ትሁታዊ የምስጋና መልዕክት ለነፃነቴ ለሳተናው አዘጋጅ።
የማከብርህ ሳተናው የልዑል እግዚአብሄር ታዛዦች ሊቀነ -
መላዕክታት እና መላዕከተ - ሠራዊት ይጠብቁህ። አሜን!
ከሥርጉተ - ሥላሴ(Sergute©Sselassie)
03.04.2018 (ከጭምቷ - ሲዊዘርላንድ።)
03.04.2018 (ከጭምቷ - ሲዊዘርላንድ።)
„የብልህ ሰው አሳቡ እንደ ክረምት ውሃ ነው፤
ምክሩም እንደ ገነት ውሃ ብዙ ነው።“
(መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፳፩ ቁጥር ፲፫)
ምክሩም እንደ ገነት ውሃ ብዙ ነው።“
(መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፳፩ ቁጥር ፲፫)
- · እፍታ!
እጅግ የማከብርህ ወንድሜ የሳተናው ድህረ ገጽ
ዋና አዘጋጅ ሳተናው እንደምን አለህልኝ? እኔ መንፈሴን ካዳነው፤ አንተ በሙሉ ልቦናህ ከፈቀድክልኝ የብዕር ልዩ ነፃነት ከሰጠኝ
የመንፈስ ትንሳኤ ጋር በእጅጉ ደህና ነኝ። በቅድሚያ ልጆች እና ባለቤት ከኖሩህ ፈጣሪ አምላክ ጥበቃው አይላያቸው ዘንድ በርከክ
ብዬ አማጸናዋለሁኝ። ለአንተንም የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሄር በሊቀ መላዕክታቱ እና በሠራዊተ መላዕከቱ ጥበቃ እንዳይለይህ እማጸነዋለሁኝ።
እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም ውጽፍተ ወርቅም ርህርህናዋ አይለይህ። አሜን።
- · ዕለቲት በምለሰት እስቲ ትቃኝ።
ታቡቱን የተሸኩመለት የዐጤ አዳም ሰገድ እያሱን
ደብር ደብረብርሃን ሥላሴን የጹሑፌ ዓውደ ምህረት ዛሬ አደረኩት። ስለምን ቢባል የእኔን የደካማዋን ሳይሆን የብርቱዎቹ አያቅት ቅድመ
አያቶቼ ያገለግሉበት ታቦተ አጋይስታዓለሙ ሥላሴ በረከታቸው እንዳይለይህ
ለመማጸን ነው ላንተ ለማከብርህ ለሳተናው። በዛ ላይ ህማማት ትዝ አለኝ። በልጅነት በቤተሰብ ይደረግ የነበሩ ሥርዓተ ክንውኖች ሁሉ
ሽው አለኝ። መጋቢት 24 ቀን 2010 ትዝታን ጠራው። ቤተሰቦቼ ከቀደመው ጊዜ ጀምሮ አገልጋዮች ናቸው በዚህ ታሪካዊ ደብር። ዓራት
ዓይናማ ሊቃነ - ሊቃናት ነበሩ በምድረ ጎንደር የታወቁ ሥምጥርም። ጋብቻቸውን፤ ጉርብትናቸውን፤ ወዳጅነታቸውን እና አብልጅነታቸውን
የሚመኙት በርካቶች ነበሩ። ፈርሃ እግዚአብሄር የቃኛቸው መሬት እንኳን ቀስ አድርጋችሁ እርገጧት ስትራመዱ አትደብዱባት በማለት ነበር
እናቴን ያሳደጓት።
እትበቴ የተቀበረው በዚህው ሥፍራ ነው። ሥርዓት
ጥምቀቴ የተፈጸመው እና „ሥርጉተ ሥላሴ“ ተብዬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የልጅነት ክብር የተሰጠኝ በዚኸው ደብር ነው። ያደኩት
ጨዋ ሰፈር ከእናቴ ጋር ሲሆን እንዲሁም አደባባይ እዬሱስ ደግሞ ከአባቴ ጋር ቢሆንም ግን ፊደል የቆጠርኩት እዚኸው ነው። አባ በጸሃ
ነበሩ የመጀመሪያ የፊደል ገበታ ያስጀመሩኝ የኔታዬ ሲሆኑ የቅኔም መምህር ናቸው። ከአቨይ የምሄደው ት/ ቤት ሲዘጋ እና ከዛ መጸሐፍት
እንደልቤ ለማንበብ ነው። ዛሬ እንደ እሳት የሚበላኝ ቀጥዬው ቢሆን እምለው ዳዊትም ተወጥኖ የነበረው በዚኸው የቅኔ ዓዋራ የታሪክ
ቃና ሰፈር ደብርብርሃን ሥላሴ ነበር።
ወደ ሰፊው የፍቅር ቤተሰቦቼ ወደ አሉበት እሚቶቼ፤
አክስት አጎቶቼ ሠፈር ስሄድ የምቧርቀበት „ዋሾ ሜዳ“ እና መግቢያው ላይ ያለው ማርገጃ ወይራ ከህማማት ጋር// ከፍልሰቲት ጋር
የልጅነት ጊዜ ሲታወስ በምልሰት ወስጤን በናፍቆት አመሰውና አተራመሰው። እናም ዛሬ እስኪ ሰኝት የሰጠኝን፤ በፍሰሃዬ ሰሞናት ላነሳሳህ፤
መንፈስ ቅዱስንም ለወዳጄ ለሳተናው ላክልኝ አልኩኝ። ረቂቅ መንፈሱን በገፍ የቀለበኝን ስስቴን ቀዬ ያለበትን የታሪክ አምድ የሆነው
የደብሩን መለያ የአምዴ ርዕስ ጉዳይም አደረኩት። ከሁሉ በላይ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሠራዊተ መላዕክት ጥበቃቸውን ለአንተም ለሳተናውም
ሰላም እና ፍቅርን ለሚመኙ ቅኖች የጹሑፌ ታዳሚ ለሆኑ ለወገኖቼም እንዳይለያቸው በማሰብ ነው - ህማማትን ከስግደቱ ጋር እባክህን
ተገናኝ ብዬ የፈቀድኩለት። ።
ደብረብርሃን ሥላሴ ታሪኩ ጥልቅ ነው። ገጸ ምህረቱን
ብቻ ላንሳ፤ በወይራ ዛፍ የተከበበ ነው። ገዳማዊ ግርማ ሞገስ አለው። የዛሬን አያደርገው እና ጸጥ ያለ ረጭ ያለ የምድር ገነት
ነበር። ደርግ ለህዝብ ቦታውን እስከ ሸነሽነው ድረስ ሁለት ባላባቶች ብቻ እስከነ መላ ቤተሰቦቻቸው የሚኖሩበት በአጽዋት እና በወፎች
ዝማሬ ብቻ የተቀደስ ሥፍራ ነበር። በዛ ላይ በሳር የተሠሩ የጎጆ ቤቶች ቅኔ ቤቱ ሲደመር መንፈሳዊ የትሩፋት ግርማው የት እዬለሌ
ነበር። በጀርባው ገላዕድ የሚባል ተራራ አለ። ይህ ደግሞ ከቅድሰት ሐገረ ከእስራኤል፤ ከቅዱሱ ወንጌል ጋር በጽኑ ትውፊት ያስተሳስረናል።
