እንባ ያቆረዘዘው የ2011መስቀል።
ሹግ እና ብርሃኑ አለቀሱ።
እጃችሁን ለእግዚአብሄር ስጡ፤ ለዘላላሙ ወደ ተቀደሰው ወደ መቅደሱም ግቡ፤
ጽኑ ቁጣውም ከእናንተ እንዲመለስ አምላካችሁን እግዚአብሄርን አምልኩ።
(መጸሐፈ ዜና መዋዕል ምዕራፍ ፴ ቁጥር ፰)
ከሥርጉተ©ሥላሴ
28.09.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።
የዕባማውም ሹግ ግማድ ጉሽ!
ከቀደሙት ዓመታት መስቀል ሳይመስለኝ ያለፈው የዘንድሮው የ2011 ነው። ፈጽሞ ጠረኑ ድብርት እና ደመመን ተጭኖኝ ነው ያለፈው። ቤተሰቦቻቸውን ለማዬት በተጓዙ ኢትዮጵውያን የደረሰው የመኪና አደጋ ማግስት ነው ባዕሉ የተከበረው። እንደ ብሂሉ ባሳብው „እንዳያም ጥራው እንዳይበላም ግፋው“ ዓይነት ሆኖ ውጥረት ተፈቅዶለት ተከብሯል። ሁሉም አምጦ እንዳከበረው አስባለሁኝ። የመርዶ ያህል መጪውን ጊዜ እያሰበ … በ ዕንባም ሰምጦ።
እኔ የ2011 የደመራ ባዕል ያለቀሰው የመስቀል ባዕል ብለው ይሻላል። ከሁሉም ዘመን እጅግ ጫና እና ውጥረት በብሄራዊ ደረጃ በበዛበት ሁኔታ የታሰበበት በዓል ቢኖር ዘንድሮ ነው። እርግጥ ነው የአማራ የማንነት የህልውና ተጋድሎ በተካሄደበት ወቅት በዕሉ በጎንደር ተሰተጓጉሏል፤ ጫናውም በብሄራዊ ደረጃ እንደ ነበር ባስታውሰውም፤ ያን ጊዜ የነፃነት ፈላጊው ጉልህ መንፈስ ጎልቶ ሲሆን አሁን ግን ማተቡንም የሚያፈታተን የልታወቀ መንገድ እዬናጣው ነው አዬሩን ነው የታሰበው... ወዮልሽ ቤተሳይዳ!
ለነገሩ የ2011 የሬቻ ባዕልስ የሚለውን ለሚዛን ግብረ መልስ ነገ የሚሰጠን ይሆናል?
ያን ጊዜ በዘመነ አማራ ተጋድሎ ባህርዳር አንድ ብጹዑ አባት እዮር ልኮ ልጆቻቸውን በመንፈሳቸው አቅፈው እና ደግፈው አጽናንተው እና አበረታተው፤ ችግሩን አብረው ተጋረተው ከጎኑም ተሰለፈው ነበር፤ የብፁዑን አባታችን የአቡነ ጵጥሮስን ገደል በመቀበል ስለ ዕውነት ቁመው የቁም ሰማዕት ሆነዋል ቅዱስ አባታችን አቡነ አብርሃም። መቼም የዘመን ጽላት ናቸው። በተገኙበት ሁሉ መፍትሄ።
የሆነ ሆኖ በዬአካባቢው በምን መልክ እንደ ተከወነ ዜና የለም። የቀዘቀዘው፤ የበረደው፤ ተስፋ የተፋቀበት ድብልብል አዬር ነው ያለው። እኔ ካላፈው ዓመትም በባሰ ሁኔታ ወስጤን ደመና ወሮት ነው ያሳለፍኩት።
የምወደውን መጻፍ አልችል ብዬ፤ አቅም አንሶኝ፤ ሌላው ቀርቶ የተፃፉ ብዙ ነገሮች አሉኝ፤ እሱን እንኳን ለመለጠፍ ደከመኝ። ቀላሉ ሥራ ለእኔ መጻፍ ነበር። ይህም አልሆን ብሎ ዝም ብዬ በጸጥታ አሳለፍኩት። ዋዜማውም ዋዜማ ሳይመስለኝ፤ ዕለቱም ዓውደ ዓመት ሳይመስለኝ ብክነት የወረረው …
