ካቴና እና ዘውድ።

ካቴና እና ዘውድ።
ከሥርጉተ ሥላሴ 03.11.2017 /ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ/
„ከምትፈሩት ከባቢሎን ንጉሥ አትፍሩ፤ አድናችሁ ዘንድ፣ ከእጁም አስጥላችሁ ዘንድ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና አትፍሩ ይላል እግዚአብሄር። "
(ትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ  ፵፪ን ከቁጥር ፲፩ እስከ ፲፪)
  • ሁለቱም።

ሁለቱም የ21ኛው ምዕተ ዐመት የተስፋ ማህደር ናቸው። ሁለቱም ወጣቶች ናቸው። ሁለቱም አንስት ናቸው። ሁለቱም ንቁ ታታሪ ወጣቶች ናቸው። ሁለቱም የዘራቸውን ማንነት ፈላጊዎች ናቸው። ሁለቱም እትብታቸው የተቀበረበት እንደ ዓለሙ የንዋይ ማዕከል አገላለጥ ጨላማ በከዘነባት በጎንደር ነው። ከሁለቱ ውስጥ አንዷ በዘመናችን ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቀው የዲታነት ህይወት በመገስግስ ላይ ያላች ስትሆን፤ ሌላዋ ደግሞ የመተንፈሻ ቧንቧዋ በካቴና የተቀረቀረ ነው። የአንዷ ቤተሰቦች በመንፈስ የነፃነት ዲታነት የልጇቸውን አባባ እያለሙ በንዋዩ በፈነደቀው የግል ዕልፍኛቸው ውስጥ እስከፈቀዱት ድረስ ያለከልካይና ያለገዳቢ በደንበር አልቦሽ ይዘናከታሉ። የልጃቸውን የህይወት አንባባ ለማዬት ሽልማቱም ዝንጥ ባለ አውቶሞቢል ያወራርዳሉ። ቅንጦቱ ጣሪያ የነካ ነው። በጥንድ የጉልበት አገልጋይ የተዋናይት ፍርያት የማነ ቤተሰቦች ዕልፍኝ ሰጊድ ለከ ይባልለታል። የነፃነት ራህብተኛዋ የእጨጌት ወጣት ንግሥት ይርጋ ቤተሰቦች ደግሞ በካቴና ውስጥ ያለችውን ልጃቸውን ከጎንደር ተነስተው ክልትምትም ብለው ወደ አዲስ አበባ ሄደው ለማዬት እንኳን ያልተፈቀደላቸው ናቸው። ሠፈራቸው በማህበረ ደራጎን የጥበቃ ሥር ውስጥ ነው። የሚተነፍሱት አዬር ሁሉ ውጥረት ውስጥ ነው። ባድማው የሥጋት ቅልቅሎሽ አና ብሎበታል። የአማራ ሊቃናት የማይጋባቸው የሚስጢር አስኳልም ይኽው ነው። አማራው በባለቤት አልቦሽነት የተጫነውን የአሽዋ ክምር እንደ ለመደው አቀርቅሮ ይገፋ ባዮች ናቸው እነ ድርብ አንጀቶች። ቢያንስ ከነዚህ ሁለት ወጣቶች የጉዞ ምስባክ የቀሰሙት የንቃት ቀብድ እንኳን እንደሌላ ነው አምክንዮቸው የሚጠቁመው።

ባለ ዛውዷ የመንበረ መንግሥቱ የቴሌቢዥን አዘጋጅ ናት „እሁድን በኢ.ቢ.ኤስ።“ ሌላዋ ደግሞ የቃሊቲው ግብረ ፈርዖን የምትተነፍሰው ንጹህ አዬር ቆጭቶት መግቢያ መውጫ ነስቶ፤ ጮርቃ ህሊናዋን በጭካኔ ጉጠት ይነቅሰዋል። በመስቃ ጦር ይተረትረዋል - ይሰቀስቀዋል - ይሾቀሹቀዋል። የትግራይ ልዕልቷ ወጣት የክት ብርሃናማ ከተማ አለቻት። ሲያሰኛት ከዛም ተገኝታ ፌስታዋን በሰናይ ታስነካዋለች። ታላቋ፣ ብርሃናማዋ ሀገረ ትግራይ፣ ሁለተኛዋ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ርዕሰ መዲና ናትና። የጀግኒት ንግሥት ይርጋ የክቷም የዘወትሯ ጨለማ የተበዬነባት፤ እሳት የታዘዘባት፤ ለመሬት ሊኳንዳ ቤት በዓይነት የተከፈተላት፤ ልጆቿ በጭካኔ መርኽ የሚዘለዘሉባት - የሚሳደዱባት ድሃዋና አሮጌ ቀሚስ ለባሿ የጎንደር ከተማ ናት። ይህቺ ድንቅ ወጣት ድምጽሽን በዕንባ አሰማሽ ተብላ ነው በፈርዖኖች የበቀል ማጎሪያ የምትገኘው። ሥምሽ ስለምን „ንግሥቲ“ አልተባልም ተብላ በተጨማሪም እስር ቤት ውስጥ በመስቃ ሹል በዕዬለቱ ትወጋለች።

ተጋሩዋ ባለዘመን በሆነችው የኢትዮጵያ ሁለተኛ ርዕሰ መዲና ብርቅዬዎቹ በቁንጅናቸው¡ በትውና አቅማቸው¡ በአማራር ጥበባቸው¡ በአርቆ አሳቢነታቸው¡ በሚዳያ ባላባትነትና በዲታነት በኢትዮጵያ ሀብት የከበሩት የዲታዎች ማህበርተኛ ናት። ሌላዋ ምሰኪን የማንነት አርበኛዋ ደግሞ ዘመን የሚባለውን ሳታወቀው የታሪክ መተከዣ፤ የመጣው ሁሉ እንዳሻው የሚደቃት፤ ሽፍትነት ያማረው ሁሉ እሷን መሽጎ ልጇቿን ባላባራ ጦርነት ከላልርህራሄ ለማገዶ ጥሬ ዕቃ አቅራቢነት የሚሰዬምባት፤ ዛሬም ሳይቀር የልጅ ብርንዶ አቅራቢዋ የቀን ተለሊት የዕንባ ማህደር የሆነችው ጎንደር ብቻ ናት ያለቻት። እሱንም አልተፈቀደላትም። እስሯ እንኳን ስንቅ ለማቀበል ከ760 ኪሎሜትር እርቀት በላይ ተበይኖባታል። ጀግኒት ንግሥት ይርጋ ቃሊቲ ላይ በማህበረ ደራጎን መስቃዊ ስላቅ ሰንበትን ዕንባዋን ስታዘራ፤ ዘመንተኛዋ ተዋነዊት ፍርያት የማነ ደግሞ ሰንበትን እጅግ በሚያምር አልባሳት ተውባ፤ በኮስሞ ባለሙያ ስክነት በተቀናበሩ ውበት አምራና ድምቃ፤ ተኩላ ከእንግዶቿ ጋር ምን በመሰለ የኢቢኤስ የተሌቪዢን እልፍኝ ኬክ ትቆርሳለች። ዛሬ ያለችው ኢትዮጵያ ማለት ይህቺ ናት እንግዲህ። ለአንዱ ብርሃን ለሌለው ጨለማ፤ ለአንዱ ገነት ለሌላው ሲኦል፤ ለአንዱ እልልታ ለሌላው ምሾ፤ ለአንዱ የልብስ - የጌጥ ፋሽነኛ ለሌላው የካቴና የእግር ብረት ሞዴልኛ፤ ለአንዱ የውጭ ሀገር የወሊድ እረፍት መቃበጫ፤ ለሌላው ደግሞ 
  • የእግር ብረት ሃኒ ሙን …


ሰማይን ያለ ካሳም ያቆመው ፈጣሪ አማላካችን ሁለቱንም ወጣት አንስታት በማይመረመረው ረቂቅ ምስጢሩ እኩል እፍ ብሎ ፈጥሯቸው ነበር። ሲፈጠሩ ሁለቱም „ሰው“ ሆነው ነበር የተፈጠሩት። አባታችን አማኑኤል አላጓደለባቸውም ማህጸን ውስጥ በረከቱን ሲቀስስላቸው። ነገር ግን ከተወለዱ በኋዋላ አንዷ ባርነት ስለተጫናት አሻም በማለቷ እግር ብረት ሲታዘዝላት፤ ሌላዋ ደግሞ የወርቅ ዘር ስለሆነች ከለምንም ቅድመ ሁኔታ ሰተት ብላ ለአራተኛ የመንግስት አካልነት አቅም በሆነው የልሳኑ እንብርት ላይ ቁጢጥ ብላለች። በደሟ ልቅና - በትግሬነቷ። ይህን ዘይትና ውሃ አንድ ወጥ አድርገን የአማራን የዘር ማጥፋት ፖሊሲ እፈለመዋለው የሚለው እንግዲህ „የጎንደሩ ህብረት ነው።“ በካቴና እና በንግሥና፤ በመስቃ እና በዕልልታ ማዕዶነት፤ በምሬትና በፈገግታ ያሉትን የኑሮ ዘባጣዎች አዋህጄ፣ አቀናጅቼ ርትህና አስገኝልሃለሁ ብሎ የጎንደር ህብረት ዓውጇል። ጎንደር የተወለደ ሁሉ ስለ አማራ ፍለስት እኩል ይጨነቃል፤ እኩል ይጠበባል ባይም ነው። በጅምላና በችርቻሮ የፖለቲካ የማልያ የቁማር ጨዋታው ይሄውን ትርካታ እያሰኬደው ነው። ይሄው ዕንባና ፈንድሻን አስማማለሁ ብሎ ከላይ ታች ይባዝናል። ይቻለው ይሆን? ወይንስ እንደ ተለመደው በቅይጥ ማንነት በሥሙ ለሚነገደው የአማራ ህዝብ የህልውና ተጋድሎ የመንፈሱን ልዩ አቅም ለሌላ ገብሮ መንፈሱንም አዘናግቶና ክዶ ግብዕት ለመፈረም ይሆን? የመሰናክል ምሳር።
  • „እናስተውል።“

