የእኔ ትእግስት።

                    የእኔ ትእግስት ስናፍቅሽ ወይንስ ስመኝሽ
                     እሙዬ የትኛው ሥም ይሻልሽ ይሆን?
                                     ከሥርጉተ ሥላሴ 05.06.2018 (ከጋዳማዊቷ - ሲዊዘርላንድ።)

            „እግዚአብሄር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤ እርሱ ለቅኖች ደህንነትን ያከማቻል፤ 
               የፍርድን ጎዳና ይጠብቃል፤ የቅዱሳኑንም መንገድ ያጸናልና። (መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፪ ቁጥር ከ፮ እስከ ፰)
  • ·         በር።

አቶ ዛሬ እምር ብሎበት ነበር የዋለው በገበርዲን በከረባት ሽቅርቅር ብሎ ወሸቤም የቆዬ መስሏል። ንግሥቲቱም ፏ ብላ በሠረገላ ተኮፍሳ አገር ምድሩን እያፍነከነከችው ነው። እልፍኟ ኑብኝ ይላል። አልባብ ባልባብ፤ ታዲያንላችሁ ሥርጉትሻ ምኗ ሞኝ። እሷም የአቶ ዛሬን ግምጃ ቤት ለመታደም በልክ በሆነ ዝነጣ ወጣ አለች። ግን ምን አለ ሁልጊዜ እንዲህ ብትሆን ይህቺ የአውሮፓ ቅምጥል። ሰዉ ይስቀላ። ቀሎታል። ደስ ብሎታል። ታውቃላችሁ አይደለም? የሆነ አውሮፓ የሚጫን ደመመን ነገር አለው። ክብድ የሚል። ግን ዛሬ፤ ዛሬማ የእምዬን ያህል አምሮበታል። አድባሩ።

ውይ ሳልነግራችሁ እነዛ ጥፍት ብለው የከረሙት ባለክንፎቹ ባንዳቸውን ይዘው ከች ለበጋ እረፍት። በጥዋት የቀሰቀሰኝ የእነሱ የንጋት ማህሌት ነበረ። ተዛንላችሁ ትንሺ ዘወርወር ብዬ መለስ አለኩኝ እና ወዜን አሳርፌ ማለት ነው፤ ያው የዘወትር የሀገር ቤት የዜና ኬወስክ እናቱ ይባል አባቱ ይባል ብቻ የአንጀት አድርሱ አይዋ ዩቱብን ከፈት ሳደርግ የምወድሽን ግኝት። ዛሬ ወግ በወግ ሆንኩኝ አይደለ … ብርሃን ደስ ይላል። በጠሐይ ጥንቢዝ ብሎ መስከር ተብሎ ይመዝገብልኝ። ህሊና ብርሃናማ እንደ የኔይቱ ስመኝሽ ሲኮን ደግሞ አገር ይናፍቃል። ሽው ይላል … ጠረኑ፤ ይመጣል ከነጓዙ ከነጉዝጓዙ የቡኒት ትዝታ።
·         መነሻ።

„Tigist Girma: ተዋናይት ትዕግስት ግርማ ትወና አቁማ የቤተክርስቲያን ዘማሪ ሆነች“
ቃለ ምልልስ ያደረገላት ዘማሪ ተዋናይ ይገርም ደጀኔ ነው። በመጨረሻ ልትለው የምትፈልገውን ሲጠይቃት፤ የመረጠችው እርእስ ጉዳይ ልቤን ነካው። ነባቢቴን ደግሞ በእልልታ አስነካው፤ እና፤ እናማ ተኮለመ በኮቢው እላችሁ አለሁኝ ….
  • ·         እንዲህም አለች። „ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሸቱ ልጆችን እናሳድግ“

 „እኔ የእውነት ይህቺ አገር የእውነት ታሳስበኛለች። የዕውነት ማለት ነው ራስን ከመሆን። ራሳችነን መሆን የመሰለ ነገር የለም። እራስን መሆን ለመፍጠር ዛሬ የወለድናቸውን ልጆች ለዛሬ 20 ዓመት ማዘጋጀት እምንችልበት። ምን አልባት በተወሰነ ደረጃ ያመለጠ ትውልድ ሊኖር ይችላል። በወላጅ ስህተት፤ እንዲሁ ስህተቱ የእከሌ ነው ብለህ ከመቆለል አንዱ ላይ፤ ብቻ በሆነ ስህተት የሆነ ያመለጠህ ትውልድ ሊኖር ይችላል። ያ ያመለጠህን ትውልድ ላታገኘው ትችላለህ። ወይም ካገኘኸው ልታስተካክለው ትችላለህ። ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ከዚህ በኋዋላ ያሉ ልጆች ግን ያሳስበኛል፤ ልጆቻችን፤ የወለደ እንደ ኢትዮጵያዊ ልጆቻችንን እናሳድግ። ያለበለዚያ ነገ „ናይን ዋን ዋን 911“ ውጪ አገር ያ ይመጣል ብሎ ማሰብ ይገባል። መጸሐፍ ቅዱስም ልጆችን መቅጣት እንደ አለብን ይገልጻል። ስለዚህ ልጆቻችን ቀጥተን ማሳደግ አለበን። ሸክላ ብቻውን ዱላ ሚጠላ ትለኛለች እናቴ። የእውነትም ነው ትናንትና በመመታቴ እኔን ዛሬ ጎድቶኛል ወይ? ተጠቅሜያለሁኝ። አንተም ተቀጥተህ ነው ያደክው። እኔም እንደዛው። ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ይህቺን ቲጂ የፈጠራት ትናንትና በመመታቴ ነው። ስለዚህ ሳይጣመሙብን ልጆቻችን። አሁን እሸት ለጋ እንደሆኑ ተጣመው እንዲቃና ለማድረግ ከሚሰበሩብን ደረጃ ሳንደርስ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሸቱ ልጆችን እናሳድግ። ስንቶቻችን ነን „ኖር“ የሚሉ ልጆች የሚያውቁ ልጆች ያሉን። እሲቲ ከዬትኛውም ቢሮ ግባ „ኖር“ የሚልህ … ተጎንበሶ ጉልበት መሳምም ትሩፋቱን „አክላለች። የኔዎቹ ቅኖች ሁሉንም ቀጥላችሁ ማድመጥ ትችላላችሁ። ክብረቶቼ መብት ነው ለማድመጥም / ለመተውም። ለእኔ መነሻ ግን ይህ ዕድምታዊ የተደሞ ቅኔ ከበቂ በላይ ነው።

