ተፈጥሮን ያዘመነው የማሰብ ፍልስፍና ልቀት ነው።

መሆንን በማሰብ፤
መሆንን በመቻል፤
መሆንን በመሆን።
„ይህ ህዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤“
 የማቲዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፭ ቁጥር ፰
ከሥርጉተ©ሥላሴ
28.09.2018
 ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።

  v   መቅድም።
መሆን በመሆን ቢጣፋ? መሆን በመሆን ቢባዛ፤ መሆን በመሆን ቢቀመር በመሆን ውስጥ መኖርን ያጠይቃል። መሆንን ማሰብ፤ መሆን በመቻል ማቻቻል፤ መሆንን በመሆን ማትጋት ሁሎችም የተፈጥሮ መብቶች ናቸው። ልዑል እግዚአብሄር የሰጠን። እርግጥ ነው መሆንን ማሰብ ገደብ የለውም። 

መሆንን መቻል ግን የሚከብዱ ነገሮች ይኖራሉ። መሆንን በመሆን ዕውን ለማድረግም እንዲሁ።አንደኛው ለምሳሌ ሊሆኑ የፈለጉትን አለማግኘት ነው።

  v   መሆንን ማሰብ።
መሆንን ማሰብ የሚነሳው ከራስ ብቻ አይደለም ከቤተብም ከአካባቢም ሊሆን ይችላል። ብቻ መሆን ማሰብ እስከ ዕድሜ ልክ አብሮ አድጎ እስከ ገሃዱ ዓለም ሥጋዊ ስንብት ድረስ አኗኗሪ ነው።

በዚህ ውስጥ ማሰብ ራሱን የቻለ መክሊትም አለው። ከአካባቢ ወጣ ያለ ምናባዊ፤ ፍልስፍናዊ እሳቤም ይኖራል። ማሰብ ድንበር የለውም እንደ ተፈጥሮ ጸጋ ለሚያዩ አካላት።

መኖር የተፈጠረው በማሰብ ሃሳብ ውስጥ ነው። ማናቸውም የመኖር ሁለመና መሰረቱ በማሰብ ልቅና የተገኘ ነው። ከማስብ ልቅና፤ ከማሰብ ብልጽግና ውጪ የሚፈጠሩ የፈጣሪ ፍጡራን እና ተፈጥሮ ብቻ ነው። ተፈጥሮን አሰልጥኖ፤ ተፈጥሮን ዘመናይ ያደረገው የማሰብ ፍልስፍና ልቀት ነው።

  v ሆንን በመቻል ማቻቻል።
ሊሆኑ የፈለጉትን ቢያገኙትም በመሆን ውስጥ ካልተከተበ ብላሽ ነው መሆንን ማሰቡም ሆነ መሆንን በመቻል ለማግኘት። መሆን በማቻል ማቻቻል የማድረግ አቅሙ ተመጣጣኝ ምቹ ሁኔታ እና የህሊና ፈቃድ ካልኖረው።

ሌላው የሚፈልጉትን ነገር ማወቅ አቅጣጫ አምልካች ሲሆን በዛ ልክ መትጋት ደግሞ መሆንን በመቻል ይቀይሳል፤ ቅዬሳው ከራስ በመነጨ ምኞት ፍላጎት ከሆነ፤ መሆንን በመሆን መቻል በማገናኘት ራስን ማግኘት ይቻላል። 

ከዚህ ባሻገር አጋጣሚ የሚሰጡ በርከቶችም፤ መርገምቶችም ይኖራሉ። ለበረከት የተፈቀደለትን ለመርገምት የሚያውል ከሆነ የባከነ ምኞት ነው የሚሆነው መሆን በማቻል ማቻቻል። እርግማትን ለምርቃት የመለወጥ የራስ ማሸነፍ አጋጣሚም ሊኖር ይችላል። 
  
ሊሆኑ የፈለጉትን አለማግኘት በራሱ አዎንታዊ ከሆነ ጥረትን፤ ታታሪነት፤ ትጋትን፤ ያለድካም መሥራትን፤ ሁኔታን፤ ቦታን፤ ፈቃድን የፈጣሪ ይሁንታ ያስፍልጉታል - በተለይ አምላክ አለኝ ብለው ለሚያምኑት።

ይህም ብቻ አይደለም መሆን የሚተረጎምበት ማሳ ያስፍልገዋል። ለምሳሌ ሙያ ከሆነ ያን ሙያ የቀሰመበት ተቋም ያስፍልጋል። የተቋሙ መኖር ብቻ ሳይሆን ለመሆን የሚፈለገው አቅም እና ብቃት መሆን ከሚጠይቀው ሞራላዊ አቅም ጋርም ላይመጣጠንም ይችላል። 