ፊት ለፊቱ ከገላዕድ ተራራው ማለቴ ነው የአጤ
ፋሲል ልጅ ድንቅ ታሪክ የፈጸሙበት ደፈጫ ኪዳንምህረት አለ። ታሪካዊ ሥፍራ ነው። ቁልቁል ሲመለከቱት አንገረብ ኮራ እና ደልደል
ብሎ ይገኛል፤ በተጨማሪ እንቡጢጣው የጵጉሚት መጠመቂያችን ኮኮችም አክሎ ሳቢ እና ማራኪ የተፈጥሮ ውበት አለው። በአንገረብ እና
በገላዕድ ተራራ ሥር ደግሞ ለጥ ያለ ቤተሰቦቼ ያርሱት የነበረ የእርሻ ማሳ ነበር። በገላዕድ ተራራ በመግቢያው ዝንጥል ብሎ ወደ
ጎን አጋሙ ሸሎቄ ሲኖር ሌላም ታላቅ ቅርስ አለ - በቅርበት። እሱን ለጊዜው ልተዎው። ቤተሰቦቼ የአብርሃሙ ሥላሴ አገልጋዮቹ ስለነበሩ
በተግባርም አድርገውበት እና ሆነውበት ኖረው ታላላቆቹ አልፈዋል። ቀደምቶቹ አያቶቼ የጌታችን መዳህኒታችን የእዬሱስ ክርስቶስ ባዕለ
- ልደትን ነዳያን ጠርተው፤ ድንኳን ጥለው አደግድገው ታጥቀው፤ ፆማቸውን በቁርጥ / በጥብስ ሥጋ እንዲገድፉ የሚያደርጉበት የምርቃት
ቦታ ነበር። የበረከት ቦታ ነው። የመኖሪያ ቤቱ ዓውራ በር መግቢያ
እራሱ ደጀ ሰላም ይመሰል ነበር። ቦታው ሳይሸነሽን። አሁን ቅርስነቱ እንብዛም ነው። ከጥንቃቄ ጉድለቶች የተነሳ ውስጣችን ጥሪት
አልቦሽ በሚያደርጉ ግድፈቶች የከተሙ ናቸው የተግባር አፈጻጻማችን ሆነ የውሳኔ አሰጣጣችን። ከዛ ቦታ የግለሰብ ቦታ ምሪት ባይኖር
የትውፊት ሥርዓቱን በነበረው መልክ ለማቆዬት ዕድሉ ሰፊ ነበር። ገዳም እኮ ነው።ቢያስፈልግም ሌሎች ቅርስ ጠባቂ ነገሮች መገንባቱ
የበለጠ ለትውልዱ ውርስ ቅርስ ይሆን ነበር። አሁን ደብሩ ጸጥታውም እርጋታውንም ተቀምቷል። ጠረኑም ከተሜ ሆኗል።
- · ጥሞናው የደብሩ።
ወደ ቤተክርስትያኑ ከመዝለቃችን በፊት ዋናው የቤተ
እግዚአብሄሩ ደጀ ሰላሙ በግርማ አቀባበል ያደርጋል። ፎቅም አለው፤ ከሌላ ቦታ መጥተው የሚያገለግሉ አቨው የሚኖሩበት የእነአባ ጌራ፤
አባ ሃይለማርያም የሚባሉ ደናግላን መኖሪያ ነበር። ማዕዳቸው የሚዘጋጅላቸውም ከአያቶቼ ቤት ነበር። በዬተራ ወስደን እንዳርስላችው
ነበር፤ ቀደም ባለው ጊዜ ቅጽር ግቢው አዱኛው፤ ጠሩኑ የተለዬ ነበር። ጠጅ እሳር፤ ነጭ እርያን፤ አክርማ፤ ግራምጣ፤ ግጫ ግራ ቀኝ
ይበቅልበት ነበር። ዙሪያውን ያሉት አግናባት የእንቁላል ግንብ ይባላሉ። ታሪካቸው እንሚናገረው በእንቁላል ውሃ የተገነቡ ናቸው።
ከእኔ በቀደሙት በወንዶች በኩል ባሉት አግናባቱ ውስጥ ማጠንት ይታይ እንደ ነበር አባቶቼ ይገልጹ ነበር። በእኔ ዕድሜም በአግናባቱ
ውስጥ ማጠንት በተሟላ ሁኔታ ይሸት ነበር። ፊት ለፊት ያሉት አግናባት ደግሞ አያት ቅድመ አያቶቼ የተቀበሩበት ሲሆን ወለል ሆኖ
በቋሚነት አግናባቱን ተጠልለው የሚያስቀድሱ ምዕመን ቋሚ ቦታ ነው። የዐጤ በካፋ፤ የእናታቸው የቅድሰት ማርያማዊት ከዲማ ድረስ መጥተው
እንዲሁም የልጅ ልጆች አጽመ ርስትም በክብር ያረፈው በዚኸው ድንቁ ደብረብርሃን ሥላሴ ነው። የታሪካችን ምስክር ነው።
ከሁሉ በፊት ትዝ የሚለኝ ጉሬዛ ነበር። ጉሬዛው
ኑሮው በሰልፍ በተጠንቀቅ ገዝፈው ይታዩ ከነበሩ የወይራ ዘሮች ላይ ነበር። የወይራ ዛፍ ከመጀመሪያው ቅጽር ግቢም ከሁለተኛው ቅጽር
ግቢም በስፋት ነበረ። እሮብ እና አርብ ቀን እና ሌሊት ጉሬዛ በምንም ታምር መሬት አይወርድም። ምግብም አይመገብም ነበር። ስለምን?
ጉሬዛ ሲፈጠር ከአንገቱ ላይ በተፈጥሮ መቁጠሪያ አድርጎ ነው ፈጣሪ የፈጠረው። ጉሬዛ መነኩሴ ነው። ጉሬዛ ከእርግብ ባላነሰ የተቀደስ
እንሰሳ ነው። ንጽህናው ጥራቱም አደቡም የተለዬ ነው።
ወደ ቤተ ክርስትያኑ ውስጥ ስንዘልቅ ከአትራኖሱ
ሥር ቀለሟን እስታሁን ድረስ አይቻት የማላውቅ የእናቴ እናት የጸበል ማሰሮ ነበረች። መክደኛም በልኳ የተሰራ ነበራት። ሁልጊዜ ጸበል
ይቀመጥባታል። ሲያስፈልግ በካህን አስቀድታ ታመጣና ቤቱን ግቢውን ሁሉ ትረጨው ነበር። ብዙ የኮክ፤ የጌሾ፤ የሎሚ፤ የበርቶ ሎሚ፤
ያዩንዶ በርበሬ፤ የቡና፤ የአደስ ተክላት/ እጽዋት ስለነበረም ጓሮው ሁሉም ጸበል ይረጫል። ወደ ቀደመው ስመለስ አትራኖሱ ሲጎድልም
ወስዳ እሷ ሳትሆን ካህናቱ አዲሱን ውሃ እንዲያጋቡላት ታደርግ ነበር። እሚታዬ ከካህናቱ ጋር ነበር ቤተ እግዚአብሄርን እኩል የምትከፍተው
ማለት ይቻላል። ሰዓታቱን ቁማ ነበር አብራ የምታነጋው። ሌላ የሚገርመኝ የእናቴ እናት ኤሊ ታረባ ነበር። ዛሬ ውጪ ሐገር ኤሊ ሳይ
በዛ ዘመን የእናቴ እናት ከኤሊ ጋር የነበራት ወዳጅነታቸው፤ የነበራቸው ትስስር እንክብካቤዋን ሳስበው ምን ያህል ጢጢዬ የቀደመች
እንደሆነች መልዕክት ይልክልኛል - ዛሬ ላይ። እኛ እኮ ሁሉ አለን። አላወቅንበትም እንጂ።
- · ሳንቃው ሚኬኤል።
ከሰዓታት / ማህሌት መቆሚያው ፊት ለፈት ከአድህኖ
ሥዕላቱ ሥር የሚታይው ሳንቃው ሚኬኤል የሚባል አለ። በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ የተመረጡ ካህን ይከፍቱታል። የአልተመረጡ ከሆነ ይወድቃሉ።