እንሰተውል ስል ፉከራ አይደለም። ቃሉ „ቃለ ወንጌል“ ነው። ዶግማ። እንደ ማህበረ ደራጎን መስጠንቀቂያም አይደለም፤ እንደ ደማችን ለመኖር እንፍቀድ ማለት ነው። አማራ የመንፈስ ድርጀቱ አማራነት ብቻ ሊሆን ይገባዋል ለማለት እንጂ። አማራ ዓርማው የመንፈሱ ቅድስተ ቅዱሳን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ልሙጡ አባቶቹ የተሰዉለት መንፈሰ - ደቂቀ አዳም ሰንደቁ ሊሆን ይገባል። ይህን ዓርማ ለማንም ለምንም ብሎ ሳይሆን የእኛነት አሻራው የደሙ ነጋሪት ስለሆነ። በሰንደቁ ላይ ሌላ ተለጣፊ ቅይጥ ፍላጎትም ሊኖርበት አይገባም። ይህ ነው የአመራ ልብ ሊሆን የሚገባው። የትም ይወለድ ውጪ ሀገርም ቢሆን አማራ በክ/ሀገር ደንበር ሊሳረለት በፍጹም አይገባም። ወንጀልም ነው። አማራ አማራ ነው ድንበሩ የዘሩ ንጥረ - ነገር ብቻ ነው።

  • የአማራ የሥነ - ልቦና አቅምን የመገንባትን አስፈላጊነት - ከልብ ማድመጥ ያስፈልጋል።

የአማራ የህልውና ተጋድሎ ለአማራ በህልውናው ለመቀጠል ቢሆንም፤ ህልውናውን በቋሚነት ለማስቀጠል ኃይል ሊኖረው ይገባል። ያ ኃይል መከላከል የሚችል፤ አንደበቱ ሊሆን የሚችል፤ መወሰንና ማስውስን የሚችል መሆን ይኖርበታል። በኢትዮጵያ የህግ የማርቀቅ፤ ህግ የማውጣትና ህግ የማጽደቅ እንዲሁም ህጉን በማስፈጸም እረገድም ሙሉዕ አቅም እስከመገንባት የሚያድርስ ሩቅ ድርብ ትልም ይዞ አማራው መነሳት ይኖርበታል። ጤናዬን ስጠኝ ተብሎ ስለ ዕለት እንጀራዬ ግን አታስብ ተብሎ አይጸለዬም።  …. እንጀራው ከሌላ እሱ የለም። እንጀራው ደግሞ የፖለቲካ ስልጣን ነው። አንሸዋወድ። ሰላሙን በጸና መሰረት የሚያስጠብቅለት የእኔ የሚለው የራሱ እንዳረሱ የሆነ ንጥር ሁነኛ ውክል አካል አማራው ያሰፈልገዋል። በሹልኩልክ፤ ወይንም በተለጣፊነት ወይንም በጥላ ያዢነት አይደለም። ፊት ለፊት አማራ ነኝ ብሎ የወጣ፤ የሚወጣ፤ ለማንም እና ለምንም የማያጎበድድ፤ ለተልዕኮው ብቻ የሚያደገድግ፤ ከስጋት የሚታደገው የተደራጀ ብቁ ኃይል አማራው ያስፈልገዋል። በዬአካባቢው እንደ ዱር አራዊት አደናውን በህግ ቀጥ አድርጎ የሚያስቆምለት። ስለሆነም አማራው የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት ለመሆን ሥነ - ልቦናውን በጠራ ሁኔታ በተከታታይ መገንባት ያስፈልገዋል። ከእንግዲህ አማራ የሌላ ሲሳይ መሆን የለበትም። የበይ ተመልካችነትንም አንቅሮ መትፋት ይኖርበታል። መጓጓዣ ጋሬም መሆን አይኖርበትም። ሌሎቹ የሚቋምጡለትን ወንበር እሱም የኔ ሊለው ይገባል። ይሰበው መንበረ - ሥልጣንን። ይቀደው - ወንበርን። ካለወንበር አቅም ጥበቃ ማግኘት ፈጽሞ አይቻልም።

በኢትዮጵያዊነት ሥም የተጠቀለሉ መርዞችን ሁለ አማራ ጠቅልሎ ከመጉረሱ በፊት፣ ፍተሻውን በቅኔዊ ጥበቡ መደመም ይኖርበታል። ደሙን የከፈለበትን ከ30 ዓመት በላይ እነ አርበኛ አበጀ በለው ሲወርድ ሲዋረድ በውርስና በቅብብል ያቆዬትን በኢትዮጵያ ሥም ያደረጀውን የሞተለትን፤ የተሰደደበትን፤ ወገኖቹን የገበረበትን መስዋዕትነት ሸልሟል - ዛሬ። የእነ አበጀ በለውን ዕርም በልቷል - ዛሬ። ይህ በዛሬው ዘመን የተከወነው ታላቅ የታሪክ ግድፈት ነው። የሚሊዮኖችን የተስፋ ጥግ ያመከነ። ሁልጊዜ ከዚህ በኋላ ይባላል። አሁንም ግን ከዛው ከስህተት ውስጥ እንደተዘፈቀ ነው ያለው የአማራው የመሆን አቅም …
  • ፖለቲካና ብልጠት።

አሁንም በብልጠት ፖለቲካ አቅሙን ለስንት ጊዜ ታናሹ ጠቅልሎ መሸለሙ መታነቂያውን አጠበቀው። በገዛ እጁ አለኝታ አቅሙን ሸበሸበው፤ ዛሬም እንደ ዋልልኝ ዘመን ራሱን ለማስጠፋት ወይንም ለማክሳት እዬፈተለ ስለመሆኑ ቁጭ ብሎ፤ ልብ ገዝቶ፤ በማስተዋል ሆኖ በተደሞ ሆኖ ሊያስብብት ይገባል - አማራው። ሊበይንበትም ይገባል። ከእንደዚህ ያለ ጅልነት በድጋሚ ላለመዘፈቅ ቆርጦና ወስኖ ከተደጋጋሚ ግድፈቶቹ ጋር መፋታት ይኖርበታል። ኢትዮጵያ የሁሉም ሐገር ናት። ኢትዮጵያን ያቆያት አማራ ብቻ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ሁሉም እንደ የዘመኑ የራሱን ድርሻ ተወጥቷል። ወደፊትም ኢትዮጵያን ሊታደጋት የሚችለው አማራ ብቻ አይሆንም። ስለዚህ አቅሙ የሚመጥነውን ኃላፊነት ብቻ ነው አማራ መሸከም ያለበት፤ እንጂ እነ ሊቃውንት ጸሐፊ ተስፋዬ ደምመላሽ /ዶር./ የሚጭኑትን የትሬኮላታ ጭነት ሊሆን አይገባም። እንደ ኢትዮጵያዊ ሊያደርግ የሚገባው እና እንደ አማራ ሊያደርግ የሚገባውን በውል በፈርጅ - ፈርጁ ለይቶ ሊሰክንበት አማራው ይገባል። አደባልቆ ወይንም ቀላቅሎ መንጨባረቅ አይኖርበትም - አማራው።

