዎች መሸነፍ ምክንያት የሆኑት ተነጥለው መቅረት፤ ጠንካሮች ነጥረው መቀጠል አለባቸው። ይህቺ ፕላኔት ይህን መስል የርትህ አደባባይ ፍልስፍና መቼ ይሆን ግሎባላይዝድ የምታደርገው ያሰኛል። ምንአልባት በ22ኛው ምዕተ ዓመት ይሆን? ይህን ይመስላል ጥልቁ አዲስ ትውልድ … ሐገር ቤት የመንፈስ አቅም ለዛውም ሃቅን፤ ዕውነትን፤ ሚዛንን፤ እጅግ በበዛ፤ በሚመስጥ ቅንነት የተቀመመ፤ ትህትናን ማዕከል ያደረገ … ሥልጡን አቅም አለ። ይሄ በዴሞክራሲ ሥነ - ፍልስፍና ሂደት የትኛውም ፓርቲ የማይፈቅደው ነገረ ረቂቅ ብቃት ነው …. ክህሎቱ ልዑቅ …  
ስለሆነም በብዙ ዘርፎች ያለውን ክንውን ስመለከተው ተስፋ ሰጪ ክህሎት አያለሁ። የመንፈስ ጠንካራ ጥሪት በትክክል ሐገር ቤት አለ። በሌላ በኩል ለማማሳከሪያነት አንድ ልከል። የዚህን ዓመት የግሼን ደብረ ከርቤ መንፈሳዊ ጉዞ ግብረ ምላሽ፤ ቃለ ምልልስ አዳምጬው ነበር። የእኔ እመቤት የቅድስት በረከቱ ይድረሰኝ ብዬ። ይገርማል። አንድ ከትግራይ የመጣ ወጣት „ግሼን ለእኔ ከላሊበላም፤ ከአክሱምም“ ይበልጥብኛል ሲል ነው ያዳመጥኩት። ይህ ወጣት „የታላቋ ትግራይ ህልመኛ“ አይደለም ማለት ነው። በተጨማሪም እንደ እሱ የሚያስቡ ወጣቶች እንዳሉ የሚያመለክት ናሙና ነው ይሄ በራሱ - ለእኔ። በተያያዘ ሁኔታ ከወለጋ፤ ከአርሲ የመጡ ማህበረ ምዕመናንም መሰል ንጡህ አቋምና መንፈስ ነው ያላቸው። ምዕመኑ የአማራ ቴሌቪዢን ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያን ከነ ሙሉዑ ዕሴቷ፤ ከእኛነት መንፈስ ጋር በህሊናቸው መቅደሳቸው እንዳደረጉ ነው እኔ የታዘብኩት። ከዚህ ባለፈ የአንድ ዕመነታዊ ወይንም ሃይማኖታዊ ቅርስ፤ የሐገር እንጂ የአንድ ዕመነት ወይንም ሃይማኖት ብቻ አለመሆኑንም አብክረው ሲገልጹ አዳምጫለሁ፤ ይህም የእስልምና ሃይማኖት ዕምነት ወገኖቻችንም ውስጥ የማደረግ አቅም እና ብቃት ነበር እኔ ያዬሁት። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝቡ እራሱ ለራሱ ማንነት ጉልበት ለመሆን ከእኛ በተሻለ፤ እጅግም በለማ ሁኔታ የእናት ሀገሩ አቅም የመሆን ክህሎቱ ረቂቅ መንፈስ ነው ለእኔ። መንፈስ ቅዱስ የረበበት።

1 ሚሊዮን ህዝብ በላይ የተገኘበት የግሸን ደብረ ከርቤ በዓል አከባበር ልዩ ዝግጅት „


ስለዚህም ፍላጎታችን ወጣ ገብ ባናደርገው መልካም ነው። ዋናው ነገር መተንፈሻ መገኘቱ ነው። ምክንያቱም እምንመካበት፤ በእጃችን ያለ ተጨባጭ አቅም የለንም። ይህን ሃቅ ቢመረንም እንዋጠው። አስተሳሰባችን እንኳን ብቁ አቅም እንዲሆን ወጥ ማድረግ አልቻልነም እንኳንስ ሌላውን ነገር። ይሄ ውይይት ለፖለቲካ ሊሂቃን፤ ሆነ የሐገሬ ጉዳይ ያገባኛል ለሚለው ያስተማረው ቁምነገር መደማመጥን ነው። ሃሳቦች በነፃነት ተንሸራሽረው የራሳቸውን ደጋፊ እንዲህ ያመርታሉ ማለት ነው። አሁን እኔ በዚህ የሐሳብ ጅረት ውስጥ ተመስጥዮ የጋዜጠኛ ኤርመያስ ለገሰ ዕድምታ ነበር። በበቂ ተዘጋጅቷል፤ ተጨባጩንም አድምጦታል። አቅማችንም በውል አውቆታል ብዬ አስባለሁ። በሌላ ዕይታ ሽምቅ ውጊያ አሁን ካለው የህዝቡ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ጋር የሚመጥን አይደለም። የህዝቡ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ከሽምቅ ውጊያ የብቃት አቅም እና ትርፍ በላይ ረጅም ጉዞ ቀድሞ ተጉዟል። በመደበኛ ውጊያ ቢታሰብ ደግሞ የዛሬ ስንት ዓመት? የሚቻል አይደለም። እንዲያው ቢታሰብ …. 
  • ፈቅ

