የኔታዋ የደወል ምህላን፤ ብትደፍረው፤ የአርሲ ነገሌ መስቀል ጉዞ ወደ ቀራንዮ


እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።

የኔታዋ የደወል ምህላን፤ የደወል አቤቱታን
ብትደፍረው ታተርፍበታለች።
የአርሲ ነገሌ መስቀል ጉዞ ወደ ቀራንዮ።

„አንተ ታካች እስከ መቼ ትተኛለህ?
ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሳለህ?“
{መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ 6 ቁጥር 9}

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ
13.01.2020
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አህዱ አምላክ። አሜን።
ይድረስ ለብፁዓን ወቅዱሳን አባቶቼ በሙሉ።
በያሉበት
         


                                      ሰማዕት ሱራፌል ሰለሞን።
                       
·       እፍታ።

ጤና ይስጥልኝ የአገሬ ቅኔዎች እንዴት ናችሁ? ደህና ናችሁ ወይ? እኔ በረጋ ጸጥታ - በአርምሞ ዝምታ - ዘመንን በቀስታ ከምታስናግደው ከእመቤት ሲዊዝሻ ጋር ደህና ነኝ። እህቴ ከወደ አሜሪካ ጎራ ባለችበት ወቅት የገዳም ከተማ ስትል የምኖርበትን ቀዬ መሰጠረችው። ለእኔም ግጥሜ የሆነው በዚህ ስሌት ይመስለኛል አብረን ገደምን። ስከነት የሰፈነበት።

ዛሬ ሁለት ዕርዕሰ ጉዳዮችን በአንድ አጣምሬ ነው እማቀርበው። „የኔታዋ የደወል ምህላን፤ የደወል አቤቱታን ብትደፍረው ታተርፍበታለች“ „የአርሲ ነገሌ ጉዞ ወደ ቀራንዮ።“ ሁለቱም የዕንባ ቤተኝነታቸው ከአንድ ማህጸን ይቀዳል።

·       ምልሰት።

በመስከረም እና በጥቅምት ወር በፌስቡኬ ላይ የኔታዋ የደወል አብዮትን ብትደፈረው ታተርፍበታለች የሚል አጫጭር ማስተዋሻዎችን ጽፌ ነበር። እስከ አሁን ለብጹዓን ወቅዱሳን አባቶቼ መልዕክቱ አልደረሰም መስል ወይንም ፈቃደ እግዚአብሄር አላገኘም መሰል ወደ ተግባር አልተተረጎመም። 

ወደፊትም ላይተረጎም ቢችል ውስጤ የሚለኝን፤ መንፈሴ የሚያዘኝን በቀጥታ ለሚመለከታቸው ንዑዳን ከላኩ በቂ ነው። „ አግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም“ ይላል አካል የሌለው የእግዚአብሄር አገልጋይ።

ኔታዋ የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት የምህላ ተደሞ ጎንደር በአርምሞ! ከጥቅምት 01 ቀን እስከ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓም።


ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ እርግጥ ነው ጎንደር ለ40 ተከታታይ ቀናት ምህላ በአደባባይ ነበር። በጎንደር  የእስልምና ዕምነት ተከታዮችም ለ30 ቀናት ድንቅ የድውኣ ክፍለ ጊዜ መስጊድ ውስጥ ነበራቸው። ባህርዳርም ለሦስት ቀናት ምህላ ነበር። አዲስ አበባም እንዲሁ። እቴጌ ትግራይ ግን በዝምታ ውቅያኖስ ውስጥ ናት። ቢያንስ ይህን በመሰለው የሃይማኖት የህልውና ጉዳይ እንዲህ አቃሎ ማለፍ ወይንም መነጠል ለዛውም ለትግራይ የሚገርም ብቻ ሳይሆን የሚያሳዝንም ነው።

እቴጌ ትግራይ ተሰወረችን ወይስ አረገች ያሰኛል። ደብረ ዳሞስ? እቴጌ ትግራይ ከሚስጥሯ እያፈነገጠች ነው። ህወሃት ትውልዱንም ከሚስጢሩ እዬነቀለው ነው። ታሪክ የሌለው ሸቀጥ ላይ ይገኛል ታሪክ ያለው ህዝብ ደግሞ በዕንቁ ታሪኩ ጢባ ጢቦ ይጫወታል። በማተብ ቀልድ የለም። ማተብ መስቀል ነው። ማተብ ቃል ነው። ማተብ ውል ነው። ማተብ የትውልድ አደራ ነው። ማተብ ሃይማኖት ነው።   

ሰሞነ - ሰላማዊ ሰልፍ በአማራ ክልል ብቻ በነበረበት ጊዜ አንድ ቀን አክሱም ላይ የጧፍ ብርኃን ያለበት የማህበረ -ምዕመናን ጉባኤ አይቻለሁኝ። ለዛውም እርግጥ ከሆነ ነው። ያም በቂ ነው ብዬ ግን አላስብም - ለትግራይ የሃይማኖት ሊቀ - ሊቃውንት ሥርዕዎ ልቅና የማዬው ነገር አይመጥንም።

የኦሮሙማ ሥርዕዎ መንግሥት ዓለም እንዲያውቅለት የሚፈልገው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የአማራ ብቻ እንደሆነ ተደርጎ እንዲታይ ይሻል። ኦነጋውያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋህዶ ብሄራዊ፤ ዓለም አቀፋዊ መሆኑን የግንዛቤ እጥረት አለባቸው ብቻ ሳይሆን በሥነ - ልቦናም እዬተሰቃዬበት ነው። 

ለዚህም ነው እሬቻን አዲስ አበባ ላይ እንዲከበር የወሰኑት። ሁሉንም ነገር ማፎካከር ምርጫዬ ብለው ይዘውታል። ባያውቁት ነው እንጂ በዘርፉ ሊቀ - ሊቃውንት ከዬትኛውም ማህበረሰብ ተፈርተዋል። ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስስታም አይደለችም። ለጋስ እሩህሩህ አዛኝ እና እናት ሆዱም ናት። 

የኛዋ የኔታ አይደለም ለውስጧ የሌሎች ሃይማኖቶችን መጸሐፍ ጽፋ የምታስተምር ወደር እና አቻ የሌላት እጬጌ ናት። የሰማዩንም የምድሩንም፤ ሳይንሱንም፤ መልክዕ- ምድሩንም፤ ቁጥሩንም ምኽዋርንም።  

የሆነ ሆኖ የኦሮሙሞ የዘመኑ ባለሥልጣኖች ቀያችን ነው በሚሉት ባለ ማተብ የኦሮሞ ዞግ ያላቸውንም የችግሩ ቤተኛ ያደርጓቸዋል። ተቀጥቅጠውም ተገደሉ። ታረደው ተገደሉ። ቤታቸው የነደደው ሁሉም በማተባቸው ነው። በጨካኝ መንፈስ ውስጥ እርህርህና የለም። ማጨድ ብቻ ነው። አሁን አቅም ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ የጨካኙ መንፈሱ ነው።

የሆነ ሆኖ ለመከራው ባለቤት እንሆናለን ያሉት ግን ያደረጉት ነገር መልካም ጥረት ነበር አብሶ ጎንደር በጣም የሰከነ ታሪክ ሠርቷል። ታሪክ ማለት የሰዎች የተግባር ውሎ ዕድሜ ጠገብ ሲሆን ታሪክ ይባላል በሥርጉተ የህሊና ብያኔ። ታሪክ መልካም፤ መልካም ያልሆነ፤ ብቻም ሳይሆን ሲቃም የሆነ አለ። ሲቃ መልካም እና መልካም ያልሆነ የተቀዬጠበት ወይንም ውህደት የፈጸመበት ማለት ነው።

በአንድ ጦርነት ሃዘን አለ፤ ድልም አለ። ድሉ ሲገኝ ሰው ተግብሮ፤ ብዙ የአገር ውርስ ቅርስ ወድሞ ነውና ድሉ ንጹህ መልካም ነገር አይሆንም፤ ወይንም ሙሉ ሃዘን አይሆንም። ሲቃ ነው የሚሆነው። ዕንባ እና ሳቅ። ትንሽ ፈንገጥ ያለ ዕይታ ነው አይደል?!