አንድ ሰው ሁለት እግር አለኝ ብሎ በአንድ ወቅት ከሁለት ዛፍ መውጣት አይችልም፤ ምርጫው አንድ ብቻ ነው። አማራ ምርጫውን ማስተካከል አለበት። የፕሮፖጋንዳ ሰላባም መሆን የለበትም። በትንሹ በትልቁም ሆደ ቡቡ መሆን አይኖርበትም። አማራ ከመከራው ልብ መነሳት ይኖርበታል። አማራው በወኔና በስሜት በሚገፉ ባልሰከኑ የፕሮፖጋንዳ ስብከቶችም ተጠቂ ወይንም ተኮማታሪ መሆን አይኖርበትም። የተያዘው ተረተረት አይደለም። ማን ብዬ ልጥራህ? የሚለውን ፖለቲከኞች እሰኪሳናቸው ድረስ የሁሉንም የጎሳ ሊቃናት ተጠርተው አማራ ላይ ሲደርሱ ሃያስያን ወገባቸው የሚያዘው አማራ ባሊህ ባይ፤ ወጥ እና ጽኑ አቋምን የተካነ፤ ክህሎቱ እንደ ተፈጠሮ አመጣጥኖ ባለመገኘቱ ነው። አማራ የሊቃውንቱን የጸሐፊ ተስፋዬ ደምመላሽን /ዶር./ ሲናሪዮ በቅንነት ሳይበሳጭ ገፋ አድርጎ፤ ለድል ስበቃ እንነጋገርበታለን እስተዚያው ቁመህ ጠብቀኝ፤ እህል ውሃ ቀምሼ እስከመጣ ብሎ በተጨባጩ ገዢ አቅም ውስጥ ለመኖር መፈቀድ ይኖርበታል። ሁለቱ ያዬናቸው ወጣት አንስት የተወለዱበት አማራ መሬት ጎንደር ላይ መሆኑ ልዩነቱን አዋህዶ አላሰዬነም። ሁለቱም ወጣቶች የቤተሰቦቻቸውን የዘር ምንጭ ፍለጋ ላይ ስለመሆናቸው ነው ጥርት ያለው፤ የነጠረው አምክንዮ ሀቁን ሳንወደው አስገድዶ የሚግተን። መነሳት ያለብንም ከዚህ አመክኖዊ አንጎል መሆን አለበት። ወጣት ፍርያት መቀሌ ላይ ፌስታውን ስታስነካው ወጣት ንግሥት ደግሞ በወልቃይት ጠገዴ የአማራ የማንነት ተገድሎ ላይ ነው የተገኘቸው። ለዚህ ሁሉ አሳርም የበቃቸው።

ለአማራ የእሱ የሆነው ብቻ ነው የእሱ የሚሆነው። የእሱ ያልሆነው የእሱ አይሆንም። የእሱ በሆነው ውስጥም ቢሆን ከመጎንጨቱ በፊት ህጻፆችን ነቅሶና አጥርቶ ነው መቀበል ያለበት። አሁን ተዋናይት ፍርያት የማነ የእሱ ትሆናለችን? በፍጹም። ለመሆኑ ከዛ ምድርን ቀውጢ ባደረገው የጎንደር የአማራ ህዝባዊ አብዮት ጋር ምን ትስስር ይኖራታል? ምንም ነው። በዕውነቱ ምንም። ንግሥት ይርጋስ ይህን ለፍርያት የተሰጣትን ዕድል በዚህ ዘመን ታገኛለችን? የማይሆነውን በመሆን መቻል ማመሳጠር ያስፈልጋል። ብልጥነት ለፖለቲካ ህይወት ባይመከረም ብልጦች አልፈውት ሲሄዱ እያዬ፤ ለብልጦቹ መተላለፊያ ጉዝጓዝና ንጣፍ መሆን ለዛሬ ከጅልነትም በላይ ቀፎነት ነው። በጫካዊ የተጋድሎ ትግል ሆነ በበትረ ሥልጣን በወያኔ ይሁን በሻብያ ጊዜም ያተረፈው አማራው አንዳችም ነገር የለውም፤ የዘለዓለም ጠላትነት ነቀርሳ ነው እነኝህ የተከሉለት። በማያባራ ጭፍጨፋ ውስጥ ነውም ያለው …
የፖለቲካ ድርጅት ውህደት በማሸነፍና በመሸነፍ መወራረድ አይገባውም። በበላይና በበታችም ሊናጥ አይገባም። በመስጠትና በመቀበል መርሁ መስከን ነበረበት። በተመጣጠነ የእኩልነት ድርሻ ነው ሊሆን የሚገባው። ጊዜ ጠብቆ ሌላውን ጭራሹን በመፍለስ ሲሆን ግን ያማል። አቅም ይምራኝ ሲባል ተውጦ አይደለም። አቅም ይምራኝ ሲባል እረግጠህኝ አልፈህ ሂድ ማለት አይደለም። አቅም ይምራኝ ሲባል የደም ታሪክ ተሽጦና ተለውጦ ለአንተ የዘር ሐረግ መጠሪያ፤ ለአንተ የሥም ልቅና፤ በአንተ እጅ ለተነደፈው ማኒፌስቶ ግብር ይሁንልኝ ማለት አይደለም። በፍጹም። መጠጊያ የሆነውን አቅሙን አክብሮ፤ አቅሙ ለተገኘበት ማህበረሰብ የተገባውን ክብርና ልዕልና ከመስጠት ጀምሮ እኩል አሳታፊ በሆነ ሚዛናዊ አስተዳደርና እሰተምኽሮ ከተማራ ብቻ ነው አቅም እንዲመራ ሊፈቀድ የሚገባው። መንፈሳችንም በዬጊዜው በብልጠት ፖለቲካ መቀጥቀጥ አይገባውም ነበር። ታማኝነትና ፍቅርን ንፉግ ላልሆነው ዜጎች።

ከዚህ ያፈነገጠ ዕይታና እርምጃ ትዕግስት ሲያልቅ ፍቅር እንደሚሰደድ አስገድዶ መጋት ያስፈልጋል። ይህ ታዲያ በእንካ-ሥላንታያ የገበጣ ላሜ ወለደች ሳይሆን፤ በተግባር አቅምን ቆጥቦ በሥርዓትና በታቀደ ሁኔታ በመምራት ብቻ መሆን አለበት። ውሳኔን ሆኖ በመገኘት ማስከበር ሲቻል ብቻ ይሆናል የደፍጥጥን ቲወሪ ልክ ማሳወቅ የሚቻለው። ድርጊቱ ብቻ ነው ፍልሚያ ውስጥ መታዬት ያለበት እንጂ ወሬው መሆን የለበትም። የቤተክርስትያን ጸበል ጠብታ ከሰውንታችን ውጪ ነጠላችን ላይ እንኳን ቢሆን ፈሰስ እንድትል ዶግማው አይፈቅድም። አዎን! የአማራ አቅም ደግሞ ጠብታዋ ለዛ ኢትዮጵያዊው አይሁድ ለሆነው ለአማራ ወገኑ የመንፈስ መጠለያ፤ የተስፋ እራፊ መሆን መቻል አለበት። ሲተርፈው፤ ካለው ደግሞ ማካፈል ልማዱ ነው። የሆነበት። በህይወቱ የትውፊት ነጋዴ ሆኖ ለማያውቀው አማራ ልግስናን ማስተማር ውሃ ሽቅብ ይሄዳል እንደማለት ይሆናል። ማነው ከዛ የኤርትራ በርኃ ላይ ለዓመታት የበለዘበትን፤ የጠቆረበትን፤ የከሰለበትን፤ ጎጆ ትዳሩን የፈታበትን፤ ትዳሩን ያፈለሰበትን በሩን ከፍቶ ባዶ እጁን ለሄደ ድርጀት „እንኳን ደህና መጣህ“ ብሎ ውስጡን የሸለመው? የትኛው ድርጅት? ከዚህ በላይ ለዚህ ዘመን አመሳካሪ ሚስጢር የለም፤ የአማራ መንፈስ የአብርኃም ቤት ነው። ግን ይህን የሚመጥን የልቅና አቅም፤ የሙሴነት አቅም ወና ነው ሆኖ የማዬው … እዬዛንኩ፤
  • ኢትዮጵያዊነትና አማራነት።

ኢትዮጵያዊነትንም ለአማራ ለማስተማር አቅም ማባከን ይሆናል፤ በተጨማሪም ከጳጳሱም ያሰኛል። ወላጆቻችን አስቀድመው የቤት ሥራውን ሠርተውታል፤ የአማራ ሊቃናተ - ጉባኤ በዚህ ጊዜ ባያባክኑ ይመከራሉ። ኢትዮጵያዊነት ለአማራው የእናት ጡቱ ነው። አማራ በውስጡ የራዕዩ ቅመም ኢትዮጵያዊነት ብቻ መሆኑን ይጠበብበታል። ይህ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ለሚሰጠው ዘመን የማይሽረው ፍቅር፤ ወጀብ የማይንጠው ልዩ መሆን ነው፤ ዘመን የማያጎሳቁለው ቋሚ አስተማማኝ የሆነ የተግባር መኖ ሆኖ ኑሮበታል። ይሄ ተመጣጣኝ ሆኖ አለመገኘቱ ነው፤ አማራን ንቡ እንደተነካበት ቀፎ „አማራነት ይከበር!“ አስብሎ ሆ! ብሎ ያስነሳው። ለዚህ አብነቱ፤ ለዚህ ተምሳሌነቱ እንኳን ቆራጣ ክብር በማንም እና በምንም ሁኔታ አልታዬም። የለምም። ስለዚህ ተወዶም ተገዶ አማራ ክብሩን ከነክብሩ በአቅሙ ማስመለስ ይኖርበታል። ይህ በልልምጥ - በመቅለስለስ - በማባበል አይደለም። ወይንም በፈግጪው በፈርግጠው መሆን አይኖርበትም። ገራመሚው ነገር አሁንም የእሱን አቅም ነው አቅማችን የሚባለው። ሻታ የሚዞረው በአሱ የደም ግብር ዙሪያ ነው። አቅሙ ለባለ አቅሙ እንዲውል ከተፈለገ በቆራጣ … በሰንጣረው የአማራ ሊቃናት ጊዜ ከማባካን ተቆጥበው በወጥ የሥነ - ልቦና አንድነት ላይ ትጉህ ተግባራትን መከወን ይሆናል መፍትሄው። ይህም ማለት የፖለቲካ ብልጠትን በአቻው የፖለቲካ ብልህነት ማሸነፍ መቻል ማለት ነው።