ደፍረው መክፈት ይሳናቸዋል። ኢትዮጵያ ሲከፋት አድህኖ ስዕሉ ይጠቁራል። ሲቀል ሸክሙ ደግሞ ይፈካል። ታላቁ የዚህ ቀን ምስክሩ አድህኖ
ሥዕሉ የሚሰጠው ምልክት ነበር። ዛሬስ ምን ይመሰል ይሆን? እንዲህ የሞት ዓዋጁ በህግ ሲከወን እላለሁኝ ሁልጊዜ ሰኔ እና ህዳር
ሚኬኤል ሲደርስ። ሁልጊዜም ሰኔ ሚኬኤል እና ህዳር ሚኬኤል መጋረጃው ሲገለጥ የሐገሬን መከራ በተለዬ ሁኔታ አስበዋለሁኝ። እርግጠኛ
ነኝ ጥቁረት እንደሚታይበት። ለዕለቱ ስለ ናፍቆቴ፤ ስስቴ የመንፈስ ብልጽግናን አብዝቶ ስለ አበቀለልኝ ደብረብርሃን ሥላሴ ለዛሬ
ተዚህ ላይ ገታ አድርጌ ብዕሬን ነፃ ስላወጣኝ መንፈስ ትንሽ ደግሞ ልበል። የዚያ ቅድስና ስጦታ ነው እና። የነፃነት ቀን፤ የነፃነት
ዜና ደስ ይላል ሲያጋጥም በግጥም።
- · ነፃነት በሳተናው ብርና።
እኔ እንደ ተዋህዶ ልጅነቴ ነፃ የወጣሁበት ዓመት
ነበር ብዬ አስባለሁኝ። ረጅም ጊዜ ጹሑፌን ያለማቋረጥ ያስተናገደው የሳተናው ብራና ነፃነቴን ሲሰጠኝ ጤናዬንም መልሶልኛል። አይዞሽንም
በሰጠኝ ነፃነት ልክ ልኮልኛል። ወንድም ጥቃት ሲያወጣ ነው ጋሻዬ የሚባለው። ጋሻዬ ሆኖል። ጥቃቴን አውጥቷል። ወጣትነቴን የገበርኩበት
የሐገሬ ፖለቲካዊ ጉዳይንም አያገባሽም ተብዬ ማዕቀብ የተጣለበት ዘመን ሥር ነቀል አብዮት ያካሄደው የጀግናዬ ሳተናው ብርና ብቻ
እና ብቻ ነው። ነፃነት ሰው የሚሰጠው እና የሚነሳው ባይሆንም ሰውም የራሱ ድርሻ አለው፤ ነፃነትን በመስጠት እና በማገድ። ሁልጊዜ
ሰዎች ጹሑፍሽን አነበብነው ሲሉኝ ካላቋረጡኝ እል ነበር። በዚህ ተፈትኖ ያልወደቀ አልነበረም፤ ከሳተናው በስተቀር። አመስግንሃለሁ
የሚለው ቃል ያንስብኛል፤ ብቻ ህይወቴን መልሰኸልኛል እና ያደኩበት ደብርብርሃን ሥላሴ ለእኔ የሰጠውን በፈተና ያለመሸነፍ ጥንካሬ
እና ብርታት ይሰጥልኝ ዘንድ አዘውትሬ ጸሎቴን አቀረባለሁኝ ላሰደገኝ ታቦት ደብርብርሃን ሥላሴ - በትጋት። ብርቀውም አድህኖ ቅርሱ
ቤቴ ውስጥ ስላለ ቀጥ ብሎ ይሰማኛል።
ዕውነት ለመናገር የድቅድቅ ጨለማ ጊዜ ነበር።
የመከራ ጊዜ ነበር። በማታውቁት ነገር የማታውቁት ክፉ መንፈስ በተሰወረ ሴራ መጠነ ያለመቋረጥ በተከታታይነት ሰፊ እገዳ ሲያስጥል፤
ስትገለሉ እጅግ ፈታኝ ጊዜ ነበር። ከሳሻችሁ አይታወቅም፤ ፈራጁም ሥም የለሽ ነው። ብቻ ከምድረ ገጽ እንድትወጡ፤ አቅማችሁ ተሰብሮ
የተረሳችሁ ዕቃ ነገር እንድትሆኑ ነበር ተጋድሎው። የፈጣሪን ሃይል ግን ማንም እና ምንም ሊነካው አይችልም።
ኢትዮጵያ ያለው ጸሐፊ፤ ጋዜጠኛ ኢትዮጵያ ብቻ
ይመስለዋል መከራው፤ እዚህም መከራው በፍጹም ሁኔታ ሊነገር አይችልም። ረቂቅ እና እጅግም ፈታኝ ነበር። ነፃነት ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን
እዚህ ያሉ ጉልበተኞችም የነፈጉትን፤ ያሰሩትን ነፃነት እስከ አሳሪዎቻቸው ማስፈታት አለባቸው። ቀድመው ኢትዮጵያ ላይ የነፃነት ተፎካካሪ
ነን ከማለታቸው በፊት። አዲስ ሥርዓት የመዘርጋት ግዙፍ ተግባራቸው አለ በመዳፋቸው ላይ - ስደትም ላይም። „መተማመኛችን ምንድነው?“
ብቻ ሳይሆን እናንተም ዕድሉን ብታገኙ እዛ ሄዳችሁ የማታፍኑ፤ የማታስሩ፤ ጋዜጠኛ እና ብዕርን የማትፈሩ፤ በፖለቲካ የተለዮችሁን
ማህበራዊ መሠረታቸውን በዘመቻ የማታናጉ፤ ነፃነትን የማትገድቡ፤ የበለጠን የማትቀናቀኑ፤ የመንፈስ በደልን በስውር የማትፈጽሙ ስለመሆነችሁ
እኛም ከዚህ መተማመኛ እንሻለን። ቁርጥ ውሳኔ በመሆን መስመር ማዬትን እንፈልጋለን። ተሰቃይተናል። ስማችን ከስሏል በወታደሮቻችሁ።
ፍጹማዊ ለውጥ እንጠይቃለን።
ሳተናው ለብዙዎቹ የመፍትሄ መንገድ ይመስለኛል
እንደ እኔ። አቅም ታቁሮ፤ ተኮድኩዶ፤ ተዳፍኖ፤ ባክኖ፤ ተቀብሮ እንዲኖር የነበረው የዘመቻ ማሳደድን መሪነት ከዚህ እንዲጀመር በተግባር
እንይ ውጪ ሐገር። ለዛው ቀለብ ስፈሩልን አላልነም በራሳችን ገንዘብ እና ጊዜ ለምንተጋው ነው ማዕቀቡ። ከዚህ በላይ መሄድ አያስፈልገኝም።
ሁሉን ቢናገሩት „ሆድ ባዶ ይቀራል“ ይላል የእትብቴ መሠረት ጎንደርዬ።
ዛሬ ይህን የምስጋና እና የእግዚአብሄር ይስጥልኝ
ሰነድ ስጽፍ ቀድሞ ሳተናው ለእኔ የሰጠኝን ነፃነት እና ዓለምዓቀፉ ማህበረሰብ መልዕክቴን ክብር ሰጥቶ ያዳመጠኝን ቀን በሀገሬ በኢትዮጵያ
በማዕከላዊ መንግሥት ደረጃ ለዛውም በአሃዱ ቀን መጋቢት 24 ቀን 2010፤ በባዕለ ሹመት ማድመጥ በመቻሌ ከማንም እና ከምንም በላይ
ፈጣሪ ከሰማያ ሰማያት ወርዶ አይዞሽ የሚል ድምጽ ያሰማኝ ነው የመሰለኝ። ድምጽ አልባው የኢትዮጵያ ሴቶች / ዕንባ የ43 ዓመት
ሙሉ ሰሚ፤ አድማጭ አለገኘም ነበር - በባዕቱ፤ በመሬቱ፤ በብትን አፈሩ። ዛሬ ዜናው ተመስገን እንድለው አድርጎኛል። ሐሤቱን እያጣጣምኩት
ነው።
- · ሴቶች ቅኔ ናቸው!
