የሌባ አይነ ደረቅ አቶ አባይ ጸሐዬ።

ብራቮ¡አቶ „የሌባ አይነ ደረቅ …“
ከሥርጉተ - ሥላሴ(Sergute©Sselassie)  
23.03.2018 (ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ)

 „ክፉ ሰው አመፃን ብቻ ይሻል። ስለዚህ ጨካኝ መላዕክ ይላክበታል።“ 
(መጸሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ 17 ቁጥር 11)


  • ·         ፊታውራሪ ማፈር ከቶ የት ይሆን አድራሻህ? እባክህን ተዚህ ነኝ በላቸው ….

ማፈር ያባት፤ መሸማቀቀም ያባት፤ ሸሽጉኝም ያባት፤ ደብቁኝም ያባት፤ የት ልግባም ያባት ነበር „በነበር“ በወጉ እንደ ኢትዮጵያዊነት ትውፊቱ። ዛሬ … ዛሬ ለመሬቷ ለትግራይ እያዘንኩኝ ነው። እንዲህ ዓይነት ጉድ ተስምቶ አይታወቅም። በዕምነት አክራሪነት እና በወግ አጥባቂነት ነበር በድሮው ዘመን እኔ እነሱን ሳውቃቸው በትምህረት ቤት፤ በተለያዩ ኮርሶች፤ አብሮ በመኖር፤ በጎርብትና፤ በጋብቻ፤ አብሮ በመሥራት አንዲህ ዓይነት ጸያፍ ነገር በፍጹም ምናቸው አልነበረም። ምኑን የጥፋት ማዕት ይሆን ያወረደባቸው - የደፋባቸውስ። ርግማን። ስስት እንኳን እኔ አይቸባቸው አላውቅም፤ አንኳንስ አልፈው ተርፈው በጠራራ ጸሐይ የሰውን ነገር ሊመኙ „ዘራፊ“ ለመባል ቀርቶ። 

የተገለበጠ ታሪክ እኮ ነው እዬተሠራ ያለው በወያኔ ሃርነት ትግራይ መሳፍንት፤ መኳንንት ወይዛዝርት ዘመንተኞች። ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥልጣን ከያዘ በኋዋላ የጥንት ወዳጆቼ ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ ባላውቅም፤ ቀደም ባለው ጊዜ ግን „ሌብነት፤ ዝሙተኝነት፤ ውሸት“ ለዛውም በድፈርት እና በዓይን አውጣነት እንዲህ አደባባይ እእ … በፍጹም ሰብዕናቸው አልነበረም። ደፍረውም ቃሉን አይናገሩትም ነበር አብሶ ከሥጋ ፈቃድ ጋር ያሉ ንክኪ ተፈጥሮዎችን። ራሳቸውን የጠበቁ ጥንቁቅ ነበሩ - እኔ በቅርበት እማውቃቸው።
  • ·         ንካሳው አንካሴ።

ዛሬ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ት/ ቤት ከፍቶ ከትውፊት ያፈነገጡ፤ በባህላችን የላተዘወተሩ፤ በወጋችን አጅግ ነውር የነበሩ፤ በልማዳችን የተወገዙ ነገሮች ሁሉ መለያ ሆኑ - ለተጋሩ ለዛውም በቤተ መንግሥት። አንካሳው አንካሴ። አዝናለሁኝ።
እንዲህ ከሰው የወረደ፤ በፍጹም ሁኔታ የዘገጠ ሥነ - ምግባራት በተዋናይነት ከነተጋሩ ማድመጥ ያስደነግጣል እንደ አገር ልጅነት። በወረራ፤ በስርቆት፤ በዝርፊያ፤ ህግ በመተላለፍ፤ በመቀማት፤ ይባስ ብሎ በአመንዝራነት በፍጹም አይቼው የማውቅ አንድም የተጋሩ ቤተኛ አልነበረም በእኔ ዕድሜ - አገር ቤት እያለሁኝ። የዕውነት በወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ዶግማ ሥሙንም - ጸጋውንም - ተፈጥሮውንም በከሉት - አከሰሉት። እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋም እንዲህ የሚገለማ ነገር ሲደመጥ መሸከም - ያቅታል። ይሄ ነው የሚባል አንድ ጥራት ያለው ተፈጥሯዊ፤ ኢትዮጵያዊ ሥነ - ምግባር ለዘር እንዴት ይጠፋል ከመሳፍንታት / ከወይዛዝርት ከነተጋሩ ባልሥልጣናት? መኃከነ!