የሆነው ሁሉ የክርስትና ዕምነት ጫና እንዲበዛበት የተደረገበት ሁኔታ ነው - ለእኔ። የጃዋርውያን መንፈስ ሁለመናን እዬተቆጣጠረ ያለ ይመስላል። እሱ ፈንድቋል። እንድለመደበት እያጣጣምኩትን ነው ደስታዬን ሳይል አይቀርም።
እሱም ተዳፍሮ ነግሮን ነበር። ሬሳው መግባት የማይችለው ሁሉ ሲል … ያ ለማን እንደሆን ልብ ያለን እናውቀዋለን። ግን የእሱ የኔት ትግል ሳይሆን መሬት ላይ ደማቸውን የገበሩበት እንደ አርበኛ ጎቤ የመሰሉም ያሉበት ገድል ስለመሆኑ እራሱም ያውቀዋል። ክህደት ጁባ እና ሱሪው ቢሆነም።
የሆነ ሆኖ ድህነታችን ያመጣው መከራ ሲቀጥል ምን ሊሆን እንደሚችል ፈጣሪ ይወቀው። አብሶ በማተባችን ዙሪያ። ዛሬ ሳቅሳቅ ቢላትም ነገም እትጌ ኤርትራ ወዮላት ነው። ይህን ቀደም ባሉት ጹሑፎች ኮልሜዋለሁኝ። ለ እስልማና ዕምነት ተከታዮች አብሶ ለአንስት የጥበብ ሰዎች ፈታኝ ዘመን እንዳይመጣ ስጋቴን ዘርዝሬ ጽፌው ነበር።
ኢትዮጵያ እንደ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ዘመን በሯን ለሁሉም እንዳሻው እንዲሆን ከፍታ አታውቅም። አባቶቻችን እጅግ ጠንቃቆች ነበሩ። ጥንቃቄያቸው ደግሞ ሴቶች የቅርብ አማካሪዎቻቸው ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን ሴቶችን የማድመጥ አቅሙም ስለነበራቸው ነው። በወንዶች ዓለም የፖለቲካ ስልት እና ጥበብ ደግሞ ቢኖርም ሴራውን ዘልቆ መቅደም አልተቻለም።
የሆነ ሆኖ ባዶ ካዝና የተረከቡት ቅኑ ጠ/ ሚር ዶር አብይ አህመድ ጉሮሮ ማርጠቢያ ፍለጋ ያደረጉት ጉዞ ገና በዋዜማው ይህን ያህል መጫንን ከማጣ ነገስ ወደሚለው ይወስደናል። እንደ እኔ መፍትሄ ይሆናል የምለው ዘራፊዎች የዘረፉትን ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቢያስገቡ ከመንፈስ ጥገኝነት የሚያወጣት የተሻለ ዕድል ይኖራል።
ምክንያቱም በቀጣዩ እርምጃ ተራፊ ሊኖር ስለማይችል። ያልተቋሳለ የለም። በቁርሾ የበከተ መንፈስ ነው ያለን። ነገ አሻናፊው ተሻናፊውን በዝም ብሎ በይቅርታ፤ በፍቅር፤ በምህረት ብሎ ነገር ከውጥኑ ነው የሚደረመሱት ጃዋርውያን። ጃዋርውያን የሰነቁት ሰፊ የመከራ ውቅያኖስ አለ። ኔቱ መረቡ እጅግ ሰፊ ነው።
የሆነ ሆኖ ዲታዎች፤ ባለሃብቶች አገርን በኢኮኖሚ የመደገፍ እርምጃዎች መወሰድ ካልጀመሩ ነገ የፖለቲካ ድርጅት፤ የብሄር ብሄረሰብ፤ የፆታ፤ የክልል፤ የዕውቀት ጉዳይ ሳይገድብ ክርስትና ቀራንዮ ስለመዋሉ አይቀሬ ይሆናል። ቀለል አድርገው የያዙም የ እስልምና ዕምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ዕምነት የሌላቸውም ዎዮ ነው።
የፖለቲካ አቅም፤ ጸጋ፤ መክሊት፤ የማድረግ ክህሎት በራስ ውስጥ መኖር የሚወስነው በኢኮኖሚ አቅም ብቻ ነው።