እኔ እምመኛት እናት እንዲህ ዓይነቷን ነው። እኔ እማልማት እናት ዚህ ዘመን እንዲህ ዓይነቷን ዓራት ዓይናማ ነው። የእኔ ራዕይ በቤቷ ውስጥ ትምህርት ዜግነት የከፈተችውን የተግባር ልዕልት ነው ስናፍቃት የኖርኩት። ተዋናይት ወ/ሮ ትዕግስት ግርማ ቀደም ባለው ጊዜም ግጥሜ ናት። የዛሬው ግጥምነት ግን የህሊናዬ ሥነ - ግጥምነት ነው የሆነችው። ስዋሰው!
በተለያዬ ሁኔታ ቃለ ምልልሶቿን አዳምጣለሁኝ። የዕለተ ፋሲካው እና የዛሬው ግን የሚያክለው የለም። የልቤ ነው የሆነችው። እርግጥ ነው ልባሙን „ሞጋቾች ትወና“ እከታተለዋለሁኝ። ፈተናዬን ስለሚነግረኝ፤ በፈተናዬ ውስጥ መሰልጠኔ ምን ያህል ብርታት እና ፅናትን፤ ጥንካሬ እና መቻልን እንዳስታመረኝ እውነቱን፤ እንቅጩን፤ ፍርጥ አድርጎ ስለሚነግረኝ አውደዋለሁኝ። ከዚህ ባለፈ የጣና ሆይ! „ሞጋቾች“ አንበል መሆኑ ደግሞ ሌላው ጣዕሜ የእኔ እንድለው አድርጎኛል። እከሌ ተከሌ ሳይባል ሁሎችንም ተዋናዮች በጥሞና ልቤን ሰጥቼ ከነፍሴ እወዳቸዋለሁኝ።

„አጋረድን“ ከባህርዳር እንዴት መርጠው እንዳወጧት ሳይ ደግሞ አቅማቸውን ምን ያህል ጉልበታም እንደሆን ለማወቅ አልተቸገርኩኝም። ድምፆዋ እና የትወና አቅሟ የሚደንቅ ነው። ጀማሪ አትመስልም። ህይወቱን ከእነቃናው ከእነተፈጥሮው ነው የሆነችበት። በብዙ ምክንያት የሞጋቾችን ጠቅላላ ይዘቱን እወደዋለሁኝ። ዛሬ በተዋናይት ወ/ሮ ትዕግስት ግርማ የትወና ብቃት አይደለም ጉዳዬ፤ የዘመናት አጀንዳዬ ሆኖ በቆዬው የልጆች ጉዳይ ነው።

  • ·         „ኢትዮጵያዊነትን ልጆቻችን እናስተምር።“ የስናፍቅሽ ትዕግሥት ግርማ ህልም፤


የሆነ ሆኖ በዛሬው የቃለ ምልልስ ስናፍቅሽን፤ ስመኝሽን አግኝቻታለሁኝ እንደ ናፍቅኳት፤ እንደ ተመኘ ኋዋት በመንፈስ ሃዲድ ተገናኘን ልክ እንደ ወ/ሮ ጽዮን ተክሉ። የእኔ የውስጥ መሻቴ ምኞት አሁን ወፍ አውጥቶታል። ሴቶች የሚደመጡበት ዘመን እዬመጣ ስለሆነ ተዋናይት ወ/ሮ ትእግስት ግርማ ይህን ፕሮጀክት ለማስፋት ጥረት ብታደርግበት ህልሜ ተሳካ ነበር።

እኔ ዬምመኛትን ጀግና እናት በአዕምሮዬ ውስጥ አገኘሁኝ፤ ለዛውም ዛሬ። „ኢትዮጵያዊነትን ልጆቻችን እናስተምር ነው።“ አዲስ ትውልድ ማለም ብቻ ሳይሆን ከውስጥ የተነሳ ትጋት እና ቁርጠኝነት ይኑረን ነው። „እንካ ስላንትያም“ „ፊደልም“ „የተስፋ በርም“ „እርግብ በርም“ ጭብጡ የሄው ነው። ይሄንኑ ነው የሚሉት የህሊና ምርቶቼ። ውርስን በመንፈስ ንጽህና ከራስ በተነሳ ሞራላዊ ሁነት ማባጀት፤ መሥራት። ነገ የሚሠራው በዛሬ ውስጥ ስለሆነ፤ ትናንት የተሠረውም በትናንት፤ በትናንት በስትያ ውስጥ ስለሆነ።
እኔ አጋጣሚውን አግኝቼ የማውቃቸው ባህሎችን እስከ የምክር አገልግሎቶች፤ እስከ መፍቻቸው ተሰርተዋል በመጸህፍቶቼ ውስጥ። አንዲት ከኦስትርያ የመጣች እህቴ ትውልዷ ወለጋ ነው። 

ሀዘን ላይ ተገናኝትን „እንካ ስላንትያን“ ሰጠኋዋት እና ይህማ ለልጆች ብቻ አይደለም ከታዳጊ እስከ አዋቂ ማለት አለብሽ ነበር ያለችኝ። የልጆችን መጸሐፍት ስሠራ በጠቅላላ ከፖለቲካ አቋሜ ወጥቼ ነው የምሠራው። ከአንድ የትውና ጭብጥ ወደ ሌላ አዲስ የትወና ተልዕኮ ሲኬድ እንደ ማለት ነው። ምክንያቱም ሥርዓት በተቀያዬር ቁጥር ዋጋ ማጣት የለበትም ሥራው። ቀጣይ መሆን አለበት። አሁን በቅርቡ ባለቅኔው ጠ/ ሚር አብይ አህምድ የጸጥታ ኃይሉን ሲያነጋግሩ „በድክመቱ ኢህአዴግ ቢወድቅ ሠራዊቱ በምርጫ አሸነፊ ለሚሆነው ፓርቲም በቀጣይነት አገልጋይ መሆን አለበት ነበር ያሉት።

 ከአዲሱ ሁኔታ ጋር ለማዳ ለመሆን በመንፈስ ስንዱ ዝግጁ መሆንን“ አበክረው ገልጸዋል። በመቀጠልም „አዲስ ሲመጣ የሚበረግግ መሆን የለበትም፤ የሚፈርስ መሆን የለበትም“ ሲሉ አዳምጫለሁኝ። በዛ መንፈስ ነው እኔ የሠራሁት። የልጆች ነገርም ስለሚጨንቀኝ፤ ልጆች ፍቅርን ብቻ ነው መውረስ አለባቸው ብዬም ስለማምን። እኛ የምንተራመስበት ጉዳይ ለእኛም አልጠቀመንም እንኳንስ የነገን ትውልድ ሊያበረከት ቀርቶ። ለወላጆች የሠራሁትም ሆነ ትዳር ሲበትን መከራውን የሚሸከሙት ልጆች ስለሆኑ፤ ትውልድን ስለማዳን ነው። ትዳርን በምን መልኩ አስደሳች አድርጎ የማህበረሰብ መሰረት ማድረግ ስለሚችልበትም ሁኔታ በዚህ መንፈስ ነው የሠራሁት። ትውልድ አገር የሚለው ፍሬ ነገር የሚነሳው እዚህ አምክንዮ ስለሆነ።
  • የምትናፍቁኝ የአገሬ የኢትዮጵያ ቅን ልጆች …

