የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዲስክርምኔሽን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት።


እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዲስክርምኔሽን
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት።

„ኃጢያት ብተሰሠራ ምን ትጎዳዋለህ?
መተላለፍህስ ቢበዛ ምን ታደርገዋለህ?“
(መጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ 35 ቁጥር 6)

ሥርጉተ©ሥላሴ
Seregute©Selassie
21.01.2020
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ

ይድረስ ለኢትዮጵያዊው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፤
አዲስ አበባ።

ግልባጭ ለ/ ዳንኤል በቀለ - የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን - ኮሚሽነር፤
አዲስ አበባ።

·        ልዑል እግዚአብሄር ለጥያቄዬ ተደማጭነትን ይሰጠው ዘንድ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይህን ጥቅስ ላጠይቅለት።

„ከግፍ ብዛት የተነሳ ሰዎች ይጮኃሉ፣
ከኃያላን ክንድ የተነሳ ለእርዳታ ይጠራሉ።“
(መጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ 35 ቁጥር 9)

እንሆ በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ የቅድሰት ድንግል ማርያም ፍቅር በጭነት ዚታ መኪና በድፍጠጣ በበላዩ ላይ ተሄደበት። እግዚኦ! ማህከነ! ተሳህለነ!

·        ር።

እንዴት ናችሁ የአገሬ ቅኖች - ቅኔዎች? ደህና ናችሁ ወይ? ትንሽ የንፋስ ሽውታ በቀዝቃዛ ርጥበታማ አዬር፤ ጭሮሮ ሆነው መለመላቸውን የቆሙቱን እጽዋት ባልስ መሰል ዳንስ ያሠለጥኑታል። ግራጫማ ጭስ መሰል የሰማይ ትንፋሽ የአዬሩን ውቅያኖስ በስሱ ይቀዝፈዋል። ልዕልት ጠሐይም በልግመት ብቅ ብላለች - እንደ ነገሩ። ለታን እንኳን ነስታ። በዚህ ማህል ጉርብጥብጥ ብሎኝ ስለሰነባበተው እስካንዳንብያ አገር ያለ የሚመስለው የኢትዮጵያዊ ብሄራዊ  የምርጫ ቦርድ ንጹህ ዲስክርምኔሽን በቁስልት የመገለውን ዕንባዬ ጋር መክረን ልንልክለት እንሆ ወሰን።

የቁስለት መግል በብልቂያጥ ቲፍ አድርጌ ሞልቼ ይላክለት አልኩኝ። ወሰንኩኝ። እንደ ወትሮው ቢሆን እንዳለ ስለማልቆጥረው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን አንድም ቀን ሥሙን አንስቼው፤ አጀንዳዬ ሆኖ አያውቅም ነበር። 

አሁን ግን መንፈሴም ከዛ አለ ብዬ አስብ ስለነበር፤ ምንም እንኳን በዬሁኔታው ተስፋዬ ዝቅ እያለ ቢሆንም የተስፋ እንጥፍጣፌዬ ከማለቁ በፊት ውስጤን መላክ ግድ አለኝ።

ለእዮርም ይህው የቁጭት ተማህጽኖ ይላካል። ይህን ጹሑፍ የሚያነቡ የሲዊዝ የአንድነት ቅኖች ቁስለቴን ይረዱታል ብዬ አስባለሁኝ። ለእኔ ክብርት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ማለት ምን ማለት እንደ ሆነች አሳምረው ያውቃሉና። ከዚህም በቅርቤ የሚገኙ ጓዶኞችም አሳምረው ይረዱታል። ከመከፋት ብዛት ስለመሆኑ አያዝኑብኝም ብዬም አስባለሁኝ።

እንዲህ የመረረ የህሊና፤ እንዲህ የሚኮመድድ የማህጸን ምግለቴን ክብርቷ በኃላፊነት ለምትመራው ድርጅት ስጽፍ እራሴንም ሞግቼም፣ አሸንፌም - አምኜበትም ነው። በማተብ ቀልድ የለም። ወ/ት ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ከቅድስት ሃይማኖቴ አትበልጥብኝም። ስለምን ወላጆቼ አይሆኑም። ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል። ፍቅርም ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል።

ክብርቷ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ርት ብርቱካን ሚደቅሳ ዕድሉን አግኝታ አገር መርታ ቢሆን እንዲህ በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ላይ የቅኖና እና የዶግማ ጥሰት፤ የእናታችን፤ የእመቤታችን የድንግል ማርያም የክብር ነቀላ ታካሄድ ነበርን ይሆን ብዬ ሳስበው „አካሄዱን አይቶ ሸክሙን ይቀሙታል“ የጎንደሬዎች ብሂል ሚስጢር ይልክልኛል።

… ግን እንዲያው ግን ተስፋችን የት ይጠጋ? በእሷ እንኳን ተስፋ ማድረግ አንቻል?! ያ ሁሉ የእሷን ሰብዕና ለመገንባት፣ ዓላማዋን ለመርዳት አቅም የፈሰሰበት መታመናዊ አመክንዮ እንዲህ ጤዛ // የሳሙና አረፋ ይሁን? ምጥ አማጠ። አዬ ጊዜ? ሚዛን ያለው ለካንስ ከጊዜ ላይ ብቻ ነው።

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ይህን ያህል ድፈረት፤ ይህን ያህል ዘመቻ ስለምን አስፈለገው ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ? ህዝባዊ ክህደት ወይንስ ግራጫማ ትዕይንት ማን ብለን እንጥራው? እዮር ሥም ያውጣለት። አንድ አገር የሃይማኖትን እኩልነት መጠበቅ ካልቻለች እንደ ሰመጠ መርከብ ትቆጠራለች።

·        ድርሻዬ።

የኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በሁሉመናዋ የበቃች ሁሉ ያላት ዲታ ናት። መዋቅሯም ከአጢቢያ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተደራጀ ነው። መዋቅራዊ አካሏን በቃለአዋዲ ህግ ትመራዋለችም። ምንጩ ግን ቃለ ህይወቱ ነው። ሥርዓቷ ወደር የለውም። እጅግ ሳቢ፤ አጓጊ፤ መሰጭ እና የማይጠገብ ነው። በፍጽምናም ልዩ ነው። ማን ጠግቧትስ!?

ቅድስቷ በዘመናት መካከል በ100 ዓመት ሊተኩ የማይችሉ ዓራት ዓይናማ ሊቀ - ሊቃውታት ቅዱሳን አሏት። ተደምጠው የማይጠገቡ። ታይተው የሚናፈቁ። ቅዱሳን፤ ጻድቃን ሰማዕታት፤ ደናግላን ሌት ተቀን በቀን ሃሩር በግርማ ሌሊት ሳይበገሩ ይጸልያሉ። 

እናታችን ለሁሉመናዋ ልቅና ያለው ሥርዓት ያላት የልዕልና ልቅና ናት። የአገርም የክብር ተክሊል ናት። ለክንውኗም የራሷ ቋንቋ አላት። እጬጌው ግዕዝ የሚስጢራት ማህደር። ጀርመን አገር በክብር ልጆቹን ያስተምራል ግዕዝን። ግዕዝ ገሃዱን ዓለም እና መንፈሳዊውን ዓለም የሚያገናኝ የፍልስፍና፤ የሳይንስ፤ የምርምር አንደበት ነው።

የሆነ ሆኖ እኔ እንደ አንድ የቤተክርስትያኗ ቀናዓይ ልጅ ልብ አምላክ ዳዊት „የቤትህ ቅናት በላኝ“ እንዳለው የመንፈሴ ዓውደ ምህረት ስቃዮዋ ሲጠና ብዕሬም ብራናዬም በቃ! ብለው መውጣት ስለሚገባ ነው ዛሬ ይህን ጹሑፍ ለመጻፍ የተገደድኩት። 

የእናታችን ጥቃት እና የትውልድ ተተኪነት እንዲህ አደጋ ላይ ወድቆ ዝምታ ከልጅ ስለማይጠበቅ የሚሰማኝን መግለጽ ግድ አለኝ። ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በተከደነ ሴራ ውሰጧ በማታውቀው አጥፊ መንፈስ እዬተፈቀፈቀ ነው። ሚስጢሯን ብታማክረው ይገልጥላታል። የታደመባታን፤ የተሰናዳላትን የሸፍጥ እጭ ፍንትው ብሎ ልታዬው ትችላለች። 

እናት ቤተክርስትያኔ የስውሩን የሸፍጥ እጭ ግን ስልቱን ገና የደረሰችበትም አይመስለኝም። በለዝታ የምትወጣው መስሏታል። ነብዬ ብ/ ጄኒራል አሳምነው ጽጌ „አባቶቻችን እንደ አቡነ ጴጥሮስ ሁኑ“ ዘመን ተሻጋሪ መልዕክት ነበር ሰማዕትነትን አቨው ይቀበሉ ዘንድ በአደባባይ የመጨረሻ ቃላቸውን ያስተላለፉት።

ሚስጢር የተገለጠላቸው ሰማዕት ልጇ ከዚህም በከፋ ሁኔታ በቅባት እና በካሬያ ሌላ መከራ እንደ ተደገሰላትም ጎንደር ላይ በነበረው ህዝባዊ ጉባኤ ቀደም ብለውም ተናግረው ነበር። „ልብ ያለው ሸብ“ ይላሉ የጎንደር ባለቅኔዎች። 

በግፍ የመገደላቸው ሚስጢርም የእነኝህ ሁሉ ቁልፍ አምክንዮችን ልቅናን ቀድመው የማመሳጠር ብቃታቸው ነበር። ከፖለቲካ ሊሂቃን ተለይተው በተሰጣቸው ሰማያዊ መክሊት ልክ በመሆን እንጂ እንደ ጋሬ ፈረስ ሪሞርኬ መሆንን በመጸዬፋቸው፤ የፖለቲካ ትንተና አቅማቸው ብጡልም ስለነበር ነው ያን ቃለ ምህዳን የተናገሩት። ነብይነትም ነው።  
    
·        መነሻ። 

(1)             የምረጡኝ ዘመቻ ጊዜ ከሚዚያ 27 ቀን እስከ ነሃሴ 05 ቀን 2012 ዓም.
(2)             የድምጽ መስጫ ቀን ነሃሴ 10 - 11  ቀን 2012 ዓም.
(3)            ዘመቻ የተከለከለለት ጊዜ ነሃሴ 6 ቀን ነሃሴ 9 ቀን 2012 ዓ.ም።
(4)             በምርጫ ክልል ደረጃ ቅድመ ውጤት ይፋ የሚሆንበት ጊዜ ነሃሴ 11 ነሃሴ 15
             ቀን 2012 ዓ.ም.
(5)             የቦርዱ የተረጋገጠ ውጤት ማሳወቂያ ጊዜ ነሃሴ 11  ቀን ነሃሴ 20 ቀን 2012
              ዓ.ም

ጉዳዬ ያለው በናፍቆት፤ በፍቅር ስለምትጠበቀው ፆመ ፍልሰቲት የድንግል ማርያም ፆም ነው። በቀለጤው ኢትዮጵያዊው ዬምርጫ ቦርድ ስለታወጃባት የጥሰት ክተት ዘመቻ ወርኃ ነሃሴ ከዕለቷ ከልደታ እስከ ቃል ኪዳኗ ዕለት ነው።