ታሪክን ዬሚተረጉሙ ሙሁራን ሳዳምጣቸው መጥፎ እና ጥሩ ከሚሉት እኔ እለያለሁኝ። በሁለቱ ማህል ያለ ሲቃ የሚባል ታሪክም አለ ባይ ነኝ። ልክ ተውኔት አስቂኝ እና አሳዛኝ ማህል ሌላ ሦስተኛም ሲቃ የሚባል አለ ብዬ እንደምሞግተው፤ በጨለማ እና በብርኃን ማህል ሌላ አለ፤ ሊነጋጋ ወይንም ሊመሻሽ ሲል ያለው ግራጫማ ጊዜ እንደምለው ማለት ነው።

ሀዘን እና ደስታ ብቻ በሚሉትም ውስጥ ሦስተኛ አላት ህይወት ብዬ እሞግታለሁኝ ያ ደግሞ ሲቃ ነው። አንዳንድ ትዳሮች ሲለያዩ ይነፋፈቃሉ ሲገናኙ ይጋጫሉ፤ የዛ ትዳር ባህሬ ለእኔ ሲቃ ነው። ጨርሰው እንዳይለያዩ የሚያደርጋቸው የማህል ሙጫው ሲቃዊ የትዳር ዓይነት ነው። ይህን አያውቁትም። ቢያውቁት ባሊህ ብለው አቀራርበው አቻችለው መኖር ይችሉ ነበር። ግን ዕድሜያቸውን ሙሉ ሲቋጥሩ ሲፈቱ፤ ሲፈቱ ሲቋጥሩ ጉልቻው ሳያምርበት ሁለቱም የፈቀደላቸውን ጊዜ ኑረው ግባዕተ መሬት ይኮናል።

·       ችግር የመረዳት ችግር።    

ብዙ ሰው ሙሽራው ኢህዴግ ብልጽግና የሚባል ቤሎ ስለ ለበሰ ምርጫዬ ብልጽግና ነው ይልሃል። ምርጫዬ ብልጽግና ነው ሲልህ ምርጫዬ ኦነግ ነው ማለቱ እንደ ሆነ አያውቀውም። አሁን ሳቅና ለቅሶ ተቀይጦ የሚታዬው የሲቃ ትዕይንት መሪ ተዋናይ ስላለው ነው። ነፍስ ሁሉ በዛ ምርኮኛ በመሆን ጽናት እዬተገበረ ነው።

 ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ ጥገናዊ ለውጡ የሲቃ ትዕይንተኛ ነው። ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ የሲቃው ተውኔት መሪ እንደ ሆኑ ይሰማኛል። አሽገው ይዘውታል መንፈሱን ሁሉ። ምን አልባት እሳቸውም እራሳቸውን መተረጎሙ ላይ ሰነፍ ሊሉ ይችሉ ይሆናል።

ስለሆነም በረጅሙ ለታቀደ የጥፋት ዓላማ የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ያላት አቋም በቂ ነው ብሎ መቀመጡ የሚበጅ አይመስለኝም። አሁን ዓርማዋ ተብሎ ተለጥፎ እማዬውን ሳይ የሲቃ ተውኔት ይሆንብኛል። ሌላም ልከል አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ተጥርቶ ውል አልባ ተውሸልሽሎ ይቀራል። ህዝባዊ ጉባኤ በአደባባይ ተጥርቶ በዚህም በዛም በመንግሥት ተወጥሮ እንዲሁ የተነቃቃው መንፈስ እንዲበርደው ሆኖ ይቀራል።

በሌላ በኩልም ከእኛ እስከ አሁን አልደረሰም ማለት የሚገባ አይመስለኝም። አንዲት እጣት ስትቆረጥ ሌላኛው አካል ሙሉ እንደሚታመም ልብ ማለት ይገባል። እኔ በማዬውና በማስተውለው የኔታዋን ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶን መናህሪያ ርዕሰ መዲና የማሳጣት፤ ክብሯን ዝቅ አድርጎ ብሄራዊ አድርጎ ያለመመልከት የፍልሰት ፖለቲካ እዬተካሄደ ስለመሆኑ ይታዬኛል። ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ናት። ቀዝቃዛ ጦርነት ላይ። እኔ ውስጤን የገለጽኩት በመስከረም እና በጥቅምት እንዲህ በሚል ነበር   

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አህዱ አምላክ አሜን።
ይድረስ ለብፁዐን ቅዱሳን አባቶቼ።
ባሉበት።
በአለፈው ሳምንት አንድ ቁልፍ ነገር አንስቼ ነበር። የኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ አላወቀችውም እንጂ የቁም እስረኛ ናት። በጠቅላላ እንቅስቃሴዋ ሁሉ በኦሮሙማ የደህንነት ተቋማት ሥር ነው።
ይህንን አውቃ ቤተክርስትያናችን ቀለል ያሉ ሰላማዊ ዬትግል መስመሮችን ደፍራ መጀመር ይኖርባታል። በተለይ በአዲስ አበባ። "ተማህፅኖ " የተባለው ቀልድ ነው። በዚህ ውስጥ ያለው ዕውነት የመንፈስ የሥነ - ልቦና ካቴና ነው።
ስለሆነም ቀደም ባሉ ቀናት እንደፃፍኩት የደወል አቤቱታን ለእዮር የምታቀርብበት ንድፍ ሊኖራት ይገባል። አሁን ሦስት ቀን ምህላ አውጃለች። ከምህላው ፍፃሜ በኋላ በሁሉም አብያተ ቤተክርስቲያናት የአንድ ሰዓት የደወል ፕሮግራም ሊኖራት ይገባል።
ይህን ሳያቋርጡ በተለይ አዲስ አበባ በሁሉም አድባራት በዬሳምንቱ ለምሳሌ ከጥዋቱ ሰዓት እስከ ሰዓት በደወል ፈጣሪያውን መጠዬቅ። ይህ አንድ ሰው ብቻ የሚፈፅመው ቀላል፣ ሥልጡን፣ ብዙ ሚስጢራትን የያዘ ተጋድሎ መስክ ነው።
የኔታዋ የኦሮሙማ ፖለቲካ መተንፈሻዋን ሙሉ ለሙሉ ከመከርቸሙ በፊት፣ መንበረ ፓትርያርኩ ከመደፈሩ በፊት፣ ብፁዐን ወቅዱሳን አባቶቻችን ከማጣታችን በፊት ቢያንስ የደወል አቤቱታ ፕሮግራሙን ደፍራ ትጀምረው።
ወስብሃት ለእግዚአብሄር።“

