„ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“
„ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“
የብላቴ ጌታ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን
ንዑድ መንፈስ - ትንሳኤ ነው።
እኔም እላለሁ …. ኢትዮጵያዊነት እልልታም ነው። ኢትዮጵያዊነት ማግኔትም ነው። ዋዜማ!
ከሥርጉተ - ሥላሴ (Sergute©Sselassie)
05.11.2017 (ሲዊዘርላንድ- ዙሪክ)
05.11.2017 (ሲዊዘርላንድ- ዙሪክ)
ማህላ ምህላ ነው። ምህላም ማህላ ነው። ማህላና ምህላ አደራም ናቸው። ማህላና ምህላም የጎለጎታ ውልም ናቸው። የቃል ዕዳ። የተከበሩ አቶ ለማ መግርሳ አደራችን ጥልቅ መሆኑን ትንሽ ቀንጨብ አድርጌ ልግልጽለዎት ፈለግሁኝ። እንሆ ተጨማሪ አደራም ይቀበሉኝ ትላለች ስደተኛ እህተዎት ሥርጉተ - ሥላሴ። አደራ መንፈሰዎትን ከማህበረ ደራጎን ጋር አለካልከው አንገታችን እንደገና እንዳያስደፉት። በዛው ሥርዓት ውስጥ ስቼው ግን አይደለም። ብቻ ለታማኝነታችን ታማኝነተዎትን በአፅህኖት እንሻለን። በዘመነ ማህበረ ደራጎን የአንድ ቅን ሰው ራህብተኛ ነበርኩ - እኔው። አሁን ምኞቴ … መንገድ ላይ ነው …
- እንደ እፍታ ….
በ2015 እአ.አ በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ጸሐፊ ለነበሩት፤ ለአውሮፓ ህብረት ፕሬዚዳንትም፤ ለቀዳማይ የሐገር መሪዎች፤ እንዲሁም በሰብዕዊነት ጉዞ ላይ ነፍሴን ለገዟት ፋውንዴሽኖች የበደሉ ሁሉ መሠረት፤ የስጋቱ ሁሉ ምንጭ የዓለም ዜጎች ስለ ፍቅራዊነት ተፈጥሮ መርህ በት/ቤት ደረጃ ስላልተማርን ነው። ልክ እንደ ሂሳብ፤ እንደ ባይወለጂ። የፍቅር ተፈጥሮና መርህ በፕላኔታችን ራሱን ችሎ የሚመረቁበት ሙያ አይደለም። የፍቅራዊነት ኤክሰፐርቶች፤ ሳይንቲስቶች፤ ተማራመሪዎች ዓለማችን የላትም። ሌላው ቀርቶ ዓለም ዐቀፍ የፍቅራዊነት ቀን፤ ሲምፖዚዬም፤ ሙዚዬም፤ ኮነፍረንስ እንኳን የለንም። ፍቅር በተለምዶ እንጂ በዕውቀት በተመሰረተ ሳይንስ አልተጠበብንበትም። „ በአንድም ሀገር የመቻቻል፤ የመከባበር፤ የቅንነት፤ የትዕግስት፤ የትህትና ወዘተ በዚህ ሥያሜ የሚጠሩ አንድም ት/ቤት የለም። ስለዚህም ለፍቅራዊነት ተፈጥሯዊ መርህ የትምህርት ሥርዓት መንደፍ ብቻ ሳይሆን እንደ ዋንኛ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ መመዘኛ መሆን ይገባዋል፤ ፍቅር ሳይንስ ነው። ፍቅር ፍልስፍና ነው። ፍቅር ሥነ -ጥበብም ነው። የሚል መሠረታዊ ጽንጸሰ ሐሳቦችን የያዘ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ ክንውኖችን ያካተተ ቅን ዕሳቤን ላኩኝ። አብዛኞቹ መልስ ጽፈውልኛል። የቀደሙት የዓለሙ የሰብዕዊነት መሪ መቼም እሳቸውም የተባረኩ ናቸው መልስ ጻፉልኝ። የሚገርመው ፖስታውን እኔ ስልከው አድርሻውን ስጽፍ በእጅ ጹሑፌ ነበር። እሳቸውም መልስ ሲልኩልኝ አድራሻዬን በእጃቸው ጽፈው ነበር። እንዴት ያምራል መሰላችሁ የእጅ ጹሑፋቸው። የቁም ጹሑፍ ነው የሚመስለው። ፖስታውም አለ ከእጄ። እና ጉዳዮን ለፖሊሲ አውጪዎች እንደሚመሩት ገልጸው በሐገሬ መንግሥት ቢጀመር መልካም እንደሆነ ምክር ለግሰውኝም ነበር።
