"የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ጥበበ ግዮን ሆስፒታል ካለፈው ሰኞ ጀምሮ አገልግሎቱ ተስተጓጎለ" BBC
"የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ጥበበ ግዮን ሆስፒታል ካለፈው ሰኞ ጀምሮ አገልግሎቱ ተስተጓጎለ"
https://www.bbc.com/amharic/articles/c8dm85jvl8zo
የፎቶው ባለመብት, BAHIR DAR UNIVERSITY
"በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስር የሚገኘው ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሠራተኞች በሚደርስባቸው ተደጋጋሚ ዝርፊያ እና የደኅንነት ስጋት በከፊል ሥራ ማቆማቸውን ተናገሩ።
ባለፈው ሳምንት “ጭምብል የለበሱ” እና ማንነታቸው አይታወቅም የተባሉ ታጣቂዎች በሆስፒታሉ ቅጥር ጊቢ ስምንት ሰዎችን መዝረፋቸው የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ሥራ እንዲያቆሙ አድርጓል ተብሏል።
በአማራ ክልል ባለው የትጥቅ ግጭት ምክንያት በሆስፒታሉ “አልፎ አልፎ” የአገልግሎት መስተጓጉሎች እንዳሉ የጠቆሙ አንድ የሆስፒታሉ ሠራተኛ፤ ከሰሞኑ በተፈጸመ ጥቃት ባለሙያዎች የደኅንነት ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሆስፒታሉ ሠራተኞች እና የሕክምና ተማሪዎች ጊቢው ያልታጠረ እና ጥበቃውም ያልተጠናከረ በመሆኑ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ ተናግረዋል።
“ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ ማንም አይወጣም። ከሕንጻው ወጥቶ ውሃ ለመቅዳት እንዲሁም ለመዝናናት መውጣት አይቻልም። ስጋቱ ያን ያህል ስለሆነ ሁሉም በሩን ዘግቶ ቁጭ ነው የሚለው” ሲሉ አንድ የዩኒቨርስቲው የሕክምና ተማሪ ስጋቱን ገልጿል።
“ምንም ዋስትና የለንም” ያሉ ጊቢው ውስጥ የሚኖሩ እና ሌላ የመጨረሻ ዓመት የሕክምና ተማሪ (ኢንተርን ሐኪም) ባለፈው እሁድ ታጣቂዎቹ ለመዝረፍ ሲሉ ተኩስ ከፍተው እንደነበር ጠቁመዋል።
የሆስፒታሉ ሠራተኞች እና ባለሙያዎች ባለፈው ሳምንት የተፈጸመውን ዝርፊያ ተከትሎ “እስከ መቼ” በሚል ጥያቄው መጠናከሩን ተናግረዋል።
የሆስፒታሉ ጥበቃዎች ክልሉ ውስጥ ባለው ክልከላ ምክንያት መሳሪያ ያልታጠቁ በመሆናቸው “ማንም ሰው ገብቶ እንደፈለገው ያደርጋል” ያሉት አንድ የሆስፒታሉ ባለሙያ፤ ይህም ስጋት አሳድሯል ብለዋል።
ስማቸው ሳይጠቀስ ለቢቢሲ የተናገሩ አንድ የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ባለፈው ሳምንት የሆስፒታሉን ሜዲካል ዳይሬክተር ጨምሮ ባለሙያዎች መሳሪያ በታጠቁ ሰዎች ዘረፋ እንደተፈጸመባቸው ጠቁመው፤ ተደጋጋሚ ዝርፊያ እና ዛቻ ስለደረሰባቸው ስጋታችን ካልተቀረፈ ሥራ እናቆማለን ማለታቸውን ገልጸዋል።
ይህን ያረጋገጡት የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘበናይ ቢተው በተለይም ከመስከረም ወር ወዲህ የታጠቁ ኃይሎች ተደጋጋሚ ዝርፊያ እንደሚፈጽሙ ገልጸዋል፤ ባለፈው ሳምንት በአንድ ቀን ብቻ እሳቸውን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ጊቢ ውስጥ መዘረፋቸውን አሳውቀዋል።
ማክሰኞ ኅዳር 03/2017 ዓ.ም. ምሽት 12፡30 አካባቢ ሦስት ሆነው የእግር ጉዞ እያደረጉ የእጅ ስልካቸውን የጦር መሳሪያ ተደቅኖባቸው እንደተዘረፉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንድ በሆስፒታሉ ዙሪያ የሚኖሩ ነዋሪ “[ዘራፊዎች] ተሸፋፍነው ይገባሉ፤ [ባለሙያዎቹ] ያላቸውን ሀብት እና ንብረት ይዘው [ዘርፈው] ይሄዳሉ። ከየትኛው ወገን ነው ለማለት ለመደምደም እየተቸገርን ነው” ሲሉ የዘራፊዎቹ ማንነት እንዳልተለየ ገልጸዋል።
የሆስፒታሉ ጥበቃዎች መሳሪያ የታጣቁ አይደሉም ያሉት ዶ/ር ዘበናይ፤ “እንዲሁ ተቀምጦ ከማየት በዘለለ አየናችሁ እንኳ አይሉንም” ሲሉ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች አስፈላጊው ጥበቃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ በባለሙያዎች ላይ በሚደርስ ተደጋጋሚ ዝርፊያ ምክንያት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የህክምና አገልግሎት እንደስተስተጓጎለ ቢቢሲ ያናገራቸው ምንጮች አመልክተዋል።
አንድ የሆስፒታሉ ሠራተኛ በተፈጸመው ዝርፊያ ምክንያት የተመላላሽ ሕክምና አገልግሎት እንደተቋረጠ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከድንገተኛ ሕክምና ውጪ ሆስፒታሉ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ያሉ ሌላ ባለሙያም፤ ሁነቱን “አድማ” ይመስላል ብለዋል።