የሰብዕና ክብደቱ ሚዛኑ ሊሆን ከተፈለገው ምኞት ጋር ያለው መመጣጠን የግድ ያስፈልገዋል። በስተቀር በጥቂት አውሎዎች ተንሳፋፊ ሆኖ ሊያከትም ይችላል።
መሆን ቢቻል ደግሞ መሆንን ለማዝመር ራሱን የቻለ የሁኔታዎች መመቻቸትን ይጠይቃል። 

አንድ ሰው ስለተማረው ብቻ በተመረቀበት በሙያው የማይሰራበት አጋጣሚ ይህው ነው። ዕድሜውን ሙሉ ተመኝቶ ደክሞ ግን ያን ክህሎቱን ወደ ተግባር የሚቀይርበት ተሰማሚ ሁኔታ ካልገጠመው ችክ ሳይል ኑሮን ለማኖር ከህልሙ ወጥቶ በሌላ ዓለም ለመኖር ይገደዳል።

ይህንም መቀበል ጸጋ ነው። በተፈቀደለት ልክ የተሰጠውን ማስመቸት መቻል ልቅናም ነው። ችግሩ በእልህ እና በቁጭት በገረዘዘው አጋጣሚ ይሁን ዕድል መጪ እላለሁ ቢል የህይወት ብክነት ይገጥመዋል። ብከነቱ አደባባይ ላይ ከሆነ ብዙ ነገሮችን ያነኩታቸዋል።
    
መሆን በመቻልን በአሉታዊ መልኩ ስንመለከተው ሊሆኑ የፈለጉትን አለማግኘት ብዙ የፈተና መረቦች አሉበት። ከሁሉ አስቀድሞ ብርቱ የሆነ የመቀበል አቅምን ይጠይቃል። መሆን ያልቻሉበትን ምክንያት የመፍቅድ ብልህነት ይጠይቃል። 

እንደ አማኝ ደግሞ ባይፈቅድ ነው፤ ለመልካም ነው ብሎ በጎ ማሰብን ይጠይቃል። መቀበል ካልተቻለ ግን አደጋው ሰፊ ነው። መፍቀድ ካልተቻለ ጦሱ ፍዳ ነው። ይህም ማለት ለሁኔታዎች አስገዳጅነት መታመን ማለት ነው። ህይወት በተፈቀደለት ልክ ተምኖ መኖር ማኖርም ማለት ነው። ሰማይ ሰማይ ነው ምድርም ምድር ነው።  

በጣም ትልቁ ችግር የተመኙትን ያለገኙ ሰብዕናዎች አልመቻላቸውን ካልተቀበሉት የውስጥ ሰላማቸው ይሸፍታል። የውስጥ ሰላም መታወክ ደግሞ ጤናን ያጎድላል።

ጤናን ማጉደል ብቻ ሳይሆን ካገኙት ጋር ተጋጭም ያደርጋል። ይህም ብቻ ሳይሆን ተስፋ ቆራጭነት ጋር የሚመጣ ሌላ መዘዝም ይኖራል። ሌላው ቀርቶ ሌሎች በተመኙት ልክ ሲሆኑ ለማዬትም፤ ለማድመጥም መፍቀድን አቅም ያንሳል። የመረረው ነገር ከዚህ ምልከታ ቅናት ስለሚመነጭ ሰብዕናን መጥላትን ይፈጥራል። መጥላት ደግሞ ከተፈጥሮ ጋር መታገል ነው።

መሆነን በመቻል ትልቁ የሰው ልጅ ፈተና ነው። ፈተናው የሚመጣው በራስ ላይ፤ ወይንም በራስ ወገን ላይ፤ ወይንም በቅርብ ሰው ላይ ከመጣ ጉዳዩ ዳገቱ ጠራራ ነው የሚሆነው። እርግጥ ነው መቻል ሲባል አንድ የሙያ መስክን ብቻ አይደለም። ሰው ለመሆን መቻልንም ይይዛል። ሰው ሆኖ መቆም። ለመቻል ራስን ችሎ በተሰጠው ሰዋዊ ጸጋ ልክ መቆም ነው።

ከዚህ በተረፈ ኑሮ ያከማቸው፤ የቀመረው እልፍ ዶግማና ቀኖና ይኖራል። እያንዳንዱ ሰከንድ መፈጠርንም ማለፍንም የያዘ ነው። ህግጋቱ ሃይማኖት የደነገገው ድንጋጌ፤ መንግሥታዊ አካል ያጸደቃቸው ዓዋጆች ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሁሎችም በመሆን መቻል ውስጥ የሚያልፉ ናቸው።

