እማዋይ የዘመን የኔታዊት!

     የጥቁር ለባሿ ልዩ ጀግና! 
      የዘመን የኔታዊት ገናና!
                                         ሥርጉተ ሥላሴ  17.02.2018 (ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።) 

                "በተቸገረ ጊዜ እግዚአብሄርን ወደ መፍራት የሚመለስ ሰው አለ ሰውነተም በተድላ በደስታ ታርፋለች።" 
                                                  (መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ፳ ቁጥር ፳፩)
  • ·         እፍታ።

እንደም ነሽ ውርሰ ጽናት እማዋይ? ደህና ነሽ ወይ? እህት ዓለም እንኳን ለዚህ አበቃሽ። ግን እንዴት ነሽ የጥቁር ለባሿ ጀግና ብቋዊት? እንደተፈታሽ ገጽሽን ሳዬው ውስጤን በጠበጠው። ተረባበሽኩኝ። ለረዥም ጊዜ በጸጥታ ውስጥ ነበርኩኝ። እኔ ጫካ በገባሁበት ጊዜ ተገናኝትን ቢሆን ኖሮ የወላጆቼን የምህረት ጥያቄ አልቀበልም ነበር። ስቃዩን እንጋራው ነበር በዱር ቤቴነት። አንድ አጋር አንስት በማጣቴ ምክንያት ነበር የተመለስኩት። በምህረት ከገባሁ በዋላም ቀዮዋን በር አይቻታለሁ። ስፈታም በቁም እስር ነበር። ሌላው ነገር ከእኛ በዋላ በአዲሱ ትውልድ የጣይቱ፤ የተዋቡ፤ የምንቴ፤ የሰብለወንጌል የጽናት እና የብቃት ንጥረ መንፈስ አምብዛም የነበር ቢሆንም ጎልታ የምተወጣ ወጣት ትንታግ ህልሜ ነበር ልክ እንደ እኛ ዘመን። 
  •                                      ስተት።

በድንገት ግን የጥቁር ለባሿ የክስተት ትርታ ባለተራ ተከሰተች። አርበኛ ንግሥት ይርጋ። ከዚህ ዋላ ግን የአንችን ጉዳይ ከደን አድርጌ ክድን አድርጌ የታገስኩት ጉዳይ መቀጠል አላቻልኩም። ቀደም ብዬ እንዳነሳሁልሽ ከ እኛ በሀዋላ ለአዲሱ ቀጠይ ተከታይ ትውልድ የነገረ ፖለቲከኛ አንስት ጭራሽ ድርቅ የመታው ያህል ይሰማኝ ነበር። ሃዲድ አልቦሽ ነበር። መንፈስ ማረፊያ አልነበረውም። ልሳን አንደበት የሆነ ለዬትኛውም ጊዜ በአጅጉ በተከታታይነት ያስፈልጋል በሴትነት ማንነትም ላይ። ይህ ለነገ የሚቀጠር አልነበረም። 

በእኛ ዘመን ብዙ ነበርን። በሴቶች ጉዳይ ብቻም ሳይሆን ከዚህም ከፍ ያለ ሃላፊነትን በብቃት የመወጣት የዕውቅና ድርሻ ነበርን። ታስታውሻላሽ አይደል? አንቺ ትሠሪበት በነበረው ወረዳ አስተዳደሪ ሴት የሺዬ ነበረች። ከእኛ ዋላ ግን መጸሐፉም ቄሱም ዝም ሆነ። ሌላው ቀርቶ በገዢው የጎሳ የፖለቲካ ድርጅትም ሚዲያ ላይ የማያቸው አንስቶች ሴት የፖለቲካ ሊሂቃን አብዛኞቹ ራሳቸውን መግለጥ የማይችሉ ናቸው። እንኳንስ ክ/ ሀገራት ላይ። እርግጥ የ42 ዓመት እሰረኛዋ የመከራዋ ጥቁራት ረቂቅ ነው ሥሙ እራሱ የአደጋ ምልክት ነው።

እንዲያው በድንገት ግን አንድ የምሥራች አደረሰኝ የጎንደሩ የአማራ ህልውና ታሪካዊ ተጋድሏዊ አብዮት። በወቅቱም ሙቀቱ አልቀሰቀሰኝም። በአደብ ሁኔታውን ግን እከታተል ነበር። አክቲብ አልነበርኩኝም። የአማራ ተጋድሎ ታታሪት የንግሥት ይርጋ፤ መታሰር፤ የክሷ መዝገብ ጭብጥ የተፋለሰ እና ተሳሳተ ስለነበር እልህ አዋለደ። እርግጥ ሌሎችም ያየሆዋቸው ዝበቶችም እልህና ቁጭቴን አቀጣጠለው። አዲሱን የትግል መስክ ልክ እንደ ጾታዊ ማንነቴ ለመቀበል እና እራሴን ለማለማማድ እጅግ ፈታኝ ነበር።ግን ይህቺ የዘመን ቀለበት ለቀጣዩ ትውልድ ምልከትነቷ ጉልህ ስለነበር ወሰንኩኝ። 