ይህን ያህል ጃዋርውያን የተንሰራፋ አቅም እና አቋም ላይ ያደረሰው ሚስጢር ይኸው ድህነታችን ያመጣው ጦስ ነው። ጃዋርውያን መግቢያ ደግሞ ጭብጥ አለ። ካልኩሌተሩን እኔ ሠራሁት የመደመሩን ሲል ከእሱ መንፈስ ጋር የተደመረውን የውጭ አገር ሃይማኖታዎ ዝንባሌ ያላቸውን መንግሥታት ማለቱ ነው።
ከዚህ ባሻገረ መሳጫ የሚሆኑ ቅርጥምጣሚዎችም አሉ ለማስረጃ - ሆነ ለማቀራረቢይ። ቅኑ ጠ/ ሚር ወደ ሥልጣን ሲመጡ ሚዲያዎች ሲያጮበኹት፤ ሲያብጠለጥሉት የነበረው ቤተሰባዊ ጉዳይ ነበር። ያ ነው አሁን እዬተፈጸመ ያለው።
ክፉው መንፈስ አገር ከገባ ማግሥት ለውጭ ግንኙነት ይፋዊ ፊርማ ነበር ወደ አረብ አገር የሄደው፤ ለሃጅነት አልነበረም። ቀድሞ ነገር በ እሳላሚ ሃይማኖታዊ ቀኖና ዶግማ እኮ ዶር አብይ አህመድ ኤክስፐርት ናቸው። መንፈሱም ሚዛናዊ ነው።
ብቻ ከስሜን አሜሪካ የጠ/ ሚሩ ጉዞ መልስ ያለው ሁሉ ነገር በቅድመ ሁኔታ የታሰረ ነው። እኔ በተደጋጋሚ ጽፌዋለሁኝ። ለቀቅ ሲሉ ይገቷቸዋል። ማህለቁ ያለው ከገንዘብ ለጋሾቻችን መዳፍ ዘንድ ነው። ይህን ጥቃት ማውጣት ያልቻለ ኢትዮጵያዊ ዲታ ቢሞት ይሻለዋል። የቁሙም እሬሳ ነው። እርግጥ አሁን አስተማማኝ ደህንነት አለ ወይ የሚለው ደግሞ ሌላ ጥያቄ ሊሆን ይችል ይሆናል?
በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አንድ መሆን፤ ክርስትና እስልምና ሃይማኖት ሊቃናት አንድነት ሰላም ያልሰጠው ያ የጃዋርውያን መንፈስ ሥራውን መሥራት የጀመረው ከሰኔ 16 ጀምሮ ነው። ያን ጊዜ ደግሞ ተንተኝ ሆኖ ወጥቶ ነበር።
የሐምሌ 19 የጠራራ ጸሐይ ግድያ፤ የጅጅጋ ቀውስ እና የአብያተ ቤተክርስትያናት ፍዳ፤ የአባቶች ሰማዕትነት ብጹዕን ቅዱሳን አባቶች በቦሌ ሲገቡ የፈጠረው ቁርሾ ነው፤ ከዚህም ባለፈ የሻሸሜነው ገመና፤ ሁሉን ባሻን ጊዜ እንዳሻን እንሆንበታለን ማን ከልካይ አለብን ለማለት ነው። ከቡራዩ የደም ዕንባ ማግሥት የመስቀል ደመራ የተደመረውም በዚህ የደም አደባባይ፤ የደም ምጥ እና ዳጥ ሰሞናት ነው።
የዘንድሮው ሃይማኖታዊ ትውፊቱ እራሱ በተሟላ ሁኔታ ተከብሯል ብዬ ማሰብ አልችልም። እንዲያውም ተቀይጧል፤ መሠረቱንም ስቷል። ነጭ ሠራሽ ርችት ምኑ ነው ለኢትዮጵያዊው መስቀል? ዲኮ ነው።
እርግጥ ነው ገጠር አብሪ ጥይት ይተኮሳል በአማራው ክልል፤ ዋዜማው ላይ ወጣት ወንዶች ሹግ አብርተው እንኳን አደረሳችሁ ይላሉ በዬሠፈሩ፤ ከዚህ ባለፈ በገጠረ ሌሊቱን ሙሉ ጅራፍ ይጮሃል። በደቡብ ደግሞ በተለዬ ህብረ ቀለማት ቤተሰባዊ ዕሴቶችን ጠብቆ ይከበራል። መስቀል በመላ ኢትዮጵያ ከገጠር እስከ ከተማ የሚከበር ታላቅ ብሄራዊ ባዕል ነው።
