የአቦይ ስብሃት ኑዛዜ - ተናውዞ - ወርዞ።

የአቦይ ስብሃት ኑዛዜ በደመመን ጫና ናውዞ …
                                          ከሥርጉተ ሥላሴ 18.11.2017 (ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ)


የእግዚአብሄር ኃይል እንዲህ ይላል „በምድር በታች ያለ እባብን አዘዋለሁ፤ በባህር ውስጥ ያለ ዓሣን አዘዋለሁ፣ በሰማይ ያሉ ወፎችንም አዛቸዋለሁ፣ በምድረ በዳ ያለ የበረሃ አህያንውንም አዘዋለሁ፣ ከአድማስ ጀምሮ እስከ አድማስ ድረስ የኔ ገንዘብ ነውና። በፊቴ ድንቅ ሥራን የምሠራ፣ ታምራትን የማደርግ እኔ ነኝናበምድርና በሰማይ ከሥልጣኔ የሚያመልጥ የለም ወዴት ትሄዳለህ ምንስ ትሠራለህ የሚለኝ የለም።“
(መጸሐፈ መቃብያ ቀዳማዊ ምዕራፍ ፳፭ከቁጥር ፭ እስከ ፮)
  • ተዬት ላይ ይጀመር ይሆን፤ ተይህ ላይ … እንዲህ

 „ፌድራል ሥርአቱ አንድ ነው።“ ይሉናል አቦይ ስብሃት። እኛስ ምን አለን፤ አዎን፣ በወያኔ ሃርነት ግዛት ሥር - የወደቀ፣ የትግራዊነት ህልም ማስከበሪያ፣ አህዳዊ ማዕከላዊነቱ የጠበቀ የትግራይ መሳፍንት ሥርወ መንግሥት። በነገራችን ላይ አቦይ … ይህቺን የክልል የምንትስ የምትለዋን የጨዋታ ማሟያ ተወት ቢያደርጓት ምንስ ነበር። „ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ“ አይሆንበዎትንም አቦይ? ለነገሩ ሽበት ሆድ ውስጥ እንጂ … 
„ከሚወድቁት ሐገር ተርታ የማዬት ምኞት “ ይላቸዋል የተቃዋሚ/ ተፎካካሪ ኃይሎችን። „አቅማቸውም በመፈንቅለ መንግሥት ለመምጣት አይፈቅድላቸውም“ ባይም ናቸው። ከፊታቸው ያለውን የታመቀ የዕንባ ቦንብ፤ የበቃኝ ፈንጅ ግን ሊያዩት ፈጽሞ አልቻሉም። ቃለ ምልልስ አድራጊውም ረጋ ብሎ የአቦይ ዓይናቸው የናፈቀው ይመስል ትኩር ብሎ፤ ግን ውስጣቸው የሚጎለጉለውን ጉድ ያሰተውላል። የውነት ግርም ብሎታል። የሆነ ነገር አልገናኝ ብሎታል። አቦይ የትኛው ፕላኔት ላይ ሆነው መልስ እዬሰጡ ስለመሆኑም በውስጡ ሙግት ላይ ያለ ይመስላል።
ወቼ ጉድ! አለ የሐገሬ ገበሬ። ይህቺ የአስር ደቂቃ ተ-ሃያአንድ ሰከንድ „የፊት ለፊት“ ቃለ ምልልስ ስንቱን ጉድ „ከደጉ ዘመን ሰዎች¡“ አስደመጠች። መጥኔ ላንቺ! ኢትዮጵያ በደም ላይ ተነከርሽ እንዲህ ዝምንምን ይሉብሻል እነ ማህበረ - ሳዖል። ቀለጡብሽ። ቅልጣናቸው ፈሰሰ … ልክም፤ ድንበርም አጣ - በአምክንዮ አቅምም ነጣም።
  • እንዲህም ሆነ