እንዴት አቶ አባይ ጸሐየ ሸሽጉኝ፤ ሸጉጡኝ፤ ደብቁኝ፤ ማለት ሲጋባቸው የሥልጣኑ፤ የገበርዲኑ፤ የከረባቱ፤ ሽክ ያለው ጫማ ከሳቸው መጠጋቱ ሲገርም በአደባባይ ይህን ያህል ዕድሜ ተሽክሞ በህዝብ ፊት አዳራሽ ውስጥ ድንጋይ ውርዋሮ? ንቀት - ትዕቢት፤ እግዚዖ! ስላንቺ ነው።

ነገ ስለሚፈጠሩት የትግራይ ዕንቡጦች አለማሰብ። ይሄነን የከረፋና የቆረፈደ ገመና የሚሸከሙ፤ የማግስት መሳቂያና መዳለቂያ የሚሆኑት እንሱ ናቸው - ያልተጸነሱት ግን ነገ የሚጸነሱት። ካለ ዕዳቸው። እንዴት ይህን የበከተ ታሪክ ትክሻቸው ችሎ ሊሸከም እንደሚችል ይጨንቃል። የእውነት ይጨንቃል፤ የመጠጊያ ያለህ ያሰኛል። ለሰሚው ግራ ነው … ስንቱ ቀዳዳ፤ ስንቱ ነዳላ ይወታተፍ …. ቅንጣት መልካም ነገር የሌለበት፤ የመከነበት ጉርድም - ጉርናት።

ሥርቁት - በአደባባይ፤ ውሽት - በአደባባይ፤ ቃል አባይነት - በህዝብ ፊት፤ ክህደት - በአደባባይ፤ ዝርፊያ - በህዝብ ፊት ይሄን ጸያፍ ነገር እንዴት ትሸከም እትዬ ትግራይ? እንደ ባልሥልጣናቱ እትብት መገኛነቷ፤ ከእከሌ እክሌ ይሻላል የማይባልበት የተሸለተ መርግ። በግድያው፤ በጭካኔው፤ በሰው ድብደባው፤ ሰውን እንደ እንሳሳ ከተፈጥሮ ውጪ በማድረግ ኧረ ስንቱ? ሚሊዮን በጥይት በቀዩ ተቆላ መድረሻ አጣ፤ መከነ። ከባዕቱ ተነቅሎ የትም ባከነ። አሁን አኮ ሰው ለሆነ ሰው የሃዘን ጊዜ ነበር፤ የሰቀቅን ጊዜ ነበር፤ አመድ ተነስንስንሶ ትንቢያ ጎዝጉዞ አቤት! የሚባልበት፤ ይህም ሆኖ የተበደለው ማህበረሰብ ተወካይ ልጆች እንዴት በአደባባይ ይዋረዳሉ እንዴት ። ሐዘንተኞች እኮ ናቸው፤ „የወንድ ልጅ እንባው በሆዱ“ ያለው የብለቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ወንዶች ሆነው ችለውት እንጂ ያን ያህል ሚሊዮን ህዝብ በግፍ ከባድማው ተነቅሎ፤ ተሳዶ እኮ ስብሰባ - ግምግማ - ሂስ / ግለ - ሂስ ቅብጥርሶ // ምንትሶ እኮ ማላገጥ ነው፤ መቀናጣት ነው፤ የቅልጣንም ነው … ነፍስ እኮ ነው ባዶ እጁን ዕትብቱ የተቀበረባትን በድንገት በፍርሃት ሰቀቀን መጓጓዣ ባዕድ ሐገር እዬተመመ ያለው። 

… ያ ሁሉ ታጭዶ … ጨለንቆ፤ ወልድያ፤ ወሎ፤ ራያ፤ ቆቦ ሞያሌ፤ መላ ሐረር። ከምን ነው የተፈጠራችሁት ይሆን? ከብረት? ሰው ናችሁ ወይንስ ምን? ምን ትባሉ ይሆን? የሚሊዮን ዕንባ በዬደቂቃው እዬፈሰሰ እናንተ ትዘምናላችሁ? መቼ ይሆን የእናንተ ጸሐይ የሚጠልቀው? በዚህ በስተ እርርጅና ዕድሜ፤ በዘመነ ምርኩዝ አዳራሽ ውስጥ የሃይላንድ ውሃ ውርዋሮ፤ ተሳህለነ! ጥጋቡ መጠንም - ልክም አጣ … 
  • ·         ይነት ያለወጣለት ፍዳ።