ነሃሴ አንድ ቀን ልደታ ማርያም ናት መቅደመ ፆመ - ዕለት፤ መቋጫው 16 ኪዳነ ቃሏ ናት። የእኔም የአትኩሮቴ ዘለበት በነዚኽው ቅዱሳን ዕለታት በተተለመው ድንብስ፤ ኢፍትኃዊ፤ በኢትዮጵያዊነት ላይ የሸፈተ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ብቻ ይሆናል።


ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትም ኢትዮጵያዊ ናት እና። በቦርዱ ውስጥ አንድም የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተቆርቋሪ ልጅ አለመኖሩም አመሰጥሮልኛል ውሳኔው። ቅድስት ኦርቶዶክስ መንፈሱን ለማረቅ፤ ባለፈም ለመቅጠት የተሰላ ቀመር ነው። እሞግትሽ አለሁ የሚል ካለ አለሁለት ዘሃበሻ ብራና ላይ ይምጣ እና ይሞክረኝ። በቁጥብነት እና በሚዛናዊነት እንዲሁም በኃላፊነት ሙሉ ስሜት የያዝኩትን አመክንዮ አፈረጠርጠዋለሁኝ።

ወደ ቀደመው ጉዳዬ ምልሰት ሳደርግ ቅብጥ ያለው የብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ከፈለገ ከነሃሴ 17 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ማቀድ ይችል ነበር። ጨቅጫቃው፤ ነዝናዛው ነሃሴ ዓላማቸውን እስኪበቃው ካላናፈጠላቸው እና ከአላስለቀሰላቸው ምሾም ካለስወረደላቸው። ያው የተረሳው፣ እንደ ዜጋ የማይታዬው የኢትዮጵያ ገበሬው እንደሌለ ተቆጥሮ ማለት ነው።

እህል ውሃም አያስፈልገውም ለራሱ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ። በቀጣይ ዓመት በመንፈስ ነው የሚኖረው። ምክንያቱም መቼ እንክብካቤ ያገኜውን ሰብል ይሆን ለቁርሽ እንጀራ የሚበቃው? „አንድ ሰኔ የነቀለውን 10 ሰኔ አይመልሰውም“ ይላሉ ቀደምቶች ሊቀ - ሊቃውንታት ከቅኔ መንደር። ወራቱ የእዝመራ ተስፋ ማዋለጃ ስለሆኑ የገበሬ ወራት ቢባሉ ይሻላል። ጓዳውም፤ ጎታውም፤ ድሆኖውም የብዙ ገበሬ ስስ ይሆናል። ጎመን፤ ዱባ፤ ድንች እነዚህ ናቸው ስንቆቹ እስከ መስከረም በልጋ እና ባህር ማሽላ እሸት እስኪደርስ። የእንጎሮጎባሽ ሚስጢርም ይኸው ነው። 

ወደ ቀደመው ጭብጥ ምልሰት ሳደርግ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ሰላሟን ማወክ፤ ሱባኤዋን ማራድ ስለሆነ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ትልሙ በዚህ መልክ ታቅዷል ወርሃ የነሃሴን መግቢያ ማዕከል አድርጎ። በፆመ ፍልስቲት ላይ ዲስክርምኔሽን በማካሄድ። እኔ እምሞግታቸው ቀናት በጉልህ /በቦልድ/ የተጻፉትን ብቻ በመሆኑ ሌላው የጊዜ ሰሌዳ አይመለከተውም የጹሑፌ አርምሞ። ከነሃሴ 1 ቀን እስከ 16 ያሉትን ቀናትን ብቻ ነው የሚመለከት አቤቱታዬ። እነዚህን ለቀቀ ነው ጥያቄ። 

የሺህ ዘመናት የፆመ ፍልሰቲት ሃይማኖታዊ ትውፊት ናቸው እና። ምርጫ ቦርድ እኮ ትናንት የተፈጠረ ነው፤ ሰው ሰራሽም ነው። አቅም የለውም የሺህ ዘመናትን ትውፊት እና ትሩፋት ለመፈታተን። ለዛውም ሃያማኖታዊ። ለዛውም የምድር እና የሰማይ እመቤትን የድንግል ማርያምን ፆም።  እግዚአብሄር ይቅር ይበለው። አሜን። ትንሽ ልክን ማወቅ ይገባል። ደረጃን መጥኖ መነሳትም። "ጎንደሮች ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል" ይላሉ።

·        የአብይዝም አሻሮ ዘመን።

ይህ እንኩሮ ዘመን ኢትዮጵያዊነትን የሚቀናቀን፤ የኢትዮጵያዊነትን ምሰሶ የሚያነቃንቅ፤ ኢትዮጵያዊነትን የሚሰልል፤ ሙሉ የዜግነት መብትን የሚፈትን፤ ሰውነትን የተደፈረ ደፍጣጭ ውሳኔ ነው በዚህ ዘመን እራሴን አድሼ ተፈጥሬያለሁ የሚለው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ እራሱን ገልጦ የሚያሳዬን። በዚህ ውሳኔ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን ጠርጥሬዋለሁኝ። የአብይዝም ልብ የተገጠመለት ይመስለኛል።

ስለሆነም ሳናቆላምጠው፤ ሳናሽበለብለው የውሳኔው ዕድምታ በንጹህ ቃል ጸረ ማርያም ነው። ኢትዮጵያዊነት ሁልጊዜም በሊሂቃኑ ከወገብ በላይ እና በታች ነው የሚተረጎመው። ኢትዮጵያን ሙሉ መንፈሷን አክብሮ የሚቀበል መሪ ለማግኜት ምን ዓይነት ሱባኤ ትግባ ይሆን አላዛሯ ኢትዮጰያ?! አሻሮ ዘመን።

በዚህ ውሳኔ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን ነፃነት በድፍረት ተጥሷል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን ፍትህ በመስጠት እረገድም መብታቸው በግፍ ተቦጫጭቋል። የኢትዮጵያዊው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን ዴሞክራሲያዊ የመምረጥ ሆነ የመመረጥ መብት ተቀዳዷል። ግለት በግፍም ተፈጽሟል። የሃይማኖት ነፃነት በማን አለብኝነት ቀራንዮ ተልኳል። ያው በሰብሳቢውም በአማካሪውም የምርጫ ቦርድ „ነፃ፣ ፍትኃዊ እና ዴሞክራሲያዊ“ እያሉ የሚነግሩን መለመለዋን ቁሟል።

እነዚህ „ነፃ፤ ፍትኃዊ፤ ዴሞክራሲያዊ“ የሰው ልጅን የሥልጣኔ ደረጃ የሚለኩ ሉላዊ ፍልስፍናዎችም በምሬት ተሸኝተዋል። አይደለም ሰፊ አባላት ያሉት 50+1 % አማንያን ላለው ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቀርቶ አንድም ሰው መብቱ ሊጣስ ባልተገባ ነበር። ለነገሩ በተኛነው ልክ ነው ጥቃትን እዬተጎነጨን ያለነው። የዛ የነፃነት ተጋድሏችን ትጥቅ ሙሉ ለሙሉ አስፈትቶ ጆራችን በደፈነው፤ ለምርኮኝነት እጅ መንሻ አቅራቢው የሊቁ የፕ/ አልማርያም „የአክ ወሬ“ የመቃብር ስጦታ።

ማንኛውም ዜጋ እኩል በሚሳተፍበት የምርጫ ወር፤ የምርጫ ቀን በበዛ ጥንቃቄ፤ ኃላፊነት በተሞላው መልክ ታስቦ መከወን ሲገባ ንጹህ ዲስክርምኔሽን እንደ ተቋም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት በብሄራዊው ምርጫ ቦርድ ተፈጽሟል። እንደ ህዝብም የአማንያኑ የኢትዮጵያ ክፍለ አካልነታችን ዜግነታችን ሙሉ ለሙሉ ያለ ይግባኝ ተሰርዟል። ያማል። ለማመንም ያቅታል። - ያቃቅታልም። ዘመንም አቃተተ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን በእገታ መንፈሳቸው ታስሮ፤ በወከባ እዬተመሰቃቀሉ፤ እንዲሁም ማህበረ - ምዕመኑ መንፈሳቸው ለእሬቻ ምርኮኛ ሆኖ እንዲንበረከክ ሆን ብሎ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ አቀደው ነው እኔን የሚሰማኝ - እማምንበትም። ይህን ህዋህት እንኳን አድርጎት አያውቅም። አብይዝም ኤድስ ነው። እያጫወት የሚሰለስል እንደ እንሶስላ* ወይንም እንደ ጉርሽጥ*
ከዚህም በላይ አፋቸውን ሞልተው „ሞትም ምርጫም አለ“ ያሉት ጠሚር አብይ አህመድ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ የደም አላባነት ፍልሰቲት ልታስተናግድም ትችላለች። በወቅተ - ሱባኤ ደም ታጭቷል።

 ሌትና ቀን አውራው ድርጅት ኦዴፓ /ብልጽግና?/ ጦር እያሰለጠኑ መሆኑንም እያስተዋልን ነው። ሞቱንም እስቀድመው ስለ አቀዱት የዓለሙ የሰላም አባት የኖቤል ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ምርጫ ቦርድ የድንግልን ሱባኤ ለዚህ የመርዶ ቀን አሳምሮ ለኢላማ አሰናድቷል። መደመር ይሉኃል ይሄ ነው በምናብ ማጅካዊ ሠረገላ ተጋብቶ ሳይሞግቱ፤ ለፋክትም ጥብቅና ሳይቆሙ አብሮ መጪ …

የሆነ ሆኖ ብዕሬም፤ ብራናዬም ሱባኤ ላይም ናቸው ይህን መርዶ ከሰሙበት ዕለት ጀምረው። ወይ ፍረድ ወይ ወርድ በማለት። በዛ በጣም በዛ። ከልክም አለፈ። አሁን የኢህዴግ ሥልጣን ሹመት ሆኖ እንዲህም እንዲያም ማድረጉ ያሳዝናል? ምኑ አዋላድቶ ይሆን? በሰመጠ መርከብ ተቀምጦ ይህን ያህል በመዘመን የህዝብን ነፃነት መጋፋት ባላስፈለገ ነበር ለኢህዴግ ሹመኞች። ለካንስ ሥልጣን መዳፈርን እንዲህም በልበ ደንዳናነት ይዳፈራልን? ህዝብን በማስከፋት፤ ህዝብን በማሳዘን ምን ይሆን ትርፉ ለሙሽራው የኢህዴግ ባለሥልጣናት?! ህዝባዊ ማክበርስ፤ ማፍቅርስ የት ይሆን አድራሻቸው?! ትውልዱ መጠጊያ አጣ - ነጣም።

„ኃጢያት ብተሠራ ምን ትጎዳዋለህ?
መተላላፍህስ ቢበዛ ምን ታደርገዋለህ?“ ቃለ ወንጌል ነው።

በሌላ በኩል ለብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ለእነሱ መዝረክረክ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ካሳ ልትከፍል አይገባም። ሰፊ ጊዜ ነበራቸው። ነገር ግን መንግሥታቸው ቀውስን በማደራጀት፤ በመምራት ውጤቱን በመለካት አገር ሲታመስ የተባጀበት መሰረታዊ ምክንያት ያውቁታል ብዬ አስባለሁኝ። ኃላፊነትን ሳይወጡ ለቆዩት ለእነሱም ቢሆን ለአቅም ማነሳቸው ስንፍናቸውን ማካካሻ፤ የቁንጫን መወጣጫ ቅድስት ሃይማኖታችን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዋጋ አወራራጅ ልትሆን አይገባም። የድክምት መሸፈኛም፤ የቂም ማወራረጃም ልትሆንም አይገባም ሃይማኖታችን።  

