ጎንደር ክፍል አንድ።

     ጎንደር ክፍል አንድ።
                     ከሥርጉተ ሥላሴ 05.04.2014 (ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ)

   „እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች የሚያረታ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሄር ነው“
                            መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፲፯ ቁጥር ፴፫



የጎንደር ከተማ ስትነሣ የፋሲል ግንብ፣ የፋሲል መዋኛ እና ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ናቸው በብዛተ የሚጠቀሱት። በከተማዋ ወስጥ ግን ከምድር በላይም ሆነ ከምድር ሥር ያልታወቁ እና የተዘነጉ አያሌ ቅርሶች ይገኛሉ።“ ( ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተጻፈ ከማህበረ ቅዱሳን ማህበራዊ ድህረ ገጽ የተወሰደ)
·       ስሜት ያልተዳሰሰ ግዙፍ ተፈጥሮ።
እንደ እኔ ስሜት ሆኖ ማሰብ ይከብዳል። በእኔ ስሜት ውስጥም ጫና ፈጥሮ ስሜቱን ለመሸጥም የሚችለው ለስሜቴ የሚመች ቅርብ ሲኖር ብቻ ነው። ስሜት ሁሉን ሰንቆ ይራመዳል። ስሜት ድምጽ አልባ ቋንቋ ነው። ቋንቋውም ጠንካራና ደንበር አልባ ነው። የውስጥ ስሜት ቋንቋው አካባቢያዊ ተፈጥሮን ንዶ፤ ተርጓሚ ባለሙያን ሥራ አጥ የሚያደርግ ረቂቅ ግን ጉልበታም፤ የማይታይ ውጤቱ ግን የሚዳሰስየሚጨበጥ ሚስጥራዊ ተፈጥሮ ያለው ነው። በዚህ መንፈስ አብረን እንጓዝ ዘንድ ለመንኩ ጸሐፊዋ ሥርጉተ ሥላሴ።

ለእያንዳንዱ ሰው የተፈጠረለትን የማንነት ዲካ በቅጡ በመፈተሽ እንደ እራስ ለመኖር በማስተዋል ተፈጥሯዊ መክሊትን ልብ ብሎ ማድመጥ ይገባል። በመሃል ሽርፍራፊ ነገሮች አውዱን እንዳያወከውም ጠራርጎ ማስወጣት ይገባል። እንደ ተፈጥሯዊ መክሊቱን እንደ እራሱ አፈጣጠር መተርጎም የሚችል ፍጡር፤ በሌላው ላይ ትርምስ ሳይፈጥር ከተፈጥሮ ጋር ተዋህዶና ተጣጥሞ ወደ ላይም ሳይንጠራራ ወደ ታችም ሳያዘቀዘቅ ሚዛኑን ጠብቆ መኖር ይችላል። ለዚህ የበቁ ሰዎች ሁልጊዜ ፍሬያማና ውጤታማ ይሆናሉ። እኔ እንድንማርና እንደንወርሳቸው የምፈልገው አብይ ነጥብ ያለው ከዚህ ላይ ነው። እንደ እራሳቸው ማንነት ስለሚኖሩ ሰዎች ብቃት ስናስብ የፈለገ ዓይነት ነገር ቢሆን ከቃል አወጣጥ ጀምሮ በራሳቸው መንገድና በተፈቀደላቸው ብቻ ነው ሂደቱን የሚያዋቅሩትና ዬሚመሩት፤ ስለሆነም ወጤታማ ናቸው።

 ይህን መሰል ጸጋ ለተጎናጸፉት፤ ሙሽራ ዓይነ ህሊና ያላቸው ልዩዎች ናቸው እላለሁ። አብነት - የቅኔው ንጉሥ ሎሬት ጸጋዬ /መድህን ማቅረብ ይቻላል፤ ዛሬ ምን አሰበ? - የእንቅልፍ ሳቅ አይነት --- አዎን ልክ እንደዛ ይሰማኛል ይህን ጹሑፍ ስጽፍ። አላገኘውማ ጥገት ጠረኑን። ይህን አስቦ ዛሬ ተነሳ። ህግ መተላለፍ መልካም ስላልሆነ የሚመክት ዘለግ ያለ ጭብጥ ሃቅን ተንትርሶ በተከታታይ ይቀርብበታል። ዕውነት ሲጎረስ ራህብ ይታገሳልና! 17ኛው መቶ ክፈለ-ዘመን የሀገራችን መናህሪያ ዋና ከተማ፤ የነገሥታት እንብርት፤ የሥልጣኔ ጮራ፣ ዕጹብ ድንቁ ቅርስና ውርስ በተደሞ በዕምቅ ሃብትነት የከተሙባት፤ የመንፈስ ዘሊቅ ሃብታት እናት ናት ጎንደር። ጐንደር ደጋ - ወይና ደጋ - ቆላ ሦስቱም የአዬር ጸባይ ያላት ክፈለ-ሀገር ናት። ሰቲት፣ አብደራፊና መተማ - በቆላ፣ ነፋስ መውጫ - ደባርቅና አንባ ጊዮርጊስ በደጋ፤ አይከል፣ ደልጊና አዳርቃይን በወይና ደጋ ምሳሌነት መወሰድ እንችላለን።