በኢሜል በዶር አብይ አህመድ ዙሪያ ከቅኖች ጋር
ሙግት እናደርግ ነበር። በዛ ውስጥ የሴቶች ጉዳይ ሲነሳ አንድ የማከብራቸው ጋዜጠኛ „እመቤት ሥርጉተ“ እናንተም እኮ በጣም ትርቃላችሁ
ሲሉኝ ዝርዝር መልሴን ሰጥቼ ነበር። በመልሴ ውስጥ የሴቶች ነፃነት
ከማለት ወደ ተግባር የሚሸጋገረው ዶር አብይ አህመድ ጠ/ ሚር ሲሆኑ ብቻ ነው ብዬ የካቲት 11.2018 በፈንጆች ልኬላቸው ነበር።
ያን ጊዜ የኦህዴድ የጽ/ቤት ቤት ሃላፊ ነበሩ። ኢሜሉም የላኩበት
አለ። አሁንም ጸሐፊው ተግተው ስለሚጽፉ ይታዘቡታል ይህን ጉዳይ። ለሌላም አካል ፍላጎቴን ስገልጽ ለጠ/ ሚር ዕጩነት ሲቀርቡ ድምጽ
አልባው የኢትዮጵያ እናቶች / ሴቶች ዕንባ፤ እንግልት መስዋዕትነት ዕውቅና እንዲያገኝ ከፈለጋችሁ የዶር አብይን በመንፈስ እገዙልን
ብያቸው ነበር። እግዚአብሄር የልብን መሻት ያያል እና መመረጣቸው ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያው የሴቶች ታላቅ የእውቅና ደወል እንሆ
በጓዳ ሳይሆን በአደባባይ ተደወለ። ቃል አባይ አላደረጉኝም። ሃሳብን በነፃነት መግለጽም እንሆ አጀንዳ ሆነ። ተፎካካሪ ሃሳብም ዕውቅና
አገኘ። ደፋር አገኘ ሁሉም ስብዕና!
በጨላማ ድቅድቅ ተውጦ የነበረው የማይደፈረው በርም
በብርሃን ተከፈተ። በተለይ ሴቶች እንደ ሌላው ማህበረሰብ ዜጋ ሆነን እንዳልተፈጠርን የታይነበት ዘመን አክትሞ እነሆ የኢትዮጵያ
ሴቶች በአጀንዳ በጉዳይነት በቁም ነገር ቀረብን። የኢትዮጵያ ሴቶች ወጣትነታችን፤ ውበታችን፤ ቀላማችን፤ አቅማችን የሰዋንበት የተጋድሎ
ምዕራፋት፤ የመኖር ጣዕማችን የገበርንበት የነፃነት ራህብ፤ የእምነት መስክ ሁሉ መና ምደረ በዳ ነበር። አቋጣሪ፤ መስካሪ፤ አክባሪ
ያልነበረው እንደ ማበሻ ጨርቅ የትሜና የተጣለ ትርፍ አንጀት ነበር።
ዛሬ ለቀኑ ቀን ሰጠው። በርግጠኝነት ሴቶች ዕውቅና
ማግኘት የሚችሉበት ምዕራፍ ስለመሆኑ መልዕከቴ የደረሳቸው ሁሉ አስተርጉመው የአዲሱን ጠ/ ሚር ንግግር ሲያዳምጡት ሁልጊዜም እኔ
የማነሳቸው ነጥቦችን የፋክት ጭብጦች መስካሪ ስለሚሆኑ ደስታዬ ሐሴት ነው። እኔ ካነሳኋቸው አንድስም እንኳን የተዘለለ ሃሳብ የለም።
ይገርማል። ብልሆች ናቸው እና ያገናዝቡታል። ያስተያዩታል። ምስክርነቴን በተግባር በአንደበት ያስከበረው የደብርብርሃኑ ሥላሴ ቅዱስ
መንፈስ ሃዲዱን ዘርግቶ በእውን መሆን ሆነው። ገና በመጀመሪያው ቀን ነበር የኢትዮጵያ ሴቶች ሆይ! የተባልነው። እንዴት የታደለ
ቀን ነበር። እንዴትስ ሥህናዊ ቀን ነበር። እንዴትስ ደማም ማዕልት ነበር። ይገርማል። አለመሞቴን ወደድኩት መኖሬንም ፈቀድኩት።
የኢትዮጵያ ችግር መፍቴሄዋ ያለውም ከዚህ ማህለቅ
ውስጥ ነው። እኛ እኮ አልነበረንም በመንፈስ ስሩዝ ነበርን። እንፈራ ነበር። እንደ ሰውም ታይተን አቅም፤ ችሎታ፤ ብቃት፤ መፍጠር፤
ማደራጀት፤ መምራት አላቸው ተብለን አናውቅም። ለምስል የማኒፌስቶ ማህበረተኞች የአንድ ሁለት አንስትን በቴሌቪዥን መስኮት ብቃታ
ማሳዬት ሳይሆን አጀንዳ የመሆናችን ቁምነገር ነው ኢትዮጵያን ሐገሬ ሊያሰኛት የሚችለው። በወገን፤ በዘመድ፤ በዞግ ያልተሰፈረ አቅርቦተ
እኛዊነት ነው ኢትዮጵያዊ መሆኔን የሚያትምልኝ። የዘወትር ኢትዮጵያዊ ነበርን በተለይ ባለቤት አልባዎች። የክቶቹ ደግሞ ሌሎች። ስንት
መገለል? ስንት መስቃ ተሰማ ታዬ? ባይተዋርነትን በዓይነት አስተናገድን። ዛሬ ዕድሜ „ለኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ካሰን!
ኢትዮጵያም እንደ ሌሎቹ የዓለም ሐገራት ሴት ልጆች
ተፈጥረውባታል ማለት የሚቻለው „አላችሁን“ ስንባል ነው። በስደት ላይ ስደተኛ እና ባይተዋር ነበርኩኝ እኔ ሥርጉተ - ሥላሴ። ጎርፍ
ያመጣኝ ምናምንቴ ….
የኢትዮጵያ ሴቶች በሐገር ምሥረታው ሂደት ግንባር
ቀደሙን ድርብ፤ ንብርብር ሃላፊነት መወጣታችን የኢትዮጵያ ግርማ ሞገስ ሆኖ አክብሮት ዕውቅና ሲሰጠው ነው „ሰው“ ናችሁ መባላችን
የሚረጋገጠው። የዴሞክራሲው መጠን የሚለካውም ለእኛ በሚሰጠው ክንድ ይለካል፤ ይመዘናል፤ ይሰፈራል። ስብዕዊነት፤ ተፈጥሯዊነት የሚባለውም
እንዲሁ … በስተቀር ግን የቁራ ጩኽት ነው …
- · እናትነት።
ከዚህ በመለስ እያለቀስኩኝ ባዳምጠመውም፤ ውስጤ
በእጅጉ ቢጎዳብኝም እኔ ስለ እናቴ እንግልት፤ የማይልቅ መከራ እና ሰቀቀን ለዶር አብይ አህመድ በጻፍኩላቸው ላይ በእኔ እናት ውስጥ
የኢትዮጵያ እናቶችን የፍዳ ልክ ይዩት ብዬ ነበር። ዛሬም እናቴ በህይወት ከኖረች ድምጼን አትሰማም፤ እኔም አልሰማም፤ የውስጡም
የውጩም ጫናው ሲበዛብኝ ግንኙነታችን መቆም ነበረበት። ቆርጬ እና ወስኜ አቆምኩት። እንኳንስ ለእኔ ለልጇ ለመንገደኛው ሁሉ እናት
የሆነችውን ብልኋዋን እናቴን ባልፈቀድኩት መፍቀድ ውስጥ ወሰኜ
ድምፆን ገደብኩት። ውስጤ ፈራብኝ። እንዳልቀማ። የችግሯ መደረቢያ እንዳልሆን ስጋቱ ናጠኝ።
ዛሬ ጠ/ ሚር ዶር አብይ አህመድ እኔ ያልኩትን
ነው የደገሙት። ንጹኽ ፍቅርን ከብልህነት እና ከተፈጠሮ ልቅና ጋር አጥብታ ያሳዳገች ግን በሥጋ የተለዬች የድንቆች ድንቅ፤ የፍቅሮች
ፍቅር፤ የዓለም ልዩ አለምን ኢትዮጵያዊቷን እናት ሲያነሱ ፈቃድ ጠዬቁ፤ በዛ ውስጥም የውስጥ ፍሬያቸው እና ሰብላቸው ሐዘናቸውን