እማዝነው እኔ ይህም ክብር ሆኖ፤ ይህም ዝና ሆኖ፤ ይህም ግርማ ሆኖ፤ ይሄም የሚያኮራ ሆኖ፤ ይህም ሞገስ ሆኖ ደጋፊዎቻቸው አደባባይ ወጥተው መሟጋታቸው። አትንኳቸው፤ አትድረሱባቸው ማለታቸው ነው። የተጋሩ ቤተኛ አብዛኞቹ ከመንፈሳቸው ጋር ለመኖር አለመፍቀዳቸው የሚደንቅ ነገር ነው። ጹሑፎቻቸው ሁሉ እኮ የትኛው ፕላኔት ላይ እንዳሉ ይቸግራል። አንድ የተጋሩ ትንሽ ልጅ „በደልን ትውደዋለህን? ስርቆትን ትውደዋለህን ወይንስ ትጠላዋለህን? ውሸትን ትወደዋለህን ወይንስ ትጠላዋለህን? ህዝብ ማሰቃዬትን ትውደዋለህን ወይንስ ትጠለዋለህን፤ ሰው መግደል ያስደስታልን?“ ቢባል ሁሎቹንም አልወዳቸውም፤ ለምን ጠዬከኝ እንደሚል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ። ከእነዚህ ትናንሽ የነገ ተስፋዎች ፊት ይህ የገዘፈ ምንትሶ እንዴት ሊወራ? እንዴትስ ሊነገር? አንዴትስ ሊደመጥ ይችላል?! በእነዚህ ቅዱሳን ፊትስ አንዴትስ ተቁሞ ይኬዳል?! ተሳህለነ!  
የተጋሩ አዋቂዎችም ይገርማሉ ዳርዳሩን ሲሄዱ ውለው ያድራሉ። ይሄ እኮ አንገት የሚያስደፋ ነው። ይሄ እኮ የሚያሳፍር ነው። ይሄ እኮ አንገት ዘቅዝቆ የሚያስኬድ ነው። ይሄ እኮ አጉብጦ የሚያኖር ነው። ሌብንት እንደ ሞገስ? ሰውን ማሰቃዬት እና በስቃዩ መፈረሽ ያሳፍራል እጅግም ያስፈራልም።
  
ዕውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ ሰማዕት ነው። ይሄን ሁሉ ችሎ፣ ተሸክሞ አብሮ መኖሩ። እሱ በዘነዘናው እዬሄደ በባይታወርነት በሦስተኛ ዜግነት ጌቶቹን ያጅባል። ቁሞ ያበላል። ጠብቆ ይይዛል። አክብሮ ቁጭ ብድግ ብሎ ይገዛል። ይገርማል። ይደንቃል። ከጨዋነት በላይ ሰብዕናው የተሟላ ህዝብ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ። በፈጣሪ የተመረቀ ግን ምርቃቱ ርግማት የሆነበት። የማያልፍለት - ያላለፈለት። ተኮርኩዶና ተሰርዞ የሚኖር - ምንዱብ።

ሥርቆት እንደ ሥልጣኔ፤ ሥርቆት እንደ ዕድገት፤ ሥርቆት ለህዘብ እንደ መቆርቆር፤ ሥርቆት እንደ የነፃት ምልክት ተደርጎ „ወያኔ ሃርነት ትግራይ ለነፃነት እና ለዴሞክራሲ የታገለ ድርጅት ነው¡“ እያሉ ከእውነት ጋር ግብግብ የሚገጥሙ እንደ ጦማሪ መምህር አቶ አብርሃም ደስታ ያሉ የዚህ ትውልድ ባለ አደራ ሳይቀሩ ብዕሩ // ብራናው ይታዘበናል እንኳን አይሉም ደፍረው ሲኮልሙት። ቀድሞ ነገር እፍረት የሚባል አልፈጠረላቸውም። ማተበ ቢስነት። የወያኔ ሃርነት ትግራይ ቀደም ባለው ጊዜ ጫካ የገባው „ለታላቋ ትግራይ ምሥረታ“ ነበር። „ትግራይን ነው የምትፈልገው ይሄውልህ“ ብሎ ደርግ ጥሎለት ወጣ። ምን ይላስ? ምን ይቀመስ? ለታላቁ ዝርፊያ እና ወረራ ትግሉ ቀጠለ። ይሄ እኮ ተረት ተረት ሳይሆን እኛ የነበርንበት ያዬነው ሃቅ ነው። ለኢትዮጵያ ህዝብ እማ በለሃሰብ ነው የፈሰሰበት። ሃቁ ይሄው ነው።