·       ነፋሻማዋ ግርማዊት።
ጐንደር ተራራማና ነፋሻማም ናት። በተጨማሪም ዬውጭ ምንዛሬ ሊያስገኙ የሚችሉ ሰፋፊ ምርት - ጠገብ ለም መሬት የነበራት ክፍለ-ሀገር ናት። መተማ፣ ማጠቢያ፣ ቋራ፣ በከፊል አለፋጣቁሳ ሰቲት ሁመራን መጥቀስ ይቻላል። ሰሊጥ፣ ጥጥ፣ ሙጫ ወይንም ዕጣን፤ ቅመማ ቅምም በእያይነቱ፣ የእህል ዘር በሙሉ፤ አትክልት በተወሰነ ደረጃ፤ ለአካባቢ ፍጆታ ብቻ የሚውል የቡና ምርት፤ የእንሰሳ ተዋፆ፤ ማርና ጣዝማ፤ ብርቅዬ እንሰሳትም። እንዲሁ፤ ምርምሩ ገፈ ብሎ ቢሄድበት ሌላም …. ሌላም እምቅ ዬከርሰ ምድር ስንቅ ባለቤት ናት - መናገር አስፈላጊ አይደለም። ቀደም ባለው ጊዜ ጎንደር በፈካ ታሪኳም ገናና የሆነች የበጌምደርና ስሜን ዋና ከተማ ስትሆን ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና ነበረች። ፍልቅልቋ ጎንደር ጥንታዊት፣ ታሪካዊት ማህደረ - ቅርሳት ያሉባት እራሷ ትውፊት የሆነች፤ ሥር በሰደደ ዝምድና መተሳሰር ሁለቱም ሃይማኖቶች ፍቅርን በገቢር የተረጉሙባት ጣፋጭ ክፍለሀገር ናት። ቅኔውም፣ ንባቡሙ፣ የአንድምታ ትርጉሙም፣ መጸሐፉም ሁሉም በፍቅር በሚስጥር የታደሙባት የወርቅ ሙዳይ - የጥበባት ሞስበ - ወርቅ ናት።

·       የአብሮነት ዕንቁዋ።
 በእስልምና እምነትም ቢሆን እምነቱ የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር ያሟሉ አቮው ተወደው - ተናፍቀው - ተከብረው - የታደሙባት ባዕት ስትሆን፤ በጋብቻ፣ በጉርብትና፤ በጡት ልጅንት በዘንጠፋ ትህትና በመስተዋድድ መኖር የሰከነባት ተምሳሌዊት ክፍለሀገር ናት። ሳቂተኛዋ ጎንደር ቀደም ባለው ጊዜ ሰባት አውራጃዎችን በርካታ ወረዳዎችን ታስተዳድር የነበረ ሲሆን አውራጃዎቿ ጭልጋ ዋና ከተማው አይከል፤ ወገራ ዋና ከተማው ዳባት፤ ስሜን ዋና ከተማው ደባርቅ፤ በጌምድር ዋና ከተማው ደብረታቦር፤ ሊቦ ዋና ከተማው አዲስ ዘመን፤ ጎንደርዙሪያ ዋና ከተማው ጎንደር፤ ጋይንት ዋና ከተማው ንፋስ መውጫ ነበር። ጎንደር የበለጸገ የእምነት ጽናት፤ እጅግ የሚመስጥ ልዩ የአብሮነት ባህል፤ የቀደምትነት የሥልጣኔ አሻራ፤ የመረዳዳት አስተምህሮ፤ የሀገር ወዳድነት ቀንዲልነት፤ የመተሳሰብ - ልዩ አንባ፤ የሥራ ደቀመዝሙር፤ የመሆን ናሙናዊ ሸማ ናት - ሙቀት።