የተገባትን ትትርና ዕውቅና ከነፍሴ ሰጠሁት። የአንችና የእኔ ግዴታችን ነው። ማተባችን አድርገን የቆዬነው የኖርንበት ደማችን ነው - ፖለቲካዊ ትግል። ወጣትነታችን የገበርንበት። ከወጣትነታችን ጋር የተላለፍንበት። የእሷ ግን ባሊህ ባይ በሌለበት፤ አይዞሽ ባይ በፈለሰበት እንዲህ ጎልታ ሳያት ዕውን ይህቺ የእኔ ናትን አስከማለት አድርሶኛል። ድፈረቷ ዕውነት ለመናገር ከእኛ በጥቂቱ ከቀደሙት ዘመን ከነበረው ይበልጣል። ጀግኒትን አዩን ሳልስት ማለት ነው። አንድ ነገር ተዚህ ላይ ከኢህአፓዋ አዩ ጋር አንድ ቀን ውጪ ሐገር ተገናኘን። እሷ እና እኔ ባመንበት የፖለቲካ መስመር በሃሳብ ብንፋለም ግን የአንገርብና የቀሃ፤ የጓንጉና የጣና፤ የአባይና የጉማራ ወንዝ በኮዳ ስደት ላይ ለዋንጫችን አሰኘን። ጥንካሬዋ የሚገርም ነው። ትንሽም ዘለግ አድርገነው ነበር ግንኙነታችን። ባልተጠበቀ ሁኔታ ነገሮች ተለዋወጡና አድራሻችን ተጠፋፋ፤ እናም ተለያዬን።

ሌላው እጅግ ከማደንቃቸው ሴት የፖለቲካ ሊሂቅ ተስፍሽ አንዷ ነበረች። „የተስፍሽን“ ከዚህ ዓለም ሞትም ስሰማ ውስጤ እጅግ ተጎድቶ ነበር። እስር ቤትም አብረን ነበርን። ሰሞኑን በሚገርም ሁኔታ ኢንተርኔት ላይ የሰጠችውን ቃለ ምልልስ አገኘሁት። ፎቶዋንም እንዲሁ። አትሜ ዓርማዬ አደረኩት። እርግጥ ከፖለቲካው ዓለም ወጥታ በዕደ ጥበብ መሪነት ላይ ነበረች። ጎበዝ ሴት ነበረች። የመጀመሪያዋ የሴት የአንደኛ ደረጃ ት/ ቤት ዳያሪክተር፤ የመጀመሪያ የወረዳ ከዛም የአውራጃ ኢሠፓ ኮሜቴ የርዮቷአለም ጉዳይ ሃላፊም ነበረች። ብቃቷም ልዩ ነበር። ቃለ ምልልሱ ላይ „አንደበቱ ርቱ፤ ተደምጣ የማትጠገብ“ ይላል። ጥሩ አንድረገው ነበር አን ጓድ ገ/ድህን በርጋ፤ ጓድ ወንደወስን ሃይሉ የቀረጹን። በዬትም ቦታና ሁኔታ አንገትን ቀና አድርጎ በተመክሮ በዳበረ አቅም ነበር መንፈሳችን የገነቡት። ጥሩ የስልጡን ትጋት ማህንዲሶች ነበሩ።

ትናንት በአንቺ መፈታት ደስ ያለው የጋራ ወንድማችን ደውሎ ሲያነጋግረኝ በጠንካራ ሴቶች ጉዳይ ስንወያይ የተስፍሽን ብቃት አነሳን፤ በሥጋ መለየቷንም ነገርኩት፤ የሰማ ስለመሰለኝ። አልቀጠለም። ስልኩን አቋረጠው። ምን አልባት ከሰሞናቱ ከደወለ እስኪ አጽናናዋለሁ። ድንጋጤውን አስታግሰዋለሁኝ ብያለሁኝም። ሩህሩህ ነው። ታውቂያለሽ የጸጥታ ችግር ሲኖር በሌሊት መጥቶ ነበር ወደ ቢሮ የሚወስደኝ። አስካሁን ድረስም ያ ቅንነቱ ሴት አንጀቱ አለ። ለማንኛውም ያ የወጣትነት ትንታግነት ዘመንን በጀግንነት አቅልመሽ ምዕራፉን የኮበብ ብርሃናማ ትውፊት አደረግሽው። የትውልድ ብሩኽ ጎህ ቀዳጅ በመሆንሽ እንኳን ደስ አለሽ ዳግማዊት እቴጌ ጣይቱ! I am proud of You!
  • ኪዳናዊት።