ይህም ብቻ አይደለም ነፃነቱ - ለሥቃይ - ለመከራ - ሰዋዊነቱን - ተፈጥሯዊነቱ፤  ባለታሪክነቱ ለመረዝ ነው። በቃ! ከዚህ ያለፈ ምን ተገኘ? እኮ ምን?! እስፓልትማ ጣሊያንም ገንብቶታል፤ ለዛውም ዘመን ተሻጋሪ እንደ ዛሬው ሽርክት ምርጊት ሳይሆን። „አትናገር“ ልክ እንደ ማሙሽ እና ሚሚ ሽሽ! ዋ! ትንፍሽ ብትል ወዮልህ! እኮ ነው አሁን ያለው … „ሰው አይደለህም“ „ሰውም አልሆንክም“ „እንደ እቃ ነው እኔ የማይህ“ „ቤተሰብህን ለማስተዳደር እንኳን አትችልም“ በዬቀኑ ዓዋጅ ነጋሪት የሚጎሰመው  … ግራ … ከነግራር። በኤልኮፍተር የተደገፈ የህዝብ ጭፍጫፋ፤ የጅምላ ጭፍጫፋ … ግፉ ቢዘረጋ የኢትዮጵያ መልክዕ - ምድር ይችለዋልን?  
  • ·         ርነት በዓይነት።

ለኢትዮጵያ የተረፋት የሌብነት ባርነት፤ የውሸት ባርነት፤ የዝርፊያ ባርነት፤ የወረራ ባርነት፤ የቅጥፈት ባርነት፤ የስርቆት ባርነት ብቻ ነው። የስጋት - ይፍርሃት - የሰቀቀን ሸክም። 27 ዓመት ሙሉ ይሄን እዬሰማ ያደገ ትውልድ፤ ከዚህ ጋር የኖረ ምልዕት … ቀራንዮ አይሉት ጎለጎታ፤ ጎለጎታ አይሉት ቀራንዮ የተቀበረ መኖር፤ ያለኖረ መኖር፤ ያልነበረ መኖር። ከወያኔ ሃርነት ትግራይ አንዲትም የሰናፍጭ ቅንጣት ታከል ተረፈ - ለመለመ - አበበ የሚባል የመንፈስ ነፃነት፤ የሥነ ልቦና አቅም አንዳችም ነገር የለም። ይሄን ነው ሚዲያ የሚባለውን ጎሽ¡ እንኳንም የዝርፍያ ባርነት፤ የወረራ ባርነት፤ የስጋት ባርነት፤ የመፈናቀል ባርንት፤ የሞት ባርነት፤ የሰቆቃ ባርነት፤ የእስር ባርነት፤ የቅጥፈት ባርነት፤ የውሸት ማህበር ባርነት አስፋፋችሁልን፤ አንሰራፋችሁልን እያላ ቅቤ ሲጠብስ ውሎ የሚያድረው። ማፈረያ! 