ከዚህ ካሉት ሲዊዛዊቷና ጀርመናዊቷ ጓደኞቼ ጋር በመሆን በጋራ መከርንበት። እነሱም ያውቃሉ ምንም መንግሥት እንደሌለኝ። የዕንባችንም ተጋሪዎች ናቸው - ሁለቱም። ብቻ ጥረቴን ቀጠልኩኝ። አሁን እግዚአብሄር ፈቅዶልኝ እረድቶኝም፤ ያው የፋሲካ ዕለት ለእኔ የዕንባ ቀን ነው። ሐገሬ ትናፍቀኛለች። የራሴ ሰዉ ይናፈቀኛል። የምሳሳለት የተግባር ጀግን ፍጹሜ አስፋው „ሐገር ማለት ለእኔ ሰዉ ነው፤ የራስ ሰው“ ያለው ዕውነት ነው። እናም መከፋቴን መዳህኒተአለም አይቶ የዕለተ ፋሲካ ለመነሻ የሆኑ አዎንታዊ አነሳሽ ቃሎችን self and gelobal awareness ሊፈጥሩ የሚችሉ ቃሎችን ብቻ የሚያስተናገድ የመጀመሪያውን የፍቅራዊነት ፖስተር ቻናል ጀምሬ እየሠራሁ በሥሜ ካለው ዩቱቤ ላይ አስቀምጣለሁ። ይቀመጥ። አንድ ቀን ፈንጠቅ ሲል እኔ እንኳን ብሞት አንድ ሰው መርሁን ቢከተለው፤ ለመነሻነት ያገለግለዋል በማለት። ቢሳካ ይህ ግራጫማ ዓለማችን መልክ እንዲኖረው ይሆናል። ሰው ሲፈጠር ክፉ - ምቀኛ - ቀናተኛ - አግላይ - ሰው ጠይ - ተፈጥሮን ተዋጊ - ጨቋኝ፤ ትዕቢተኛ፤ በቀለኛ፤ ዘራፊ፤ ገዳይ፤ ሆኖ አልተፈጠረም፤ ከተፈጠረ በኋዋላ ነው እነኝህን አጥፊ ባህሪዎች የሚማረው … እና የቀድሞውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጸሐፊ የተናገሩት ትዝ ያለኝ መንግሥት ያለኝ መስሏቸው ነበር ያነ ጊዜ „በሐገርሽ መንግሥት እንዲጀመር እስክ ላኪላቸው ብለውኝ የነበርው“ ይህን ቃል ስሰማ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“ በቀጥታ በውስጤ ሰተት ብሎ ገባ። ጥላቻን ከሥሩ የሚደረምስ ነውና። እናም ወደፊት ምንአልባት ኢትዮጵያ ላይ የመጀመሪያው የፍቅራዊነት ሥርዓተ - ትምህርት ይቀረጽ ይሆናል። ኢትዮጵያ ቀዳማይት እምቤት ናት እና …. የድንቅነሽ ማህጸንተ ወርቅ። አብነት - አርያዊት። እስቲ በህይወት ከኖርኩኝ ቀኑ ሲደርስ ጽንሰ ሀሳቡን በግል ለሳቸው እልክላቸዋለሁ።
- እንደ መንደርደሪያ …
ባለፈው ዓመት የብላቴ ጌታ ሎሬት ጸጋዬን በሥጋ መለዬት መታሰቢያ በማድረግ አንድ ጹሑፍ ጽፌ ነበር። ያው በዬዓመቱ እንደማደርገው ሁሉ። ብሩኩ ወንድሜ ሳተናውም ተባብሮኝ ለጥፎልኝ ነበር። ሌሎችም ለዜግነት ድንበር ያልሠሩሉት፤ ሐሳብን በነፃነት በመግለጽ እረግድ በእጅቸው በሚገኘው ነፃነት ላይ ማዕቀብ ያልጣሉት ወገኖቼም ተቀባብሎው በዬፔጃቸው ለጥፈውታል። ቅን ወገኖቼም በማህበራዊ ሚዲያ ተረባርበውበታል። ፍላጎታቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁት። አጋ ያለዩት። አማራጭ የመንፈስ ማረፊያ ሚዲያ ማለትም ይሄው ነው። የወል ራዕይ የሚባለውም ይሄው ነው። ፈቅዶ መንፈስን እግር ከወርች አለማሰር … በሴራ አለመተብተብ … ጠቃሚውን ነገር ከማንም ከዬትም ይሁን ከውስጥ መቀበል፤ የእኔ የማለት … የሁላችንም የማለት … አቅምን በአቅም የመጋንባት ….
ወደ ቀደመው እንደ አቨው ስመለስ „ኢትዮጵያዊነት ማለት ጸጋዬ ገ/መድህን ማለት ነው። አፍሪካዊነት ማለትም ደግሞ ጸጋዬ ገ/መድህን ማለት ነው።“ ይል ነበር ርዕሱ። ዛሬ እንሆ ያን ራህብ ቁጭ ብዬ ከቤቴ ትንሳዔውን አዬሁት። እጅግ ይመስጣል። እጀግም ያጽናናል። እጅግም ይፈውሳል። እጅግም ጥግ ይሆናል። እጅግም ለነቃው የመንፈስ ክፍል ስንቅ ይሆናል። እጅግም ሩኽን ይቀድሳል። „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“ አሉን አቶ ለማ መገርሳ። ለእኔ ቃሉ በራሱ ቅብዕ ቅዱስ ነው የሆነኝ ሜሮን። በስንት ዘመን በራበኝ ይህን መሰል ውስጥነት በክኽሎት በላይ ላይ ዘልቆ ጣና ላይ ሰከነ። ግዮን ላይ ቆረበ። ፋሲል ላይ ተናኜ። ላሊበላን ሊይ ተጓዘ። ከዚህ ቅናዊ መንፈስ ለመድረስ እንጃ የትውልድ ያህል ርቀት ነበረው። ህልም ነገር ነበር። ኢትዮጵያዊነት ኬኛ። ኢትዮጵያ ኬኛ ግሩም ነው …. ሁሉም የእኛ። ሁሉም ኬኛ!