ለሁለቱም ጣምራ ምኞቴ ናሙናዬ ስመኝሽ ቲጂ ሁነበታለች። „ታማኝነት“ ትልቁ ነገር ነው። መቼም ከሰው አካል በላይ ክቡር ነገር የለም። የሰው ልጅ አካሉን የሚሰጥበት ማለት ነው ጋብቻ። ከባድም ውሳኔ ነው። ለዛውም ለማያዋቅቱ፤ ላልተወለዱት ባዕድ። አስፈሪው የኤድስ ህመም ይዞት እንኳን አብሬህ ልሙት ብሎ መወሰን እጅግ ፈታኝ ጉዳይ ነው። ባለቤቷ ፈተና ሰጣት፤ ፈተናው ስታልፈው ለሚሊዮን የታማኝነት እርህብተኞች አርበኛ ድምጽ መሆኗን አላስተዋለችውም። ከታማኝነት በላይ ዓለምን፤ አገርን የሚሠራ ምንም ነገር የለም። አካል በአጋጣሚ ይጎድላል፤ ከጋብቻም በኋዋላ ቢሆንም። እስከ መጨረሻው ያነን የሃዘን ጊዜ ፈቅዶ መዝለቅ ሰው የመሆን ጥያቄ ነው። 

ዛሬ ኢትዮጵያ ስሰማ ራስን መውደድ የገነነበት እንደሆነ ነው፤ የእህት ልጅ ቀርቶ እራሱ እህት ወንድም የሚባለው እኮ ቋንቋ ሆኗል። የተሻለው አንድ ነገር አለ ቢባል ሁሉም ልጅ ወላጆቻቸውን ይወዳሉ። ከዚህ የተረፈው ግን ትርፍ ነው። የፈለገ ድከሙ፤ ህይወታችሁን ገብሩ፤ ኑሯችሁን አጎሳቁሉ፤ ወጣትነታችሁን ተላለፉት፤ ዕድላችሁን አሽሉኩ፤ አፈር ድሜ ግጣችሁ ያሳደጋችሁት/ ያሰደጋችሁት እህት እና ወንድም ጊዜ የለውም ለእናንት። ለወላጆቹ ግን ጊዜ አለው። ይሄ የታማኝነት ተፈጥሮ ጥቁር ልብስ ነው በዚህ ዘመን። ለቤተሰቡ ታማኝ ያልሆን እንዴትስ ለ አገሩ ታማኝ ሊሆን ይችላል? በጣም ለፍቅር ቆጥቋጣ እና ገብጋባ ትውልድ … ስለነገ ሲታሰብ መርግ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ እንዲህ ናት። 

ተዋናይት ወ/ሮ ትዕግስት ግርማ ይህን አሸንፋ የወጣች የድርጊት እመቤት ናት። ባለቤቷ „ኤድስ በምርመራ ተገኘብኝ“ ያላት ለመፈተን ነበር። „አብሬህ ለመሞት ተዘጋጅቻለሁኝ“ ብላ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ እዛው ላይ ወሰነች። ልሰብበትም፤ ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ ላማክርም አላለችውም። እምሞተውም ከአንተ ጋር ነው አለች። ይህቺ ንጹህ ሴት ኢትዮጵያ ለምትሰጣት ማናቸውም የኃላፊነት ቦታም ብቁ ናት። ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ዜጎች ያስፈልጓታል። መከራዋን፤ ጥቁር ልብሷን አብረው የሚለብሱ። ታማኝነታቸውም ብልጭልጭ ያልሆነ፤ ቅጂ ያልሆነ የትውስት ያልሆነ፤ ከቀዬው የበቀለ፤ በባዕቱ የሰከነ፤ ተፈጥሯዊ ታማኝነት ነው የራባት እናቱ ኢትዮጵያ።
  • ·         የልጅነት ጨዋታ።

ዘመኑ ለሰውኛ ስለተፈቀደለት ተመክሮዬን ትንሽ ልበልለት። እንደ ድሮ ወንጀል ቢሆን ግን ወንጀል ነው። „ግምገማ የለብኝም ስለ ቤተሰባቸው አሸኛኘታቸው ላይ ሊገልጹ ሲፈቅዱ“ አይደል ያሉት የቀድሞው ጠ/ ሚር አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ። ድህረ ገጽ ላይ አዲስ ጹሁፍ ተልጥፏል ብሎ መረጃ መስጠት የሚያስወግዝ ነበር እዚህ ውጪ አገር። ዛሬ ተመስገን ነው። ከልጅነት ህልሜ ጋር ላገናኘው ነው የቲጂን ነገር። በልጅነት የትዳር ነገር ሲነሳ „አብሮ አደግ የልጅነት ጓደኞቼ እኔ ልጅ ያለው አልፈልግም፤ እኔ ይሄ ያለው፤ ይሄ የሌለው“ ሲሉ ዛሬም ጎረቤቶቻችን እንደ ተረት ያነሱታል አሉ። 

እኔ ደግሞ መሃን ብሆን ባሌን፤ ብወደው፤ እንዳላጣው ባልፈልግ፤ እንፋተ መሃን በመሆንሽ ቢለኝ ምን እሆናለሁ፤ ስለዚህ ቀድሞ የወለደ ቢሆን እምርጣለሁ እል ነበር፤ በመልክ፤ በቁምናም ሲመጣ፤ አስተሳቡ ደካማ ያልሆነ ይሁን እንጂ እግዚአብሄር የሰጠኝን እቀበላለሁ እል ነበር። ይሄም ብቻ አይደለም። ሞቴ ከባሌ በፊት እኔን ይውሰደኝ እል ሁሉ ነበር። የእውነት ነው የምነግራችሁ። ምክንያቱም እሱ ትቶት የሄደው ዓለም ለእኔ ምኔ ነው። ወ/ሮ ትዕግሥት ግርማን ስናፍቅሽ የምላትም ለዚህ ነው። አብሬ እማላሳድገው ልጅ አልወልደውም እል ሁሉ ነበር። ለእኔ ተጋብቶ ከወለዱ በኋዋላ መለያዬት የወንጀሎች ሁሉ ቁንጮ ነው። በጣም በረጅሙ ነበር የማስበው በልጅነት ጊዜዬ። ያን ጊዜ 12/ 13 ዓመት ላይ ነው ይሄን ወሳኔ የወስንኩት። አብሮ ለመኖር የቆረጠ ሰው ነው መወለድ ያለበት።