እማዋይ ትውልዳዊ ድርሻሽን በአግባቡ የተወጣሽ ኪዳናችን ነሽ። ጥበባችን ነሽ። ስለእኛን የተማገደሽ ዘመናችን ነሽ። የማይችለውን በማይቻል ሁኔታ ችሎ ራስን ከመስጠት በላይ ሰማዕትነት የለም። መመካትም፤ መኩራራትም ባይኖርም ግን ትውልድን በተግባር በናሙናዊነት በማነጸሽ እጅግ አድርጌ ላመሰግንሽ ክብሬ፤ ጀግናዬ፤ እምቤቴ  ልልሽ እፈልጋለሁኝ። የዕውነት ዕውነት ነሽ። ይህን የንጽህና ብርታትሽን፤ ይህን ውርሰ ጽናትሽን፤ ይህን የአይበገሬነት አቅምሽን ለልጆችሽ ማውረስ በመቻልሽም ደግሞ ዕድለኛ ነሽ። ለነገሩ የአማራ ወላጆች ትውልዳዊ ድርሻቸውን ተወጥተዋል ብዬ አስባለሁኝ። 

የማያቸው ህዝባዊ ተጋድሎች ከአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ህብር ጋር ህብራዊነቱ በህሊና የታተሙ ናቸው። ወጣቶቹ ጎሳ በፖሊሲ ደረጃ በሚተገበርበት ሐገር እያደጉ፤ አማራነት በልዩ ግለት እና ጭቆና ፈተና ውስጥ በከተመበት በዚህ ቀራኒያዊ ድቅድቅ ወቅት ኢትዮጵያዊነት ሳይጠፋ አንዲህ ጎምርቶ ማዬት የሰማይ ታምር ነው። ሰሞኑን ጥበበኛው ቴወድሮስ ካሳሁን በነበረው ኮንሰርት ላይ ብሄራዊ ሰንደቅዓለማችን ለታዳጊ ወጣቶች፤ ለወጣቶች ማተባቸው ነበር። ስቴዲዮሙ እንዴት መንፈስን የሚያረካ ነበር። ብሄራዊ ሰንደቅ ዓለማችን ተጎንበሰው ሁሉ ሲሳለሙት ነበር። ይገርማል ልዩ ይህ የዘመን ፍጽም ክስተት ነው። 

ለዚህ ነው እኔ ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢርነቱን መርሄ ያደረኩት። በውነቱ የአማራ ወላጆች ታሪካዊ ሃላፊነታቸሁን በማይናወጽ አዕማዳት ላይ ገንብታችሁታል። ስለሆነም ያውም ካንቺ አንዲህ ዓይነትን የብቃት እትብተ ውርስ ወልደሽ በማሰደገሽ ብዙም የሚደንቅ ባይሆንም የልጆችሽ አንቺን ለማድመጥ መፍቀድ፤ የአንችን አርማ ለማንሳት መትጋት፤ በተጋድሎው ውስጥ ዘመናቸው የሚፍቅድላቸውን ተጋድሎ ሁሉ ለመፈጸም መትጋት መታደል ነው። ልዩ የተልዕኮ ፍሬዘርም ነው። ወጣታ ልጅሽ ትጋቷን አያለሁ እሰማለሁ። ይህ ህያውነት ነው። አሉሽ አሉን ማለት መቻላቻላችን በራሱ አጽናኝ መንፈሳችን ነው።
በተረፈ የእኔ የነባቢቴ አነባቢ ጀግኒት እማዋይ ምስጋናዬ፤ ክብሬ፤ ፍቅሬ፤ አክብሮቴን በትሁት መንፈስ ይድረስሽ ብያለሁ። ብጡል ነሽ። ፋናችን ነሽ። መሪያችን ነሽ። እወድሻለሁ የቃልኪዳን አርማዬ!