ብልጠትን በነቃ ብልህነት በዕውን ልቦና እንዳላዩ ሆኖ አልፎ፤ ግን የመንፈስ ዘራፊውን ጥቃትን በድርጊት መርታት ይቻላል። ብልጠትን በብልህንት ክህሎት በእጅ ባሉ የድጋፍ ሰጪ መንፈሶች ቁጥብነት መስመር ማስያዝ ይቻላል። ለዚህ ነው የአማራ የሥነ - ልቦና ወጥነት በተከታታይ የአማራ ትጉኃን ተግባር ሊሆን የሚገባው … እስቲ ገልብጣችሁ እዩት። የኦሮሞ ሊሂቃን ወጥ የኦሮሞ ሥነ - ልቦና በ40 ከዛም ባለፈ ዓመት ሂደት ገነቡ። ከዚህ በኋዋላ አሁን ወደ ኢትዮጵዊነት መጥተናል እያሉን ነው። ኢትዮጵያዊነት ማግኔት ስለሆነ። ከሆነ እሰዬው ነው።  የአማራ ሊቃውንት ደግሞ እነሱ ከመፈጠራቸው በፊት ኢትዮጵያዊነትን አባቶቻችን ሠርተውበታል፤ የቤት ሥራውን ተክነውበታል። አባቶቻችን ያልሠሩበት „አማራነትን“ ነው። ስለዚህ ለአማራ ሊቃናት በተሠራው ተግባር አቅምን ከማባከን ባልተሠራው ኃላፊነቱ ላይ መትጋቱ ነው የወቅቱ ተግባራቸው ሊሆን የሚገባው። ማለትም የአማራ ሊቃናት የወቅቱ የትኩረት ምግባር ተጠቂ የሆነውን የአማራ ማንነት አህታዊ አድርጎ በሥነ-ልቦና አቅም አጎልብቶ ማውጣት ይሆናል ማለት ነው። የአማራ ሊቃናት የኃላፊነታችሁን አቅም ተረዱት። ታሪካዊ ድርሻችሁንም በውል ፈትሹት። አታደባልቁት ወይ አትቀላቅሉት። ከዚህ ላይ ሃላፊነትን ሽፍት የማድረግ ክህሎት ይኑራችሁ። የኦሮሞ ሊቃናት ግባቸውን ሰለመቱ ነው ወደ አልሠሩበት ኢትዮጵያዊነት ሽፍት በማድረግ ላይ ያሉት።  የአማራ ሊቃናት ደግሞ የዘመኑ ግባቸው ጋር ገና አልተገናኙም … አሁን ሊቃናቱ የጸሐፊ ተስፋዬ ደምመላሽ /ዶር./ ንድፋዊ ማንፌስቶ የሚያሳዬው ይሄንኑ ነው። አባቶቻችን በሠሩት ላይ እንዳክር ነው የሚሉት። መርከቧ ካለ ሹፌር ትሸከረከራለች ነው የሚሉን። የሚገርመው ከአማራ ሊቃናቱ ይልቅ የህዝቡ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ቀድሟቸው የትና የት ተጉዞ የአማራ ሊቃናት መቀደማቸውን እንኳን ማደመጥ ተሳኗቸዋል። ማለት መምራቱ ቀርቶ በኋዋላ ሆኖ ለመከተል አቅም አነሰ …. ነገረ ትርትር …

በዬትኛውም ሁኔታ እንዲጠፋ የተደነገገበት አማረ አቅሙን ለሌላ ስንቅ በፍጹም ሁኔታ ማበክን አይኖርበትም።  ለአቅሙ የቁጠባ ልዩ ተቋም መክፈት ይኖርበታል - አማራ። የራሱን መንፈስንም በሆነ ባልሆነው በተርት ተረት የትወና ሥራ .. ሥር መቅኖ ማሳጣትም የለበትም። አሁን ተዚህ ላይ እንደ ምሳሌ ላንሳ „ አማራ ብሄረሰብ ነው ወይንስ ብሄር“ የአማራ ትጉሃን /አክቲቢስት/ በማህበር የተደራጁት ናቸው ወይንስ የማህበራዊ ሚዲያ ትጉሃን ናቸው“ ይሄ አሁን አቅምን የሚተረትር ብቻ ሳይሆን፤ ሞራልንም የሚፈታተን ነው የሚሆነው። በገጀሞ የሚጨፈጨፍ ቤተሰብ አስቀምጦ በዚህ የቃላት ገበጣ መንፈስን ማባከን ከዘመናዊነት ባለፈ ጸረ ሰብዕነትም ነው። አማራ ስንክሳር ጉቶዎችን ንዶ በመንፈሱ አንድነት ብቻ ላይ ነው ተግባሩን በተከታታይና በታታሪነት መከወን ያለበት። ኧረ! ከዋርካው ከጎጃም ህዝብ ተማሩ። ለአማራ የዘላቂ ህልውና ተጋድሎ የቃላት ጨዋታ ግቡ ሊሆን አይገባም። ለአማራ የህልውና ተጋድሎ ምራቅን መዋጥ ያስፈልገዋል። ሴራም መርኹ ሊሆን አይገባም። አማራ በራሱ በእጁ ያለውን አቅሙን እያወቀ ድካም - ገብ ማድረግ አይገባውም። ንፈስ - ገብ ማደረግ የለበትም። ብርድ - ገብ ማድረግ አይኖርበትም። ታሪክም ላይ ብዙ ጊዜ ማባከን አያስፈልግም። ባለሙያዎች አሉበት። የአማራ የህልውና ተጋድሎ በራሱ የኃላፊነት ደንበሮች ላይ ጥንቃቄና ልዩ አትኩሮት ማድረግ ይገባዋል። አላስፈላጊ ቅራኔዎችን ውስጥ ገብቶ መነከር የለበትም፤ ጠላት ገዝ ከሆኑ አቲካራዎችን ለመግዛት መባከን የለበትም። የራሱ ታሪካዊ ኃላፊነት እኮ ህልቆ መሳፍርት ነው። አቅሙን ለዛ ያውል፤ ልብ ሸምቱ!