ሰቀቀኑ አይቻልም አባት እናት ተለያይቶ ማደግ። ሰው ራስ ወዳድ ስለሆነ ብቻ የራሱን ፍላጎት ለማሟላት አባትም ሆነ እናትም ሆነች ልጆቻቸውን በትነው ይለያያሉ። ልጅ በማህል በስቃይና በፍዳ የወደፊት ህይወቱ ጨልሞ ዘር አልባ ሆኖ ይቀራል። እንደዛ ያደገ/ ያደገች ልጅ ዓለምን ይፈሩታል። የትዳርን ህይወት ደፍረው አይወስኑበትም። ቢወስኑበትም በስጋት ነው የሚኖሩት። ከፍቺ በኋዋላ አብዛኛውን መከራ የሚሸከሙት ደግሞ የኢትዮጵያ እናቶች ናቸው። አሁንም በጠ/ ሚር አብይ አህመድ የእናታቸውን ዕሴት ከውስጣቸው የታተመ በዚህ ጉዳይ ነው። 

ይሄ እንደ አንድ ግድፈት ተቆጥሮ ተተችተውበታል። ቀድሞ ነገር በእኛ ዕድሜ ኃላፊነት የሚሰማው አባት እኮ እንብዛም ነው። ከንፍሮ ጥሬ ያወጣው። ማግባት እና መፋታት ቀላሉ የቤት ሥራ ነው። አይደለም ያን ጊዜ ሌላ መረጃ ትቶ የ2010 እኤአ የዘንድሮን የማለዳ ኮከቦች የምርቃ ሥርዓትን ዕንባማ ሲቃማ ያደረገው ይሄው ነበር። በምልሰት አዳምጡት የቻላችሁ። ቦጋስ/ የማለዳ ኮከቦች ዩቱዩብ ገብታችሁ። መከራውን ሁሉ እምትሸከመወ እናት ናት። 10 ለምርቃት የቀረቡት ተወዳዳሪዎች በሙሉ „እናቴ፤ እናቴ፤ እናቴ፤ ለእናቴ፤ ስለ እናቴ“ ነበር ያሉት። ለዛውም በዕንባ ነው።  የኢትዮጵያ እናት ፍደኛ እናት። የመጀመሪያ ልጇ ሴት ከሆነችም ውርሷ ይሄው ነው። የእሷን ቀንበር መውረስ እና መሸከም። ኑሯውን ረስታ የእህት እና የወንድምን ህይወት ማደራጀት። መጨረሻ እሷ ዋቢ አልባ ባክና መቅረት …  

  • ·         ስለ እነ „ኖር!“ እና ጉልበት ተጎንብሶ መሳም።

በምድር የመጀመሪያዋ የህይወት ትምህርት ቤትም መምህርም እናት ናት። ይህንንም ከስመኝሽ ከተዋናይት ወ/ሮ ትዕግስት ግርማ አግኛቻለሁኝ።  „ኖር“ የአክብሮት ተቋማችን ነው፤ ቅርሳችን ነው። ባህል ዕለታዊ የሰዎች ክንዋኔ ዕድሜ ጠገብ ሲሆን ባህል ይባላል፤ እንደ ሥርጉተ ሥላሴ ፍልስፍና። ባህል ሦስት ልጆች አሉት - ለእኔ ። የመጀመሪያው ልማድ ነው። ልማድ ማለት የባህል የዕለት ተዕለት ሥራ አስፈጻሚ አካል ማለት ነው። ወግ ማለት ሥ/ አስፈጻሚው ተግባሩን በትክክል ስለመፈጸሙ፤ ሳይፈጽም ሲቀር ደግሞ የሚከታተል፤ የሚቆጣጠር የደህንነት አካሉ ነው። የይትባህልን ድንጋጌ የተላለፈ ደግሞ ቅጣትም ይኖራል፤ ተግሳጽም ይኖራል። ሦስተኛው ትውፊት ነው። ባህልን ከነፍሱ ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስረክብ ማለት ነው። ዝክረ የክንውን ማዕከል ነው ትውፊት። ውርስ ቅብብል እንደ ማለት። አሁን „ኖር“ ቃልም ነው ትውፊትም ነው። ልክ እንደ „በላ ልበልኃ፤ ተጠዬቅ“
 
ሦስቱንም ነው አጣምራ የፈጸመችው። ማን? ስናፍቅሽ ወ/ሮ ትእዕስት ግርማ፤ ወ/ሮ ስመኝሽ ትዕግስት ግርማ። ከትውና፤ ከዝግጅት፤ ከኑሮ የምትመርጠው „ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሸተውን“ ትለዋለች። ጸሐፍትንም ቁንጥር አድርገው ጠረናችን ለቅመም የሚጠቀሙ ከሆኑ የስናፍቅሽ ምርጦች / ምርጫዎች ናቸው፤ ለዛውም የህሊናዋ። እንደ ኢትዮጵያዊ መኖርን ፈቅዳዋለች። ልጆቿን እምትገራው በዚህ ሥርዓት ህግጋት ነው። የታደለች!

  • ·         ልጆችን በብሄራዊነት፤ ሃላፊነት እንዲሰማቸው አድርጎ ስለማሳደግ።

ይሄ ወሳኙ ጉዳይ ነው። 27 ዓመት ሙሉ ያልተሰራበት። እንደ ዋዛ የተዘለለ። እንዳልባሌ የትሜና የተጣለ። ቁስ ላይ ብቻ ነበር ትኩረቱ። እንደዛ እምለው እኔ ልጅ እያለሁን አባባ በሥሜ ባህርዛፍ ያስተክሉኝ ነበር፤ አባባ ደን የሚያለሙበት የገዙት ቦታ ሁሉ ነበራቸው። አንድ ነገር ልከል ተጨማሪ፤ የራስን ጉዳይ እራስ ለመፈጸም አቅም፤ ነፃነት በመስጠት እረገድ ያደርጉት የነበረውን። ልብስ ምርጫዬ ላይ ማንም ጣልቃ እንዳይገባብኝ ያደርጉ ነበር። ልብስ ሊገዙልኝ አብረን ስንሄድ አባባም እና እምዬዋም ውጪ ነው የሚቆሙት። መርጬ ከጨርስኩኝ በኋዋላ ነው እነሱ የሚገቡት፤ ክፍያ ለመፈጸም። አባባ የቃብቲያ ሰው ናቸው፤ በጎንደር ክ/ ሀገር በወገራ አውራጃ በባዕተ ወልቃይት የሚገኝ አዱኛማ ሥፍራ ነው። 

