ጎንደር - ክፍል ሁለት ።

     ጎንደር - ክፍል ሁለት ።
                           ከሥርጉተ ሥላሴ  25.05.2014 (ሲወዘርላንድ ዙሪክ)
                „አቤቱ በአንተ ታምኛለሁ እና ጠብቀኝ።“  (መዝሙር ምዕራፍ ፲፭ ቁጥር ፲፩)

  
·       እፍታ።
„መታደሌን የማውቀው ከጎንደር ጠንካራ፣ ቅንና እና ግልጽ ህዝብ ጋር እንድሠራ ፓርቲዬ ኢሠፓ ስለፈቀደልኝ ነው። ስለዚህም ከጎንደር የበቃ ታሪክና ታታሪ ህዝብ ጋር ሆኜ ማናቸውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ። የጎንደር ክ/ሀገር ህዝብ እምነት የሚጣልበት፤ ኃላፊነት የሚሰማው ልዩ ኃይል ነው።“

ይህን  አፈሩ ይቅለላቸውና እኒያ ቅንና ብሩክ ጓድ ገዛህኝ ወርቄ የኢሠፓ ማዕከለዊ ኮሜቴ አባልና የጎንደር ክፍለሀገር ኢሠፓ አንደኛ ጸሐፊ በህይወት በነበሩበት ጊዜ በሙሉና በአጥጋቢ ኢትዮጵያዊነት ስሜት የተናገሩት ነበር። እንዳሉትም አደረጉ። በ18 ቀኑ የጎንደር የፋመ የመከላከል ውጊያ ኤሊኮፍተር ከማዕከላዊ መንግስት ቢመጣላቸውም የጎንደርን ህዝብንና ጓዶቼን ከእሳት ማግጄ እኔ አዲስ አበባ ብቻዬን አልሄድም ብለው ኮማንድ ፖስታቸውን ወደ ላይ አርማጭሆ አዙረው፣ ቀና ድጋፍ ከመንግሥት አገኝቼ ለድል እንበቃለን ሲሉ ጦርነቱ የእርስ-በእርስ ስለነበር፤ እንዲሁም ጎንደር ላይ የወያኔ ቅስም ቢሰበር ጸጉራቸው የሚቆሙት ሽውራር ስሜቶችም ታክለው የታሰበው ሳይሆን ቀረ። እሳቸውም በወሰዱት ጥንቃቄያዊ በሳል እርምጃ ጎንደር ከተማ አንዲት ነፍስ ሳይጠፋ፤ ቅርሶቿም በጠላት ሳይወድሙ ህይወታቸው እስከ ልጃቸው ድረስ ጎንደር - አርማጭሆ ላይ ቀረ። 
                                                  
እጅግ የማከብራችሁ የሐገሬ ልጆች በውስጥ መኖርን ለመትርጎም ውስጥን በሚገባ ማወቅን ይጠይቃል። ማወቁም ብቻውን በቂ አይደለም ውስጥን ፈቅዶ ገልጦ ማሳዬቱ ነው ፍሬው ነገር። እንደ ውስጡ ለመኖር የፈቀደ ሰው እራሱን ሆኖ መኖሩ ረቂቅነቱን ብቻ ሳይሆን ጭብጣዊነቱን ያብራራል። በግድመት መሄድ ወይንም መኖር ዘንባላና ያረገረገ እንዲያም ሲል ምስጥ በላሽ ቀኖና ያደርጋል። ባለፈው ጊዜ ማለትም ክፍል አንድን በጨርፍታ ገባ ብለን ማዬታችን ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ ወደ ክፍል ሁለት አብረን እንዘልቅ ዘንድ ሰው ማክበር ሰብዕናው የሆነው ማህበረሰብ የጎንደር አንጡራ ሃብት  ነውና በዚኽው መስመር ፍቅርን ሰንቀን አብረን እንቆይ ዘንድ በትህትና ለመንኩ - እናንተኑ ጌጦቼን።

