#አሳቻው ዘመን #ከእኔ ምን ይጠይቃል??? መልስ። የጭካኔ መንፈስ ቤተኛ እንዳልሆን #እራሴን ማዳን። BBC "በሰሜን ሸዋ ደራ ስለ ተከሰተው እና ስለ አሰቃቂው ቪዲዮ እስካሁን የምናውቀው"
መልስ።
የጭካኔ መንፈስ ቤተኛ እንዳልሆን #እራሴን ማዳን።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
ግን ደራወች በፋኖ ተደራጅተዋልን? ከ30 ዓመት በላይ ቀራኒዮ ስለሆነ ኑሯቸው።
ኢትዮጵያ በአሳቸ ዘመን ላይ ትገኛለች ብዬ ወደ #አምስት ዓመት ጽፌያለሁኝ። መስቀለኛ ለሚሉት ፖለቲከኞች አይመቸኝም። አይደለም በዛች ቅድስት አገር ቀርቶ በሌላም ታሪክ ተሰምተው የማይታወቁ አሰቃቂ፦ ሰቅጣጭ፤ አስደንጋጭ አረማዊነት መስማት ከጀመርን ስድስት ዓመት አለፈ።
በቀደሙት ጊዚያት ብዙ አሰቃቂ የሰባአዊ መብት ጥሰቶች በነፃ አውጪ ግንባሮች እንደ ተፈፀሙ ይነገራል። ያን ጊዜ እንደ ዛሬው ማህበራዊ ሚዲያ ስላልኖረ ሊሆንም ይችላል። ወይንም የእኔም ከእኔ የቀደመውም ትውልድ በሰባዊ መብት ጥሰት የነበረው አትኩሮት #ደብዛዛ ሆኖ ሊሆን ይችላል።
ዛሬ ግን መሻገሬያውም #አሳቻ፤ ዘመኑም አሳቻ፤ መሪወችም #አሳቻ ስለሆኑ የችግሩን መንስኤ፤ የመፍትሄ ጎዳናውን ለመቀዬስ እጅግ እዬከበደ መጥቷል። የሚሰሙ ሰቅጣጭ ነገሮች ሁሉ ለህመም ዳርገውናል። ለበጎ ነገርም ቢሆን እኔ ተያይዘው የሚላኩልኝን የቪዲዮ ክሊኮች አልከፍትም። ውስጤ ያለው ሃዘን ነው። ዕንባዬ ደርቋል። ዓይኔም በተደጋጋሚ ለኦፕራሲወን ተጋልጧል። ውስጤም ተጎድቷል። ስለሆነም እኔ የተለቀቀውን ቪዲዮ አላዬሁትም። ወ/ሮ ሃንሻ ከወረባቦ በህወሃት ሰራዊት አዛውንት እናታቸው ተገድለው እያዩ አካላቸው ለጅብ ሲሰጥ የዚህች ወ/ሮ ህይወት ቀጣይነት ማሰብ ነው። ሻሸመኔ፤ ዝዋይ፤ አርሲ ነገሌ፤ ሀረር ሳይቀር መሰል ሰቅጣጭ ድርጊቶች ተከውነዋል።
17 + 1= 18 እነኝህ የአማራ ወጣቶች በደንቪዶሎ ዩንቨርስቲ ሲታገቱ፤ አንዷ ገራገር ወት አስምራ ሹምዬ ተለቃ መልሳ ስትታፈን ጠያቂ የለም። ይህም ብቻ አይደለም የአንዷ ታጋች እናት አዕምሯቸውን ስተው ነበር። ይህን ያዬ ወንድም እራሱን በገመድ #አንቆ ገደለ። አባት ባዶ ቤት ቀሩ። ህይወታቸው እንዴት ይቀጥል? ሙሉ ስድስት ዓመት አማራ መሬት ትምህርት ስቃይ ነው። በዚህ ዓመት ሊገቡ ከታቀዱት 7 ሚሊዮን ተማሪወች መሃል 2.4 ሚሊዮን ብቻ ራድ እና ትምህርት በጭንቀት። ይህም ይቀጠል አይቀጥል አይታወቅም። ህክምና፤ ትምህርት ቤት፤ እርሻ ሥራ ላይ እያሉ ከሰማይ ቦንብ ሲዘንብስ፤ ህዝብ መኖሩን በደስታ ሊቀጥል ይችላልን????