አባባ እንደዛ የሚያደርጉት በእኔ ምርጫ ላይ የእነሱ ተጽዕኖ እንዳይጫነኝ፤ መወሰን እንድችል ነው። ምን አልባት እናቴ ብታማርጠኝ የእሷን ጣዕም ይሆናል እኔ እምመርጠው። ይህ የጥገኝነት መንፈስ አብሮ እንዲያድግ ያደርጋል። ለዚህም ነው በውሳኔዬ ወለም ዘለም የሌለበት። የእኔ ውድ አባት አባባ ግን ይህን ቀድመው ተጠብበውበታል። አንድ የኢሳት ውይይት ላይ ጸሐፊ እና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ኤርመያስ ለገሰ ስለ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ኢፈርትን የመምራት አቅመ ቢስነት ሲገልጥ „ለዛውም ከወልቃይት¡“ በማለት ሲያሾፍ ጥራዝ ነጠቁ ትንተና የተቃጠለ ካርቦን መሆኑን አረጋገጥኩበት። 

ስለምን? ቀደም ብዬ ከገለጥኩላችሁ በላይ የሆነ ልቅና፤ ተመክሮ ያለው፤ አርቆ የሚያስብ፤ ስለ ነገ የሚጨነቅ እና የሚጠበብ ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ማህብረስብ ነው ወልቃይትና ጠገዴ ማለት። እሱ ብቻ አይደለም ትልቅ ካርታ ነበር ከቤት የዓለም፤ እያንዳንዱ አገር ኢንደስትሪያዊ ዕድገቱ ምን እንደ ደረስ፤ እኛ ደግሞ ያልነበትን ደረጃ በንጽጽር አባባ ያስረዱኝ ነበር። አባባ የሁመራ ዘመናዊ አራሽ ነበሩ። እዚህ ሲዊዘርላንድ ውስጥ ካንፕ ውስጥ ሲኖር ሁሉን ወጪ የሚከፍለው መንግሥት ነው። ሙሉ ቀን መብራት ይበራል። እዬዞርኩ ነበር የማጠፋው። እኔም አልክፍልበት ሌላውም ስደተኛም አይከፍልበትም ግን ኃላፊነት ይሰማኛል። ፊቴን ስታጠብ ለዛች ቅጽበታዊ ጊዜ ቧንቧ ውሃውን እዬከፈትኩ እዬዘጋሁኝ ነው። 

ልጆች ሁሉንም ነገር በት/ ቤት አያገኙትም። ቤት ውስጥ ነው የሚማሩት። አሁን ወ/ሮ ትዕግስት ግርማ የምታደርገው ይሄውን ነው። ልጆ መንገድ ላይ ቆሻሻ አይጥሉም። እሷን እራሷን ይቆጣጠሯታል። እንደዚህ ሃላፊነት የሚሰማው ትውልድን መሥራት ዛሬ ከቻልን ብቻ ነው ኢትዮጵያ እንደ አገር ልትቀጥል የምትችለው። በስተቀር እረፍታችንም የሰላም አይሆንም። ሰው መሥራት ከባዱ ፈተና ነው። ይህን ዘለብላባ ዘመን የሚያሸነፍ ጊዜ ይሆናል የአብይ መንፈስ ዘመን ብዬ አስባለሁኝ። ዛሬ ወፏ ከወደ አገር ቤት ጥሩ ዜና በዬዕለቱ ስለምታቀበል …

  • ·         „አሁን በፈጣረችሁ ይህቺ አገር ምኗ ይሰራቃል ትለናለች?“ የኢትዮጵያ ዋቢዋ ተዋናይት።

የሞጋቾች ተዋናይ ትግስት ግርማ የሀገር ፊቅርን በሽለላና ፉከራ ስትገልፅ/ Tigist Girma

የቆዬ ነው ይሄ። ነገር ግን ስለ እሷ ካነሳሁ ዘንዳ ተዛማጅ ነገሮችን የሚያጠናክርልኝ ስለሆነ ዘመነ አብይ ደግሞ ዘመነ ሴቶች ስለሆነ ዕንቆዎቻችን ዕውቅናቸው ሁለገብ ስለመሆኑ ለማመሳጠር ነው። እኔ የዴሞክራሲ ግንባታ ቢሮ በዚህ መስል ፍልስፍና እንዲገነባ ነው የምሻው። ኢትዮጵያ የምትናፍቃቸው ወገኖች የሚመክሩበት የሚዘግሩበት። በባዕቷ ኢትዮጵያም ስደተኛ ስለሆነች። በዚህ መሰል የነጠረ ንጽህና መንፈስ ነው የነገይቱን ኢትዮጵያ የማልማት ራዕይ ርስት ሊሆን የሚገባው። በዚህ ጉባኤ ላይ ተዋናይት ወ/ ሮ ትዕግስት ግርማ ዳኛ ነበረች። ስለሆነም ባገኘቸው ዕድል የኢትዮጵያን ፍቅር በአንድ ደቂቃ ውስጥ የመግለጽ ዕድል … ነበራት።
·         እንዲህም አለች …

 „ኢትዮጵያን በአንድ ደቂቃ መግለጽ ቅድም ማጣፊያው ሲያጥረን ሰምታችኋዋል። ይከብዳል። በጣም የተከበረች፤ ከሦስት ሺህ ዘመን በላይ ዕድሜ ያላትን አገር መግለጽ አሜሪካኖች እንኳን የእኛ አገር እያሉ ሲያወሩ እኛ „ይህቺ አገር“ የሚለውን እናቁም እና አገራችን ሁላችንም የእውነት እንውደዳት፤ መውደድ ማለት፤ አገሬን አውዳታለሁኝ ማለት አይደለም። የተሰጠንን የሥራ ድርሻ፤ በአግባቡ መወጣት ነው። የዛኔ አገራችነን እንደምንወዳት በሥራችን እንመሰክርላት አለን፤ በአፍማ ማንም አውድሻለሁ ነው የሚላት። ምክንያቱም እዬኖረባት ስለሆነ። አገራችነን መውደዳችን እምናሳውቀው ሁላችንም እንደዬሙያችን የተሰጠንን በአግባቡ ስንሠራባት ነው። እንዲያው እግዚአብሄር ያሳያችሁ፤ ከዚህች አገር ምኗ ይሰረቃል? እንዲያው ከድሃ?! እንጨት ተሸክማ ካሰደገች እናት የመስረቅ ያህል ነው። አይደለም? ስለዚህ ሁላችንም ሥራ እንሰርቃለን፤ ጊዜ እንሠርቃለን፤ ይሄ ራሱ ወደ ብር ሲመነዘር አገራችን ይጎዳታል። ስለዚህ አገራችነን መውደድ፤ በምግባር ማሳዬት ነውበአፍማ ሁሉም ሊወዳት ይችላል። የአፍ ወዳጆች አንሁን የምግባር አገር ወዳደዶች እንሁን።“  
   