ጎንደር ላይ እንግድነት ከ5 ደቂቃ በላይ ቆይታ የለውም። እንግዳ የሚባል ነገር ኖሮ አያውቅም። ወዲያውኑ አዬሩ ቤተኛ ያደርጋል። ማህበረሰቡ ቀረብ አድርጎ፤ እቅፍ ድግፍ አድርጎ ቤት ያፈራውን አካፍሎ የእንግድነት ስሜቱን ቢና ጢና የማውጣት ጥበቡ ሆነ ባህሉ ዝልቅና ዝቀሽ ነው። አያያዙ ወዲያውኑ ለማዳነት አቅልሞ ሸማውን በሙቀት ያላባብሳል። የቤተኝነት ስሜቱ ጉልበታም ስበት እንዲኖረው የማደረግ ጥበቡ ልዑቅ ሥነ - ሕይወት ነው። አንድ የምርምር ተግባር ያስከውናል። ቃላቶችን አደራርቤ ብጽፋቸው ይህን እውነት ከቶውንም አይገልጽልኝም። የሚል ነበር ክፍል አንድ። ክፍል ሁለትስ? እንሆ የእኔ የመንፈሴ አበባዎች።

  • ጎንደር - ክፍል ሁለት

በሌላ በኩል የጎንደር  የአስተዳደር ይዞታ በዬዘመኑ እንደ ተቆራረጠ ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ። ዛሬ ላይ ደግሞ የአንድ መንደር ክብር ያጣች እጅግ ተጨቋኝ ተጠቂም ክፍለሀገር ጎንደር ናት። ተፈጥሯዊ ይዞታዋ ቀደም ባለው ጊዜ በወሎ በኩል እሰከ ሃይቅ እና በጎጃም እሰከ ባህርዳር እንዲሁም በሱዳን፤ በተጨማሪም እስከ ግብጽ ድንበርም እስከ ኑቡያ ስናር ነበር ይላሉ የታሪክ ሊቃውንታት። በተለይ በጎረቤት ሀገር የነበራት ሰፊ ይዞታ ዛሬ ለተቆራረጠችው፤ ወያኔ እንደ አወጣ ለሚቸበቸባት ለገናናዋ  የአፍሪካ ቁንጮ  ልጆች ሊያስተምር የሚችል ተቋም ነበር ማለትም ያስችላል።

„ጎንደር ቢያጉረመርም ፋሲል ፈረስህ
ኑብያና፡ ስናር፡ ወርቁን፡ ጫነልኽ።
ሣሩን፡ ተጠዬፈ፡ ዬፋሲል፡ ፈረሱ
ክምር፡ የሱዳን፡ ወርቅ፡ ገፈራው፡ ነው፡ ለሱ። (ገፅ 154)*

የአፄ ፋሲል ግዛት በኑብያም በበታቻቸው „ጊዮርጊስ“ የሚባል ንጉሥ አንግሰው እስከ ምድረ ግብጽ ጠረፍ ገዝተዋል። የፈረሳቸው መታሰሪያና መቀለቢያ ስናር ነበር።“
 
ጎንደር በዚህም በዚያም ይዞታዋ መነጠቋ አልበቃ ብሎ ዛሬ ደግሞ ከወያኔ እራቁት ህልም ጋር „ለታላቋ ትግራይ“ እውንነት እስከተፈለገው ድረስ እንድትተለተል - ተፈርዶባትል። የወገራና የስሜን አውራጃ እንዲሁም በጭልጋ አውራጃም ሰፊው ለም መሬቷ ለሱዳን፣ ለትግራይ „ለቤንሻጉል“ ተሸልሟል። ይህ ዘመንን ያሻገተ እርምጃ ዬት ሊያደርስ እንደሚችልም አቅጣጫውን ማወቅ ባይቻልም ቀን ያረገዘውን የተገላገለ ዕለት ሁሉም ልኩን ይይዛል የሚል ግምት አለኝ - ጸሐፊዋ እኔ።