ቀይ ምንጣፍ አንጥፎ „ታዋቂ ሰው¡ ምርጥ ሰው¡ ድንቅ ሰው¡“ ብሎ ይሄንን ማህበረ ዝርፍያ፤ ማህበረ ጭካኔ ቪዲዮ ሲያነሳ፤ በፊልም ሥራዬ ብሎ ሲያቀናብር፤ ኮንፍረስ እያለ ሲደልቅና ሲያስደልቅ፤ ማይክራፎን ደርድሮ ቃለ ምልልስ ሲያደርግ፤ በተገኘው የብራና ማሳ ሲለቀልቅ ውሎ የሚያድረው። ይሄ ነው የጋዜጠኝነት ሥነ - ምግባር በኢትዮጵያ የሌብነት አጋፋሪነት፤ የስርቆት ሊጋባነት፤ የወረራ ፊታውራሪነት፤ የጭካኔ አሳላፊነት። ለምን? ስለምን? እንዴት? ብሎ አንድ ተቀጣሪ ጋዜጠኛ አይጠይቅም። ነግ  ለእኔንም አስቦት አያውቅም። ይህም ይቅር ቢያንስ ዜናውን ሲሰራ፤ ሲያነበው እንዴት አይቀፈውም፤ እንዴትስ ከፍቶት ገጹ ጨልሞ አይሆንም? በመከራ ላይ ቁሞ ዳንስ የለም - መቼም? በጨለማ ላይ ሆኖ ጭፈራ የለም - መቼም። በቀን ስንት ጊዜ ነው ለአንድ ስብሰባ ማስተባበያ የሚሰጠው? ስንት ውሳኔ ነው ሲደለዝ፤ ሲሰረዝ፤ አክሮባት ሲሳራ ተውሎ - የሚታደረው? የማፈርያ ግርፊያ!
  • ·         ይነ - ጸጋው፤

አቶ ለማ መግርሳ፤ አቶ አብይ አህመድ እኮ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ያዘረከረከውን፤ ያሰፈነውን ሥርዓት አልበኝነትን፤ ጭምልቅልቅ ያለበትን መዋቅር፤ የተቃጠለውን አዬር፤ ውልቅልቁ የወጣውን ሰብዕና አጥንት ገጣጥሞ፤ ነፍስ ዘርቶ እንደ ሰው ለማድረግ ነው ትግላቸው። ይህን ሁሉ ገመና እና ጉድ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ተሸክመው ትወልዳዊ ድርሻቸውን ለመወጣት ለምህረት እና ለሥርዬት ቀን ተሌት እዬባተሉ ነው ያሉት። የወያኔ ሃርነት ትግራይ እና ተባባሪዎቹ ከተዘፈቁበት ክርፋት ይነጹ ዘንድ እዬተጉ ነው የሚገኙት። በእያንዳንዱ ቅን የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ውስጥ ተከፍቶ ቢታይ የሁለቱም ሥማቸው እንደ መዳኛ ተከተቦ ነው የሚገኘው ከእኔ ጀምሮ።

ይሄ ሁሉ ቁልል መከራ እኮ የሚብሰው በሚብሰው ላይ ነው። 95 ሚሊዮን ህዝብ ለ5 ሚሊዮን አባይን በጭልፋ ነው። አንድ ለስንት? መከራው ግዙፍ፤ ውጤቱም መርግ ነው። መጪው ዘመን እጅግ ከባድ እና ሊወጣ ከማይቻልበት አረንቋ ላይ የታደመ ነው። ቢረፍድም በአገኙት አጋጣሚና ወቅት መልክ ለማስያዝ ፍቅርን ነው የሰበኩት፤ አብሮነትን ነው ያስተማሩት፤ መዋደድን ነው የዘመሩት። በእያንዳንዳችን ያለው ጭንቀት እኮ ከቶውን ሊመዘን ሊለካ አይችልም። አንዱ ያለ ሌላው፤ ሌላው ያለ አንዱ ክብርና ሞገስ የለውም። እጣት ታመመች ተብላ ተቆርጣ አትጣልም። አንድትድን መንከባከብ ነው ቀዳሚው ነገር። አፍን ሞልቶ አካሌ አይደለም አያገባኝም ማለት አይቻልም። የወርቅ ድልድይ አለች። ዘጠኝ ወር አርግዛ፤ ሦስት ዓመት ያጠባች እናት። እሷ ስትታሰብ ልብን የሚፈትሽ፤ አቅምን የሚፈታተን ጭብጥ ያፋጥጣል። እናት ምንግዜም እናት ናት እና።