- እኔ እና „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“ ተቃቅፈን ተኛን።
ትናንት ማምሻው ላይ ይህን የብሥራት ዜና ሰምቼ ሰለነበር ለሽ ብዬ ተኛሁኝ። ተካስኩኝ ብል ይሻላል። የሬቻው እልቂት ቁስለቴን ለምድራዊ መሪዎች ብቻ ሳይሆን ለመዳህኒት - ዓለምም ፖሰታ ቤት ሄጄ አስከ አሰገበሁባት ደቂቃ ድረስ ከዕንቅልፍ ጋር ተፋትቼ ነበር። ከእህል ውሃ ጋርም። አምና መስከረምን ሸኝቶ ወርሃ ጥቅምት አንዴት ናችሁ የኔዎቹ ሲል ዕንባ የሚሊዮን ስለተቀበለው። በዘንድሮ ውርሃ ጥቅምት የትናንትናው እንቅልፌ ደግሞ የወደኩበትን ሳላውቀው ነበር ጥዋት የነቃሁት። ስነሳ ሸክሜ ሁሉ በአንድ ሌት ብን ይል ይመሰል ቀለል አለኝ። እንዲህም ለእኔም፣ ለባለቤት አልባዋ በመንፈስ ቅድስና የት ነው ያለሽው የኔዋ የሚል፤ አስሶ ውስጧን የሚያገኝ አጽናኝ - የራሴን - የነፍሴን ሥጋዬን ሳገኝ ስለምን ሃሳቤን ጣል አድርጌ ለሽ አልል። በዚህ አያያዝ ካለ ስጋትና ጭንቀት አብሮ አደጌን፣ ውሃ እዬተራጨሁ ያደግሁትን፣ ጓደኛዬን - ስስቴን - ዓለሜን ወላጅ እናቴም በህይወት ካለች ደውዬ ሃሎ የምላት ቀን ይመጣል ማለት ነው። የዛች መከረኛ ጎንደር ኖሪ በመሆኗ ሰቀቀን ላለመጨመር ድምፆን ካልሰማሁት ይኸው ድፍን አራት ዓመት ሞላኝ። እኔም በሰቀቀን ሃሳቤን ከመግለጽ እንዳልታቀብ በማለት። ለሁለታችንም የውስጥ ሰላም … ሲባል። ተስፋው እስተዚህ ድረስ ውስጥን በፍቅር ዳሰስ፣ በሙቀት ደበስበስ ያደርጋል። ጎንደርዬም ያልፍላት ይሆን?
ብቻ ሰሞናቱ ሃዘን ተፍሰሃ ድባብ ነበረው። ግን እንዴት ደስ ይላል። እንዴትስ ይደላል። እንዴትስ ይመቻል። እንዴትስ ይፈውሳል። እንዴትስ እረፍት ይሰጣል። እንዴትስ ስጋታን ድል ይነሳል። እንዴትስ መከራን ይታደጋል። እንዴትስ ሥርዬትን ይፈውሳል። እንዴትስ አዲስ ቀን ና ወደ እኛ ብሎ ይጣራል። እንዴትስ አማራጭ ብርሃን ይፈንጥቃል። እንዴትስ ሸክምን ያቃላል። እንዴትስ ይጥማል። ለእኔ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“ አሉ አቶ ለማ መግረሳ ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ የመጸሐፈ ቅዱስ ወንጌሌ ነው። ለዛውም ባለቤት በሌለው በተገፋው ህዝብ መካከል በአማራው ጉባዔ ቆመው። የበቃህ ዋዜማ ይሆን ለዛ አይሁዳዊ ኢትዮጵያዊ አማራ ….
አቤት! ቅጽበቷ ምንታምር፤ አቤት! የቃናው እፍታው እንዲህ ያለለት ምን ይዋብ፤ አቤት! ባለውጊዜ በባይታዋርነት ለተቀጠቀጠ መንፈስ ፋሲካ ሆነ። እንዲህ ትፍስት ከሰማይ ዱብ። አቤት! ይህቺ ቀን በስንት የምጥ ዘመን ደጋ - ቆላ - ቁልቁለት - አቀበት - ክረምት - በጋ - ሸለቆ - ሸንተረር ሀገይ - መኸር - ስንቱን አባጣና ጎባጣ፤ ስንቱን ስንጥርና ትርትር፤ ስንቱን ገደልማ ኮረኮንች፤ ስንቱን ሸካራማ አፋፍ፤ ስንቱን የበረሃ ግለት እና ወላፈን፤ ስንቱን በረዷማ አለት ተሻጋራ ብሥራተ - ዜናን አወጀች። ለእኔ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“ መጸሐፈ ቁራኔ ነው። አሁን በወቅቱ የምሻው ከትዕቢቱ ወረድ ብሎ አጽናኝ መንፈስ ብቻ ነበር። ይሄውና የኔው ራህብ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“ ደረሰ። መጣልኝ። በዚህ ሱስ የቁጥር ስሌት ውስጥ ሥርጉትዬም አለች ማለት ነው። በባይታዋርነት ከተቀጠቀጭበት ማሳ ቀና ትላለች ማለት ነው። … ይሁን ይሁን! - እሰይ እሰይ! - እልል - እልል! ብለናል እኔ እና አይታክቴ ብዕሬ ተብራና ሳተናው ጋር በወልዮሽ ሁነን ሐሤትን በዕሴት ሰናይት አህዱ አልነው … ዕለተ ሰንበትን። ተመስገን።
ይህ የተናፈቀ፣ ይህ በስስት የተጠበቀ፤ ይህ በናፍቆት የዋኜ፤ ይህ በትዝታ የቀለመ፤ ይህ በሽውታ የበቀለ፤ ይህ በኤዶም ገነት የተሞሸረ፤ ይህ በጽረኽ አርያም ትንፋሽ ያሸተ ቃል ለእኔ የህይወቴ መርኽ ነው። „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“ ራህብ - ጥማት የሆነው የቅናዊነት መንገድ፤ የፍቅራዊነት መንፈስ፤ የመቻቻል መርከብ ነው ለእኔ። ያ ድንቅ የጥበብ ሰው ነባቢተ ነፍሰ ቴወድሮስ ካሳሁን „ፍቅር ያሸንፋል“ ብሎ ስበከቱን ጀመረው። ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ደግሞ ክህነቱን በቆመስነት ባረኩለት። ተመስገን! ከዚህ በላይ እኔ ህልም የለኝም። ነገን እንደ ተፈጥሮዬ በንጹህ ቅንነት እና በድንግል እንዲሁም በአክብሮት ነው የምጠብቀው … ስለነገ ስጋት የለብኝም። የትውልዱ የነገ ጉዳይ ነፍሴን አንጠልጥሎ ሲያባዝተው ኖሯል፤ አሁን ግን ትንፋሽ አግኝቻለሁ … ኢትዮጵውያን በማይታዩ ረቂቅ የውስጥ ጉዳቶች የተጎዳን ነን። ውስጣችን በእጅጉ ተጎሳቁሏል። ልብሱ ጌጡ የላይ ነው። ውስጣችን ዕንባ የከተመበት ነው … ውስጣችን በሃዘን ብዛት የከሰለ፣ የጠወለገም ጥንዙል ነው። ተስፋችን ጥግ አጥቶ በተሰደድንበት እንኳን አይዞህ! አይዞሽን! ያጣን ምንዱባን ….ነን። እኔ እምጽናናው ሐገር ቤት አቅማቸውን በቅንነት ያስታጠቁ ወጣቶችን ትትርና ሳይ ብቻ ነበር። አሁን ደግሞ መሪ - አናት - ሙሴ እንዲህ ከች ሲል ስለምን አልፈንድቅ …. ስለምን እልልልልል አልል። እልልታውን አስነካው። ማን ከልካይ ሲኖርብኝስ ….