በዋዜማው ወይንም በማግስቱ መስቀል ይደመራል በአደባባይ። እንደ ጎንደር ባሉት ከገጠር እስከ ከተማ ድረስ ባሉት ደግሞ ሠፈርተኛው በወል ሆኖ ይደምራል። ንጋት ላይ ይቀጣጠላል። ሪሚጦ፤ ማሽላ እሸት የቡና የምሳ የወላዊ የፍቅር ጊዜ ማህበረሰቡ ያሳልፋል። ስለት ደረሰለኝም ሥጦታም አለ። ለመጪው ዘመንም ስለት ይጎርፋል፤ ዘንድሮ በምን መልክ እንደ ተከወነ አላውቅም። የአዲስ አባባው ለእኔ ብሄራዊ ናሙናነቱ መከራ የተጫነው ዕንባው ያቆረዘዘ ሆኖ ነው የታዬኝ። ግን ስለምን ምሽት እንዲሆን ተፈለገ? ምንድን ነው ይህ ዕድምታው? ምን ለመጣስ ነው? ምንስ ለመሸፈን? ጀግኖች ነን በምሽት በሰላም በ ዓሉ ተከወነ ተብሎ መግላጫ ሊሰጥ አዲስ አባባው የከንቲባ ጽ/ ቤት?
አማራ ክልል እንዲያውም ብአዴን በዕለቱ ከሰዓት በኋዋላ ላይ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። ይህ ሆን ተብሎ በመስቀል ደመራ ባዕል ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ታቅዶ የተከወነ እንጂ አጋጣሚ የፈጠረው ነው ማለት አልችልም። ቅንነት ካቦታው ብርቅርቅ ብቻ ስለሆነ ...
የህዝብን ሃይማኖታዊ ትውፊታዊ፤ ዕሴታዊ ጉዳዮችን እያለሳለሱ መጫን ለቅደስት አገር ለ ኢትዮጵያ ምን ያህል ያሰኬዳታል ነው ጥያቄው። የ27 ዓመቱ አልበቃ ብሎ የዛሬው ደግሞ በሰለጠነ መልኩ የተፈጸመ ዘመም ያለ ጉዳይ ነው። ምን አለ መስቀል ከመድረሱ ቀደም ባሉት ቀናት ወይንም ካፈለ በኋዋላ ቢካሄድ?
ብሄራዊ ባዕሉ በዛ በደም አደባባይ ሲከበር ቀድሞ ነገር ማታ ላይ ደማራ ተቀጣጥሎ አይታወቅም። ልክ ቻይናዎች የኢትዮጵያን ባህላዊ አገሬ ልብስ ተክተው በፋፍሪካ እንደ ሰሩት ፌክ የሆነ አከባበር ነበረው ማለት እሻለሁኝ። ደህንነቱን ለማሳዬት የጸጥታ ሃይሎች ነበሩ፤ ግን በካንፕ ውስጥ የተከበረ፤ ነፃነቱን የተገፈፈ፤ ትውፊቱን የተቀማ፤ በአደባባይ ትሩፋቱ የተገረፈ ባዕል ነው የተከበረው። ዕውቅናውም የሚዲያ ሽፋኑ በመቁንን ነበር።
ለነገሩ አሁን እኔ የሚያሳስበኝ የብጹዕ ወቅዱስ አባቶቼ የነፍስ ጉዳይ ነው። ጨካኞች ምን ሊያደርጓቸው እንደሚችሉ አይታወቀም። ምክንያቱም ከመልካም የምሥራቹ ቀጣይ ጥቃት እንደሚፈጸም እዬተከታተልኩት ስለሆነ። መልካም የፈጸመውን መንፈስ ማጥቆር የጃዋርውያን ቡድንተኞች መሪ ስትራቴጃዊ መርህ ነው።
- · ሌላ የገረመኝን ደግሞ ልከል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በማህበረ ቅዱሳን እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ወይይት መጨረሻ ላይ ብጹዑ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ኬክ ሲቆርሱ ተመልክቻለሁኝ እያዘንኩኝ። የት ነው የሚመጣው ይህ ጉድ?