አነኝህ ሁለት የዘመናችን ዓይኖች የተሰጣቸው አዳራ ከፈጣሪ ነው። ግዙፍም ነው። ለዚህ ለውጥ ፈልገን ለውጥን ለምንፈራ የዛሬ ሰዎች በድፍረት እና በሙሉ ልብነት በአማኑኤል ቸርነት ፊት ለፊት ወጥተው ተሟግተው፤ ዲያቢሎሳዊ ዕሳቤን ያሸንፉ ዘንድ ሲፈጠሩ የተቀቡት መክሊታቸው ነው። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል እና። ጊዜ - ሁኔታና ቦታ ፈቅዶ የሰጣቸው ከነሙሉ ስብዕና እስከ ሙሉ መሳሪያው ነው። ዕድሉን መጠቀም ወይንም አቅልጦ ማፈሰስ ምርጫው የባለ ጉዳዩ ነው … ከዚህ አልፎ ተርፎ ግን የፈጣሪን ጥበብ እና ጥሪ መዳፈር በራስ ላይ ማዕት አውርድ ብሎ መሬት መደብደብ ነው … መጪው ጫን ተደል መከራ ከተቻለ …
  • ·         የነፈረ ገመና  መውጫው …

ወያኔ ሃርነት ትግራይ ብስጩ ትወልድን ነው የገነባው። ወያኔ ሃርነት ትግራይ ቁስ አምላኪ ትውልድን ነው የገናባው። ወያኔ ሃርነት ትግራይ ራሱን ያሾለከ ትውልድ ነው የገነባው። ከዚህ ያመለጡ ሊኖሩ ይችላሉ፤ ግን የአሽዋ ግንባታው የበለጠውን እጅ ይይዛል። ከዚህ ከወያኔ ከበከተ ዶክትሬን ትውልዱ መውጣት አለበት። የዚህ የበከተ የትወልድ ግንባታ ፕሮግራመር ደግሞ አውራሪሱ አቶ በረከት ስምዖን ናቸው። ለዚህም ነው እዬታገሉት ያለው አዲሱን ጤነኛ የ ኦህዴድ ብርቱ ድርጅታዊ አቋም። ህልሙ የባከነ ኢትዮጵያዊ ትወልድ ማዬት ራዕያቸው ነው እና።

በዘመነ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሰው ብቻ አይደለም ስደተኛ የሆነው። ዜግነት ተሰዷል፤ ዕውነት ከነተፈጥሮው ተሰዷል። ተፈጥሯዊነት ተስዷል። ትውፊት - ባህል - ወግ - ልማድ - ሃይማኖት - ሰብዕና - ቤተሰባዊ ግንኙነት ተሰዷል። ማህበራዊ ግንኙነቱ በጥርጣሬ የተሞላ ነው። ልብን ጥሎ ያሻውን ላሻው ማውጋት ዛሬ አይቻልም። እንቅጩ ነገር ሰው ፈርተናል። ተፈራርተናል። የጎሪጥ የሚተያዬው ህልቆ መሳፍርት ነው። ዕውነት ተሰደደ፤ ሃቅ ተሰደደ፤ መተዛዘን ተሰደደ፤ ደግነት ተሰደደ፤ አብሮንት ተሰደደ፤ ተፈጥሯዊነት ተሰደደ፤ አለማፈር በዓዋጁ ሆነ። ውሸት በታማኙ መንግሥት አንደበት ዝማሪያዊ ሆነ። ዘረፋ በራሱ በአስተዳደሪው በመንግሥት በፖሊሲ ደረጃ ሆነ። ውሎ የሚያድር ቅንጣት የእውነት ጓል ፈጽሞ የለም - መንግሥት ተሁኖ፤ እንመራለን ተብሎ፤ ድምጹ ራሱ ደረቅ ነው። የድምጹ ምት የፈለሰ ነው። መንፈሱ ህውክት የሰፈነበት ገራራ ነው። ተስፋ ለትውልዱ የጠነዘለ የጠወለገ ነው። ነገ የሚፋራ የሚያስፈራ ነው። አቅጣጫ የለሹ ወጀብ አስጊ ነው …

ስለምን? መሪዎች ዋሾዎች፤ ዘራፊዎች፤ ቀማኞች፤ ወራሪዎች፤ ሥርዓት - አልበኞች ስለሆኑ። በቃ! ቅንጣት ዕምነት የሚባል ነገር የለም። የተፋቀ ነው። ቅንጣት „መንግሥት አለኝ“ ማለት አይቻልም። ማዕከላዊ ኃፊነት የተፈገፈገ ነው። አንድስም እንኳን ከቤተኞች በስተቀር „መንግሥታችን፡ ይቆዩልን የሚል የለም። ያላቀን! ነው።