ይህ እንግዲህ ፌስቡኬ ላይ ሳስተላልፍ የሰነበትኩት አቤቱታ ነው፤፡

·       የዛሬው መነሻዬ - የድርሻዬን።
„የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሀገሯ የት ይሆን ???“ በሚል እርእስ የተጻፈውን፤ በፎቶግራፍ የተደገፈውን ልብ ላላቸው ማህበረ ምዕመናን የደወሉ፤ የመስቀሉን፤ የጽናጽኑን፤ የታቦቱን፤ የጢሱን፤ የቀኖናውን፤  የአድህኖተ ሥዕላት፤ የቤተ መቅደሱን፤ የደጀ ሰላሙን፤ የቅዱሱ መጽሐፍትን፣ የዶግማውን መከራ እንግልት በአጽህኖት የገለጸውን እርሰ ጉዳይ ባሊህ ይባል ዘንድ ነው ይህን የጻፍኩት።
አንዱን ሳንጨርስ በላይ በላይ ዕንባ እዬተጫነን ቢያንስ ለታሪክ በሚያመች ሁኔታ አቅል ሳንሰጠው ከቀረን ነገን ማሰናዳት ያቅታል። እንኳንስ አሳምረን የተረከብናትን አገር ለማስከርብ፤ የነበረችውንም ለማስረክብ ዳግት ነው። ምጥ። ኢህዴግ ሲመራት የነበረችው የክፍልፋዮች ግጥምጥም እሷ እንኳን ዛሬ የለችም። ባዶ እጁን ለገባ ለኦነግ ነፃ አውጪ ድርጅት በራሷ የጥሪት አቅም አቋቁሞ እርክክብ እዬተፈጸመ ነው። ይመራል። መንፈሱ ላልተማረከ። 
·       እንዲህ በሚል ነበር ዘገባው የቀረበው …
„የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሀገሯ የት ይሆን ???“ ዛሬም እምዬና ልጆቿ በአርሲ ነገሌ እያለቀሱ ነው። እኔም ልቤ ደምቷል ስለ ቤተክርስቲያኔ ውስጤ ያለቅሳል። እንባችን ይውረድ፣ ይጠራቀም፣ እኛም ሳናቋርጥ እናለቅሳለን። አሰለቃሾች ግን ወዮ፣ ወዮላችሁ በየቦታው የሚፈሰው እንባ ተጠራቅሞ ጎርፍ የሆነ እለት ስም አጠራራችሁ ድምጥማጡ ይጠፋል። አሁንም እግዚአብሔር እድል ሰጥቷል። ሀገርን ከሀገር ማሳደድ፣ ሀገርን በሀገር ላይ ማስለቀስ ይብቃ። አለበለዚያ በቃል ብቻ ኦርቶዶክስ ሀገር ናት እያሉ ሀገርን ማፍረስ በኋላ ዋጋ ያስከፍላል። ሉሌ ቋንቋዬነሽ“ ( Zemari Dn Lulseged Page  January 5 at 9:13 PM)
አሁን አሁን የቅድስት ኦርቶዶክስ ብጹዓን ወቅዱሳን አባቶቼ ወደ አገር እንዲገቡ የተደረገበት የደባ ሚስጢር ዲካ የለሽ ሆኖ አያለሁኝ። ቅንነቴን እዬፈተነው ነው። በቀሉ በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ መንፈስን በመንቀልም ላይ በማዛል ትጋቱን እንደ ቀጠለ አስተውላለሁኝ። ወዮልሽ አገሬ!  ከተኛሽ?? ብዙ ሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጥቃት ብቻ ይመስለዋል። እእ። 
ኢትዮጵያዊ ቀለም የተዋህደው ኢትዮጵያዊው እስልምናም ጊዜውን ጠብቆ አይቀርለትም። ጠብቁት። በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያዊ የእስልምና ዕምነት ተከታዮችም እባካችሁ በስሜት ስስ ሳትሆኑ መከራውን በጥሞና ታጠኑት ዘንድ በትህትና ላሳስባችሁ እወዳለሁኝ። ፍርሰት ላይ ነን።   
·       ተደሞ።
የኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አንድ በመሆኗ ጠሚር አብይ አህመድን የበለጠ እንድናምናቸው ያደረገ መሰረታዊ መንፈሳዊ ጉዳይ ነበር። ልብ እና ኩላሊት የሚመረምረው አምላክ በሚያውቀው አንዲት የሰናፍጭ ታክል ልዩነት የነበረን አይመስለኝም እኔ ዛሬ ላይ ሆኜ እራሴን ስገመግመው። የእኔን መንፈስ ለማሸነፍ ብዙ እርቀት የተጓዘ እርምጃ ነበር  የእርቅ ሂደቱ፤ አቀራረቡ እና አያያዙ አክብሮቱም።

እግዚኦ!