ለነገም ቢሆን አዲስ ዴሞክራሲ ሥርዓት ሲመሰረት የጎንደር ሙሉ ክብር እስካልታመለሰ ድረስ፤ በትጋት ትግሉ እንደሚቀጥል በማስተዋል የቤት ሥራውን ማንኛውም የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ቅኑ ዜጋ ሊያስብበት የሚገባ በትረ ጉዳይ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ማስታወስ እሻለሁ።
በጎንደር - በአምላከችን ፈቃድ የተመሰረተው እራሱም የገደመው መጋቢት 27 ቀን 485 ዓ.ም የተመሰረተው ማዬ ዮርዳኖስ የሚገኘብት ድንቁ ዋልድባ ገዳም እና ዘመን ጠገብ ገዳማት እንደ ማህበረ ሥላሴና ሌሎቹም እጹቦች ይገኙባታል። በዪኒስኮ የተመዘገበው የስሜን ፓርክ ፋሲል ግንብ ጨምሮ ካልተመዘገቡት ውስጥ ድንቁ 2ኛወ ዬአፄ እያሱ /አዳም ሰገድ /ታቦቱን የተሸከሙለት ደብረ ብርሃን ሥላሴ፤ ቁስቋምና በርካታ መንፈስን በምልሰት መስጠው እኛነትን የሚያሳዩ ቅርሰ መስታውታት ይገኙበታል። ዘመነ መሳፍንታት በጎንደር ስልጣኔና ገቢር - ውበቱ ፈልቆ በጎንደር ሁሉም አምሮበት ደምቆና ጎልቶ እንዲሁም ጎልብቶ ይታይ ነበር። ዛሬ ግን እም! ነው።
 
 „ ወዴት፡ ሄዶ፡ ኑሯል፡ ሰሞነኛው፡ ቄሱ
ታቦት፡ ተሸከመ፡ ዘውዱን፡ ትቶ፡ እያሱ።
የተሸሸገውን፡ ያባቱን፡ ቅስና
ገለጠው፡ እያሱ፡ ታቦት፡ አነሣና፡፤
አዬነው፡ እያሱን፡ ደብረ፡ ብርሃን፡ ቆሞ
ከኪሮቤል፡ ጋራ፡ ሦስቱን፡ ሥላሴን፡ ተሸክሞ።
ሰውነቱን፡ ትቶ መልእክ፡ ሆነ፡ ደግሞ።
ሥላሴን፡ ቢሸከም፡ እያሱ፡ ገነነ
ላራቱ፡ ኪሩቤል፡ አምሰተኛ፡ ሆነ።  (ገፅ 181)*“

በደብረ ብርሃና ሥላሴ እጅግ ድንቅ ዕጹብ የሆነ፤ ታሪክን ቆሞ መስካሪ ቅርሳችን ይገኛሉ። አግናባቱ በእንቁላል ውሃ የተሰሩ በመሆኑ „የእንቁላል ግንብ“ ይባላሉ። ጸጥ ረጭ ባለው ሰዓትም ጉሬዛ ሲያንፏጭ በአግናቡቱ ውስጥ ጽናጽል ከነከርቤው ይታደሙ እንደ ነበር አቨው ይነገሩ ነበር። በነገራችን ላይ ቤተሰቦቼ የተፈጠሩት ያገለገሉት፣ እኔም የተወለድኩት፣ እትብቴ የተቀበረበት፣ ሀሁ የቆጠርኩበት ጀምሬ ያልጨረስኩት የዳዊት መድገም የወጠንኩበት እዚህኸው ቅኔ መንደር ነው። ሌላ ቦታ የማይይገኙ እንደ ቁስቋም፤ ደብረ ምቅማቅ አብነተ - አብዬተ ቤተክርስትያናት ተደላድለው የተመሠረቱባት የ44ቱ እናት ናት ጎንደር - ራስ ዳሽንንም አክሎ። ስለ ጎንደር ማሰብ ስጀምር ሁለመናውን አሟልቼ ለመግልጽ አቅም ያንሰኛል። ያለ ግነት ጎንደር ምስክር ናት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ዶግማነት።