ለመሆኑ ስሙን እራሱ „ኬክ“ የሚለውን ቅድስት ቤተ ክርስትያናችን የት ታውቀዋለች? ዳቤ፤ አነባበሮ የሙሃይ ቂጣ ፤ ሙጌራ ነው ትውፊቱ። ማንነቷን ለማጣት መንገድ መጀመሯን ቅድስት ኦርቶዶክስ እያዬሁኝ። ደግሞም አይምርባትም። "የሰው ወርቅ አያደምቅም።" እሷ ምን አጥታ? እንዲያዋም ከትውፊቷ ስፋት እና እርዝመት ዓይን ዓዋጅ የሚያደርጉ ብዙ እጅግ መጠነ ሰፊ ቅርስ ያላት ናት። ምን ብድር አስኬዳት?
ያቺ ቅድስት አገሯን ውስጧ ያደረገችው ተዋናይት መቅደስ ጸጋዬ ሰርጓን በድፎ ዳቦ በማንነቷ ልክ ነበር ያደረገችው። ኢትዮጵያን ዕወቋት ብላ ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ያሉትን ትውፊታዊ ትይንታዊ እኩላዊ በሆነ ሁኔታ ተቋም ከፍታልን ነበር።
እምወዳት መቅዲ እራሱ የባህላዊ ኢትዮጵያዊ ምግብ ሴሪሞኒዋ በዩኒስኮ ቅርስነት ሊያሰመዝግብ በሚችል መልኩ ነበር ያደራጀችው። ይህቺ ወጣት የባህል እና የቱሪዝም ሚ/ር ብትሆን ምን ልታደረግ እንደምትችል ሳስብ እሩቅ፤ ጥልቅ ሚስጢር እንደ ሆነች እረዳለሁኝ። ለነገሩ በዬትኛዋ ኢትዮጵያ? በአብያዊው ወይንስ በጃዋርውያን?
የሆነ ሆኖ እሷ አንዲት ቅንጣት ብላቴና ናት፤ ያን የመሰለ ሁለመናው ሙሉዑ የሆነ አካታች ትንግርት ያሳዬችን።
ቅደስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ግን ተቋም ነው። የመንግሥት ያህል ሥልጣን ያለው፤ በመንፈስ ከመንግሥትም በላይ ዲታም የሆነ ነው። እና በኬክ ቆረሳ ስምምነትን፤ መስቀልን በአርቲፊሻል ርችት፤ መጋረጃው የሰይጣን ኮከብ በሩን ግድግድ አድርጎ በዘጋ ሁኔታ ባዕሉ ማቅ ለብሶ እያነባ ሲከበር መስቀል አምርሮ፤ ሆድ ብሶት አለቀሰ አስለቀሰ።
የሚገርመው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ራፊ ጨርቅ ይዘው የሚያውለበልቡ ዘማርያንን ተመለከትኩኝ፤ ቀለሙን መቀዬጥ አስፈለገ እና ነጭም ታክሎበታል። ነጭ ሰላም መሆኑን አውቃለሁኝ። ግን ዕድምታው ከሰንደቁ ጋር ያለውን ትግል ያሳያል። መዘባረቅ? ለማን ሲባል ለጃዋራውያን ሲባል። ቅደስት ቤተክርስትያን ሰማይ ላይ ሰንደቋ በታዬ ማግሥት እዮርን ድጣ ለሥጋዋ አድልታ ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ ለማታወቀው ማንነት ሰገደች። እግዚኦ!ምን አለ እንደማንነቷ ኑራ ሰማዕትነትን ብትቀበል ያን በመለሰ ጃዋራውያን ዳንቴል ባትጠቀለል? ተሳህለነ?