አንዲህ ሆኖም በዚህ ቅጥ አንባሩ በጠፋበት፤ ውሉ ባልተገኘበት፤ ውልብልቢቱን ማግኘት በተሳነ ወቅት ቀደም ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በፈጣሪ ጥበብ እና ታምር ጭራሽም ይሆናል ተብሎ ሊታሰብም // ሊገመትም በማይችል ሁኔታ ነው እነኝህ የዘመን ነባቢቶች አቶ ለማ መግርሳ እና ዶር አብይ አህመድ የተገኙት። ታሪክ ነው የፈጠሩት። ታሪክ ነው የሠሩት። የትም ቦታ፤ በዬትኛውም ሁኔታ ምስክርነት ሊሰጥላቸው የሚገቡ የዓይን ጸጋ የተሰጣቸው ድንቅ የኛዎች ናቸው። ሊታሠሩ፤ ሊገደሉ ይቻላሉ ግን የፈጸሙት ግድል በእነሱ አቅም አልነበረም። በፍጹም። ፈጣሪ የቀመረው የኖኽ መርከብነት ነው። ሥጦታው ሙሉዑ ነው። ሃርድ ዌር ብቻ አይደለም ያላቸው ሶፍት ዌሩም ሙሉዑ ነው። ጭንቅላት ብቻ ሳይሆን አዕምሮም ህሊናም ንዑድና ቅን ብሩህ ሃሳብም ያላቸው ናቸው። ለዚህም ብሩህነት የ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው መንፈስ ጥግና ከለላ መሆኑ ደግሞ የፈጣሪን ጥበብ ማስተዋል ያቸለ ትንግርት ነው  - ለእኔ። ፈጣሪ አምላክ መሽሎኪያ አዘጋጅቷል። ግን ማድመጥም ማዬትም ከተቻለ ብቻ።

ሌባም ከዘረፋው፤ ዋሾም ከቅጥፈቱም፤ ወራሪም ከመስፋፋቱ፤ ዘማዊም ከቅሌቱ፤ አፍራሽም ከናዳው፤ ሸረኛውም ከጉድጓዱ፤ ሴረኛውም ከሸለቆው፤ አስመሳዩም ከግርዶሹ፤ የማደጎ ልጁም ከራሱ ጋር መክሮ እና ዘክሮ ሱናሜው ሳይውጠው ከመልካሙ መንፈስ ጋር እራሱን ዝቅ አድርጎ ለመማርም ሆነ ለመታረም፤ እንደ ጥፋቱ ልክም ራሱን ለመቅጣትም፤ የህዝብን ፍርድን ለመቀበልም መዘጋጀት ግድ ይል ነበር።

ደርግ ቢወድቅ እኮ ተጠቂው ሁሉ ነበር። ወያኔ ቢወድቅ ግን የበለጠ የሚጠቃው ወያኔ ሃርነት የተፈጠረበት መሬት ቡቃያ ነው። የታመቀ እልህ አለ። ነዲድ ቁጣ አለ። አቅጣጫው ያልታወቀ ብስጭት አለ። የተከዘነ ቂም አለ። በዛ ላይ „ተው!“ የሚል የዚያን ያህል ነው። እና እሳትና ጭድ ነው መጪው ጊዜ። መፈራት ያለበት ይህ እንጂ የለውጥ መንፈሱ ሊሆን አይገባም። አዳኝነቱ በፍቅረ ንዋይ ላበዱት፤ በሥጋ ፈቃድ ለባከኑት፤ ለግለኝነት ላደገደጉት ጭምር ነው።

 …. ልብ ቢኖር … ሌብነት ሹመትም ሽልማትም አይደለም። ስርቆት ዝቅተኝነት ውርዴተኝነት ብቻ ሳይሆን ውስጥን የሚያቆሽሽም ውርዴ ነው። ለማ አብይ አንድ ነገር ቢሆኑ ሚሊዮን ተክተው ነው። እያያችሁት ነው 100 ስታስሩ ሁለት መቶ ለመታሰር የፈቀደ በቃችሁን! አንገሸገሻችሁን! ልናያችሁ ከቶውን አንሻም! እያለ ትውልዱ ወደ ሞት እዬገሰገሰ ነው። ከገሃነም ወደ ገሃነም ፈቅዶ እና ወዶ እዬነጎደ ነው። በዛ መረራ እና በጉፈነነ እስር ቤታችሁ ለመታጎር፤ በጭካኔ የምትለቁትን ጥይት ጎርሶ ወህ ለማለት ግንባሩን እዬሰጠ ነው - ትውልዱ። ሥልጣናችሁን በአሻም እያነጠፈላችሁ ነው ትቢያ ላይ። ዕውነት ለማናገር ማዬትን እራሱ አይፈቅደውም። አረመኔነት ምኑ ይታያል፤ ጭካኔ ምኑስ ይናፍቃል?  ይህን መስመር ለመስያዝ ነው የለማ መንፈስ ፍዳውን እዬከፈለ ያለው። እና … ዱላ በማን ላይ? ፈጣሪ አምላክ መንፈሱን በፈቀደላቸው የፍቅር ሐዋርያት ላይ? ፍርድ ካለበት ይኖራል … ትውልድ የሚባል ቀጣይም እኮ አላችሁ አይደል?!
  • ·         ውርነት።