ዛሬ ብርቅና ድንቅ ሆኖ ብዙ የሚባልለት „አባይን“ በሚመለከትም ከደጉ ንጉሥ ከዐጼ ፋሲል በፊት ቅዱሱ ንግሥናቸውን  ትተው ገዳም የገቡት ቅዱስ ላሊበላ የሠሩት ድንቅ ተግባር ነበር።„ከአክሱም ነገሥታት እነ አብርሀ አጽበሐ እነ አልአሜዳ እነ ካሌብ ስመ ጥሩ እንደ ነበሩ ሁሉ እንደዚሁ ከዛጔ ነገሥታት ውስጥ የ9ኛው ንጉሥ የላሊበላ ሥም በጣም የገነነ ነው። ለመግነንም ምክንያት የሰጠው በዚህ በላስታ ያን ጊዜ አሠርቷዋቸው የነበሩት ፍራሻቸውን ምልክታቸው ሲሆን ዬ11ዱ አብያተ ክርስትያናት ህንጻዎች ሌላው ድንቅ ተግባራት ናቸው። ቀጥሎም የአባይ ውሃ ወደ ግብጽ እንዳይሄድ አድርጎ የግብጽን ንጉሥና ህዝብ ማስቸገሩ በሰፊው ይተረክለታል“ ( ገጽ 15 )* ይህን ምሳሌ ያነሳሁት አባይን በሚመለከት ልክ እንደ ንዑዱ ንጉሥ ላሊበላ አዋቂውና ብልሁ አፄ ፋሲልም  በዘመናቸው የሠሩት ግሩም ተግባር ስላለ ነው። „አባይን“ በሚመለከት ቅኑው አፄ ፋሲልም አስቀድምው ተልመው ዘመናቸው የፈቀደላቸውን የከወኑበት ውብ ተግባር አለ። 

እንዲህ ይሉናል ሊቁ ጸሐፊ ተክለ ፃድቅ መኩሪያ  „ለመንግሥታቸውና ለሕዝባቸው በሰፊው ከማሰባቸው የተነሣ ከእርሳቸው በፊት የነበሩት ነገሥታት ያልሠሩትን የአባይን ድልድይ አንዱን በአፈርዋናት አንዱን በአንድአቤት ሁለት ድልድይ አሠርተውለት ከሞቱ በኋላ አንኳን ነጋዴው ሆነ መንገደኛው ሲያልፍ፤ የፋሲልን ነፍስ ይማር እያለ ያልፍ ነበር። መሃል በጌምድርም ርብን ድልድይን፤ ጉንደር ከተማ አጠገብ የአንገረብ ድልድይን አሰርተዋል። በዘመኑ ለአሳቢው ንጉሥ የተገጠመው እንዲህ ይላል። ከግእዝ ወደ አማርኛ ተመልሶ ቅኔ ነው ቅኝቱ የቀደመውን የሥነ ጹሑፍ እድገትና ምጥቀት ስለሚለካ እንዳላ አቅርቤዋለሁ ---- እንዴትም የበለጸጉ ዕንቁዎች እንደ ነበሩ በህሊና ችሎት አብረን እንቀመጥ ዘንድ በታላቅ ዘንካታ ኢትዮጵያዊ ትህትና ጠዬቅሁ - እኔው። ከመዳህኒተአለም በታች ታላቁ ዳኛ ህሊና ነውና።

„ርብና፡ አባይ፡ መንጠቅ፡ የለመዱ
እንደ፡ ልማዳቸው፡ ሰውን፡ እንዳይገድሉ
በፋሲል፡ ዳኝነት፡ ተፈጥመው፡ ሄዱ።
ርብና፡ አባይ፡ ሸፍተው፡ ሲኖሩ
አላፊ፡ አግዳሚውን፡ ከጎራ፡ እያሰሩ
በትላልቅ፡ ድንጋይ፡ ተደብድበው፡ ቀሩ።
አብርሃም፡ ነው፡ ጣና፡ እንግዳ፡ ተቀባይ
ከቤቱ፡ ቢመጡ፡ ርብና፡ አባይ
ሌቦች፡ ናቸው፡ ሳይል፡ ግብራቸውን፡ ሳያይ
መንገዱን፡ መራቸው፡ እንዲሄዱ በላይ።“ እንዴት ዕጹብ ድንቅ ነው። (ገፅ 154)* 

„ፋሲል፣ ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ግምቦችንና 7 የማያንሱ ቤተክርስቲያኖችን እንዲሁም 7 ድልድዮችንና አክሱም ጽዮን ግንብ አሰርተዋል።“ (ከወጣት ታሪኩ አሰፋ ፌስ ቡክ የተወሰደ) ከዚህም በተጨማሪ በኤርትራ በኩል ገፍተው ከሳቸው የቀደሙት ያልከወኑት በኽረ ተግባር ከውነዋል ደጉ ንጉሥ ዐፄ ፋሲል። እቅማቸውም እጅግ ያደምጡት ያከብሩትም የነበረው ህዝባቸው ነበር።