ጊዜው ካለ በውስጥነቱ ላይ ያሉ ዕሴቶችን፤ ትውፊቶችን አደባባይ እያዋሉ የሥነ - ልቦናውን አቅም በጽኑ ወጥነትነት መገንባት ነው የሚያስፈልገው። ድርጀት ኃይል ነው። ነጋ ጠባ ድርጅት ለመፍጠር ከመትጋት ያሉትን በአቅም አጎልብቶ በመንፈስ ረድቶ ግድፈታቸውን እያረሙና እያስተካከሉ ማጠንከር ያስፈልጋል። ማን እንበላችሁ? ማን ብለን እንጥራችሁ? እንደ ብላቴ „ሥም አጠረኝ“ እስኪባል ድረስ፤ ለመሆኑ አላችሁን? ለሚሉት ሁሉ በሙሉ ሞራላዊ አቅም፤ አብዛኛው መንፈሱን ሊመስጥበት የሚችላቸውን ጨዋ ወገኖችን ደግፎና ከብክቦ ማውጣት ይገባዋል። የአማራ አገሩ ኢትዮጵያ ናት። በመላ ኢትዮጵያ ያለው ይሁን ውጪ ሐገር እንደ ጨው ዘር ተበትኖ የሚገኘው አማራ የራሱ መንፈስ ነፍሱ እንድትነግረው ማድረግ የሚቻለው በንጡር ሥራ ብቻ ነው። ተቀናቃኞች መንፈሱ ለመኮርኮም ያገኙታል። ውጪ ሐገር ሳይቀር ፊት ይነሱታል፤ ያገሉታል፤ በደቦ ያጠቁታል ያልተገኘው አማራው እራሱን በራሱ ውስጥ ፈልጎ ከማገኝቱ ላይ ነው። ራሱን አማራው ራሱ ፈልጎ እንዲያገኝ እና ለራሱ የጸና መንፈስ እንዲኖረው ማደረግ ነው የሊቃናቱ ሥራ መሆን ያለበት። ከዚህ በተጨማሪ አማራ ከአባቶቹ የተማረው ታላቅነት „መቻቻል“ ነው። „አብሮነት“ ነው። ከእንሳሰቱ ጋር ተቻችሎ የሚኖረው አማራ በዬትም ሁኔታ፤ በዬትም ቦታ ከዚህ ሥነ - ምግባር ማፈንገጥ አይኖርበትም። አማራን በመንፈሳቸው የሚያገሉት እጅግ በርካቶች ቢሆኑም፤ እሱ ግን ያልተቆጠበ ፍቅሩን ለመለገስ ቆጥቋጣ መሆን አይኖርበትም። ምንጊዜም፤ በምንም ሁኔታ ሰላምታን በቅንነት መስጠት አለበት። ምንም ፊት ቢነሳው በግልም ሆነ በጋራም እሱ ግን ለፍቅር ተፈጥሮ ቅን እና ምቹ መሆን ይኖርበታል። በመንፈሱ ማህጸን ክፋትን እና ጥላቻን እንዲሁም ቅናትን ለደቂቃ ማስቀመጥ አይኖርበትም። አማራ ከተፈጥሯዊ ሰብዕናው ማፈንገጥ በፍጹም አይኖርበትም። ሌሎች ይጥሉት፤ እሱ ግን በቅንነት ይውደዳቸው - ከልቡ፤ አማራ የወላዊ እሴቱን ቀኖና በፍጹም ሁኔታ መተላለፍ አይኖርበትም። ዕሴቶቹ፤ ለመንፈሱ ክህሎት የትውፊት አዋለጆች ናቸውና። አማራ ዕሴቶቹ ሆነ ትፊቶቹ ህገ መንግሥቱ ሊሆኑለት ይገባል። „ህግ ተላላፊዎችን ጠላሁ“ ይላል ነብዬ እግዚብሄር ንጉሥ ዳዊት። መተላለፍ ጥሩ አይደለም … አብሶ ተፈጥሮን …  
  • ቄሮና ብጡሉ ገቢረ - ልቡ።

„አገር ትልቅ ቀውስ ውስጥ ናት- ኳሷ ኦህዴዶች ጋር ናት“ ከጸሐፊ አቶ ግርማ ካሳ
„የሌላውን ማህበረሰብ ሊያረጋጋ የሚችል ቁልፍና መሰረታዊ፣ ተጨባጭ፣ ከወሬና ከመግለጫ፣ ጣና ሄዶ እምባጭ ከመልቀም ያለፉ ተግባራት መፈጸም አለባቸው። በዚህም ረገድ አዎንታዊ እርምጃ እስካሳዩ ድረስ ሊደገፉም ይገባል።“ ያሳዝናል። ይገርማል። የአስተሳስብን አሽዋማነትንም ያመላክታል።
ጸሐፊ አቶ ግርማ ካሳ ከቶ ምን አድርገናቸው እንደሆን አይታወቅም በዚህ መሰል ጠናና ፍልስፍና ሐሤታችን እንዲህ፤ ፍሰችን እንዲህ የሚነጥቁን፤ ሰናያችን እንዲህ ጥላሸት የሚለቀልቁት፤ ሲሳያችን እንዲህ መቃብር የሚልኩት፤ ተስፋችን እንዲህ መቅኖ የሚያሳጡት። የማከብረዎት አቶ ግርማ ካሳ የቄሮ ጉዞ ወደ ጣና በህሊና የበቀለውን አረም ለመንቀል ነው የተመመው እሺ … ይሄ በሴራ ፖለቲካ እሚብጠለጠለውን ቅንነት ለማረቅ፤ ወጌሻ ሆኖ ለመጠገን፤ የፈለሰውን መተሳሰብ - መረዳዳት - መደማመጥ - መተዛዘን - መቻቻል ትንሳኤውን ለማወጅ ነው …. „ጣና ኬኛ“ ከሰማይ የተላከ የምህረት ዓዋጅ ነው - ለእኔ። ወደ ሥልጣኔ እንብርቱ ነው ቄሮ የማተበው። በመደዴ ከሌላ ኩስምን ፍላጎት ወይንም ብትክ አምክንዮ ጋር እባከዎትን አያጣርዙት። ስለ መዳህኒተዓለም ብለው …።

ቄሮ በዓለም ኢትዮጵያን ተጭና የድንቃዊነት ተሸላሚዋን ትግራይን ሊጎበኝ አይደለም የሄደው። መከራን ለመጋራት እንጂ። ዕንባን ለመካፈል እንጂ። ቄሮ የበካፋ፤ የገላውድዮስን፤ የሱሱንዮስን፤ የፋሲልን መንፈስ ሊፈትሽ ነበር ወደ መንፈሳዊ ዕትብቱ ወደ ልዑቅ ባዕቱ የገሰገሰው። ቄሮ ልቡ ትልቅ ነው። የበርሊንን ግንብ የደረመሰው በቃላት አልበረም። 200ቶቹ የአብቾ ቅኔዎች ውስጣቸውን ፈልገው አግኝተውታል። ፍቅርን ሰንቀዋል። ወያኔ የቁቤ ትውልድን ሲገነባ ከዚህ የዕትብተ መሠረቱ ኦሮሞን ለመንቀል አስቦ፤ ከታሪኩ ጋር እንዳይተዋወቅ በቋንቋ ቀፍድዶ አሰረው። የፌድራሉ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ሆኖ፤ ግን የቁቤ ትውልድ በስውር ሴራ ማዕቀብ ተጣለበት። ትግራይ ላይ ግን ይቻላል። የትግራይ ልጆች የትም ቦታ በዬትኛውም ማዕከላዊ የመንግሥት ተቋማት፤ በሥነ - ጥበባት ዘርፍ ባለሙሉ መብት ናቸው። አማርኛ እንዲናገር የማይፈቀድለት ትውልድ ያለው ማህበር ደራጎን በወረራ በሰፈረባቸው በወልቃይት፤ በጠገዴ፤ በራያ ያሉ አማራዎች ብቻ ናቸው። ስለምን? እትብቱን ከእትብቱ ጋር በሴራ መቀስ ልክ እንደ ቁቤው ትውልድ ለመበጣጠስ። ለወደፊትም ወያኔ ሆነ መሰሉ አሸኮኮ ከተሰዬመ ከወልቃይትና ከጠገዴ እንዲሁም ከራያ የሚፈጠሩ ሳተና ወጣቶች ሀገራዊ ለሆኑ ጉዳዮች ባይተዋር ይሆናሉ ማለት ነው። እና የአብቹ ጀግኖች እስከ ጥግ ድረስ ሄደው ነው ሴራውን የደረመሱት። ውይ አንድ ነገር ትዝ አለኝ …  በቁቤ ትውልድ ለካንስ „ከበቡሽ“ የሚባል ሥም አለ። አዬዋት ወጣት ከበቡሽ ቶለሳን። „ከበቡሽ“ የጎንደር አማራ ዋነኛው ሥም ነው። ሚዲያ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥሙን ሳዬው የነፍሴ ሥም ስለሆነ አፍጥጬ ነበር የቀረሁት። ቄሮ ወደ ተዝቆ ወደማያልቀው ከምድር በላይ ብቻ ሳይሆን፤ ከከርሰ ምድርም ውስጥ ወዳለው ጥልቅ የሚስጢር ብታቱ፤ እትብታዊ መንፈሱ ነው የተመመው። አቶ ግርማ ካሳ ይህንን ልቅና ነው የሚያጣጥሉት፤ የሚያብጠለጥሉት፤ …ቅኝት የድህነት … ወጣቶች በቅኔዊ የህሊና ልቅና በልጠውናል ይህን እንቀበለው … 