ይህን  የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሴራ ገመድ በዬትኛውም ዓለም የሚገኙ የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን እና ወዳጆቿ ሁሉ ሊያወግዙት ይገባል። ይህን ግልጽ ዲስክርምኔሽን አቋም ሊይዙበትም ይገባል። ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አቅም ላላቸው የዲፕሎማሲ ማህበረሰቦች ማሳወቅ ትውልዳዊ ድርሻቸው ስለመሆኑም ቢያስቡበት መልካም ነው እላለሁኝ  - በትህትና። ነገ ጠቁሯል። ማግስት ማድያታማ ሆኖ ይታዬኛል ከመምጣቱ በፊት።

ዛሬ በህልሜ አንድ ነገር አዬሁኝ። በጣም ብዙ ባዶ የሬሳ ሳጥኖች በማዕረግ ተሰልፈው ሥም ተጽፎባቸዋል። ሰዎቹ በህይወቱ አሉ። እራሳቸው ሰዎቹ ባሉበት ባዶ ሳጥኖቹ በቅደም ተከተል ግብአተ መሬት ሲፈጸም አይሁኝ። የቁም ቅብረት ማለት ይሆን አልኩኝ። ወይንስ ህወሃት ያደርገው እንደ ነበረው የሙት በቃ የሚፈረድብን ሰወች እንኖር ይሆንም አልኩኝ። እስኪ ፍቱት - ቅኔዎቹ። 

·        መቅድም።

በፌስ ቡኬም ስጽፈው የባጀሁት ቁም ነገር ነበረኝ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አንባሳደር ሊቀ - ሊቃውንቱ እርጉው ዶር ካሳ ከበደን የበላ ጅብ አልጮኽ ብሏል። የት ገቡ? እሳቸውም እንደ አላዛሯ ኢትዮጵያ ታገቱን ይሆን? እሳቸውስ እንደ የኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ማዕቀብ ተጣለባቸው ይሁን?

 በሳቸው ላይ ፍጹም የሆነ ዕምነት ስለነበረኝ፤ ቤተክርስትያኗም ስለምታምናቸው ይህን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት የታዘዘባትን ሁለገብ የጦሮ ማዕት በዝምታ ሲያስታምሙት መተመን ሆይ! የት ነህ ያለኽው ማለቴ አለቀረም። በስንቱ ነፍስስ ይታዘን? የተስፋ ስጥመት በሁለመና። ማልቀስ ብቻ የሚቋቋመው አይመስለኝም። ቁጭት አሻምን አምጦ መውለድ ያለበት ይመስለኛል። ቢያንስ ለፈጣሪ በዕንባ አቤት ማለት። ሰላማዊ እርምጃዎችንም ደፍሮ መውሰድ።  

በምርጫም ካርድም ድምጽ በመንሳት ሙሉ ለሙሉ ዘረ የኦሮሙማ፤ የእሬቻን ተደማሪን የህሊና ቤተኛ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሁሉ መቅጣት ያስፈልጋል ፊት መንሳት „ሙያ በልብን“ መስጥሮ። ስብሰባ ሲጠሩም አለመሄድ። እዬሞቱ መኖር የለም እና። ማተብ የማይደራደሩበት የነፍስ ጉዳይ ነው። ከዚህ በላይ የሚጠበቅ ነገር የለም። 

በዚህ ውስጥ የአገር ሉዕላዊነትም ሲታሰብ ሌላ የመከራ አለርም አለ። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ አቀማመጧ እስትራቴጂካዊነት የተነሳ አልመው ግን ከሽፈው የኖሩት የዘለቄታ ጠላቶቿ ግባቸውን እያሳኩ ይመስላል። በሯ ቧ ብሎ በሁሉም አቅጣጫ ተከፍቶላቸዋል። 

ምን ያህል ሚሊዮን ዶላር ይሆን የዛን ጊዜ አዲስ አመራር ሲመጣ የተቸረው? የዛ መዘዝ ለኑዛዜ ሳያበቃ ብዙ ብሄራዊ መብት በለጋሾቹ መዳፍ ውስጥ ስለመግባቱ ማስተዋል ይችላል። ለዚህም ልዕልናዊ አመክንዮ ዶር ካሳ ከበደ ማህንዲሱ ነበሩ - ትናንት። የዛሬን የሉምና አቋማቸውን በሚመለከት እሚታወቅ ነገር የለም። ብቻ ግን ደህና ይሁኑ - የአገር ሃብት ስለሆኑ።  
  
·        የተስፋ ምጥ።

ቅልጣን ቅረበኝ ያለው ኢትዮጵያዊው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ „ነፃ፣ ፍትሃዊ፤ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ፤ መንግሥትም፣ መሪም፤ ህገ - መንግሥትም ባላት አገር“ የሚል ዕድምታ ያለው ድምጸትን ሲያሰማን እንደ አፉ ያድርግለት ብለን ዝም አለን። 

መርኽን ማስከበር ተስኖት የገዢው ፓርቲ የኦህዴድ ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ በመርኽ ጥሰት ተፈጠርኩ ያለውን ሙሽራውን ኢህዴግ /ብልጽግና?/ ህግ ተጥሶ በቱማታ ዕውቅና ሲሰጥ ሞግትን ሰሚ አልተገኘም። ለዓለም ሚዲያም፤ ለተመድ የተራድዖ ድርጅት ሚስሊድ እዬተደረገ እንደሆነ እናስባለን። ሁሉም ነገር በተሳካ ሁኔታ እዬተከወነ ነው እንደሚባል። ይህም ሌላ የብሄራዊ አደራን ተጠዬቅ የሚያሰኝ የምዕት ገመና ነው። 
  
አሁን ደግሞ በቀጥታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ሰቅዞ ለማያዝ ነሃሴ ወርን መርጦ ጾመ ፍልስቲትን ትንፋሽ ነስቷታል ክብርት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የምትመራው ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ። ጉዳዬ መበቀል ይመስላል። „ነው“ አላልኩም ይመስላል ነው። ከምናዬው የብሄራዊ ባዕላት መስተጓጎል እና መንግሥታዊ ጫናም አንጻር ሲመዘን። በውስጥ ፖሊሲ የተያዘ የተከደነ ነገር እንዳለ ይሰማኛል።

ይህን ምጥ መላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ማህበረ ምዕመናን፤ የቤተክርስትያኗ ወዳጆቿ እና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከልቡ ሆኖ ሊያውገዘው ይገባል። ሌሎች ሃይማኖቶችም ነግ ለእኔ ብለው አሻም በማለት ወሩን በጠቅላላ ማስለወጥ ያለባቸው ይመስለኛል። አገር ያቆሙ ባላወች እዬተናጉ ናቸው። መንፈስ ከሸፈተ አካል አይኖርም። 

ለዚህ ነው ጉዳዩ „ከፈረቃም ከተረኝነትም“ በላይ ስለመሆኑ ቀደም ባሉ ሙግቶቼ ስገልጽ የቆዬሁት። አሁን ያለው ክርክር ለወቅቱ ፓለቲካ አይመጥንም እምለውም ለዚህ ነው። አገር በጠላት እጅ እንደ ወደቀች ይሰማኛል። በቀጥታ ጦሩ የት ላይ እንደ ተመዘዘ አርምሞን አቤት ይላል። 
  
የሆነ ሆኖ ይህ ድፍረት በረመዳን ፆም አይሞከርም። ይህ ድፍረት በነብዬ መሀመድ መውሊድ ቀን አይሞከርም። ይህ ድፍረት በሬቻ ክብረ ባዕል አይደፈርም። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ግን ድፈረቱ ተከናውኗል። ንቀት! ይህን ማህበረ ምዕመኑ ቁጣውን ሊገልጽበት ወይንም ቅጣቱን ሊያሳይበት የሚገባ በኽረ ጉዳይ ነው። በቃ! መባል አለበት። 

የነብዬ ብርጋዴር ጄኒራል አሳምነው ጽጌ ንግግር ተደጋግሞ ሊጤን ይገባዋል። „እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል ሰው ግን አይስተውለውም“ ይላል አካል የሌለው  የእግዚአብሄር አገልጋይ ቅዱስ ወንጌል። „ አባቶቻችን እንደ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕት ለመሆን ተሰናዱ“ ያሉትን በሁሉም ዘርፍ እያዬነው ነው። ገራሚው እና አንጀት በጣሹ ጉዳይ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳም በገቪር የአብሮነቷ ጉዳይ ነው።

ይህ ሂደት በሚቀጥሉት 5 ተከታታይ ዓመታት በምን ዓይነት በተመሰጠረ ሁኔታ የእምነቱ ተካታዮችን በፖለቲካ ተሳትፎ እንዴት ከእርስት ነቀላ እንደሚከናውን በ2011// በ2012 ዓ.ም በታዬው የመሰቀል ባዕል አከባበር፤ አሁንም በጥምቀት የታዬ ነው። 

አሸባሪዎች የሚመጡት፤ የሚሰማሩት፤ የሚያዙት፤ መግለጫ በመንግሥት የሚሰጠው ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ባዕለ ሃይማኖት በአደባባይ ሲኖራት ብቻ ነው። አሁን ወደ ዓዋጃዊ አፆማት ተሸጋግሯል ሃይማኖታችን የመስበር ዘመቻው። ይህን ሉላዊ የሆነ አቅም ፈጥሮ መሞገት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቀ - ሊቃውንት ታሪካዊ ድርሻ ይመስለኛል። ለዚህም ይህን ጽፌ ነበር።

የኔታዋ የደወል ምህላን፤ ብትደፍረው፤ የአርሲ ነገሌ መስቀል ጉዞ ወደ ቀራንዮ

ለዓለምም አቅሙ ያላችሁ የቀናቱን ክስተቶችንም በተጨባጭ ማሳወቅ ይገባል። መተኛት አያስፈልግም። የመንፈስ ወረራ ላይ እንዳሉ ይሰማኛል የኦዳ ንጉሳን። ወረራቸውም ድል ላይ ነው። ገዢውን መሬት ሙሉ ለሙሉ እዬተቆጣጠሩት ነው። ሌት እና ቀን እነሡ እዬሠሩ ነው። 

ነባሩን ቅዱስ ኢትዮጵያዊው የአብሮነት መንፈስ በማፍረስ አዲሱን ኦዳዊ የመጫን መንፈስ በማስፈን ላይ ናቸው። ይህን የሚመክት ፖለቲካዊ በሳል ጉልበታም አቅም ያስፈልጋል። ቢሠራበት ዓለም እጁን ዘርግቶ ነው የሚቀበለው ይህን መሰል ተጨባጭ ክስተታዊ ዕውነት። „የምርጫው ፍትኃዊነት፤ ነጻ መሆን እና ዴሞክራሲያዊ መሆን“ እዬታዬ ነው። ሰፊውን  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን ባገለለ ሁኔታ።   