ይህ ቀደምት ተግባራትን በመጠኑ ያነሳሁት ከአንድ ጎጆ ቤት አንዲት እሳር የመምዘዝ ያህል ነው። ታሪኳና ብቃቷ፤ ተፈጥሯዋና ማንነቷ ጥልቅና ሥህን እንዲሁም የዳጎሰ - አምክኗዊ ገድል ብጡል ነውና።  ታሪኩን በዚህ ገታ አድርጌ ወደ ሌሎች ጉዳይ ላቅና … ለነገሩ ህትምት ላይ ባላው 7ኛ መጸሐፌ የፊት ለፊት ሽፋኑ፤ ዕርእሱ፤  የመታሰቢው ሥጦታና መግቢያው ላይ የተወሰን ጉልት ተመድቦለት ተሠርቷል ከዚያም የተወሰደ ነው የጹሁፌ መግቢያ። ስለምን? ዱላው የበዛበት፣ አሳሩን የሚከፍል ህዝብና ባዕት ስለሆነች ጎንደር ። ነገር ግን ቢሸፈን - ቢረገጥ ዕውነትነቱ ግን ሊጨፈለቅ ወይንም ሊደፈጠጥ ፈጽሞ አይችልም። ጎንደር እውነት ናት!

  • ማህበራዊ ኑሮና ጎንደር።

ጎንደር ላይ ኢትዮጵያዊነት መንፈሱ ሙሉዑ ነው። ስለሆነም ከዬትኛውም አካባቢ፤ የዬትኛውም ብሄረሰብ አባል ይሁን ደጋ - ቆላ - ወይና ደጋ እስከ ደከመው ድረስ ቢሄድ „ጸጉረ ልውጥ“ መጣ ብሎ አካኪ ዘርፍ የሚል አንድ ቀንጣ ሰው አይገኝም። አንድ ጊዜ በማህበረ ቅዱሳን „በሐመር“ መጽሄት ሌላ ክፍለሀገር የገጠር ጉዞ ጎርባጣ ገጠመኝ ልዑኩ ፈትኖት እንደ ነበር አነበብኩና ተንቀጠቀጥኩኝ፤ ጎንደር ዶሮ - በግ - ፍዬል - ሙክቱን ሳይቀር እያረደ፣ እያነጠፈ፣ ብድግ ቁጭ ብሎ እያስተናገደ፣ አደግድጎ እዬጎዘጎዘ ፍቅርን ሰጥቶ ፍቅርን ፈጥሮ የሚሽልም እጅግ ሰው ናፋቂ መሆኑን በእግሬ ተጉዤ ከጫፍ እስከ ጫፍ አይቸዋለሁና። አብረውኝ የሚሄዱት ለሥራ የመጡ ወገኖቼ ናቸው። ግን የእኩልንት ገጹ በፍጽምና ጎንደር ላይ ይከወናል። ጎንደር ላይ የኢትዮጵያዊነት ብሩህ ህሊና ከነሙሉ ወርዱ አለ። ይህ ከገጠር እስከ ከተማ ከደም ጋር የተዋህደ ረቂቅ የጎንደር ልዩ ጠረን የተላበሰ ብቃት ነው።  በሰው እጅ ያልተሠራ፣ በፈረኃ እግዜአብሄር የለማ፣ የሰብዕዊነትን ክብር ያደመጠ፣ ቅጥ ያለው ወጥ የማንነት አንጡራ ሃብት ነው።

እራሱ ይህን ጹሑፍ ስጽፍ ያ … በሰልፍ እንግዳን የሚያስተናግደው የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን የሚታረደው ፍዬልና በግ፣ የሞስብ እንጀራው፤ የወጭቱ፤ የገንቦው ጠላ፤ የቆለምሽሹ ቆሎ፤ የምቸቱ አይብ፤ የግሬራው እርጎ፤ ሰልፍ በምን ቋንቋ በምንስ ብቃት ይገለጻል? ጥበቡ ጥበብን መግልጽ ከሚችለው በላይ የላቀ ነውና። እንግዳ ሲመጣ ሽሚያ ነው። ካልተሄደም ኩርፊያ ነው። ተጎንብሶ እንደ አባት አደሩ ገበታውን ቀረብ አድርጎ ዬአባወራው እግር አጠባው እራሱ በሽሚያ ነው። አንጥፎ - ደልድሎ - ማስተናገዱ የክቱን አውጥቶ አልብሶ ማቅበጡ አልበቃ ብሎ፤  ወፍ ጭጭ ሳይል ሰፈርተኛው ሁሉ እንግዳው በሰላም ስለማደሩ ለማወቅ ጉጉቱን ሳስተወስ - ለእኔ ሰማዬ ሰማዕት የዘለቀ የሰብዕዊነት ቅንብር ነው።