ግብረ ደራጎን አልዋለም አላደረም ዘመቻውን ሲጀምረው። የጥላሸቱ ዘመቻው በቅጽበት ነበር ሁልአቀፍ ሆኖ አገር ምድሩን ያካለላው። እነተጋሩ ቀንዳቸው ነበር የሰላው። ያን የቡርቃ ዝምታ ደማሚት ከሙት መንፈሱ አስነስቶ አማራን ሲያሳጭድ የነበረው ሚዲያ ሁሉ ለዛ ሴራዊ ዘመቻ ሲያሰደገድግ ነበር ትናንት። የሸሩ ተራራ ሲደረመስ ደግሞ እንደ ዕብድ ነው ያደረገው ማህበረ ደራጎን …. እሰከነ ሚዲያው። ተበቅሎታልም። ስለምን „ጣና ኬኛ“ ሰውኛ አልነበረም። የ40 ዓመት ከዛም የሚያልፍ ጣሊያን የቀበረውን የፈንጅ የቤት ሥራን ነው ከሥሩ ያናገዳገደው። የናደውም። ለነገም የታጨ ታላቅ ሴራም ሊኖር ይችላል። „ከመቃብርህ ከመቃብሬ“ የሚሰኝ። እርግጥ „ጣና ኬኛ“ በሁሉም ዬነፃነት ፈላጊዎች ተወዳጅ ላይሆን ይችላል „የጣና ኬኛ“ እርምጃው። ግን ሚሊዮኖችን አስፈንድቋል። ለነገም „ሰከን“ በልን አስተምሯል። ሰዉ „የኦሮሞ ደም ደሜ ነው“ ነው ሲል የአማራ ተጋድሎ ለላንቲካ ይመስለዋል። ምንጭና መሠረት አለው። ሰንሰለቱ እትባታዊ ነው … የኦሮሞ ሊቃናቱ ለሥምና ለማንፌስቶ ሲሉ ለቄሮ ባያመሳጥሩለትም ግን ሰማይ ደውሎ ነገረው - ለቄሮ። ጽህረ አርያም ሃሎ አለው - ለቄሮ። ነገረው - አርያም አስተማረው እናም ፈጸመው …. ቅድሰተ - ቅዱሳን ይሏችኋል ይሄ ነው። ኢትዮጵያዊነት ሊመጣ የሚችለው በዚህ መስመር ብቻ እንጂ ወጣቶችን በመንፈስ በመጫን አይደለም፤ እንደ አማራ ሊቀ ሊቃውንቱ ጸሐፊ ተስፋዬ ደምመላሽ/ ዶር/ ማንፌስቶ።

ሌላው በቄሮ የተጋድሎ አንባ ምንም ማንም ትውር አይልበትም። ለተለጣፊ አፍቅሮተ ማልያ ቄሮ ልብ ውስጥ ብጣቂ ቦታ የለውም። ድፍረቱም የለም ወደ ዛች ጠጋ ለማለት። የጥለቷን ጫፍ እንኳን ለመንካት። ተጋድሎው ዓራት ዓይናማ ብቁ ባለቤት አለው። ተጋድሎው በግራ በቀኝ ሙሉ ጋራንቲ አለው። ቄሮ ልቡ ትልቅ ስለሆነ ለመናጆ መሸመቻ፤ ለሥም አንቱታ መሸቀጫ ለመሆን አይፈቅድም። ፈጽሞም አይደፈርም። „በሞኝ ክንድ ዘንዶ ሲለካበት“ የሚታዬው በአማራ ዬህልውና ተጋድሎ ብቻ ነው።

ይህንን የግንዛቤ ክፍተት ለሞሙላት የሚተጉትን ወጣት የኔታዎችን ነው ሊቀ ሊቃውንቱ ጸሐፊ ተስፋዬ ደመላሽ /ዶር./ “የዜሮ ድምር ጨዋታ” „ነውጠኞች፤ ይህ ነገድ ተኮር አስተሳሰብ ለአማራዉ ተሟጋች በሆኑ በርካታ ስብስቦች ዘንድ ሰፍኗል። በተጨማሪ፣ ለየት ባለ ቅጅት አስተሳሳሰቡ የአማራዉንና የሌሎች ነገዶችን እንቅስቃሴዎች በብልሃት ለራሳቸዉ ፖለቲካ አላማዎች መከታተያ መሣሪያ ማድረግ በሚጥሩ ወገኖች በተለይ ሻቢያ በግንቦት ሰባት ድርጅትና ሚዲያ አማካኝነት በሚያደርገዉ ሙከራ“ የሚሉት። ሌሎቹ ደግሞ „ወያኔ በጎሳ ፖለቲካ ያሰታጠቃቸው፤ መልምሎ የላካቸው“  በማለት ያሸማቀቁዋቸው። አኒህ ብርቅዬ ሊቃ ተጨባጩን ያላሰሰ የተንሳፈፈ ጹሑፍ ነበር የጻፉት። ለነገሩ እንደ አሉታዊ ማውጫ ለዘለዓለም ያገለግላል። ከጥቅም ውጪ አይደለም እንደማለት … የሰብዕዊነት እንጥፍጣፊ እንዴት አማራ ሆኖ ተፈጥሮ ምድረ በዳ ይሆናል። አማራ ሳይሆኑ ብቻ በሰው ተፈጥሮ ስሌት…  በቀስታና በገጀራ የሰው ልጅ በባዕቱ በደም አላማ ሲነከር፤ ነፍሱጡር ጫካ ላይ በሰቀቀን እና በስጋት ስትወልድ ቅዱሳን ወደ መሬት ሲመጡ ገጀሞ ሲቀበላቸው … ግን እንዴት … አማራ ዋቢ አልባ፤ ባለቤት አልባ እንደባዘነ ብን ብሎ ይቅር ይባላል። መሃከነ!

የሆነሆኖ ሙሁሩ የሚሉት አንጋችነታችሁን እንጂ ለኢትዮጵያዊነት መፈለግ ያለበት ከፍ ላለው የፖለቲካ መድረክ እናንተ ምንድ ናችሁ ዓይነት ነው። አንገታችሁን ቀና አድርጋችሁ በአማራነት መውጣት የለባችሁም ነው። ይህን የሚያቀነቅን ውግዘ ታርዮስ ነው የሚሉት። ናፍቆቶቼ ሰንበት እና እኔ በመዝመሩ ዳዊትና በኢትዮ ሚዲያ እነሰክናለን። ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር ይህን ጹሑን ያነበብኩት። ስጨርስ እንባዬ ተዘረገፈ። ለመንፈሳችን እንኳን እንደ ሊቀ ሊቃውንትነታቸው ስለለምን እንዳልሳሱለት ይገርም ነበር፤ እና ሌሎች ነገሮች ገጥመውኝ እንጂ ከጋሼ ተክሌ የሻው በፊት እኔ ነበር መልስ ልሰጥበት መሰናዶ አድርጌበት የነበረው። የጸሑፉ መንፈስ የመርዝ ብልቂያጥ ነው። ማላታይን ወይንም ዲዲቲ።  

ህም! የአማራን ተጋድሎ ትጉንን የደራጎኑ ማህበር  „ሻብያና ግንቦት 7 ያሰማራቸው“ ይሏቸዋል። ግንቦት 7ትም ደስ እያለው ሽልማቱን ያስተናግዳል። ምንም ያልተገበረበት መና ከሰማይ ሲወርድለት ሊፈረድበት አይገባም። ማህበረ ዳረጎን የአማራ ተጋድሎን አብዮት አክሎ በዚኸው በሌሌና በአማራ መንፈስ ውስጥ በጭራሹ ባልተጠነሰሰ፤ ንክኪም በሌላው ሁኔታ በአሉታዊ አምክንዮ ይጠቅልለዋል። ያን ሰፊ የሚሊዮኖች ድምጽ የበቃኝ ተጋድሎ። እሳቸው ደግሞ ሊቁ ጸሐፊ ተስፋዬን ደምመላሽ /ዶር/ ማለቴ ነው በተጋድሎው የደም ግብር የመንፈስ ተጠቃሚ ለመሆን ይሻሉ፤ ግን ከመሰረታዊው የተጋድሎ ሚስጢራት ለመነሳት ድፍረታቸው እንደ አቶ ገድሉ አንዳርጋቸው ሾልኳል ወይንም ተላልፈውታል። እንደ ዘመነ ኢህአፓ የአማራ ልጅ ከእንግዲህ በጅ ማለት በፍጹም የለበትም። እነ ዋለልኝ የተከሉት ነቀርሳ ነው ዛሬ የአማራ ኦሾቲዝም በምደረ ኢትዮጵያ እንዲህ አና ያለው። ሁለተኛ ዋለልኝ ለአማራ በፍጹም ሁኔታ አያስፈልገውም። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ሲሰላ አማራው ለራሱ፤ እራሱ ብቻ ሳይሆን በራሱ ውስጥም እሱን የሚታገሉ ህጻጾች ዛሬም እንዳሉ ያሳያል። ለዛውም በዚህ ዘመን ልክ እንደ ዛሬ 50 ዓመት የሚያስቡ ሰዎች መኖራቸው ባያስገርምም፤ የትውልዱን የብቃት ክፍተት ግን ወለል አድርጎ ያሳያል … ይህም ብቻ ሳይሆን ተጨባጩ ከማህበራዊ ንቃተ ህሊና ክህሎት ጋር ያለውን መስተዋድድም የማድመጥ፤ የመመርምር፤ አቅም ሆነ ለመወጥታ የፈቃደኝነት ውሳኔንም ውስኑነትንም ያመለክታል። በዚህ ማህል ነው የእነ ጀግኒት ንግሥት ይርጋ መካራ ከቁጥር የማይገባው፤ የእነኮ/ ደመቀ ዘውዴ ተጋድሎ ተርጓሚ አልቦሽ የሚሆነው፤ የእነ አቶ አታላይ ዛፌ መስዋዕትንት ጥግ አልባ እንዲሆን የተገመደለበት፤ በሺህ የሚቆጠሩ የወልቃይትና የጠገዴ አበው፤ ወጣት እልቂት ከውስጥ አለመኖሩን የሚያመሳጥርልን …. ጸሑፍ ነበር የሊቁ ጸሐፊ ተስፋዬ ደምመላሽ/ዶር./ አመክንዮ።