ስንት የባከኑ፤ ስንት አቅል ያጡ፤ ስንት መሠረታቸውን ስተው ያፈነገጡ ክፍተቶች፤ ሰባራ ሰንጣሮች፤ ስንት ራሳቸውን ያወኩ ትርትሮች መስመር ያዙ። አዎን! መሪን ሂደት ይፈጥረዋል። መሪን ዕንባ ይፈጥረዋል። በዛ ሰሞን በጻፍኩት ጹሑፌ በቴዲ አፍሮ ጉዳይ ላይ እኔ መፍትሄ ከሰማይ ነው የምጠብቀው ብዬ ነበር። ምክንያቱም ዝንቁ ነገር አይሎ በማዬቴ። የሚቀድመው ምናባዊ ስሌት ስሜታዊና የተንጠለጠለ ብቻ ሆነ ስለማዬው። ይህ ገድለኛ ቃል „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“ ይሄው ወደ እኔ ገሰገሰ … እራሃቤን ሁሉ አስታግሶልኛል። የውስጤን ሰላም አደላድሎታል። በሰላምም ለሽ ብዬ ነበር የተኛሁት። ተመስገን!
- ክህሎትን ስለነገ።
„ስንት የኦሮሞ ልጆችን በደህንነት ቢሮ እያሳደነ ያሰጨረሰ እንዴት ደርሶ ከዚህ የህዝብ የፍቅር ጣሪያ ደረጃ ሊደርስ ይችላል“ „እንዴትስ ማልያ ሊሆን ይችላል?“ ይባላል። ያን የመከፋት ዘመን የቆይታውን ጊዜ ሲያነሱት የሚንገሸገሹ እጅግም በብልጫ በልቤ በአክብሮት የጣፍኳቸው ወገኖቼን ተምልክቻለሁ። እንዲያውም ወያኔ „በያዘው ይዞ ይቀጥልም ቢመርም ብለዋል።“ አቅም የሚባለው አቅም አግኝቶ ክፈተቱን እሲኪሸፍን ድረስ።“ ለእኔ ይሄ የማልሸምተው ነበር። ሁሉጊዜ ታቱ ጊዜ መብላት የለበትም። ባለፈወም ጽፌዋለሁ አሁንም ልድገመው ቅብዕ የሰው ጥበብ አይደለም። ቅብዕ ጠብቀኝ እስከምጣ አይባልላትም። ሥልጣነ -እግዚአብሄር ነው። የተቀባ ሰው ካለ በፈለገ ሁኔታ ቅባውን ያገኘዋል - ቢዘገይም። „ሰው ያስባል እግዚአብሄር ደግሞ ይፈጽማል“ እግዚአብሄር ምህረት ሲልክ ከጸጸት ማህጸን ውስጥ ነው። ከቶ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስንት ጊዜ ነው ጌታውን፣ ፈጣሪውን፣ ክርስቶስን የካደው። እና በኋዋላ ደግሞ እንዴት ነው የቤተ ክርስትያን ጽኑ አለት፤ መሠረት የሆነው? ለወንጌል ዶግማ ተከታይ የምህረቱን አዋጅ ምድራዊ አድርጎ ሳይሆን ልክ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የምርቃት ወተት አድርጎ ሊመለከተው ይገባል ባይ ነኝ። አብሶ ለክርስትና ዕምነት ማህበረ - ምዕመናን ሚስጢሩን በዚህ መልክ መቃኘት ያለባቸው ይመስለኛል። መግደያ ባሩድ ያመረቱ፤ የፈለሰሙ ሰዎች ዓለማችን አፍርታለች። በመጨረሻው ግን የልዑቅ ፍጥረታት የተሰጥዖ የሽልማት ግሎባላዊ ማዕከል ሆነዋል። ያ ገዳይ መንፈሳቸው አዳኝ፤ አበረታች፤ አነሳሽ፤ አጽናኝም ሆኗል። ከሞት ወደ ድህነት ሰው ሰራሽ የእጅ ሥራ አይደለም። አምላካዊ ምርቃት፤ ታምራት፤ ገድል ነው። አብሶ ጸጸትን ለሰነቀ ሰማያዊ ምርቃት ገደብ አልተሰራለትም … ለደግነት - ለበጎነት - ለመልካምነት መሰናዳት ብሩክነት ነው። ግልጽነትን ለተዋበ መንገዱ ብሩኽ ነው።
ደግሞስ ‚ሀ‘ ሲባል በቅንነት መሆን ይገባል። ጅምር ከቀንበጡ ላይ ሊቀነበጥ አይገባውም። ጊዜ ሰጥቶ፤ አደብ ገዝቶ መሰከን በእጅጉ ያስፈልጋል። ሁሉንም አደብ ገዝተን እንዳዬነው ሁሉ። ዕድሉ ለሁሉ እኩል መሰጠት ይኖርበታል፤ ቅንነት ተሰንቆ። ዕንባ ላይ ተቀምጦ ሙቅና ቀዝቃዛ ማማረጥ ዘመናይነት ነው ለእኔ። „ልጅ የያዘውን ይዞ ነው የሚያለቅሰውና“ …. ከውስጥ ለተሰረዝነው፤ ለሌለነው ምን ያህል የውስጥ ፍላሎት፤ የውስጥ ጢስ፤ የውስጥ ነበልባል ለታቀፉ እንደ እኔ ላሉ ማህበረ ግፉዕን ማረፊያ ብጣቂ እራፊ መሬት እንዳልነበረን አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው። በውስጥ ለታቀፉት ብርዱ ላይሰማቸው ይችላል። የእኔ የሚሉት ተንከባካቢ አይዞህ/አይዞሽ ባይ አላቸው እና።