·        የምርጫ ቦርድ የምርጫ ውጤት ህልም ዝንባሌ ግንጥል ጌጥነት።

የምርጫ ቦርድ የምርጫ ውጤት የተስፋ ዝንባሌ የሙሽራው ኢህዴጉ አውራ ፓርቲ ኦዴፓ በብልጽግና፤ ኦንግ በኦፌኮ፤ የቀስተዳመናው መንፈስ በውርስ ኢዜማ  እንዲመረጥለት የመሻት አዝማሚያ አያለሁኝ። ምንም እንኳን መጨረሻ ላይ እልባት ቢያገኝም በዚህ ስሌት ሲስተዋል ኢዴፓ ላይ ተነጣጥሮ የነበረው ሸፍጥ፤ ኢኃን ላይ የነበረው ማጓተት፤ አብን ላይ ያለው የመሪዎች የካቴና ሽልማት እና ለከት የለሽ ወከባ ለምርጫ ቦርድ ለምለማዊ ጉዞ ይሆን ማለቴ አልቀረም። አቅሙን ሙሉ ተጥቅሞ አልሞገተውም በተለይ በአብን ጉዳይ።

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በሌሎች ጎልተው ባልወጡ የፖለቲካ ድርጅቶች ያለው ስጋት እንብዛም ነው። እነሱ የፈለጉ ቢፍጨረጨሩ መንግሥትን ለማያዝ አይችሉም በሚል ቸል ሊላቸው ይችል ይሆናል። በተለዬ የአማራ መንፈስ ያለባቸውን ግን በመጫን እና በማጉላላት እረገድ የሚታዩ ግድፈቶች ገዝፈው አያቸዋለሁኝ ባለፉት ወራት። እርግጥ አሁን ኦፌኮን የሞገተበት ማለፊያ መንገድ ነው። ይህ በራሱ የኃይል አሰላለፉን እንደ ገና የሚበውዘው ሲሆን፤ ድፍረቱ ግን የአብይዝም ፈቃድ እንዳለበት አሰባለሁኝ።

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከኦፌኮን ጋር የጀመረው ሙግቱ ያን ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለኢትዮጵያዊነት ቅዱስ መንፈስ በሸፍጥ የተደለዘውን የተከደነ፣ ሥውር፣ ትብትብና ግርዶሽ ተዳፍሮ አሸንፎ ከመወጣ የሚታይ ይሆናል። ብዙ ያለዬላቸው የኃይል አሰላለፎች ስላሉ። 

አሁን መከላከያ፤ ፌድራል ፖሊስ፤ አዬር ኃይል፤ ደህንነት ቢሮ፤ ሪፓብሊካን ጋርድ የማነው? የሚለው እራሱን የቻለ ሞጋች አመክንዮ ነው። መንግሥት አቅዶ የሚፈጽማቸው ሸፍጦችም አሉ። ለፖለቲካ ትርፍ። አሁን ባለው ሁኔታ ግን መልካም ነው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያሳዬው ድፍረት፤ ለዜና ሸቀጥ ብቻ ካልሆነ።

ጃዋር ቀነ ገደብ ያስቀመጠውን የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ፈርሞ ተቀበለ (ጎልጉል እንደዘገበው)


·        እናታዊነት ውስጡን በመሆን ብቃት ማበልጸግ በእንዴት አመክንዮ?

እኔ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ይህ ኃላፊነት ሲሰጣት እናታዊ ሰብዕናዋን ጸጋ ሁሉ የመጠቀም አቅምን ከእሷ አብዝቼ ጠብቄ ነበር። እናት አታዳላም። እናት ለሁሉም ልጆቿ እኩል ናት። ይህን እናታዊ መክሊት ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጠብቄ ግን ብዙም አላዬሁም። 

የክት እና የዘወትር ልጅነት አስተውላለሁኝ። ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት በአማራ የፖለቲካ ሊሂቃን ያለው መንግሥታዊ ጠናና አመለካከት ምርጫ ቦርድ ላይ የለም ብሎ ለመናገር የሚያስችለኝ ሁኔታ የለም። አፍጦ የሚታይ ዕውነት ነውና።

አቶ ክርስትያን ታደለን፤ አቶ በለጠ ካሳን ሳስብ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንዴት አንድነት ፓርቲ ላይ የደረሰውን መከራ ሲደገም በዝምታ ልታልፈው ቻለች? ሞገተች ሲባል ሰምቼያለሁኝ። ሙግት ብቻ ሳይሆን ኃላፊነት እስከመልቀቅ የሚያስወስን ጉዳይ ነበር። የራሷ ጉዳይ ነውና የተደገመው። ሙግት መለኪያው ስኬቱ ነው። 

ምክንያቱም የአብን የጽ/ቤት ኃላፊ፤ መካች፤ ብቁ፤ ባለ ተሰጥኦ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መታሰር ማለት አንድን የፖለቲካ ድርጅት ለመራ የህግ ባለሙያ ይጠፋዋል ብዬ አላስብም። ወገቡ ተጎረደ ማለትም ነው። መዋቅሩን ማናጋት ማለት ነው። 

አከርካሪ አልባ ሰብዕና ማለትም ነው። በዚህ ሂደት ቢያንስ የህግ ሰውነት በስሱ ለማዬት አልተቻለኝም። የእግዚአብሄር ሥራው ረቂቅ ነው እና በቀሪ ጊዜያት የተሻለ ሚዛናዊ የሆነ አሰራር ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ሊከተል ይችላል ብዬ ልመን እና የተስፋ ፍርፋሪ ወይንም ቅርጥምጣሚ ነገር እንዲኖረኝ ልፍቀድለት - ለህሊናዬ። ልብ ከሰጠው ኢትዮጵያን ከወገብ በላይ እና በታች እማያያት ከሆነ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ።

·        የቀኑ መራዘም።

የቀኑ መራዘም ተፈልጎ የተከወነ ነው ብዬ ነው እማስበው። በተባለው ቀን ምርጫው ይከናወናል ብሎ ለማሰብም ከባጀብን የሸፍጥ፤ የሴራ መቅሎ ፖለቲካ እንጻር እራሱን የቻለ ተደሞ አለው። ምኑ ይታመናል የኦሮሞ ፖለቲካ የሊሂቃኑ ድንገቴም ግራጫማም እርምጃ። ስለዚህም ቀኑ ሳብ ማለቱ ከኦሮሙማ የፖለቲካ ትርፍ ጋር የሚታይ ነው።

የኦሮሞ ፖለቲከኞች ያጩት አዲስ አመክንዮም ሊኖር ይችላል። አብይዝምን ያመነ ጉም የዘገነ ነው። ለዚህ ሁሉ የፖለቲካ ግሽበት ተጠያቂዎች ተደማሪዎችም ናቸው። ሙሉ አቅም በሙሉ መንፈስ አሳፋሾች እነሱው ናቸው እና የጉሮሮ አጥንትም ናቸው። 

ብቻ እነሱ ቁንጮ ላይ ቤተ - ተጋሩ፤ ቤተ - አማራ ስሜነኛ ብቻ አይሁን። ሌላው ግድ አይሰጣቸውም። የሚገርመው መጋለቢያው ደግሞ አማራ ነው። ለዚህም ያበቃው። ወሳኙ በኢትዮጵያ ምስቅልቅል ተጠያቂው ግን ታሪክን ለበላሃሰብ የሸለመው ግርባው ብአዴን ነው።

ቢያንስ ታሪክን ምርኮኛ ማድረጉ ተችሎ ሚዛኑን በማስጠበቅ የኢትዮጵያን ህዝብ ህልውና ዋስትና እንዲኖረው ማድረግ ሲችል ግርባው ብአዴን ተኝቶ በለኝ አለ። የኢትዮጵያዊው ምርጫ ቦርድ የተልዕኮ ጉዞ ኦነግ በሥውር መንፈሱ፤ ኢህዴግ በኦዴፓ {በጨረቃ ቤቱ ብልጽግና፤} ሌላ ታሳቢ የውህድ አካል በቀስተደመናው መንፈስ ኢዜማ አብላጫውን ወንበር እንዲያዝ ይሻል ይሆን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሚልም ምልከታ አለኝ። ለእነዚህ ሦስት አካላት አልጋ ባልጋ ነው ሁሉም ነገር። የስለት ልጆችም ናቸው ለብሄራዊው የምርጫ ቦርድ ብዬም አስባለሁኝ።

ይህን ጥምረት ምዕራባውያኑ እና አውሮፓውያኑ ህጋዊ አድርገው እንዲቀበሉት ያልተገደበ አቅም መስጠት፤ የሚያፋፋ አቅም መመገብ፤ ዓለምን ሚስሊድ በማድረግ ዕውቅና ማስገኜት ነው ምኞቱ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ። እነዚህ ኃይሎች አቅሙን ካገኙለት ኦሮሙማ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊ የመሆን አቅሙ መሰረት ይይዛል በብልጽግናው የአንድ ነፍስ ምናባዊ ማጅክ። በመደመር አንድዮሽ የምናብ ምኞት የተማረከ ይመስለኛል ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ።

ስለሆነም ቦርዱ ተደማሪዎችን እንደ ምርጥ ዘር ተፎካካሪ አድርጎ ነው የሚያቸው። በአንጻሩ ዕውነተኛ ተፎካካሪዎችን በታመቀ መጫን የስሜን ፖለቲካም ደህና ሰንበት ዋና ተልዕኮው ይመስላል። አሁንም ይመስላል ነው ያልኩት „ነው“ አላልኩም። የስውሩ ሴራ ሚስጢር ይህ ነው እኔን እስከሚገባኝ። ለዚህ ተልዕኳ ደግሞ በሚገባ ብሄራዊ ምርጫ በመንፈሱ ልክ ተዋቅሯል።
  
በዚህ ውስጥ የህወሃት አቋም እና የደረጃ አቅም በሚመለከት ከጨዋታ ውጪ ማድረግ ይመስላል ትልሙ። እንግዲህ ኦነጋውያን ከራሩ ነው ይህም። የኦነግ ፖለቲካ አቋም የለሽ ስለሆነ የኃይል አሰላለፉን በአዲስ ሊበውዘው ይችላል። ብአዴን የአግር ሚዜ አድርጎ ኦህዴድን ለድል እንዳበቃም፤ ህወሃትን የኦነግን መንፈስ እግር ሚዜ አድርጎ ጢባ ጢቦሽ ሊጫወትባቸው ይችላል።

ይህ ማለት እያንዳንዱ የምርጫ ሂደት ትንፋሽ በትርታዋ ልክ ሊለዋወጥ፤ ሊሸጋሸግ፤ ሊሰባጠርም ይችላል። አሸናፊው ኃይል ህወሃትን አቅፎ የመምጣትም አዝማሚያም ሊኖረው ይችላል። ማሸነፍ በአቅም ልክ ነው። ኦነጋውያን እና ህወሃታውያን በመሠረታዊ የስትራቴጂ ልዩነት የላቸውም እና። ኦህዴድ እና ህወሃትም እንዲሁ። 

ኦህዴድን የሚደግፉ ተደማሪዎች ይህንም ጽላታቸው በማድረግ ነው የቀጠሮ ፓርቲዎች ሙሉ ድጋፋቸውን በመለገስ፤ በመቸር ላይ የሚገኙት። በዚህ ማህል ሾልኮ የሚቀረው ተረጋጩ፤ አንቋላጩ ግርባው ብአዴን ይሆናል። አሰር ላይ ይሆናል ደረጃው ወይንም ሽሁራር ላይ። የሚፈለገው እሱን በቀስተዳመናው ኢዜማ የመተካት ነው ሂደቱ። ይህ የአብይዝም ጉልህ መዳረሻ ነው። ከቶ ሚስጢር አወጣሁን ይሆን?