  • ·         ትኩሮት የተነፈገው ዕምቅ አዱኛ።

አትኩሮት የተነፈገው ዕምቅ አዱኛ የሴቶች የማድረግ አቅም ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን ኢትዮጵያ ከዓለም ተለይታ ወንድ ብቻ የሚወለድባት፤ የሚያድግባት፤ የተብዕት ማህበረሰብ ብቻ የሚኖርባት ብቸኛዋ ፕላኔት ናትን ያሰኛል። ኢትዮጵያን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሸጋጋርም ረገድ ወንዶች ብቻ የተጉበት ታሪክ እንደሆነ ነው ጭብጡ፤ መሬት ላይ ያለው ሃቅ የሚያውጀው። ነገረ እኛ ምድረ በዳ ነው።
የወንዶች የፖለቲካ ማህበር አጥበቆ ይፈራናል። የሚገርመው እስር ቤት መከራው ረቂቅ ነው። እራስን ማጣት ነው። በተፈጥሮ ውስጥ ተሰርዞ ለዘለዓለም መኖር። ያን ያለፈበት ሁሉ ያውቀዋል። በተለይም ለዬት ላሉት፤ ለዬት ያለ የዕድሜ ልክ ፋስ አለ። ልርሳው ቢባል እኳን ሁልጊዜ እዬገዘገዘ፤ እዬተከታተለ ሰላም የሚነሳ። 

የውስጥን ሰላም የሚያውክ። ይህም ሆኖ አሁን ያን ሁሉ መካራ ተሻግረው የማይሽር ረቂቅ ሰቆቃም አዝለው የወጡት የጣይቱ አርበኞች እንጫልትሻ፤ ድርቤ፤ እማዋይ አቀባባል በእውነቱ እጅግ ደንዛዛ፤ ቀዝቃዛም ነበር። ለሴት የፖለቲካ እኩልነት ተጋድሎ ዋጋ ለከፈሉ አንስት ጀግኖች ቢያንስ በተውኔት፤ በሥነ - ጥበብ ቤታዊነት ያሉ ሰውን ማዕከል ያደረጉ አንስቶች ያልጀመሩት ድንቡልቡል ገመና ነው ይህ አመክንዮ። ዕውነት ለመናገር የታመመን መጠዬቅ፤ የታሰረን እግዚአብሄር ይፍታህ ማለት፤ እንኳንም አስፈታህ ማለት ሰማያዊ ግዴታ ነበር ግን አንድስም እንኳን አልሆንም። ሴት እስር ቤት የደረሰባቸውን ረቂቅ ፈተና አብሮ ለመጋራት አለመፍቀድ እራስን በራስ የመሰረዝ ያክል ነው። 

መከራን አብሮ መጋራት ባይቻል ቢያንስ ደስታን እንዴት አብሮ መጋራት ያቅታል? በቃ የሰርግ ሚዜነት ብቻ ነውን ተልዕኳችን? በቃ ቀይ መንጣፍ ላይ መዘናከት ብቻ ላይ ይሆን ፆታዊ ጥሪያችን? ያሳፍራል ይሄ ለ ለአንዲት ዕውቅና ላላት ተዋናይት/ ጋዜጠኛ/ ጸሐፍት/ የሰብዕዊ መብት ተማጋች/ የአንስታዊነት ማህበርተኛ። ሴት ልጅ አመለካከቷ ልዩ በመሆኑ በህሊናዋ እስረኛ ልትሆን አይገባም። ምክንያቱም የሴት ተፈጥሮ ሰማያዊ ነውና። ጥበብ መከራን ካልተጋራ ሞረድ የሌለው ክህሎት ነው የሚሆነው።

 … ስለ ትናንት እምቶች ብቻ ትረካ በቂ አይደለም። ዛሬ ባለው ህይወት ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ለሚተጉት ትዳራቸውን፤ ኑሯቸውን፤ ወጣትነታቸውን ለሰጡ የሙሉ ነፃነት ግንባር ቀደም አርበኛ እህቶች ያልሆነ ታዋቂነት ይበጣጠስ  ትላላች ሥርጉተ ሥላሴ ተዚህ ተሲዊዘርላንድ። ይሄ ሴታዊነት የሚባለው ወጣት የሥነ - እኩልነት የተጋድሎ ድርጅት ይህን መከወን ካልቻለ፤ ለዚህ ጥቃት መከታ መሆን ካልቻለ ስለምን ተፈጠረ? ሚዲያም አለ በሥም „የጣይቱ“ የሚነገድበት። 

