ጃዋር ቀነ ገደብ ያስቀመጠውን የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ፈርሞ ተቀበለ (ጎልጉል እንደዘገበው)


እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።
„በውን እግዚአብሄር እንዴት እንደሚያዝዛቸው
የደማናውን ብርሃን እንዴት እንደሚያበራ አውቀሃልን?“
(መጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ 37 ቁጥር 15)

የጉጉሱን መጨረሻውን ያዬው ሰው።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Seregute©Selassie
21.01.2020
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ

·       መቅድም
 እንዴት ናችሁ የኔዎቹ። እኔ ለብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ጠንከር ያለ አቤቱታ ላቀርብ ጹሑፍ ጨርሼ እርማት ላይ ነበርኩኝ። ነገር ግን የተለወጠ መርጃ ካለ ብዬ ድህረ ገፆችን ስዳስስ ይህን አዲስ መረጃ ከጎልጉል አገኜሁኝ። 

የእኔ ከዚህም ከፍ ያለ ስለሆነ ሙግቴ ይቀጥላል። የሆነ ሆኖ ይህም ጎሽ የሚያሰኝ ስለሆነ እነሆ ሙሉውን ትታደምቡት ዘንድ አጋራሁኝ።

ይህ የእርምጃ አወሳስድ ጉዳይ የሃይል አሰላላፉን እንደገና የሚበውዘው ይመስለኛል። ኢትዮጵያ የትኛው መንግሥት እንደሚገዛትም ይለይለታል። ግርዶሽ የተሠራላቸውም ነገሮች ገለጥለጥ ይላሉ። በዚህ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ድፍረት ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ፈቃድ እንዳለበት አስተውያለሁኝ። ድፍሩቱ የሚቀዳው ከዛ ነውና።

ዘገባው የጎልጉል ነው። ለዚህም ነው ትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ያስገባሁት። ፎቶውም ከጎልጉል የተወሰደ ነው። 

·       መነሻ።

ጃዋር ቀነ ገደብ ያስቀመጠውን የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ፈርሞ ተቀበለ

ለቀረበለት ሕጋዊ ደብዳቤ ዛቻን አስቀድሟል


„ከለውጡ በኋላ ወደ ፖለቲካ ሥልጣን የመጠጋጋት ህልምና ውጥን እንደሌለው ሲወተውት የነበረው ጃዋር በቅርቡ ኦፌኮን መቀላቀሉን ተከትሎ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ሊልክለት በዝግጅት ላይ መሆኑ ትላንት በመረጃ ገልጸን ነበር ዛሬ (ማክሰኞ) የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ እንዳመለከተው ጃዋር የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ፊርማ ያረፈበት ደብዳቤ እጁ ገብቷል፤ ፈርሞ ተቀብሏል። ደብዳቤው እንዳይዘጋጅ ያደረገው ሩጫ ሳይሳካ በመቅረቱ ዛቻ እየሰነዘረ መሆኑም ታውቋል።

በተደጋጋሚ የሕግ የበላይነትን በማንሳት ዲስኩርና ማብራሪያ የሚሰጠው ጃዋር፣ ምርጫ ቦርድ በጻፈለት ደብዳቤ መቆጣቱና ወይዘሪት ብርቱካን ላነሱት የሕግ ጥያቄ መልስ ከመመለስ ይልቅ ዛቻን መመረጡን የጎልጉል መረጃ አቀባዮች ይፋ አድርገዋል።

በሚያስተዳድራቸው ሠራተኞቹና አበል በሚከፍላቸው ጭፍሮቹ ዘንድ የተለያዩ የማዕረግ ስሞች ባለቤት የሆነው ጃዋር፤ ከግራኝ አሕመድ ቀጥሎ 21ኛው ክፍለ ዘመን ልዩ ክስተትና ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆኑንን ደጋግሞ ይገልጻል። ከዚህም በተጨማሪ የሚያሳድማቸውና ለሚፈልገው ዓላማ በቅጽበት የሚያሰማራቸው፣ ደማቸውን እኔ አወራርዳለሁ ሲል የሚማግዳቸው የጎዳና ላይ ነውጥ ፈጣሪዎች ስላሉት ራሱን መንግሥት አድርጓል። ፈላስፋ ነኝ ባይልም አዋቂ መሆኑንን በተደጋጋሚ ይናገራል፤ ብዙ ዕውቀት አለኝ፤ ብዙ ችሎታ አለኝ ሲልም ተደምጧል ከዚህ ስሜቱ በመነሳት እንዴት ደብዳቤ ይጻፍልኛል? በሚል ለሕግ ተገዢ እንደማይሆን የጎልጉል ዘጋቢ መረጃ አቀባዮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