አንድ ምሳሌ ላንሳ፣--- ነፃነት የምትፈልግ ከሆነ የሌላውን ነፃነት መጋፋት አያስፍልግም። ለአንተ ነፃነት እታገላለሁ ከሆነም በዛ ውስጥ አንተ መኖርህ የሚረጋግጠው ሌላውን ላለመጫን ከራስህ ሆነህ መሆንን ስተለማማደው ብቻ ነው።

ቀድሞ ነገር ለነፃነት የሚታገል ሰው ለራሱ ነፃነት መስጠቱን በመጀመሪያ ማረጋገጥ አለበት። አንዳንድ ጊዜ ራሱ በሌለበት የነፃነት ጽንሰ ሃሳብ ውስጥ መዳከርም ይታያልና።

ነፃነት አንዱ ያለውን ያህል ሌላውም ያለው መሆኑን መቀበል ግድ ይላል። በአንድ ሰው የግል ሰብዕና ውስጥ ለሰብዕናው፤ ለመንገዱ መራጩ እራሱ ነው። አንድ ሰው ለሰብዕናው ለመንገዱ ማህንዲሱ እራሱ ሆኖ ሳለ አንተን እኔ እወክልሃለሁኝ ሊባል አይገባም። ያ ሰው እንደ ተጫኙ መንፈስ ሰው ሆኖ መፈጠሩን መዘንጋት የለበትም።

አንድ ሰው እንደ ዛፍ ቅርንጫፍ ተቀጣጥሎ የበቀለ አይደለም። ወይንም እንደተገጣጣሚ ቤት የተበጀ አይደለም። አንድ ሰው ሙሉ ሰው ሆኖ የተፈጠረ የፈጣሪ ፍጡር ነው። ስለዚህ ነፃነት የዛም ሰው የተፈጥሮ ጸጋው ስለመሆኑ መቀበል ግድ ይላል።

ስስታም ሰብዕና የራሱን ህሊና ለሚፈለገው እዬተጠቀመበት ሌላ ተጨማሪ ህሊናም የመውረስ፤ የመስረቅ፤ የመዝረፍ ፍላጎት ይኖረዋል። ይህን ዓይነት ሰብዕና እንኳንስ ሌላውን ከማህጸኑ፤ ከአብራኩ የተፈጠረውንም በዛ ልክ ህሊናውን ለመውረስ፤ ለመዝረፍ አለመቻሉን ጠንቅቆ መረዳት ይኖርበታል። በሞፈር ዘመት ህሊና አውራሽ አይገኝምና።

ይህ አካሄድ የአንድን ሰው ህሊና ውርስ ለማድረግ ምኞት ያለው ሰብዕና እንደ አንድ ዛፍ ወይንም ዋርካ ወይንም ባንባ የሰውን ልጅ ያህል ፍጡር ዘንጥዬ፤ ዘንጥፌ ልወሰድህ ማለትም ነው።

እኔ የአንተ ቀያሽ ማህንዲስ ነኝ ከሆነ ጉዳዩ ምኞቱ ተቆርጦ ነው የሚቀረው። ከዚህም ባለፈ መጨረሻ የሚመጣው ግጭት ነው። ግጭቱ ተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን ኢ- ታዕማኝነት በማራባት ራሱ ተጫኙ ግጭቱን ያስፋፋዋል ማለት ነው።

ያልተሰካ፤ የማይሳካ፤ ሊሳካ የማይችል ሃሳብ ጀምሮ፤ ወጥኖ ከመውደቅ ቀድሞውንም አለመጀመሩ ለጤና የሚመች ይሆናል። ምክንያቱም የማያውቁት አገር ስለማይናፍቅ። ለነገሩ በነፃነት ጉዳይ ላይ የማያውቁት አገር ነው የሚሆነው ለተጫኙ መንፈስ እንጂ ጭነትን ተሸከም የሚባለው አሻም ማለቱ ከተጫኙ የተሻለ የነፃነት ግንዛቤ አለው ማለት ያስችላል።

በዚህ ማህል ያለው ሰባቃ የጽንሰ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን የድርጊት በር ከፋች የሚሆኑ ነገሮች ይኖራሉ። እጭናለሁ የሚለው የመንፈስ መናወጽ ሲደርስበት፤ አልጫንም ያለው ግን የማድረግ አቅሙን ያጎለብትበታል። በዛች የምትገኘውንም ፍሬ አሳልፎ ላለመስጠት ትጋቱ ከቀደመው የበለጠ ጉልበታም ይሆናልታል ማለት ነው። ጽናቱም ጽላቱ ይሆናል።