ፈቃዱ ስለ ነበር በንጽህና እና በቅድስና ነው የተቀበልኩት። 27 ዓመት ሙሉ ችግሩ፤ ፈተናው የተፈጠረ እስከማይመስለኝ ድረስ ነው የህሊናዬ ድንግልናው የሚደንቅ ነው። በዚህ ዙሪያም ቀንበጥ ብሎጌ ላይ ገብቶ ማዬት ይቻላል ውስጤን ገላጭ የብዕር ምርቶች በርከት ብለው ተከትበውበታል። ዶር አብይ አህመድንም በስፋት ነበር ያመሰገንኩት። ከመቀራረብ፤ ከፍቅር፤ ከምህረት፤ ከይቅርታ፤ ከእርቅ በላይ ለሰው ልጅ መንፈሳዊ ህይወት የሚያስደስት፤ መኖርን ለማኖር አቅም ያለው ጉልበታም አምክንዮ ምን አለና?!
በጣም ለረጅም ጊዜ ማለት እችላለሁ አዎንታዊ ሥርዓቱን እዬደገምኩኝ፤ እዬሰለስኩኝ አስተውለውም ነበር። አቀባበሉም፤ አያያዙም መልካምነትን አይቸበታለሁኝ። ያው እንጨት ተለቅሞ ማሰሪያ ልጥ አልባ ሜዳው እንደሚቀረው በመጨረሻው የበረከት ቀን ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ፈቃዳቸውን የፈጸሙላቸውን ታላላቅ የአገር አቨውን አክብረው በሥርዓት ባይገኙም የሰማያት ቅዱሳን፤ ጻድቃን መላዕክታን የረበቡት እንደ ነበር ግን አምናለሁኝ።
አጋር የክርስትና እና የእስልምና ዕምነት የሃይማኖት አቨው በዕለቱ እንደዛ አንደበታቸውን ከፍቶ ያን የመሰለ ለዛ ያለው ቅኔ ያዘረፋቸውም በቦታው የነበረው ሰማያዊ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ በጽኑ አምናለሁኝ። ኢትዮጵያዊነት የፈራበት ዕለትም ነበር።
·       ፈተና።
የኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እርቀሰላምነት ያበሳጨው ዲያቢሎሳዊ ጨካኝ መንፈስ 9 አብያተ ቤተክርስትያናትን በማቃጠል ነበር አቀባበል ያደረገው። ይህ የመግቢያው መቅድመ - ፈተና ነበር። እርግጥ ነው ቅዱሳን አበው እና እመው ፈተና ከጠፋ ስለምን ፈተና አራቅክብን ብለው ሁለት ሱባኤ ይገባሉ። ፈተና የጽናት መሰረት ነው። ከልቅ ምግባር የሚገራ፤ በቁጥብነት እንራመድ ዘንድ የሚያንጽ ነው። ለዚህም ነው የእግዚአብሄር ቃል „ከፈተና በስተጀርባ ታላቅ ክብር አለ“ የሚለው።
የኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ፈተናዋ እጅግ በርካታ፤ ውሰብስብ ሲሆን በዬዘመኑ መፍቻውንም ከምርቃት ጋር እዮር ስለሚልክላት ተወጥታዋለች። የአሁን ፈተናም ያው የለመደባትን ፈተና ታግሳ ታሳልፈው ዘንድ የመጣ እንደሆነ አሰባለሁኝ። በዘላቂ ጽናቷዋ ውስጥ የተሰጣት ጸጋ ረቂቅ ስለሆነ ለድል ትበቃለች ብዬም አምናለሁኝ።
እርግጥ ነው የአሁኑ የፈተናዋ ዓይነት ከቀደመው ፈተናዋ በላይ ስለሆነ ግን ጠንከር ባለ አቅም መሞገት እንዳለበት በትህትና በአክብሮት እና በተመሰጠ ልቦና ዝቅ ብዬ ልገልጽላት፤ ላሳስባትም እወዳለሁኝ።
የኔታዋ ትጥቋን ማጥበቅ ይኖርባታል። ጸሎቷ በተለመደው ጊዜ ከሚሆነው በላይ፤ ሱባኤዋ ከተለመደው በላይ፤ ስግደቷ ከተለመደው በላይ፤ ጾሟ ከተለመደው በላይ፤ ሱባኤዋ ከተለመደው በላይ ሊሆን ግድ ይላል። ደወሏም ከተለመደው በላይ።
ዛሬ እኔ እንደማስበው፤ እኔን እንደሚሰማኝ የኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እንደ አናንያ፤ እንደ አዝርያ፤ እንደ ሚሳኤል እሳት ውስጥ እንዳለች መቀበል ያለባት ይመስለኛል። ዘመን በተለዋወጠ ቁጥር በተወጣቸው መንገድ ብቻ ፈተናዋን ልታቃልል ትችላለች ብዬ አላምንም። 
ምን አልባትም ባዕለ መስቀልን አዲስ አባባ መስቀል አደባባይ ላይ ለማክበር ቀረጥ ክፍይ ልትባል የምትችልበት ዘመን ይመጣል። ወይንም ከአዲስ አባባ ከተማ ውጭ የሚከበረው ባዕል ይበቃል ወይንም ወደ ደብርብርሃን ጎራ በይ እና እዛ አክብሪም ሊመጣ ይችል ይሆናል። ቢሆን ብሎ ማሰብ ይገባል። 
የ2011 ዓ.ም እንዲሁም የ2012 ዓ.ም የብርኃና መስቀል ባዕል አከባበር ጦርነት የታወጀበት ነበር በትዕግስት፤ በበዛ መቻል ተይዞ ነው እንጂ። 2013 ዓ.ም የከፋ እንደሚሆን ነው እኔ አማስበው። „አያያዙን አይቶ ሸክሙን ይቀሙታል“ እንዲሉ።
የአዳማ ሥርዕዎ መንግሥት ወዘተረፈ ውሽማ ወይንም ቅምጥ ፍላጎቶችን ታቅፎ ነው አገር እዬመራ ያለው። ቅምጥ ፍላጎቶቹን እንደዬቅደምተከተላቸው ብቅ እያደረገ በመንግሥት ጉልበት፤ በኢትዮጵያ አንጡራ መንፈስ ማህበረ ምዕመናን በሚከፍሉት ታክሲ ቀረጥ በድል ላይ ድል እያነባበረ ሳያፍር፤ በድፍረት በዓዋጅ እዬተናገረ እዬተገበረ ነው የሚገኜው።
የዴሞግራፊ ፍልስፍናው የመሬት ወረራ ብቻ አይደለም። የህሊና ነቀላ እና ተከላም እንጂ። የባህል፤ የትውፊት፤ የቋንቋ፤ የሥነ - ልቦና፤ የሃይማኖት፤ የወግ፤ የልማድ፤ የታሪክ፤ የቅርስ፤ የትውልድ ሥነ - ልቦና ወረራም ነው። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ እራሷ የህልውና አደጋ አለባት የምለው። እንድትበወዝ ይፈለጋል። እንደ ካርታም እንድትሸጋሸግ። አሳዛኙ እና አስማጩ ጉዳይ ግን ኢትዮጵያ የህልውና ተጋድሎዋን የሚመራ አቅም ያለው ብሄራዊ ድርጅት አለመኖሩ ነው። ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶም የህልውና አደጋ ላይ ናት።
እንዲያውም ሞቷን አብረው ለማረጋገጥ፤ ለማቀላጠፍም መገነዣ ሲያቀርቡ እምመለከታቸው ተደማሪ ድርጅቶችም አሉ። ማዳኑ ቢቀር ማምታቱ፤ ለህዝብ ውግንና ቢቀር ጆክር ሆኖ አለማገልግሉ ቢታወቅ ምንኛ መልካም በሆነ ነበር። ብልህነትን የሚያሰፍን መንፈስ ፈጣሪ በጥበቡ ካለፈጠረ በሰው ሁሉ ህሊና መሃል ላይ ሆነው እንቅፋት ፈጣሪዎች ሁሉንም እያሳጡን ይገኛሉ።
ስለሆነም የቅድስት ኦርቶዶክ የተዋህዶ ሃይማኖት አማንያን አቅምን በማንኛውም ዘርፍ ከማዋጣት የመቆጠብ ሰማያዊ ግዴታ አለባቸው። ደፍረው ካልጀመሩት ያው አብሮ መስመጥ ነው። የኦሮሙማ መንግሥት እንዲህ በልቅ ያሻህን አድርግ ተብሎ ከተፈቀደለት ግን የሚተርፍ አንዳችም አገራዊ ቅርስና ውርስ ነገር የለም። 
·       ዝለት።
እንደማስተውለው። የኔታዋን የኢትዮጵያ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በዝለት ታምቃ እንድትቆይ የሚያደረገው አውሬው መንፈስ ሙሉ ለሙሉ አቅም እስኪያገኝ ድረስ ነው። ቅድስቷ አላወቀችውም እንጂ እሷ በኦሮምያ ክልል ንጉሣን ሥር ነው ያለችው፤ እንጂ በፌድራሉ ሥር አይደለችም። ታግታለች። እንደ ሰርዲንም ታሽጋለች። ልክ እንደ አዲስ አበባ ህዝብ። ይህ ዘግይቶ ይሆናል የሚገባት።
ኦሮምያ ላይ የሚወጡ መመሪያዎች ሁሉ እሷን ይመለከታል። አደብ ገዝታ፣ ለእኔም ነው ብላ ታዳምጠው። የኦሮምያ ፖሊስ ሰላማዊ ሰልፍ በክልሉ ሲያግድ አዲስ አበባንም ጨምሮ ነው። ይህን ቅዱሳን ወብፁዕን አባቶቻችን ጌታችን መዳህኒታችን ሚስጢር እንዲገልጽላቸው ቢጠዬቁት ይገልጥላቸዋል። በህልም ፍንትው አድርጎ ሊያሳይ ይችላል።
አሁን ለእኔ እንደሚሰማኝ የኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የቁም እስር ላይ ናት። የቁሙ እስሩ በታመቀ በታጠረ ሁኔታ ነው። ዙሪያ ገባውን እሷ በማታውቀው ሁኔታ ታጥራለች። ብጹዓን ወቅዱሳን አባቶቻችንም ቢሆኑ እንዲሁ በዓይነ ቁራኛ ቁጥጥር ሥር ውለዋል ብዬ ነው እማስበው በተለይ ታላላቆቹ እና ደፋር ተናጋሪዎቹ።