ስለዚህ የአማራ ተጋድሎ አቅሙን ላለማስደፈር፤ አቅሙን ለራሱ አቅም ብቻ ሊያውል የሚችልበትን የአቅም አስተዳደሪ፤ መሪ፤ ሙሴ፤ ቀያሽ መሃንዲስ በእጅጉ ያስፈልገዋል። ጥቃትን ብቻ እሽሩሩ ከማለት የነገንም ጥቃት በአቅም ለመመከት የሚያስችል የማህበራዊ ንቃተ ህሊናውን ከፍ ወደ አለ ደረጃ ማሸጋገር ይኖርበታል። እርግጥ ነው አቅም ያለው ሚዲያ ያሰፈልገዋል። „የብራና ራዲዮ“ አያያዝ ጥሩ ይመስለኛል። እርግጥ የትረካ ራዲዮ መሆኑ ተደጋፊና ተመራጭ ባይሆንም፤ ከሴራ ፖለቲካና ከአፍቅሮተ ማልያ ያፈነገጠ በመሆኑ በቂ እገዛና በቂ እንክብካቤ ቢደረግለት የተሻለ መሥራት ይቻላል ብዬ አስባለሁ። አብሶ ከግዮን ጋር በጋራ ለመሥራት ቢያስቡ ቢያንስ የሥነ - ልቦና አቅምን በአማራ ቁመና፣ ወርድና ሥፋት ልክ በመገንባቱ እረገድ የራሱን ድርሻ ለመወጣት ይችላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ … አማራ  በአፄውስ ሆነ በደርግ ዘመን ከቶ ምን አግኝቶ። የትኛው ወጥ አማራ ነውስ ቁልፍ የሆነ የሀገር ጠ/ሚር እና ፕሬዚዳንት የሆነው። አሁን እንኳን ለመንፈስ እጮኛ የሆነ አማራ የለም። ያሳፍራል!
በበይ ተመልካችነቱ እንኳን የወቃሳ ናዳ ነው አናቱን ሲበጠርቀው የኖረው። አሁን ግን አማራው የፖለቲካ ተወዳዳሪ፤ ተፎካካሪ ሆኖ ለመውጣት አቅሙን በአቅሙ ብቃት ከብክቦ መገንባት አለበት። ነጥሮ መውጣት አለበት። የሌሎችን የጎሳ ድርጅት መሪዎች ይዘረዘርና አማራ ላይ ሲደረስ ማን ብዬ ልጥራህ? ሥም የለህምና ይሆናል ዕድምታው። አሁን ባለፈው ጸሐፊ አቶ ያሬድ ጥበቡ የጻፉትን የትችት ዕይታ ደጋግሜ አንብቤው ነበር። ጨካኙን የወልቃይትና የጠገዴ እናቶችን አምካኝ አረመኔ ዶር. አረጋይ በርኽ በሥማቸው ነበር የጠቀሱት። አማራውን በዞጉ የወል መጠሪያ አንስተው መልስ ሳይሰጠብት መቅረቱን በተደሞ ተደምመውበት ግን እንደ ሎሬቱ ሥም አጠረኝ ሆነባቸው። „ማን ይበሉት? ምን ይበሉት?“ ሞት ነው ወኔ ላለው አማራዊ መንፈስ። አቅሙ ተፈጥሯዊ ለሆነው አማራ … ውርዴት ነው ውርዴም። አቅም የማይችለው የእንቢተኝነት አማራዊ ነበልባል አገር ቤት እያለ …

በሌላ በኩል ቄሮን ሊቃነቱ አንበሶቻቸውን፤ ጀግኖቻችን፤ ውርሳችን፤ ቅርሳችን፤ መሪዎቻችን፤ ጥቃት አውጪዎቻችን በማለት  የኦሮሞ ሊቃናት ይመኩባቸዋል፤ ጥግና ከለላ ለመንፈሳቸው ሆነዋል። ለቄሮ የአቅም መንፈስ እጅግ በሚመስጥ ሁኔታ ጥንቃቄውን ተክነውበታል። ሙሉ አትኩሮትም አለ። ለዚህም ነው የሥልጣኑን ክፍተት እንሞላለን የሚሉት ይሎች ውስጥ ሁለት አውራዎቹ በመሪነት ቁብ ብለው በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት። ያ አቅም ነው ከተረሱበት በፍለጋ እንዲገኙ ያደረጋቸው። የእኛዎቹ ሊቃናት ደግሞ የአማራ ህልውና ተጋድሎ ትጉን ብቻ ሳይሆን በአንድ ወር ውስጥ ስለ አማራነቱ 20 ሺህ ወጣት ለካቴና የተዳረገበትን፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የሞቱበትን፤ ከኑሮ የተፈናቀሉበትን፤ ትዳራቸውን ያጡበትን፤ ፍሬዎቻቸውን የገበሩበት የአማራ የማንነት ታላቅ መንፈስ፤ ጥንግ ድርብ ብቃቱን ያስመሰከረውን የአማራ ተጋድሎ ማሳ ታታሪዎችን ደግሞ „ነውጠኞች የግንቦት ሰባትና የኢሳት ተዘዋሪዎች እያሉ ያብጠለጥሏቸዋል።“ ልክ እንደ ማህበረ - ደራጎን።
ይህን ክፍተት ለመሙላት ከነፍሳቸው ያሉ አማራዎች ቢያንስ ሚዲያ ላይ ዝበቶችን ደፍረው ወጥተው ሃይ ሊሏቸው ይገባል።  የአማራ ተጋድሎ ታታሪዎችም ከቄሮ ነፍሶች የአያያዝ ጥበብ ለመማር፤ ልምድ ለመቀስም መትጋት ይኖርባቸዋል። የመረጃ ፍሰቱ እራሱ በሚያሳዝን ሁኔታ የሌላ አቅም አድማጭ መገንቢያ ሆኖ ነው የሚታዬው። መረጃ ማለት እኮ ማሸነፍ ነው። መረጃ ቀድሞ ያገኜ ሃይል ሁልጊዜም በድል ላይ ይጓዛል። ብራና ራዲዮ አቅሉን በዚህ ላይ ማስከን አለበት። የዝግጅት ቀን መጠበቅ የለበትም። እንደ ደረሰው ወዲያወኑ በአጭር ሠርቶ ማሰራጨት አለበት።

  • ትኩረትን ስለማትጋት። 

የአማራና የኦሮሞ ጉልበታም የነፃነት ተጋድሎዎች መንፈሳዊ ግንኙነቱም በሥላሴ ሚስጢር እንደ ተዋህዶ ዶግማ ዓይነት መስመሩን በጠራ፤ በነቃ ቅንነት ሊያይዙት ይገባል። ነፋስ ሳያስገቡ „ሙያ በልብን“ መርቸው ሊያደርጉት ይገባል። ግን በለበጣ አይሁን፤ የወረትም አይሁን። ወጀብ በተነሳ ቁጥር በተሰናበቱት የቅራኔ ቡቶቶ መጠቅለል አይኖርባቸውም። በሴራ ፖለቲካ መርዝ ቅኝትም መሆን የለበትም፤ የኔነት/የእኛነት 200 የአብቹ የቅኔ ቅኝቶች በመንፈስ ድንግልና ጣና ላይ የሠሩትን ቅናዊ ተግባር ሰብከተ - ፍቅርን ሊያመልኩበት ይገባል። ለእኔ የተራራው የብፁሃን ስብከት ነበር „ጣና ኬኛ።“ ልብ - ለልብ ተያያዙ። ልብ - ለልብ ተፈላለጉ። አንድ መንፈስ አለ … ቅዱስ የሆነ እትብቱን ከእትብቱ ያቀራኘ … ወደ ሚስጢራችሁ አተኩሩ ግራ - ቀኛችሁ። ኢትዮጵያን የሚታደጋትም ይሄው መስመር ብቻ ነው። ከሴራ ፖለቲካ የጸዳ ንጹህ ልብ ያስፈልጋል። አምላክም እንዲረዳ …
የኦሮሞ ወገኖች ቢያውቁት ወያኔ ማንፌስቶውን እንደገና ማደስ ቢያስፈልገው „ጠላቴ አማራና ኦሮሞ ነው“ እንደሚል በሙሉ ልብ መናገር ይቻላል። ልክ እንደ አካፋና ዶሞ መንፈሱን እስከ ተጠቀመበት ድረስ ነው እንጂ ወዳጅነቱ ከዚያ ካፈነገጠ ድርድር የለም በማህበረ ደራጎን ቤት … ይሉኝታ፤ ማተብ፤ ፈርሃ እግዚአብሄር ብሎ ነገር የለም … ቀድሞ ነገር አልተፈጠረምም …
    
  • የነገ አሉታዊ ምስለ ከረባት።

አሁን ለአማራው የጨለማ ዘመኑ ነው። አማራ ኢትዮጵዊ አይሁድ ነው። በተገኘበት ቦታ በተገኘው የመግደያ ዓይነት ተጨፍጭፎ እንዲሞት የተፈረደበት። መውጫ መግቢያ ተነስቶ እንደ አጥነት በገጀሞ የሚከተከት። እንደ ማገዶ በቤቱ እያለ እሳት የሚለቀቅብት። እንደ ዱር እንሰሳ በጦርና በቀስት ታድኖ የሚገደል። በተንቀሳቀሰበት ቦታ ሀሉ ለመንፈሱ እራፊ መሬት አልቦሽ የሆነ። ሀገር እልቦሽ የሆነ። እርስት አልቦሽ የሆነ - የህግም የመንፈስም፤ ሃማኖታዊም፤ ኪነ ጥበባዊም ጥበቃ የማይደረግለት ምንዱብ ከቶ እንደ አማራ ማን አለና?