ሻሸመኔ ተገድሎ፤ ያ አልበቃ ብሎ #ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ ህዝብ ተሰብስቦ እሰዬው ሲል ሲጨፍርም ተመለከትን። ቡራዩ ቪዲዮወች አልወጡም እንጂ የጭካኔ ዓይነቱ ለመቀጣጫ ነበር። የአሶሳ፤ የዋተር፤ የወለጋ፤ የመተከል፤ የወልቃይት ጠገዴ፤ የደራ፥ የራያ የመተከል፤ የአማሮ፤ የገድዮ፤ የጋንቤላ በመላ ኢትዮጵያ ያልሰማናቸውን አሰቃቂ ክስተቶች ጨምሮ አንገታችን ቀና አድርጎ የሚያስኬድ አይደለም። ለዚህ ነው እኔ ከ4 ዓመት በፊት #አብረን #እንፈር ብዬ የፃፍኩት። አውዲዮም አለው።
የታጠቀ ኃይል፤ መንግሥትም፤ ሲሳካላቸው ብቻ ሳይሆን ከመሳሪያ እና ከስልጣን ጋር ያሉ ንክኪ ኩነቶች ብዙ ሰብዕናን የሚፈትኑ፤ የሚፈታተኑ ጉዳዮች ይገጥማሉ። በረጋ እና በሰከነ ህይወት ተሰደው የሚገኙ ሊቃናት እንኳን ርጋታቸው፤ ስክነታቸው ሊፈተን እና ብስጩ ሊሆኑ ይችላሉ። በሚሰሙ፤ በሚደመጡ ጭካኔወች ብቻ ሳይሆን የስኬት #ስክነቱ ፈተና ላይ ሲወድቅ።
እኛም በግል የምንተጋ በማንመራው መንፈስ ከፍ እና ዝቅ ዝንቅንቅ ሁነት ጤናችን አደጋ ላይ ይወድቃል። ሱባኤው ሁላችንም ያስፈልገናል። አደቡም ለሁላችን ይረዳናል። የኢትዮጵያ ሚዲያወች ብቻ ሳይሆኑ በውጭ ተኮር የሚተጉት ሳይቀር አንድ ጊዜ አልበቃቸው ብለው ሁለት ጊዜ "#ሰበርን" ይጽፋሉ፤ ወደ "#ሰበር" ስያሚያቸው የተቀዬሩ ሚዲያወችም አሉ። ያ ለአድማጭ ህሊና መረጋጋት ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳለው ማሰብ ይገባል። ሰበር የሚሉትን እኔን ለመሰበር ፈቅጄ አላዳምጣቸውም። የውጭም ዜናም ቢሆን።
የሆነው፤ እዬሆነ ያለው፤ ወደፊትም የሚሆነው ከቀደመው የከፋ እና #የከረፋ ሊሆን ይችላል። ይህንን ለመቋቋም የዘመኑን የፖለቲካ ባህሬ በልቶ ቁሞናውን ማወቅ ይጠይቃል። ይህን የሚመክት #ተጽናኝ ሰብዕና፤ ተስፋ ቆራጭነትን ድል የነሳ ሙሉ አቅምን #በአደብ #በጥበብ መፍጠር ይጠይቃል ---- ዘመኑ።
1) ማን አጠፋ?
2) ማን ወጠነው?
3) ምን ለማትረፍ?
4) ይህስ ዛሬን አጠንክሮ ነገን አደርጅቶ ለመቀበል ምን አቅም አለው?