… አዬነው ሁሉንም … ታማኛነታችን „ታማኝነትን“ አለበቀለውም ክው አድርጎ አደረቀው እንጂ። አክብሮታችን „አክብሮትን“ አልፈጠረም እንጥፍጣፊ አልቦሽ አድርጎ አከሰመው እንጂ። … የዛሬን መከራ የሚፈታው የዛሬ ብልህነት ብቻ እንጂ ብልጥነት አይደለም። እኛ የተገፋን ኢትዮጵውያን ለከረባት እና ለገበርዲን የምርጫ ሞድ ቤት ልንክፍት አይገባም። የተመኘነው መከፈታችን በርትህ አደባባይ እንደ ሰው ራሱን ዝቅ አድርጎ በጣፈጠ ቅንነት የሚቀድስልን „ሰው“ ብቻ እንጂ። ሁሉንም በፈለገኝ ሰዓት ብቻ ሳይሆን በመንፈስ እስከ አለህበት ድረስ እኔ እራሴው ወደ አንተ እመጣ ዘንድ ዝግጁ ነኝ ማለት ነው „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“ ማለት። ከቶም አልጠግብህም ናልኝ ማለት ነው። ለነፍሱ ማረፊያ የክትና የዘወትር የማይባልበት ሰተት ተብሎ የሚገባባት የተስፋ በር ነበር ያመረን። ሽው - ትዝ ያለን እንደራሳችን ቅልል ብሎን እንደ እናት ጓዳችን ዘው የምንልበት ቅን መንፈስ ነበር - የናፈቀን። በራሳችን ውስጥ የበቀለ የውስጥ መሃንዲስ። በውጪ በማናቸውም ሃይልና ፈቃድ የማይመራ። ውስጣችን በውስጥነት የመተርጎም አቅም እና ብቃት ያለው ውስጥነት ነበር ራህባችን። እያንዳንዷን የፍቅራዊነት ሂደት የሚያነብ፤ የሚያተረጉምና የሚያመሳጥር የፍቅራዊነት መርህ ተፈጥሮ ምስባክ ነው አምላካችን እንዲሰጠን የተማጸነው። ሥነ - አዕምሮዊ ጥበብ ያለው። የናፈቀን ሥነ - ህይወትን እንደ ተፈጥሮው ክህሎት ከውስጥ የሚቀበል ነው። በአገላለጹ የማያሰከፋን፤ በአነጋጋሩ የማይጎረብጠን፤ በአወጋጉ የማይነጥለን፤ በምልከታው የማያገለን … በመርሁ የክትና የዘወትር የማይበይንብን … ንጹህ ልብ፤ ንጹህ ቅንነት …. እንደ ሰማይ የራቀን ይህ ነበር።
እኔ ትፍስህት ተሰምቶኛል። እኔ ሰናይ ተስምቶኛል። እኔ ፍሰክ ተሰምቶኛል። እኔ ህይወት ተሰምቶኛል። እኔ መኖር ተሰምቶኛል። የማላውቀው ሐገር አይናፍቀኝም። … ወይንም „የቆጡን አውርድ ብላ የብብቷን ጣላች“ መርሄ፤ መስምሬ እንዲሆን አልሻም፤ አልፈቅድምም። የፊት የፊቱን እንደ ጓያ ነቃይ ነው እምለው። የራህቤን ማስታገሻ እሻለሁ - እናፍቃለሁም እና … እንጀራ እርቦኝ ኬክ አያምረኝም። አቅም ይምራኝ የምለው፤ በመንፈሴ ጽድቅ ላይ የሚኮፈስው እኔ ባህር ማዶ ያለሁትንም ብቸኛ፣ ሆደ ቡቡዋን ሥርጉተ ሥላሴን በቤተኝነት የሚፈቅደኝን እንጂ ከስደት ላይ ስደት የሚጭንልኝ የመከራ አጭታን አይደለም።
እጅግ የምንፍቃችሁ ወገኖቼ አንድ ነገር ልንገራችሁ ወደድኩኝ „የቴወድሮስ ራዕይን“ ጥቅምት 7 ቀን እዚህ ሲዊዘርላንድ በዙሪክ ቤዲኮን ከተማ ልታደም ሄድኩኝ። መቼም የምትገርም- እጅግ ከጣሪያ በላይ የምትደንቅ ልክ እንደ አሁኗ ወጣት የማለዳ ኮከቦች ውጥን ተዋናይት ተወዳዳሪ እንደ ምዕራፍ ጎሳዬ ያለች ጥንግ ድርብ ወጣት ነበረች እቴጌ ተዋቡን ሆና የሠራችው። እቴጌ ተዋቡ በመንፈሷ መጥታ ብቻ ሳይሆን በህሊናዬ ባለ እርስት እስከትሆን ድረስ ነበር ልቅናዋ። የሚገርመው ይህቺን የድንቅነት ልዑቅ እመቤት የ4ወር ህጻኗን ትታ ነው ይህን ትውልዳዊ ድርሻ ለመወጣት የወሰነችው። አምሰተርዳም ነው የምትኖረው። እና „የቴዎድሮስ ራዕይ“ የምልከታ የጹሑፌን ፎቶ እሷን ማደረግ ፈለግሁ። ግን ተሳካልኝን?