አሁን ነው እንዴት ዋልሽ ልል ናፍቆቴን ኢትዮጵያን ገባ ስል የአቦይ ስብሃትን በፍጹም ሁኔታ ደመመን የተጫነውን ኑዛዜ ያዳመጥኩት። ዝም ብዬ ለተወሰነ ደቂቃ አስቁሜ ቁጭታቸውን፤ ውስጣቸውን፤ ተክለ ሰውነታቸውን በጥሞና ጠለቅ ብዬ ዳሰስኩት። ግብረ ምላሹ የመላዕከ ሞት እስትንፋስን ነበር ያስተዋልኩት። የምር። አቦይ የሆነ ደመመን ተጭኗቸዋል። የሆነ መከራ ረቦባቸዋል። ወይ በእግዜሩ ቁጣ ሞታቸው ተቃርቧል፤ ሰኔል እረጥቧል፤ ልጡም ተዘጋጅቷል። ወይ ከበላያቸው ላይ ህንጻው ሊደረመስ ኤሉሄ! እያለ ወይ ደግሞ ስደቱን ሊቀላቀሉት ነው፤ ወይ ደግሞ „ማነው ባለ ተራ ይጥመድ“ … አንተም ተጠርነፍ ከች ሊል እያኮበኮበ ይሆን ያሰኛል። እንጃ ፊጢጥ ማለቱም ከመጣ በጭንቅ አምጦ ነው። ዝብርቅ ብቻ ሳይሆን ቅጥ አንባሩ መልክ አልባ ሆኖባቸዋል። አፋቸውን እሬት … እሬት ብሏቸዋል። ብቻ ምን አለፋችሁ ወገኖቼ የሆነ ነገር ከባድ ደመመን አዝለዋል። ጭጋግ፤ ወይ ደመናዊ ጨለማ፤ መርግ ነገር እንጃ - እራሳቸው እሳቸውን መሸከም ተስኖታል። በእንተ - እፍረቱን ነው እያዘገሙ ያለው። ውስጣቸው ንጥረ ነገሩን ሁሉ ክተት ወደ መቃብር ያለ ይመስላል … ለእኔ የታዬኝ እንዲህ ነው እናንተስ ውዶቼ የጡሑፌ ታዳሚዎች?
አቦይ ስበሃት እና ደመመን ጫን - ተደል ያለበት ኑዛዜያቸው በሥርጉተ ዕይታ ተመጥና ….እነሆ 

የለበሱት ልብስ አሻንጉሊቶች ለሞድ ማሻሻጫነት በዬልብስ መደብሩ ደመነፍሳቸውን የተገተሩበትን ምስል ጎብኙ የሚል እስኪመስል። በውነቱ ቀለም እለቦሹ ገበርዲን ውስጣቸው የቀረውን ባዶነት በጥብቅ ያሳጣል። ተንክርፍፏል። አልተጠጋቸውም። የተውሶ ነው የሚመስለው። ከንፈራቸው ኩበት ሆኖ ክው ብሏል። ልሳናቸው ደርቋል። አፋቸው ሲጣጣ ያደረ አንድ ከነስካሩ፣ ከእንጎልቻው ያለቀቀው አቶ „ሀ“ ባትቶ፣ ምላሱ ተያይዞ፣ መተንፈስ ተስኖት፣ እሚይዘውን እሚጨብጠው ግራ ገብቶት፣ ከዚህና ከዚያ ሲውተረተር የሚያሳይ ገጸ ባህሪ ነው የሚመስለው። ምን አለፋችሁ የሰካራም ትርኢት ተውኔት ነው የሚመስለው። ገራሚው ነገር ግራዝማች ምላስ የአልተረታሁም ውጪ ነፍስ ግቢ / ነፍስ ፍጥጫ ላይ መሆኑ ቁልጭ ብሎ ይታይበታል። በራሱ በሚናገሩት ስሜት ውስጥ እሳቸው የሉም። ስሜታቸው እና እሳቸው ፍች ፈጽመዋል። ከአንድ በጎሳ ፖለቲካ ከትሞ ዕድሜውን ከገፋ ፍጡር  እንዲህ አንደበት መላ አጥቶ ሲወድቅና ሲነሳ፤ አፋፍ ላይ ሆኖ እግዚኦ! ሲል ሳይ በህይወቴ የመጀመሪያዬ ነው። ያለ ግነት።
ያ ትቢት፤ ያ መኮፈስ፤ ያ መንጠራራት፤ ያ ካለልክ መወጠር፤ ያ ያዙኝ ልቀቁኝ መንክትከት ሁሉ ብን ብሎ ጠፍቷል። ቀኗ ስትመጣ አቦይን ያዬ ሰው። መቺስ አትቀር። እያንዳንዷ ቃላት በጣር ላይ ሆና ነው ተገጣጥማ ስንኝ የምትሆነው፤ በጭንቅና በመከራ ነው ሐረጉ የሚፈጠረው። ስዋሰውንማ ተውቱ፤ እሱ የቅንጥ ነው፤ በቃ! አፍ ያአልፈታ እንቦቀቅላ እኮ ነው የሚመስሉት። የአቦይ የሰብዕና ንጽህናቸው ለህጻናት ንዑድ መንፈስ ቅርብ ነው እያልኩ አይደለም። የጥያቄና የመልስ ድባቡ መልስ ለመስጠት የነበረውን የጣረሞት ጊዜ ለመግለጽ እንጂ። ከሌባ ምን ቅድስና አለና። ከገዳይስ ምን ንፅህና አለና። ይገርማል … በዛ ላይ የእንግሊዙ ቋንቋ ሲታከልበት የመምህርነት ሰብዕናው እራሱ ጥሏቸው መኮብለሉን፤ በሳቸው ላይ ሃራም ብሎ መሸፈቱን ያውጃል።