ሌላም አደጋ አርቅን ብናስበው ሃይል የምንለውን፤ መጠጊያ የምንለውን ኤርትራ አያድርገውና መሪው ቢያልፉ፤ መሪው መፈንቅለ - መንግሥት ቢደርስባቸው፤ ወይንም ሃሳባቸውን ቢቀይሩ፤ ወይንም በአካል ጉዳት ሳቢያ ኮማ ውስጥ ቢገቡ ምን ይኮናል ብሎ ፈቅ አድርጎ ማሰብ፤ ማቀድ የተገባ ይመስለኛል። ከዚህም ባሻገር ውጪ ሐገር ምንም ደጋፊ የሌለው በዝምታ በቅምጥ ሃብትነት ያለው የቲፒዲኤም ጉዳይም በምን ሊመነዘር እንደሚችል አይታወቅም። የታመቀ ልሙጥ ነገር ነው። ወይንም ድንቡልቡል። ስለሆነም የሚታመነው በእጅ ያለ የእኔ በሚባል ወጥ የሥነ - ልቦና አቅም ሲኖረን ነው። ይህን ደግሞ ፍተሻውን ከራስ ጀምሮ አካባቢውን በማሰስ ግብረ- ምላሹን ሚዛን ላይ ማስቀመጥ ይቻላል። ማማረጥ የምንችለበት ጊዜ ላይ ያለን አይመስለኝም። ማማረጥ ለእኔ ዘመናይነት ይመስለኛል። የተገኘውን አክብሮ በሥርዓት ጥቅም ላይ የሚውልበትን ስልት ተግባብቶ መንደፉ ነው የሚሻል የሚመስለኝ።
  • የዕምነት ጽናት ይኑረን።

24 ሰዓት ያለማቋረጥ የሚጸልዩ፤ የሚፆሙ፣ የሚሰግዱ ዘመናቸው ሁሉ ሱባኤ የሆነ ንዑዳን አቨውም አሉን። እነሱ አኮ ከዚህ በገሃዱ ዓለም አለን ከሚባለው ማናቸውም የሠራዊት „በበቂ ሁኔታ ከነ ሙሉ መንፈሱ በመዳፋችን ካለን“፤ አለኝ የሚለው የወያኔ ሠራዊትም፤ ሆነ የደህነትነት መዋቅር በላይ የፈጸመ፣ የበቀለ አቅም ባለቤቶች ናቸው። በእስስልማና ሃይማኖትና በክርስትና ሃይማኖት እንደተጫረው እሳት፤ በዘመነ የትግሬ መሳፍንት፤ እንዲሁም አባሎቻቸው በሚታዬው የተዛባ አያያዝ፤ አድሎና፤ ግለት የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እና ኢትዮጵያ የምትባል ሐገር እኮ ጨርሶ የምትጠፋ ሐገር ነበረች። ኢትዮጵውያነት እኮ በትክክል የመቻቻል ተቋም እኮ ነው። አሁን ያለው በዬቦታው የሚደመጠው አንዱ ጎሳ በሌላው ላይ የማነሳሳት ሂደት አኮ እሳት አኮ ነው። ቤንዚን እኮ ነው። ይህን ሁሉ አቻችሎ፤ አመዛዝኖ እንዲሄድ የሚረዳው በክርስትና እና በእስልምና የሃይማኖት አባቶች ያለው ያልተቋረጠ ወደ እግዚአብሄር የማመልከት ተደሟዊ ዬቅኖና ጊዜ ነው። እሱንም ከግምት ማስገባት የሚገባ ይመስለኛል።
  • የአቅም ምንጭ ህዝብ ብቻ ነው።