ቀድሞ ነገር እንግዳ የሚያስበው እንዴት ከነዚህ ንጹኃን መለዬት እንደሚችል እንጂ፤ ምን ያህል ከዛ ገጠር መንደር እንደቆዬ አይደለም - በፍጹም። ምን የሚጎድል አለና። አዘውንታት በዛ ለዛ በለው ቃናዊ አገላላጽ ሲተርቡ፤ ኮበሌው እኔ እቀርብ እኔ እቀርብ ከአጠገብ ተቀምጦ ሲታከክ - ተጠግቶ ለመቀመጥ ሲጣደፍ፤ ሴቶች ጠጋ ብለው እያሻሹ ማተብን ሲዳስሱ፤ ህጻናት ከፊት ለፊት መጥተው ሲቧርቁ ከዚህ በላይ የህዝብ ፍቅር ምን ትንግርት የሚባል አለና። ዛሬ በዓለም ያሉ ታዋቂ ሰውችን ለማስፈርም ያለው ጥድፊያ ጎንደር ላይ በቅሎ ከሰከነ ዘመናት ተቆጥረዋል። ያለግነት ለጎንድር ህዝብ „ማስተናገድ“ የህይወቱ በኽረ በትሩ ነው ማለት ይቻላል - የተፈጠረበት - የኖረበትም።

በከተማ በአንዳንድ ቦታ ስትሄዱ እውሃ እንኳን ለማግኘት ጋዳ ነው። ለቅጽበታዊ ቆይታ። ጎንደር ላይ ግን አንድ ሰው ቤት ቀይሮ ወደ አዲሱ ሰፈር ሲገባ ሰፈርተኛው „እንኳን ደህና መጣህ“ በማለት በነፍስ ወከፍ በማንቆርቆሪያ ወይንም በገንቦ ጠላ እዬያዘ ይሄዳል። ምንም የማያውቀውን አዲሱን ጎረቤቱን የቡና ተርቲም አባልተኛነት ፈቅዶ ከቤቱ ድርስ እማ ወራዋ ሄዳ ትጋብዘዋለች። ጾመ ፍልሰቲትን ተንተርሶ ሰፈርተኛው ሙሴ መርጦ 16 ቀናት ማታ ማታ በወል በቆሎና በጠላ ያሳልፋል። „አድርሽኝ“ ይባላል። ሲያበቃ በግ አርደው በጋራ ይገድፋሉ። 

ፍልሰቲት በገባች ቀን አዲስ ጎረቤት ቢመጣ ታዳሚ እንዲሆን ሙሴው ሄዶ በአክብሮት ይጠራዋል። እንጀራ ሲጋገር ያው ሙጎጎ /ምጣድ/ ለማድመቅ ብዙ እንጨት ስለሚፈጅ ጥዋት አንዲት ሴት ቀድማ ካደመቀች  ጸሐይ ብርሃኗን አስክትገድብ ድረስ ሰፈርተኛው ሁሉ አስፈላጊውን ይዞ በደመቀው ምጎጎ ይጋግርል። አዲሷ ጎረቤትም ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ትታደማለች። የፈትል - የስፌት ደቦ ከኖረም በፍቅር ትጋበዛለች።