እንጅብራ ላይ ታምሩን አሳዬን እኮ እዮር። ለዬትኛው ዕድሜ ነው አበው ይህን ነገር መድፈር የሚሳናቸው። ሞት ተሸክመው እንደሚኖሩ ያውቁታል። ህግ መተለላፍ ስለበረከተ፤ ህግ ስለተጣሰ፤ በማግስቱ ሌላ የመሬት መራድ ታዬ ደቡብ ላይ። ራሱ የቁጣው ዲዛይኑ ሲታይ መሬቱን በጉራጌው ዞንድ ሰኔ መግቢያ 2010 ላይ እንደ ተሰነጠቀ ነው መኖሪያ ቤቱ የተረተረው።
በመርሐቤቴ 6 ቀበሌዎች የመሬት መንሸራተት አደጋ አጋጠመ
ዙሮ ዞሮ ያው የሚበደለው ደሃው ነው። እኛ ይህም የሰማይ ቁጣ አልበቃን ብሎ ሠው ሰራሽ ችግር ስናምርት ውለን እንድራለን። እዮራዊ ቁጣው ይቀጥላል ብዬ ነው የማስበው።
ተደሞን ገንዘብ እሰከ አላደረግን ድረስ።
በዚህ አጋጣሚ ለአማራ ህዝብ እኔ ወስጤ የሚለኝን ነገር ብለው ደስ ይለኛል። ክብሪት እና ቤኒዝን ስለተዘጋጀለት ያን እለፈኝ ብሎ አካባቢውን መጠበቅ፤ ለአካባቢው ህዝብ ዘብ መሆን፤ ጎረቤቱን ጎረቤቱ መጠበቅ ከመቸውም በላይ እንደ ጎንደሮች የእስልም እና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ የባዕላት መረዳዳት መሬት ላይ ሴራን መቀብር ይኖርበታል።
አሁን ያለው መንፈስ ዲያቢሎሳዊ ስለሆነ እሱን ላለመታባበር ኖሪውን የመጠበቅ፤ የኗሪውን ንብረት የመንከባከብ፤ የሥነ - ልቦና ስብራት ጉዳት እንዳይደረስ፤ ባይታዋርነት እንዳይሰማው ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል። ለነገሩ እርግጠኛ የሆነ ዜጋ ማን ስለመሆኑ አሁን ይፈተናል።
ከሁሉም በላይ ሰላም ይበልጣል። ከተስፋም በላይ ሰላም ይበልጣል። ፊት ለፊት የወጡ አታጋዮችም ቢሆን ተንኳሽ ከሆኑ ነገሮች መቆጠብ ይገባል። ጦርነት ናፈቀኝ መሆን አያስፈልግም።
አማራ መጫሪያ ገል መሆን የለበትም። በዚህም በዚያ፤ በእንዲህም በእንዲያም መከራውን አማራ ስለኖረበት መከራው ካሰተማረው ኑሮ መማር አለበት የሚል ዕምነት አለኝ።
ተደሞ፤ እርጋታ፤ ስክነት፤ እዮባዊነት፤ አደብ፤ መቻል፤ አይቶ እንዳላዩ ማሳለፍ ይገባል። ወርቅ ከቀለጠ እንደሚፈስ እራቅ አድርጎ ማሰብ ይገባል። ነገን ለማግኘት ዛሬን መጠበቅ ያስፈልጋል። ነገን ለማሰብ ዛሬን መጠበቅ ያስፈልጋል።
ሰላም ይቅረበን!
„አቤቱ እንደ እኛ ጥፋት ሳይሆን እንደ ቸርነትህ ማረን!“
ባጠፋነውም ይቅር በለን። አሜን!
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
በጸሎት እንበርታ።
ማለፊያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