ዛሬ በቅጡ ካልተያዘ የነገ የጨላማ ዘመን ከአሁኑ መዘርጋቱን አማራው በጥላቻ ተውጦ ሳይሆን፤ ምራቁን በዋጠ ማስተዋል ሊታደመበት ይገባል - በነጠረው በሃቁ ዙሪያ። አማራ ወጥ የሥነ - ልቦና አንድነትን በአስቸኳይ ገንብተህ መታጋል ካልቻልክ፤ ነገም ዘመቻ ምንጠራው አይቀሬ ነው። አፍሪካውያን „አማርኛ“ የአፍሪካ ህብረት ቋንቋ እንዲሆን ይተጋሉ። የሀገር ተስፋ ይሆናል የተባለው ብሄራዊ ፓርቲ ጉባኤውን ሲያካሂድ መፈክሮች ሁሉ በትግረኛ ቋንቋ የተሞሸሩ ነበሩ። አንድም እንኳን መፈክር በአማርኛ የተጻፈ አልታዬም። ተልዕኮውን ለመፈተሽ ጥቅሉን ዕሳቤ በተን ለማደረግ ያጋብል ግራ። እና አይዋ አማራ አንተ ብቻ አይደለህም በረጅም ጊዜ ሂደት ቋንቋህም የተደገሰለትን አይታወቅም። አንተ ስትጠፋ፤ አንተ ስተከስም፤ አንተ ስተሟሽሽ የቋንቋ ስያሜህም አብሮ በአዲስ መልክ ይሰዬማልሃል። የዘመናት ዕሴቱም የሌላ ሲሳይ ይሆናል። በአንድ ጊዜ ለማጥፋት 26 ዓመት አልተቻለም፤ ግን ሌላ 26 ዓመት ታጭቶለታል ማለት ነው። ለአማርኛ ቋንቋ በታዬው የዕውነት አንባ ዕምቅ ድርጊቱ በዕዝነ ልቦና ሲፈተሽ። ለዛውም የመንፈስ ሴል በሆነው አማራው ሙቶ፤ ደምቶ፤ በመሠረተው ድርጅት የአቅም ጥሪት ላይ ተሁኖ። የዛሬው የወልቃይትና የጠገዴ የማንነት ጥያቄ የእንብርቱ አስኳል ነበር ያ ቀደምቱ የአርበኛ ድርጀት፤ ሲደራጅ የመከላከያ ኃይሉን ክፍተት ለመተካት ተብሎ ነበር። ዓላማውም ግቡም ይሄው ነበር። ዛሬ ግን የሚሰማው ደግሞ ሌላ ነው … እና ነገስ በአሉታዊ ታቱ እያለ መሆኑ ከቶ አይታይህምን - ማህበረ አማራ? „ልብ ያለው ሸብ“ ይላል የጎንደር አማራ …
  • ማያያዣ … 

ቆንጅዬዋ ተዋናይት ፍርያት የማነ የመቀሌ ሴቶችን አብዳ ስታሳብድ፤

Sunday with EBS/ እሁድን ..ኤስ: Entertainment / Interview with Mekdes Tsegaye

 

ማህጸንተ ጀግኒት ንግሥት ይርጋን ለጀግንት የተፈጠረችበት የነፍስ ዐውደ ምህረት - ምስባክ።

ይህ ጎንደር ነው! ይህ የአይበገሬነትና የፅናት ድምፅ ነው!

https://www.youtube.com/watch?v=efE7s4ymR_U&t=115s

ታላቅና ታሪካዊ የተቃውሞ ሰልፍ በጎንደር ዉስጥ ተደረገ
ክወና።
ስታውሳላችሁ አይደል የኔዎቹ … ነባቢተ ፍሬዋ ተዋናይት መቅደስ ጸጋዬን የሠራቸውን ትውፊታዊ ታምር። አሁን እራሱ ሳስበው ህልም - ህልም  ነው የሚመስለው። ለካንስ የህዳር ልጅም ናት። ህዳሮች ቁጥር ስፍር የሌለው ፕሮጀክት ነው በስፋት የሚያቅዱት። አያልቅባቸውም። እንደ ጸሐፊ አብርኃም ጉዝጉዜ ዕይታም ንጹሃን ናቸው ይላቸዋል። የሆነ ሆኖ ወያኔ በመቀደሙ ተጸጽቷል። ተጽዕኖ ልታሳድር ትችላለች ወደሚላት ለእንደራሱ አዲስ ደጎስ ያለ ተጫማሪ በር ከፍቷል። ያ የተግባር ንግሥቷ የመቅደስ ጸጋዬ የመንፈስ አቅም ርቀት ለወያኔ እንቅልፍ አልሰጠውም። ስለሆነም በእሱ መንፈስ ውስጥ ያለች ነፍስ አስፈለገው እና ለፉክክሩ በሚያመች መልኩ የመጀመሪያ „እሁድን በኢ.ቢ.ኤስ።“ የዚህን ፕሮግራም መክፈቻ እፍታ ከራሱ ምዕናባዊ መንፈስ ጋር ማጣመር ፈለገ። … የነገ ቀጣዩ የሰርግም የመንፈስ የህሊና አቅሙ በትውስት ወይንም በኩረጃ  ከተገኜ የሚታይ ይሆናል። … የሆነ ሆኖ እስኪ ተዋናይት ፍርያት የማነ „ውሎን“ አሳይታናለች። መንገድ ላይ ሻይና ቡና ሸጠው የሚያድሩ የእነዛን ባለቤት አልባ ወጣት የአዲስ አባባ ሴቶችን የቀን ውሎ ምን ገጸ ባህሪ እንዳለው። ብዙ ሽልንግንም ስትቆጥር አይቻታለሁ። እንጃ መደበኛ ተዳዳሪዋ በቀን ይህን ያክል ትሸጣለች ብዬ ለማሰብ ከበደኝ። ኧረ እግዜሩም ያዳላል መሰል … ነው እንጂ …
እሰቲ  ደግሞ የማህበረ ደራጎን ውሎ በትውልድ ቦታ ከምትጋራት እሰረኛ ንግሥት ይርጋ ዘንድ ሄዳ፤ ያን ነፍስን በጋለ ብረት በሚገርፈው የአረመኔዎች ከተማ ኑሮውን ‚በውሎ‘ ዝግጅቷ ትጋራው ይሆን? ጠበቃስ አቁማ ትሟገትላት ይሆን? ማለቴ እንደ አብሮ አደግ የቀሃ እና የአንገረብ  ውሃ ተጋሪነት … እንደ አንድ የሚዲያ ሰውነትም ሰብዕዊነትን መርህ እንደ አደረገ ሰው እንደ ማለት።
የእውነት አንድ ነገር ግን ወድጃለታሁ። ያው የጎንደርን ውሃ ጠጥታ አይደል ያደገችው። ረጋ፤ ደልደል ያለች ናት። ትምክህትም አላዬሁባትም - በጭራሽ፤ እርግጥ የተሰጣትን ኃላፊነት አቅሟን ለክታው ይመስላል ገና አላመነችውም። ውስጡ ላይ ሆና አላዬኋትም። ነፍሱን ያገኘችው አይመስለኝም። የሆነ ሆኖ ስክነቷን እጅግ አድርጌ ወድጀዋለሁ። እራሷንም ዝቅ አድርጋ ነው የጀመረቸው። መልካም ነገር ነው። ለነገሩ ከዚህ ልውጣ ብትልም አትችልም። ስለምን ? የአማራ ሥነ - ልቦናዊ ተጽዕኖ አለና። ከማህበረሰቡ ሳታውቀው በህሊናዋ ውስጥ የበቀሉ ብርቅዬ ወጥ የአማራ ዕሴቶች አሉና።  
በሉ እንግዲህ … የኔዎቹ እኔም እንደ ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድ እንደሚለው  „ልብ ያለው ልብ ይበል“ ብዬ ልሰናበት ….
„አማራነት ይከበር!“

መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።