ኢትዮጵያ እራሷ እናት ያስፍልጋታል። ይህን ደግሞ ተዋናይት ወ/ሮ ትዕግስት ግርማ አሟልታልኛለች። የልቤ ስለሆነች ላመሰግናት እሻለሁኝ። የእኔ እመቤት፤ የእኔ ልዕልት ድንግልዬ፤ ውጽፈተ ወርቅ፤ እመ ብዙኃን መንገድሽን ሁሉ ታቃናልሽ። ትደግፍሽ። ለእናት ኢትዮጵያ እንዲህ ውስጧ እንደ ሆንሽልታል ሁሉ በጎደለው ሁሉ የውስጥሽን ርህርሂት ትሞላ ጓድውን ሁሉ። ልጆችሽን ለቁምነገር ታብቃልሽ። ትዳርጅሽን ጎጆቸሽንም ከክፉ ነገር ትጠብቅልሽ። ወሎሽን ሁሉ የበረከት፤ የረድኤት ታድርግልሽ። አሜን!
  • ·         ለኢትዮጵውያን ፎቶ አንሺዎች።

እግረ መንገዴን …. እናንት የቤተ ጥበብ እማ/ አባ ወራ የምለው አለኝ። የፎቶ ግራፍ ባለሙያዎች ሆይ! ሥራችሁን እርግፍ አድርጋችሁ ረስታችሁታል ወይንም ተዘናግታችኋል፤ ፎቶ ማግኘት አልቻልኩም። የዛ አንጋፋ የአባ ግሡ የተዋናይ ኪሮስ ኃ/ ሥላሴ የተውኔት ግርማ ሞገስ ፎቶ ማግኘት አልቻልኩም። ያገኘሁት ጉግል ላይ ሁለት ነበር። አንዱ ጉርድ ጨለማ የዋጠው፤ ሁተኛው ቆሞ ነው እሱንም ውስጡን በትክክል ሊገልጸው የማይችል። እንዴት እንዳዘንኩኝ። ለዛውም ዛሬ ቆሞ እዬሄደ፤ መቼ ነው የእሱ ታሪክ ዝክራችን ሆኖ በአግባቡ በወጉ ከእነ ሙሉ ማዕረጉ ስብስቡ ሊሠራ የሚችለው? ስናጣው ነውን? በኋዋላው የተፈጠሩት የት ደርሰው? ውስጡን የሚገልጥ ፎቶ ባለፈው የዓይን ህመሙን ሰምቼ ለመጻፍ የት አባቴ ላምጣው። ቢጨንቀኝ የመደቡን ቀለሙን ቀዬርኩት። እሱም በግርዶሽ የተሠራ ነው የሚመስለው። ታሪክ እኮ ዛሬ በሚሰራ ነገር ነው ነገ ታሪክ ሊሆን የሚችለው። ታሪክ አልቦሽ እዬሆን ነው።

የሰዎች መልካም ይሁን መልካም ያልሆነ ድርጊት ዕድሜ ጠገብ ሲሆን ታሪክ ይሆናል። ስለሆነም የዚህን የተውኔት ጉልላት ምስል እንኳንስ እማምርጠው ለዕለት የሚሆን ማግኘት አልቻልኩም። እጅግ ነው ውስጤን ህመም የተሰማኝ። የሥዕል ቤተኞችስ ቢሆኑ ትውልድ ሊተካቸው የማይችሉ ቀደምቶችን እንዴት እንዲህ እንደ አልባሌ ነገር ያዮዋቸዋል። ከቅርስ በላይ እኮ ናቸው። ኢትዮጵያን እራሷን ማለት እኮ ናቸው። ኧረ በፍጥነት ሳያመልጡን በሁሉም ዘርፍ ያሉ ሃብቶቻችን የተጉበት መስክ ትኩረት ተሰጥቶ ባህል እና ቱሪዝም ራሱ በፕሮጀክት ይዞ ነፍስ ያለው ተግባር ይከውንበት - እንላላን እኔ እሜቴ ብዕሬ። ዝክረ ትውፊት እኮ ናቸው።
እስቲ ወደ ጎንደሩ ደብረብርሃን ሥላሴ ጎራ በሉ። ያን የመሰለ ቅርስ እኮ የተረፈው የቀደሙት ስለሠሩበት ነው። ዐጤ ፋሲል በሮቹ ሳይቀሩ በዙሪያው ያሉ አድባሮች ሳይቀሩ መቼ በማን እንዳ ተሠሩ ሁሉ እኮ አለ። ከሦስት መቶ ዓመት በፊት የተከወነ እኮ ነው። ከዛም የቀደሙ አሉ። የቅድስት ማክዳ መልዕከተኛ ሥም ሁሉ የተሰዬመበት በዛ የሚጠራ ሥፍራ ሁሉ አለ እዛው ባዕት፤ መታሰቢያ አድባራትም አለ። … ስለምን ዛሬን የሰጡን ያን ሠርተውበት ነው። እያንዳንዱ ነጥብ ጣቢያ፤ አድባራት ሁሉ ከነሙሉ ታሪኩ ለመነሻ የሚሆን አለበት ዘመኑ ሁሉ። ለዛውም ጦርነት ታሪኳ በሆነች አገር … በዛ የሥልጣኔ ዘመን።
  • ·         በስንቱ እንሹለክ?