ፍዳው ህወሃትንም ኦነጋውያንንም በግልጽ የሚጻረሩ መንፈሶች ግን ያው ሲደርስ ቢታይም የፊት ለፊት ትኳኩስ ብርንዶ መከራዎች ይጠብቃቸዋል። „የጥላቻ ህጉም“ ለእነሱ የተረቀቀ ነው። ይህ ሳይታለም የተፈታ ነው። ከምርጫ በፊት መሸኜት ያለበት ነፍስም ካለ ግድ የለውም የፈርኦን መንፈስ ለሰኔል እና ቹቻ ያስረክበዋል።

የአማራ ሊሂቃን ቀድመው የተሸኙበት፤ ህይወታቸው የተረፈውም ከምርጫው ዋዜማ በፊት ቀድመው ለካቴና የተዳረጉበት ለዚኽው ለ2012 ዓ.ም ምርጫ ነው። ሌላው „እንዳያማም ጥራው፤ እንዳይበላም ግፋው“ በኢትዮጵያ ካሉት ሃይማኖቶች ሁሉ ባይተዋሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ነው። ተቋማቱን የማፈራረስ ሂደትም ቀጣዩ ትልም ነው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አንዱን ዘርፍ ተልዕኮ እዬሸፈነ ነው። ከዚህ ከ2012 ምርጫ በኋላ የምርጫ ጊዜ የሚሆነው በቋሚነት ነሃሴ ይሆናል። በ50በ60 ያረጠ ቲወሪ። ጾመ ፍልሰቲትን ከእርስቱ መንቀል - ለዘላለም። ይህ ድርሻ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በኽረ ተልዕኮ ነው። አብይዝም ህም - እም - ኦም ነውና። 
  
·        የኢትዮጵያ ህጻናት የተዋህዶ ልጆች በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ በግልጽ ዲስክርምኔሽን ሥር ወደቁ!

ፆመ ፍለሰቲት ከዓዋጅ አፆዋማት ውስጥ ብቸኛዋ የቅድስት ድንግል ማርያም ፆም ናት። ከነሃሴ 1 እስከ 16። አጭር፤ ተናፋቂ፤ ተወዳጅ፤ የማትጠገብ ፆም። ሁለተኛው ጾመ ጽጌ ነው። የፈቃድ ነው። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ስደትን አስቦ የሚካሄድ ነው። 

ከመሰከረም 26 ቀን እስከ ህዳር 6 ቀን ነው። ለውጽፍተ ወረቅ ልዩ ፍቅር ያላቸው፤ አቅም ያላቸው በፈቃዳቸው ወደው የሚፆሙት ነው። የበረከቱ ጉርሻም ዲል ያለ ነው። ስለ ውስጠ ይዘቱ ለሊቀ - ሊቃውነቱ አቨው ትቼ በህይወቱ ውስጥ እንዳለ አማኝ ግን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድን በዬኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ላይ ያወጀውን ግልጽ፣ ንጹህ ዲስክርምኔሽን እምለው ይኖረኛል።

ፆመ ፍልሰቲት የልጆች ፆም ናት። ዕድሜው ከ7 ዓመት ጀምሮ ያለ የቅድስት ተዋህዶ ሃይማኖት ልጅ የአፅዋማት የፊደል ገበታው ናት - ፆመ ፍልሰቲት። ልጆች ፆምን የሚጀምሩት በፍልሰቲት ነው። የፆም ሀሌታው ሀ። አሁን ይህ ትምህርት ቤት ነው የተዘጋው። በዚህ ፆም መላው ከ7 ዓመት ጀምሮ ያለ ልጅ ይፆማል፤ ይቆርባል፤ በሞራል ተኮትኩቶም ያድግበታል። ከ7 ዓመት በታች ያሉት ደግሞ ማለትም ከክርስትና ማግስት ጀምሮ እስከ ስድስት ዓመት ያሉት ደግሞ ቅዳሜ እና እሁድ ቅዳሴው ጥዋት ስለሆነ ይቆርቡበታል። 

ጡት የሚጠቡ ልጆች ቅዳሴ ከተገባበት ሰከንድ ጀምሮ ጡት ወይንም ወተት ይከለከላሉ።
ስለሆነም ይህን ኃላፊነት ከወላጅ ባለነሰ የክርስትና እናት እና አባት ብርቱ ጥረት የሚያደርጉበት የትውልድ ቀረጻ ፍጹም ልዩ ተቋም ነው። አቤቶ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ይህን ዝክረ ትውፊት ነው በድፍረት የናደው፤ በምን ታመጣላችሁ የጣሰው፤ በማን አለብኝነት የጠቀጠቀው - የረጋገጠውም።

 በቀጥታ ዲስክርምኒሸኑ በቅድስት ኦርቶዶክ ተዋህዶ ጡት ከሚጠቡት ጀምሮ ያሉ ህጻናት፤ ልጆችም ላይ ነው ያካሄደው። አንድ ኢትዮጵያዊ ብሄራዊ ተቋም የአገርን ትውፊት፤ ብሄራዊ ታሪክ፤ አገራዊ ትሩፋት በማስጠበቅ ትውልድን መቅረጽ ሲገባው ነገር ግን ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ተጻሮ በመቆም ተተኪ መንፈሷን እንዲሸማቀቅ ቀዝቃዛ ጦርነት አውጆባታል - በዬኔታዋ።

·        የሀሌታው ሀ የፆም መቅድመ - ሥርዓታዊ ሂደት በልጆች ጽኑ መንፈሳዊ ህይወት ላይ። 

በዚህ በፍልስታ ወቅት እንደ አባት አደሩ እያንዳንዱ ልጅ ለቁርባን ከመሄዱ በፊት፤ እያንዳንዳንዱ ወላጅ እና ክርስትና አባት፤ እና እናት በነፍስ ወከፍ ብርቱ ጥንቃቄ እና ጥበቃ ለልጆች ያደርጋሉ። የልጆች ንጽህናቸው ይጠበቃል። የአንገት ልብስ ይዘጋጅላቸዋል። አጣፍቶ አደግድጎ መልበስንም ይመሩበታል። በቁመታቸው ልክ ከፈትል የተሰራ ነጠላ ይዘጋጅላቸዋል።

ለቁርባን የተሰናዱ ልጆች ተሳስተው እውሃ እንዳይጠጡ፤ ምግብ እንዳይቀምሱ በተአቅቦ ክትትል ሙሉ ቀን ይደረጋል። ለቁርባን ሲሄዱ የሚለብሱት ልብስ በንጽህና ይሰናዳል። ቆርበው ሲወጡ የሚቀምሱት መክለፍት ቀረጢት ተሰፍቶ ከአንገታቸው ላይ ተደርጎ ይሰናዳላቸዋል። ወደ ቁርባን ሲሄዱ መክለፈቱን ከወላጆቻቸው እቃ ጋር አደራ ሰጥተው ይሄዳሉ። ሲቆርቡ ወላጆች ይዘዋቸው ነው ወደ ቅዱስ ቁርባኑ የሚያቀርቧቸው። 

በተለይ ክርስትና ከተነሱ ህጻናት ጀምሮ እስከ 14 ዓመት ላሉ ልጆች። ቆርበው ሲወጡ ልጆች መክለፈት እስኪቀምሱ ድረስ እንዳይናገሩ ይጠብቋዋቸዋል። ከዛ ወላጆች ተከታትለው መክለፉትን ያቀምሷዋቸዋል። ከቁርባን በፊት ከነበረው በላይ ከቅዱስ ቁርባን በኋላ ሰፊ ጥበቃ እና ጥንቃቄ ለልጆች ይደርግላቸዋል ወላጆቻቸው።

ከቤተክርስትያን መልስ ቁርባን የተቀበሉ ልጆች ውጭ ወጥተው እንዲጫወቱ አይፈቀደም። እሚከለከሉ ብዙ ነገሮችም አሉ። ህፃናት ከሆኑ ሲተኙ ወላጆች ልጆች እንቅልፋቸውን ጨርሰው እስኪነሱ አጠገባቸው ሆነው ይጠብቋቸዋል። 

ይህን ሃላፊነት ወላጆች እንዳይወጡ በተወጠረው ነሃሴ ወር ደግሞ ወላጆች በውጥረት፤ በመንፈስ ብክነት እንዲሆኑ አቤቶ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ወቅቱን በውጥረት እንዲናጥ አድርጎታል። መንፈስን በማባከን።
ልጆችም ቅዱስ ቁርባን የመቀበል ጉጉታቸው ካለ አግባብ ተከርችሟል ለ50በ60 ድንብልብም ምናብ። ልጆች ወላጆቻቸውን አልባ መቁረብ አይፈቀድላቸውም። በፍጹም! ይህን እንዴት ያዬዋል የዳኛ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እናታዊ ህሊና? ይህ የፍትህ ጥሰት እስከ አራስ ልጅ ድረሰ የተራዘመ ዴስክርምኔሽን እንደ እናት እንዴት ታዬዋለች የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ? ማለቴ በቀደመው ሰብዕናዋ ውስጥ ካለች። አገር መምራት እኮ የገበጣ ጨዋታ አይደለም።

መኖርን የሚወስን ነው ምርጫ። ኢትዮጵያዊነት ማንበብ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያዊነት ቀለም የሌለው እስክርቢቶ አይደለም። ፆመ ፍልሰቲት አንዱ ኢትዮጵያዊ ቀለም ነው። ይህን መሰል ህብራዊ፤ ሞራላዊ ዕሴታዊ ቅንብር አይንህ እንዳላይ ነው የተባለው። አንባቢም ተነባቢም ቢያገኝ ኢትዮጵያዊነት በዚህ ውስጥም አለ። በዚህ አቅም ደረጃዋ የክብርት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አደብ ያለው ኢትዮጵያዊነት የት ላይ እንዲመደብ ትፈቀድ ይሆን?!

·        ማዕዶተ ፍልሰቲት።

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ማታ ከምኝታ በፊት ከ7 ዓመት ጀምሮ እንደዬቤተሰቡ ሪቷል ይለያያል በእኛ ቤተሰብ ግን ከምኝታ በፊት ምህላ አለ። „ ኦ! ማርያም እለምንሻለሁ ባርያሽ እስኪ አንድ ጊዜ ስሚኝ ቀርበሽ ባጠገቤ ቁመሽ፤ ጽኑ ጉዳይ አለኝ ለአንቺ እምነግርሽ ወዘተ …“ ጻድቃኑ፤ ሰማዕታቱ ሁሉ እዬተነሱ በወል ቤተሰቡ መሬት ላይ ተቀምጦ ምህላውን በተመሰጠ ምስጋና፤ ልመና እጅግ ሰማያዊ በሆነ መንፈስ ህብረ - ዜማ ያዜማል። ከምህላ በኋላ ውጭ መውጣት አይፈቀድም። ይህ እንግዲህ ትውፊት ነው።

እኔ መሬትን ስትረግጧት ተጠንቅቃችሁ ተራመዱ፤ አትደብድቧት ከሚል ቤተስብ ስለወጣሁኝ በዚህ መልክ ነበር ተቀርጬ ያደግኩት፤ ሞራሌም የተገነባው በዚህ ትውፊት ልክ ነው። ይህ ሁሉ ነው አሁን በድፍረት ጥሰት የተፈጸመበት። 

የ16 ቀኑ ሱባኤው አንድም ቀን አይሰተጓጎልም። ውግዘትም ነው። ይህን የለመዱ ልጆች ወላጆቻቸው በምርጫ ዝግጅት የተመደቡ ሺዎች፤ ለምርጫ  በእጩነትም ሆነ በመራጭነትም መሳተፍ የሚፈልጉ ሚሊዮኖች ሁሉ ግዞት ተፈረደባቸው - እግዚብሄር ይይለት ቅንጡው እና ቀለጤው የብሄራዊ የምርጫ ቦርድ። አሜን!