የእርቀሰላሙ ሚስጥር ሁሉንም አባቶች እንዲህ ሳያውቁ አሰባስቦ ለማገት ይመስለኛል። ይመስለኛል ነው ያልኩት፤ ነው አላልኩም። ነው ለማለት እንደ መረጃ ሰራተኞች መሪዎች አቅሙን የሚለካ አቅም እዛው መሬት ላይ ሲኖር ብቻ ነው። እኔ እንደማስበው የኦሮሙማ መንግሥት አሜሪካ እና ራሺያ በሚሰላሉበት መንገድ ቅድስት ኦርቶዶክስን የሰለላ መረብ ዘርግቶ እንደሚከታተላት ይሰማኛል።
የኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በአማራ ክልል ብቻ ሰላማዊ ሰልፍ እንድታደረግ ሲፈቀድ ይህን ለሊቀ ሊቃውንቱ አንባቢም፤ ተርጓሚያን፤ አመሳጣሪም የሚያስፈልገው አይመስለኝም። ተነጥላ እንደምትታይ ልትቀበለው ይገባታል። ደንበር ተሰርቶላታል። 
በዚህ ውስጥ ኦሮምያ ላይ ቤተ መቅደስ ይነዳል፤ አማራ ክልል ላይ ደግሞ መስጊድ ይነዳል። ይህን አውራ ሚስጢር ቁጭ አርጎ መፍታት የዕድምታ ሊቀ - ሊቃውንት ሰማያዊ ኃላፊነት ይመስለኛል። ከፈቱት አንዱ ለሌለኛው፤ ሌለኛው ለአንደኛው ህሊናዊ ፈውስነትን ይመጋገባሉ። ይህ ከሆነ ሰይጣን ያፍራል። ልጆቻቸውም ይድናሉ። መዳን! - በቅንነት እና ሚስጢርን በማመሳጠር አቅም ይወሰናል።
·       አቅምን በቅጥ የማስተዳደር ብልህነት የኢትዮጵያዊነት ሚስጢር የመረዳትን አቅም ይጠይቃል።
ዛሬ የኔታዋ ልጆች በአንድም በሌላም በቅንነት የሚያዋጡት አቅም ነገ የመጥፊያቸው ስለመሆኑ ልብ ብለው ሊያስተውሉት ይገባል። ይታወስ ከሆነ አንድ ወንድማችን ለየኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ሰላማዊ ሰልፍ ከካናዳ አዲስ አበባ ሄዶ በአደባባይ ነው የተረሸነው።
ያንን ልጇን ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ባሊህ ሳትለው፤ ሳትደደመምበት አልፋዋለች። ታሪኳም ነበር። ያ ቅን ሰው ሰማዕቷ ነበር። ቅዱስም ነበር። በጸሎትም አዘውትራ ልታስበው ይገባ ነበር። 
አሁንም በቤታቸው ውስጥ ተቃጥለው እንዲሞቱ የሚደረጉት፤ በሰንጢ ተወግተው የሚሞቱት፤ በድንጋይ ተቀጥቅጠው የሚገደሉትን ዝርዝራቸውን በመያዝ ለደላቸው እና ጊዜ ለሰጣቸው የሥም ግንባታ እምታፈሰውን ሚሊዮን ለተጎጂ ቤተሰቦች ማድረግ አለባት ብዬ አስባለሁኝ። ባፈለው ለኢንጂነር ታከለ ኡማ የሰብዕና ግንባታ 10 ሚሊዮን ብር ለግሳለች። ህዝባዊ ጉባኤ በአደባባይ መስቀል አደባባይ ላይ ተከልክላ። ልጆቿ በጠራራ ጸሐይ ሰማዕትነትን በዬቀኑ እዬተቀበሉ። እናት ዕንባ ብቻ ሆኖ ስንቋ።
ስለምንድን ይሆን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ላይ ኮሽ ባለ ቁጥር የመንግሥት ከፍተኛ አካላት ወደዛ የሚያመሩት? በሚስጢር የተወሰነው ውሳኔ እንዳይጓጉል ነው። ፍርደኛ ናት ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ። ኢትዮጵያዊነት በውስጧ ከትሟል ተብሎ ስለሚታሰብ ብቻ ሳይሆን „ኦርቶዶክስ አገር ናት“ ማለት ሌላ ማለት አይደለም። 
ኢትዮጵያን ተጻሮ ለሚነሳ ማናቸውም መንጦላዊት መንፈስ የጥቃት ኢላማነት ነው። „ኢትዮጵያ ካልፈረሰች ኦሮምያ ሰላም አታገኝም“ ከዚህ ሚስጢር ጋር አቀናጅቶ በማስተዋል መመርመር ያስፈልጋል። ዕውነትና እምነት የሚል ሰው ዛሬን ከግብታዊነት፤ ከስሜታዊነት፤ ከቂመኝነት፤ ከበቀላዊነት ወጥቶ በጥሞና ሂደቱን ሥራዬ ብሎ ማጥናት ይገባዋል። አደጋው ዝልቅ፤ ፈተናውም ልቅ ነው።  
ብሄራዊነትን በሚመለከት ሰፊ እና የታቀደ የማጥቃት ሁኔታ ነው ያለው። እራሱ አማራ ክልል ያለው የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አቅምን ሊሸረሽሩ የሚችሉ እርምጃዎች ሲወሰዱ በቅደም ተከተል በተደሞ ሆኑ መከታተል ያስፈልጋል። በንጽህና ቢኮን ሂደቱን መመዘን ይቻላል።
አብይዝም ቀላል ሂሳብ አይደለም። አብይዝም ሲፈጠርም በቀላል ቀመር አይደለም። ህይወቱ ላይ የተወሰኑ የግል ውሳኔዎች ቢሆኑ በቀላል የሂሳብ ስሌት የተቃኙ አይደሉም። ብዙ ሰው አብይዝምን አቃሎ ይመለከታል። 
ማቅለል የማይቻልን ሰብዕና አቃሎ ማዬት ሽንፈትን ለራስ መሸለም ነው። በተገባው ልክ አቅሙን ዕውቅና መስጠት ይገባል። እኛ እኮ ከሺህ በላይ ጥኑ አቅም የነበራቸው ወገኖች ነበሩን። ግን አሁን እነሱ ድብዛቸው ጠፍቶ የማን መንፈስ ገኖ እንደ ወጣ ብቻ ሳይሆን የፈለገውን በፈለገው ሁኔታ እዬከወነ እንደሚገኝ ተመልክተናል። ያ ችግሩ አቅም ስንመግብም፤ አቅም ስንተችም በማህል ባለው የኛው ዝንጉ ክፈተት የተናቀው ነጥሮ ይወጣል።
·       መልስን ለማግኜት ሂደትን ማጥናት።
ሌላው በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስለምን የአማራ ማህበረሰብ ላይ ጥቃቱ ጠና ብሎ ቢታሰብም መልሱ ይገኛል። አማራዊነት አገራዊነት ነው፤ አማራ በኢትዮጵያ ሉዕላዊነት ላይ አይደራደርም። ይህን ጭብጥ ይዘን ስለምን የመንግሥት ሹመኞች አማራ መሬት ላይ እንዴት እና እንዴት ባለ በተከደነ ሁኔታ ምደባው እዬተከወነ ነው ተብሎ ቢመረመርም መልስ አለው - እርምጃው።
ስለምን? ጠሚር አብይ አህመድ ወደ ራሺያ አቅኑ እሱም እራሱን የቻለ ዕድምታ አለው። ምንን ለማዛል? ምንን ለማጠወልግ? ቢገባን እዬፈረስን ነው። መርዶ አይደለም ዕውነት ነው እኔ እምናገረው። ለዚህ ታዲያ ቂም በመቀፍቀፍ አንወጣውም። በማግለልም አይሆንም። መከራን ችሎ ለመውጣት የመንፈስ ድንግልና ያስፈልጋል። ቅን መሆን። በዬቀኑ ለዬኔታዋ የታቀደ ተንኳሽ ፈተና ይታቀድለታል። በዬዕለቱ መሰናክል ይበጅላታል። ልጆቿ እንግልት ላይ ነው ያሉት። ልጆቿ ተስፋ በማጣት ላይ ነው ያሉት። ዋቢ ትሁናቸው። አይዟችሁ እኔ አለሁላችሁ ትበላቸው።
በሌላ በኩል በአንድ ቀን የተሠራ ሃይማኖት ስሌለ አለስፈላጊ ሃይማኖታዊ ስንጥቆችን መፍጠር በራሱ የተገባ አይደለም። ግጭት ጠማኝ መሆን የተገባ አይደለም። ኢትዮጵያዊ ነኝ ካልኩኝ ሁሎችም የእኔ የውስጤ ናቸው ማለት ይገባኛል። አይደለም የሚያምነው ሃይማኖት ያለው፤ ሃይማኖት የሌለውም የማያምነውም ቤተ - እኛዊነት ነው ብሎ መቀበል ይገባል። ኢትዮጵያዊነትን መተርጎም በራስ ውስጥ ነው በአሻጋሪ እጣትን ቀስሮ ክስ ከመላክ።  
በሌላ በኩል „ቂም ይዞ ጸሎት ሳል ይዞ ስርቆት“ ለዝምብሎ የተቃኜ አስተምህሮ አይደለም። ድካሙ ተንጠልጥሎ እንዳይቀር ሐዋርያ ነው ተምሳሌቱ። ቂመኛ ከተሆነ ቅንነት ከሌላ መንገዱም ዳጥ ውጤቱም ምጥ ነው የሚሆነው። ለዛውም ፈተና ዙሪያ ገባው ባለበት፤ ፈተናው ረቂቅ በሆነበት ሁኔታ እንዲህ ባለ የግብር ይወጣ ጉዞ ጥምዙን፤ ቅይጡን መሰናክል ማለፍ አይቻልም። ከሁሉ በፊት ሁሉም እራሱን ሊያሸነፍ ይገባል። ቂመኛ አለመሆን፤ በቀለኛ አለመሆን። ይህን መሆን ሲቻል አቅም ይፈጠራል፤ ድካሙም እዮር ያዳምጠዋል። ስኬትም ይሆናል። ትውልድም ይተርፋል።  
በጎደፈ፤ በአጎረፈ፤ በአጎፈረ ህሊና አገርን፤ የትኛውንም ሃይማኖትን፤ ትውልድን፤ ትውፊትን፤ ታሪክን ማትረፍ አይቻልም። በፍጹም። ሌላው ክፉ ይሁን ስለምን እኔ ክፉ እሆናለሁኝ? ሌላው ቂመኛ ይሁን ስለምን እኔ ቂመኛ እሆናለሁኝ? ፈጣሪ ሲፈጥረኝ ክፉም ቂመኛም ሁኚ ብሎ አይደለም። 
ስለዚህ የተሰጠኝን መንፈሳዊ ቅዱስ ጸጋ አጽድቆ ማስቀጠል ህሊናዊ ግዴታዬ ሊሆን ይገባል። እኔ እማምነው እንዲዚህ ነው። ክፋትም፤ ሽንገላም፤ ቂመኝነትም መልካም አይደለም። ይህን የሚከተሉ ሲኮስሱ እንጂ በሃሳብ በልጽገው ረድኤት ሲፈስላቸው አይታይም። ዲታነት የመንፈስ እንጂ የማዋለ ገንዘብ አይደለም። ወይንም የዝና ተራራ አይደለም። ዝና የሳሙና አረፋት ነው።
·       ቢሆን - ትህትናዊ ተማህጽኖ።

የኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ብታደርገው ብዬ እማስበው።
(1)           እሳት ላይ እንደ ተቀመጠች አምና ትቀበለው። ለዚህ ዕውቅና ትስጠው።
(2)           ችግሩን ግለሰባዊ አድርጋ ባታዬው ጥሩ ነው፤ ድንገቴ አድርጋም
             አትሰበው፤
(3)            ከእህት አብያተ ቤተክርስትያናት ጋር ያላትን ግንኙነት ታጠናክር።
(4)           ከሌሎች የሃይማኖት አቨው ጋር ያላት ግንኙነት የሚያስመሰግን ስለሆነ፤ መከራዋን ተጋርተው በጸሎት ይረዷት ዘንድ በትህትና ከማሳሰብ አትቆጠብ።
(5)           ምዕመኗ በንቃት ሁሉን ነገር ይከታተሉ ዘንድ ታስተምር። በጸሎትም እንዲተጉ አበክራ ትናገር።
(6)           ከፌድራል የሚሰጣትን ማናቸውም አዛይ ውሳኔዎች ሳትመረምር፤ ሳትጸልይበት፤ ጥሞና ሳትወስድበት አትቀበል። ያልተገባ የ ኦሮምያ ክልል ትዕዛዝ ሲመጣም አትቀበል። እነሰብስብሽ እንዘዝሽ ሲመጣም ከኦሮምያ ሹመኞች አሻም ማለትን ትልመደው። ከመሄድ ሃይማኖቱን ታስከብረው። ክብሯን ጣል ጣል አትድርገው።
(7)           ባለቤት እንደሌላት ትቀበል። ለዚህም ዕውቅና ትስጠው።
(8)           አቅም እንዳላት ግን በአጽህኖት ትመን። ለዚህም ዕውቅና ትስጠው።
(9)           የጥበብ ጸጋ እንዳላት፤ ባለ መክሊት እንደሆነች ትመን፤ ዕውቅናም ትስጠው።
(10)      የህልውና ፈተና ላይ እንዳለች ዕውቅና ትስጥ።
(11)       ሰላማዊ ትግል ትጀመር። እኔ ሰላማዊ ትግል ከምላቸው ውስጥ በመስከረም፤ በጥቅምት ወርም ላይ የጻፍኩት የደወል ምህላ መጀመር እንዳለባት ነው። በሳምንት አንድ ቀን ለአንድ ሰዓት ያህል አቤቱታዋን በደወል ታሰማ። 
    ለደወል አንድ ደዋይ ብቻ ነው የሚያስፈልጋት። ምዕምኑን ማስወጣት አያስፈልጋትም። ልጆች በማይተኙበት፤ ሥራም በሌለበት ቀን ለምሳሌ ቅዳሜ ዕለት በዬሳምንቱ ከቀኑ 11 እስከ 12 ሰዓት ያልተቋረጠ በሁሉም አብያተ ቤተክርስትያናት የደወል ሥርዓት ብትፈጽም ታተርፍበታለች።
(12)       ደወል!  
. ለእዮር አቤቱታ ነው።
. ለፌድራሉ መንግሥትም አቤቱታ ነው።
ሐ. ለምዕምኑም ማንቂያ ነው። ቢያንስ በደወሉ ደቂቃ ሁሉም በያለበት ወደ አምላኩ አቤት ይላል። ምን ዘመን ልበለው? የመቃብር ሥፍራ ዘመን ላይ እንዳለን ይሰማኛል። መሪዎችን ሳይሆን ዘመኑን እዬፈራሁት ነው።
እኔ እንደማስበው ፌድራሉ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ለኦሮምያ ክልል የሸጣት ነው የሚመስለኝ። በዛ እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሥር እንደ ወደቀች ነው የሚሰማኝ። ያ ማለት የአርሲ ነገሌ ጉዳይ ሰተት ብሎ ይመጣል ነገ ማለት ነው። በሁሉም ቦታ። ይህን ጠብቁት። ደረጃ በደረጃ ይህ ሳጥንኤላዊ እርምጃ እያለማመደ ሁንሉም ያደርሰዋል። ተደሞ፣ ጥሞና ያስፈልጋል። ጠንክሮ መጸለዬም። ጸሎት የደነገለ ህሊናን ይሻል።
·       አርሲ ነገሌ ላይ መስቀል አለቀሰ። የአርሲ ነገሌ ጉዞ ወደ ቀራንዮ!