እንደዚህ ወጣ ብለው የሚፈጠሩ ዜጎች እኮ ሃብትነታቸው ለወላጆቻቸው አይደለም። የኢትዮጵያ አንጡራ ሃብት ናቸው። ስለሆነም ለዚህ መሰል የኢትዮጵያ ሃብታት የፎቶ ጋላሪ ራሱን ችሎ ያስፈልገናል። የዛሬ 50 ዓመት ኢትጵያ ውስጥ ምን ነበር ለማለት በዚህ አያያዝ አደጋ ላይ ነው። ሞድ ላይ፤ ፖለቲካ ላይ ያሉ ሰዎችን ፎቶ ብቻ ነው ያለው። ሁለገብ በሆኑ ሁልአቅፍ ተግባራት ላይ ለናሙና የሚጠቀሱ ዕውቅ ባለመክሊቶችም ማግኘት አልተቻለም። ዕወቅ መምህር፤ ዕውቅ ጽዳተኛ፤ ዕውቅ ቡና አፍይ፤ ዕውቅ እንጀራ ጋጋሪ፤ ዕወቅ ቀማሚ፤ ዕውቅ አገልግለት ሰጪ፤ ዕወቅ ሃኪም፤ እውቅ ትሁት፤ ዕውቅ ቸር፤ ዕውቅ ሰው አክብሪ፤ እነማን እንደሆኑ አይታወቁም።

ለምሳሌ ጎንደር „አበቄሌሽ ጠጅ ቤት“ የሚባል ነበር። ራሱ ትውፊት ነው። ይኑር አይኑር ዛሬ አላውቅም። ጠላ ቤትም „እንኮዬ መስክ“ የሚባል አለ። ጃንተከል ዋርካው እራሱ ቅርስ ነው። አሁን በምን ሁኔታ እንዳለ መረጃው የለኝም። ፋሲል ግንብ „እንኮዬ በር“ የሚል ሁሉ አለው። በሮቹ እራሳቸው የሚገሩሙ ናቸው ከነ ሙሉ ተግባራቸው ገላጭ ናቸው። የቀደሙት አግናባት ሲገነቡ እንኳን ከትውፊታቸው ጋር አያይዘው ነው። ይሄን ካጣን አይቀጠልም ትውልዱ። ዛሬ የተገኘው እኮ በቀደመው አሻራ ነው። እኛ እኮ እንገርማለን። የቀደመውን አናከበርም፤ ወይ የዛሬውን አንሠራበት። ራሱን የሸጠ፤ ራሱን የተዋሰ፤ ራሱን የለጠፈ፤ ራሱን ያሾለከ ትውልድ ነው ማግሥት የሚጠበቀው። ትልቅ በጣም ግዙፍ አደጋ ነው። በፍጥነት ክፍተቶችን ለመድፈን ካልተጣደፍን በስተቀር … እያለቅን ነው … አንድ ፎቶ የአንድ ዋርካ ተዋናይ ማጣት … ጉግል ላይ ማጣት ምን ይባል?
  • ·         ሥነ - ስናፍቅሽ።

የማከብርሽ የእኔ ተዋናይት ወ/ሮ ትዕግስት ግርማ የአንቺም በቂ አይደለም። ውስጥሺን ሊገልጽልኝ የሚችል ፎቶ ማግኘት በፍጹም አልቻልኩኝም። ሲጨንቀኝ ወደ ፋሲካው ቃለ ምልልስሽ ሄጄ ቆራርጬ ተሳክቶልኛል። እኔ ሰውንም ፎቶንም ሳይ ውስጥን ፈልጎ ከማግኘቱ ላይ ነው አትኩሮቴ። ሙሉ ሰብዕናው ከጹሑፌ ወይንም ከቪዲዮ/ ከፊልም ክሊፔ ጋር ካልገጠመ አንገናኝም። ዋነኛው የመንፈሴ ጭብጥ ሾልኳል ማለት ነው። ስለዚህም መድከም አይኖርብኝም ማለት ነው። ረጅም ጊዜ የሚወሰድብኝ መጻፍ አይደለም። መጻፍ ለእኔ የውሃ ቧንቧ የመክፈት / የመዝጋት ያህል ቀላል ነው፤ የዝንተ ዓለሙ የችግረኛውን የውሃ ጥመኛ የጎንደሬውን ቧንቧ ግን ማለቴ አይደለም። የሲዊዝዬን ማለቴ ነው።  ፎቶ መምረጥ አንዱ ወሳኙ ተግባሬ ነው። ብዙ ጊዚዬን የሚበላውም በፎቶ ምርጫ ነው። ትስጥዖዬም ነው። ግን የሚመረጥ ሲገኝ ነው። ስለዚህ አንቺም ፎቶ አንሺዎችም ሰንፋችኋዋል። ለዛውም በዚህ በዲጅታል ዘመን ምነው እናቴ? ይህን እኮ ልጆችሽ የሚያደርጉት እኮ ነው። ራሱን የቻለ ፎቶ ማግኘት አልቻልኩኝም። ወደ ዬትኛወም ቦታ ስትሄጂ ከሙሉ ግርማሽ ጋር መጀመሪያ ፎቶ ተነሺ። ይሄ አንዱ መፍትሄ ይሆናል።

በዚህ ዘርፍ አልተጀመረም ብል ነው የሚሻለው። እኔ እኮ የብላቴው ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን አንዳንድ ነገሮች ሥሰራ የቀደሙት የሠሩት እርሾ ነገር ስላለ ነው። አሁን በፓን አፍሪካኒዝም፤ በተጨማሪም በኢትዮጵኒዝም የሠሩ ወገኖቼን በሚመለከት የፖሰተር ቪዲዮ ማዘጋጀት እሻለሁኝ። ግን ፎቶው የተሟላ አይደለም። ይሄን እዬሰራን ማቆዬት አለብን። ትውልዳዊ ድርሻ ማለትም ይሄው ነው። አሁን እኔ እምሰራው ሰው ላይረዳኝ ይችላል። ፍቅራዊነት LOVEISM የፍቅር ተፈጥሯዊ መርህ ሙያ ነው የሚል ነው። ፍቅር ፍልስፍና ሳይንስም ነው የሚል ነው። መርሁን ልንማራው የሚገባ ነበር። ፍቅር ህግጋቱ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ተነፍጎታል፤ ተገፍቷል፤ ትኩረት አልተሰጠውም የሚል ነው ሙግቴ። አሁን ዕውን አይሆንም ግን ሃሳቤ ሳላወጣው ባልፍ ተቀብሮ ይቀራል። ስለዚህ እዬሰራሁ አስቀምጣለሁኝ። አንድ ቅን ሰው በተባረከ እለት ቀጥሎ በመሥራት ወደ ዕውቅና ያሸጋግረዋል። ቢያንስ ሃሳቡ ተሸጋጋሪ ያደርገዋል። ስለሆነም ዛሬ ሰው ሳብስክሪፕት አላደረገውም፤ አልተጠቀመበትም ብዬ አልዘናጋም፤ እዬሠራሁ አስቀምጣለሁኝ። ልቤ ምን እንደሚያስብ፤ ምን እንደሚያስጨንቅኝ። ዓለም ታስፈራለች። ዓለም ለ እኔ ግማሿ ጸሐይ በግርዶሽ ሆና ነው የምትታዬኝ።
  • ·         ኢትዮጵያኒዝም።

