"የሶማሊያ ፌደራል መንግሥትን እና የጁባላንድ ግዛትን ውዝግብ ውስጥ ያስገባቸው ምንድነው?" BBC
" የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እና የጁባላንድ ግዛት ፕሬዝዳንት አህመድ ሞሐመድ ኢስላም"
"የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካንን ጨምሮ 18 ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ተቋማት እንዲሁም ሀገራት ረቡዕ ዕለት በጋራ ባወጡት መግለጫ በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት እና በጁባላንድ መካከል ያለው አለመግባባት እየተባባሰ መሄዱ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
የፌደራሉ መንግሥት እና ጁባላንድ “ከተንኳሽ” ድርጊቶች እንዲቆጠቡ የጠየቁት ተቋማቱ እና ሀገራቱ፤ “ገንቢ እና አሳታፊ ውይይት” እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
በሶማሊያ ሰላም ማስከበር ላይ የተሰማራው የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ እና የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ጭምር የተካተቱበት ይህ መግለጫ የወጣው በሁለቱ አካላት መካከል ያለው መካረር እየተባባሰ መሄዱን ተከትሎ ነው።
ከሁለት ሳምንት በፊት ኅዳር 1/2017 ዓ.ም. ጁባላንድ ከፌደራል መንግሥት ጋር ያላትን ሁሉንም የትብብር ግንኙነት ማቋረጧን አስታውቃለች። ግዛቲቱ፤ አዲስ የምርጫ ኮሚቴ ማቋቋሟን ይፋ ስታደርግ የፌደራሉ መንግሥት እርምጃውን “ሕገወጥ” ሲል ፈርጆታል።
ምንም እንኳ የምርጫ ኮሚቴው በፌደራሉ መንግሥት ተቀባይነት ባያገኝም የጁባላንድ ምክር ቤት አባላትን ለመምረጥ ምርጫ ተካሂዶ ማክሰኞ ኅዳር 10/2017 ዓ.ም. የምክር ቤቱ አባላት ተመርጠዋል። አዲሶቹ የምክር ቤት አባላት ደግሞ ትናንት ሐሙስ አዲስ አፈ ጉባኤ መርጠዋል።
በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ደግሞ የጁባላንድ ፕሬዝዳንትን ለመምረጥ ምርጫ ይካሄዳል። የግዛቲቷ ፕሬዝዳንት አህመድ ሞሐመድ ኢስላም በድጋሚ ይመረጣሉ የሚል ግምት ተሰጥቷቸዋል።
የምርጫ ኮሚቴ ከማቋቋም እስከ የግዛቷን ፕሬዝዳንት መምረጥ ያሉት ሂደቶች ግን የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ የፌደራል መንግሥትን አላስማማም። የሁለቱ አካላት በሚያወጧቸው መግለጫዎች እና አመራሮቻቸው በሚያደርጓቸው ንግግሮች የሚታየው የቃላት ምልልስም ቀጥሏል።
ያላስማማው የምርጫ ሥርዓት ለውጥ
ከሶማሊያ የፌደራል ግዛቶች መካከል አንዷ የሆነችው ጁባላንድ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር እሰጣገባ ውስጥ የገባችው የፌደራሉ መንግሥት እና ሌሎች ግዛቶች የሀገሪቱን የጎሳ መሪዎች ላይ መሠረት ያደረገውን የምርጫ ሥርዓት ለመቀየር መስማማታቸውን ተከትሎ ነው።
ከፊል ራስ ገዝ የሆኑ አምስት የፌደራል ግዛቶች ያላት ሶማሊያ፤ የፌደራል መንግሥቱ እና በየግዛቶቹ መንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት የተወሰነው የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ለሁለቱ አካላት በሰጠው የሥልጣን ክፍፍል ላይ ነው።
የውጭ ጉዳይ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ኢሚግሬሽን እና የገንዘብ ፖሊሲ ጉዳይ ለፌደራል መንግሥቱ በብቸኝነት የተሰጡ ሥልጣኖች ናቸው።
የሶማሊያ ግዛቶች በሀገሪቱ የተለያዩ ጎሳዎች የሚመሩ ሲሆን የጎሳዎቹ መሪዎች በምርጫ ሥርዓቱ ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው። የሶማሊያ የምርጫ ሂደት በብዙ ሀገራት ከሚተገበረው የተለየ እና ውስብስብ ነው። ከ18 ሚሊዮን በላይ የሆነው የሀገሪቱ ሕዝብ በቀጥታ መሪዎቹን አይመርጥም።
በሶማሊያ የፌደራል መንግሥት እና በግዛቶች ለምክር ቤት አባላት እንዲሁም ለፕሬዝዳንትነት ምርጫ የሚያካሂዱት በየራሳቸው የምርጫ ኮሚቴዎች ነው።