በዘመነ ዓጤው ትግሬ መጮሂያ በዘመን ደርግ ደግሞ ገነት ተራራ የሚባለውን ጋራ ትራስ አድርጋ የተመሰረተችው እርአስ ከተማዋ ጎንደር 17ኛው መቶ ክፈለ ዘመን የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ በመሆን ዘመኑ የፈቀደላትን ሁለገብ ድርሻዋን በብቃት በአንቱታ ተወጥታለች።

ጎንደር የልዑላን፤ የነገሥታት፤ የእቴጌዎች፤ የወይዛዝርት፤ የሊቀ - ሊቃውንታት (የአራት ዓይናማዎች) የደናግል፤ ቅዱሳን የሚፈልጓት፤ የሼኮች የሐጂዎች ማህጸነ ወርቅ ቦታ ናት። ዛሬ ግን በዘመነ ወያኔ ጎንደር ከወራዳ ያነሰች እጅግም የተዋረደች፤ እንደ አልባሌ ዕቃ ተወርውራ ቋሳ ያሰኘውን ያህል በግራ ቀኝ የሚቀጠቅጣትና የሚደቃት፤ በባዕድ በሱዳን ጭምር ሳይቀር በቡጤ የምትፈለጥ መከረኛ ክፍለ - ሀገር ናት - ለባእድ ክብሯ እንዳወጣ የተሸጠባት ደም የምታለቅስ ቦታ ናት። እንዲሁም ጎንደርን ከሱዳን ጋር የሚያውስኗት ተፈጥሯዊ ደንበሮቿን ሁሉ በጉልበትና በኃይል ወመኔው ወያኔ የቀማት፤ ግፍን በዬዘመኑ አብዝታ የተቀለበች፤ አሳር የገረፋት ክፍለሀገር ናት። ነገር ግን ጎንደር ውስጧ ውበት ሲሆን በአንድ ወቅት ጸሐፊ ካትሪን ሄልድማን እና ፊተስንራተር ጎንደርንየኮዝሞፖለቲክ እናትሲሉ አሟናሙነው ጽፏዋታል። ዘይቤውና ዘርፉማ ቃናዋ፤ መንፈስን የሚገዛ የአኗኗር ጹዑመ ዜማ ያላት በመሆኑ ይህ ጽኑ መቀነት ሆኖ አገልግሏታል። 

ስለዚህም ልጆቿን ቀጥተኛና ግልጽ ባህሪያትን የሚደፍሩ አድርጋ ለማሳደግ ትጥቅና ስንቅ ሆኗታል። በተለያዬ ጊዜም የውጭ ጸሐፊዎችን ጎንደርን በቋሚነት ለረጅም ጊዜ በመንፈስ ውስጥ በትዝታ የመቆዬት አቅም ያላት ማራኪና ሳቢ፣ ተወዳጅም፤ የዬትኛውም አካባቢ ህዝብ ተስማምቶ ሊኖርባት የሚችል ሲሉ አጉልተዋታል።
·       እንግዳ ክብሯ ነው።
 የጎንደር ክብርና ሞገስ እንግዳ በመሆኑ ሰው በልቶም የጠገበ አይመስላትም - የበሞቴ ዬአፈር ስሆን እናት - ጎንደር። በሌላ በኩል የጎንደር ህዝብ ልክ እንደ ሌሎች አካባቢ ወገኖቹ ለሰንደቅዓላማውና ለዳር ደንበሩ እጅግ ቀናዕይ በመሆኑጎንደሬን ጎንደር ተደፈረች ድረስ ከሚባል፤ ኢትዮጵያ ተደፍራለችና ድረስቢባል እንደሚቀለው በአንድ ወቅት አዕምሮ ጋዜጣ ላይ 1985 . ጽፌ ነበር። ከፊት ሆኖ የሚታይ ጋሻ ህዝብ ያላትም ናት ከዚህም ባሻገር ዘመን ሊያሻግር የሚችለው የመኖርን ጥበብ ልኬታ ሲመዘን መንፈስ አጥግብ ሥነ - ነፍስ አለው። ለዚህም ነው በተጨማሪነትአዕምሮበሚባል ጋዜጣጎንደር ሲመጡብሽ በለቅሶ ሲሄዱብሽም በለቅሶብዬ 1986 ድጋሚ ጽፌ የነበረው። ስለምን? አንድ ሰው ከሌላ ክፈለ-ሀገር ወደ ጎንደር ተመደብክ ሲባል የሚያለቅስውን ያህል ሳይሆን እንዲያውም በእጥፍ ከጎንደር ተነስተህ ወደ ሌላ ክፍለ - ሀገር ተዛውረሃል ሲባል የሚያፈስው ዕንባ ሰፊ መሆኑን እውነቱን ለማጠዬቅ ነበር።
·       የቅንነት ጉልት።
የቅንነት መቀነቷን ጎንደርን ለምዶ መለያዬት እጅግ ይቸግራል። ከከተማ እስከ ገጠር ጎንደር መንፈሱኢትዮጵያዊነትነው ይህን ደግሞ ወደ ኢህአፓ የተቀላቀሉ ኢትዮጵውያን ሊመሰክሩት የሚችሉት የሃቅ ዕንቁ እንክብል ነው። ከዬትኛውም አካባቢ የጎንደርን ጫካና ዱሩን የተመኙ የኢህአፓ ወጣቶች የተመሙት ወደ ጎንደር ተፈጥሯዊ ምሽጎች ስለነበረ ማተብን ጠብቆ አደራን በማዋጣት አንቱ የሚያሰኘውን የአይነታ ተግባር አርበኛ ስለመሆኑ አፍ ሞልቶ ያናግራል። ዬብቃትና የሙሉዑነት ሰብዕና ሃብቷ ስለመሆኑ በህይወት ያሉ ሁሉ ቀደምት የኢህአፓ ታጋዮች፤ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት፤ ሊመሰከሩ እንደሚችሉ አምናለሁ። በእድገት በህብረት ዘመቻም መሰሉ ምስክርንትን እንደሚኖር አስባለሁ። 