አቦይ „ህዝብ አልተበሳጨም ይልሉ።“ ሱናሜው አጥለቅልቆ ጠራርጎ እሲከወስዳቸው ድረስ ህሊናቸው ሊይ፤ ከቶውንም ሊያስተውል አልፈቀደም። ይህ ችግር የሳቸው ብቻ ሳይሆን የማህበረ ሳዖል ሊቃናት ወልዊ በሽታ ይመስላል። እሳቸውን ከነቀፏቸው ሲመለክቷቸው የ100 ዓመት ህልም ለሚሊዮን ዓመት የመሽሎኩን ነጋሪት ጉሰማውን ማዳመጥ ይችላል። ዛሬ ባይሆንም ነገ ሌላ ቀን ስለመሆኑ በዕውን የትግራይ ሥርወ መንግሥት ዕጣ ፈንታ ለዘለዓለም ክስመቱ ዋዜማ ላይ መሆኑን ይጠቁማል። ውስጣቸው በፍጹም ሁኔታ ተስፋው ተጋግጧል። ተስፋው ልቅላቂ፤ እንጥፍጣፊ አልቦሽ ጭልጥ ብሎ መጪ ብሏል … ሹክቻው ትርፋማነቱ በቀጣይነት ስለመዝለቁ ውሃን የመዘገን ዓይነት ይመስላል …

አቦይ ከ90.00 ዶላር ዐመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ወደ ዛሬው ዬከፍታው ዘመን ወደ 800.00¡ ዶላር ማደጉን ነግረውናል። ይህ በዬትኛውም ዘመን ያልሆነ ፋሲካ ነው ይሉናል። የትኛው ዘመን ላይ ሆነው የኢኮኖሚ ሊቅ እንደሆኑ ግልጥ ባይሆንም፤ በግ በ5.00 የኢትዮጵያ ብር ተገዝቶ ቆዳው በ12.00 በኢትዮጵያ ብር ተሽጦ ሥጋው ከ4.00 ብር ትርፍ ጋር በነፃ ይታደልባት የነበረውን የቀደምት የአባቶቻችን የተድላ ርጥብ ጊዜን በምልሰት ሊቃኙት ቀርቶ ሊያስቡት እንኳን አልቻሉም። ዶሮ ባሳንቲም ነበር የሚገዛው። ይህን በሳቸው ዕድሜ መቼም ያዩት ነው። በእኛ ዕድሜ በውል ያዬነው፣ ልንመሰክረው የምንችለውም በጥቂት ብሮች ከነቤተሰብ ሙሉ ግብዣ ማደርግ ይቻል ነበር። 180.00 ግብሩ ሳይቀነስ የኢትዮጵያ ብር አንድ ደሞዝተኛ  አምስት ቤተሰብ በማዕከላዊ ደረጃ ሳይቀናጡ ደልደል ብለው ይኖሩበት ነበር። የብሩ የመግዛት አቅም ሙሉዑ ነበር።

በአዲስ አበባ ላይ በ30.00 የኢትዮጵያ ብር 500 ካሬ ሜትር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚመራበት ጊዜ ነበር። ዛሬ ደግሞ አንድ ካሬ ሜትር ሺዎችን አስቆጣሪ ሆኗል። ለዛውም ከተገኘ ነው። የኢኮኖሜ ሊቁ አቦይ ስብሃት ያለንበት ዘመን 21 ምዕተ ዓመት መሆኑን፤ ህውሃት በብድርና በዕርዳታ የሚገኘው ጣሪያ የነካ ዶላር ለተጋሩ ከርስ መዋሉን ትዝብቱን እንዴት ሊያገናኙት እንደሚችሉት ቢያንስ ደመነፍሳቸው ሊነግራቸው እንዳይችል አልፈቀዱለትም። ዛሬ እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ወጣት ህፃናት የሚቧርቁበት ብጣቂ መሬት እንኳን የለም … ደስታ ነጥፎበታል … ማጋበስ … የተያዘው የተረዘዘው ሁሉ። … መንፈሳዊ ኩነቶች እራሳቸው ዋቢም ሁነኛም የላቸውም። የተጨናነቀ፤ የተወጠረ፤ በስጋት የተናጠ ትውልድ ነው ያለው … ጠግቦ ማደሩ ቀርቶበት … 
የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅሙ እና የህዝቡ ፍላጎት መመጣጠን Demand and Supply ተስኖት የዋጋ ግሽበት Inflation ሙላት በሚያነከረባብሰው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ተቀምጠው እስከ ዘር ማንዝራቸው የሚንፈላሰሱበት የኢትዮጵያ አንጡራ ሃብት የምቾት ግሳት ተጨባጩን ሊያሳያቸው ቀርቶ፤ እውር ድንብሱን እንኳን ታቱ ሊሉባት አልፈለጉም። ኢትዮጵያ ከመጨረሻዎቹ ደሃ ሐገሮች ላይ የተቀመጠችበት ዋናው ሚስጢር እኮ  ኋላቀርነቷ ነው። ኋላቀርነት ያልተመጣጠነ ኤኮኖሚያዊ እድገት ነው። አሁን የተጋሩ ዕሳቤ ኤኮኖሚው ብቻ ሳይሆን ያልተመጣጠነ እድገቱም በአሰተሳሰብ ደረጃም ጭምር ከዛው ላይ እዬረገጠ መሆኑን ያመላክታል። ለማንኛውም ይህን ዘርፈ ብዙ የኤኮኖሚ ወጣ ገባ ዝብርቅ ኢትዮጵያዊ የኢኮኖሚ ሊቀ ሊቃናት፣ ፈላልስፎችና ሳይንቲስቶቼ ስላሉበት እሱን ትቼ ወደ ሌላው ጉዳዬ መጪ ልበል …