ሰርግ ሲሆን ሁለት ድንኳን ወይንም ዳስ ይዘጋጃል። አስተናጋጅም እንዲሁ፤ ከብቱም በመሰሉ ይከወናል። አንዱ ለእስልምና አንዱ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን። የሁለቱ የእምነት ፍቅር እጅግ ጥልቅ ባለማርዳ ነው - ናርዶስ።  ዬእስልምና አማንያንን ዝምድና ተፈልጎ የማይገኝ በመሆኑ ጡት በማጥባት፤ ግርዛቱን አቅፈው እንዲያስፈጽሙ በማድረግ ጥምረቱ - ውህደቱ በፍቅር ለፍቅር ይታደማል። እንዲያውም አንድ የእስልማና ዕምነት ወዳጅ ያለው ዕድለኛ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው። ኢትዮ - እስራኤላውያን በነበሩበትም ጊዜ ተመሳሳዩ ተግባር ይከወናል። 

አንድ ሹፈር ከመሃል ሀገር በድንገት መጥቶ ህይወቱ ቢያልፍ ሃዘንተኛውን መለዬት እስኪቸግር ድርስ ነዋሪው በሙሉ ኃላፊነቱን ተረክቦ ፍጹም ልዩ በሆነ በተሰመጠ ሀዘን እንዲሁም፤ በባለቤትነት ስሜት ያስተናግዳል። ይህ ህብረ ብዙኃን ብልህነት፤ በማስተዋል የተጠለፈ ተግባር ከእውነት በላይ እውነት ነው። እውነትን እራሱ ያበቀለ - ያጸደቀ። እራሱን ላወቀ፤ በዬዘመናቱ መበደሉን እያወቀ ግን በአርምሞና በትእግስት የላቀችውን እናት ሀገሩን ጉዳይ በማስቀደም በተደሞና በአርምሞ እንዲሁም በጭምትንት የተቀመጠን ህዝብ ሰብዕና፤ ከእኛም አልፎ ዬዐለም ሃብትና ቅርስ የሆኑ ውድ ጌጦቻችን ያሉበትን ቦታ፤ ለማንኛውም ቋያ ነክ ግዳጅ መቆስቆሻው የሆነውን ወርቅ ህዝብ ዛሬ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይብጠለጠላል በሶስት ተመድቦ …. ይከተከታል ግን ለምን?!!!
ውዶቼ ልሰናበት ጥቂት ደቂቃዎች ቀሩኝ። 

ክፍል አንድን ያላነበባችሁ ሊንኩ ቀጣዩ ይሆናል። http://en.wikipedia.org/wiki/User:Aatebeje በነገራችን ላይ  ጹሑፉ ካለቀ በኋላ በማራኪው ጎንደርኛ ጹዑም ቃና በድምጽም ሽሙንምን ብሎ ይቃኛል። ሞትን መቅደም ብልህነት ነው። ስለ ብልሆችም መመስከር ሰምዕትነት። ከዚህ ሌላ ያው የተለመደው ራዲዮ ፕሮግራም ጀግና ወዳጁ መንፈስ - ሐሙስ የቀን ቅዱስ በ22.05.2014  ከ15 እስከ 16  ሰዓት የወረሰውን ትውፊት አብሮነት ይዞ ቀርቧል። አርኬቡ ላይ ስለሚገኝ፤ መኮምኮም ይቻላል - ሜዞ አልቦሽ።

አሃ! ምን ቀረኝ  ጊዜያዊ ስንብት።
ዬክፍል ሁለት ክወና። የምወዳችሁ ክብረቶቼ  በዬአጋጣሚው የምትሰሙትን ጎንደርን ጥላሸት የመቀባት ድልዝ -ዝክንትል ዕይታ በህሊና አደባባይ ችሎት አደላድላችሁ ፍርዱን ትሰጡ ዘንድ በትህትና ዝቅ ብዬ እኔ ሎሌያችሁ ሥርጉተ ሥላሴ እዬጠዬኩኝ በቀጠሮ ክፍል ሦስት ይዤ እስክቀርብ ድረስ ደህና ሰንብቱልኝ - ማገሮቼ።

ማሳሰቢያ። የኮከብ ምልክቶች ዬጹሑፉ ምንጭ ነው። ከዐፄ ልብለድንግል እስከ ዐፄ ቴውድሮስ ከሊቁ ፀሐፊ ተክለፃድቅ መኩሪያ መጸሐፍ የተወሰደ መሆኑን ያመለክታል።
ትውልዳዊ ድርሻችን በህብረትና በአንድነት እንወጣ!


ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።














አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።