   





ቅድሷቷ ደሟን ገብራ ባቀናቻትም፤ ባቆዬቻትም አገር እንዲህ ስደትተፈረዳባት። ውግዘት ደረሰባት። እዛ የሚኖሩ የዬኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኗሪዎች እንደሚገልጹት ከሆነ እያንዳንዱ ቀን በስጋት ውስጥ፤ እያንዳንዱ ሰከንድ በፍርኃት ውስጥ ሆነው ለቅሶ ላይ እንዳሉ ነው ሲጽፉ እማነበው። አሁን ጥምቀትን እራሱ ከመምጣቱ በፊት በጣም ፈርተውታል።
ልጆች እራሳቸው „አገራችን የት ነው?“ እያሉ እዬጠዬቁ እንደሆነ ነው አማነበው ፌስቡክ ላይ። እሰቡት ልጆች አገራቸው መሬት ተቀምጠው „አገራችን ወዴት ነው?“ ብለው ሲጠይቁ። ይህ መራራ ነገር ዛሬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አቅም ሳላት መመከት ካልተቻለች ነገ ከመሰረቱ የመነቀል መከራ ይኖራል። መፍለስ እኮ የደቂቃ ሥራ ነው። ማጥፋትም እንዲሁ። መገንባት ነው ከባዱ ተግባር።
መስቀል እንዲህ ሲያለቅስ? መስቀል እንዲህ ሲከፋ? መስቀል እንዲህ ሆድ ሲብሰው? መስቀል እንዲህ ሲሰቃይ? መስቀል እንዲህ ሲነቀል፤ መስቀል ወደ ቀራንዮ ሲጓዝ ቅድሰት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አገር አለኝ ብላ ዝምታን መመረጧ እጅግ ያሳዝናል። እጅግም ያስፈራል። እጅግም ያርዳል። እጅግም ያዋርዳል። ዛሬ አርሴ ነገሌላ ማህበረ ምዕመኑን ሄዶ ለማጽናናት እንኳን ፈቃድ አይገኝም።
·       ተጨባጩን እንደ ሐዋርያ ብንወስደውስ? 
የባዕለ መስቀል አከባበር በ2011 ዓ.ም በስቃይ ላይ ነበር የተከበረው። መስቀል በስቃይ ተከብሮ እሬቻ ግን በሰናይ ነበር የተከበረው። ኮሽ ሳይል።
ሾግ እና ብርሃኑ አለቀሱ።
በ2012 ዓ.ም መስቀል በጫና ተከብሮ እሬቻ ግን በዕልልታ በብሄራዊ ደረጃ ነበር የተከበረው። መስቀል ደብረዘይት ላይ ማክበር አልተቻለም። ብጹዐን አባቶቻችን ታግተው ነበር የዋሉት። ምዕምኑ በስፋት እንግልት ደርሶባቸዋል። እናቶች ተጎድተው ሁሉ አይቻለሁኝ። 
ለወደፊት የኦሮሙማ ሥርዓዎ መንግሥት መስቀልን በብሄራዊ ደረጃ በሂደት ለማክብር ይፈቅዳል ወይ? ጊዜ የሚፈታው ቢሆንም እኔ ኦሮምያ ክልል ነው በሚባለው ላይ በሚቀጥለው ዓመት እራሱ የሚቀጥል አይመስለኝም። በዚህ ውስጥ ብሄራዊ ሰንደቃችን ተቃጥሏል፤ ተወርውሯል። በእግራቸው እርግጥግጥ አድርገውታል።
አዲስ አበባን ሰው አላወቀም እንጂ በማያስጠጣ መልኩ ለኦሮምያ እርክክብ ተፈጽሟል። ድርድሩ ይሄው ነው የአብይ ሌጋሲ እንዲቀጥል ከፈለገ። ለዚህ ነው መታበዩ ጣሪያ ነክቶ ምድር አልበቃው ያለው መንፈስ የአቶ ሺመልስ አብዲሳ የዕለት ውሎ በድንፋት የታጀበ ከመሆን አልፎ በቅድስት ኦርቶዶክስ ታላቅ ጉባኤ የመገኘቱ ሚስጢር።
በሌላ በኩል ገመናው እንዳይጋለጥም ሚስጢሩ እንዳይዘረገፍ የአነ አቶ ለማ መገርሳ በቅዱስ ሲኖዶስ የመገኜት ሚስጢርም ይህው ነው። ይህም ብቻ አይደለም አቶ ለማ መገርሳ ኦሮምያን ይመሩ በነበረቡት ጊዜ የሁሉም ሃይማኖት መሪዎች ያሉበት ልዑክ ወደ ትግራይ እና ወደ ባህርዳር ሲላኩ ከእሳቸው ነበር መመሪያ የተሰጠው። ምን ማለት ነበር? አባቶቻችን ይህን እንደ ሊቀ - ሊቃውነትነታቸው ሳይታደሙበት አልፈውታል። ኦሮምያ ለብሄራዊ ሃይማኖታት ምን መብት አለው መመሪያ የመስጠት?  
ለምን ስትሉ? ሁሉም ብሄረዊ ኃይማኖቶች መቀመጫቸውን አዲስ አባባ ያደረጉ በኦሮምያ ክልል ሥር ስለመሆናቸው ለማመሳጠር ለማጠዬቅ ነው ድርጊቱ በዛ መልክ የተፈጸመው። ተኝቶ ለሚያዳምጥ ሊታዬው አይችልም። ነቅቶ ለሚጠብቅ ሁሉም ነገር በታቀደው ሁኔታ እዬተከወነ ስለመሆኑ ተርጓሚም፣ አመሳጣሪም አያስፈልገውም። የቀረው የዲፕሎማሲ ማህበረሰቡ ደግሞ ቀስ እያለ ይቀጥላል ከእኛ ፈቀድ ውጪ መግለጫ ማውጣት አትችሉም ይመጣል። ይህ ሟርት አይደለም። ብዙም ሳይቆይ የሚታይ ይሆናል።
ነገረ አርሲ ነገሌ ሲከወን በአደባባይ ከእንግዲህ መስቀልን ማክበር ተከለለከለ ማለት ነው። ማክበር የሚችሉት እስከ ተወሰነ ጊዜ በፍርኃት ውስጥ ሆነው በቤተ ክርስትያን ብቻ ይሆናል። አሁን ይህን ስታስቡት ዘመናዩ የጠሚር አብይ ንግግር ሊዋህዳችሁ ወደ ህሊናችሁ ይመጣ ይሆን? የሳቸው ድርጅት ነው ይህን ሁሉ የሚያደርገው። 
·       በውጭ የሚኖሩ ማህበረ ምዕመን ሚና።
በውጭ የሚኖሩ ማህበረ ምዕመናን በሙሉ በአንድ ልብ ሆነው ለሚችሉት አካላት የማሳወቅ ብርቱ ኃላፊነት አለባቸው። ኃይማኖት የትውልድ ትውፊት ነው። ትውፊትን የማስቀጠል ሃላፊነት ደግሞ በቸልተኝነት ሳይሆን በንቃት በሚደረግ ተሳትፎ ነው። ሃይማኖት እኮ የውስጥነት ገዢ ፍጹም ልዕልና ያለው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው። ሃይማኖት ባይኖር ብላችሁ ዓለምን እሰቧት ሽርክት ትሆንባችሁ አለች።
„እጃችሁን ለእግዚአብሔር ሥጡ፣ ለዘላላም ወደ ተቀደሰው ወደ መቅደሱ ግቡ፤ ፅኑ ቁጣውም ከእናንተ እንዲመለስ አምላካችሁን እግዚአብሄርን አምልኩ።“ (መጽሐፈ ዜና ማዋዕል ካልዕ ምዕራፍ 30 ቁጥር 8)
·       እያለንም እዬሞትንም እስረኝነት?

በ09.01.2020 ኢትዮ 360 በነበረው ዝግጅት አንድ ማህጸኔ ያለቀሰበት ነገር አዳመጥኩኝ። እሬሳ ይዞ ወደ ኦሮምያ ለመሄድ የዞግ ቢዛ? ምን እዬሆን ነው? እያለንም እዬሞትንም እስረኝነት። የፖለቲካ ተንተኙ አቶ ሃብታሙ አያሌው እንደ እናት ሆነው ያሳደጉት ጎረቤታቸው በዞጋቸው ኦሮሞ ናቸው፤ እህታቸው አርፈው ወደ ደብረዘይት ለቀብር ሄዱ፤ ወንድማቸው ሜዲካል ዶር. ስለነበሩ ከሳልስት ሃዘን በኋላ ወደ ሥራ አዲስ አባባ መጡ፤ ከሥራ መልስ ወደ ደብረዘይት መሄድ ፈለጉ። 

ነገር ግን ማህል ላይ በቅርቡ በተነሳው የቄሮ አመጽ መንገድ ተዘግቷል፤ እህታቸውም ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ፈልገው መንገድ በመዘጋቱ  አልቻሉም። ወንድማቸው ወደ ደብረዘይት መመመለስ ቢፈልጉም ባለመቻላቸው ከጎረቤት ተጥገተው አደሩ። በጥዋት ከተኙበት ሞተው ተገኙ።


ሰፈርተኛው አብሮ እሬሳውን ይዞ ለመሄድ ቢፈቅድም ነገር ግን ኦሮምኛ መናገር ካልተቻለ ይለፍ ማግኜት ሰለማይቻል ቋንቋ የሚችሉ የኦሮሞ ወገኖቻችን ተመርጠው በአባ ዱላ አውቶብስ መስኮት ተከፍቶ በዬኬላው እዬተፈተሹ በኦሮምኛ እዬተናገሩ ለቀበር በዛ መልክ ወደ ደብረዘይት ሄዱ። እሰቡት እሬሳ ይዞ ለመሄድ የቋንቋ ቢዛ የበቀለ መርዛማ ማንፌስቶ እንዲህ እዬሰራ ነው።

ሃዘንን ለማጽናናት እራሱ እንዴት እንደ ተሸነሸን፤ እንዴት እንደተቆራረጥን፤ እንደምንስ እንዳነስን? እህት ለመመለስ መንገድ ተዝግቷል፤ ወንድሞ ለመሄድ መንገድ ተዝግቷል በማህል ካለቀጠሮ ተጨማሪ ሞት መጣ፤ እሬሳ ይዞም ለመሄድ የቋንቋ ቢዛ። 

እህት እህትንም ቀብራ የወንድም ሬሳው ደግሞ ተጨመረበት። ይህን መከራ አይደለም ተኮራርፍን፤ አይደለም ተራርቀን፤ አይደለም ተነኳኩረን፤ አይደለም ፊት ተነሳስትን፤ አይደለም በስሜት እንጥሩብ ዘለን፤ ሰክነን፤ ስሜታችን ገዝተን፤ እንደ አንድ ልብ መክረን አንድ ላይ ሆነንም ተረዳድተንም አናልፈውም።

በዚህ ምንዛሬ የቤተ - መንግሥቱን የድግሥ ውሎ፤ የምርጫ መለከት፤ የዴሞክራሲ እንጡርብ ዝላይ የሚያሰኘው የወግ ገበታ፤ የሚደያው ኦርኬስተር እሰቡት። ህዝቡ ያለበትን የመንፈስ ድቀት እና እገታም አሰተውሉት። በማን ነው የተወረርነው?! የትኛው መንፈስ ነው እዬገዛን ያለው? የገዢያችን ቃናው ምንኛ ነው? 