አሻነፊ መንፈስ በአሉታዊ ገጹ በልኩ ከተያዘ የበለጠ ሃይል ገንቢ፤ አቅም ፈጣሪ ነው የሚሆነው። ችግር የሚሆነው አሸናፊው መንፈስ ያገኘውን ዕድል አጠቃቀም ላይ አያያዝ ሳያውቅበት ከቀረ ነው።

ያ አደገኛው እና ቅስምም ሰባሪ ጉዳይ ነው። በተለይ የአደባባይ ሰዎች መልሰው አገግመው ለመነሳት ስለሚከብዳቸው የአሸናፊነት መንፈስንም፤ የአሸናፊነት በረከቶችንም፤ ደስታቸውንም በልክ መያዙ ለቀጣዩ ጉዞ መንገድ ቀያሽ ይሆንላቸዋል። ለዚህ ነው ጎንደሬዎች „ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል“ የሚሉት።

  v ሆን በመሆን።
መሆንን በመሆን፤ ///  መሆንን በመሆንም ቢሆንም አሉታዊ እና አዎንታዊ ናቸው -  ለእኔ። አንድ ሰው በሚፈለገው ልክ የሚፈልገውን አግኝቶ እያቻለ ግን በዛ ውስጥ ለመቻል ማቻቻል፤ ወይንም ማስማማት ካልቻለ አሉታዊ ነው።

ዕድሉን ካሾለከው ወይንም አጋጣሚውን ሊጠቀምበት ካልፈቀደ መሆን እያቻለ መሆን በመሆን ወስጥ ማስታረቅ ባለመቻሉ ከቀደመው ካለፋበት ልፋቱ በላይ ዋጋ ሊያስከፍለው ይችላል። ለዛውም ደግሞ ለማግኘት ከረዳው።

ምክንያቱም ቦታ፤ ሁኔታ፤ እና ጊዜ በዛ መሰመር ለመምጣት ላልፈቀደ ትእግስት አልባ በመሆናቸው የራሳቸውን የሽፍትነት ውሳኔ ሊወስኑበት ይችላሉ። በረዶ ውስጥ የገባን ክስተት አይደለም በነበረው ሙቀት ለማስቀጠል በጀማሪነት ደረጃ በለብታው እንኳን ሁንበት ቢባል በጅ የማይሉ የተፈጥሮ ህሊናዊ ወጣ ገብ አውሎዎች፤ ስበቶች፤ ሰበቃዎች ይኖራሉ እና።

አብሶ የህሊና የመንፈስ ጉዳይ ከሆነ ሲጀመርም አድካሚ ነው፤ ለማስረጽም ፍዳ ነው፤ እንደገናም የበረደውን መልሶ ለማሞቅም ድርብ አሳር ነው። ለዛውም መዋለ መንፈሱን ለመቀበል ፈቃደኛ ከተገኜ ብቻ ነው። ይህም ቢሆን በሃዲዱ የጥገና ሥራው እጅግ አድካሚ ነው የሚሆነው። ምክንያቱ መታመን የ አንድ ጀንበር ቀመር አይደለም እና።

አዎንታዊው ግን ዋናው ቁም ነገር ዕድሉን የእኔ ብሎ አቅርቦ መያዝ ያስፈልጋል። በዛ በተፈቀደለት ዕድልም ውስጥ ሁሉን ፈላጊ አለመሆን ሌላው ጉዳይ ነው።
አንድ ሰው መሆን በሚችለው ልክ ብቻ ነው መሆን የሚችለው። ስለዚህ በራሱ የመሆን ማሰብ፤ መሆን በመቻል፤ በመሆን መሆን ውስጥ ያለ ስብዕና በአቅሙ ልክ የሚችላቸውን ፈርጆች ብቻ ላይ ትኩረት ማድረግ አቅምን አያባክንም። የውስጥ ሰላምን ያሰፍናል። የሌላንም ሰላም አያውክም። የሌላውን ድካምም ይቀንሳል።

ከዚህ ጋር እንደ ማጠቃለያ ሃሳብ የማነሳው ግን አለመርካትን ነው። በመቻል ውስጥ ያሉ፤ በመዳፍ በሚገኙ በረከቶችን እርካታን ለመግኘት መፍቅድ በራሱ ኑሮን ያሰምራል። „ … ይበቃኛልን ተምሬበታለሁና … “ ያለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዛ ፍዳ ውስጥ ሆኖ ነው። እኔም በዚህው ሃሳቤን ልከውን።

ዓራት ዓይናማው መንገዳችን ቅንነት ብቻ ነው!
የኔዎቹ ኑሩልኝ።

ማለፊያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።