ሲገልጹት ከ50 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱትን ድምጽ አልባዎችን የኢትዮጵያ ሴቶችን እልቀተ ቢስ መከራ በዛ ውስጥ ለማዬት ፈቀዱ። ፍቅራቸውን፤
ውስጣቸውን፤ አክብሮታቸውን በታላቅ ክብር በኪዳን ውል ከኢትዮጵያ እናቶች ሴቶች ዕንባ ጋር አስተሳሰሩት። ይህ ነበር እኔ ተግቼ
ሥሰራበት የኖርኩት አጀንደዬ። ተዚህ ንቅንቅ አልልም ስለው የነበረውን ዛሬ ባለቤት በሀገሬ መሬት አገኘ። አረፍኩኝ። ተመስገን።
ምኞቴም ታጋድሎዬም ይህ ቀን እንዲመጣ ነበር። ከመሞቴ በፊት ይህን መስማቴ ሌላ የህይወት የአቅም እና የሃይል የተስፋ ምዕራፍ ከፍቶልኛል።
ይሕንኑ ነው ያሉት ዕድማታው „አንዲት ኢትዮጵያዊ ሴት እናቴን ሳስባት ዛሬ በህይወት ከጎኔ መቆም ባትችልም በሷ ውስጥ የኢትዮጵያን
እናቶች አያቸዋለሁ“ ነበር ያሉት። አሁንም ዕንባዬ ያስቸግርኛል - ስጽፈው። ስንት ሐሤት አተረፍኩኝ? ሰንት ሐሤት ይኖረኝ? አርቲስት
ጌትሻ አብሮ አደግ እንደሆነ ገልጾ ሰሞኑን በሰጠው ቃለ ምልልስ ውስጡ „ተንኮል
አስቦ የማያውቅ ብቻ ሳይሆን ስጦታችን ነው ታድለናል“ ነበር
ያለው። ለጥፌዋለሁኝ ከሥር። በዕንባ እና በመከራ 43 ዓመት ሙሉ ድቅቅ ላሉት ለድምጽ አልባዎቹ ለኢትዮጵያ እናቶች የትንሳኤ መባቻ
ነው። ጸሐይ! የዚህ ሁሉ መሠረት ግን ዘመኑን በመሆን የቀደሙት የአቦ ለማ እርምጃ እና ጥልቅ ውሳኔ ነው። አሳቸው እራሳቸው የገነት
ውሃ ናቸው። የማይጠገቡ። ትናንት ቤተ - መንግሥት ውስጥ ሳያቸው እንዴት እንደ ሆንኩኝ … ልዩ መዝገብ ናቸው። የመሆን ድንጋጌ።
- · ሚስቶች ሆይም ደስ ይበላችሁ።
ሚስቶች ሆይም የሚል አንድ ጹሑፍ በጸጋዬ ድህረ
ገጽ ጽፌ ነበር። በሌላ በኩልም የትውልድ መሰረቱ መልካም ትዳር ሥለሆነ ለዛም „ርግብ በር“ መጸሐፌን ስጽፍ ሚስቶች እናትነት የሰጣቸውን
ጸጋ ለልጆቻቸው ብቻ ሳይሆን በትዳራቸው ላይ የማሳዬት የተፈጥሮ ግዴታቸው እንደሆነ ጽፌ ነበር። ይህንም ባለቤታቸው ቀዳማይ እመቤት
ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው መፈጸማቸው እናታዊ ስብዕናቸውን ለትዳራቸው መፋፋት ብቻ ሳይሆን የሥጋ እናታቸውን አደራ ተረክበው ሃላፊነታቸውን
መወጣታቸውን ሲነገር፤ ምስክርነት ሲሰጥ፤ ሴት ጥበብ መሆኗን በብሄራዊ ቤተ መንግሥት ተመሰከረላት። ተወደሰች። ሴት እኮ የመኖር
ሰቅ ናት! ራሱ የመኖር ነባቢት ናት። ዕውነትም የመሆን መሆን ዝናቸው ለሁላችን ታዬን። ተከሰተ።
አቶ የትዳር አጋርም በእቅፉ ያለችውን ሚስቱን፤
እናቱ፤ እህቱ፤ ጓደኛው እና አማካሪው ትሆን ዘንድ ልዩ አብነታዊ ጥሪ በዚህ ለምለማዊ የፋካ እለት ተላልፏለታል። የጋብቻ ክቡርነት፤
የጣና ዘገሊላ ሚስጢር /ለታውህዶ አማንያን/ ተመሳጥሯል። ለማህበራዊ ኑሮ ሴቶች መሥራቾች ነን፤ ለፖለቲካዊ ህይወትም መዳህኒቱ፤
የእናት የአደራ ተግባራዊነት ማረጋጫውም ሆነ የሚስትነት ክህሎት ለቤተሰባዊ ሃላፊነት ጉልቱ ነው፤ የቤተሰብ መሠረትነት የትውልድ
ተልዕኮ ነው፤ የብልህነት እና የመሪነት ብቃት በሴቶች ተፈጥሮ ላይ ማዕዛው ጎልብቶ እና ጎልቶ በፍጹም ሁኔታ የወጣበት ታሪክ ከንጉሦች
ንጉሥ ከዳግሚያዊ ዐጤ ሚኒሊክ ወዲህ ዕለተ „ሰኞ“ መጋቢት 24. 2010 የመጀመሪያው ቅዱስ ዕለት ነበር። ብርሃነ ዘ-ኢትዮጵያ
ጣይቱ እንደገና ተፈጠረች። ከእኛ ብዙ ነገር አለ፤ ልብ ላለው አዕምሮ ላለው ለተሰጠውም። ይህም ለእኔ ከሽልማት በላይ ነው፤ ለዛውም
ሰማያዊ።
- · ጥልቀት።
የማከብርህ ሳተናው አንተ ስለሆንክበት ምንም የቤት
ሥራ የለብህም። ከእኔ ጋር መሥራት ከባዱ ነገር ሥራ ላይ እኔም አይደክመኝም ሰውም ይደክመዋል ብዬ አስቤ አላውቅም፤ ችግር አለብኝ፤
እናም ጫናዬን ተሸክመኽ፤ በዛብኝ ሳትለኝ፤ ውስጤ የሚለኝን ሳትቀንስ ሳትጨመር እንዳለ ስታወጣልኝ መቆየትህ በራሱ አዲስ አብዮት
ነበር። አልፎ አልፎ አንዲት ወይንም ሁለት ቃል ስትጽፍልኝም ቁመው በጥልቀት ይሰብኩኛል። ከእኔ ቤት ፈሶ የሚቀር አንድም ቁም ነገር
የለም። ሁሉም በቁም ነገር ተመዝግቦ በፍሬም ሆኖ እንደ መምህር ነው የምጠቀምበት። ለመማር ዝግጁነቴ ነውም እነዛ በፍጹም ሁኔታ
በአዘቦቱ ሊገኙ ከማይችሉት መሪዎቼ ነፍሳቸውን ይማረው እና ጓድ ገዛህኝ ወርቄ፤ በህይወት ይኖራሉ ብዬ እማስባቸው ጓድ ስለሺ መንገሻ፤
ጓድ ወንደወስን ሃይሉ፤ ጓድ ገ/ መድህን በርጋ፤ ኮ/ አሰፋ ሞሲሳ፤ ጓድ አበበ በዳዳ፤ ጓድ ዘርጋው አስፈራ በእኔ ላይ የነበራቸው
ተስፋ እጅግ ብሩኽ ስለነበር በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሰብዕናዬን ለመቅረጽ ሁሎችም ይታትሩ ነበር። መደበኛ ሥራቸውም ነበርኩኝ። ዕድለኝነቴ
ከ - እስከ አይባልም። ከወላጆቼ በላይ ይሳሱልኝ፤ ይንከባከቡኝ ያቀርቡኝ ነበር።
የትም ቦታ ሆነው፤ በዬትም ሁኔታ ላይ ሁነው ተቀይረው
እንኳን ጎንደር ሲታሰብ ሥርጉተ ሥላሴ አለች። ይደውሉልኛል፤ ያገኙኛል። ጎንደርን ሲለቁም ችግር እንዳይገጥምኝ ማዕከለዊ ላይ ሁሉ
ሰዎችን አደራጅተውልኝ ነበር። ብዙ ህልም ነበራቸው እኔን በማብቃት ሊያገኙት እና ሊዩት የሚመኙት ልክ እንደ አቦ ለማ መግርሳ።