ከነሃሴ አንድ ጀምሮ የምርጫ መሰናዶ የሚከወንበት በመሆኑ መንፈስን ክፉኛ ያባትላል። ይወጥራል። መረጋጋትን ይቀማል። በዚህ ውስጥ የልጆች የፆም ነፍስም ይታወካል። „የምረጡኝ ዘመቻ ጊዜ ከሚዚያ 27 ቀን እስከ ነሃሴ 05 ቀን“ ከመሰናዶው በተጨማሪም የምረጡኝ ዘመቻ እስከ ነሃሴ 5 ስለሆነ በዚህ ወቅት ህዝብ መሰብሰብ ሊኖርበት ነው። ልጆች ምን ይሁኑ?!

የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን እነሱም ፆሚዎች ናቸው። በሌላ በኩል የልጆቻቸው ከፍተኛ ትውልዳዊ ግዙፍ ኃላፊነት አለባቸው። የክርስትና አባትም እናትም እንዲሁ። ይህን ምስቅልቅል እንዲል ነው አጤ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የኦሮሙማን ሙሉ ፍላጎት ለማሟላት ይህን ደንቀራ ፕላን ያወጣው።

 በሌላ በኩል የድምጽ መስጫ ቀን ነሃሴ 10 - 11  ቀን 2012 ዓም. በዚህ ቀን ልጆች መቁረብ ቢፈልጉ ወላጆች ሊተባበሯቸው አይችሉም። በወላጆች እና በልጆች መሃከል ከፍተኛ የሆነ ጦርነት ይነሳል። ቤተሰብ መታወክ ለምርጫ ቦርድ ኬኩ ነው በዚህ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት። አስከ ቤት ድረስ የዘለቀ ልጆችን የጨመረ የሰላም ህውከት። ልጆች ኢትዮጵያዊ ዜጎች አይደሉምን? አገር ከአለ ህፃናት/ ካለ ታዳጊ ወጣቶች/ ካለ ወጣቶች ብሄራዊ መንፈስ አደራዋን ምን ላይ ሊያስቀምጠው ያስባል ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ? ቁምሳጥን ውስጥ? እግዚኦ!

·        እንቀጥል።
  
… ቅድመ ውጤት ይፋ የሚሆንበት ጊዜ ነሃሴ 11 ቀን ነሃሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. እኝነህ ቀናትም ቢሆን ምርጫ የህልውናም ጉዳይ ነውና እና በሱባኤ ወቅት የመንፈስ ህውከትን ብቻ ሳይሆን የሥነ - ልቦና ድቀትንም ያስከትላል። ውጥረት። ለዚህም የመጀመሪያ ኢላማ የተደረጉት የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ህጻናት እና ልጆች የሆኑት። መሠረቱን ሥር አልባ ለማድረግ። በዚህ ሂደት አድሏዊነት ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ በልጆች የቀጣይ የሃይማኖት ህይወት ፈጽሟል። ዲስክርምኔሽንም ነው።

የቦርዱ የተረጋገጠ ውጤት ማሳወቂያ ጊዜ ነሃሴ 11  ቀን ነሃሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ይህን ምን ሊፈጠር እንደሚችል አይታወቅም፤ አባቱን፤ እናቱን ሊያጣ ይችላል አንድ ልጅ። „ምርጫ ኮንስኮይንስ“ አለው ተብለናል።  ከላይ ያነሳሁት „መሰዋትም ምርጫም“ ይኖራል የጠሚር አብይ አህመድ ንግግር ሲታሰብ ኮሶ ይሆናል ሁለመናው። ዋዜማውም ነው ለአዲስ ዓመት፤ ለነገሩ አላዛሯ ኢትዮጵያ ምን አዲስ ዓመት በሰላም አክብራ ስታውቅ ነውና?!

ስለዚህም ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለአፓርታይድም፤ ለዲስክርምኔሽንም ቀዳሚ ተጠቂ ያደረገው ሃይማኖቴን ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን ነው። መፈተኛ አደረገው። ሃይማኖት እንዴት እንደሚረጋገጥም መለማመጃ አደረገው። ሁልጊዜ እኔ እምለው እኔ ገና ላልተፈጠሩት፤ በሃሳብም ላልተጸነሱት ከ20/25 ዓመት በኋላም ስለሚፈጠሩት ልጆች ነው እማስበው፤ እምሞግተው እምለውም ለዚህ ነው።

ልጆች ባለቤት የላቸውም - በኢትዮጵያ። ለዛውም እሷ እስር ቤት ሆና ልጇ ታዳጊዋ ሃሌ እንዴት እንዳደገች ለምታውቀው ለክብርት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ልጅ ማለት በአፋኝ ሥርዓት ውስጥ እንዴት እንደሚያድግ ተቀጥታበት፤ አሁን እሷ ነጥላ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ልጆች እንዲጠቁ ተባባሪ እዬሆነች መሆኑን በአስተውሎት ልትመረምረው ይገባል። ይህን በጥልቀት ካላዬችው ይሄው ጽፌዋለሁኝ። መርምራ አንድ ውሳኔ ትድረስበት። ታሪክ እያደፈረሰች መሆኑንም ልታውቅ ይገባታል። ጉዲት በምን እንደምትነሳም ይጠፋታል ብዬ አላስብም።

እኔ ገና ላልተወለዱትም ያሳስቡኛል እምለው እንዲህ ዓይነት ጎግ - ማንጉግ ዘመኖች ስለሚያሰፈሩኝ ነው። አሁን ይህን እኔ የሚያሰፈራኝን ጎግ - ማንጉግ ዘመን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እያጨው ነው። በፍጹም እንደዚህ አይነት የሻከረ ኃላፊነት ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መንፈስ አላሰብኩትም ነበር። ሰብሳቢዋ ወ/ር ብርቱካን ሚደቅሳ ሆነ አማካሪያዋ ወ/ት ሶልያና ሽመልስን በዚህ ሰነፍ ውሳኔ ውስጥ አገኛቸዋለሁኝ ብዬ አላሰብኩም ነበር። አሁን ግን መኖር ደጉ ይፋዊ ጦርነቱ ተጀምሯል።

·        ፆመ ፍልሰቲት የሱባኤ ፆም ናት። 

ፆመ ፍልሰቲት ልዩ የሚያደርጋት ብጡሉ አመክንዮ ደግሞ ፆመ ፍልሰቲት የሱባኤ ፆም መሆኗ ነው። ጋብቻቸውን በቅዱስ ቁርባን ለማድረግ የወሰኑ የንሥኃ ፆማቸውን ብዙውን ጊዜ ፆመ ፍልሰቲትን ይመርጣሉ። በሌላ በኩል የዓመት እረፍት ወስደውም ሱባኤ የሚይዙ ጥሬ ቆርጥመው መሬት የሚተኙ ሺዎች የሃይማኖቱ ልጆች አሉ። በእነዚህ ቀናት ወስጥ ጭራሽ ከሰው ጋር የማይገናኙም ይኖራሉ። ወደ ገዳምም የሚሄዱ ይኖራሉ።

አሁን ምርጫ ቦርድ ፈንግጡት የራሳችሁ ጉዳይ ነው፤ ዜጎችም አያደላችሁም፤ እናንተ ብትመርጡም ባትመርጡም ጉዳያችን አይደለም እያላቸው ነው። እናንተን አይመለከተኝም እዬተባለ ነው። እራሱ የምርጫውን ዜና ሂደቱን ማዳመጥ አይችሉም ብዙዎቹ። ይህም ሌላ የመብት ጥሰት ነው። የምርጫ ዜና የመኖር ጉዳይ ነው። 

ስለምን ነው ለዜናው ሩቅ እንዲሆኑ የሚበዬንባቸው ለሱባኤተኞች? እነዚህ ዜጎች ሱባኤ ላይ ስለሚሆኑ ከብዙ ነገር ይታቀባሉ። ራዲዮን፤ ቴሌቪዥን፤ ስልክ አቋርጠው ነው ሱባኤ የሚያዙት። ሺዎችም ናቸው። የእመቤታችን ፆም ቃላት አይገልጸውም ምን ያህል እንደሚናፈቅ፤ ምን ያህልም እንደሚወደድ። ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ግን የግለሰብ ቤት ሄዶ የመጎብኜት ያህል ብጣቂ ክብር እንኳን አልሰጠውም። አዝናለሁኝ። እርግማንም ስለሆነ ጉዲትን እንዲህ መናፈቅ። 

ከዚህም በላይ እራሳቸውም ቅዱስ ቁርባን የሚቀበሉ ሚሊዮኖች አዋቂዎችም ይኖራሉ። ቅዱስ ቁርባን ሲቀበሉት ስንብቾውን በጣም በሰከነ መንፈስ ነው ዕለቱ የሚጠበቀው። ጥሞና ይሻል። ከብዙ ነገር ተቆጥቦ ነው የሚከወነው። የአርምሞ ጊዜ የሚፈልጉ ተደሟዊ አመክንዮዎች ጥልቅ ናቸው። የክርስቶስ ሥጋ እና ደም ከህሊና በላይ የገዘፈ ጉዳይ ነው። ይህም ብቻ አይደለም ፆሙን ማቋረጥ አይፈቀድም። ፍጽሞ።

ሞት  ወይንም የከፋ ህመም፤ ወይንም ነፍሰጡር ሴቶች ካልሆኑ በስተቀር ፆሙ አይቋረጥም:፡ ይህም ብቻ አይደለም ጥዋት የጸሎት ሥርዓት አለ በቤተ ክርስትያን፤ ከረፋድ ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት የቤተ ክርስትያን የቅዳሴ ሥርዓታዊ ሂደት፤ እንደገናም ምሽት ስብከተ ወንጌል ፍልሰቲትን በሚመለከት በዬአጥቢያ አድባራት ይኖራል። ይህ ሁሉ ነው ይጣስ የሚለው ቅንጡው ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ። ፍርድ ከእዮር ይጠበቃል።

ሌላም የጎንደር ብቻ ባህላዊ ዕሴትም አለ። „አድርሽኝ“ ይባላል። የእመቤቴ ወዳጆች ሙሴ መርጠው በቋሚነት ከአንድ ሰው ቤት ማታውን ደግሞ የአብሮነት የሱባኤ ጊዜ ይኖራቸዋል። ፆሙ ሲፈታ በጋራ እርድ ጥለው አብረው ይፈስካሉ። 