·       ምስራቅ ሀረርጌ የክርስትና እምነት ተከታዮች የቤት ቃጠሎ።

ከሰሞናቱ ፌስ ቡክ ላይ አዳምጬው ነበር። ግን እውነትነቱን ማረጋገጥ ስለነበረብኝ ቆዬሁኝ። አንዳንዱ መረጃ ካልቅጥ ይገናል፤ አንዳንዱ ጭራሽ ሃሰት ይሆናል፤ ሌላው ደግሞ ተንኳሶ ይቀርባል። ስለዚህ ሁነኛ ምንጭ እስኪገኝ ረጋ ብሎ በማስተዋል ቆይቶ ሃሳብ መስጠት ያተርፋል።

ስለ እረጋሁኝም ትናንት ምሽት ላይ በኢትዮ 360 „ፖለቲካችን“ የ11.01.2020 ፕሮግራም ሳዳምጥ መረጃው ትክክል ነበር። ምስራቅ ሀረርጌ ላይ ዬክርስቲያኖች ቤት እየተለዬ 12 ቤቶች ተቃጥለዋል፤ ይቀጥላልም ነው ስጋቱ። እንዲሁ ተጨማሪ የመረጃ ማረጋገጫ ያለገኜሁለት ኢሊባቡር ዞን ዳሪም ወረዳ ላይ የደረሰ የቤት ቃጠሎ ጥር 3 ቀን 2020 አንብቤ ነበር። ጉዳትም የልጆች አለበት እንዲሁ።


በዚህም በዚያም የሚደመጠው አሰቃቂ፤ አስፈሪ ዜናን ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እዬለመደችው የሄደች ይመስላል። ምጽዕተ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ይለመዳልን?! ቢያንስ ስለዘመኑ ልታለቅስ ይገባታል። በተከታታይ ልታለቅስ ይገበታል። አገር የምትድነው በሠራዊት ብዛት አይደለም በፆም በጸሎት ነው። 
 
·       የኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ እና ተተኪወቿ ሰማዕትነት ዘወትራዊ መሆን።
                                   ሰማዕት ሱራፌል ሰለሞን።

በሌላ በኩል አንድ ወጣት በአዋሳ ዩንቨርስቲም በስለት ተወግቶ ሞቷል። ሰማዕት ሱራፌል ሰለሞን ይባላል። የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዘማሪ የነበረ ነው። ይህም ብቻ አይደለም ትምህርት በሚሰጥበት ቦታ የፆም ምግብ አይዘጋጅላቸውም ተብለው እንዲገድፉ ይገደዳሉ ልጆቿ፤ ይህም ጉዳዮዋ ሊሆን ይገባል። ይህም አጀንዳዋ ሊሆን ይገባ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በእዬ ዩንቨርስቲዎች የሚታገቱት፤ የሚገደሉት፤ የሚሰደዱትም፤ የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ወጣት አማንያን ናቸው።

እራሱ ለቀው እንዲወጡ ሲበይንባቸው ኦሮምኛውን ተርጉመው የነገሯቸው በደንቢ ደሎ የተዋህዶ ልጆች ዞጋቸው ኦሮሞ የሆኑ ስለመሆናቸው ከሚዲያ አዳምጫለሁኝ። በዚህ ውስጥ የሚታዬው የአንድ ህዝብ ጭንቀት፤ የፍርኃት አኃቲነት ግን ሁሉም በሚችለው አካሉን፤ እትብቱን ለማትረፍ፤ ያለውን ለማድረግ ጥረቱን ስትመለከቱ የኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ልጆች ዞግ ሳይለያቸው ወላዊ ማተባዊ ጭንቀት ውስጥ መሆናቸውን ነው። የኔታዋ ሙጫውን የማስቀጠል ተግባር ደግሞ የእሷ ነው።

የኔታዋ ልጆቿን ነፃ የማስወጣት ታላቅ ተጋድሎ ማድረግ ይጠበቅባታል። ልጆቿን ብቻም ሳይሆን በሰውኛ እሳቤ የጠፉ ነፍሶችን ሁሉ ልትታደግ ይገባታል። ባህርዳር ላይ በነበረው ህዝባዊ ስብሰባም „አባቶቻችን እንደ ሰማዕቱ ጵጥሮስ ሁኑ“ ዬነብዬ ብ/ጄ አሳምነው ጽጌ የመጨረሻ የአንደበታቸው ቃል ነበር። „የመጨረሻውን ቃል ለጀግናው ተውለት“ የቅኔው ልዑል፤ የኢትዮጵያዊነት ጽላት የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ትንቢት ይፈጸም ዘንድ።

ጎንደር ላይ በነበረው ህዝባዊ ስብሰባም „በቅባት እና በካራ“ አዲስ ጦርነትም ሊኖር ይችላል ሲሉ በጥልቀት የችግሩን የቅደም ተከተል አመጣጥ ተንብዬው ነበር ነብዬ ብ/ ጄኒራል አሳምነው ጽጌ። 

ይህን በኽረ ጉዳይ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊው ዲሞክራት ንጉሥ ደጉ አጤ ፋሲል በዘመናቸው በጥበብ ሊቀ - ሊቃውንቱ ተሰብስበው እራሳቸው ተወያይተው በአመክንዮ ተሟግተው አምክነዎት ነበር። „ ብ/ጄኒራል አሳምነው ጽጌን ነብዬ ቃሉን አልሰረቁኩኝም ከሰኔ 15 ጀምሮ ፌስቡኬ ላይ የምጠቀምበት ቃል ነው“ እኔን የሚሰማኝ እንደዛ ስለሆነ። ያልታዩ ግን ሊታዩ የሚችሉ፤ ሊጠፋ የተፈለገ ግን አልጠፋም ብሎ እራሱን እዬገለጸ እዬሞገተም ያለ ሃቅ ስለአለ።

ይህን እያዳመጠች ቅድስት ኦርቶዶክ ተዋህዶ ምን ትጠብቃለች?  ቢያንስ አቅሟ ደወል ነው። ትደውል! ትደውል! ትደውል! ደወሏን ብቻ በሳምንት አንድ ቀን ሥራ ላይ ታውል። አዲስ አበባ ብቻ ማድረግ ትችላለች። ሌላ ቦታ ሳትሄድ። የሚያስፈልጋት አንድ ደዋይ ነፍስ እና ዕለተ ቅዳሜ ብቻ ነው። ወጪ የለባት ምን የለባት።

ጀንበር ስታዘቀዝቅ ከ11.00 እስከ 12.00 ሰዓት ለአንድ ሰዓት ያልተቋረጠ ደወል መደወል በቂ ነው። ደፍራ ትጀምረው። ከዛ የኦሮምያ ፖሊስ ደግሞ መግለጫ ያውጣበት እና „ቁርጥ ያጠግባል“ እንደሚሉት ልባሞቹ ጎንደሮች ቁርጧን ትወቅ። 

 በክንብንብ ተሸፍንፍኖ ያለው ገመና ይገለጥ እና በመሬቷ ላይ የመብት ደረጃዋን ትወቅ። እሷስ „በመጤነት“ ተፈርጃ ስለመሆኑ ምን ታውቃለች እና? ብዙ የተተበተበ ገመና ነው ያለው። ለማፍታት ደግሞ ሰማዕትነት ይጠይቃል።

·       እርገት ይሁን።

የኔታዋ አሁን ባለው አቅም እና ተቀባይነት ካልተጠቀመችበት የሚከተላትን ማህበረ ምዕመን ሁሉ ሙሉ አቅም ልታጣ ትችላለች። ዕውቅናዋም ሊቀንስ ይችላል። እራሷን ለማዳን ሰንፋ ነው እማያት። በቤተ - መንግሥት ሽንገለ ዝላ ነው የማያት። በቃላት ብርንዶ ተዘናግታ ነው እማያት። 

አይሰማ ነገር የለም፤ እነሱ ከእሷ በጥበብ በልጠው እዬመሯት ነው እነ አቶ ሽመልስ አብዲሳ። ግን ታውቀዋለችን የኔታዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ በማን ሥር መሆኗን? „ልብ ያለው ሸብ“ እንደ ጎንደሮች። ሁለመናው በተከታታይ መከወን አለበት። ጸሎቱ፤ ምህላው፤ ሱባኤው፤ ስግደቱ፤ ሱባኤው።

ወስብኃት ለእግዚአብሄር።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።