የማይጣደፍ፤ ቱማታ ያልሆነ ልባም ፖለቲከኛ፤ ብልህ መንፈስ ቢያገኝ ጠቅልለን ከሚፈራው ገደል ደመግባታችን በፊት ሊታሰብበት የሚገባ አውራ ጉዳይ ሊሆን ይገባል።
ሃዘኑ #ልብሳችን፤ ድንገተኛ ዜናው #ጌጣችን፤ ዕንባው ስንቃችን ለሆነው እራሳችን ያጣንበት ዘመን ስለሆነ በጥሞና እንገኛለን። በሌላ በኩል ደግሞ ሰው የሚለው ታላቅ ተፈጥሯችን የዩደቂቃው ፈተና የገቢ ምንጫችን በሆነበት ዘመን ኢትዮጵያ፤ ልጆቿ፥ ትውልዱ እና ነገ፤ ተስፋ እና መኖር አቀበት ሆኖ ይገኛል።
አንድ ቀን የሃዘን ቀን፤ አንድ ቀን ብሄራዊ ሰንደቅ ዝቅ ያላለባት አገር፤ አይዟችሁ የማይደፈርበት፤ አጽናኝ መንግሥት በሌለበት ሁኔታ ይህን ሁሉ መከራ የተሸከመው ህዝብ ትዕግስት፤ የመቻል አቅም፤ በልቶ የማደሩ ሁኔታ ለእኔ ታምርም - ትንግርትም ነው።
#የኢትዮጵያ #ህዝብ #በሙሉ #የሰባዕዊ #መብት #ተሟጋች ሊሆን የሚገባበት ዘመን ላይ እንገኛለን። ትርፋ ለፖለቲካ ሳይሆን ኢትዮጵያ የሰባዕዊነት ምድረ በዳ ናሙና እንዳትሆን ከማድረግ ላይ ቢሆን ምርጫዬ ነው።
1) ወንጀለኛው ማነው?
2) ምንስ ይገጥመዋል?
እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የተወሰደ #እርምጃም አላዬነም። የፍትህ ሚኒስተሩ ሁለተኛ ቁልፍ የኢትዮጵያ ሰው ሆነው ከሹመት ላይ ሹመት ሲዳብር፤ ትዳራቸው ሌጋሳቸውን ያስቀጥሉ ዘንድም ፍትህ የግል ሳሎን ቤት ሲገባ አዬን። የሚፈራ ጠፋ። #ሃግ የሚልም የለም። ለስልጣን ያሰጋሉ የሚባሉት የአማራ ልጆች ታስረው፤ ታግተው እስከ ቤተሰባቸው ከመንገላታታቸው ውጪ ፍትህ በኢትዮጵያ ምድር አናይም። ባለፈው ሰሞን በአብይዝም መንግሥት የተደራጄ ማፍያ እንደአለ የውጭ ሚዲያወች አጋልጠው ነበር። ከዛ በፊትም መከራው የደረሰባቸው ወገኖች አጋልጠው ነበር። እኔም ከማያቸው ምልክቶች ተነስቼ አሳስቤ ነበር። ስለሆነም ይህን አሰቃቂ ድርጊት ደራ ላይ እዬፈፀመ ያለው ማን ነው ለሚለው ለመርማሪ ጋዜጠኞች እና ለሰባዕዊ መብት ቋሚ ሞጋቾች የሚተው ይሆናል።
የወንጀሉ ባለቤት ማነው ለሚለው እራሱ ለመመለስ አስቸጋሪ ነው። #አሳቻ ዘመን፤ #አሳቻ መሪ ኢትዮጵያ ስላላት። ጉዳዩን የሚያከብደውም ይኽው ነው። ጭካኔ ቁምነገር ሆኖ ፋክክር ሊደረግበት ባልተገባ ነበር። ባለመታደል ግን የኢትዮጵያ ፖለቲካ መንፈሱ #ጭካኔ የረበበት ነው። ለዚህ መፍትሄው እያንዳንዱ ከእግዚአብሄር ከአላህ ጋር ግንኙነቱን አጠንክሮ መቀጠል እንደ አለበት ይሰማኛል። ዘገባወች ሲሰሩ መንፈሳቸው እራሱ ይሰቀጥጣል። ያቺ እናት ምን ትሁን???