„ለሃጣን የመጣ ለፃድቃን“ ሆኖ የነገ ህፃነት ናቸው ለእኔ ጉዳዮቼ … ለእናንተ እንጦርጦስም ሲያንስ ነው፤ ከእነ ሪሞርኬው አቶ በረከት ስምዖን ጋር … ኢትዮጵያ የሰው ድሃ እንድትሆን ተግተው ሠሩ። ሰው አንዳይወጣባት ነበር ተልዕካቸው። ሰብዕናው ሙሉ ሰው ሲለቅም፤ ሲታደን ተኖረ። የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁሉ አከርካሪ እዬተመታ የካቴና እራት ሆኑ፤ የሚገደለው በመርዝም፤ በመኪና አደጋም የተገደለው ተገደለ፤ በጠለፋ፤ በመሰወር፤ ድብዛው የጠፋ፤ የአ ዕምሮ በሽተኛ ሆኖ የቀረ ቤቱ ይቁጠረው። ውጪ ሐገርም አይቀራቸውም። የዚህ ፕሮጀክት ዲዛይነር ናቸው አቶ በረከት ስምዖን። ወያኔ ሃርነት ትግራይ ያለው ሃርድ ዌር ብቻ ነው። ሶፍት ዌሩ የአቶ በረከት ስምዖን ነው። የኢትዮጵያ አንጡራ ነቀርሳ እሳቸው ናቸው። በስውር ያሰደዱትን አሰድደው፤ በስደትም የከውኑትን ሸክፈው፤ አገር ቤትም ያደረጉትን አድርገው ኢህድግን የሚተካ ግንባር አይኖርም እያሉ ሲለጠጡ የነበረው ለዚህ ነው። ደባቸውን ያውቁታል። ልክ ያስያዙትን ያውቁታል። ሁሉም መከራ በሳቸው ሴራ የተፈተለ ነው።

በድንገት ግን ትህክታቸውን ጥሶ ከግንባራቸው ውስጥ ፈጣሪ ጥበብ ሰራ እናም አበዱ! አጎሩ! አቅራሩ! ፎካከሩ! ታሪኩ ይሄ ነው። አሻንጉሊት መሆን ቀረ። መወሰን ቢችል እኮ ስበስቡ ቀድሞ ነገር ጡረተኛ ገብቶ እንዲህ ባልዋኘበት ነበር። የኢትዮጵያ ህይወት እንዲህ በአለቀበት የዘገ ባትሪ መጫወቻ ባልሆነ ነበር …

ግን ግን … የሌቦች ማህበር፤ በሰው ግብር እና ደም የሰከረው ማህበረ ሲዖል እዚህ ድርሷል፤ ነገስ …? በተተኛው ወይንም በተመከተው ልክ ይወሰናል ዕድሉም ሆነ ተስፋው። … የዛሬ የሃይላንድ ውሃ ነገን የራስን ትውልድ የሚያበረክት ከሆነ ትዕቢቱን ፈጣሪ ይዳኘው … በልክ ባልተሰራ እጀ ጠባብ አገር መምራት ቀርቶ ማሰብም ይቸግራል። ያለቀ ነገር አለቀ ነው። ተሟጧል።

„ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“
(ከአቶ ለማ መግርሳ የተወሰደ)
„ኢትዮጵያዊነት ከጅብ ቆዳ የተሰራ ከበሮ አይደለም።“
(ከዶር. አብይ አህመድ የተወሰደ።)
በቃችሁ ይበለን አምላካችን። አሜን!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። 

  

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።