በማህበራዊ ኑሮ፤ በፖለቲካው የአስተሳሰብ ነፃነት፤ በሃይማኖት እኩልነት፤ በርትህ ጥበቃ፤ አፈጻጻምና ኩነት፤ በባህል ህያዊነት፤ በሰባአዊነትና በተፈጥሯዊነት ያሉት መስተጋብሮች ሂደቶች ያለውን ቅይጥና መጠነ ሰፊ የቀውስ አብዮትም አቦይ ትውር አላሉበትም። ለነገሩ በነፍሳቸው ውስጥ አልነበሩም … ክደውታል ነፍሳቸውን እራሱን….

„ኢትዮጵያን መፈንቀለ መንግሥት አያሰጋትም“ ይሉና ቀባ ያደረጓት ወደ ክልሎች አፈፍ ብለው ያገኙትን ህገ መንግሥታዊ ነፃነት አይጣሉትም አሉና ወደ እንብርቷ አርዋል። ተዚህች ላይ እንኳን እንቅጩን አፍርጠውታል። „ህገ መንግሥቱ አሁን ያለው የተጋሩ ሠራዊት አንጡራ ሃብት ነው“ ብለውናል። „የሞተለት፤ የተሰዋለት ነው“ ይሉናል። „የህገ መንግሥቱ ፈጣሪ እሱ ነው“ ለነገሩ መነሻው ትግራይ ስለነበር ይህ በራሱ ዝበት አለበት። ኢትዮጵያን እንዲህ በለስ ይቀናናል ብለው አልመውት አያውቁም ነበር። ብቻ መንገዱ ሲቃና የተፈጠረ መሆኑን ግምት ውስጥ ማስገባት ይቻላል። የማይካደው ግን ወያኔ ሃርነት ትግራይ ገዳይ ማንፌስቶው የህገ መንግሥቱ እንብርት ነው። አሁንም አዛው ላይ ናቸው። ስለሆነም „የራሱ ጠላት ራሱ ሠራዊቱ ሊሆን አይችልም፤ የራሱን ህገ መንግሥቱን አይቀደውም“ ይሉናል። ይህ እውነት ነው። እስከዛሬ ድረስ  የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ድምጽ አጸደቀው የሚባለው ህገ መንግሥት በጫካ ማህበረ ደራጎን መንፈስ ውስጥ የተፈጠረ ስለመሆኑ በአንድም በሌላ መንገድ በኩል መግለጻቸው የ26 ዓመቱ ዳንኪራ ያው በስከር ልቦናቸው ፍርጥርጥ አድርገውታል። „ሆድ ያባውን“ አይደል የሚባለው። ያን ዕብለት ዘመን ህገ መንግሥቱን የኢትዮጵያ ህዝብ አጽድቆታል የሚሉትን ግብዕቱንም እልል እያሉ እራሳቸው አቦይ ትቢያ አልብሰው ድንጋይ አንተርሰውታል።። ተዚህ ላይስ ወሸኔ ብያለሁ። ወያኔ በመቃብሩ ላይ መቃብሩ ይሆናል ማለት ነው። እርግጥ ነው ባለፈው ሰሞንም በዚህ ጉዳይ ላይ የህገ መንግሥቱን የቅብ ቁመና የተከበሩ ዶር. ነጋሶ ጊዳዳም አብራርተውት ነበር።

ሠራዊት የሚሉት አቦይ „አሰተውሉ“ ወገኖቼ „የተጋሩውን“ ብቻ ነው። ሌላው አንጋች ነው። ተዚህ ላይ የአቦይ ንዟዜ ያልገባው መሠረታዊ ጉዳይ ትምክህቱ በምን ያህል የጫካ አባላት ውርርድ ይሰክናል የሚለውን ነው? እነሱ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ስለመሆናቸው አስበውት አያወቁም። ያው የሰማዩ ዳኛም አለ ብለው ስለማያምኑ ያ ከቁጥር የሚገባ አይደለም - በሳቸው ቤት። የሆነ ሆኖ እንደ ቀደመው አሁንም ያው ለከፈን ያበቋቸውን እህት ተለጣፊዎቻቸውን እንደ ነበሩ፤ እንደ አስቀመጧቸው ያሉ ብቻ ሳይሆን አቅመ ቢስ ስለመሆናቸውም እግረ መንገዳቸውን ገረፍ አድርገው አልፈውታል። የት ይደርሳሉ? ጸጥታው፤ ኢኮኖሚው፤ ግዛቱ በእኛ ሥር ባለ ሁኔታ „አትቀናጡ“ ዓይነት ይመስላል።