ልዩ የሆነ የአብሮነት ትውፊታዊ ወቅት ነው። ሳቢ፣ የማይጠገብና ተናፋቂ ጊዜ ነው። ይህ ማለት ከጥዋቱ ጀምሮ እሰከ ምሽት ድረስ ለቅድስት ድንግል ማርያም መታሰቢያ የተሰጠ መንፈስ ቅዱስ የሚረብበት ጊዜ ነው ወርኃ ነሃሴ። ይህን የሺሕ ዓመታት ትውፊት ነው የጣሰው፤ የሰረዘው፤ የዳጠው አ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ። ከሥሩ ለመንቀልም ነው የተሰናዳው።

ለ2012 ዓ.ም ብቻ ሳይሆን በዬ5 ዓመቱ በዙር ለሚመጣ ምርጫ ቋሚ ወርህ ነው ታስቦ የተሰናዳው። ድንግል እንደ እናትነቷ በእሷ ሳይቀር የታቀደውን ጸረ ማርያም ተልዕኮ ልክ እንዲይዝ ለልጇ ለወላጇ አቤት የምትልበት ሁኔታ ነው ያለው። ታቅዶ፤ ተሰልቶ በቀመር ነው እዬተከወነ ያለው። አብይዝም ውስጠ ወይራው እንዲህ ነው። በዚህ እንኳን አደረሳችሁ በዚህ ደግሞ ከእርስት ነቀለ።

·        ነዝናዛው ነሃሴ።

ነሃሴ ጨቅጫቃ ነው። አያባራም ያው ሲያለቅስ ውሎ ያድራል። በዚህ ወቅት ነው የምርጫ ክንውን የተሰናዳው። እራሱ እያንዳንዱ ዜጋ ጥላ ይኖረዋል ተብሎ አይገመትም። ከአንድ ቤት ለምርጫ የደረሱ 5 ሰዎች ቢኖሩ አምስት ጥላ ላይኖር ይችላል። የአገርን ተጨባጭ ሁኔታም ያላገናዘበ ውሳኔ ነው።

እዚህ የሰለጠነው ዓለም አይደለም ክረምት በጋ ስንዱዎች ናቸው። ሃብቱም አለ ጥበቡንም ሰጥቷቸዋል። አንድ ጊዜ የጓደኛ ልጅ የትምህርት ቤት ትዕይንት ኗሯት ተጋብዤ ስሄድ ሜዳ ላይ ስለነበር ሥርዓቱ ዝናብ ጣለ። ለዛ ሁሉ ሺህ ህዝብ በነፍስ ወከፍ ወዲያው የዝናብ ልብስ ታደለ። ለነገሩ ክብርት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የአውሮፓ አገሮችን በተለይም የስካንድንብያ፤ እና እንደ ጀርመን፤ ሲዊዝን ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ የምትመራ ነው የምትመስለው መግለጫዋን ስትሰጥ ከውስጥ ሆኖ ለሚያዳምጣት።

ምን አለብት ምናባዊው መሪዋ ይህን ምናባዊ ትዕይንት አሻግርውላት ይሆናል። በዛን ቀን በነፍስ ወከፍ ለሚሊዮኖች በነፃ የዝናብ ልብስ በምናቧ አሰናድታም ሊሆን ይችላል። ይህ ጉዳይ የሌሎችን የሃይማኖት አባላት እና ሃይማኖት የሌላቸውንም የሚመለከት ችግር ነው። የት ይሆን የሚኖሩት ነገረ ምርጫ ቦርዶች? ጁቢተር፤ ሳተርን፤ ኡራኖስ? የአገራቸውን ተጨባጭ ሁኔታ፤ የአገራቸውን የአዬር ሁኔታ፤ የአገራቸውን የኢኮኖሚ አቅም፤ የአገራቸውን ዕሴታዊ ትውፊት ገና ፊደል መቁጠር ያለባቸው ይመስለኛል። የሉም በውስጡ። ውሳኔውን መዝኑት ክረምት ላይ?! ህም! 

·        ገበሬውና ነሃሴ አንገት እና እራስ ናቸው።

ግን ብሄራዊ ብርጫ ቦርድ ኢትዮጵ የገበሬ አገር መሆኗንስ ያውቃልን? ነው ወይንስ ከተማ ብቻ ይሆን ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት? ይህ እኮ የነፍስ ውጪ ግቢ የሥራ ወቅት ነው ወርሃ ነሃሴ ለኢትዮጵያ ገበሬ። ይህም ብቻ አይደለም እኔ የገበሬ አደራጅም ነበርኩኝ። የጉዞ ዳጡን፤ የወንዝ ሙላቱን አውቀዋለሁኝ። ብዙ ወንዞችም ይሞላሉ። ህዳር ሳይታጠን ቤተሰብ አይገናኝም። ትንንሽ ወንዞች እራሱ ቲፍ ነው የሚሉት። ጎርፉ እራሱ አያንቀሳቅስም። ለነገሩ በዬትኛው የህይወት ተመክሮ ኢትዮጵያ ትተርጎም?!

ያው ቅንጡው ምርጫ ቦርድ ስለመጪው ዘመን የምርት ጉዳይም አያገባውም ወይንም ግድ አይሰጠውም፤ ከዚህም በላይ በከተማ የሚፈልጋቸው ሦስት የድርጅት ነፍሶች ካሸነፉ ገበሬው እንደሌለ ቁጠሩልን እያለ ነው። ሚዛን አልቦሽ ገዳዳ ውስኔ። ግርድፍም።

ገበሬው ጥላም መጠለያም ጭራሽ የለውም። ሜዳ ላይ ደግሞ ጨቅጫቃው ነሃሴ ዶፉን ይጥለዋል፤ ወረቀቱም አብሮ ይታጠባል። ኮሮጆውም የውሃ ሙላት ያሰናብተዋል። በተከታታይ ቀናት ያላበራ በረድም ወጀብም ሊኖር ይችላል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የኋላቀርነቱ መንስኤ የተፈጥሮ ጥገኛ ስለሆነ ነው። በዚህም ስሌት ሲታይ ሽርክት ውሳኔ ነው። እያለ የሌለ ቦርድ። ዕብንነት!

ለምረጡኝ ቅስቀሳም ከነሃሴ አንድ ቀን ጀምሮ እስከ አምስት የት ላይ ሊሰበሰብ ህዝብ? ላዩ ውሃ ታቹ ውሃ እኮ ነው? ገጠር ላይ አዳራሽ የለም። ለምርጫ አስፈጻሚ የሚሄዱትም ብዙ መንገዶችን ሊቋቋሙት የማይችሉ ክረምት ሰጥ አደጋዎች ሊገጥማቸው ይችላል። ነው በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምናብ በአራት ወራት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች አስፓልት ይዘረጋል የሚል ግምት ሊኖረው ነውን?

ከዚህም በላይ ገበሬውም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አማንያንም የሆኑ አሉ። ገጠር እኔ እስከማውቀው ድረስ እስልምና፤ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፤ እና ቤተ - እስራኤላዊ እምነቶች ነው ያሉት።
ለተዋህዶ ልጆች በዛች በተናፋቂው ፆመ ፍልሰቲት ይህ መታቀዱ በገበሬው ዕምነት ላይም ተጨማሪ የግብርና መባተሉ በላይ ሌላ ጫናም ነው። 

ያው ገበሬው በ27 ዓመት የህወሃት መራሹ ዘመን ከፖለቲካ የተገለለበት ስለሆነ መመረጥ ብሎ ነገር ትውር እንደማይልለት ስለሚታወቅ። ያለው የመምረጥ መብት ብቻ ነው። ግንጥል ጌጥ ፖለቲካ። አሱም አሁን ከእርሻ ወቅት፤ እና ከፆም ጋር ሦስተኛ ደግሞ ሌላ የመንፈስ ውጥረት ታክሎለታል። አዘኔታ የሚባል ነገር የለም። ማስተዋልም ለስደት። ኢትዮጵያዊነት እኮ ቁሳዊነት አይደለም። ኢትዮጵያዊነት ህይወቱን መኖር ይጠይቃል።
  
·        የተሳትፎ አድማስ።

በዚህ ምርጫ ሂደት በታዛቢነት፤ በአስፈጻሚነት፤ በሎጅስቲክ ድጋፍ ሰጪነት፤ በመራጭነት፤ በተመራጭነት እጩነት ሚሊዮኖች ይሳተፋሉ። ምርጫ ህዝብ አሳታፊ ዓውድ ነው። አዋቂዎች፤ ወጣቶች፤ ጎልማሶች፤ አዛውንቶች የሚሳተፉበት ወላዊ ማዕዶት ነው ምርጫ። ነገር ግን  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማንያን ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት አማንያን የፆመ ፍልሰቲት የበረከቷ ናፋቂዎች ናቸው። የጥሞና ጊዜያቸው ነው። ነገር ግን በምርጫ ብቻ እንዲያተኩሩ የሃይማኖታቸውን ህገ - ሥርዓት ተፃረው እንዲቆሙ፤ መንፈሳቸው በሌላ ጉዳይ እንዲጠመድ ወይንም እንዲብከነከን፤ ህሊናቸው እንዲሰረቅ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እዬተጫናቸው ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ራዕያቸውን እዬደረመሰው ነው። ጥቃቱ አካላዊ ሳይሆን ሥነ - ልቦናዊ እና መንፈሳዊውም።
  
ከከተማ ወደ ገጠር ለዘመቻ የሚሄዱት በአነሰ ግምት አንድ ሳምንት ያስፈልጋቸዋል። አንድ ሳምንት ሙሉ ከሱባኤ ይሰተጓጎላሉ። አሁን ምርጫ ቦርድ ለቅድስት ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ያቀረበው ምርጫ ወይ ሃይማኖትህን ወይ ኢ- አማንያነትህን ምረጥ ዓይነት ነው። ግፍ ነው! በላህሰብነትም ነው! ፈርኦናዊነትም ነው! አርዮሳዊነትም ነው! በቀል ያለበት ይመስላል የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ላይ።

ቅኖና ዶግማዋን ለማክሰም ተሰናድቷል። ለ27 ዓመት የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን በፈለገው ዓይነት ሙያ ዘርፍ የተገለሉበት ሚስጢር መግለጫው በዘመነ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት የበለጠ አቅም ሊሰጥ ይሆን ይህ የምርጫ ቀናት ሰሌዳ የተሰናዳው እላለሁኝ ብቻዬን። እኔ እስከዚህ ድረስ ነው እምሄደው።

አቅም ያለው፤ የፖለቲካ ሥልጣን ያለው ተቆርቋሪ ልጅ በመጥፋቱ ዛሬ በቅድስት ኦርቶዶክስ ካቴድራል ላይ በጥምቀት ባዕል ያዬነው ድፍረት የዚህ ሁሉ ጥምር ወላዊ ውሳኔ እንደሆነ ይሰማኛል። ቀጧትም። ትቢያ ትለብስ ዘንድ፤ አንገቷትን ትደፋ ዘንድ፤ ጥገኝነት እና ባይተዋርነት ይሰማት ዘንድም ተረባረቡባት - በዬኔታዋ። ሰማይ እና መሬት የፈጠረው አምላክ ይህን ይፍረደው። አሜን!