ሌላው አቅም ፈጣሪው ህዝብ ነው። የህዝብ አቅም ደግሞ በሚዲያ፤ በፖለቲካ ድርጅቶች ማንፌስቶ ወይንም በወታደር ሃይል የሚበቅል አይደለም። ችግር፤ መከራ፤ ዕንባ፤ ሰቆቃ፤ ባይታዋርነት፤ ራህብ፤ ጥማት፤ ስደት፤ ግለት፤ ባይታዋርነት፤ አድሎ፤ ጉስቁልና መጋፋት የሚፈጥረው ነው። ዛሬ ላለው የበቃኝ ሙቀት ባለቤት አለ ቢባል ዕለታዊ ችግርና መከራው ብቻ ነው። የበቃን ትጥቀና ስንቁ ዕንባ ብቻ ነው። በዚህ ዙሪያ ለዚህ አቅም የባለቤት ጥረቱን፤ ጥሪቱን በፉክክር ከማቅለም ዕውቅና ሰጥቶ ታሪክ ሰሪነቱን ደፍሮ መመስከር፤ ደፍሮ ማክበር፤ ደፍሮ ከህዝብ የበቃኝ አቅም በታች፤ ከሥሩ ሆኖ ለመተዳደር መፍቀድን በአጽህኖት ይጠይቃል። ይህን ማድረግ በራሱ አንድ ልቅና ነው። አንድ ታላቅ ጥበብ ነው። ችግሩን የማድመጥ ብቃት ነው። በአጅ ያለ ሃብት የህዝብ አቅም ብቻ ነው። ጦሩም ጋሻውም የበቃኝ መከራው ብቻ ነው።  ወፍ አውጥቷቸው ይህን ችግር አድምጠናል፤ ገብቶናል፤ የሚፈረድብን ፍርድም በህዝብ አደባባይ ከህዝባችን ጋር ሆነን እንደ አንድ ተርታ ዜጋ እንጋራለን የሚሉ ሲመጡ ደግሞ እንኳን ደህና መጣችሁ ማለት ይገባል። ወቀሳ ለነፃነት ትግል ስንቅ አይሆንም። ስንቅ የሚሆነው አቅሙን ለአቅም ለማዋል ጥበባዊ አያያዝ ሲኖረን ብቻ ነው። 
  • ቅብዕነት።

የመሪነትን ቅብዕነት ብዙ ሰው ይዘለዋል። መዝለል የለለበት ጉዳይ ነው። የፈለገ አቅም ቢኖር፤ የፈለገ ዕውቅት ቢኖር፤ የፈለገ ተመክሮ ቢኖር፤ የፈለገ ንብረት ቢኖር መሪነት ቅብዕነት ነው። የተቀባ ብቻ ነው መሪ መሆን የሚቻለው። ለቅብዕነት የተመረጠ ሰው ጊዜው ቢረዝም፤ ሁኔታዎች ቢመሰቃቀሉም፤ ጉዞው አታካች ቢሆንም የተቀባው ሰው ሲፈቀድለት መሆኑ አይቀሬ ነው። አሁን የአሜሪካው ህዝባዊ ምርጫ ዴሞክራቶች ለሌላው ተፎካካሪ ዕድሉን እንዳይሰጡ እንቅፋት የነበረባቸው ምክንያቱ ቅብዕው ለፕሬዚዳንት ትራንፕ የተሰጠ ጸጋ ስለነበር ብቻ ነው እንጅ፤ በዛ ሁሉ የፖለቲካ ትርም ውስጥ ካሉ የዴሞክራት ተወዳዳሪ ይልቅ አቋራጩን የጠራ መንገድ፤ ወጣቱ መሉ መንፈሱንና ህሊናውን የሸለማቸውን ሌላው የዴሞክራት ተወዳዳሪ ቢከተሉ የተሻለ ዕድል ይኖራቸው ነበር ዴሞክራቶች። ስለዚህ ቅብዕ ስለተፈለገ፤ ስለታለመ፤ የሚሆን አይደለም። ፈቃደ እግዚአብሄር ነው። የተቀባ ሰው ካለ ማንም፣ ምንም አያግደውም፤ ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢል አይቀርም። ካልተቃባ ደግሞ በተፈለገው ስሌት ቢወጣ እንኳን አይበረክትም። ይልቅ አቅምን ለመምራት ጥበበኛ ከመሆኑ ላይ ቢሆን ብልሃቱ መልካም ነው፤
  • መከወኛ።

ኢትዮጵያን ለማዳንም መንገዱ ከወንበር ስሌት እና ቀኖና መውጣት የሚገባ ይመስለኛል። የሃሳብ ጅረቶችን ከዚህ ፍላጎት ማዕቀፍ በጣም በራቀ ሁኔታ ማስተናገድ ይገባል። ሐገርን ለማሰብ የእያንዳንዱ ዜጋ በነፍስ ወከፍ ግላዊ ነፃነቱን …. አለመጫን …. ማሰሪያ አለማበጀት፤ ማሸማቀቂያ አለማሳናዳት  …. ያስፈልግ ይመስለኛል። ይብቃኝ።
ወገኖቼ … እንዲህ በቅርብ ቀን ልጽፍ አላሰብኩትም ነበር። ማድመጡ ይበልጥ ያስተምራል፤ ከመሳተፉ። ብቻ ውይይቱን ሳዳምጥ ለመሆኑ እኛ ምን ይሆን የምንፈልገው ብዬ እራሴን ፈተና ላይ አስቀመጥኩትና … ተጣፈ እላችሁ-አለሁ።
ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።

„ፍቅር የሽንፋል“

መሸቢያ ጊዜ። ደህና ሁኑልኝ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።