ሌላው በተቃዋሚዎች ላይ ያለው ንቀት አንድ ቀን የኢትዮጵያ/ የኤርትራ ሊቃናት ግምት ውስጥ ገብቶ አለመታወቁ የወረርሽኝ በሽታ ዓይነት ነው። ቢያንስ በሥነ - ልቦና መሸነፉን እንኳን መቀበል አልተቸለም ማህበረ ደራጎን። ዛሬ ከዛ ጠቅጥቀው፣ ጨፍልቀው አገርጥተው ከቀበሩት „ኢትዮጵያዊነት“ ጋር ምህረት ለማግኘት ላንቃው እስኪወልቅ ድረስ ሚዲያቸው ሲያቅራራ እና ሲፎክር እዬዋለ አላዬሁህም፤ አለሰማሁህም ማለት በውነቱ ዕብንነት ነው። በፖለቲካ አስተሳሰባቸው የሚያሥሯቸው ሺህዎች እኮ ምንም የተገኘባቸው የለም። ቅራፊ የምንም የወንጀል ቤተኛ አይደሉም። እጅግ ጨዋ ናቸው፤ „ኢትዮጵያ“ ስላሉ ብቻ ነው። ወይንም እነሱ እነ ተጋሩ ኢትዮጵያ ባሏት ሐገር ውስጥ ትግራዊ ዜግነትን ለመጫን በሚያደርጉት ግብግብ አሻም ያሉትን ነው ግዞት ውስጥ የከተቷቸው። የሴት እስረኛን ጥፍር የሚነቅሉ /ንግሥት ይርጋን/ ጉዶች … የሃይማኖትም አቨው የላችውም፤ እንኳንስ የዕድሜ አዛውንት። እኔ እንጃ ትግራይ ድንጋይ ተሸክማ ኢትዮጵያን ይቅር በይኝ ብትል እንኳን የልጆቿ በደል ጣሊያን ከሰራው ግፍ እጅግ የከፋ እና የከረፋ ነው …

አሁን የጋዜጠኝነትን ሙሉዑ ሥነ - ምግባር በጨዋነት እና በሚመስጥ ክህሎት ያሟላው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከእስር ሲለቀቅ እኮ ሱማሌ ላይ ታሥሮ የተፈታ እንጂ በሀገሩ በኢትዮጵያ መሬት ታሥሮ የተፈታ አይምስልም። አርጅቶ፤ ግርጅፎ፤ ውስጡ በመከፋት ዝሎ እኮ ነው የወጣው። የእነሱ አዲስ ምላጭ ጦማሪና መምህር አቶ አብርሃም ደስታ ሲፈታ ደግሞ ሽርሽር ለዛውም የሙሽርነት ያህል ተውቦ ነበር የወጣው። የጹሑፌ አንባቢዎቼ የማከብራችሁ የሁለቱንም ፎቶ አቅርቡና ሥራዬ ብላችሁ እንደ እኔ ጎን ለጎን አስቀምጣችሁ እዩት። ጦማሪ መምህር አቶ አብርሃ ደስታ ጫጉላ ጊዜ ቆይቶ የወጣ ነበር የሚመስለው። ይህ ሲታይ እንዲያውም በእስር ቤቱ መቆዬቱ በስንት ጣዕሙ ያሰኛል። ከነክብሩ፣ ከነ ግርማ ሞገሱ ጋር - የእኛም መንፈስና አቅል በፍቅር እንደ አንጠለጠለ እዛው ቢቆይ ያሰኛል እስር እንደ አብርሽ ከሆነ። መቼስ የህዝብ ፍቅርን የሸቀጥ ህግ አይገዛው ነገር  … ያን ጊዜ እብድ አድርጎን ነበር የዛሬን አያድርገው እንጂ። አይፈረድም „አንድ ለወልዴ፤ አንድ ለእናቱ ነበር“ … ካለ ተቀናቃኝ … በልቦናችን ውስጥ ተደላድሎ ጉብ ብሎ ነበር።