- እንዲህም ሆነ …
… ልክ ጎንደር ባታ እስር ቤት እያለሁ ታምሜ በወታደር ታጅቤ ለህክምና የሄድኩበት ጊዜ ነበር የታወሰኝ። ያው እንደተለመደው ዙሪያ ገባው በጥበቃ ሥር ነበርኩኝ። ጥሪው መዝናኛ መሆኑን ጀማሪ ፓለቲከኞች ተደባልቆባቸዋል። ጥበቃው ተዋናዮችን እንዳለገኝም እሰከዚያ ድንበር ድረስ ይደርሳል። ይሄን የኖርኩበት ስለሆነ አይደንቀኝም። … ብቻ አጠገቤ አንድ የማከብረው ወንድሜ ስለነበር ጠጋ ብዬ አማከርኩት። ቁጭ ብለሽ ትችያለሽ አለኝ። ያው እሱም ባለድርሻ ነውና። ከተቀመጥኩበት ሆኜ ፎቶዋን ከነ ገድሏ ለማስቀረት ካሜራዬን ሳስተካክል በቅጽበት የዜግነቴ ደረጃዬ ስላልፈቀደ ወታደሮች አስቆሙኝ። ቅጽበቱ እጅግ ይደንቅ ነበር። ትዕይንት ነበር የሚመስለው። ከዛ በፊት ከፊት ለፊቴ ሌላ ተመልካች ፎቶ ሲያነሳ ከልካይ አልነበረውም። ሰው ገንዘቡን ከፍሎ ከያዘው ሁቴል፤ ሰው ገንዘቡን ከፍሎ ባዘዘው ምግብ ላይ፤ ሰው ገንዘቡን ሳይከፍል በባህር ዳርቻ ሲንሸራሸር በጥበቃ ሥር ነው እዚህ ሲዊዘርላንድ። በርሊን እና አምሰተርዳም ግን ይህ ጫና አልነበረም። ሌላው ቀርቶ ለዓለምዬ ለመራሂተ ጥበብ „ተስፋ መጸሐፌ ላይ ስለእሷ የገጠምኩት የሥጦታ ሥነ - ግጥም ስለነበረ፤ በሌላ በኩልም „ለቴወድሮስ ራዕይ“ ደራሲ ለጥበባት ዋርካው ለነፍሱ ለጌትነት እንዬው „የርግብ በር“ ትዳር እንዴት መያዝ አለበት ለቀጣዩ ትውልድ ሲባል የሚለው ሰባተኛው መጸሐፌ ለንጉሦች ንጉሥ ላጤ ቴወድርስ ማስታወሻነት የተሰጠ ስለነበር፤ ለእሱም የተጋባ በመሆኑ ይሄን አዘጋጅቼ ነበር የሄድኩት። በጥበቃ ሥር ሆኜ እንዴት ብዬ? እያንዳንዷ እርምጃዬ ቁጥጥር ነበራት። ለስበሰባቸው ስሄድ የለመድኩት ነው ይገባልም ካለዞጌ፤ ካለደረጃዬ ለማለቅልቀ ስለነበር ስባትል የነበርኩት።
ያ ግን ልዝናና ነበር የሄድኩት። በስንት ዘመኔ ቲያትር ላይ። ያን የናፈቀኝን የሐገር ፍቅር፤ የብሄራዊ፤ የራስ፤ የጎነደሩን የሲኒማ ባርን ቲያትር ዓውደ ምህረትን በምልሰት ልፍነሸነሽበት ነበር አካሄዴ። ያው የቲያትሩ አቅምና ጉልበት አንቱ ስለነበር ጫናውን ጥሶ ፍሰሃ ሸለመኝ። እናላችሁ ያቺን ድንቅ ሳላሳያችሁ ቀረሁ። ጸሑፉም በራሴ ፎቶ ወጣ። ብቻ …. የሆነ ሆኖ ነገስ ለሚለው …. ሐገር ቤት ብቻ ሳይሆን ውጪም እስረኛ ናት እናት ሐገር እስከነመንፈሷ። በዕውነቱ ልጃቿ ሰሰቀን ላይ ነው ያለነው። ተሰፋችን ተፍቋል፤ ተፈቅፍቋልም። ስለዚህ ይህን የተስፋ ጸሐይ ስናይ ስለምን አንፈንድቅ፤ ስለምንስ ፍንሽንሽን ፍልቅል አንበል። ስለምን ሐሤት አይሰማን። ስለምን እንደ ልጅነታችን መቧረቅ አያምረን …. የናፈቀን ረቂቅ ሚስጢር አለ። ከአፍቅሮተ ማልያ ውጪ እኩል የምንታይበት አዲስ ዘመን። ማልያ በጥብጦናል - አውኮናል። የውስጥ ሰላማችንም ረብሾታል - ነጻነታችንም ቀምቶታል።
ከሰው ተፈጥረን ሰውን ፈርተን እንድንኖረው ተገደናል። አንዳንድ ጊዜ ስንቱ ተፈርቶ ያሰኛል። ስለሆነም የናፈቀን የክትና የዘወትር የማይለይበት ቢያንስ በተሰደድንበት ሐገር አቅማችን አደባባይ እኩል ለህዝብ ጥቅም የሚውልበት አዲስ የዜግነት ዘመን …. ናፍቆናል። „የምታውቁት መሪ ነው። አዲስ አይመጣም“ የሚባለው ለእናንተው ለቤተኞች፤ ለክቶቹ እንጂ ለእኛ የሩብ ዜግነትን እንኳን ላላገኘነው አይሆንም። አይደለምም። ቤታችሁ እዬመጣን ተቀጣን እስኪበቃን ድረስ። ለዛውም ስደት ላይ ለባይታዋርነታችን እንኳን ለእራፊ ጨርቅ አለበቃትም ጥሪያችሁ። … የውስጥ ማንበቢያ መሳሪያ ቢኖር መግሉንም ታዩት በነበረ … ለነገሩ ራህብን የተራበ እንጂ ያልተራበ ከዬት ሲያውቀው። አልደላንም። አልተመቸነም። ስለዚህ ቁሞ የሚያስጠብቅ ኤሉሄ የለም እንደማለት ….