„ማብቃት“ ታላቁ ተልዕኳቸው ነበር። ብዙ የማይታይ ረቂቅ መንፈሳቸውን
በእኔ ላይ አፍስሰዋል። ሳይስቱ ፍቅራቸውን ሰጥተውኛል በተለዬ መልኩ። ሙሉ ሰው ለማድረግ እጅግ ደክመዋል። የነበረኝ ወጣትነት ሆነ
ውበቴ በእድሜዬ ሊመጡ የሚችሉትን ሁሉ ማረቄ በቤተክርስትያን ሊቀውንተ ሥነ ምግባር ውስጥ ማደጌ፤ ለሥጋዊ ነገር ባዕዳ መሆኔ፤ በልዩ
ሁኔታ ነበር የሚመሰጡበት። ነፍሷን ይምራት እና ጓድ ተስፋለም አበራ አንድ ቀን ሊፒስቲክ ተቀብቼ አብረን ስንሄድ ይህ ሊፒስቲክ
ከሥርጉተ ላይ ሳይሆን ከተስፋለም ላይ ነው ይላል ዛሬ ያዬን ሰው አለችኝ። ስለምን? ዕይታቸው እና የሚጥሉብኝ ዕምነት እጅግ ጠንካራ
ስለነበር።
ስብሰባ ላይ ማዕከላዊ ሲገናኙም አጀንዳቸው የወል
ሥርጉተ ነበረች። በጋራ ሁነው ፈርመው ሁሉ ደብዳቤ ይልኩልኝ ነበር። ዛሬ ከዚህ የጠጅ አንቡላ ስርክራኪ የለቀለቀውን ደካማዋን ሥርጉተ
ስዕል ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን እላለሁኝ። ከስለትም ልጅ በላይ ነበርኩኝ። አቅማቸውን ሁሉ የሚያፈስቡኝ። ድፍረቴ፤ ግልጽነቴ፤ ሥራ
ማብዛቴ ሁሉ የሚሳሱለት ነበር። እኔን ለመቅረጽ፤ መንፈሴን ለማደረጀት ገብቼ ከተማርኩት ፖለቲካ ት/ቤት በላይ፤ ከተሳተፍኩባቸው
ሰሚናሮች በላይ መሪዎቼ ለእኔ ያጠፉት ጊዜ የቀለቡኝ ቀለማም ዕወቅት የማይዝግ እና የማይማርት ነው። ከፈጠሯቸው ከሥጋ ልጆቻቸው
በላይ ዓይተው እንኳን አያምኑኝም ነበር። ጓድ ስለሺ መንገሻ የትግራይ አንደኛ ጸሐፊ በነበሩበት ጊዜ ጎንደር ይመላለሱ ነበር። መጀመሪያ
ልጄን አምጡልኝ ነበር የሚሉት። አዎን። ፍቅር ነበር ያስተማሩኝ። አክብሮትን ነበር የመገቡኝ። ትህትናን ነበር የቀለቡኝ። ስንት
ምርጥ መሪዎች እኮ ኢሠፓ ነበረው። ሶሻሊዝም ዘር አልባው ቀበረው እንጂ።
አሁን ኮ/ አስፋ ሞሲሳ ስለ ኮ/ ጎሹ ወልዴ የልጅነት
ንቃት፤ ብርታት፤ ልዩ ተስጥዖ ይነግሩኝ ነበር። ያስተምሩኝ ነበር። ያስጠኑኝ ነበረ። ኮ/ አሰፋ ሞሲሳ ለተጠዬቁኩት ጥያቄ ብቻ አጭር
እና ግልጽ መልስ መስጠቴ በኔ ውስጥ ሥራ መስራት እንዳለባቸው አስወሰናቸው። ሲያስተምሩኝ ሁልጊዜ አብነት የሚያደርጓቸው ኮ/ ጎሹ
ወልዴን ነበር። በሳቸው ላይ ሰፊ ተስፋ ነበራቸው። ዛሬ ላይ ሆኜ
ሳዬው ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸው በራሱ ከድንቅ በላይ ነው። የመሠረቱትንም ፓርቲ መድህንም አዲስ ሳተና ተተኪ ወጣቶችን
ፈጥረው ነበር በፈቃዳቸው ያስረከቡት። በአጋጣሚ በጋዜጠኝነት ህይወቴ ውስጥ ከአዲሶቹ ወጣት የመድህን የፖለቲካ ሊህቃናት ረ/ ፕሮፌሶሮች
ጋርም ተገናኝቼም አቅማቸውን መለካት ችያለሁኝ። ወጣት ደግሞ ብልህ እና ምራቃቸውን የዋጡ ነበሩ ተተኪያቸው።
የትናንት መሪዎቼ ዛሬም እንደ መሪዬ የምመለካታቸው
ከእነሱ ከተለየሁበት ጊዜ ጀምሮ አይደለም የሌላ ፓርቲ የምንም ማህበር አባል እንኳን ሆኝ አላውቅም። ገብቼ ልበጥብጥም ልመስም የሚል
ፍላጎት አድሮብኝ አያውቅም። በውስጤ አንድ ንጹሕ መንፈስ ነበር። በልጅነቴ ከእድሜዬ በላይ ክብር፤ ግርማና ሞገስ የሰጠኝ ፓርቲዬ
ኢሠፓ ለዘር ሳይተርፍ ከሞተ በኋዋላ ከሌላ የፓርቲ ማንፌስቶ ጋራ ትዳር ላለመምሰረት
ለራሴ ቃል ገብቼ የሌላ ፓርቲ አባል ብሆን ሊቀንስልኝ የሚችለውን መከራ በእጥፍ አበራከትኩት። ለምወደው ፓርቲዬ ለኢሠፓ አሁንም
በድንግልና ነው ያለሁት። ለወደፊትም። በዛ ላይ የሚያጓጓኝ ብቻ ሳይሆን የሚያግባባም የተምክሮ ማሳ ማግኘት ተዚህ ከጋዳ በላይ ነው።
ቋንቋ የለም ከእነሱ ጋር የሚያግባባኝ። በምን ስሌት እንዴት ሊሠራ? ኢሠፓ ዕንቁ ሰዎችም ነበሩበት። ሰውን መፍጠር የሚችሉ። ጊዜም
ዘመንም የማይተካቸው የዳበረ እና የጎለመሰ የተመክሮ ጥሪት የነበራቸው በርካታ ነበሩ። ምን ያደርጋል ሶሻሊዝም አብዮታዊ ዴሞክራሲ
ጠቅልሎ አባከነው አቅሙን ሁሉ እንጂ …
በተረከብኩት የእውቀት ማሳ ፈተናዬ አጅግ ቢበዛም
ትክሻዬን ደህና አድርገው አደንድነው ስላሳደጉኝ በጠንካራ የፖለቲካ ፍልስፍና አጎልምሰው ስላሰደጉኝ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። ደስታ
በደሰታ ውስጥ ሳይሆን ይልቁንም በመከራ ውስጥ ያለው - ጣፋጭ። ከሁሉ
በላይ የሐዋርያውን የቅዱስ ጳውሎስ „የይበቃኛል“ መንፈስ አግብቼው ስለምኖር ውስጤ ሰላም እና በፍጹም ሁኔታ የተረጋጋ ነው። የምወደውም
ጸጥታ አብሮኝ ነው። መሪዎቼ የሰጣችሁኝ፤ ያስተማራችሁኝ ወርቅን ደግሞ አቅልጬ አላፈሰስኩትም። ይሄው እስከ አሁን ድረስ እታገላለሁኝ።
ጫካም ነበርኩኝ። ታስሬም ነበር። ስደተኛ ነኝ
አሁን። ሁሉም መከራ በ ዓይነት ተስተናግዶ ግን የእናንተ የመንፈስ ጥሪት ዳብሯል፤ ፋፍቷል ከአመራር ሰጪነት እና አደረጃነት ወደ
ጸሐፊነት እና ወደ ራዲዮ ጋዜጠኝነት ተሻጋግሯል። በዚህ ዙሪያ ሳተናው ድህረ ገጽ የሰጠኝ ፈቃድ ፍሬያችሁን ለማዬት ትችሉ ዘንድ
አብቅቶኛል። ስለሆነም ድንገት እንዲያው ድንገት ጹሑፌ ከእጃችሁ ቢገባ ይህን ነፃነትን የሸለመኝን ድህረ ገጽ ቤታችሁ አድርጉልኝ
- አደራ። በዚህ ውስጥ የእናንተ ጥረት እና ፍሬ ባክኖ አለመቅረቱን ታገኙታላችሁ። ከምታስሱላት ከዛች ቀጭንዬ ግን የግንባር ሥጋ
መንፈስ ዕውነትም ጋርም ትገናኛላችሁ። ትናፍቅኙላችሁ!!!