ዘመኑ የሚጠይቀው እኔን የጭካኔ መንፈስ ቤተኛ እንዳልሆን የመከላከል አቅምን መገንባት ይመስለኛል።
ክብሮቼ እንዴት አደራችሁ?
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
22/11/2024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
https://www.bbc.com/amharic/articles/c704y4d9e17o
"በሰሜን ሸዋ ደራ ስለ ተከሰተው እና ስለ አሰቃቂው ቪዲዮ እስካሁን የምናውቀው"
"ከደራ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እና በአሰቃቂ ሁኔታ ልጃቸው የተገደለባቸው አቶ አማረ ተስፋ"
21 ህዳር 2024
"በሰሜን ሸዋ ደራ ወረዳ አንድ ወጣት በታጣቂዎች ተይዞ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከታየ በኋላ በርካቶችን አስቆጥቷል።
በአካባቢው በተለያየ ጊዜ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የሚጋጩት የፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ይንቀሳቀሳሉ።
ጉዳዩን በሚመለከት ቢቢሲ ኦሮምኛ ያነጋገራቸው ግለሰቦች ግድያው የተፈጸመው በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ “የፋኖ ታጣቂዎች” መሆኑን ይናገራሉ።
ነገር ግን ይህንን ክስ በተመለከተ ከፋኖ ቡድን የተሰጠ ምላሽ የለም፤ ቢቢሲም በአካባቢው ይንቀሳቀሳል ከተባለው ቡድን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረትም አልተሳካም።
ድርጊቱ የተፈጸመው ከሁለት ወራት በፊት ነው የሚለው ዳንኤል ገመዳ ወደ ሰሜን ሸዋ ደራ አካባቢ አምርቶ የሟችን ቤተሰቦች ማነጋገሩን ለቢቢሲ ገልጿል።
ግድያው የተፈጸመበት ወጣት ደረጀ አማረ ተስፋ እንደሚባል እና የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ ቤተሰቦቹ የሄደ እንደነበር ዳንኤል ጨምሮ አስረድቷል።
በሰሜን ሸዋ ደራ ወረዳ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንዲሁም የፋኖ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ በተለያየ ጊዜ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ይጋጫሉ።
ቢቢሲ ከኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፣ የደራ ወረዳ አስተዳደር እና የፀጥታ ኃላፊዎች ግድያውን በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ሐሙስ በሰጡት መግለጫ በሰሜን ሸዋ ደራ ከተፈጸመው ድርጊት ጋር “አሸባሪ እና ጽንፈኛ ቡድኖች በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙት” የጭካኔ ድርጊት ነው በማለት አውግዘዋተል።
ኃላፊው ጨምረውም ቡድኖቹ “የተለያየ ቋንቋ ይናገሩ እንጂ ድርጊታቸው ተመሳሳይ ነው” በማለት ድርጊቱ በሕዝቡ መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር የተፈጸመ ነው ብለዋል።
መንግሥት ሸኔ የሚለው ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች የሕዝብ ደኅንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ እና ልማት እንዲደናቀፍ እያደረገ ነው ያሉት አቶ ኃይ፤ኡ፤ ፋኖ ደግሞ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች በንጹሃን ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደሪ አቶ ከፋለው በበኩላቸው ይህ ድርጊት ወደ ተፈጸመበት ስፍራ በመሄድ ሁኔታውን አጣርተው እንደሚናገሩ ለቢቢሲ ኦሮምኛ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን እንደሰማ ገልጾ ማጣራት መጀመሩን እና የደረሰበትን ውጤት ወደፊት እንደሚያሳውቅም ገልጿል።