ሕግን በማስከበር ረገድ በተግባር ተፈትነው ያለፉት ወይዘሪት ብርቱካን ለጃዋር ዛቻና ምልጃ ጆሮ ሳይሰጡ የአሜሪካ ዜግነት ይዞ በኢትዮጵያ ፖለቲካ መፈትፈት እንደማይችል ጠቅሰው፤ ቀነ ገደብ አስቀምጠው፤ ጥርት ያለ ምላሹን ሕጋዊ ሰነዶችን በማያይዝ በሕጋዊ ወኪሉ ወይም ራሱ በአካል ተገኝቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ተረጋግጧል። በኢትዮጵያ ካካበቱት የሕግ ዕውቀታቸው በተጨማሪም አሜሪካ በቆዩበት ወቅት የአሜሪካንን የሕግ አሠራር በቅርብ አውቀው በመምጣታቸው /ሪት ብርቱካን ሊቀርቡ የሚገባቸውን ሰነዶች አስቀድመው የሚውቁ መሆናቸው ይታወቃል።  

በለውጡ ማግስት ሜኔሶታ ጠቅላይ ግዛት ጣምራ ዜግነትን የሚከለክለው የኢትዮጵያ ሕግ እንዲቀየር ሲወተውት የነበረው ጃዋር፣ የአሜሪካ ዜግነቱን ለመመለስ የሚያስችለውን ሂደት ማከናወኑንና በቀናት ውስጥ ጉዳዩ እንደሚያልቅ በኤል ቲቪ የጭውውት ክፍለ ጊዜ መናገሩ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ይህ ዜና እስከታተመ ድረስ ሕጋዊ ሰነድ አላቀረበም። አስፈላጊውን ሕጋዊ ፎርማሊቲ ሳያሟላ ዜግነት፤ ኢትዮጵያዊ በማለት መታወቂያ የሰጠው / መረራ የሚመሩት ኦፌኮ ነው።

ምርጫ ቦርድ ከጃዋር በጊዜ የተገደበ ደብዳቤ ምላሽ በኋላ ኦፌኮን በይፋ ሕግ ፊት እንደሚያቆመው የጎልጉል የመረጃ አቀባዮች ሰምተዋል። ኦፌኮ ምን ይዞና በየትኛው መመዘኛና የሕግ መሥፈርት ይህንን መታወቂያ ሊሰጥ እንደቻለ ማብራራት፣ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የከረረ ሕግን የመተላለፍ ቅጣት እንደሚጠብቀውም ለመረዳት ችለዋል።

ዳጎስ ያለ ገንዘብ እየከፈለ ከቦታ ቦታ በማዘዋወር በሚያሰማራቸው ውስን ጭፍሮቹና የሚዲያ አውታሮቹ አማካይነት ጫና በማድረግ በሰላማዊ ትግል የሚታወቁትን አክራሪ ማድረጉ፣ በተለይም በሰላሌ በቅርቡ በእሱ አቀነባባሪነት ያሰራጨው የውክልና ቅስቀሳ በርካታ ሰላም ወዳድ የኦሮሞ ልጆችን እንዳሳዘነ ጎልጉል ያነጋገራቸው የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናግረዋል። እነዚሁ ክፍሎች እንዳሉት ኦፌኮ በጃዋር አማካኝነት ካርዱ ተበላሽቷል

ዜግነትን ስለመመለስ ወይም ስለመቀየር ሰፊ ትንታኔ የሰጡት የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣንና የዓለም ዓቀፍ ህግ ባለሙያ አቶ ባይሳ ዋቅ-ወያ፤ ዜግነትን መቀየር በተመለከተ አንዳንድ ነጥቦች በሚል ርዕስ ለጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ በላኩት ዘገባ ችግሩ “… ዜግነት የሚባለውን እሳቤ እንደ ሰብዓዊ መብት ከመቁጠር የተነሳ ይመስለኛል ሲሉ በሰፊው ማብራሪያቸው ይጠቅሳሉ። አያይዘውም ዜግነትን የመስጠትም ሆነ የመንሳት መብት ያለው መንግሥት ስለሆነ ዜግነት የሰብዓዊ (መብት) ሳይሆን የሕጋዊ መብት እንደሆነ ማወቁ ተገቢ ነው በማለት ጉዳዩ የሕግ እንጂ በእብሪትና በጎዳና ነውጥ የሚታደል የማንነት ማረጋገጫ እንዳልሆነ ያስረዳሉ። በተለይ ከአሜሪካዊ ዜግነት ስለመቀየር የጻፉትን ሕጋዊና ሙሉ ትንታኔ እዚህ ላይ ይገኛል

/ሪት ብርቱካን ቀነ ገደብ ቆርጠው ለጃዋር የላኩት ደብዳቤ በተሰጠው ቀን ምላሽ ካልተሰጠበት የሕግ ጥያቄው ጃዋርን ብቻ ሳይሆን ኦፌኮንና የፓርቲውን አመራሮች በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው የሕግ ባለሙያዎች አስተያየት ይሰጣሉ።“

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።