- · ኢሠፓ ፓርቲዬ በፆታዬ ላይ ያደረሰብኝ ጭቆና አልነበረም።
እኔ በፓርቲዬ በኢሠፓ ውስጥ ለደቂቃ የፆታ ጭቆና
ደርሶብኝ አያውቅም። ከሴት አደራጅነቴም በፍጥነት ነበር ወደ ሌላ የማህበረሰብ አደረጅነት የተሸጋገርኩት። አክብሮትም ሆነ ተቀባይነቱ
ከበቂ በላይ ነበር። እድገቴም እጅግ ፈጣን ነበር። ሴት ስለሆነች አቅሟ በዚህ ይወስን አላለም ፓርቲዬ ኢሠፓ፤ እንዲያውም የመጀመሪያዋ
ወጣት የክፍለሐገር የሠራተኛ እና የገበሬዎች አደራጅ እኔ ብቻ ነበርኩኝ። ከብሄራዊ ጉባኤ ላይ ከአደራጆች ሁሉ ሚጢጢም ሴትም እኔ
ነበርኩኝ። ለዚህ ነው ቃልኪዳኔን ሳላፈርስ የኖርኩት። ደንቤ ውስጤ ነበር። እያንዳንዱን አንቀጽ በአንቀጽ አውቀው ነበር። ዛሬ እርግጥ
ነው ረስቸዋለሁኝ። ማደራጀት ህይወት ነው። ህይወት ይሰጣል። ማደራጀት ገምጋሚም ነው። ማደራጀት ራስንም ሌላውንም የሚያሳይ መስታውት
ነው። ሙያዬ በመከራም ውስጥ ደስታዬን ፈጥሬ እንድኖር አደርጎኛል። ኑሮዬም መንፈሴም በፍጹም ሁኔታ የተዳረጀ እና የሰከነ ነው።
ያ ቁጥብነት ዛሬም አለ።
ዛሬ የሳተናው ልዩ የምስጋና ቀንም ቢሆን በእኔ
የፖለቲካ ህይወት ውሰጥ አሻራቸውን ያስቀመጡ የማከብራቸውን መሪዎቼን በህይወት ያሉትን አመስግናቸዋለሁኝ። የሞቱትንም ነፍስ ይማርልኝ።
የእነሱ ልጅ ስለመሆኔም እንዲያውቁ እፈልጋለሁኝ። ደከመን እና ሰለቸን ሳይሉ ለእኔ ሁለመናቸውን ሳይስቱ ሰጥተውኛል። ፍቅራቸውን
መግበውኛል። መንፈሴን በመስኖ አቅም በልምድ፤ በተመክሮ በፖለቲካ ዕውቀት አልምተውታል። አብቅተውኛል። የቀረብኝ አንዳችም ነገር
የለም። በማንኛውም ሁኔታ በመንፈሴ ጽኑ የሆነ የሚበቃኝን ያህል የፖለቲካ አቅም ሸልመውኛል። ስለሆነም አክብሮቴ በናፍቆት፤ ምስጋናዬም
በአድናቆት ባላችሁበት ይድረስልኝ ብያለሁኝ - ለውዶቼ።
በተረፈ የእኔ ሳተናው ለሰጠህኝ ንጹህ ፍቅር፤
ለፈቀድክልኝ ሙሉ ነፃነት፤ ለነበረህ የመቻል ጥበብ፤ ላስተማረኝ ትዕግስትህ በህይወት ካለችም ለእናቴ የምሳሳላትን ያህል ለብርናህ
እንደምሳሳለት ላረጋግጥልህ እውዳለሁኝ። እንዲያወም ብነግርህ ቢሮዬ ሁሉ ይመስለኛል። ቅንነትህ፤ መሆን መቻልህ፤ ለእኛ ለሴቶች ያለህ
እውነተኛ ተቆርቋሪነት፤ ሥርጉተ - ሥላሴን በመንፈስ ነፃ ከማውጣት በላይ ተጋድሎ የለም። እኔ እኮ በሰንሰለት በተተበተ ኢንትሪግ
በድርብ ብረት የተዘጋብኝ ጽኑ እስረኛ ነበርኩኝ። እስሩ ሰውር ነበር። እና መቼውንም እፈታለሁ ብዬ የማላስብ ምንዱብ ነበርኩኝ።
ዕድሜ ለአንተ ቅዱስ መንፈስ። ሰንሰለቱን በጣጠሰው። ዕድሜ ለአንተ
ቅንነት መሆን መቻልን ሆንክበት። ቃለ ምልልስ ክፍል አንድን ከአንድ ሰው ጋር ሠርቼ ሁለተኛውን ለማግኘት ቃለ ምልልስ ያደረኩለትን
ሰው ደግሜ ማግኘት አልችልም። እኔን በኢሜል የሚያገኙኝ ሰዎች ስም በሚስጢር የተያዘ ነው። ስለምን? ድልድዩን እንደሚቆርጡት ስለማውቅ።
የሦስተኛው ዓለም ጦርነት በእኔ ላይ ተካሄዷል። ከወያኔ ሃርነት ትግራይ ሰላዮች በላይ በነፃነት ታጋይ ተብዬ የደረሰው ግፍ እና
መከራ ሶሻሊዝም ያሸከመን በደላችን ነው። ሶሻሊዝም የቅንነት ነቀዝ ነው። ፈጣሪ አምላኬ እስከነ ቅል ቋንቁራው ሶሻሊዝም እና ጦሱን
ብን አደርግልን። የ ኢትዮጵያ ትክክለኛ ትንሳኤ ሙሉ ለሙሉ የሚረጋገጠው ከሶሻሊዝም ጋር ያለው የ80 ፊርማው ሲቀደድ ብቻ ነው።
ነቀርሳ ተተክሏል። ባልሰለጠነው ከንድፈ ሃሳቡ ጋር ትውውቅ ከሌላው አዕምሮ ሲኮን ደግሞ አዳጋው ከፋ ከረፋም። አያውቁትም በድምስሱ
መልካሙን አቅም ሁሉ ድፍጥጥ ያለዋቂ ሳሚ ነገር ….