በዘመን ኢዲዩ ሆነ በከፋኝ ዛሬም በአርበኞች ግንባር የጎንደር ህዝብ እራሱን ሰጥቶ፤ በፍቅር ወገኖችን የማስተናገድ ብቁ ተፈጥራዊ ልኩን በህይወት እያለሁ ቁሜ እንዲህ እመሰክራለሁ። በማህበራዊ ሥነ ልቦና፤ በሥልጡነንት፤ በራስ የመተማመን ጥብቅነት፤ ለወደዱትና ላመኑበት ጉዳይ እራስን አሳልፎ በመስጠት፤ ቃልን በመጠበቅና በመንከበከብ፤ ሽፍን ክውን አድርጎ ኃላፊነትን በመወጣት፤ ዕምነትን በመጠበቅም ጎንደር ላይ ያለው ጤነኛ መንፈስ እጥፍ ትውልድን ሊገነባ የሚችል ፍጹም የሆነ ልዩ የእርግጠኝነት ጥሪት ስለመሆኑ በልበ ሙሉነት እናገራለሁ።
·       ማዕዶት።
ማዕዶተ - አብሮነት በጎንደር ሲገመገም ደግሞ ያጠግባል። እንግድነት 5 ደቂቃ በላይ ቆይታ የለውም። እንግዳ የሚባል ነገር ኖሮም አያውቅም። ወዲያውኑ አዬሩ ቤተኛ ያደርጋል። ማህበረሰቡ ቀረብ አድርጎ፤ እቅፍ ድግፍ አድርጎ ቤት ያፈራውን አካፍሎ እያቆላመጣእናትዬ - ሆድዬ - ዓለምዬእያለ የእንግድነት ስሜቱን ቢና ጢና የማውጣት ጥበቡ ሆነ ባህሉ ዝልቅና ዝቀሽ ነው። አያያዙ ወዲያውኑ ለማዳነት አቅልሞ ሸማውን በሙቀት በቁመት ልክ ያለብሳል። የቤተኝነት ስሜቱ ጉልበታም ስበት እንዲኖረው የማደረግ ጥበቡ ልዑቅ ሥነ ሕይወት ነው።
·       ክውና።
አንድ የምርምር ተግባር ያስከውናል። ቃላቶችን አደራርቤ ብጽፋቸው ይህን እውነት ከቶውንም አይገልጽልኝም። የማከብራችሁ የሀገሬ ልጆች በዬአጋጣሚዊ በመጥፎ ተምሳሌነት የሚሳለውን የጎንደር ህዝብ ክብር መጠበቅ ግድ ስለሚል ክፍል ሁለትን በቀጣዩ ጊዜ አቀርባለሁ። መግቢያው በዚህ መልክ፤ ሐተታው ደግሞ በቀጠሮ፤ ለምትመድቡልኝ ወርቃማ ጊዜ የሚመቻችሁን እንደፈቃዳችሁ ፈጣሪዬ ይስጥልኝ።

እልፍ ነንና እልፍነታችን በተግባር እልፍ አናድርገው።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ። መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።