ቢቢሲ ቪዲዮው መቼ እና የት እንደተቀረፀ ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
- የተመራጩ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ፓርቲ ከኢትዮጵያ ጋር ስለተፈረመው ስምምነት ምን ይላል?20 ህዳር 2024
- የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ጥበበ ግዮን ሆስፒታል ካለፈው ሰኞ ጀምሮ አገልግሎቱ ተስተጓጎለ21 ህዳር 2024
- “ሰው መሃል ሆኜ ሁሉም ጨካኝ ሆኖብኝ ነበር” - የፀጋ በላቸው ዘጠኝ የጠለፋ ቀናት18 ህዳር 2024
በአሰቃቂው ቪዲዮ ላይ የሚታየው የ10ኛ ክፍል ተማሪ የነበረ እና የዓመቱን ትምህርት አጠናቅቆ ለእረፍት ወደ ቤተሰቦቹ ያመራው ደረጀ እንዲሁም ጓደኛው ከማል ሁሴን በአንድ ቀን መገደላቸው ተነግሯል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ በከጀማ ተራራ ሸሽተው ነበር። ደረጀ እና ሌሎች ግን በቀያቸው የቆዩት በበረት ታስረው የሚገኙትን እንስሳትን ለመጠበቅ ነበር።
በአካባቢው የነበሩ የፋኖ ታጣቂዎች ደረጀ እና ከማል ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የደረጀ አባት የሆኑትን አቶ አማረ ተስፋ ቶላን አግኝቼ አነጋግሬያለሁ የሚለው ዳንኤል፣ “ያን ቀን አሳድደው እግሩን ተኩሰው መትተው ከያዙት በኋላ ሳርኩላ ወደ ሚባል ቦታ ወሰዱት። እዚያ ቦታ ነው የፋኖ ታጣቂዎች በብዛት የሚንቀሳቀሱት” ይላል።
ደረጀ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሎ አስከሬኑ ለአውሬ የተጣለው እዚያ ቦታ መሆኑን የተናገሩት አባትየው፣ የልጃቸውን መገደል ቢሰሙም አስከሬኑን አግኝተው መቅበር አለመቻላቸውን ጨምሮ ገልጿል።
የደረጀ እናት እና አባት በልጃቸው ሞት ምክንያት አእምሮ ጤናቸው መቃወሱን ዳንኤል ይናገራል።
“የደረጀ እናት አእምሮአቸው ተጎድቷል እና አትናገርም። ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም። ለማንም አይመልሱም።”
ደረጀ ለቤተሰቡ ታናሽ ልጅ ሲሆን ወንድሞቹ እና እህቶቹ አግብተው ከቤት በመውጣታቸው እናት አባቱን ለማገዝ በቤት ያለ ብቸኛ ትንሽ ልጅ መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።
ቢቢሲ በደራ ወረዳ ቱሉ ጉዳ መንደር በሼህ ሁሴን መስጂድ አቅራቢያ ነዋሪ የሆኑና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ነዋሪ በርካታ የፋኖ ታጣቂዎች በሼህ ሁሴን መስጊድ አካባቢ እንደሚኖሩ ያስረዳሉ።
እኚህ ነዋሪ በተለያየ ጊዜ የፋኖ ታጣቂዎች ሰዎችን ገድለው ወደ ወንዝ እንደወረወሩ ይናገራሉ።
“ብዙ ጊዜ ለምነን ሬሳውን እንቀብራለን፤ ሳይቀበሩ የቀሩም አሉ።”
በአካባቢው ባለው ተደጋጋሚ ግጭት እና ጥቃት የተነሳ ያመረቱት ምርት መቃጠሉን የሚናጉት እኚህ ነዋሪ ከየቤታቸው ሸሽተው መሄጃ ያጡ ነዋሪዎች በመስኪዱ ዙሪያ ተሰብስበው ለመኖር መገደዳቸውን ገልጸዋል።
እኚህ ግለሰብ አክለውም ታጣቂዎች ደረጀን ለመግደል ሲዝቱ እንደነበር መስማታቸውን ጨምረው ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪ ታጣቂዎችን የመንግሥት ኃይሎች ከመጡ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላትን ትመግባላችሁ በሚል ጥቃት ያደርሱብናል በማለት ፍርሃት እንዳለባቸው ይናገራሉ።