- · ክውና።፡
„ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ“ ይላል የፈጣሪ ቃል
እና አክብሮቴን በክብር ጠልፌ፤ ምስጋናዬን በትህትና አቅልሜ፤ የምስጋና ህሊናዬን በዕምነቴ ልክ በቅንነት ልኬልሃለሁ። እጅግ አድርጌ
አመሰግንሃለሁ። በአቦ ለማ መንፈስ „ከጣና ኬኛ ጀምሮ እስከ ዶር አብይ የጠቅላይ ሚኒስተር ሥልጣን እርክክብ ድረስ የሃሳብ ሙግቶችን
ፈቅደህና ወደህ ማሳህን ያለምንም ገደብ ማዘጋጀትህ ለእኔ ብቸኛው የነፃነት ቀኔ የአድዋ ድሌ ነው። የሎሬቱ ድሌ የታቦት የንግሥና
ጉልላቴ ነው።
ወንድም ዓለም ሰው አለመረጥከበትም። አቅሜን አላገለልከውም
ወይንም አልፈራኸውም። ሞራሌ አልተሰበረበትም፤ ተስፋ ቆራጭነት ዝር እንዳይልበት ዘብአደር ወታደር ሆንክ ያውም የመንፈስ። በዚህ
ሂደት ሰቀቀን አልተሰነቀበትም። ስጋት አልተቋጠረበትም። በሙሉ ልብ እና በድፈርት ሃሳቤን፤ ምኞቴን፤ ቁስለቴን፤ ተስፋዬንና ራዕዬን
ከእናትም በላይ ሁነህ በሆደ ሰፊነት አስተናግደህልኛል። እጅግ አድርጌ አከብርሃለሁ። በኢትዮጵያዊነት ላይ የሚሠሩ የሐገሬ ሚደያዎችም
ከዚህ የነፃነት ማሳ ብዙ መማር ያለባቸው ይመስለኛል - በትህትና። ከቻሉ።
ስለነገ የሚያውቀው ፈጣሪ ነው። የታገልንበት፤
ሌትና ቀን የታታርነበት ጉዳይ ግን የተደላደለ ሥፍራ ላይ ደርሷል። „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው አሸንፏል“ „ጣና ኬኛ“ ድል አግኝቷል።
„አባይ ኬኛም“ ፋፍቷል። ለማዋያንነቴም አብቧል። የህዝቡ ድጋፍም ከሊቅ - አስከ ደቂቅ ከተገመተው በላይ ሆኗል። ሥርዓቱ አክብሮቱ
ውብ ነው መጨረሻውን ያሳምረው … ፈሪ ነኝ …
እኔ ስጀመረው የነበረው የዶር አብይ አህድ ሥም
ወደ 300 አካባቢ የነበረው ዛሬ ጉግል ላይ ወደ 656,000 ሺሕ
ተሸጋግሯል፤ ለሙግቴ ስጠቀምባቸው የነበሩ ማመሳከሪያ ንግግሮችም በሚደንቅ ሁኔታ የታደሚ ተሳትፎ ዳብሮበታል። በዛ ላይ በዬቀኑ ስለመቆጣጠረው
ከሥር የሚሰጡ አስተያዬቶች እራሱ ብስጩ የነበረውን የማህበራዊ ሚዲያ ሰላሙ የተረጋጋ እና ስክነትን ቀልቧል። ቅን መንፈስ ተሰብስቦበታል።
ተጋድሎው ለዚህ ነበር „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ፈሶ እንዳይቀር። አሻነፊ እንዲሆን፤ ትውልድን እንዲያተርፍ፤ መቻቻልን እንዲጠራ፤
ፍቅራዊነትን እንዲያበለጽግ፤ ቅንነትን እንዲያውጅ፤ ጥላቻን እንዲጸዬፍ፤ ቂም በቀልን አንዲቀብር፤ ምቀኝነት እንዲሰብር ያለምነው
ተሳክቷል። ያሰብነው ሆኗል። የተሟገትንለት ለድል በቅቷል። ብርሃን ጭላንጭሏም መከበር ስትችል ሁሉን የማድረስ አቅም አላት። አብዛኛው
መንፈስ ተስፋን አልሟል። ጤና ነው …
ይሄው የኢትዮጵያ ሴቶች ጉዳይ ሆነን፤ ዓላማና
ግብ ሆነን ለወግና ለማዕረግ ደረስን። እንኳን ደስ አላችሁ ባለቤት ያልነበራችሁ፤ ሰብሳቢ ያልነበራችሁ፤ ተጠሪ ያልነበራችሁ፤ አቋጠሪ
ያልነበራችሁ ግን ግብር በገፍ በዬዘመኑ ስትሰፈሩ ለነበራችሁ
የኢትዮጵያ ሴቶች በሙሉ። አንድ የምሥራች ቀን አንድ ሌላ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ነን - ዛሬ። የትናትናውን ደስታ አያክለውም የሰብዕዊ
መብት ተማጋቿ አርቲስት ክብረት አርቲስት አስቴር መዳኔ እንዳለቸው ዛሬን እንኳን „እንደ ብሄራዊ በዓል ቆጥራችሁ ተውን“ ነበር
ያላቸው። ሊንኩን ከሥር ለጥፈያለሁኝ ሙሉ መንፈሱን ለማድመጥ።
አንድ ገበሬ ታተሩ አለስልሶ አርሶ፤ አረምን ነቅሎ፤
ዘሩ አሽቶ - አፍርቶ - በስሎ - ታጭዶ - ተከምሮ - ተበራይቶ - ፍሬው ለጎታ ሲበቃ ነው የገበሬ ህይወቱ። ግን ገበሬ ሰማዩ
ከለገመ ዘሩ የመሬት ስንቅ ሆኖ ይቀራል። መክኖ። ወንድሜ ሳተናው አንተ የምህረት የሰብል የጸደይ ሰላማዊ ዝናብ እና የጸሐይ ብርሃን
ነበር የሆንከኝ ለእኔ። ጸበሌ ነህ። ኑርልን ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለቅኖችም በተለይም ባለቤት ለሌለን ግዑፋን ንጣይ ሴቶች።
በመጨረሻ በዚህ የተጠዬቅ መስናዶ የሙግት ሂደት
ደክመሽናል፤ ሰልችተሽናል ሳትሉ ሰፊውን ትዕግስታችሁን በልግስና ሸልማችሁ ለዚህች የምሥራቼ ቀን ላደራሳችሁኝ እጅግ ለምትናፍቁኝ
የሐገሬ ቅን ፍቅሮች ስስቶቼም ከመቀመጫዬ ተነስቼ የማመስግናችሁ ዛሬ በተለዬ ሁኔታ ነው። ለክብራችሁ በተለዬ ሁኔታ የገዛሁትን አረንጓዴ
ሻማ አብርቼ ነው። አረንጓዴ ተስፋ ነው። ብሩክ ናችሁ እና የተባረከ ቀን እንዲኖራችሁ እምኛለሁ - የኔዎቹ። ኑሩልኝ ለእኔ ብቻ
ሳይሆን ለእናት ሐገር ለኢትዮጵያም። አንተም ወንድም አለም ሳተናው ኑርልን። ዕድልን ማበከን አይገባም ይኽንንም ኢሜል ላይ ስንሟገት
ከነበረው የብዕር ጓዴ ጋር ተነጋግርነበታል ዛሬ ከ600 ሰው አንድ ማዕልት ከማለቅ ወደ 600 ሺሕ ህዝብ መፈናቀል የተደረሰው በዕድሎቻችን
በአግባቡ ባለመጠቀም ነው ብያቸው ነበር ለጸሐፊውና ለጋዜጠኛው ተወያዬ፤ አዎን አሁንም እምለው ይኸው ነው ወርቅ ከእጅ ከገባ ቀልጦ
እንዳይፈስ „ልብ ያለው ሸብ“ ነው።
- · ምርኩዝ ለማጠናከሪያ።
awaze news
የዶር አብይ የልብ ጏደኛ ጌትሽ ማሞ አስገራሚ ንግግር Dr Abiy Ahmed Ethiopia
እስራኤል ላይ የዶር አብይ ተስፋ እና የ አሁኑ የጉዞ አቅጣጫ …
„Ethiopia: አርቲስት አስቴር በዳኔ ስለ ዶ/ር አብይ የሰጠችው ያልተጠበቀ አስተያየት | Aster Bedane Comment on Dr. Abiy“
https://www.youtube.com/watch?v=YqxOPssP5iM
ETHIOPIA
- የጠቅላይ ሚኒስትራችን እናት! - DireTube News
https://www.youtube.com/watch?v=Ar7sm6z4zMs
Ethiopia
: ጠቅላይ ሚንስትሩ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ጋር አድርገውት የነበረው ቆይታ
„ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“
(ከአቦ ለማ መግርሳ የተወሰደ)
ሁላችንም አድግን አልጨረስንም።
(ከወ/ሮ ጽዮን ተክሉ የተወሰደ)
ዕልፍ ነን እና ዕልፍነታችነን በተግባር እና በሙሉ
ምግባር እልፍ እናድርገው።
ሴቶች ቅኔ! ሴቶች ጥበብ! ሴቶች ረቂቅ ናቸው!
ተባረኩ። መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