አሁንም እማሳስበው ውጭ የሚኖረው የቅድስቷ ልጆች የዚህ የብሄራዊ የምርጫ ቦርድን ሸፍጥ ማገለጥ ይኖርባቸዋል። አጭር እና ግልጽ የሆነ ፒቲሽንም ማሰባሰብም ያስፈልግ ይመስለኛል። ተዋህዶ ጥቃት የሚያወጣ ልጅ ካላት ወይንም ከኖራት። በማህበራዊ ሚዲያም ሰፊ ዘመቻ ማድረግ ይገባል። እርግጥ ነው ቁንጥንጡ የኦሮሙማ ፖለቲካ በላይ በላይ በሚጭነው የሴራ እና የደባ ቡፌ ሳይዘናጉ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ዘመቻ ማድርግ ይገባል። የሚያስፈልገን ዜጋን እኩል የሚያደርግ የሥርዓት ለውጥ ነው።  

·        ዴሞክራሲ።

ዴሞክራሲን ባገኜችው ዕድል ወ/ት ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ እንዲህ እያሳዬችን ነው። አማራን ያገለለ የተጫነ ስለመሆኑ ከሰኔ ግርግር ጀምሮ ተያይዞ በአብን ላይ ያለውን ሁኔታ አስተውለናል። ሞግታ ማሸነፍ ስትችል። አሁን ደግሞ በ2012 ዓም የምርጫ ሂደት ከአራስ ህፃናት ጀምሮ ያሉ የትውልዱ ቤተኞች በሃይማኖታቸው ላይ መብታቸው መዳጥን እንዲማሩት ተቋም ተከፍቶላቸዋል። ዴሞክራሲ?
 
ካህናት፤ ዲያቆናት፤ የቤተ ክርስትያን ሊቀ - ሊቃውንታት፤ መርጌታዎች፤ የወንጌል መምህራን፤ የቅኔ - የድጓ - የፆመ ድጓ - የንባብ፤ የመጽሐፍ - የአቋቋም - የዜማ መምህራን እና ዘማርያን ሁሉ ይህ ፆም ልዩቸው ነው። ብዙ ሃይማኖታዊ ሚስጢራት በህብራዊነት የሚከወኑበትም ነው። በዚህ መንፈሳዊ ረቂቅ ወቅተ በረድማ የቂም በቀል ዶፍ ነው ያወረደው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ። ነሃሴ ፈጽሞ ሊታሰብ የማይገባ ነበር። 

ታስቦበት ሆን ተብሎ ነው የታቀደው። ሲመከርበት ባጅቷል። በግልጽ ኦርቶዶክስን የሰረዘ ዴሊት ያደረገ የምርጫ ንድፍ ነው። ካህናት እና ዲያቆናት ከአውዱ ውጭ ነው የሚሆኑት። የአገልግሎት ወቅታቸው ነውና ፆመ ፍልሰቲት። አይደራደሩበትም። ኢትዮጵያ ምን ያህል ካህናት ምን ያህልስ ዲያቆናት አሏት? እነዚህ ሁሉ ለብሄራዊ ምርጫ እንደ ዜጋ አይቆጠሩም።

·        በምርጫ ተሳትፎ ላይ ስለሚሰማሩት አማንያን።

በምርጫ በቀዳሚነት የሚሳተፉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች ከፆሙ ዋዜማ ጀምሮ ነው ቀልባቸውን የሚያጡት። የህሊና መቅድመ መሳናዷቸው ሁሉ አስቀድሞ እንዲሸረሸር ታልሟል። አጀንዳቸው ምርጫና ምርጫ ብቻ እንዲሆን ነው የታቀደው። መንፈሳዊ ህይወታቸው የሚያሰገኘው በረከትም እንዲተን ነው የታወጀው። አቅል መሰወር።  

ስለሆነም አማንያኑ ግማሽ ልቦና ይኖራቸዋል። በግማሽ ልቦና ውስጥ ደግሞ የመንፈስ መመሳቀል ይኖራል። በመንፈስ መመሳቀል ደግሞ የሥነ - ልቦና አለመረጋገት ወይንም ስክነት ማነስ ሊፈጠር ይችላል። ፆመ ፍልሰቲትን ልተዋት ቢሉ እንኳን የምርጫ ቦርድ የሚሰጣቸውም ሙሉ ኃላፊነት የመወጣት አቅማቸው ይሰላል። 

ስለዚህ ግድፈት የጠናወተው ይሆናል የተልዕኳቸው ሰቅ።  ኃላፊነት ሳይበታተኑ፤ ሳይብሰከሰኩ ጫና ሳይኖርበት ካልሆነ ስኬቱ እሮ ይሆናል። ወይንም ተባደግ።* ዓለም ለሚታደምበት የምርጫ ውጤት እንዲህ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ በሆነ አመራር ደግሞ ያው እንደ ለመደብን የኋላቀር አገሮች ምርጫ አሽሙርን ተሸካሚ ያደርገናል። ይህም እንደ ዜጋ የሚያም ጉዳይ ነው።

·        ርገት።

ዜጋን በመኖር ውስጥ አለማስብ የአስተዳደር ብልሹነት መግለጫው ነው። ዜጋን መኖሩን የሚቀሙ ማንኛውቸም እርምጃዎች ተፈጥሮን የሚጥሱ ህግ አልባ መንገዶች ናቸው። በህግ አልባ መንገዶች ትውልድን በሞራል ለማነጽ አቀበት ነው። ማናቸውም በብሄራዊ ደረጃ የሚታቀዱ ትልሞች ቀጣይ ትውልድን አስቦ ሊሆን ይገባል። ትውልድ አልባ አገር አይኖርም። ትውልድ ደግሞ እንደ ቦንዳ ጨርቅ ማከፋፈያ ላይ አይሸመትም አይቀናም።

ህዝባዊ ኃላፊነት ሰውን አክብሮ መነሳት ይገባዋል። ሰውን በመፍጠር እረገድ ወሳኝ በሆነው የመኖር ትውፊቶች ላይ እኩላዊ ሂደቶችን መከተል ተተኪን ለማፍረት የሚደረገውን ጉዞ ያሳልጠዋል። 21ኛው ምዕተ ዓመት የአትኩሮት አቅጣጫ ሰብዐዊነት ነው። ከዚህ ዓውድ የወጣ ማናቸውም እርምጃ ግድፈት እያዋለደ ትውልድ የማባከኑን ሂደት አቅም ይሰጠዋል። ይህ ደግሞ ገዳዳ መንገድ ነው።

በሁሉም መስክ የትልሞች ስክነት ትውልድን በመገንባት ላይ ማተኮር ይገባቸዋል። ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆቿን የምታሰለጥንበት አንዱ መንገዷ አፅዋማትን በጥዋቱ ፊደል ገበታዋ ማድረጓ ነው። አባቶቻችን ፍልሰቲትን አጭር እና የእመቤታችን ሲያደርጉ እናት ለልጇ መቅረቧን፤ ልጆችም ጾሙ ተራዝሞ እንዳይሰለቹም አቅማቸውን መጥነው፤ የመለማመጃ ድልድይ ይሆን ዘንድ ነው።

ይህ ፆመ ፍልሰቲት ጥልቅና ብዙ ሚስጢራዊ መስተጋብሮች ተማክለው የሚገኙበት የትውልድ ሞራላዊ ዕሴት ነው። አዲስ ትውልድም ከቡድናዊ ህግ ጣሽነት ወጥቶ ሥርዓታዊ ሆኖ ተኮትኩቶ ያድግ ዘንድ በፈቀደ እግዚአብሄር ኃይል የተሰናዳ እራስን በመቅጣት፤ እራስን በመቆጠብ ጠንክሮ የመውጣትም ብልህነት ነው። ይህን ሰፊ በሆነ ልቅና እና ልዕልና የታወጀን ብሄራዊ አፆዋማትን ለማፋለስ ጥሶ መነሳት በቀጥታ ዲስክርምኔሽን ነው በትውልድ ላይ የተካሄደው።

ጉዳዩ በአዲሱ የትውልድ ተቋማዊ እነጻ ላይ ሲሆን ቀጣይ የኢትዮጵያ ተስፋ ምክነትን ያውጃል። ፆመ ፍልሰቲት የትውልድ ተቋም ናት። የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አንዱ የማንነት መገለጫዋ ነው። የኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን ከቅድስት ድንግል ማርያም በረከት፤ ረድኤት መነጠል ወንጀልም ብቻ ሳይሆን ኃጢያትም ነው። ከእመቤቴ ጋር ተጣልቶ ብሄራዊ ምርጫን ማወጅ ማዕት አውርድ ብሎ መሬትን መደብደብም ነው።

ስለሆነም ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ጉዳዩን በአርምሞ፤ በጥሞና እና ኢትዮጵያዊ በሆነ ማስተዋል ተመልክቶ፤ የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ብሄራዊ መብትም ጉዳዩ እንደሆነ በሚሰጠው ውሳኔ ይታያል። ስለዚህም ለችግሩ በኽራዊነት መፍትሄ ይሰጥበት ዘመንድ አቤቱታዬን አቅርቤያለሁኝ በአክብሮት። የሰማዩ ዳኛም መልካሙን አስመልክቶ ውሳኔው ያስለውጥ ዘንድ ዝቅ ብዬ አልምነዋለሁኝ።

·       

·        መፍቻ

1) እንሶስላ እና ጉርሽጥ …  ሁለቱም አበቃቀላቸው እንደ ካሮት ነው። መሬት ተምሶ ነው የሚገኙት። ሁለቱም በገብያ ይሸጣሉ፤ እንዲሁም ሜዳ ላይ እንደ አጋም እና ቀጋም ይገኛሉ። ሁለቱም የሴቶች ባህላዊ የእግር እና የእጅ ማስዋቢያ ናቸው። የገጠር ሴቶች በሠርጋቸው ዕለት፤ የከተማም የገጠርም ሴቶች አብሶ በጥምቀት ባዕል የሚዋቡበት ነው።

አሰራሩ…. እንሶስላው ወይንም ጉርሽጡ ይሰለሰላል፤ ከዛ ይቀቃል፤ ከዛ በዛ በተደጋጋሚ እግርም እጅም ይታሻል ስለስሉ እዬሞቀ። መጨረሻ ላይ የወይራ ጢስ ነገር ይታጠናል። በበነገታው በጣም ጥቁር ወይንም እሳትማ ይመስላል። ውበት ይደምቃል። እንሶስላ ወይንም ጉርሽጥ መቀባት ሳይሆን የሚባለው መሞቅ ነው የሚባለው። እንሶስላ ጠንከር ይላል፤ ጉርሽጥ ግን ለላ ያለ ነው በማቅለም አቅሙ። አሁን አሁን እኔ ሳስበው ለጸጉርም ሊሆኑ እንደሚችሉ ይሰማኛል።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በራሱ ጊዜ ይለቃል። ሲለቅ ግራጫማ እዬሆነ ይሄዳል። ይህ በስሜን ኢትዮጵያ የተለመደ ባህላዊ ትውፊት ነው። እንደ አረቡ ዓለም እና ህንድ አገር ሂና ማለት ነው።
2) ተባደግ …  ተባደግ ያልተመጣጠነ፤ የአስተሳሰብ እድገት፤ ያልተመጣጠነ አስተሳሰብ፤ ያልተስተካከል ሁኔታ ማለት ነው።

የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ህጻናት ልጆች መብት ይጠበቅ!
የቅድስት ኦርቶዶከስ ተዋህዶ ማህበረ - ምዕመናንም ኢትዮጵያዊ ዜጎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዜግነቷ ኢትዮጵያዊ ነው!
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
ፍቅር ሲያልቅም ትዕግሥት ይሰደዳል።

የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።






አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።