በተጨማሪም የፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ከመጡ ደግሞ ቤት ያቃጥላሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ይገድላሉ ሲሉ ነዋሪዎች መናገራቸውን ዳንኤል ይናገራል።
ለዚህም ማሳያ አንድ የአካባቢው ነዋሪ “ፋኖ ታጣቂዎች” ወደ ቤታቸው መጥተው አንደነበር ገልጸው “ባለቤቴ እና አማቴ ቤት ነበሩ። አማቴ ልጄን ደብቃ ከአባቷ ጋር ወጥታለች ብላ አሸሸቻት። እርሷን መትተዋት ባለቤቴን ይዘዋት ወጡ” ይላሉ።
ግለሰቡ ባለቤታቸውን ለማስለቀቅ 10 ሺህ ብር ቢከፍሉም ከቀናት በኋላ ግን ባለቤታቸው በታጣቂዎች መደፈራቸውን መስማታቸውን ለቢቢሲ ኦሮምኛ ተናግረዋል።
“መጀመሪያ አንደተደፈረች ደብቃ ነበር። ነገር ግን የአካባቢው ሰዎች ማውራት ሲጀምሩ ነው ለእኔ የነገረችኝ። እኔ እንዲለቋት ብዬ 10 ሺህ ብር ከፍዬ ነበር።”
በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ከሚፈጽሙት የንብረት ውድመት እና ዘረፋ በተጨማሪም በተደጋጋሚ የመድፈር ጥቃቶች ይፈጽማሉ ሲሉ ነዋሪዎች ይከሳሉ።
በችግር ላይ የሚገኙት ነዋሪዎች
ሌላ በአካባቢው በሚገኝ መስኪድ ውስጥ ከሰኔ ወር ጀምሮ ተጠልለው የሚገኙ አንድ ነዋሪ “መውጫ መንገድ የለም። ለመንግሥት ይግባኝ ለማለት ምንም መንገድ የለም። መንገድ ዘግተው ያሉት እነርሱ [የፋኖ ታጣቂዎች] ናቸው” ይላሉ።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች አርሶ አደሮቹ ያመረቱትን ዘርፈው፣ የተረፈውን በማቃጠላቸው በአሁኑ ጊዜ የሚበላ ነገር በእጃቸው አለመኖሩን ይናገራል።
“በፊት በዘር እና በሃይማኖት ሳንከፋፈል አብረን እንኖር ነበር” የሚሉት እኚሁ ግለሰብ፣ “በጾም ወቅትም አብረን ጾምን ነበር። በኢሬቻ ጊዜ እንኳን ከአማራ ተወላጆችጋር አክብረናል” ሲሉ በአካባቢው የሚኖረው ማኅበረሰብ የነበረበትን ትስስር ይገልጻሉ።
“አሁን ግን እነዚህ ታጣቂዎች መጥተው አብረን የምንኖረውን ሰዎች በእኛ ላይ አነሳሱብን” በማለት የተለያዩ ሰቅጣጭ ጥቃቶች እና ግድያዎች መፈጸማቸውን ለቢቢሲ ኦሮምኛ በዝርዝር አስረድተዋል።
ሌላው የደራ ወረዳ ነዋሪ በበኩላቸው ከፍርሀት የተነሳ ማገዶ ለመልቀም እንኳ የምንሄደው በጋራ ነው ይላሉ።
ለዚህም ምክንያታቸውን ሲያስረዱ “ምናልባት አንዱ እንኳ ቢያዝ ጮኽን ለማስለቀቅ በሚል ነው በጋራ የምንሄደው።”
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በቀን አንድ ጊዜ እንኳ ለመመገብ እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ።
ባለፈው ዓመት መንግሥት የእርዳታ እህል ወደ ስፍራው ቢልክም በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እጅ መግባቱን ይናገራሉ።
መንግሥት ጉዳዩን በሚመለከት እስካሁን ድረስ ያለው የለም።
በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በታጣቂዎች በሚደርሱ ጥቃቶች የተነሳ በርካቶች ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።
የፌደራል መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር የገባውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለሁለት ዙር በታንዛኒያ ያካሄደው ድርድር ያለውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