የሆኖ ሆኖ ገድለነዋል ያሉት „ኢትዮጵያዊነት“ ትንሳኤው ታውጇ መታዬቱ፤ የወያኔ ሃርነት ትግራይ የግራዚያኒ ማንፌስቶ ሞቱን ብቻ ሳይሆን እንጦርጦስ መውረዱን ያመለክታል። ይህ ከሞቱ አሟሟቱ የድርጅቱን እርቃን ፍንተው አድርጎ ያሳያል። አሁን ወያኔ ሃርነት ትግራይ የሥነ - ልቦና የበላይነት በዳግም ላያነሰራራ ግብዕቱ መፈጸሙን ቁጭ ብለው እያዩት ነው። አቦይ በዚህ ቃለ ምልልሳቸው ምን እንደሚመስሉ እራሳቸውን ደግመው ደጋግመው ቢመለከቱት ቆዳ መልስ ነው የሚመስሉት …
ከላይ እሰከታች አምስት ለአንድ የዋቀሩት ስልትም እንደ አሮጌ ኬሻ ብጥቅጥቁ ከወጣ ቆዬ፤ የብል ራት ነው የሆነው። ባለፈው ዓመት አስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ እኮ ያሳወጀው፤ አሁን ደግሞ በአዲስ ስልት አዲስ ወታደራዊ ማነቆ እንዲቀረጽ ያስገደደው እኮ የሄሮድስ መለስ የሙት መንፈስ ታሪክ እልቦሽ ሆኖ ትቢያ በመልበሱ ነው። ይህን እውነት አቦይ መቀበል አልቻሉም። „የተበሳጨ ህዝብ የለንም“ ይላሉ ደረታቸውን እንደ አቅሙ በዛ በዛለ ጥንዙል መንፈስ ገፋ አድርገው … „ሥራ አጥ“ የሚባለውንም ወጣትም በጥቂት ቅርጥምጣሚ እንደ ተለመደው ብጣቂ ነገርን በማጎራረስ ልክ እናስይዘዋለን፤ እንቢኝ ካለም ባለጠመንጃዎቹ እኛ፤ ሁሉ በእጃችን በደጃችን ባይ ናቸው … „ማን ጌታ አለብን“ አይነት …

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ያው ለቅብረት ታጥቀው የተነሱበት ጉዳይ ነበር። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በማያቸው ማናቸውም ሁነት ወጣቶች ዝንጥ ብለው ግን ማተባቸው ከአንገታቸው አይጠፋም። መስቀላቸው በጥቁር ክር  ከአንገታቸው አትለይም። ኮራሁባቸው። ይህን ለሚይ ሰብዕናው ለተሟላ ፍጡር በሁለቱም አቅጣጫ ያለው የሥነ - ልቦና ልቅና አብነት ትውልድን አንደላቆ ከዘመን ዘመን ያሻግራል። የለውጥ ፈላጊው ማህበረሰብንም የዝምታ አብዮት ቁልጭ ብሎ አናባቢም ተነባቢም፤ ግሥም ሰዋሰውም ሆኖ ይታያል - መሬት ላይ። የወያኔ ሃርነት ትግራይ ህልም እንፉርሽቃ ነው የሆነው ለከብት መኖ ብቻ …
ከዚህ ጋር የሚታዬው ነገረ - አማራ ነው። ነገረ አማራ እስከ ቋንቋው እስከ ዕሴቱ የሚታይ፤ የሚጨበጥ ሙሉዑ አቅም ላይ ይገኛል። አይዟችሁንም አግኝቷል። አለንላችሁን አግኝቷል። የሄሮድስ መለስ ዜናዊ የጠላትነቱ መሰሪ ሥር ከሥሩ ተገንድሷል። አልፎ አልፎ የሚታዩ ቅሪት አካሎችም ያው የወያኔ ውጥኖች ናቸው፤ ይህም ቢሆን በሂደት መልክ ይይዛል። ከተኖረበት መከራ አንጻር በመጪዎቹ ጊዜያቶች አማራ የሚከፍለው መስዋዕትነት ወያኔ ሃርነት ትግራይ እንዳቀደው እና እንደ ተለመው ሊሆን እንደማይችል ቁጭ እንዳለ ተጋሩ እዬመረረው ተግቶታል። እነዛ አባ ገዳዎች ሰውን ባይፈሩ እግዜሩን ስለሚፈሩ ነገን ቢያንስ በጸሎታቸው ሁሉንም መልክ ለማስያዝ ጥረታቸውን ይቀጥላሉ ብዬ አስባለሁ። ለሃይማኖት አባቶች ትውልድ እንጂ እንደነ አቦይ ሥጋ ሲቆጥሩ አይገኙም እና … በተጨማሪም አማራዊ ሥነ - ልቦና ከመቼውም በላይ የህሊና ርስት ሆኗል። ርቁቅ ነው። አይታይም አይጨበጥም አይዳሰስም ነገር ግን ሃብቱን በሃብት ማመሳጠሩ አይቀሬ ነው …