የማሊያ አባልተኝነትን ያልፈቀደነው … ቢያንስ ተሰደን በምንኖርበት ሐገር የእኩልነት አንባ ናፍቆተኞች ነን። የፍትህ እናት ሐገር ራሃብተኞች ነን። የርትህ ቀዬ ጥማተኞች ነን። አዎን እኔም እንደ ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ ደስ ብሎኛል። ተስፋዬ አራት ዓይን አብቅሎ አድሯል። ጆሮዬም ዓራት ዓይን አብቅሎ አድሯል። አዎን! እኔም እንደማንኛው ቅን ኢትዮጵያዊ ከመጠን ባለፈ ሁኔታ ደስ ብሎኛል። እግዚአብሄር ይስጥልኝም ማለት እሻለሁ የተከበሩ አቶ ለማ መገርሳን። ይሄን ማን አይቶበት። በሩቁ ህልም ውስጥ ፍትሃት ሲመጣ …. ነፍሴ በደስታ ተዋበች። በስደቱም ላይ ያለውን በራስ ወገን ባይታወርነት እንዲህ በርቀት ሄዶ ተጉዞ ለባለቤት አላባዎቹ የመንፈስ - የህሊና፤ የተስፋ ስንቅ ለሰነቀ፤ ከትዕቢት ጋር ለተፈታ ብሩህ ጭንቅላት እኔም ፍቅሬን፤ ልቤን፤ አክብሮቴን፤ ታማኝነቴንም ለመሸለም ስስታም አይደለሁም። ልብ ይሸለሙ ብለናል …
መጀመሪያ ቅንነትን ሳይቆጥቡ መለገስ። ለዛ ለተሰጠው ቅንነት ታማኝነትን ከተላባሰ እሰዬው ነው፤ ካልተላበሰ ደግሞ „ጨው ለራስህ“ ስትል ነው … ትዕግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል። እኔ በቅንነት ነው ማናቸውንም ውጥን እምመለከተው። ሂደቱን ግን በትክክል ሆኜ በተመስጦ እታደምበታለሁ። ሥራዬ ነው። የተፈጠርኩበት። ሲካፋኝም ገልጬ እንገራለሁ። ኢትዮጵያን ለመጥራት በሚያነገሸግሻቸው መሃል ይህን መሰል ቅዱስ መንፈስን ያልተንከባከብን የቱ ሊሆን ይችላል ምርጫችን። አገላለጹ እያንዳንዱ ቃል ልብን አሳምሮ ይገዛል - ይነዳል - በፍቅር ያባብላል - በፍቅር ያወጋል - በፍቅር ያጽናናል - በፍቅር አይዟችሁ ይላል። የናፈቀኝ አይዞሽ የሚለኝ ልሳነ ወርቅ መንፈስ ነበር። ዛሬ ይህን መንፈስ አግኝቸዋለሁ። ተመስገን። ህይወቴ ጣናዘገሊላ ላይ ሰክናለች። ይህ ማለት ያ መያዣ መገረዣ ያልተበጀለት ህልቆ መሳፍርት የሌለው፤ መጨረሻ ደንበር ያልተሰራለት ሐገራዊ ችግር በእፍታ ይጠፋል የሚል ቅዠትም የለኝም፤ ሂደት፤ ጊዜ፤ ሁኔታ የሚፈታቸው አምክንዮች አሉ። የፖለቲካ ትፍስህት የሂደት ዓወደ ምህረት እንጂ የፕሮፖጋንዳና የዓዋጅ ጃንደረቦች አይደሉም።
አሁን የሚያሰፈልገው መተንፈሻ ቧንቧ … ነው … ለራሱ ለእስረኛው ኢትዮጵያዊነት።
ቅን ኢትዮጵውያን እንኳን ደስ አለን። ዛሬ ፋሲካችን ነው። ዛሬ ቅዱስ ዮኋንሳችን ነው። ዛሬ ልደታችን ነው። ዛሬ የረመዳን ፆም መፍቻችን ነው። ዛሬ ለቅኖች ብቻ ዓውደ ዓመታችን ነው። ዛሬ አዎን ዛሬ እንኳን ደስ ይበለን አዎን! „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው።“ አዎን! ኢትዮጵያዊነት ማግኔት ነው። አዎ! ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ የሚስጢር በኲራት ነው። አዎ! ኢትዮጵያዊነት የፊደል ገበታ ነው። አዎ! ኢትዮጵያዊነት አናባቢም ተነባቢም የነፍስ ቃናዊ ቅዱስ መንፈስ ነው። አዎን! ኢትዮጵያዊነት ተወዳጅና የማይጠገብ ነው። በጉባኤው ላይ አንድ አባት „ልጆቻችነን ፍቅርን እናስተምራለን ብለው ቃል ገብተዋል።“ ድሮም አርሲ … ጭላሎ … በቆጂ … የፍቅር ወተት ነው …. አምኛና ሴሮ ፍቅር ነው፤ ዲክሲስ - ጠና - ሮቤ ፍቅር ነው …. ከፍቅር ቤት ፍቅር ይቀዳል። ኢትዮጵያም ፍቅር ናት። ኢትዮጵያዊነትም ፍቅር ነው። እንዲህ ይመርብን እንጂ … ተመስገን!