በዚህ ዘርፍ እኔ ሳዬት ተዋናይት ወ/ሮ ትዕግስት ግርማ የኢትዮጵያኒዝም አክቲቢሰት// ታታሪ ናት። በዛሬው ዘመን አክቲቢስትነት ብዙ ጊዜ ከራሱ አይጀምርም። ስለምን? ለሌላው ነፃነት ሲታገል ለራሱ ነፃነት ሳይታገል ነው። በሰው ልብ መኖርን፤ በሰው ውሳኔ መኖር፤ በሰው ፈቃድ መደገፍን // መቃወምን ሥራዬ ብሎ ሲይዘው የእሱን የማድረግ ነፃነት ለሌላ እዬሸለመው ስለመሆኑ አይረዳውም። ስለሆነም የሰው ልጅ ነፃነቱን ከቤቱ መጀመር አለበት።
አንድ አክቲቢስት አንድን ጠ/ ሚር / አንተ እና አንቺ እያለ ቢጥለው አክቲቢዝም አይሆንም። እርግጥ ነው አክቲቢዝም ለመልካም መልካም ላልሆነም ሊሆን ይችላል። አሁን ይልቅ ሊጋባው ፌስ ቡክ እራሱ ለአሉታዊ ከሆነ፤ ለማህበረሰብ የማይጠቅም ከሆነ ፔጁን በመዝጋት ላይ ነው። ዛሬ ለጎሸችው ዓለም መልካምነትን ማውረስ ያስፈልጋል። ለዛውም በባህል ህብርነት የፋፋ ተመክሮ ላላት አገር፤ ሰውም አክብሮታዊ በሆነ አጠራር እርሰዎ ብሎ መጀመር ከተሳነው ከኢትጵያዊነት ባህል የወጣ ነው። ስለዚህ ያ ታታሪ ወይንም ያቺ ታታሪ ለማንም ለምንም አይሆንም/ አትሆንምም። አብሶ እንደ ኢትዮጵያ ላለ የፈርሃ እግዚአብሄር መንበር አክብሮ መነሳት የሚጀመረው ኢትዮጵያን ከማክበር መነሳት አለበት። አክብሮ ተነስቶ ግን ዱላውም ክትከታውም ይደረሰብታል።
  • ·         ያመለጠ የደም ገንቦነት።

ስለ ተዋናይ ከተነሳ አንድ ለመንገድ ልበል፤ የቲጂን ፎቶ በሥሟም የረባ ነገር ሳጣ በተዋናይት ወ/ሮ ሸዊት ከበደ ሞከርኩት፤ ሁሉም ታርጋ ያለበት ሆነብኝ፤ ለዛውም እኔ ላሰብኩት ተልዕኮ ጋር መቀራረብ አልቻለም። ያም አልሆን ሲለኝ ደግሞ በተዋናይት ወ/ሮ መቅደስ ጸጋዬ ሥም ስጎግል አዲስ ፎቶ አገኘሁኝ። ድንቅ ብሎኝ አፍጥጬ ተመለከትኩት። የአራስ ህፃን ደም ያለው ነበር። እሸት ነው። ፎቶው የተዋናይት ወ/ሮ መቅደስ ጸጋዬ በሙሉ ወርድ ቀሚስ የተነሳቸው ፎቶ ነበር። ተዋናይት ወ/ሮ አምለሰት ሙጬን ጨምሮ የቀረባችሁ ነው? ትንሽ ትቆርቁራችሁ እስኪ? ለመልሳችሁ ከዚህ በላይ የሚያስውባችሁ አልነበረም። ትጊስ ምን ታስቢያለሽ ከሙሉ ወርድ ጋር … መቼ ነው የምትገናኝው?

ውዴ መቅዲ ሙሉ ወርድ ቀሚስ እንዴት ያምርብሻል። እንዴት ደም ግባትሽ ፏ ፍንትው ብሎ ወጣ መሰለሽ? ፈለፈል ነው የሆንሽው። ፏፏቴ። እውነት ብናገር አይጠገበም ይህ ደም ግባት። ረጅም ጊዜ ነው ያዬሁት። ይህን የምለው ግን የእኔ ውዶች እኔ ጎንደሪት ስለሆንኩኝ ሳይሆን የቱ እንደሚያምር የቱ የውስጥን ውበት ሚስጢር እንዳወጣው ማንም ሰው አይቶ ይፈረደው። የ ዓለም እመቤት ነው የሆነችው ተዋናይት ወ/ሮ መቅደስ ጸጋዬ። የተዋናይት ወ/ሮ መሰረት መብራቴን ሰርግ ያሰብኩት በዚህ ሙሉ ወርድ ቀሚስ ነበር። ሁለታችሁ እስከ ዛሬ ከለበሳችሁት ሁሉ ይሄ የበለጠ ያምራል እንደ እኔ። ደማችሁን እንዴት በተፈጥሮው ልክ እንዳመጣው። እና ስናፍቅሽም ቅኚ በማለት ወደ ጎንደርን ብቅ ይበሉ እስቲ … ብለናል፤ የጫጉላ ጊዜው እንኳን ይሄን ያህል ውበቱ ግጥም ብሎ በሙላት አልመጣም …
  • ·         ስንብት ይሁን ከአቶ ዛሬ ጋር።

ለወ/ሮ ስናፍቅሽ ግርማ ለእኛዊነት አርበኝት ደጎስ ያለ ትህትናዊና ፍቅር ላክ አድርጌ፤ መንፈሳችሁን ለእኔ ሽልም ላደርጋችሁት አብራችሁኝ ለቆያችሁት የኔዎቹ ቅኖች ደግሞ ዘንክት ያለ የእግዚአብሄር ይስጥልኝ ምስጋና አቅርቤ፤ ለግራ ቀኛችሁ ኑሩልኝን ሸልሜ ልሰናበት።

  • ·         ጊዜው ሲኖር … ኑልን ይላሉ …

Kenebete (ቀንበጥ)
Sergute Selassie YouTube
ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!
እልፍ ነን እና እልፍነታችን በምግባር እልፍ እንድርግው።
  • ·         ፎቶ ምንጭ ከአይዋ ጉግል።

            መሸቢያ ጊዜ።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።