በሆስፒታሉ ዙሪያ የሚኖሩ ነዋሪም ባለፉት ቀናት “ድንገተኛ እና ወላድ ክፍል” ብቻ አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር ጠቁመው፤ ሌሎች ክፍሎች ግን ሥራ ስለማቆማቸው እንደሰሙ ተናግረዋል።
የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊም ዝርፊያውን ተከትሎ የሆስፒታሉ ሠራተኞች “የደኅንነት ዋስትና ያስፈልገናል” በሚል ሥራ ለማቆም መምከራቸውን ገልጸዋል።
የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር በበኩላቸው አብዛኞቹ ሐኪሞች ሆስፒታሉ ጊቢ ውስጥ እንደሚኖሩ ጠቁመው፤ “የደኅንነታችን ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ነው” በሚል ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄዎች ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
“የተለመደውን መደበኛ አገልግሎት ለመስጠት ህልውናችን አደጋ ላይ ስለወደቀ በአፋጣኝ መፍትሔ ይሰጠን የሚል ነገር [ባለሙያዎቹ] አድርሰውናል” ብለዋል።
የደኅንነት ስጋቱ እና ዝርፊያው “ትኩረት እንዲያገኝ” በሚል ከሰኞ ኅዳር 09/2017 ዓ.ም. ጀምሮ በሆስፒታሉ የተለመደው መደበኛ አገልግሎት መሰጠት እንደተቋረጠም ተናግረዋል።
ሆኖም የድንገተኛ ሕክምና እና የተመረጡ ሕክምናዎች እየተሰጡ እንደሆነ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ “የሠራተኛው ጥያቄ ሥራችንን በአግባቡ እንድንከውን ጠንካራ ጥበቃ ያስፈልገናል የሚል ነው” ብለዋል።
የሆስታሉ አገልግሎት በመስተጓጎሉ ሪፈር ተብለው የሚመጡ ታካሚዎች ለእንግልት እና ላላአስፈላጊ ወጪ እየተዳረጉ መሆኑን የተናገሩ አንድ የሆስፒታሉ ባለሙያ፤ “አገልግሎት እየሰጠን አይደለም ተብሎ በይፋ ሊነገር ይገባል” ብለዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ ዝርፊያውን ቢያረጋግጡም የሆስፒታሉ አገልግሎት ግን “አልተስጓጎለም” ሲሉ አስተባብለዋል።
“ሐኪሞቻችን ለአንድም ቀን ቢሆን ሥራቸውን አቋርጠው አያውቁም። አይደለም በዚህ ቀለል ባለ ዝርፊያ ይቅርና አካባቢው የጦርነት ቀጠና በነበረበት ጊዜ ሁሉ ሥራቸውን በአግባቡ እየሠሩ ያሉ፤ የሆስፒታሉን አገልግሎት ያስቀጠሉ ሐኪሞች ናቸው ያሉት” ሲሉ አገልግሎቱ አለመስተጓጎሉን አመልክተዋል።
የዩንቨርስቲው ፕሬዝዳንት ችግሩን ለመፍታት የአካባቢው ነዋሪዎች ለሆስፒታሉ ሠራተኞች ከለላ እንዲሆኑ እና መንግሥት ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር እንዲያውል ውይይቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል።
“የመንግሥት አካል እዚያው አጠገብ አለ። [ዘራፊዎች] እየተኮሱ ሲወጡ ለምንድን ነው እነሱ እንኳ ማዳን ያልቻሉት? አንደኛ ሆስፒታል ነው፤ ትልቅ ሆስፒታል ነው፤ ሪፈራል ሆስፒታል ነው። ይህን [ሆስፒታሉን] መጠበቅ የነበረበት መንግሥት ነው” ሲሉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ስለፀጥታ ሁኔታው ተናግረዋል።
ከባሕር ዳር ከተማ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሆስፒታሉ “የመንግሥት ኃይሎች” ሠራተኞ ላይ ተደጋጋሚ ድብደባ፣ እስራት እና ዛቻ እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ።
“ከሁለቱም ወገን አንደኛው ሌላኛውን ታክማለችሁ ይላሉ” ሲሉ ከሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች ጫና እንደሚደርስባቸው ያመለከቱት አንድ ባለሙያ፤ ሠራተኞች ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ከስድስት ዓመት በፊት ኅዳር 01/2011 ዓ.ም. ተመርቆ ሥራ የጀመረው ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በክልሉ እየተካሄደ ባለው የትጥቅ ግጭት ጫና ምክንያት ባለፈው ዓመትም አገልግሎቱን አቋርጦ እንደነበረ ይታወሳል።
ጥበበ ግዮን ሆስፒታል ከ500 በላይ አልጋዎች ያሉት እና ከክልሉ በሪፈር ወደ አዲስ አበባ የሚላኩ ታካሚዎችን እንግልት የሚያስቀር እና የጤና ተቋማትን ጫና እንዲቀርፍ በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ስር የተቋቋመ ሆስፒታል ነው።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