ለመሆኑ ይህ ሴታዊነት ለዛውም በወርሃ የካቲት የኮፐን ሀገርን መለከት በተነፋበት የተስፋ ወርህ ላይ ክፍተቱን በድፈረትና በሙሉ ልብነት መወጣት ከተሳነው ስለምን ተቋቋመ? የቄሮ አንበሶች እኮ ማንንም ሳይፈሩ እና ሳይቸሩ እኮ ነው መድፍ እዬረገጡ ፊት ለፊት ወጥተው ጀግኖቻቸውን በእልልታ፤ በሆታ፤ የተቀበሉት። አንስቶች እስከመቼ ተኝተው በለኝ እንደሚሉ እጅግ የሚገርምም የሚያስጨንቅም ሌላ እጥፍ ድርብ ግማድ ነው። መከራውን አብሮ ተኑሮ ፍሰሃውን ብግለት ማህጸንን ማዬት ደም ያስለቅሳል። እርር ኩምትርም ያደርጋል። የሚነሽጣት አንስት የመከነባት አገር ኢትዮጵያ መቼ ይሆን የሴቶችን ልቅና በወጉ የምታስተናግደው? ስለመኖራችን ዕውቅናው መቼ ይሆን የሚታወጀው? በክንፈ ሚስጢራዊ የማሰልጠኛ ተቋም የኮተቤ ምሽግምን የታሰሩም ይኖራሉ። ለነገሩ እዛ ያሉ ምንዱባን በሥምም፤ በጉዳይም፤ በአድራሻም የማይታወቁ ነፍሶች መቼ ይሆን ከመቃብር ይፍታህ/ ይፍታሽ የሚባሉት? ማንስ ይሆን ዋቤያቸው? የይስሙላው ፍ/ቤትም አያውቃቸውም እኮ። 

… አዬ አቦይ ክንፈ ሞተህም የኦሾቲዝም ጉድጓድ። ለ አንዲት የጥበብ እውነተኛ ቤተኛ ማገዶነትን መድፈር ካልቻለች ሰማያዊ መክሊቷን ትተላለፈዋላች። መከራ ይጥማል። ወደውና ፈቅደው ሲኖሩበት፤ ምድራዊ ሰምዕትነት ነው። ቢያንስ ለእነዚህ አንስት ጀግኖች ቆራጣ ጊዜ እንዴት ይጠፋል ለአፍታ አቀባበል?

ሥነ - ጥበብ እኮ ጥበብነቱ መከራን መሸከም መቻል ነው። ከዚህ ውጪ ጥበብ የለም። በመከራ ውስጥ ያላለፈ የጥበብ ቤተሰብ ድርቅ ነው። ጥበብ መከራን ከፈራ ተፈጥሮውን እንጦረጦስ ፈርዶበታል ማለት ነው። የ ዕምነት ሰዎችም የገሃዱ ዓለም ሱባኤ በሰው እጅ የወደቁ ነፍሶችን ቢያንስ አይዟችሁ ማለት ነው። ጽድቅ ሰማይ አይደለም ምድር ላይ ፈታናን ወደው ፊት ለፊት ሲገሰግሱለት ነው።
 
  • ·         ክወና።

የእኛ ጀግኖች በማሟያነት ሳይሆን፤ በስማበለውነት ሳይሆን፤ በመናጆነት ሳይሆን ለእውነተኛ የአንደበት ነፃነት፤ የ አቅም ሙሉ መድረክ፤ በመሰን አቅም የባልድርሻነት ሚና በትግል ለማምጣት ተኝቶ በለኝን መገነዝ ያስፈልጋል። ዛሬ ዓይን ራሱ ድርቀት ገብቶታል፤ የነፃነት ተጋድሎው በግማሽ ሹሩባ ነው መጪታውን የተያያዘው … ግን እስከመቼ? አይታወቀም። የ አማራ ተጋድሎ ሆነ ቄሮ ለተብዕት ጀግኖች የመሰጠውን ሙሉ ክብር ለ አንስት ጀግኖችም መስጠት ቀዳሚው የተጋድሎ አድማስ ሊሆን ይገባል። ሁሉም ነገር ከመጀመሪያዋ የህይወት ትምህርት ቤት ከሆነችው የ እናት ተፈጥሮ መሆን አለበት። የነፃነት ትግላችን ድል ርቀትም ይኼው ነው።

ሴቶች የነፍስ ሥጦታዎች ናቸው።
ሴቶች የፍቅራዊነት አብነቶች ናቸው።
ሴቶች የመሆን ጀግኖች ናቸው።
ውዶቼ ለሰጣችሁኝ ስስት ዝር ያላለበት ጊዜ ኑርልኝ ሸልምኳችሁ።

መሸቢያ ጊዜ።   

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።