የፌደራሉ መንግሥት ፕሬዝዳንት የሚመረጠው 275 አባላት ባሉት የተወካዮች ምክር ቤት ነው። ፕሬዝዳንቱም የሚመርጡት ደግሞ የእነዚህ የምክር ቤት አባላት በሚመርጧቸው የጎሳ መሪዎች ነው። በየግዛቶቹ መንግሥታት የሚመረጡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮችም የምክር ቤቱ አባል ናቸው።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ፤ ይህንን የምርጫ ሥርዓት በብዙ ሀገራት ወደሚተገበረው ዜጎች ቀጥታ ወደ ሚሳተፉበት ድምፅ የመስጠት ሂደት የመቀየር ሀሳብ አላቸው። ይህ ሀሳብ ከዚህ ቀደምም ንግግር ሲደረግበት የነበረ ሲሆን፣ የሀገሪቱ ግዛቶች ለሀሳቡ ድጋፋቸውን ገልጸው ነበር።
መስከረም ላይ ከሀገሪቱ ግዛቶች ተወካዮች የተካተቱበት ብሔራዊ የምክክር ምክር ቤት ውይይት የፌደራል መንግሥቱ በቀጣዩ ምርጫ ላይ ይህንን የምርጫ ሥርዓት የመተግበር ዕቅድ እንዳለው አስታውቋል።
በሀገሪቱ የውጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የፌደራሉ መንግሥት ከምርጫ ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ ሦስት አሠራሮችን የመቀየር ፍላጎት እንዳለው ገልጿል። የፌደራል መንግሥቱ በሀገሪቱ የሚካሄዱ ምርጫዎች አንድ እንዲሆኑ ይፈልጋል።
ዜጎች የሚሳተፉበት የአንድ ሰው አንድ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ ሌላኛው የፌደራሉ መንግሥት ፍላጎት ሲሆን፣ በሀገሪቱ የሚካሄዱ ሁሉንም ምርጫዎችን የሚመራ አንድ የምርጫ ኮሚሽን የማቋቋም ዕቅድም አለው።
ይህንን አሠራር ለመተግበር እንዲቻልም የፌደራል እና የክልል መንግሥታት የሥልጣን ዘመን በአንድ ዓመት እንደሚራዘም ተገልጿል።
ይህ የምርጫ ሥርዓቱን የመቀየር ዕቅድ በጋልሙዱግ፣ ሂርሸበሌ እና ሳውዝዌስት ግዛቶች ተቀባይነት አግኝቷል። የጁባላንዱ ፕሬዝዳንት አህመድ ሞሐመድ ኢስላም የምርጫ ሥርዓቱን ለመቀየር ሲደረግ የነበረውን ውይይት ጥለው ወጥተዋል። የፑንትላንድ ግዛትም በተመሳሳይ ተቃውሞዋን ገልጻለች።
ከጁባላንድ የተገኙት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምሴ አብዲ ባሬ፤ የግዛቷ መሪዎች የሶማሊያ ምርጫን አንድ ለማድረግ እና ለመለወጥ በተጀመረው ሂደት ላይ እንቅፋት በመሆን ከስሰዋል። የጁባላንድ መሪዎች በበኩላቸው ምክክሩን አቋርጠው መውጣታቸውን በማስታወስ ስምምነቱ እንደማይመለከታቸው እየገለጹ ይገኛሉ።
የፌደራሉ መንግሥት እና ሦስት ግዛቶች ከተስማሙበት የምርጫ ሂደት በተቃራኒም በነባሩ አሠራር የምክር ቤት አባላትን መርጠዋል። በሚቀጥለው ማክሰኞም የፕሬዝዳንት ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ የሁለቱ አካላት መካረር “አሳስቦናል” ያሉት 18 ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ተቋማት እንዲሁም ሀገራት፤ ጁባላንድ ወደ ምክክሩ ተመልሳ መግባባት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮችን እንድትፈታ እና ከፌደራሉ መንግሥቱ ጋር የነበራትን ግንኙነት እንድትቀጥል ጠይቀዋል።
መግለጫውን ያወጡት ተቋማት እና ሀገራት ሶማሊያ “አካታች እንዲሁም አሳታፊ ወደሆነው የአንድ ሰው አንድ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት” የምታደርገውን ሽግግር እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
ተቋማት እና ሀገራቱ፤ “ማንኛውም የምርጫ ሂደት ከመጠናቀቁ በፊት ሁሉም አካላት ከተንኳሽ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ እና ወደ ግልፅ ውይይት እንዲመለሱ እናበረታታለን” ብለዋል።
በጁባላንድ እና በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት መፍትሄ የማያገኝ ከሆነ ጁባላንድ ነጻነት እስከማወጅ ልትሄድ እንዲሁም ግጭር ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት በአንዳንዶች ዘንድ ተፈጥሯል።
ይህም ጽንፈኛውን ታጣቂ ቡድን በመዋጋት ላይ ባለው እና ነጻነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ፍጥጫ ላይ ለሚገኘው ለሶማሊያ መንግሥት ሌላ ራስ ምታት እና ሥልጣኑን ለማጠናከር ለሚያደርገው ጥረት እንቅፋት ይሆንበታል።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