እነ ተጋሩ ነገን ለማዬት ዛሬ ላይ ያለውን ለመረዳት ከሥካር ወጥቶ የቆሙበት ቦታ መናዱን፤ እዬሰመጠ ያለ መሆኑን በማስተዋል መመርመሩ ነው „ምርጥ፣ ወርቅ ዘርን“ ሊያተርፍ የሚችለው ይሄው ብቻ ነው። የወል ጭንቁ ይሄው ነው። በተለይ „ሰው“ መሆን ለሚቀበሉ ኢትዮጵውያን አሁን የጭንቅ ጊዜ፤ የሱባኤ ወቅት ነው የሆነው። ጆሯችን አቅንተን፤ ልቦናችን ወደ አምላካችን አሰማርተን ነገ እንዳይጎመዝዝ አቤት! የምንለውም ይሄንኑ ነው። አማራው የለመደው ነው ሰቆቃውን 40 ዓመት ሙሉ ከርሞ - ባጅቶበታል። ልምድ አለው ለመካራው። እድሜ ይንሳችሁ እንጂ ሰልጥኖበታል አሳሩን። ተዋህዶም እንዲሁ። ጋንቤላው በሞቱ ውስጥ መኖሩ ብቻ ሳይሆን ህፃናት ወደ ባዕድ ሀገር ሲወረሱ ቅጭጭ የማይለው አውሬ ነው ኢትዮጵያን እዬገዛት የሚገኘው። ጥቃቱ ጥጋቡን የሚያፋፋለት ዕብን … ግዑዝ …

እስልምናም ያን ሁሉ ሰቆቃ አሳልፎ አንዱ ታሳሪው ህክምና የተነፈገው ያ ለእምነቱ የቆመ አርበኛ ቀንበጥ አቶ አህመዲን ጀበል … የነገን የተስፋ ምክነት፤ የህውሃትን የህልም ቅዠት ደረጃን ምን ያህል ኢ-ሰብዕዊ እንደሆነ ያሳያል። ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የተነፈናቀለው የኦሮሞ ማህበረሰብ ጉዳይም እዬታዬ ያለው ሰቆቃ መሬት የረገጠ ሲሆን፤ ነገም ባለተራው ይቀጥላል … እያንዳንዷ አማራ ላይ የደረሰው ማናቸው ግፍና በደል በሁሉም ላይ ቀኑን ጠብቆ ሊደርስ የሚችል ሃቅ ነው። ወያኔ በአገዛዙ ከቀጠለ። ሁሉም ባለተራ ነው። ወያኔ በፈለገው መልክ ኢትዮጵውያንን ይጠማል፤ አቅም ወይንም አገልግሎት ሲያረጅ እንደ አሮጌ አካፋና ዶማ ወርውሮ ይጥላል … ከዛሬ 5/ 6 ዓመት በፊት በፊደል ከሀ እስከ ፐ ጥቃቱ በዬተራ ሊደርስ እንደሚችል ተንተን አድርጌ ጽፌው  ነበር … „ሀን“ ለማጥቃት ከ“ለ እስከ ፐ“ ያሉትን እንዴት ወያኔ በለበጣ ክናድ እንደሚያቅፍ። „ሀ“ መጠቃቱን ካረጋገጠ በኋዋላ ደግሞ ወደ „ለ“ ተሻግሮ „ለን“ እስከያጠቃ ድርስ „ከሐ-ፐ“ ያሉትን በጊዚያዊነት እንዴት እንደ አካሉ አድርጎ  በአርቲፊሻል መልክ እንደሚይዝ በዝርዝር ጽፌ ነበር። ዘሃበሻም ተባብሮኝ ፖስት አድርጎልኝ ነበር። ያን ጊዜ ብንነቃ ቢያንስ ከግማሽ ሚሊዮውን በላይ የተፈናቀሉትን ወገኖቻችን ሆነ እስልምናንም ከጥቃት ማተረፍ ይቻል ነበር። ለነገሩ ዛሬም … ህም ነው።
  • የአሉታዊ ዕሳቤ ሽግግር፤ 

አንድ የትግራይ ወጣት ከአሜሪካ ድምጽ የትግረኛው ክፍለ ጊዜ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ በአምርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ሳተናው ላይ አንብቤዋለሁ። ካለ ትግራይ ሊሂቃን ኢትዮጵያ ተስፋ ቢስ እንደሆነች። „እሚሉሽን ብትሰሚ ገብያ ባልወጣሽ ነው።“ ኤርትራም ያን የተንጣለለ ግራ ቀኝ ወደብ ይዛ ከበለጸጉት ሐገሮች ተርታ አልተሰለፈችም … የኤርትራ ቀንበጦቿ ስደት እዬባላቸው፤ ከተማው ያችው ባለችበት አሮጌ ቆርቆሮ ተከዝና በዝመታ ተውጣ ነው የምትገኘው፤ እንኳንስ እትዬ ትግራይ …. ስደቱ ነው ለኢትዮጵያ የሚተርፋት። „ጨው ለራስህ“ ብትል ነው፤ ኢትዮጵያ የሚቀርባት አንዳችም ነገር የለም። ዛሬም የመብራቱ ቦግታ በኢትዮጵያ አንጡራ ሐብትና የመሬቷ ለምነት ነው እንዲህ የሚያአቀናጣው። ኢትዮጵያ ማዕዛዋ ብቻ ይበቃል። ጠረኗ ብቻ ይበቃል። በዓለም መኪና ውስጥ ተሁኖ ምግብ እና መጠጥ ታዞ እሚፈርሹባት ሐገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ኢትዮጵያ ቅዱስ መንፈስ በገፍ የሰፈነባት፤ የረበበባት ንዑድ ሐገር ናት። ረድኤት አላት። ምርቃቷ ረቂቅ ነው ከነጣዕሙ። … ከዚህ በላይ መሄድ አያስፈልግም …
ከትግራይ ውጪ ስለሚኑሮት የተጋሩ ህፃናት ይልቅ እሰቡ፤ ከበያችሁበት ተራራ ወረድ ብላችሁ … ሁለት ፍሬዎችን በአውሮፕላን ማጓጓዝ ሳይሆን መፍትሄው ጊዜ ጥሎችሁ እዬሄደ ስለሆነ፤ ልብ ገዝታችሁ ዘራችሁን ለማትረፍ ቢያንስ ልብ ግዙ፤ ልብ ከሚገዛበት በጭረታ ይሁን በውርርድ የገብያ አዳራሽ …. ብኩኖች … ዛሬ እንጂ ነገ የማይታያችሁ ብኖች … ስለነገ የትግራይ ህፃናት እንኳን ግድ የማይሰጣችሁ የኢጎ ግብዞች … 
  •  ምስቅልቅል