- ከልብ ስለመሆን።
ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ አንድ ነገር ለስታውሰዎት እሻለሁ። ከዚህ ደማቅ ተቀባይነት ጋር የፖለቲካውን ሴራ ትብትብ አደራ እንዳይዘናበት። በዬትም ቦታና ሁኔታ ጥንቃቄ ይሁን መርሆዎት። ልባም የሚጠቃው በራሱ የእኔ በሚለው ነው። አብሶ የምግብ ብክለት … ይህቺን ደመቅ ምዕራፍ የሚተኛላት አይኖርም። አደራ። ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም። አሁን የእስረኛ የፖለቲካ መሪዎችን መታሠርን ሁሉ እኩል ይጎረብጠዋልን? አይመስለዎት … መገለል፤ መወገድ ያለበትን … ልብ ይሻል። ሥልጣን በሽታም ይመስለኛል። ርህርህና ሆነ ሰብዕዊነትን የሚፈታተን። ሞራልና ሥልጣናዊ ምኞት ብዙም ተቀራራቢ አይመስሉኝም። እና „ልብ ያለው ሸብ“ ቅንነትን በጥንቃቄ ደንብር ይሁኑበት … የህዝብ ፍቅር አይሸመተም፤ አይቀናም። ይጠንቀቁለት፤ ያክብሩትም።
- ወቄት።
ለእኔ እኒህን ብርቅዬ ወጣት ፖለቲከኛ እንደ አርበኛዬ አብዲሳ አጋ ብቻ አይደለም የማያቸው። ጀግናዬ አብዲሳ አጋ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ነው ያደገው፤ ያን ገድለኛ ማንነት በተጋድሎ ያደመቀው በሰው ሐገር በማንነቱ ውስጥ ነው መሆንን ያደመቀው። እኒህ ደግሞ ሐገር አልባዋ በሆነችው ኢትዮጵያ ውሰጥ „የለችም፤ ገና አልተፈጠረችም“ በተባለበት ዘመን፤ እራሱ ማንነቱ እስር ቤት በአግር ብረት በበባዕቱ ባለበት ወስጥ አድገው ነው ለኢትዮጵዊነትን ግርማ ሞገሱ የሆኑት። የማይቻለውን በመቻል ውስጥ መቻል ያደረጉ ድንቅ ሰው ናቸው። ሁሉም እኮ ኮተቱን ተሸክሞ ነው ኢትዮጵዊነተን ለመናጆ የሚያሻው። አጋጣሚ ሲያገኝ ሲያዳልጠው እንያለን - እንታዘባለን። እኒህ ሰው ደግሞ ቅኔያቸውን ለማዬት - ለማደመጥ - ለመሆን የተካኑበት መንገድ ይማርካል፤ ይስባል፤ ያጓጓል። ጥላ ከለላ፤ ጥግና መከታ በሌለው ማንነት ውስጥ ነው እኔ አለሁልህ በዚህም ዘመን አይዞህ ኢትዮጵያዊነት ያሉት። ስለዚህ ልቅናቸው ልብ ነው። ብልህናቸው አንጎል ነው። ይጨርስላቸው። አሜን! ሌላው በሀገር ደህንነት ተግባር ውስጥ ያለፉ ሰዎች የመሪነት ዕድል ሲያገኙ አቅማቸው ሙሉ ሆኖ ነው እኔ የማያቸው። ምን እንደሚፈልጉ፤ ምን እንደሚችሉ፤ ምን እንዳላቸውም፤ ምን እንደሚሰጡም ጠንቀቀው ያውቃሉ። ውሃ በቀጠነም የሚዘወሩ አይደሉም። ይህን ሙሉ ብቃት ከሌላ ሐገር መሪ ተመክሮ አስተውዬዋለሁ።
- እርገት ይሁን።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለማልያ ያደሩ ፖለቲካ ተንታኞች እና ያደሩም አሉ። አብሶ ለማልያ ያደሩት የፖለቲካ ተንታዮች ደንጋጦች ናቸው። የአረፍተ ነገሩ አወቃቅር እራሱ ዝብርቅ ይልባቸዋል። ከዛች ከተሰመረላቸው እልፍ እንዳይሉ ብርቱ ጥንቃቄ ያደርጋሉ። በራስ የመተማመን ንጥረ አቅም ያንሳቸዋል ሃቅን በማንጠር ዙሪያ። የማልያ አባል ያልሆኑት ደግሞ ደፋሮች ናቸው። መስመር ጥሰው መሄዳቸውን ስለማያውቁት የልባቸውን ነው የሚነግሩን። ሃሳባቸውም ጉልበታም ነው። አሳሪ ገመድ የለባቸውም። አይወቀሱበትም አይነቀሱበትም። በሌላ በኩልም በእያንዳንዱ የሃቅ ዙሪያ ትንተናዊ ሙግት ማልያ የሚያሥራቸው ጋዜጠኞች እና ለማልያ ያለፈቀድን ጋዜጠኞችም አለን። ያው ባለማልያዎች ጥንቃቄያቸው ከሥነ- ሙያ ምግባራቸው ጋር ሲፋጠጥ ሁልጊዜ ይታያል። ይህን ሳይ ምን አስጨነቀቻውና ነው ነፃነታቸውን ለማልያ የሚሸልሙት እላለሁ። ለናሙና የማልያ አብልተኛ ያልሆነውን የጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ በአቶ ለማ መገርሳ ዙሪያ የቀደመ ዕይታ እና አሁን ያለውን የጭብኝ መዳረሻ ሁለቱንም ለህሊና ዳኝነት ማያያዣውን ለጥፌዋለሁ። ከሃቅ የመነሳት አቅም አዎንታዊነቱ ምልከታ ብቻ ነው ሊረዳን የሚችለው …. ፈጣሪም መንፈሱን የሚልከው በዚህ መስመር ብቻ ነው። መመለክ ያለበት ሃቅና ተጨባጩ እንጂ ሌላ ሊሆን አይገባም። መጠራጠሩ ደግሞ ይደርሳል። አሁን ይህን ቅን መንፈስ በቅንነት እንኳን ደህና መጣህልን እንበለው። የአቶ ለማ መገርሳ የአሁኑ አያያዝ ልቅናቸው ነባቢት ነው። ብልህነታቸውም ንዑድ ነው። ምን ይባላል ይጨርስላቸው። አሜን!
- ምርኩዝ።
President lemma megersa of oromia regional state to pay a historical visit to Amhara regional state.
https://www.youtube.com/watch?v=Yp5a2ruY-p8
Leaders of Ethiopia's major nations, oromo annd amhara, ascert that they need each other
- እስቲ የኔዎቹ ዘና ፈታ ደግሞ በሉ …
„አዲሱ በኦሮሞና በአማራ ዙሪያ የተለቀቀዉ ነጠላ ዜማ በመንግስት ዘንድ ተቀባይነትን አጣ“
ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
እልፍ ነና እና እልፍነታችን እልፍ እናድርገው።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