 „በትጥቅ ትግል እኛን ሊያሸነፍ የሚችል የለም“ ሲሉ አድማጫለሁ። ይህን ለባለ አቅሞች ሸኝቼ አቦይ ግን የትም ቦታ የተቀበረ የመከርኛ ህዝብ በፍጹም ሁኔታ የጠለቀ የምሬት ፈንጅ እንዳለ ልብ ሊሉት ይገባል እላለሁ። እርስዎ ኤርትራ ላይ አልጠብቅም ሲሉ ከጉያዎት ዕንባ፤ ምሬት፤ መገፋት፤ ባይተዋርነት ያንገሸገሸው አንድ ቅጽበት ብው ይልና ምድር ቀውጢ ልትሆን ትችላለች። የህዝብ ማዕበል ህግ አልተሰራለትም። ዛሬ ጸጥ ብሎ የሚሠራው ህግ ነገ ይጣሳል። የካባችሁት ድንጋይ ሁሉ በሰከንድ ይናዳል። አዩ አቦይ ሲከር ይበጠሳል ሲሞላም ይፈሳል። ሌላው ግን ተቃዋሚ ሃይሎች እኮ አይደሉም ኢትዮጵያን ከሚፈርሱ ሀገሮች ተርታ ያሰለፉት፤ ምኞታቸውም አይደለም፤ እናንተው እኮ ናችሁ አውርዳችሁ ታች ላይ ያንዘገዘጋጅኋት። ሸንሽናችሁ፤ ተርታራችሁ ቆራርጣችሁ ለውጭም ሸልማችሁ ቅጥ መጠኗን ያሳጣችኋት። ህልማችሁ ይህ ነበር። መንግሥት አይደላችሁ¡ ከ90.00 ዶላር የነፍስ ወከፍ ገቢ ወደ 800.00 ዶላር ያአሸጋገራችሁ ምርጦች … ሃሃሃሃ። ፐፐፐፐ¡
የሆነ ሆኖ ተፎካካሪዎቻችሁ ከዚህ ተጠያቂነት ነፃ በፍጹም ሁኔታ ነፃ ናቸው። አንድስም እንኳን ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ብጣቂ አመክንዮ የለም። ይሄን እንኳን ማገናዘብ አልቻላችሁም። ግዴታ ያለባችሁ እናንተው ናችሁ። በታሪክም ተጠያቂ ናችሁ። ዕድሜ ልካቸውን ልጆቻችሁ፤ የልጅ ልጆቻችሁ ሲወቀሱ - ሲነቀሱ አንገታቸው ጎብጡ እንዲቀር ያደረጋችሁ መራራዎች …
  • ክወና።

ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ሆነ ተጨባጩ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉዑና ብቁ ነው። የቀረው አንድ ተደሞ አለ። እሱ ደግሞ  የእግዚአብሄር ሥራ አንጅ የሰው ሥራ አይደለም። ራሱ ፈጣሪ አሁን እዬሠራው ያአለው ጥልቅ ጥበብ አለ … ለስውራን አይታይም … ቀዳዳዎችን ወታትፋችሁ ከእንግዲህ 100 ዓመት ለመግዛት ተስፋው እንጦርጦስ ላይ ያለ ይመስላል … ቢበዛ ጥቂት ዓመት … ምን አልባት። ምን አልባትም ምጥ ገላጋዩ …  ይብቃኝ ተዚህ ላይ ….
አቦይ ስብሃት „በፊት ለፊት“ ፕሮግራም።
Mekelle: አቶ ስብሓት ነጋ ተናገሩ "ወታደራዊ መፈንቀል መንግሥት"

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።


ውዶቼ፤ እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ደህናም ሰንብቱ፤ ደግሞ እስኪ ከምወደው፤ እጅግም ከምመሰጥበት የጸጥታ ጸጋዬ ጋር ድብቅ ልበል። መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።